ጋዜጠኛ እና የበርካታ መጽሀፎች ተራኪ ደጀኔ ጥላሁን ከ 1976-2014 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ፣ ፋና ፣ ሸገርና ዩቲዩብ ላይ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል ። በአሁኑ ወቅት በራሱ በዩቲዩብ እና በማስታወቂያ ስራ ላይ ተሰማርቶ በሙያው ደስ ብሎት እያገለገለ ይገኛል ።
ትረካዎቹን የሰሙ ሁሉ መልክና ቁመናውን የሚገምቱት ባለ አስደናቂ እና ተወዳጅ ድምጹ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ምልክት ስለንባብ በብዕሩ የከተበ። በመላው ዓለም ያሉ ብዕረኞችን ቀለም በድምፅ ያስከረከበ፡፡ የሬዲዮ ፕሮግራም በማዘጋጀት እና በማቅረብ ከ 25 ዓመታት በላይ ያገለገለ የመጽሐፍት ተራኪና የ 3 መጽሐፍቶች ደራሲ ነው ደጀኔ ጥላሁን ።
ውልደቱ በአዲስአበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ አዲሱ ገበያ አካባቢ 1948 ዓ.ም ነበር፡፡ አባቱ አቶ ጥላሁን በዳሶ እና እናቱ ደግሞ ወ/ሮ ቦጋለች ሮበሌ ይባላሉ፡፡
ደጀኔ እንደ ወቅቱ ሁሉ ቄስ ትምህርትቤት ገብቶ ፊደል ቆጥሯል ።ዳዊት ደግሟል ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀለመ ወርቅ ትምህርትቤት ሲማር 2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት አጠናቋል ። በ1972 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነፅሁፍ አጥንቶ 1975 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቋል ።
ደጀኔ ጥላሁን እንደዛሬ ዘመን ምሩቃን ጫማ ሳይጨርስ ወዲያው እንደተመረቀ 1976 ዓ.ም ወርሃ መስከረም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ ተቀጠረ ። ለስራው በነበረው ፍቅር የተነሳ በሙያው ላይ ዕድገቶችንም በየደረጃው አስመዝግቧል ። ከፍተኛ አዘጋጅ ፣ ዋና አዘጋጅ ፣ የሬዲዮ የመዝናኛ ዘርፍ ማለትም የአማርኛ ፣ ኦሮምኛና የትግርኛ ቋንቋዎች የመዝናኛ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኃላፊ በመሆን ጡረታውን አስከብሮ በገዛ ፈቃዱ እስከተሰናበተበት 2003 ዓ.ም ድረስ ከ 25 ዓመታት በላይ አገልግሏል ።
በኢትዮጵያ ብሮድካስት በተለያዩ ዘርፎች ሲያገለግል ደጀኔ ከሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች
ከመጽሐፍት አለም አንዱ ሲሆን እጅግ በርካታ ከሆኑ አድማጮች ጋር የተዋወቀት ነበር ። በተለይም ‹‹ብርቅርቅርታ›› የተሰኘውን የትርጉም መጽሐፍ ከትሩፋት ገብረየስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በተረከበት ወቅት እርሱም ፕሮግራሙም በጣቢያው አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ተወዳጅነትን አትርፈውበት ነበር። በተጨማሪም በዕለተ ቅዳሜ የኪነጥበባት ምሽት ፣እሁድ ጠዋት የተለያዩ እንግዶችን በመጋበዝና ውይይት በማድረግ እንዲሁም መጣጥፎችን በማዘጋጀትና በማንበብ ፣ወቅታዊ ፕሮግራም ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ ሀገርህን እወቅና ሌሎችም ይጠቀሳሉ ።
ከመጽሐፍት ዓለም ፕሮግራም ማዘጋጀት የጀመረው ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ለ 30 ዓመታት ያህል የተለያዩ ልቦለድ መጽሐፍቶችን ለትረካ በማዘጋጀትና በማቅረብ ዘልቋል ። የመጽሐፍት ዓለም ቅርጽ ይዞ ሲዘጋጅ በደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብርን በደጀኔ ጥላሁን አዘጋጅነት ወጋየሁ ንጋቱ ተርኮት የነበረ ሲሆን ለፕሮግራሙ መወደድ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው ሲሆን ለረዥም ጊዜያት በርካታ መጽሐፍቶች እየተዘጋጁ እንዲተረኩ እና ፕሮግራሙ ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል የደጀኔ ጥላሁን የመጽሐፍት አመራረጥ ትልቅ አሻራ ጥሎ አልፏል። እየተወደደ በርካታ መጽሐፍት በደጀኔ ጥላሁን ከመዘጋጀት አልፈው ለብቻውና ከሌሎች ጋር በመሆን አቅርቧል ።
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ካዘጋጃቸው ወጥ የትርጉም እና ረዥም ልቦለድ መጽሐፍቶች መካከል የነበረው እንዳልነበር ፣ የታንጉት ሚስጢር ፣ የውበት ወጥመድ ፣ ጥቁር ደም ፣ የወዲያ ነሽ ፣ ቃል ኪዳን፣ ሳቤላ ፣ እሾሀማ ወርቅ ፣ ከአድማስ ባሻገር ፣ ቆንጆዎቹ ከአባይ በማንኪያ እንደማለት ሲሆኑ በተለይም ደግሞ ፍቅር እስከ መቃብርን 2 ጊዜ አዘጋጅቶ አቅርቧል ።
ለሸገር ሬዲዮ ጉንጉን እና አንድ ለእናቱ የተሰኙ መጽሐፍትን አዘጋጅቷል ።
ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን በርካታ አጫጭር ልቦለድ እና የወግ ድርሰቶችን አዘጋጅቶ ያቀረበ ሲሆን ከሚጠቀሱት አንዱ ሞገደኛው ነውጤ ነው። እራሱ የተረካቸው ረዥም ልብወለድ መጽሐፍት ደግሞ ብርቅርቅታ ፣ ኦሮማይ ፣ምንዱባን ፣ ሰንሰለት ሲሆኑ በፋና ሬዲዮ ሀኖስን በማዘጋጀት ተርኳል ። በኢትዮጵያ ሬድዮ ሌላው ሰው በተጨማሪም በዩቲዩብ እመጓ እና ወዘተ…ይገኛሉ ። ደጀኔ ጥላሁን ከመጽሐፍት ትረካዎቹ በተጨመሪ በርካታ ተወዳጅ ግጥሞችን አንብቧል ።
አጭር ልቦለድ እና የወግ ድርሰቶችን በብዛት የተረከ ሲሆን ማሕሌት ፣ ከሕይወት አንድ ጥግ ፣ የተሸጠው ሰይጣን ፣ ፕሮፈሰሩ ፣ የጨነገፈ ብዕር ፣ አሮጊቷ ፣ 5 , 6, 7 ፣ ሽማግሌውና ባህሩ ፣ ዶክተር አሸብር ለአብነት ማሳያ ናቸው ። ጋዜጠኛና ተራኪ ደጀኔ ጥላሁን ከመጽሐፍ ትረካዎቹ በተጨማሪ ሥነጽሑፍን ለሕብረተሰቡ ለማስተዋወቅ በሚያደርገው ጥረት እያንዳንዱ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ ተተርኮ ሲያበቃ የአድማጭን አስተያየት በስልክ ፣ በአካልና በደብዳቤ ተቀብሎ መልሶ በማቅረብ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችን በተተረከው መጽሐፍ ላይ በማወያየት እና ደራሲውን ወይም ተርጓሚውን ስለ ህይወት ታሪኩና ስራዎቹ በማነጋገር አቅርቧል ። ደራሲያኑን ከስራዎቻቸው በተጨማሪ ከማህበረሰቡ የማስተዋወቅ ሥራ ሰርቷል።
ጋዜጠኛና ተራኪ ደጀኔ ጥላሁን ከመጽሐፍት ትረካዎቹ ባሻገር የተለያዩ የዶክመንተሪ ስራዎችን የተረከ ሲሆን በሚሽል ፓፓታኪስ የተዘጋጀው የአደዋ ድል 100ኛ ዓመት የድል በዓል ዶክመንተሪ ጎላ ብለው ከሚጠቀሱት ሥራዎቹ መካከል አንዱና ዋናው ነው። በተለያዩ ፕሮግራሞች ለምሳሌ በእሁድ ጠዋት ፣ በቅዳሜ የኪነጥበባት ምሽት የሙያ ባለቤቶችን ቃለመጠይቅ አድርጓል ። ከኪነጥበቡና ከሳይንሱ መካከል ደራሲና ዲፕሎማት ክቡር ሀዲስ አለማየሁ ፣ ገጣሚና ባለቅኔ ክቡር ከበደ ሚካኤል ፣ ታላቋ ድምፃዊት ንጋቷ ከልካይ ፣ አስናቀች ወርቁ ፣ የሀገረሰብ ሙዚቃ አድባርና የሙሽራዬ ሙዚቃ ደራሲ በሻህ ተክለማርያም እና የናሳው ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉ ቃለመጠይቅ ካደረገላቸው እጅግ በጣም ጥቂቶቹ እና አንጋፋዎቹ ናቸው ።
ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን በሙያው አጋጣሚ የኢትዮጵያን ህዝብ ባህል ፣ ወግ፣ ታሪክና መልካምድር በአብዛኛው ስፍራ በአካል ተገኝቶ የተለያዩ ፕሮግራሞችን አዘጋጅቷል ። ከነዚህ ቦታዎች ውስኖቹን ለመጥቀስ ያህል አክሱም ፣ የሀ ፣ ላልይበላ ፣ አድዋ ፣ የጣና ደሴቶች ፣ የጥያ ትክል ድንጋዮች ፣ የጅማ አባጅፋር ሙዚዬም ፣ የኢሉባቡር ደኖች ፣ የባሌ ተራሮች ፣ ጋንቤላ ፣ ቤንሻንጉል ፣ ሐረር ጀጎል ይራንቦ መኖሪያ ቤት ፣ አፋር ፣ ሱማሌ ፣ ሙስታሂ ፣ ሞያሌ ፣ የከሬ ፣ አሰብ …ወዘተ የማየትና ፕሮግራሞች የመስራት ትልቅ ዕድል ገጥሞታል ። ሀገሩንና ባህሉን በስፋት ለማወቅም ትልቅ አጋጣሚ ሆኖለታል ።
ደጀኔ በ 1977 ዓ.ም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን አሳዛኝና አሰቃቂ ድርቅ በአብዛኛው በቦታው ተገኝቶ መከራውን በዓይኖቹ እየተመለከተ ጣሩን በጆሮዎቹ እያዳመጠ ዘግቧል ። ከዘገባው ባሻገር ሰፊ ፕሮግራምም አዘጋጅቷል ።
ደጀኔ ጥላሁን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚሰጡ የሙያ ስልጠናዎችን የተከታተለ ሲሆን በ EBC ቆይታው ለአዳዲስ እና ነባር የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ስልጠና ይሰጥና የሙያ ልምዱን ያካፍልም ነበር። ስለ አነባበብና ቃለመጠይቅ ብዙ ስልጠናዎችን ሰጥቷል። ” ይህ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው ” የሚለው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የጣቢውያ መክፈቻ ድምፅ እንዲሁም ” ከመጽሐፍት ዓለም ” የሚለው የፕሮግራሙ መክፈቻ ድምጽ ከብዙ የኢትዮጵያ ሬዲዮ አድማጮች ጆሮ የማይዘነጋ ብዙዎች እንደ ምልክት የሚወስዱት የታሪካዊ ድምጽ ባለቤት ነው።
ደጀኔ ጥላሁን 1981 ዓ.ም ከንጉሴ አየለ ጋር በመሆን ጣዝማ አስደናቂው የደራሲያን ህይወት በሚል ርዕስ መጽሐፍ በማሳተም ደራሲያን ከሥነጽሑፍ ስራዎቻቸው ጀርባ ያለውን ህይወታቸውን የሚሳይ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኘ ትልቅ ሥራን ሰርቷል ።
በድጋሜ በ 2002 አነባበብ እና የድምጽ አጠቃቀም በሬዲዮና በቴሌቪዥን በሚል ርዕስ ሙያዊ መጽሐፍ ጽፎ ለአንባቢያን ሲያቀርብ ለጽሑፉ መነሻ የሆነው የሚታዘበው ነገር ነውና ” እኔ የራሴን የአነባበብ ደረጃ የደረስኩበት እረጅም ጊዜን ወስጄ ነው ። ይህ ስለሆነ ወጣቱ የኔን ያህል ጊዜ ሊወስድ አይገባውም ። ትምህርትቤት ያለ ቢሆን’ኳን እንደተጨማሪ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል ይላል ” ደጀኔ ጥላሁን ።
2010 ዓ.ም የ 5 ደቂቃ የህይወት ታሪኮች( Five Minute Biography’s ) የተሰኘውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ወደ አማርኛ መልሶ ለህትመት አብቅቷል ። የመገናኛ ብዙሃኑን እና ባለሙያዎችን ባለው አቅም ሁሉ በጉልበቱም ሆነ በውቀቱ በውዴታ አገልግሏል ።
ጋዜጠኛና ተራኪ ደጀኔ ጥላሁን መጽሐፍት ማንበብና መተረክ ፣ ስነጽሑፍን ለህብረተሰብ በማስተዋወቅ ፣ አድማጮች እንዲያነቡ በማነሳሳት ፣ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ብዕር እንዲያነሱ በማድረግ የራሱን ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ። ለሙያው እድገት በርካታ ሥልጠናዎችን ሰጥቷል ። በጻፈው መጽሐፍ ላይ ተጋብዞ ማብራሪያዎችን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰጥቷል ። ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ጋዜጠኞች በመጽሐፉ አሰልጥኗል ። ብዙዎች መጽሐፍቶቹን እየተገለገሉባቸው እንደሆነም ይናገራል ።
ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን EBC በ 2003 ዓ.ም በራሱ ፍላጎት በፈቃዱ ከለቀቀ በኋላ በፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ይሰሩ ከነበሩ ተከታታይ የሬዲዮ ዲራማዎች በተወሰኑ ደረጃ የቀን ቅኝት ፣ የረገቡ ስህተቶች 140 ክፍል ፣ የብርሃን አፅናፋት 140 ክፍል ያሉትና የእባብ ጉንጉኖች 52 ክፍል ያለው ድራማ አዘጋጅቷል ። በአሁኑ ጊዜ በራሱ ዩቲዩብ እየተረከና የማስታወቂያ ሥራ ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል ።
ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን በዓለም አቀፍ የሬዲዮ ቀን በሀገራችን ኢትዮጵያ በ 2012 በተከበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን EBC ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እና ዩኔስኮ በጋራ በመሆን የህይወት ዘመን ምርጥ የሬዲዮ ጋዜጠኛ በሚል ርዕስ ሬዲዮ በኢትዮጵያ ተወዳጅ ሆኖ እንዲቀጥል ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የምስጋና እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ሲሰጡት የወርቅ የአንገት ሐብል ሸልመውታል። በድጋሜ በ 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፍ የበጎ ሰው ተሸላሚም ነበረ። በፍላጎቱ ያለ እረፍት EBC ን ከ 25 ዓመታት በላይ አገልግሏል። ፊልም ማየትና መጽሐፍት ማንበብ የሚያዝናና ጋዜጠኛ ደራሲና ተራኪ ነው።
ደጀኔ ጥላሁን በግል ህይወቱ እና በቤተሰቡ ጉዳይ የ 3 ልጆች አባት ሲሆን አያት ለመሆንም በቅቷል ።