ይፍቱስራ ምትኩ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ ይገኛል። በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጧል።

ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችና የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል። በተጨማሪም በሳይንስ፣ በመምህርነት፣ በምህንድስና እና በሌሎችም ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ አንባቢ እያመጣን እንዲታወቁ ጥናትና መረጃ ማድረግ ለሚሻም ተደራሽ ስናደርግ ቆይተናል።

የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።አሁን በዚህ ፅሑፍ ታሪኳን እጥር ምጥን አድርገን የምናቀርብላችሁ ደራሲ የ35 አመት ወጣት ስትሆን ይፍቱስራ ምትኩ ትባላለች ። የህይወት ታሪኳን ዕዝራ እጅጉ ሰንዶታል።

ይፍቱሥራ ምትኩ የተወለደችው ጋሞ ጎፋ ሳውላ የምትባል ከተማ ጥር 07/1983 ዓ.ም ነው። ከአምስት ዓመቷ ጀምሮ ከአያቶቿ ጋር ወደጎጃም በማቅናት መጀመሪያ መርጦለ ማርያም ለሁለት ዓመት ከዛም ደብረማርቆስ እስከአምስተኛ ክፍል ድረስ ተምራለች። ከዛም በሌላ የህይወት መንገድ ከስድስተኛ እስከአስረኛ ክፍል በአዊ ዞን በሚገኙ አችጊ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ችባችባሳ አንደኛ ደረጃ ት/ቤትና አንከሻ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምራለች።

የመሰናዶ ትምህርቷን ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ታቦር ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት አጠናቅቃ በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ ለመማር ተቀላቅላ ሦስተኛ ዓመት እንደተጀመረ በግል ምክንያትና ውሳኔ የዩኒቨርስቲውን ትምህርት አቋርጣ ወደ ሥራ አለም ገባች።

ከዩኒቨርሲቲ ከወጣች ጀምሮ በሽያጭና ተያያዥ ስራዎች በቋሚ ቅጥርና በኮንትራክት ስትሠራ የቆየች ሲሆን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በግል የማስታወቂያ፣ የሁነት ማስተባበር እንዲሁም የሽያጭ ስራዎችን ሰርታለች።

በ2014 ዓ.ም የመጀመሪያ መጽሐፏን ‘በተለይ አስራ አንደኛው’ የተሰኘ ልቦለድ ካሳተመች በኃላ ከዛ በፊት በአለፍ ገደም ትሠራ የነበረውን የመጽሐፍ አርትዖት ስራ፣ የሰዎችን የህይወት ታሪክ መፃፍና ተያያዥ ስራዎችን በቋሚነት በመስራት ስራዋ ወደ ሙሉ ጊዜ ፀሐፊነት ተለውጦ አሁን ላይ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሆናለች። ሁለተኛ መጽሐፏን ‘ወድቆ የተገኘ ሐገር የተሰኘ መጽሐፍ በ2015 ዓ.ም ለህትመት አብቅታለች።

#የቴሌግራም ምጥን ቃለ-ምልልስ

ሰው ሲያመሰግንሽ ደስታሽ ከልብ ነው ወይስ ከላይ ከላይ ?

መልስ፦.ለምን ያመሰግነኛል ሰው? ያን ያህል በምስጋና ሰውን ቁጭ ብድግ የሚያስደርግ ሥራ የሰራሁ አይደለሁም።

ፌስ ቡክ ላይ በምትፅፊው አከብርሻለሁ። ጥሩ እንደምትፅፊ ይታወቅሻል?

መልስ ፦ ፌስቡክ ከወዳጆች ጋር እንደመጫወቻ ሜዳ ነው የምቆጥረው በክብ ሆኖ ወሬ እንደማውራት።ደግሞ መጥፎ ፀሐፊ ነኝ ብዬ አላስብም።

ታሪኬ ለትውልድ ያስተምራል ብለሽ ታምኛለሽ?

መልስ፦የማንም ሰው ታሪክ በደንብ ቢነገር ማስተማሪያ ነው ብዬ አስባለሁ።

ያንቺም የልጅሽም አክባሪ ነኝ። መንገዳችሁ ይቃና። አመሠሰግናለሁ እንዳትይ አሁን ምን ተሰማሽ? ሲመሰገን የሚደነገግጥ አለ? ይበዛብኛል የሚል ስላለ ነው።

መልስ ፦ አሜን እንደ ምርቃትህ ይሁንልን ! ምን ተሰማሽ ? ስትል ….. ክብር ይሰማኛል።እኔና ልጄ የመጣነው መንገድ ረዥምና ብዙ ነው። እና ሰው አስተውሎን መልካም ሲመኝልኝ በጣም ክብር ይሰማኛል።

ልጅሽ ጓደኛሽም ነች። እርሷ ስለ አንቺ የምታስበው ይገባሻል( ትረጂዋለሽ)
ስለ አንቺ ጎበዝ ፀሀፊነት ሌሎች ይመስክሩ። አንቺ ግን ብዕርሽ ፣ አፃፃፍሽ ይማርክሻል?

መልስ፦ ጥሩ እፅፋለሁ ብዬ አስባለሁ።

እናትነት፣ ደራሲነት ለኑሮ ተፍ ተፍ ማለት ላይ እንዴት ነሽ? ለራስሽ ውጤት ስጭ ።

መልስ፦ በቻልኹት ነኝ ባልኹት በኩል ላለመጉደል እሞክራለሁ።እናት መሆኔ ለድርሰቱ በብዙ መልኩ የረዳኝ ነገር ነው።የኑሮ ተፍ ተፍ ምንስ ቢሆን መቼ ሊቀርልኝ? ውጤት መስጠት ይከብደኛል።

ባለፈው የላክሽው የህይወት ታሪክሽ ተመችቶኛል። እስቲ ለመዝገበ አእምሮ የሚሆን መሳጭ ታሪክሽን ቀንጭቢልማ==

መልስ እሺ። እልካለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *