ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅአለ መደነቅ ያለባቸው ባለውለታ መሐንዲስ
ለኢትዮጵያ ለዋሉት ውለታ እናመሰግናለን ። ቀሪ የሥራ ጊዜዎት የተባረከ ይሁን
ተወዳጅ ሚድያና ኮምዩኒኬሽን ለአገር የሠሩ ሰዎችን የሙያና የሕይወት ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። በሚድያ፣ በኪነጥበብ፣ በህክምና፣ በምህንድስና፣ በመንግሥት አስተዳደር፣ በመምህርነት በሌሎችም 20 ዘርፎች የባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነድን ለተመራማሪዎች ተደራሽ እንዲሆን እያደረግን እንገኛለን።
ብዙ በሳል ባለሙያዎች ቢኖሩንም ማን እንደሆኑ ፣ምን እንደሠሩ ጎግል ላይ መረጃው አይገኝም። በተለይ ቅልል ፣7 5 አመታት ከ500 በላይ ሰዎችን ታሪክ በቀላሉ ጎግል ላይ እንዲገኙ አድርገናል። tewedajemedia.com በተሰኘው ድረ ገፃችንም ላይ ታሪኮቹ እየተነበቡ ይገኛሉ። ከድረ ገፅ ባለፈም መዝገበ አእምሮ በሚል ርዕስ በሁለት ቅፅ ታሪኮቹን በመፅሀፍ አሰባስበን ለማሳተም እና ለማሠራጨት በቅተናል። በዚህ ሥራችን ተጠናክረን የምንቀጥል ሲሆን ከእኛ በኃላ የሚመጣው ትውልድም የእኛን መንገድ ያስቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ከሰሞኑ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ እና ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር ያዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ታድሞ ነበር። ከመታደም ባለፈ አንድ ሙሉ ቀን የፈጀውን የኮንፈረንሱን ሁነት በቪድዮ እና በፎቶ ለመቅረፅ ችሏል።
በዕለቱ ኮንፈረንሱ ላይ ከቀረቡት የጥናት ወረቀቶች አንዱ Circular Construction for Built Environment የሚል ሲሆን የወረቀቱም አቅራቢ ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅአለ ሲሆኑ የጥናት ወረቀቱም የግንባታ ማቴሪያሎችን ከጥቅም ውጭ ሲሆኑ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን መንገድ ያመላከቱበት ባለ 28 ገፅ የጥናት ወረቀት ነው። ተባባሪ ፕሮፌሰር ውብሸት በአገራችን በኮንስትራክሽን ዘርፍ አንቱታ ያተረፉ በ2014 በመምህርነት ዘርፍ የበጎ ሰው ሽልማት ያሸነፉ ሰው ናቸው። በቅርቡ 61 ዓመት የሚሞላቸው ዶክተር ውብሸት ዠቅአለ ከተወዳጅ ሚድያ መስራች እና ባለቤት ታሪክ ሰናጅ እዝራ እጅጉ ጋር ባደረጉት ቆይታ አገራቸውን በማገልገላቸው ፍፁም ርካታ ይሰማቸዋል። ለሙያው ማደግ እየተጉ የሚገኙት ዶክተር ውብሸት ወደፊት ታሪካቸውን ፅፈው እንደሚያስነብቡን ተስፋ እናደርጋለን። እስከዚያ ግን በኮንስትራክሽን ዘርፍ ምን ሠሩ ? እርሳቸው ማናቸው ? የሚለውንም ሰንደነዋል። ዕዝራ እጅጉ የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው አጠናክሮታል።
ዶ/ር ውብሸት ዠቅአለ በትምህርትና ስልጠና ረገድ
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን (BSC) በሲቪል ኢንጅነሪንግ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እና በህግ (LLB) ከባህርዳር ዩንቨርሲቲ በተልዕኮ ትምህርት፣አግኝተዋል።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (MSC) በስትራክቸራል ኢንጅነሪንግ ከስትራትክላይድ ዩንቨርሲቲ /Strathclyde University/ UK፣
የሦስተኛ ዲግሪያቸውን (PHD) በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ማኔጅመንት ከኖርዌጂያን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ኖርዌይ / Norway፣
ከፍተኛ ዲፕሎማ (Higher Diploma) በከፍተኛ ትምህርት ማስተማር ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ፣አግኝተዋል።
ወደ ሥራ ዓለም
በሥራው አለምም ለ38 ዓመት በዋንኛነት በአካዳሚክስ፣ በመንግስትና በግል የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።በጥቂቱ ለመጥቀስም ያህል፣
በከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ውስጥ የፊዚካል ፕላኒንግ ማስተባባሪያ ፅህፈት ቤት ከጀማሪ መሐንዲስነት እስከ ፅህፈት ቤት አስተባባሪ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፤ በፅህፈት ቤቱም በጊዜው ለነበሩ 2 ዩንቨርሲቲዎች እና 13 ነባር ኮሌጆች የከፍተኛ ትምህርት Facility ዎችን Inventory በማድረግና በመለየት እንዲሁም ተጨማሪ ፍላጎቶች በማዘጋጀት ወደ ዲዛይን እንዲቀየሩ በማድረግ በተለይ በስትራክቸርና ሳኒተሪ ዲዛይን በቀጥታ በማሳተፍ በተጨማሪ በግንባታ ቁጥጥር ላይ በመሳተፍ የመጀመሪያዎቹን 8 ዩኒቨርሲቲዎች እንዲፈጠሩ አስችለዋል።
ምርምር እና ማስተማር
ዶክተር ውብሸት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከሌክቸረርነት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ሲያገለግሉ በማስተማር፣ምርምር በመሥራትና በማሠራት ከ200 በላይ የማስተርስ እና የፒ.ኤች.ዲ መመረቂያ ምርምሮችን በማማከር፣በመገምገም እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩ የማማከር አገልግሎቶችን በፕሮጀክት መሪነት እና በባለሙያነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
በውጪው ዓለም በዲናርዶ ፓርትነርሺፕ (Dinardo Partnership) አማካሪ ድርጅት በጀማሪ ስትራክቸራል ዲዛይን ኤክስፐርትነት ሲያገለግሉ ፈጠራ የታከለበት በአጭር ጊዜ የኮንስትራክሽን ሥራውን ሊያከናውን የሚያስችል ሁኔታዎችን በመፍጠር አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በቀድሞው የአቅም ግንባታ ሚንስቴር ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅም ግንባታ ዳይሬክተር ሆነው Engineering Capacity Building Program በሚቀረፀበት ጊዜ አገር(ን ወክለው ከጀርመን /expert /ጋር በመሆን አብረው ቀርፀዋል፣
በሃገራችን ከሰሩ SMEC እና SPAN ከሚባሉ የውጭ ኮንሰልታንሲ ድርጅቶች ጋር በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት፣ በኮንትራት /Contract/፣ በክሌይም /Claim/ እና በአለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች /dispute Resolution / ኤክስፐርትነት ባገለግሉበት ወቅት የዘርፉን ኮንስትራክሽን የማዘመን ጥናት ላይ የበኩላቸውን አድርገዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውብሸት የኮንስትራክሽን መርሀ ግብርን ትክክለኛነት ማረጋገጫ መንገዶችንም ዕውን በማድረግ ትልቅ አሻራ ማኖር ችለዋል። ይህንንም ማረጋገጫ በሶፍትዌር ጭምር እንዲለማ በማድረግ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።
የክሌይም /Claim/ ማስተዳደር እና አለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች /dispute Resolution Management manual / እና surveying ፣ ለመንገድ ስራዎች ለኮንስትራክሽን ማቴርያል የአስራር ስርአት ቀርፀዋል።
እኒህ ታላቅ የምህንድስና ባለሙያ ለሀገራችን የ30 ዓመት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታ እና 10 ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ዝግጅት የመሩና ስራውን እንደባለሙያ የተሣተፉ ናቸው።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውብሸት ዠቅአለ፣ የመስኖ ዘርፍ ፍኖተ ካርታ ረቂቅንም አዘጋጅተዋል። 26 የመስኖ ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ሥራዎች ማከናወኛ ኮድና ስታንዳርድ አስተባባሪ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ።
እርሳቸው በሙያቸው ያገለገሉና እያገለገሉ የሚገኙ አንጋፋና ብርቅዬ የሀገራችን የኮንስትራክሽን ባለሙያና ተመራማሪ ምሁር ናቸው፡፡
ለሽልማት ያበቋቸው ሥራዎች
የመጀመሪያው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ማኔጅመንት ዶክተር በመሆናቸው፣
የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት 18 የእውቀት መስክ (Body of knowledge) እና አንድ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት /code of practice / እና በዘርፉ ለአለም አቀፍ የዕውቀት መስክ ተጨማሪ 4 የዕውቀት መስክ(የእውቀት አውድ/Context /፣የእውቀት መስክ /Body of Knowledge/ የኩባንያ እድገት ደረጃ/Maturity level ለሀገራችን እንዲዘጋጅና በመምራትም በባለሙያነት አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ለኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ከሚታወቁት 13 የዕውቀት መስኮች በተጨማሪ 8 የዕውቀት መስኮች ለአለምአቀፍ አገልግሎት ግብአት እንዲሆኑ አበርክተዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውብሸት የኮንስትራክሽን ኩባንያ እና የባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ መመሪያን በሥር ነቀል ደረጃ በሚሻሻልበት ጊዜ አስተባባሪ እና ተሳታፊ ነበሩ።
ከዚህም ባሻገር በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የፒኤች ዲ ዲግሪ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገር ውስጥ ሲከፈት የካሪኩለም ክለሳ፣ እንደዚሁም ቅኝት አድርገዋል። በአሁኑ ሰዓትም እዚህ በአገር
ውስጥ 6 የፒ ኤች ዲ ተማሪዎችን እያማከሩ ይገኛሉ። በአለምአቀፍ ደረጃም በኤክስተርናል ፈታኝነት በማገልገል ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ተወጥተዋል።
የንግድ ባንክ ህንፃ ድርድር ጊዜ የውጭ ምንዛሬ ለውጥ ቋሚ ሆኖ እንዲወሰን ዶክተር ውብሸት ባደረጉት አስተዋጽኦ ግንባታው በሚጠናቀቅበት ጊዜ የተፈጠረውን የዋጋ ልዩነት እስከ 2ቢልየን ማዳን ተችሏል።
በምሥራቅ አፍሪካ በከፍታው አንደኛ የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንፃ የቴክኒካል አማካሪ ቡድን አባል በመሆን ከፕሮጀክት ዝግጅት ጀምሮ ውለታ እስኪፈፀም ድረስ የላቀ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው፣ኢትዮጵያ ምንጊዜም የምታመሰግናቸው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ባለውለታ ናቸው።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበርን በመስራችነትና በፕሬዝዳንትነት ለ6 አመታት እና የማህበሩ የአማካሪዎች ምክር ቤት መሪ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው።
በማደግ ላይ ላሉ አገሮች እና ለኢትዮጵያ የሚሆን የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ሽግግር ሞዴል በማዘጋጀታቸው፣
በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ካሪኩለም በመቅረፅ የተሳተፉና ተግባራዊ በማድረግና ለትምህርት ክፍሉ መማርና ማስተማር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና እና ማኔጅመነት ሙያን ለማሳደግ በ8 ዩንቨርሲቲዎች በቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ላይ በማስተማር ከ200 በላይ የምረቃ ጥናታዊ ፅሁፍን በማማከር እና የምረቃ ጥናታዊ ፅሁፎችን የውስጥና የውጭ ፈታኝ በመሆን (Internal & External Examiner) አገልግሎት ሰጥተዋል።
ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተዋናዮች ከ50 በላይ የሆኑ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ነክ አጫጭር ሥልጠናዎች በመስጠታቸውና ሙያው በእውቀት እንዲመራ ላደረጉት አስተዋፅኦ፣
መንግስት በተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች፣ የሬጉላቶሪና የህግ ማእቀፎች ሲረቀቁ በንቃት በመሳተፍ እና ግብአት በመስጠታቸው፣ይመሰገናሉ።
ለ14 የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ የመጀመሪያ Dispute Resolution Review Expert ሆነው የሠሩ እና ለዚህም መንግስት ለውጭ ባለሙያዎች በውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ክፍያ ይከፍል የነበረውን በማስቀረታቸው ትልቅ ባለውለታ ናቸው።
በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ የህንፃ (የጤና፣የአካባቢ ደህንነት እና የእሳት አደጋ ) ኮዶች ዝግጅት የመሩና ያስተባበሩ እና እንደ ባለሙያ የሠሩ በመሆናቸው፣
በሦስት የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት የእውቀት መስኮች ላይ የማስተማሪያ ፅሁፍ በመፃፋቸውና ለተማሪዎችም ሆነ በስራ ላይ ላሉ ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲሠጥ በማበርከታቸው የሚከበሩ ባለሙያ ናቸው።
በበርካታ ፕሮጀክቶች ላይ በአማራጭ የግልግል መፍቻ ዘዴዎች (በArbitiration እና Conciliation) በመሳተፍ እና ይህም አማራጭ በአገሪቱ እንዲዳብር እና እንዲለምድ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ከኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት እና ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ሙያ ጋር የተያያዙ ከ40 በላይ ሳይንሳዊና የምርምር ፅሁፎችን በተለያዩ መፅሄቶችና መድረኮች በማሳተማቸውና በማቅረባቸው፣
በቀድሞው የአቅም ግንባታ ሚንስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ዳይሬክተር በመሆን በማገልገላቸው እና የኢንጅነሪንግ እና የዩንቨርሲቲ አቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ሲቀረፁ ከፍተኛ ሙያዊ አስተዋፅኦ ያበረከቱም ናቸው።
ለተማሪዎቻቸው አባታዊ እና ወንድማዊ አቀራረብ በመፍጠር ተማሪዎቻቸው በእውቀት፣ በክህሎት እና በሥነምግባር ታንፀው እንዲመረቁና በተለይም የስራ እድል እንዲያገኙ በማመቻቸት እያደረጉት ያለው አስተዋፅኦ፣የሚጠቀስ ነው።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ማዕከላት ሥርዓተ ትምህርት ሲቀረጽ ድጋፍ በማድረጋቸው፣
በከፍተኛ ትምህርት ዋና መምሪያ የፊዚካል ፕላን ማስተባበሪያ ኃላፊ በመሆን ለ6 አመታት ያገለገሉ ሲሆን በዚህም ወቅት የ2 ዩንቨርሲቲዎችን እና 13 ኮሌጆችን የኮንስትራክሽን የፊዚካል ፋሲሊቲዎችን የዲዛይንና እና ሱፐርቪዥን ስራዎችን በልዩ ብቃት አከናውነዋል።
የግል ዩንቨርሲቲዎችን የቅድመ እውቅና፣ የእውቅናና የእድሳት ግምገማ በሚከናወንበት ጊዜ የHERQA የውጭ ገምጋሚ ኤክስፐርት /External Assessor/ በመሆን በማገልገላቸው
በግል የራሳቸውን የአማካሪ ድርጅት በማሳተፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ያለበትን የእወቀትና የኮንስትራሽን ክፈተት ለመሙላት practice on job training ስልጠና በመስጠት ፣የተለያዩ የግል ኮንስትራክሽን ድርጅቶችን የአሰራር ስርአት በመቅረፃቸው እና ፣
በዘመናዊ የፕሮጀክት አቅርቦት ዘዴዎች (Design Build[DB]) በአገሪቱ ውስጥ በተለይም በመዲናቸን አዲስ አበባ ያሉ አዲሱን የንግድ ባንክ ህንፃ ጨምሮ የመንግስትና እና የግሉ ዘርፍ high rise building ባለቤትን በመወከል ከጨረታ ሠነድ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ውለታ መፈፀምና/chief Negotiator /በመምራት፣Design review/ የዲዛይን ክለሳ በማድረግ እንዲሁም የግንባታ ጥራት ቁጥጥር /Quality control / በመስራት እና Contract Administration /ኮንትራት በማስተዳደር/ የሠሩ በመሆናቸው
በአርክቴክቸራል የመጀመሪያ ዲዛይን መረጣ ወቅት ከ10 በላይ የሙያዊ ዳኝነት /jury Service / የሠጡ በመሆናቸው ፣
ከኢትዮጵያ ኮንሰትራክሽን ባለስልጣን ጋር በመሆን የ/Alternative Dispute resolution /፣ partnering procedures እና ለ Conciliation, DRE Board እና Arbitration ጥናታዊ ፁሁፍ ሲዘጋጅ በአመራርና በአባልነት የሠሩ ናቸው።
ከወጪ በተለይም ከUK, Norway, Kenya , Hong Kong, Germany ዩንቨርሲቲዎች የPHD coordinator ,የውጪ ፈታኝ/examiner/ ፣lecture note ፣Course note በማዘጋጀት የሠሩ በመሆናቸው ይከበራሉ።
እኝህ ያገር ባለውለታ ምሁር ለሠሩት የተለያዩ ስራዎች ከመንግስት ከግልና ከተለያዩ አካላት ምስጋናና የዕውቅና ሽልማት የተበረከተላቸው ቢሆንም በበጎ አድራጎት ስራቸው እሳቸውም ይፈዊ በልሆነ መንገድ ልግስናቸው ያልተዘመረላቸው ለመለገስ፣ለመርዳት እና ለመስጠት በእጃቸው ብቻ ሳይሆን በልባቸውና ከልባቸው እሚለግሱ በጎ አድራጊ ናቸው።
ዕውቅና እና ሽልማት
አንደኛው ያገኙት ሽልማት ከአዲስ አበባ መስተዳድር እና የከተማ ልማት ሚኒስትር የሕይወት ዘመን የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ባለሙያ ነው።
ሌላው የኢትዮጵያ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች ማህበር የሕይወት ዘመን የሲቪል ምሕንድስና ባለሙያ ዕውቅናንም አግኝተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር distigushed ‘የተለዩ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ባለሙያ’ የሚል ትልቅ ዕውቅና አግኝተዋል።
የበጎ አድራጎት ሥራ
ከቤተሰብ ርቀው ወደ አዲስአበባ እሚመደቡ የተለያዩ ክልል ተማሪዎችን እንደ ወላጅ በመቅረብ በገንዘብ በመደጎም፤ተመርቀውም ሲወጡ አንዳንድ ወጪዎቻቸውን በመሸፈንና ሥራ በማፈላለግና በማስቀጠር የሙያ አባት ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ወላጃዊ አባት በመሆን ፍቅር የሚለግሱ አባት ናቸው። እርሳቸው ይህን ሲያደርጉ ልበ ሩሩህነት ብቻ ሳይሆን ሳይማር ያስተማረኝን አርሶ አደር ውለታ የከፈሉ የሚመስላቸው ቅን ልብ ያላቸው መምህር ናቸው።
በመኖሪያ ሠፈር እና ቢሮ አካባቢያቸው የተለያዩ ወጣቶችን አስፈላጊው የሙያ ስልጠና ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ እና ስራ በማስያዝ የሚታወቁ፣ናቸው።
በጥልቅ ድህነት ውስጥ የሚገኙ አቅመ ደካሞችን በማሳካም ወርሃዊ ተቆራጭ የሚያደርጉ ናቸው።
በሱስ የተያዙ ወጣቶችን ያለመታከት ምክር በመለገስ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ በገንዘብ በመርዳት ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚታትሩ እንዲሁም የአእምሮ ዕክል የገጠማቸውን ወጣቶች ህክምና እንዲያገኙ የሚረዱ ናቸው።
የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ፕሮግራሞቻቸውን እንዲያሳኩ በገንዘብ የሚረዱ በተለይም የህብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑ ሴቶችን ለመርዳት ልዩ ፍላጎት የተነሳ የሴቶች ዐቅም ግንባታ ስራ ላይ የሚሰሩ በጎ አድራጎት እንደ ወጣት ሴቶች ክርስቲያን ማህበርን (YWCA) በመለገስ የሚታወቁና በዚህም እውቅና ያገኙ፣
የተለያዩ የሙያ ማህበራትን ጊዜን ፣ ገንዘብንና እውቀትን በመለገስ የሚታወቁ ቢሆንም በተለይ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽንና ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበርን (ECoTMPA) ( ቢሮ እና የቢሮ እቃዎችን በመለገስ እና በማሟላት እንዲሁም ለማህበሩ ቢሮዋቸውን ለ 10ዓመት ሠጥተው ማህበሩ በእነዚህ አመታት ለቢሮ ኪራይ ከፍተኛ ብር ይከፍል የነበረውንና አቅም ላልነበረው ማህበር እጅግ ከፍተኛ ወጪ ይሆን እንደነበር እሙን ነው። ፤በዚህም የተነሳ እኝህ በጎ አድራጊ በሙያ ማህበሩ አባላት ልብ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ናቸው።
በሚኖሩበትም ወረዳ የኮብልስቶን ስራ በሚከናወንበት ወቅት በገንዘብ እና በሙያቸው ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል።
በተለያየ ጊዜ የኮንስትራክሽን ሚንስቴር ለባለድርሻ አካላቶች ሙያዊ ገለፃ ፣አጭር ስልጠና እና ሙያዊ ድጋፍ ያለምንም ክፍያ ሥልጠና ይሰጣሉ።
በተጠየቁበት የእምነት ተቋማት ሁሉ በተለያየ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው
ለኮንትራክተር አሶሴሽን በተለያዩ ጊዜያቶች ሙያዊ ገለፃ እና ምክር መስጠታቸው
የ PHD እና ማስተርስ ተማሪዎች የመመረቂያ ምርምር ፁሁፍ በሚያደርጉ ጊዜ ተጨማሪ ድጋፍ በስጠት የሚታወቁም ናቸው።
ከላይ በተቀነጨቡ በጎ ሥራዎች በተማሪዎቻቸው በተለያየ ጊዜ የእራት ግብዣና በየኣመቱ በተመራቂ ተማሪዎች ሽልማት ማግኘታቸው የበጎነታቸው እማኝነት ይሁን እንጂ የእኝህን በጎ አድራጊ ግለሰብ ማንነት በዚህ ብቻ ከትበን አንቋጭም። ወደፊትም መፃፋችን ይቀጥላል ። ለዶክተር ውብሸት ዠቅአለ መልካሙን እንመኛለን።
፧