ፀሐይ መላኩ

ደራሲት ፀሐይ መላኩ ፤ ግንቦት 16 ቀን 1944 ዓ.ም. ዐዲስ አበባ ከተማ ተወለደች። ፊደል የቆጠረችው በቄስ ትምህርት ቤት ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ዐዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ፤ መለስተኛ ኹለተኛ ደረጃን ደብረ ታቦር በዐፄ ቴዎድሮስ እንዲሁም ኹለተኛ ደረጃን ጎንደር፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሙያ ትምህርት ቤት አጠናቀቀች።

በኋላም በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመምህርነት ኮርስ እንዲኹም በንግድ ሥራ ትምህርት በዲፕሎማ፣ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋና በሥነ-ጽሑፍ በዲግሪ ተመርቃለች።ከልጅነቷ መንፈሳዊ የግዕዝና የአማርኛ መጻሕፍትን ከዘመናዊው ትምህርት ጐን ለጐን ታነብብ ነበር። ይህም ወደ ሥነ-ጽሑፍ መሥመር የመራት ሲኾን፤ ዝንባሌዋን በተግባር የሞከረችውም የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኾና በሥነ-ጽሑፍ ክበብ ውስጥ ተሳታፊ በነበረችበት ወቅት ነው።

ፀሐይ ወደ ሥራ ዓለም የገባቸው በ1963 ዓ.ም በአሰላ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የንግድ ሥራ መምህርት ኾና ነው። ቀጥላ በ1973 ዓ.ም. ዐዲስ አበባ ተመልሳ በጄኔራል ዊንጌት የሙያ ትምህርት ቤት በጸሐፊነትና በመምህርነት አገልግላለች።

በዛ ወቅት ነው ከለገዳዲ የትምህርት መገናኛ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ተገናኝታ በተለያዩ የብዕር ስሞች መጣጥፎችን ማቅረብ የጀመረችው። በተለይ “ቅዳሜን ከ’ኛ ጋር”፣ “እሑድን ለአንድ አፍታ” እና “ብዕር በሴት ዐምባ” በተሰኙ ዝግጅቶች አስተማሪና ማራኪ ጽሑፎችን ታቀርብ ነበር። ይህም አጋጣሚ ችሎታዋን የፈተሸችበትና ራሷን ፈልጋ ያገኘችበት ነው።ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ ወደ ረጅም ልብ ወለድ ድርሰት ፊቷን አዞረች። ‹‹ቋሳ›› በ1982 ዓ.ም ለንባብ ያበቃችው የመጀመሪያ የረጅም ልብወለድ ሥራዋ ነው። በኋላም አንጉዝ ለንባብ በቃ። ከ1995 ዓ.ም መስከረም ወር ጀምሮ በፈቃዷ ጡረታ በመውጣት ሙሉ ጊዜዋን ለሥነ-ጽሑፍ ሰጠች። በዚህ ጊዜም ‘ቢስ ራሔል’ የተሰኘውን መጻሕፍ ለንባብ አበቃች። ቀጥላም እመ-ምኔት እና የንስሐ ሸንጎ የተሰኙ መጻሕፍትን አስነበበች። የኹለቱ መጻሕፍት ሽያጭም ለማኅበረ ቅዱሳን የቢሮ ሕንጻ ግንባታና በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስም ለተሰየመው ገዳም (ወሎ) ማጠናከሪያ እንዲኾን በስጦታ አበርክታዋለች።የጴጥሮስ ዋዜማ፣ ‘The Drastic Charity’ የተሰኙ ታሪካዊ ልብ ወለዶች፤ ‘ጀግና እንደ ቴዎድሮስ፣ ቆራጥ እንደ ጴጥሮስ’፣ ’ኰሎኔል ታደሰ ሁንዴ’ የተሰኙ የግለ-ታሪክ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅታለች።

ከእነዚህ በተጨማሪ፥ የዘመን ቀለማት፣ ዜማ ብዕር (ቁጥር 1 እና 2) በጋራ የአዘጋጀቻቸውና በመድበል የአሳተመቻቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህ ብቻ ሳትወሰን፤ የስሜት ትኩሳት (ቁጥር 1 እና 2) የግጥም ስብስብ መጻሕፍት አስነብባለች። የተለያዩ የሬድዮ ተውኔቶችንም ጽፋለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *