ደረጄ ገብሬ በመጋቢት 1949 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ስሙ አንጭቆረር በተባለው ቦታ ተወለዱ። በዋዩ አንደኛ ደረጃ፣ በደብረ ብርሃን ኃይለ ማርያም ማሞ ኹለተኛ ደረጃ እና የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በዐዲስ አበባ ዮንቨርስቲ ተምረዋል። በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአማርኛ ቋንቋ የማስተማር ሥነ-ዘዴ ደግሞ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል።
በዐዲስ አበባ ዮንቨርስቲ ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት በማገልገላቸውም በተጨማሪ የተከታታይ ትምህርት ፕሮግራም አስተባባሪ በዩንቨርስቲው የሚዘጋጅ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር የአማረኛ ቋንቋ የሥነ-ጽሑፍ እና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ኃላፊ በመኾን አገልግለዋል ። ደረጄ ገብሬ የኢትዮጵያን ሥነ-ጽሑፍ ትምሀርት እና ዕድገት የሚያግዙ መጻሕፍትን እና የጥናት እና ምርምሮችን አካሂደዋል ። በተለያዩ መድረኮች አቅርበዋል፣ አሳትመዋል። ከመጻሕፍቱ ውስጥም ጠይም ዕንቁና ሌሎች የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ፣ ተግባራዊ የጽሕፈት መሳሪያ፣ በተማሪዎች የቤት ሥራ የመምህራን እና የወላጆች ሚና መራኄ ንባብ የማንበብ ክኺል፣ ልጆችን በተረት ማስተማር፣ ተረት እንደገና የማንበብ የመጻፍ ችሎታ ማዳበሪያ፣ ጀግኖቻችን፣ አጫጭር የታዋቂ ግለሰቦች ታሪክ ለልጆች ይጠቀሳሉ። በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል የታተሙ እና ለልጆች ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ ለ3ተኛ እና ለ4ተኛ ክፍል ተማሪዎች የሚያገለግሉ 13 ያህል መጻሕፍት ታትመውላቸዋል። በርካታ ወጣት እና አንጋፋ ደራሲያን ባሳተሟቸው መጻሕፍት ውስጥ በማማከር አስተያየት በመስጠት እና የአርትኦት ሥራ በመሥራት የተወጡት ሚና ለሥነ-ጽሑፍ ዕድገት የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍም “ፕሮጃይኒስት” በተሰኘ ዋና ትኩረቱን በሴቶች እና ሕፃናት ላይ ባደረገ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ውስጥ በቦርድ አባልነት ከ1998ዓ.ም ጀምሮ ነጻ ግልጋሎት እየሰጡ ይገኛሉ ። በተማሪዎች የቤት ሥራ የመምህራን እና የወላጆች ሚና በተሰኘው መጻሕፍ ላይ በዐዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ልምዳቸውን አካፍለዋል። ‹‹በልኅቀት የንባብ ማዕከል በጎ አድራጎት›› ድርጅት ውስጥ በበጎ ፍቃደኝነት ያገለግላሉ።
በአኹኑ ግዜ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዐዲስ በጀመረው “ብላቴና” የልጆች መጽሔት ላይ ዓምድ ተሰጥቷቸው እየተሳተፉ ይገኛሉ። ለአማርኛ ቋንቋ መምህራን የሙያ ላይ ስልጠና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ሰጥተዋል። በተለያዩ ግዜያት በሚደረጉ የሥነ-ጽሑፍ ውድድሮች ላይ በዳኝነት እና በአስተባባሪነት ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ከዐዲስ አበባ ዮንቨርስቲ ፕሬስ ጋር በመተባበር የሚዘጋጀውን የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ እና ባዛር እንዲሁም “የተማረ ያስተምር ስኮላርሽፕ ፈንድ” የተሰኘ የተቸገሩ ተማሪዎችን የሚረዳ አሜሪካን ሀገር ባሉ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ በጎ አድራጎት ድርጅት በኢትዮጵያ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ኾነው አገልግለዋል። ደረጄ ገብሬ በርካታ የመጀመሪያ እና የኹለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ከማማከር ባሻገር የገንዘብ አቅም ላጠራቸው በርካታ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ መጻፊያ ወረቀት ገዝቶ በመስጠት እና በመሰል በጎ ሥራቸው ይታወቃሉ ። ደረጄ ገብሬ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ለበርካታ ዓመታት መርተዋል ። እኤአ ከ2007 ጀምሮ የሮታሪ ኢንተርናሽናል ክለብ ዐዲስ አበባ ኢስት አባል፣ የኢትዮጵያ ፊሎሎጂካል ማኅበር አባል እና የማኅበሩ መጽሔት ኤዲቶሪያል ኮሚቴ አባል ኾነው አገልግለዋል። ከዚህም ባሻገር ልዩ ልዩ ሽልማቶች ከተለያዩ አካላት አግኝተዋል ።