ገዛኸኝ መኮንን ደምሴ

ገዛኸኝ መኰነን ደምሴ ጋዜጠኛ ጸሐፊና የፊልም ባለሙያ

ገዛኸኝ ከአባቱ መኰነን ደምሴ እና ከእናቱ ዘውዴ አበበ በሰኔ ወር 1967 ዓ.ም ዐዲስ አበባ ከጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት አካባቢ ተወለደ:። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ዐስረ ሐዋሪያት አንደኛ እና መለስተኛ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ተማረ፡፡ በትምህርት ቤትም የዛሬው ሙያው ጋዜጠኝነትና ጸሐፊነት ተጀመረ፡፡ የሚዲያ ሥራ በራሱ ፈቃድ እና በመምህራኑ እገዛ በመጀመር በሰልፍ ላይ በየጠዋቱ ልዩ ልዩ መረጃዎችን ያቀርብ ነበረ።

በ1984 ዓ.ም ወደመድኃኒዓለም ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተቀላቅሎ 12ኛ ክፍል እስካጠናቀቀበት ግዜ በሥነ-ጽሑፍ ውድድሮችና በሚዲያ ክበቦች በንቃት በመሳተፍ ልዩ ልዩ ሀገር አቀፍና ከተማ አቀፍ የሥነ-ጽሑፍ ውድድሮችን ከማሸነፉም በላይ በወቅቱ በነበሩ መገናኛ ብዙኃንም ላይ ጽሑፎቹን ማበርከት ጀምሮ ነበር።

ለአብነትም ዐዲስ ዘመን ጋዜጣና ኢትዮጵያ ሬዲዮ ይጠቀሳሉ። በሥነ-ጽሑፍ፣ በድራማ፣ በጋዜጠኝነት የተለያዩ ክበባት ውስጥ አባል በመኾንና በመመሥረት በኪነ-ጥበብና በጋዜጠኝነት በመሳተፍ፤ ጋዜጣ በማሳተም ፣ ታዳጊዎችን በማሠልጠን አገልግሏል ።

ለአብነትም በጴጥሮስ ወጳውሎስ የቴአትርና ሙዚቃ ክበብ ፣ በውበት አማተር ጋዜጠኞች ክበብ፣ በራዕይ የወጣት ጋዜጠኞች ክበብ እና በሌሎችም በተሳተፈባቸው ክበባት ጉልህ አሻራውን ትቷል። በዐዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪ በመማር ላይ እያለ በወጣ የሥራ ቅጥር ተወዳድሮ በ1991 ዓ.ም የዐዲስ አበባ ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ተቀጥሯል፡፡ ቢሮው በሚያሳትመው ዐዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይም በዜና ሪፖርተርነት ሠርቷል።

ጥቂት ቆይቶም ወደዓምድ አዘጋጅነት በመሸጋገር በጋዜጣው ላይ እስከቆየበት 1996 ዓ.ም ድረስ የባህል ዓምድ አዘጋጅ ኾኖ አገልግሏል። ከዚህም በተጨማሪ በዚያው ቢሮ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ድራማዎችን በመጻፍና በማዘጋጀት ልምድ አካብቷል። ገዛኸኝ ወደሚወደው የፊልም ዘርፍም የገባው በ1990 ዓ.ም መጀመሪያዎቹ ‹‹መዘዝ›› የተሰኘ ፊልሙን ከጓደኛው ሚሊዮን አየለ ጋር ባቋቋመው መቅደላ የፊልም ፕሮዳክሽን አማካኝነት ፕሮዲዪስ በማድረግ ከቀዳሚውን የቪ ኤች ኤስ ዘመን አክሽን ሰስፔንስ ፊልም አበርክቷል። ፊልሙ በኢምፔሪያል ሆቴል ተመርቆ በሸራተን ዐዲስ ለዕይታ በቅቷል።

ኹለተኛ ፊልሙ ‹‹ጎዳኒሳ›› በሚል ርዕስ በ1990ዎቹ አጋማሽ በዓለም ሲኒማ ተመርቆ ለዕይታ በቅቷል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የዘጋቢ ፊልሞችን በሀገር ቤት ሠርቷል። ከዐዲስ ልሳን ጋዜጣ በ1996 ዓ.ም በፍቃዱ ከለቀቀ በኋላ ባቋቋመው ‹‹ዐዲስ ውበት›› መጽሔት የኅትመት ዓለምን ተቀላቀለ። ይህቺ ልዩ መጽሔት ሦስት ዕትሞች ከታተመች በኋላ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ማግስት መንግስት የነጻውን ፕሬስ ሲዘጋ በዚያው ቀረች። ገዛኸኝ መኮንን ከባለቤቱ ጋዜጠኛና ደራሲ ሶስና አሸናፊ ጋር ባቋቋሙት ‹‹ኩኩ መለኮቴ›› የተሰኘ የቤተሰብና የልጆች ጋዜጣ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋዎች በማሳተም በልጆች ሚዲያ ላይም አሻራውን አሳርፏል።

በትምህርት ዓለም ከቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ በተጨማሪ በዓለምአቀፍ ግንኙነት እና ፖለቲካል ሳይንስ በመዓረግ ዲግሪውን የተቀበለ ሲሆን፤ በሚኖርበት ካናዳም በፊልም፣ በኢሚግሬሽን ሎው እና በኮሚኒኬሽንና ሚዲያ ልዩ ልዩ ፖስት ግራጁዌት ዲፕሎማዎችንና ሰርተፍኬቶችን ተቀብሏል። በሀገር ቤት ሳለም ከጓደኞቹ ጋር አቋቁመውት በነበረው PEN Ethiopia የተሰኘ የዓለምአቀፉ ፔን አካል የኾነ የሥነ-ጽሑፍና የሀሳብ ነፃነት ድርጅት በመመሥረት በቦርድ አባልነት አገልግሏል። ኑሮውን በካናዳ ካደረገም በኋላ ከባለቤቱ ጋር ባቋቋሙት ‹‹ዐዲስ ቅኝት›› በተባለው ሚዲያ ከጋዜጣ ኅትመት በመጀመር በኋላም ወደሬዲዮ በመሻገር አኹን ደግሞ በካናዳ ከሚገኙ ትልልቅ የቴሌቭዥን ኔትዎርኮች ዐንዱ በኾነው ሮጀርስ ኦምኒ ቻናል ላይ ዐዲስ ቅኝት ቴሌቪዥንን ፕሮዲዩስ እያደረጉ ማቅረብ ጀምረዋል። ከባለቤቱ ሶስና አሸናፊ ጋር በልዩ ልዩ መድረኮች እና ኅትመቶች ላይ በጋራ የተለያዩ ታሪኮችን ያሳተሙ ሲኾን በሀገር ቤት ለምሳሌ በፔን ኢትዮጵያ በታተመው ‹‹የነገ ናፍቆት›› የአጫጭር ታሪኮች መድብል ውስጥ ሥራቸው ታትሟል።

ገዛኸኝ፣ በተለያዩ የካናዳና የአውሮፓ የኅትመት ውጤቶች ላይ ጽሑፎቹ ለኅትመት በቅተውለታል። በሀገር ቤትም ዐዲስ አድማስን ጨምሮ በሌሎቸ በርካታ የኅትመት ሚዲያዎች ላይ የትርጉም እና የፈጠራ ሥራዎቹ ታትመዋል። በቅርቡም ለንባብ በበቃውና የተለያዩ ሀገር ደራሲያን በተሳተፉበት የፔን ካናዳ ራይተርስ ኢን ኤክሳይል ኅትመት በኾነው “The Uncaged Voice” መጻሕፍ ላይ ሥራው የታተመ ሲኾን መጻሕፉ በካናዳ በስፋት እየተነበበም ይገኛል። በፊልም ዘርፍ ገዛኸኝ መኰነን በካናዳ ከሦስት በላይ ፊልሞችን ሠርቷል፡፡

“Tizita” ለካናዳ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “CBC” In search of Human Philosophy ” ለቴሌቪዥን ኦንቴሪዮ/TVO/ ይጠቀሳሉ። ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የፊልም ባለሙያ ገዛኸኝ የPEN Canada የቦርድ አባል ከመኾኑም በላይ በዚሁ ሥር WiEx ቼር ማን ኾኖም እያገለገለ ይገኛል። የዐንድ ወንድ ልጅ አባ የኾነው ገዛኸኝ በዐዲስ ቅኝት ሁለገብ ሚዲያ ሥራዎቹ በካናዳ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ተቀብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *