ዶ/ር ጌትነት ንጉሴ
የ22 ሺህ ዓይናማዎች አባት›
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በልዩ ልዩ ሙያ ሀገራቸውን እያገለገሉ ያሉ ብርቱ ሰዎች በዚህ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ የህይወት ታሪኩን የምናቀርብላችሁ ሰው በህክምናው ዘርፍ ላለፉት 30 አመታት ያገለገለው ዶክተር ጌትነት ንጉሴ የሚሰራው ተግባር ለሌሎች እንደትልቅ አርአያ የሚቆጠር ነውና እዝራ እጅጉ ግለ-ታሪኩን እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡ ‹የእኔ ደስታ የወገኖቼ ብርሃን ተመልሶ ማየት ነው!› የሚለው ዶ/ር ጌትነት በአሁኑ ወቅት ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው፡፡ የራሱን ቦናፋይድ የተባለ የህክምና መሳሪያዎች አስመጪ ድርጅትም ከፍቶ ከ100 በላይ ለሆኑ ወገኖቹ የሥራ ዕድል ከፍቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንጀምር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምስት ገበያ ህዝብ አስከትሎ እያስተማረ ወደ እየሩሳሌም ሲያመራ ከውልደቱ ጀምሮ አይነ ስውር የነበረ አንድ አዛውንት የእኔ ብጤ ከመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር፤ ክርስቶስ በእዚያ በኩል ሲያልፍ በሚከተለው ህዝብ ብዛት ያለ ወትሮው ግርግር የተሰማው የእኔ ብጤ እንደምንም ብሎ በአጠገቡ የሚያልፍን አንድ ሰው ልብሱን ጨምድዶ ‹ምንድነው እዚህ አካባቢ እየሆነ ያለው ?› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ክርስቶስን እየተከተለ ያለው ሰው ልብሱን ከሽማግሌው እየመነጨቀ ‹የናዝሬቱ እየሱስ በእዚሀ በኩል እያለፈ ነው!› ይለዋል፤ ይህን ጊዜ በክርስቶስ ላይ ፅኑእ እምነት ያለው የእኔ ብጤ እየጮኸ ‹ እየሱስ! እየሱስ! የእግዚአብሐር ልጅ! አድነኝ!› እያለ ክርስቶስ ወደ ሄደበት አቅጣጫ ቦታ ሲሄድ ክርስቶስ ድምፁን ሰምቶ ቆም ይልና ‹አምጡት ወዲህ!› ይላል፤ ከደቀመዛሙርቱ መሀከል ሁለቱ የእኔ ብጤውን አይነ ስውር ግራና ቀኝ ደግፈው ይዘው ክርስቶስ ፊት ያቀርቡታል፤
‹ምን እንዳደርግልህ ትሻለህ?› አለው ክርስቶስ፤
‹ማየት እፈልጋለሁ!› አለው ፤ክርስቶስም ሁለት እጆቹን አይኑ ላይ አድርጎ
‹እይ!› አለው፡፡ ሽማግሌው አይኑ በራ፤ በአካባቢው ያሉ ሰዎችንና ጀምበሯን የተመለከተው ሽማግሌ መፈንጠዝ ጀመረ፤
ይህ የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ በእግዚብሔር ለሚያምኑና በእውቀት ላይ ተመስርተው ወገኖቻቸውን ለሚያገለግሉ ሁሉ የሚሰራ ይመስላል፤ ከውልደታቸው ጀምሮና ከጊዜ በኋላ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ከ22 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን የዓይን ሞራ ግርዶሽ በቀዶ ጥገና በማከም የአይን ብርሃናቸውን የመለሰው የአይን ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶ/ር ጌትነት ንጉሴ ከእንደነዚህ አይነት ባለሙያዎች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ ዶ/ር ጌትነት ንጉሴ ባለፉት 30 ዓመታት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በመዘዋወር የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ወገኖቹን ብርሃን በመመለስ ሙያዊ ግዴታውን የተወጣ ሰው ነው፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ከሃብታም፣ እስከ ድሃ፤ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከአርሶ አደር እስከ ነጋዴ፤ ከሙስሊም እስከ ክርስቲያን ወዘተ ዶ/ር ጌትነት ሁሉንም አይነት ወገኖቹን በነፃ በማገልገል የዓይን ብርሃናቸውን መልሷል፡፡
በአይን ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ቢያንስ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን አይነ ስውራን ሰዎች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 50 ከመቶው ሊታከም በሚችለው በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ናቸው፡፡ በዶ/ር ጌትነትና ሌሎች በጎ አድራጊ ተቋማት በየጊዜው በሚደረገው በየጊዜው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ቁጥሩን ለመቀነስ ጥረት ቢደረግም ቁጥሩ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም የሚሄደው፡፡
ምክንያቱም ይላል ዶ/ር ጌትነት ከዚህ በፊት በህክምና እጦት በአይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር እንዳለ ሆኖ ከስር ከስር ደግሞ በየዓመቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን የሚያጡበት ሀገር ነው፤ እድሜ ሲጨምር አይን በሞራ የመጋረድ እድሉ ሰፊ ስለሆነ ቁጥሩ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይሄድም ይላሉ፡፡
በመሆኑም ይላሉ ዶ/ር ጌትነት በግላኮማ፤ በስኳር፤ በደም ግፊትና በልዩ ልዩ በሽታዎች ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ያም ሆኖ በህክምና እርዳታ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህመም ተጠቂዎችን ዶ/ር ጌትነትና የስራ ባልደረቦቻቸው ኑሮአቸውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አድርገው ብርሃን ላጡ ብርሃን እየሆኑ ነው፡፡ ከ100 በሚሊዮን በላይ ህዝብ ባለባት በሀገራችን የዓይን ሐኪሞች ቁጥር ከ120 በላይ አይደለም፤ያም ሆኖ ግን በግለሰብ ደረጃ ለ22 ሺህ ሰዎችን ብርሃናቸውን መመለስ የውቅያኖስን ውሃ በማንኪያ ቢመስልም ጉዳዩ የዓይን ጉዳይ መሆኑ ሲታሰብ የዶ/ር ጌትነት ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ አካባቢ የተወለዱት የ53 ዓመቱ ሐኪም ዶ/ር ጌትነት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በፈለገ ህይወት፤በየካቲት 23 እና ከዚያም በኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጀ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት፡፡ ከትምህርት ቤቱ ጎበዝ ተማሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት ዶ/ር ጌትነት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አምጥተው የህከምና ትምህርት ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመግባት ከ7 ዓመታት በኋላ በጠቅላላ ሐኪምነት ተመርቀዋል፡፡ የመጀመሪያ የስራ ዓለምን የተቀላቀሉት በመርሐ ቤቴ አለም ከተማ ነበር፤ አዲስ አበባ ለዚያውም መርካቶ አካባቢ ተወልዶ ላደገና ከከተማ ወጥቶ ለማያውቅ ሰው አለም ከተማ ከባድ ፈተናው ነች፤ ለዶ/ር ጌትነትም ገጠራማዋና ተራራማዋ አለም ከተማ ፈትናዋለች፤ መብራትና ውሃ እንደልብ ባልነበረባት አለም ከተማ በየጊዜው የሚመደቡ ሀኪሞች አይበረክቱባትም ነበር፤ ዶ/ር ጌትነትም ተመድቦ እንደሄደ የአካባቢው ሽማግሌዎች እንደ ሌሎች ሀኪሞች ተማሮ ለቆ እንዳይሄድ ፕሮግራም አዘጋጅትው ነበር የተቀበሉት፤ እየዋለ ሲያድር የእዚያ ገጠር ህዝብ ችግርን በሙያው መጋፈጥ ጀመረ፤ለራሱም ቃል ገባ፤ ለ3 ዓመት በአለም ከተማ ሲቆይ የአካባቢውን ህብረተሰብ ባህል አጠና፤ እንደባህል ከተያዙ ጉዳዮች መካከል ልጆችን ክትባት ማስከተብ አልተለመደም፤ ዶ/ር ጌትነት ቦታው ላይ ሲሄድ በአካባቢው ከሚወለዱ ህጻናት 36 ከመቶ ብቻ ነበሩ የሚከተቡት፤ ይህንኑ ችግር በመመልከት ‹‹ሜንሽን ፎር ሜንሽን›› ከተባለው የጀርመን ድርጅት ጋር በመተባባር ፕሮጀክት በመቅረፅ የአካባቢውን የክትባት መጠን ‹ከ36 ከመቶ ወደ አንድ መቶ ከመቶ አደርሰዋለሁ› ብሎ ለክልሉ ጤና ቢሮ እቅድ አስገባ ፤ የክልሉ ሰዎች ‹ሊሆን የማይችል እቅድ!!› በሚል ስሜት ቢቀበሉትም እቅዱ ይሳካል የሚል እምነት አልነበራቸውም፤ ግን የጠየቀውን በጀት ፈቀዱለት፤ በዓመቱ ግን የአካባቢው ህብረተሰብ የህጻናት ክትባት ምጣኔ 106 በመቶ መሆኑ በጥናት ተረጋገጠ፤ በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳር በነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ በተገኙበት ዶ/ር ጌትነት እውቅና አገኘ፤
ከመርሀ ቤቴ ወደ ደብረብርሃን ተዛውሮ ለ3 ዓመታት ያህል የሰራው ዶ/ር ጌትነት ወደ አዲስ አበባ ተመልሶም ተወልዶ ያደገበት በአዲስ ከተማ አካባቢ የግሉን ክሊኒክ ከፈተ፤ ክሊኒኩ ለበርካታ ሰዎች አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም አትራፊ ሆኖ ሊቀጥል አልቻለም፤ ክሊኒኩ አትራፊ ሊሆን ያልቻለው የሚያስከፍለው ክፍያ እንደ መንግስት ሆስፒታል በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ቁጥራቸው ቀላል ለማይባሉ ሰዎች በየዕለቱ በነፃ ህክምና በመስጠቱ ነበር፤ ‹ተወልጄ ባደኩበት ሰፈር ያሉ ሰዎችን እንዴት ብዬ ነው የማስከፍላቸው› ይላል ዶ/ር ጌትነት ክሊኒኩ ስለተዘጋበት ምክንያት ሲናገር፡፡ ክሊኒኩ ሲዘጋ ዶ/ር ጌትነት ከጠቅላላ ሀኪምነት የዓይን ህክምና በመማር የዓይን ስፔሻሊስት ሀኪም ሆነ፤ የጠፋውን የወገኖቹን ዓይን የማብራት ተግባሩን ‹ ሀ ›ብሎ የጀመረው ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው፡፡በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ወገኖቹን ለመርዳትም ከኦርቢት ኢንተርናሽናል ጋር ይገናኛል፤ ኦርቢስ በገጠር አቅም ለሌላቸው ሰዎች በነፃ የዓይን ህክምና ይሰጥ ስለነበር ለዶ/ር ጌትነት ዓይን የማብራት ፍላጎቱን አሳካለት፡፡ የመጀመሪያ ጉዞው ወደ ወልቂጤ ነበር፤ የ300 ሰዎች ዓይን ቀዶ ጥገና በማድረግ ብርሃናቸው መለሰ፤ እንደገና በወሩ እዚያው ወልቂጤ ተጨማሪ 300 ሰዎች በድምሩ ለ600 ሰዎች ህክምና አደረገ፤ ለዓመታት ዓይነ- ስውር ሆነው በመንገድ መሪና በረዳት ተቸግረው የነበሩ ሰዎች ዓይናቸውን ታክመው ዓይናቸው ሲበራ ፊታቸው ላይ የሚያየው ደስታ ያረካው ጀመር፤ ዓይናቸው የበራላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸውም ጭምር መርቀውት መርቀውት አልረካ ሲሉ ‹ሆድ ይመርቅ !› ብለውት ነበር የሚሄዱት፡፡
በወልቂጤ የተጀመረው የአይን ብርሃን የማብራት ህክምና ላለፉት 30 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በመዟዟር ለተቸገሩና ብርሃን ላጡ ወገኖች ብርሃን መሆን ችሏል፤ጉራጌ ዞን ቸሃ ወደ አላባ፤ወላይታ፤ከምባታ፤ሶማሌ ደገሃቡር፤ ጂግጂጋ፤ቀብሪዳሃር፤ ሐረር፤ደሴ፤ደብረማርቆስ፤ወልዲያ፤ጎዴ፤ አሰበ- ተፈሪ፤ አሳይታ፤ አሰላ፤ ፍኖተ- ሰላም፤ ደብረ ታቦር፤ ወዘተ የአይን ብርሃን የማብራት ሥራውን ኑሮውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አድርጎ ለብዙዎች ተስፋ ሰጥቷል፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከ600 እስከ 1200 ድረስ ሰዎች ህክምናውን ያገኙ ነበር፤ ዶ/ር ጌትነት በመጀመሪዎቹ ሁለት ዓመታት በገጠር እየዞረ ህክምናውን ሲሰጥ ቆይቶ ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ገባ፤ የዓይን ህክምና ክፍል ሀላፊ ሆኖ በአስተዳደርም በህክምና ስራ ለ7 ዓመታት ያህል ቆየ፤ በወቅቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ለዓይን ህክምና ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የዓይን ብርሃን ያጡ ሰዎች በወቅቱ የሚሰጣቸው ቀጠሮ 2 ወር ከ15 ቀን ነበር፤ ዶ/ር ጌትነት ክፍሉን በበላይነት መምራት ከጀመረ በኋላ ግን ከሀኪሞች ጋር በመነጋገርና ፕሮግራም በማውጣት ዛሬ የመጣ ሰው ነገ ቀጥሮ ተሰጥቶት ታክሞ አይኑ በርቶ ወደቤተሰቦቹ እንዲሄድ ማስደረግ ችሏል፤ የተበላሹ የሆስፒታሉ የህክምና መስጫ መሳሪያዎችንም ከኪሱ አውጥቶ በማሰራት የህክምና ሂደቱ እንዳይስተጓጎል ብርቱ ጥረት አድርጓል፤ ሐኪሞች ከመደበኛ የስራ ሰኣታቸው በኃላ በዚያው በሆስፒታሉ ውስጥ በተወሰነ የክፍያ ለውጥ ህክምና እንዲሰጡ የተደረገውም ዶ/ር ጌትነት ምንሊክ ሆስፒታልን በሚመራበት ወቅት ነበር፡፡ ሰዎችን ከማከሙ በተጨማሪ የህክምና ቡድን አደራጅቶ ከላየንስ ክለብ ጋር በመተባበር ወደ ገጠር እያቀና የብዙዎችን ብርሃን መልሷል፡፡
ዶ/ር ጌትነት የህክምና ቡድኑን ይዞ የዓይን ሞራ ህክምና ወደሚደረግባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፕሮግራም መሰረት ሲሆን በመንግስት ሆስፒታል እዚያው አካባቢ ባሉሐኪሞች በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ተመዝግበው እንዲዘጋጁ ያደርጋል፤ ህክምናውም የሚሰጠው በመንግስት ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከህክምናው በኋላ ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ህመምተኞች የሆስፒታሉ ሀኪሞች እንዲከታተሏቸው እድል ይሰጣል፤ በመሆኑም ቡድኑ በቦታው ሲደርስ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ በቀጥታ ወደ ቀዶ ጥገናው ነው የሚገባው፤ በቀን ከ60 እስከ 80 ሰዎችን በአንድ የጉዞ ፕሮግራም እስከ 800 ሰዎችን የሚያክመው ዶ/ር ጌትነት ቀዶ ጥገና የተደረገለት ሰው ዛሬ ተሰርቶለት ነገ አይኑ ስለሚበራለት በሰው ድጋፍ የመጡ ሰዎች እየጨፈሩ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ መመልከት ስራውን እንድወደው አድርጐኛል ይላል፡፡ ያም ሆኖ የመንግስት ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጠው ለተላላፊ በሽታዎችና ገዳይ ለሚባሉ በሽታዎች በመሆኑ ለእንደዚህ ዓይነት የዓይን ህክምና ጉዳይ የሚይዘው በጀት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ህብረተሰቡም የዓይን ሞራ ግርዶሽ በህክምና በቀዶ ጥገና የሚስተካከል መሆኑን ስለማያውቅ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ዓይናቸው ጠፍቶ ከምርታማነት ውጪ ሆነዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታትም ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ከለጋሾች ጋር በመተባባር መንግስት ብሄራዊ የዓይነ-ስውርነት ማስወገጃ ኮሚቴ በመመስረት ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ ተሞክሯል፤ የኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ያገለገለው ዶ/ር ጌትነት በዚህ በኩል ህክምና የማግኘት እድሉ ያልነበራቸው የገጠር ነዋሪዎች ህክምናውን በነፃ እንዲያገኙና ብርሃናቸው እንዲመለስ አድርጓል፡፡
ምስክርነቶች
ዶ/ር ጌትነት የዓይን ብርሃን ያጡ ሰዎች ብርሃናቸው ተመልሶ ማየት ሲችሉ የሚያሳዩት ድርጊት እየማረከው ሲመጣ ቀዶ ጥገና የሚደረግላቸውን ሰዎች ከህክምናው በፊትና በኋላ ቪዲዮ ማስቀረፅ ጀመረ፤በዚህ መልክ ከሰራቸው ከ22 ሺህ በላይ ሰዎች መሀከል ከ1500 በላይ የሚሆኑ ባለ ታሪኮችን በቪዲዮ አስቀርፆ ይዟል፡፡ብዙዎቹ በሰዎች ድጋፍ ሲመጡ የሚታዩ ሰዎች ቃለ- ምልልስ ሲደረግላቸው ዓይናቸው የሚበራ አይመስላቸውም፤ ህክምናው ተሰጥቷቸው ዓይናቸው ሲፈታ ደግሞ የሚታየው ሁኔታ ብዙ ጊዜ የሚያሳዝንና የሚያስለቅስ ነው፤ ዶ/ር ጌትነት ህክምናውን ሰረትቶ ዓይናቸውን ሲፈታቸው በአንዳንድ ሰዎች ድርጊት አብሮ ሲያለቅስ በቪዲዮ ላይ ይታያል፤ የአንዳንዶቹን ምስክርነት ማቅረብ ለእማኝነት ያግዛልና እነሆ!
አቶ አብዱ ሱማሌ ክልል ጎዴ ነዋሪ ናቸው፤ለ13 ዓመት አይነ ስውር ነበሩ፤ ከገጠር ወደ ከተማ በስንት መከራ እንዲመጡ ተደረገ፤ተሰራላቸውና ዓይናቸው በርቶ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፤ በማግስቱ አቶ አብዱ ተመልሰው መጡና ዶ/ር ጌትነትን ማግኘት እፈልጋለሁ አሉ፤
‹ምንድነው?› ሲላቸው፤
‹ልጆቼ አታለውኛል› አሉ፤
‹በምን ምክንያት?› ሲላቸው፤
ሰውየው በአካባቢው የታወቁ ሃብታም ናቸው፤ እናም ሶስተኛ ሚስት ማግባት እፈልጋለሁ ሲሉ ልጆቻቸው አንዲት ሴት አምጥተው ያጋቧቸዋል፤ ሁለት ዓመት አብረው ሲኖሩ ሚስት ልትወልድላቸው አልቻለችም፤ ‹በአላህ ስራ አልገባም› ብለው በተቀመጡበት ሰዓት ዓይናቸውን ታክመው ማየት ሲችሉ ያገቧት ሴት ድምፃ ነው እንጂ የልጅ ዕድሜዋ የገፋ መሆኑን ይመለከታሉ፤ በመሆኑንም ይላሉ አቶ አብዱ ‹በመሆኑም ይህቺን ሴት እውነታውን ደብቀው ልጆቼ ያጋቡኝ ወራሽ እንዳይመጣ ነው፤ ስለዚህ አሁን ካለኝ 60 ግመሎች ውስጥ ዓይኔን ስላበራህልኝ 30 ግመሎችን ልሰጥህ ነው መጣሁት› ይሉታል፤ ዶ/ር ጌትነት ግመሎቹን ባይቀበልም ታሪኩን መዝግቦ አስቀምጧል፤ የስምንት ዓመቷ ቀብሪዳሃር ከተማ ነዋሪ የሆነችው ታዳጊ ከውልደቷ ጀምሮ ዓይኗ አያይም ነበር፤ ዶ/ር ጌትነት ጋር በእናቷ አማካይነት መጥታ ቀዶ ጥገና ከተሰራላት በኋላ ዓይኗ ሲገለፅ በአካባቢያዋ ከነበሩ ሰዎች መሀከል እናቷ ነበረችበት፡፡ ነገር ግን እናቷን የምታውቃት በድምጿ ብቻ በመሆኑ እናቷ ምንም ነገር እንዳትናገር ተነግሯት ዝም አለች፡፡
ልጅቷ ማየት ስትጀምር እናቷን መለየት አልቻለችምና ግራ ተጋብታ እየጮኸች ወደ ውጭ ትሮጣለች፤ ይህን ጊዜ እናቷ ስሟን እየጠራች ስትከተላት ቆመች፤ለመጀመሪያ ጊዜ እናቷን አየቻትና ተቃቅፈው ሲላቀሱ ይታያል፤ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ56 ዓመቱ አርሶ አደር ከጊዜ በኋላ ዓይነስርውር ሆኖ ነበር፤ እናም የእነ ዶ/ር ጌትነት የህክምና ቡድን ሰቆጣ ሲመጣ ህክምናውን ለማግኘት ሆስፒታል መጣ፤ በየዓይኑ ምክንያት ስራ ፈትቶ ወደ ደጅ ለመውጣት እንኳ የሰዎችን እርዳታ ለመጠየቅ የተገደደው አርሶ አደር ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ዓይኑ ሲበራ ደስታው ወሰን አጣ፤ ‹አሁን ምን ታደርጋለህ;› ሲባል በማግስቱ ወደ እርሻ ስራ ለመሰማራት እንደሚፈልግ ነው የተናገረው፤
ሽልማቶች
ድምፁን አጥፍቶ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየዞረ ብርሃን ላጡ ወገኖቹ ብርሃን ሲሰጥ የኖረው ዶ/ር ጌትነት ልታይ ልታይ የማይል ብርሃናቸው በተመለሰላቸው ሰዎች ደስታ የሚደሰት በጎ አድራጊ ነው፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት ላከናወናቸው ተግባራትም ከ53 በላይ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በርካታ ምስክር ወረቀቶችና ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክተውለታል፤