ዶክተር ጳውሎስ ቀነዓ(1924-2018)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። እስካሁን ከ500 በላይ ሰዎችን የሰነድን ሲሆን ሁሉም ጉግል ላይ በስማቸው ሲፈለጉ ይገኛሉ። እስካሁን የባለታሪኮች የሙያ ታሪክ የያዙ ሁለት ኢንሳይክሎፒዲያ ያሳተምን ሲሆን የ21 ሰዎችንም ታሪክ ለየብቻ በሰዎቹ ጠያቂነት ሠርተን። ለታሪክ እንዲቀመጥ አድርገናል። በዚህ ፅሑፍ ታሪካቸው የተሰነደው ሰው ዶክተር ጳውሎስ ቀነዓ ሲባሉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአይን ሀኪም ሲሆኑ ታሪካቸውንም ቤርሳቤህ ጌቴና እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው አጠናክረውታል።

ትውልድ እና ልጅነት ፣ ትምህርት

ዶ/ር ጳውሎስ ቀነኣ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 24 ቀን 1924 ዓ.ም በአርሲ፣ ከአባታቸው ከአቶ ቀነኣ በጂ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘነበወርቅ ተፈራ ተወለዱ።

የሁለት አመት እድሜ እንደሞላቸውም ቤተሰባቸው ወደ አዲስ አበባ በመዛወሩ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜያቸውን ጉለሌ በሚባለው አካባቢ አሳለፉ። በመጀመሪያ በመድኃኔዓለም መደበኛ ትምህርት ቤት፣ በመቀጠልም በዊንጌት ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፣ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ሊባኖስ በመጓዝ በቤሩት አሜሪካዊ ዩኒቨርሲቲ (American University of Beirut) ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።ዶ/ር ጳውሎስ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አገራቸው በመመለስ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዓይን ሐኪም (ophthalmologist) ሆኑ።

አገር ወዳዱ ሰው

ሕይወታቸውን ሙሉ አገራቸውን ለማገልገልና ሌሎችን ለመንከባከብ የሰጡ ሲሆን፣ እስከ 2015 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ድረስ በሕክምናው ዘርፍ በንቃት አገልግለዋል። በሙያ ዘመናቸው የመጨረሻ ዓመታት እንኳ በላንድማርክ ሆስፒታል በሳምንት ስድስት ቀን ይሠሩ የነበረ ሲሆን፣ በየቀኑ ወደ ሥራ በእግራቸው ይመላለሱ ነበር፤ ይህም የሕይወታቸው መገለጫ የነበሩትን ሥነ-ሥርዓት፣ ቀላልነት እና ታማኝነት የሚያሳይ ነበር።ዶ/ር ጳውሎስ ትሑት፣ ደግ እና ጥልቅ ርኅራኄ ያላቸው ሰው የነበሩ ሲሆን፣ የኖሩትም ከእውቅና ይልቅ በአገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወትን ነበር። ስኬቶቻቸው እጅግ አስደናቂ ቢሆኑም፣ ሁሉንም ነገር በእርጋታና በትሕትና በማከናወን ይታወቁ ነበር። ለአሥርት ዓመታት ያህል እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በመጠቀም ብርሃን ለመመለስ፣ ሕመምተኞቻቸውን ለመንከባከብ እና በኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና እድገት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።


የእሳቸውውርስ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስጀመሩት የሕክምና ሙያ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በለጋስነታቸው፣ በትጋታቸው እንዲሁም ለአገራቸውና ለሕዝባቸው በነበራቸው የማይናወጥ ቁርጠኝነት በነኩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥም ይገኛል።

ያኖሩት አሻራ

ዶክተር ጳውሎስ ​በ1956 ዓ.ም (1964 እ.ኤ.አ) ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ «ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ አንድ የዓይን ሀኪም» የሚል ከባድ እውነታ በሀገሪቱ ሰፍኖ ነበር ማለት ይቻላል። ዶክተር ጳውሎስ ግን በውጭ ሀገር የሚጠብቃቸውን ምቹ ህይወት ወደ ጎን በማድረግ «ሀገሬ የኔ እውቀት ያስፈልጋታል» በማለት በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል አገልግሎት ጀመሩ። ከዚያ በኋላ ምኒሊክ ሆስፒታልን ጨምሮ ​ብዙ ተቋማትን ማገልገል ቀጠሉ ፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በጥቁር አንበሳ፣ በግል ክሊኒካቸው እና በኢሲኤ (ECA) እየተመላለሱ በከፍተኛ ትጋት ሙያዊ አደራቸውን ሲወጡ ነበር።

​የሰው ኃይል እጥረቱን ለመቀየር ብቸኛው መንገድ የሀገር ውስጥ ባለሙያ ማፈራት መሆኑን ቀድመው የተገነዘቡት ዶክተር ጳውሎስ፣ የሚከተሉትን ታሪካዊ ስራዎች አከናውነዋል።
​የዓይን ሕክምና ክፍል በመመስረት ረገድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስር የመጀመሪያውን የዓይን ሕክምና ክፍል ብቻቸውን የመሰረቱ ሲሆን
​የድህረ-ምረቃ ስልጠና (Residency) በ1970ዎቹ ማጠቃለያ ስልጠናውን አስጀምረዋል፣ የሰልጣኞቻቸው የተግባር ልምድ እንዳይጎድል በማሰብ ፕሮግራሙን ወደ 4 ዓመትም አራዝመዋል።

​በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦፕታልሞሎጂ ሶሳይቲን የመሰረቱ ሲሆን፣ ከ1963 እስከ 1968 ዓ.ም. (1971-1976 እ.ኤ.አ) የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ሆነው መርተዋል።

ያፈሯቸው ተማሪዎች

​እርሳቸው ያፈሯቸው ሊባሉ የሚችሉ እንደ ፕሮፌሰር አበበ፣ ዶክተር መነን፣ ዶክተር አብይ፣ ዶክተር ይልቃል፣ ዶክተር ወንዱ አለማየሁ፣ ዶክተር ትልቅሰው፣ ዶክተር ደረጀ፣ ዶክተር ሳዲቅ እና ዶክተር መሰረት ያሉ በርካታ ምሩቃን በሀገሪቱ የሕክምና ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት የቻሉ ናቸው። በአንድ ሰው ህልም የተጀመረው የአይን ሕክምና ክፍል ዛሬ ከ118 በላይ የዓይን ሕክምና ስፔሻሊስቶችን ማፍራት የተቻለበት መሆኑ ትልቁ ስኬት ነው።

​ ዶክተር ወንዱ አለማየሁ የዶክተር ጳውሎስ ቀንኣ የቀድሞ ተማሪ ሲሆኑ ዶክተር ጳውሎስን የኢትዮጵያ የአይን ህክምና አባት ሲሉ ይገልጿቸዋል።ዶክተር ወንዱ እንደሚመሰክሩት ​«ዶክተር ጳውሎስ ለሰው ልጅ የዓይን ጤና ያለው ክብርና ተቆርቋሪነት ከወለደው ልጅ በላይ ነው ይህም ለሙያቸው የሰጡትን አክብሮት የሚያሳይ ነው ።» ብለዋል።ዶክተር ወንዱ።

​ዶክተር ጳውሎስ ቀንኣ ጋወናቸውን አውልቀው የተቀመጡት በዛሉ አረጋዊነት ሳይሆን፣ እስከ 92 ዓመታቸው ድረስ ሰዎችን በማከም፣በዚህ ቅዱስ ተግባር ላይ ጸንተው በመቆየት ነበር። በስተመጨረሻም በጡረታ ሲሰናበቱ፣ የሕክምና መሳሪያዎቻቸውን በክብር አሽገው በታላቅ ምርቃት ነበር የሽኝት ፕሮግራም የተደረገላቸው።

​ስለ እርሳቸው ድንቅ ህይወት እና ተጋፍጧቸው ስለነበሩ ፈተናዎች ብሎም ስላከናወኗቸው ተግባራት የሚያወሳ “Dr. Pawlos Quanna: The Story of Ethiopia’s First Ophthalmologist” የተሰኘ መጽሐፍ ተጽፎ ለንባብ በቅቶላቸዋል።

ልጃቸው ብሌን ጳውሎስ አባቴ የብዙዎችን ብርሀን የመለሰ፣ ለሰው ልጅ የሚቆረቆር ፣ በልዩ ትጋቱ የሚደነቅ በመሆኑ በእርሱ ምንጊዜም እኮራለሁ ስትል ከልብ የመነጨ ምስክርነቷን ሰጥታለች።

​ዶክተር ጳውሎስ ጊዜያቸው በሥራ የተጠመደ ትጉህ ሰው ነበሩ። የቀን ውሏቸውን ብንመለከት ከጠዋቱ 11 ሰዓት በውሃ ዋና ቀናቸውን ይጀምራሉ፤ ከዚያም የህክምና አገልግሎታቸውን በኤርላይንስ፣ በራሳቸው ክሊኒክ፣ በጥቁር አንበሳ፣ በምኒሊክ እና በኢሲኤ (ECA) መካከል እየተመላለሱ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ያከናውኑ ነበር።

ሐዋኒ ንጉሴ የዶክተር ጳውሎስ የእህት ልጅ ስትሆን ​ዶክተር ጳውሎስ ለቤተሰባችን የመጀመርያው ትልቅ አባወራ ወንድና ለሁላችንም የምንወደው አጎታችን ነበር። የዓይን ሀኪም ብቻ ሳይሆን፣ ህይወትን በምን አይነት መልኩ መምራት እንደምንችል ለብዙዎቻችን ያስተማረን አርአያችን ነው።” ስትል ለአጎቷ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ገልጻለች።

​ዶክተር ጳውሎስ ከልጆች ጋር ልዩ የሆነ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው። በቤሩት አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ (AUB) በነበሩበት ወቅት፣ ህክምና ከተማሩ በኋላ ተጨማሪ አንድ ዓመት ህጻናት ሕክምናን (Pediatrics) አጥንተው እዚያው ሰርተው ነበር። ከልጆች ጋር የነበራቸው ልዩ የፍቅር ትስስር ምናልባትም ከዚህ ልምዳቸው የመጣ ሳይሆን አይቀርም።


​ዶክተር ጳውሎስ ለስራ የሚሰጡት አክብሮትና የሚያሳዩት ትጋት እንዲሁም «ጽናት» (Perseverance) የሚለው መርሀቸው በጣም የሚደነቅ ነበር። ሀገራቸውን ለማገልገል ያሳዩት ቁርጠኝነት በሥራ ብዛት እንኳን ያልዛለ እንደነበር ማስተዋል ይቻላል። በአንድ ወቅት በአገሪቱ ብቸኛ የዓይን ሀኪም በነበሩበት ጊዜ፣ ጠዋት በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልና በጤና ጥበቃ፣ ከሰዓት በኋላ በራሳቸው ክሊኒክ፣ ማታ ደግሞ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በማስተማርና በማከም ያለ እረፍት ይሰሩ ነበር።

ብዙዎች ከዶክተር ጳውሎስ የሚወዱላቸው ነገር ሰዎችን በትልቅና ትንሽነት የማይለያዩ መሆናቸው ነው። የባለስልጣን ልጅ፣ ባለስልጣን፣ የሀገር መሪም ሆነ ተራ ሰው ምንም ልዩነት ሳያደርጉ ለህክምና የሚሰለፈውን «ተራችሁን ጠብቁ!!» በማለት እኩል ያስተናግዱ ነበር። የሰውን ዘር፣ ዜግነት ወይም ደረጃ አይተው አድሎ ማድረግን በፍጹም ይጠሉ ነበር።

የዶክተር ጳውሎስ እውነተኛነታቸው እና መርህ መከተላቸው በቤተሰባቸው ዘንድ ትልቅ አክብሮት እንዲጎናፀፉ ያደረጋቸው ልዩ ባህሪያቸው ነበር።

​ዶክተር ጳውሎስ ፣ በየቦታው ተልከው የሰሯቸው ተግባራት (በኮሌራ ምክንያት በጉራጌ፣ በሀረር፣ በትግራይ፣ በጎንደርና በተለያዩ ክፍለ ሀገራት በበቅሎና ባህያ ሳይቀር እየተጓዙ የሰጡት አገልግሎት የማይረሳ ነው። ለሀገራቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ከሀገር ውጭ ሲሄዱ እንኳ ሁልጊዜ የአገራቸውን ባህላዊ ነጭ ልብስ ለብሰው ነበር ፕሮፌሽናል መድረኮች ላይ የሚቀርቡት። ይህንንም የሚያደርጉት የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ከፍ ያደርጋል ብለው እምነት በማሳደራቸው ነው።

ዶክተር ወንዱ አለማየሁ እንደመሰከሩት ​ገና በወጣትነት እድሜዬ የዶክተር ጳውሎስን ትጋት፣ ጥረት፣ ጥልቅ እውቀትና ለዓይን ሕክምና የሚሰጡትን ታላቅ ክብር ስመለከት፣እኔም በዚያ መሠረት የህይወቴን አቅጣጫ መራሁ በዚያ አርአያነት ተመስርቼም በ1973 ዓ.ም. የዓይን ሕክምና ስፔሻላይዜሽን ስልጠናዬን ተቀላቀልኩ፤ ከትምህርት በኋላም እስከ 1991 ዓ.ም. ድረስ ለ15 ዓመታት ከታላቁ መምህሬ ጎን በመሆን ሀገሬን አገለገልኩ።” በማለት እጅግ ስለሚያከብሯቸው ሰው ወዳጃዊ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

​ዶክተር ጳውሎስ ​ጠዋት ማህደራቸውን ከፍተው የቀዶ ጥገና እቃዎችን እራሳቸው በማስተካከል ይጀምራሉ ፤ ከቀዶ ጥገና በኋላ ወጥተው ታካሚዎችን ያስተናግዳሉ ፣ ተማሪዎችን ያስተምራሉ ፣ ሳይንሳዊ ምርምሮችንም ያካሂዳሉ። «ይህ የኔ ስራ አይደለም» ብለው ስራ የሚመርጡ አይነት ሰውም አይደሉም።

​ከሊባኖስ ቤሩት አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሲመለሱ በሀገሪቱ የነበሩት የዓይን ሀኪሞች አልነበሩም። ዶክተር ጳውሎስ ግን ብቸኛ የመሆንን ክብር አልፈለጉም፤ ይልቁንም በዳግማዊ ምኒልክና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ስልጠናዎችን በማስፋፋት፣ የድህረ-ምረቃ ስልጠና በሀገር ውስጥ እንዲጀመር አደረጉ።


​ ዶክተር ጳውሎስ በህክምና ታሪካችን ውስጥ አባት ናቸው! አካላቸው ቢለይም፣ እሳቸው በዘሩት ጽኑ ዘርና ባፈሩት ብቁ ትውልድ አማካኝነት ዛሬም ቢሆን በየሆስፒታሉ ብርሃን ለሚያጡ ዜጎች በሚደረገው ተጋድሎ ውስጥ የዶክተር ጳውሎስ ቀንኣ አበርክቶ አሁንም ህያው ሆኖ ይኖራል።

ዶክተር ፈቀደ መንግስቱ ስለ ሙያ ባልደረባቸው እና መምህራቸው ሲናገሩ

​”.. ስለ እሳቸው ትልቅ ስብዕና፣ ለሀገር ስላበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ እና በህዝብ ዘንድ ስላላቸው ፍቅርና አክብሮት ለመናገር አሁንም ቢሆን በቂ ጊዜ ወስዶ፣ ሀሳብን አዘጋጅቶና ተዘጋጅቶ መናገርን ይጠይቃል። ምክንያቱም እንደ እሳቸው ያለ ታላቅና እድሜ ልኩን ሀገርን ያገለገለ ሰው ታሪክ በጥንቃቄና በታላቅ ክብር ሊዘከር የሚገባው በመሆኑ ነው።» በማለት ሀሣባቸውን ሰጥተዋል።

ዶክተር አበበ ሀረገወይን

“..ዶክተር ጳውሎስ በኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመን የመጀመሪያውና ከ50 አመት በላይ በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታልና በግል ክሊኒኩ ህዝባችንን ባልተቆጠበ ችሎታው ሲረዳ ኖሯል። ” ሲሉ በማህበራዊ ድረ ገፅ ባጋሩት ፅሁፍ ተናግረዋል።

ዶክተር ጳውሎስ በድሀና በሀብታም በባለስልጣንና ምስኪን መሀል ምንም አድልዎ የማያውቁ የሙያ ተምሳሌት ነበሩ።

በደርግ ዘመን ጄነራል ተፈሪ በንቴ ሊታከሙ ካርድ አውጥተው ከተራ በሽተኛ ጋር ተራቸውን ሲጠብቁ የዶክተር ጳውሎስ ረዳትና አስተናጋጅ የጠቀማቸው መስሎት ካርዳቸውን ላይ አስቀምጦ ተጠርተው ገቡ። ይህንን የተገነዘቡት ዶክተር ጳውሎስ በንዴት እኔጋ ማንም ከማንም አያንስም እርሶ የደርግ ሊቀመንበርና ጄነራል ቢሆኑ የርሶ በሽታ ከሌላው አይበልጥም ብለው ካርዳቸውን ከሁሉ ስር አደረጉት። ትሁቱ ጄነራልም ደንግጠው ላብ ግምባራቸው ላይ ቲፍ ብሎ እኔኮ ቅድሚያ ይሰጠኝ አላልኩም ይቅርታ እያሉ ወተው ተራቸው ሲደርስ ገቡ። ይህም የዶክተር ጳውሎስ መገለጫ ነው።

ዶክተር ጳውሎስ ዘመድ ወዳድ፣ ቀልድና ቁምነገር አዋዝተው ማቅረብ የሚችሉ ታላቅ ሰው ነበሩ። በሁለት ታናናሽ እህቶቻቸው በወይዘሮ ምህረት ቀንዓ እና በሲስተር አንቀፀ ቀንዓ የሚወደዱት ዶክተር ጳውሎስ ቀንዓ በልጅ ልጅና በዘመድ አዝማድ ተከበው ፍቅር ሲለግሱ የነበሩ የቤተሰቡ ተወዳጅ ዋርካ ነበሩ።

ላለፉት 62 አመታት በሙያቸው ያገለገሉት ዶክተር ጳውሎስ ቀንኣ ረጅም ጊዜያት ህመም አያውቃቸውም። ነገር ግን በዚህ አመት ባጋጠማቸው ህመም ፣ ህክምናቸውን በላንድማርክ ሆስፒታል ሲከታተሉ ቆይተው ነሐሴ 2 2018 ዓ.ም በ93 አመታቸው ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል። ዶክተር ጳውሎስ ቀንኣ የአንዲት ሴት ልጅ አባትና የአንድ ልጅ አያት ነበሩ።

ዶክተር ጳውሎስ ቀነኣ በዘሩት ጽኑ ዘር፣ ባፈሩት ብቁ ትውልድ እና ለሀገራቸው ባበረከቱት የማይጠፋ ውለታ ምክንያት ዛሬም ቢሆን በየሆስፒታሉ ብርሃን ለሚያጡ ዜጎች በሚደረገው ተጋድሎ ውስጥ ህያው ሆነው ይኖራሉ ።

 አንጋፋው ሐኪም  ዶ/ር ጳውሎስ ቀንኣ ነሐሴ 7 2018 በሉትራን ቤተክርስቲያን የሽኝት መርሀ ግብር ተደርጎላቸው፣ ከቀኑ በ 9 ሰዓት የቀብር ሥነሥርዓታቸው ተፈፅሟል። 

ተወዴጅ ሚድያ፣ ቅኔ ኢቬንትስ ፣ እና በላይ እለፋቸው ፣ ክንዲሁም ዳንኤል አርጋው ከቤተሰብ ጋር በመሆን የሽኝት እና የሀዘን ሥነሥርዓቱን አዘጋጅተውታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *