ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ለአገር የሠሩ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ሲሰንድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ከዚህ ቀደም፣ በሚድያ እና በኪነ ጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን መዝገበ አእምሮ በተሰኘው ባለ 600ገፅ መፅሐፍ ላይ ተሰንዶ፣ ታትም እና ተመርቆ ከአንባቢያን እጅ የደረሰ ሲሆን በቅፅ 1 እና ቅፅ 2 ሁለት ጊዜ የ400 ባለሙያዎች ታሪክ በመፅሐፉ ላይ ተካተው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
በቀጣይ ደግሞ ዘርፎቹን ሰፋ በማድረግ በባህል በመምህርነት፣በሚሊተሪ፣ በሕግ ሙያ፣በሕክምና፣በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በባህር ኃይል ባለሙያነት፣በምህንድስና፣ በአገር አስተዳደር እና በመሪነት፣በንግድና ሥራ ፈጠራ፣በሚድያ እና ኪነጥበብ፣በእናትነት፣በኢንፎርሜሽንቴክኖሎጂ፣በቱሪዝም፣በዳያስፖራ፣በአርበኝነት፣በተመራማሪነት፣በባንክና ኢንሹራንስ፣ዘርፎች ለአገራቸው ጉልህ አሻራ ያኖሩ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ እንሰንዳለን፡፡
እስከዛሬ የሕይወት ታሪካቸውን የሰነድንላቸው ሰዎች ጉግል ላይ ሲፈለጉ ይገኛሉ።
“በልዩ ልዩ ዘርፍ “በርካታ ኢትዮጵያውያንን ለመሰነድ ሥራችንን የጀመርን ሲሆን በመዝገበ አእምሮ ቦርድ ታሪካቸው እንዲሠራ የተመረጡ ባለሙያዎችም ትብብር እንደሚያሳዩ ይጠበቃል፡፡
ዲያቆን ፍሬው ሰይፉ የኢትዮጵያን ባህል እና ታሪክ በአሜሪካ በማስተዋወቅ ትልቅ አሻራ ያኖረ ነው፡፡ የአርአያ ሰው ሽልማት በሚልም ለባለውለታዎች ዕውቅና ሲሰጥ 10 ዓመት ሆኖታል።
የዲያቆን ፍሬውን የሕይወት ታሪክ ቤርሳቤህ ጌቴ እንደሚከተለው አጠናክራዋለች።
ከላይ የለው ከታች፤ የቤቱ ብርቅ ነው። ከወላጅ አባቱ ጋር የነበረው ቆይታ ገና በ6 ዓመቱ በሞት ሲለዩት ቢቋረጥም እናትም አባትም ሆነው ያሳደጉት እናቱ ወይዘሮ ብርቄ ደምሴ በስብዕና ግንባታቸው በእርግጥም ተሳክቶላቸዋል።
ዛሬ ላይ ሀገሩን ወዳድ፣ ሀይማኖቱን አክባሪ ትልቅ ሰው ለመሆን የበቃው በብርቱ እናቱ ያላሰለሰ ጥረት እንደሆነ እርሱም በኩራት የሚመሰክረው ነው። በሀይለኛነታቸው የሚፈራቸው ወላጅ እናቱን ” በእንቁላሉ ጊዜ ስለቀጣችኝ ነው የዛሬውን ፍሬው የሠራችው!!” ብሎ ይገልፃቸዋል።
ዲያቆን ፍሬው ሰይፉ የትውልድ ዘመኑ ሐምሌ 15 1972 ዓ.ም ነበር።በድቁና አገልግሎቱ ቤተክርስቲያን በሰጠችው ተልዕኮ እየተሰማራ በፀጋ ማገልገሉ እንደተጠበቀ ሆኖ በአለማዊው ተልዕኮው ለሀገሩ አምባሳደር በመሆን ባህሉን አክብሮ በማስከበር ኢትዮጵያን እያስተዋወቀ የሚገኝ ኩሩ ዜጋ ነው። 365 ቀናት የሀገሩን ምርት፤ ባህሉን ለብሶ ለተመለከተው ውበቱና ድምቀቱ ከሩቅ የሚጣራ መሆኑን ይመሰክርለታል። እርግጥ ነው አለባበሱን የቀየረው በ2000 አመተ ምህረት አርአያ የሆኑለትን እነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሀቅንና አርቲስት ማሪቱ ለገሰን ምሳሌ በማድረግ ቢሆንም ይሄ ስብዕና በአንድ ጀምበር የሚፈጠር ሳይሆን ከስር ከመሰረቱ እየተገነባ መጥቶ የተገለጠ በመሆኑ ለስብዕና ግንባታው ለእናቱ የሚሰጠው ድርሻ እንዳለ ሆኖ የአካባቢ ማህበረሰብ፣ቤተክርስቲያንና የትምህርት ተቋማትም የራሳቸውን ሚና ተወጥተዋል። ዲያቆን ፍሬው ተወልዶ ያደገው ከጃንሜዳ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው በተለምዶ አጠራር “የኮርያ ዘማቾች” ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነበር።ኮሪያ የዘመቱ ወላጆችና ልጆች፣የልጅ ልጆቻቸው በሚገኙበት፣ የቀድሞ ሠራዊትና ማዕከላዊ ዕዝ ወይም ክቡር ዘበኛ ሰፈር ላይ ማደግ ለሀገር ያለን ፍቅር ምን ያህል ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ለመገመት አይከብድም። ሀገራቸውን ወክለው ለሰው ልጆች ሲሉ እራሳቸውን መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ የነበሩ ውድ የሀገር ልጆች መገኛ ነውና ሰውነትን፣ሀገርን፣እምነትን ጠንቅቆ ለመረዳት ጥሩ መንገድ ሆነውለታል።
የወታደሮቹ የሰንደቅ አላማ አያያዝና ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር ሲሰቅሉም ሆነ ሲያወርዱ ያላቸው ጥንቃቄና አክብሮት ወደተመለከታቸው ሁሉ የሚጋባ ነበረና እነ ፍሬው በልጅነት የሀገር ፍቅር መንፈስ ሊጋባባቸው የግድ ሆኗል።
ፍሬው ሰይፉ በቤቱ ብቸኛ ልጅ ይሁን እንጂ በአንድ ግቢ ውስጥ በርካታ ሰዎች የሚኖሩበት ሁሉም ቤት የሁሉም ልጆች የሆነበት ጠንካራ ጉርብትና በነበረበት መንደር ውስጥ በማደጉ ብቸኝነት ሳይሰማው ለማደጉ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጎለታል። በልጅነቱ ከማይረሳው ትዝታ አንዱ ከአጥራቸው ጋር የተያያዘው የወታደሮች ካምፕ በቀድሞ አጠራሩ የጀነራል ደበበ ካምፕ ይባል ነበረና በደርግ ዘመን ኩባዎች የሚኖሩበት ጊቢ ነበር። ታዲያ እነ ፍሬው በልጅ እግራቸው ተሯሩጠው ለኩባዎቹ በታዘዙ መጠን እንደ ሽልማት የሚሰጣቸውን ሩዝና ሌሎች ምግቦች የጊቢው ልጅ በሙሉ በጋራ እንደ ቤተሰብ እየተመገቡ በመተሳሰብ ማደጋቸውን ሲሆን የተማሩትም የሚጫወቱትም በጋራ መሆኑ ብቸኝነቱ እንዳይሰማው አድርጎታል። በቅርባቸው የሚገኘው የቀበና ወንዝ ለአካባቢው ልጆች ልዩ ትዝታን የሚያጭር ነበር። ፍሬው የማይዘነጋው ግን ለእርሻ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ከቀበና ውሀ እየቀዱ እርሻቸውን የሚያጠጡበትን እና የሚያገኟቸውን ትናንሽ አሳዎች እንደነገሩ ጠባብሰው የሚመገቡበትን ጣፋጭ የልጅነት ትዝታ ነው። የዋና ነገር ከተነሳ ግን መዋኘት በፍሬው ዘንድ አይታሰብም። ይልቁን የልጆቹን ልብስ መጠበቅ ነው የእርሱ ኃላፊነት።
እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከየኔታ ቤት የጀመረው የቀለም ቆጠራ ወደ መደበኛ የትምህርት ሥርአቱ ሲገባ በህብረት ፍሬ እና ደጃዝማች በላይ ዘለቀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቱን ካጠናቀቀ በኋላ በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ፈለገህይወት የሰንበት ትምህርት ቤት የጀመረውን የቤተክርስቲያን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ቆይታው በቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ በነገረ- መለኮት ለሦስት አመታት ትምህርቱን ተከታትሎ በ1996 ዓ.ም ዲፕሎማውን ተቀብሏል። በተማሪነት ዘመኑ ከቀለም ትምህርቱ ባልተናነሰ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በፍቅር ይሳተፍ ነበር። የጠረጴዛ ቴኒስ እና እግር ኳስ ጨዋታ ላይ በልዩ ሁኔታ ይሳተፍ ነበር።፣” ቃኘው ኮሪያ” የእግር ኳስ ቡድን አባል በመሆን ፍቅሩን ተወጥቷል። ጃንሜዳ ለዚህ ፍቅሩ መቀስቀስ ምክንያት ሆኖለታል።
የሥራውን ዓለም ሲቀላቀል አጎቱ ይሠሩበት በነበረው ትላልቅ ተቋማቶች ከአትክልት ተንከባካቢነት እስከ ተቆጣጣሪነት ባለው ሙያ ኃላፊነቶቹን በብቃት ሲወጣ ቆይቷል። ከዚሁ ጎን ለጎን በሰንበት ትምህርት ቤት በነበረበት ጊዜ ቤተክርስቲያን የሰጠችውን ድቁና ሳይዘነጋ ለወንጌል አገልግሎት በተጠራበት ስፍራ ተዟዙሮ ተልዕኮውን ከመፈፀም አልቦዘነም። ዲያቆን ፍሬው ባደገበት መንደር አብሮ አደጉ ከነበረችው ከአሁኑ ባለቤቱ ቅድስት ወርቁ ጋር ጋብቻ ፈፅሞ በአሜሪካ ኑሮውን እስካደረገበት ጊዜ ድረስ በሙያው በሀገሩ ላይ ሲሠራ ቆይቷል። ወደ አሜሪካ ከማቅናቱ በፊት የሀገሩን ባህል የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በመኖሪያ ቤቱ እያሰባሰበ ማስቀመጥ ደስታ የሚፈጥርለት ነበረና ሀገር መቀየር ግድ ሲሆንበትና ኑሮውን በ2007 ዓ.ምበአሜሪካ ሲመሰርት መኖሪያ ቤቱን እንደ መለስተኛ ሙዚየም መልክ በማስያዝ፤ የሀገሩን ባህል የሚገልፁ ቁሳቁሶችን ለተመልካቹ ሳቢ በሆነ መንገድ በማኖር ለጉብኝት እንዲበቃ ማድረግ ችሏል። ሀገር በአለባበስና ቁሳቁስን ሰብስቦ ለእይታ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን የምትገለጠው የሰሩላትን በማመስገንና እውቅና በመስጠት ጭምር ነው በሚልም እይታ ዓድዋ የባህል እናየታሪክ ኅብረትን የተባለ ለትርፍያልተቋቋመ ድርጅትን ለመመስረት በቃ።ይህ ድርጅት ሲመሰረት ምሳሌ የሆናቸው የቀዳማዊኃይለ ስላሴ ሽልማት ድርጅትን ነበር።
በዚህም በሚኖርበት ዳላስ ቴክሳስ የሚገኙ ተማሪዎች ስለ ሀገራቸው ወግና ባህል እንዲያውቁ ማስተማር አንዱ ሥራቸው ሲሆን ‘በአርአያ ሰው ሽልማት’ በርካቶችን እውቅና መስጠት ላይ በትኩረት ሲሠራም ቆይቷል። ‘እናቀዳድማለን እንጂ አናወዳድርም!’ በሚል መርሀቸው ላለፉት 10 አመታት በተለያዩ ዘርፎች ለሀገራቸው በጎ ነገር ሰርተዋል ላሏቸው ሰዎች እውቅናና ሽልማት አበርክተዋል። በአርአያ ሰው እውቅናና ሽልማት ካገኙት ሰዎች መካከልም የቱሪዝም አባት ጋሽ ሀብተስላሴ ታፈሰ፣ የሐረሩ ሼህ አብዱላሂ ሸሪፍ የግል ሙዚየም ባለቤትና የቅርስ ሐኪም፣ የተወዳጅ ሚድያና ኮምዩኒኬሽን መስራችና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተጠቃሽ ናቸው።
የአርአያ ሰው ሽልማት በአሁኑ ሰዓት የአርአያ ሰው የሽልማት ፋውንዴሽን ወደ ሚል ተቋም ያደገ ሲሆን ነሐሴ 16 2018 በዳላስ 10ኛ ዓመቱንና ለአገር ውለታ አበርክተዋል ላላቸው ሰዎች የሽልማት ሥነ ሥርዓት አዘጋጅቷል። ላለፉት 18 አመታት በአሜሪካ ጎዳናዎች የኢትዮጵያን የባህል ልብስ በመልበስ የባህል አምባሳደርነቱን በተግባር ያሳየ ሲሆን ይህም ከፍተኛ የሕሊና ርካታ እንደሚሰጠው ይናገራል።
ዲያቆን ፍሬው ሰይፉ እንደሚመሰክረው “መሻቴን እንድኖር ባለቤቴ ከጎኔ መቆሟ ትልቅ ዕድል ነውና ሳላመሰግናት አላልፍም!” ይላል። ከትዳር አጋሩ ሁለት ልጆችን ያፈራ ሲሆን ናትናኤል እና ኖህ ብሎም ሰይሟቸዋል።