ጌታቸው ቦሎዲያ/ተባባሪ ፕሮፌሰር /(1922-1984)

ተወዳጅ ሚድያ በህዝብ ዘንድ ፈፅሞ የማይረሱ ሰዎችን እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ ሰዎች ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ ይገኛል። ታሪካቸውን ሰንደን ካቆየንላቸው ባለሙያዎች መካከል ጌታቸው ቦሎዲያ አንዱ ሲሆን ቤርሳቤህ ጌቴ ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንዳዋለች።

​ተባባሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ቦሎዲያ በአራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ (በቀድሞ አጠራር)
የመምህርነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ጥሎ ያለፈ ብዙዎችንም ያፈራ የሀገር ባለውለታ ነው። ሳይንስን ከማህበራዊ ህይወት፣ እውቀትን ከትህትና፣ ስራን ከፈገግታ ጋር አዋህዶ የኖረ ድንቅ ምሁር ነበር።
​ዛሬ በዘርፉ የሚገኙ ሁሉ ስለ ባዮኬሚስትሪ ሲያስቡ ከቀመሮቹ በፊት ትዝ የሚላቸው እንደ ሳይንስ ቀመር የከበደና እንደ ጨዋታ አዋቂ ፈገግታ ደግሞ የቀለለው ጌታቸው ነው። ጌታቸው ቦሎደያ ፈገግታ፣ ፈጣን ምላሾቹና ያ የማይረሳው ሳቢ ማንነቱ ይወደዱለታል። እርሱ በክብር የኖረ፣ እውቀትን ለሰው ልጅ ደስታና ፈውስ የገበረ፣ ዛሬም በታሪኩ መዝገብ ላይ በደመቀ ቀለም የሚታወስ ምሁር ነው።

ጨዋታ አዋቂው ባዮኬሚስት ጌታቸው ቦሎዲያ በ1922 ተወልዶ በ1984 በ62 አመቱ ያረፈ ታላቅ መምህር እንደሆነ ይነገርለታል።

አጠር ቀጠን ብሎ ጠቆር ያለ፣ መነጸር የሚያዘወትር፣ ቄንጠኛ የድሬደዋው ልጅ ጌታቸው ቦሎዲያ ፤ የትምህርት ጊዜውን በሀረር መድሀኒያለም ትምህርት ቤት መማሩን የሚያውቁ ወዳጆቹ ነግረውናል።

እድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻን ጎንደር ዘምቷል።
ማስተርሱን ከካናዳ ፣ ፒኤችዲ ደግሞ ከካምብሪጅ የሰራው ጌታቸው ​ባዮኬሚስትሪ (Biochemistry) ለብዙዎች የህይወት ምስጢር ሳይሆን ተራራ የመግፋት ያህል የከበደ ሆኖ በሚታይበት ጊዜ እርሱ ግን ያንን የተወሳሰበ የሴሎችና የኬሚካሎች ውህደት እንደ ሙዚቃ ቅኝት አቅልሎ የገዛ፣ በዕውቀት አውድማ ላይ መቆም የቻለ እንደነበረ ይመሰከርለታል።

“እውቀትን ከፏፏቴው ኑና ጠጡ!! ይህ ከፊታችሁ የቆመው በአለም ላይ ምርጡና ከአፍሪካም ብቸኛው ባዮኬሚስት ነው” ብሎ ስለራሱ በኩራት የሚናገር ነው። ስሙን “ጌታቸው ቦሎዲያ” (Getachew Bolodia) ከሚሉት የመጀመሪያ ፊደላት በመነሳት ራሱን የሚያቆላምጥበት የጨዋታ ስልት ነበረው። በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እየተጋበዘ ሲያስተምር ራሱን የሚያስተዋውቀው በፈገግታ ተሞልቶ “ከየትኛውም ቦታ ‘GB’ የሚል ጽሑፍ ካያችሁ ወይ ታላቋ ብሪታንያ (Great Britain) ናት፣ ወይም ደግሞ እኔው ጌታቸው ቦሎዲያ ነኝ!” እያለ ያስተዋውቅ ነበርና እስከዛሬም የማይረሳ ንግግሩ ሆኖ ቀርቷል።

ያንን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኬሚካል መስመሮች ያሉበትንና ተማሪን እንቅልፍ የሚነሳውን ትምህርት፣ በራሱ ማራኪ የፈጠራ ስልት ሰባብሮ ያቀርብ እንደነበረ የቀድሞ ተማሪያቸው ፕሮፌሰር ዘነበ ታደሰ ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ጌታቸው ለተማሪዎቹ መምህር ብቻ አልነበረም፤ ከከበደው ሳይንስ በስተጀርባ ያለውን የህይወት ውበት የሚያሳይ መነጽር እንጂ።

​የጌታቸው ዕውቀት በክፍል ግድግዳዎች ብቻ አልተገደበም። በ1965 – 1966 ዓ.ም. የፓስተር (የአሁኑ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት – EPHI) ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ተሹሞ ነበር።
​የሳይንስና የላቦራቶሪ ጥበቡን ይዞ ወደ ምርምር ማዕከሉ ሲዘልቅ፣ ተቋሙን በዋናነት የመሩ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ተርታ ስሙ በወርቅ ቀለም ተጻፈ።

ወረርሽኞችን በሳይንሳዊ መንገድ የመመርመር፣ የሀገሪቱን የጤና አቅም የመገንባትና ተቋሙ በምርምር ራሱን እንዲችል የመስራት ሀላፊነት ነበረበት። እርሱም በሳይንሳዊ ምልከታውና በጽኑ አመራሩ ለሀገር የሚበጅ ጠንካራ መሰረት ጥሎ አለፈ። ወዳጆቹ እንደሚሉት ጌታቸውን በሞት ባይለየን ብዙ ሀገሩን ሊያግዝ የሚችልበት ትልቅ አቅም ነበረው። በአገልግሎቱ ስኬትም ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት የፌሎ ተሸላሚ ለመሆን የበቃ ነው።

​ጌታቸው ከፕሮፌሰርነቱና ከዳይሬክተርነቱ ማዕረግ ጀርባ፣ እጅግ ማራኪና ሳቢ የሆነው ሰውኛ ማንነቱ ይገዝፋል። በአካዳሚክ ማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ መብረቅ በፈጠነው ምላሹ የቅጽበታዊ ቀልድ ባለቤት መሆኑ ተመስክሮለታል።
​ማንኛውንም የከረረ ክርክር፣ ማንኛውንም የከበደ ስብሰባ በአንዲት ቃል ቆንጥጦ በሳቅ የማፍረስ አስገራሚ ተሰጥኦ ነበረው። ሰዎች እርሱን ለመቅረብ አይፈሩም፤ ምክንያቱም ከአካዳሚክ ኩራትና ከሹመት ርቆ፣ ትሕትናን የለበሰ ነጻ ሰው ነበር ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ እንደሚመሰክሩት።

አባቱ የህንድ ቤት ዘበኛ ነበሩና ‘ድሬደዋ ስትሄዱ ታገኙታላችሁ’ እያለ በድፍረት የሚናገር ነው’ ራሱን ሆኖ የኖረና ራሱን ሆኖ የሞተ ሰው ነው ይሉታል ወዳጆቹ።

የምድራችን ጀግና ከሚለውና የዶክተር ተወልደብርሃን የህይወት ታሪክን ከሚያስነብበን መፅሐፍ ውስጥ ስለጌታቸው ቦሎዲያ የተናገሩትን ሀሳብ ዘነበ ወላ እንደሚከተለው አስፍሮልናል።

” ​ከዶክተር ጌታቸው ቦሎዲያ
ጋር ስንገናኝ ገና ዶክትሬቱን አላገኘም ነበር:: ማስተሬቱን እንደተቀበለ ነው። በዕድሜ ከእኛ ቢበልጥ እንጂ ገና በጣም ወጣት
ነበር:: ከመምህርቼ ሁሉ ከእሱ ጋር ያለኝ ልዩ ትዝታ እንዲህ ነበር::
​አንድ ‘ፊዚዮሎጂ’ ያስተምረናል:: በተለይ የሰው ፊዚዮሎጂ:: የእኛ አካል እንዴት እንደሚሠራ ነበር የሚያስተምረን::
ጡንቻ እንዴት እንደሚንቀሳቀስ እንደሚጨበጥ እንደሚላላ እሱን በተመለከተ ያስተምራል። ዝርዝሩን ሲያስረዳኝ ልክ እንዳልመሰለኝ ሁኔታ ዘርዝሬ ተቃውሞዬን ከይቅርታ ጋር አሰማሁ።
​አየና አሰበ። «ለምን ልክ አልመሰለህም?» አለኝ። እኔም አስረዳሁት። ወዲያው «በማንኛውም ጥሩ። እኔም ሄጄ አነባለሁ፤ አንተም ሄደህ አንብብ። በሚቀጥለው ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግረን ተስማምተን ከዚያ በኋላ ትምህርት እንቀጥላለን» አለኝ። ​በሁለተኛውም ቀን አልተስማማንም። እኔ በዚህ ላይ ምንም
የሚነበብ መጽሐፍ አላገኘሁም። እሱ ጥያቄውን ለመመለስ ያብራራው ጉዳይ አልተዋጠልኝም። በሦስተኛው ጊዜ የእኔ ጠያቂነት ገፋፍቶት ፈልጎ ፈልጎ መጽሐፍ አገኘ። ክፍል ውስጥ አስረዳኝ። አጥጋቢ መልስ አገኘሁ። ከዚያ በኋላ እሱም ስለእኔ እንደተናገረ እኔም ምንጊዜም እንዳከበርኩት ኖርኩኝ። ​ ተሳስቻለሁ፤ እስኪ አብረን እንፈልግ ያለኝ መምህር
ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ያጋጠመኝ ዶክተር ጌታቸው ቦሎዲያ ብቻ ነው። አብዛኛው አስተማሪ በአንዲህ ዓይነቱ ወቅት ተዋረድኩ ብሎ ነው የሚበሳጨው። እንዲያውም ጥያቄ የሚያበዛ ተማሪ ሲያጋጥመው መመለስ የማይችል መምህር ይበሳጫል። ተማሪውንም ስለሚጠላው ኃይለኛ መፈራራት ይፈጥራል። በአንዲህ ዓይነትአጋጣሚ የማያቋርጥ ጥያቄዎቻችንን እንቀጥላለን። በዚህ ጠያቂነቴ ግን ከዶክተር ጌታቸው ጋር እንደ ተዋደድን ነው የተላለፍነው። እኔንም በመልካም ተማሪነቴ ያነሳኝ ይህ አጋጣሚ ነበረ።” ብሎ የጌታቸውን የመምህርነት መለያ አስነብቦናል።

ጌታቸው በትዳር ልጆችን ያፈራ ሲሆን 1984 ሚያዝያ ወር ውስጥ ነበር ያረፈው። ከሞቱ በኋላም በፕሮፌሰር ኤርሚያስ ዳኜ አነሳሺነት በጌታቸው ቦሎዲያ ስም ፋውንዴሽን ተቋቁሞም ነበር። አላማው ባዮኬሚስትሪ ለሚማሩ ጎበዝ ተማሪዎች በወር 30 ብር እየተሰጠ እንዲበረታቱ ለማድረግና ቤተመፅሀፍት በስሙ ለማቋቋም ያለመ ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *