ተወዳጅ ሚድያ ለሀገር የሠሩ ነገር ግን በህዝብ ዘንድ ብዙም የማይታወቁ ሰዎችን የሙያና የህይወት ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።እነዚህ ሰዎች ጎግል ላይ በስማቸው ሲፈለጉ የሰገኛሉ። እስከዛሬ የ500 ሰዎች ተሰንዶ ድረ ገፅ ላይ የተቀመጠ ሲሆን በሁለት ኢንሳይክሎፒዲያ መጽሐፎችም ታሪኮቹ መታተም ችለዋል።በዚህ ፅሑፍ የምናነሳው የሚድያ አሰልጣኝ የሆኑትን እና በብስራተ ወንጌል በዜና አንባቢ የሚታወቁትን ወይዘሮ አለምሰገድ ህሩይን ነው። ዕዝራ እጅጉ ተሻሽሎ የቀረበውን ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል።
ትውልድ እና የቤተሰብ ማንነት
ወይዘሮ አለምሰገድ ፈቃደሥላሴ የብላቴንጌታ ህሩይ ወልደላሴና የራስ እምሩ ኃይለስላሴ የልጅ ልጅ ናቸው። አባታቸው ልጅ ፈቃደሥላሴ ህሩይ ለአገራቸው ነፃነት በአለምአቀፍና በአገር ውስጥ የታገሉ በ30 ዓመት እድሜያቸው በፋሽስት ወታደሮች በአሰቃቂ መንገድ ህይወታቸውን ያጡ ታላቅ ሰው ናቸው።ወይዘሮ አለምሰገድ ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን አለምሰገድ ህሩይ ብለው ትክክለኛው ሙሉ ስማቸው ግን አለምሰገድ ፍቃደሥላሴ ህሩይ ነው።
ጠይም ፍልቅልቅ፣ አንገተ ብርሌ፣ ጥርሰ በረዶ፣ ፓንክ ቁርጥ ጋዜጠኛና አሰልጣኝ ዓለምሰገድ ፍቃደሥላሴ ህሩይ በመዲናችን አዲስአበባ ከተማ ከአባታቸው አቶ ፍቃደ ሥላሴ ህሩይ እና ከእናታቸው የምሥራች እምሩ በግንቦት 1925 ተወለዱ፡፡ ገና የ 4 ዓመት ህጻን ሳሉ ጨካኙ ፋሽስት ኢጣሊያ ድንበር ጥሶ ወደ ሀገር ገብቶም በጥቁር ታሪክ ውስጥ የማይረሳውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ አደረገ፡፡ ከ 30,000 ሺህ በላይ የአዲስአበባ ነዋሪዎች በሚዘገንን ሁኔታ ህይወታቸውን እንዳጡም ይነገራል።
ታዲያ ከዚህ አሰቃቂ ሞት ለመራቅ ያለ የሌለ አማራጭ ተጠቅመው ከመሞት መሰንበት እያሉ ንጉሰ ነገስቱን ጨምሮ ወደሰው ሀገር የተሰደዱት ብዙዎች ነበሩ። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል እኝህ የ 4 ዓመት ህፃን አንዷ ነበሩ። ዓለምሰገድ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን በጎሬ በኩል ወደ እየሩሳሌም ገቡ።
ጨካኙ ፋሽት ኢጣሊያ የበላውን በልቶ የፈጀውን ፈጅቶ ያልሞት ባይ ተጋዳይነት ጊዜው አብቅቶ ባህልና ወጎቻችንን ቋንቋዎቻችንን በርዞ ሲመለስ እነ ዓለምሰገድ በተራቸው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመለሱ። ተመልሰው በ 6 ኪሎ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ቆይተው በአዳሪ ትምህርት ሳቢያ በድጋሚ ተመልሰው ከሀገራቸው ወጥተው ወደ እንግሊዝ ሀገር አቀኑ።
ከእንግሊዝ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር
ከእንግሊዝ ሀገር ትምህርታቸውን ጨርሰው በመመለስ በማስታወቂያ ሚንስቴር ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። በመሀል የልጃቸው አባት የሆነውን አቶ አባተ ጌታቸውን አግብተው በድጋሚ ከሀገራቸው ኢትዮጵያ በመውጣት ወደ ስዊዲን ሀገር ተጓዙ። ስዊዲን በትዳር ላይ ሳሉ የመጀመሪያ ልጃቸውን ዶ/ር ሻሽኪን አባተን ወልደዋል። ይሁን እንጂ ልክ እንደርሳቸው ሁሉ ልጃቸውን ሻሽኪንን ገና በሁለት ዓመት እድሜዋ ይዘዋት ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመለሱ።
ብስራተ ወንጌል እንደአሰልጣኝ
በድጋሚ በማስታወቂያ ሚንስቴር ውስጥ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ወደ ብስራተ ወንጌል ተዛውረው ዜና በማንበብና ጋዜጠኝነትን በማሠልጠን ለረዥም ጊዜ አሳልፈዋል። በመካከልም ለተወሰነ ጊዜ ወደሆላንድ አቅንተው የአሰልጣኞች አሰልጣኝ ሥልጠና ወስደዋል። አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋዜጠኝነትን ሲያሰለጥኑ የቆዩ ቢሆንም በርካታ የሚዲያ ሰዎችን በብስራተ ወንጌል ውስጥ እውቀት አስጨብጠዋል።
ደርግ ሲገባ በ1969 ዓ.ም ብስራተ ወንጌልን የወረሰው በመሆኑ በጣቢያው ውስጥ የነበሩት ነጮች በሙሉ በመልቀቃቸው ምክንያት ዓለምሰገድ ህሩይ አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋን ቢሠሩበትም ፈረንሳይኛ ግን ሜዳ ላይ በመውደቁ ፈጥነው በመድረስ ማንበብ ችለዋል። በኋላም በሦስት ቋንቋዎች ማንበብ ጀምረዋል። ፈረንሳይኛ አንባቢ የነበረው አቶ ጌታቸው ተድላ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ዓለምሰገድ ፈረንሳይኛን ተራቀውበት ቆይተዋል።
ሥልጠና
ዓለምሰገድ ህሩይ አሰልጣኝ በነበሩበት ዘመን እነ መለስካቸው አምሃ፣ ይንበርበሩ ምትኬና ኃይሉ ወልደፃዲቅን የመሣሠሉ በርካታ ጋዜጠኞችን አስተምረዋል። የጋዜጠኝነት ፍልስፍናን የተረዱ ናቸው የሚባሉት ዓለምሰገድ ከሚሰጧቸው ስልጠናዎች መካከል
- የሬዲዮ ጋዜጠኝነት እና ምንነት
- የፕሮግራም ዝግጅት ቴክኒኮች
- የሬዲዮ ድራማ ዝግጅት እና በሬዲዮ ድራማ ውስጥ የሙዚቃ ተጽእኖ እና
- ሪፖርት አደራረግ ቴክኒኮች … የመሣሠሉ በርካታ ስልጠናዎችን በመስጠት የሚዲያ ባለሙያዎችን አፍርተዋል። የጋዜጠኝነት ሥልጠና በወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሚሰጥ መሆኑን ተገንዝበው የሚያስተምሩ ባለሙያ ናቸው። ዓለምሰገድ በተለያዩ ሀገራት እየተንቀሳቀሱ ያሰለጥኑ ስለነበር በየቀኑና በየሳምንቱ ፕሮግራም አያዘጋጁም ነበር። ቢሆንም ግን ባላቸው የቋንቋ አቅም በተለይም እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ዜናዎች ይሠሩ ነበር።
የሬዲዮ ጋዜጠኝነትን መርህ ያስጨበጡ፣ ያላቸውን እውቀት ለማካፈል ዝግጁ የሆኑና የማይሰስቱ ለሥራ ጓዶቻቸው እንደ እናትም፣ እንደ እህትም የሆኑ ትልቅ ባለሙያ ነበሩ ይላቸዋል የሥራ ባልደረባቸውና የወቅቱ ሰልጣኛቸው አቶ መለስካቸው አምሃ፡፡ በ1966 ዓ.ም መጨረሻ ክረምት ወቅት ላይ በብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ሰልጣኝ በነበረበት ወቅት ነበር ዓለምሰገድ ህሩይን የሚያውቃቸው። መለስካቸው ከሥራ ቦታ ባሻገር በነበራቸው ቅርበት የተነሳ በግሉ እድገት በህብረት ሲዘምት ስንቅ ቋጥረው መጽሐፍት አዘጋጅተው እንደሸኙት ያስታውሳል። የዓለምሰገድ የመኖሪያ ቤታቸውም ካዛንችስ ይገኝ ነበር።
ጉልህ አሻራ ያኖሩ
ዓለምሰገድ ህሩይ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ትተው ያለፉ ባለውለታ ነበሩ።ብዙዎችም ምስጋና የሚቸሯቸው ሀገራቸውንና ሚዲያቸውን ለተሻለ መገኘት ሲያሰለጥኑ የነበሩ ባለሙያ ነበሩ፡፡ በህይወት ሳሉም እንግሊዝኛ ቋንቋን በቤታቸው ውስጥ በነፃ ሲያስተምሩ የቆዩ መምህርት እንደነበሩ እንዲሁም በኢሕአዴግ መንግስት ወቅት Powerful Women Association በማቋቋም ፊልም እንደሠሩ ልጃቸው ዶ/ር ሻሽኪን አባተ ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር በነበራት ልዩ ቆይታ ተናግራለች። ዓለምሰገድ ፊልም ከመሥራት በተጨማሪ ማየትና መጽሐፍቶችን ማንበብ ይወዱ ነበር ትላለች።
ወይዘሮ አለምሰገድ እና መጽሐፋቸው
ወይዘሮ አለም ሰገድ ህሩይ የተለያዩ ፅሑፎችን በመፃፍ የሚታወቁ ሲሆን” The resurrection “የተሰኘውና በ1986 ዓ.ም ለህትመት የበቃው መጽሐፋቸው ይታወቃል።ይህ መጽሐፍ 64 ገፆች ያሉት ሲሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሲጓዙ የገጠማቸውን ያሰፈሩበት ነው።ይህ መፅሀፍ ስለ ድህነት አንዳንድ ሀሣቦችን ያሰፈረ ሲሆን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም በመጽሐፉ ላይ ቀርበዋል። ዶክተር ሻሽኪን አባተን ነሐሴ 8 2018 ዓ.ም ደውለን ጠይቀናቸው እንደነገሩን ይህ መፅሀፍ ቅኔያዊነትን በተላበሰ መልኩ የተፃፉ ፅሑፎችንም ይዟል። ወይዘሮ አለምሰገድ ይህን መጽሐፍ በነፃ ያድሉት እንደነበር ልጃቸው ዶክተር ሻሽኪን ነግረውናል።
ለኪነ ጥበብ፣ በተለይም ለስዕል የተለየ ፍቅር ያሳደሩት ወይዘሮ አለምሰገድ ለእናት ለአባታቸው አንድ ሲሆኑ ፒያኖ በመጫወትም ጊዜያቸውን ያሳልፉ ነበር።ባለቤታቸው አቶ አባተ ጌታቸው በ1996 ህይወታቸው እንዳለፈ ይታወቃል።
ዓለምሰገድ ህሩይ በሀገራቸው እና በአፍሪካ ሀገራት የሚዲያ ዘርፍ ላበረከቱት የጋዜጠኝነት ሥልጠና እና ትምህርት ለሠሩት ስራ ምስጋና ሳይቸራቸው በአግባቡ ክብርንም ሳይጎናፀፉ መኖራቸውም እንኳን በውል ሳይታወቅ በ መጋቢት 23 2006 ዓ.ም አርፈው ፣ መጋቢት 29 2006 ዓ.ም በ 81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።