ደምሴ ዳምጤ

ደምሴ ዳምጤ

ለ 40 አመታት ያህል ስለ ሀገሩ ስፖርትና ስፖርተኞች ሲናገር ሲዘግብ ዘመናትን ተሻግሯል ሁለንተናው ሁሉ ስፖርት ነው ፍፁም ኢትዮጵያዊ ስፖርት፡ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ፡፡ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ታላቅ አሻራ አሳርፈዋል ብሎ ያመነባቸውን ሰዎች በዚህ ድረ-ገጽ ላይ እያኖረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ የማይረሱ ባለውለታዎች አንዱ ደምሴ ዳምጤ ነው፡፡ ህይወቱ ካለፈ 9 አመቱን ያስቆጠረው ደምሴ ከእያንዳንዱ ስፖርት አፍቃሪ ልብ ውስጥ እንደኖረ አለ፡፡ የተወዳጅ ሚድያ የግለ-ታሪክ ረዳት ኤክስፐርት አንተነህ ደምመላሽ የደምሴን ግለ-ታሪክ እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡

ትውልድ እና እድገት

በ1945 ዓ.ም ሐረርጌ ጋራ ሙለታ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ተወለደ፡፡ አባቱ አቶ ዳምጤ በድሬደዋ ስሚንቶ ፋብሪካ በወዝ አደርነት ይሰሩ ስለነበር ልጃቸው ደምሴን ወደ ድሬደዋ ይዘውት መጡ፡፡ ህይወት ቀጠለች፡፡ ድሬደዋ ስሚንቶ ፋብሪካ የራሱ ድሬደዋ ሰሚንቶ የሚባል የእግር ኳስ ክለብ ስለነበረው ፡ ክለቡ ጨዋታ ባለው ጊዜ አቶ ዳምጤ ልጃቸው ደምሴን ወደ ድሬደዋ ስታዲየም ይወስዱት ነበር ፡ ከ አባቱ ጋር በመሆን ወደ ስታዲየም የመግባት ዕድል የነበረው ልጅ ደምሴ እግር ኳስንና የተለያዩ ጨዋታዎችን እየተመለከተ አደገ፡፡ ስፖርት የመውደድ ጅማሬውም ሆነ ፡፡

ደምሴ ፣ በልጅነቱ እንደማንኛውም ታዳጊ ከእኩዮቹ ጋር ልጅነታዊ ጨዋታዎችን ተጫውቶ አድጓል ፡፡ አንድ ቀን የአዲስ ከተማና የገንደ- ቆሬ ሰፈር ልጆች የእግርኳስ ግጥሚያ ሲደረግ ባለ ቅልጥማሙ ልጅ ደምሴ አዲስ ከተማን ወክሎ ወደሜዳ ይገባል ፡፡ ጨዋታው ከተጀመረና እየተጫወቱ እያለ ደምሴ ይጎዳና ይወድቃል፡፡ በወቅቱ የደረሰበት ጉዳት ለእድሜ ልክ ከ እግርኳስ ተጫዋችነት ዓለም አገለለው፡፡ ደምሴ በጉዳት ከተጫዋችነት መድረክ ቢወገድም እራሱን ወደ ጥሩ ተመልካችነት አሸጋገረ ፡፡

የጋዜጠኝነት ዝንባሌ በልጅነት

ገና በ 13 ዓመቱ ደምሴ የ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የስፖርት ዘጋቢዎች ሰለሞን ተሰማና ነጋ ወ/ስላሴ የሚያቀርቡትንና ሌሎች በድሬደዋ አካባቢ የተካሄዱ የስፖርት ውድድር ክንውኖችን አሰባስቦ በተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ሲያቀርብ ፡የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራኖች በአርምሞ ያደምጡት ነበር ፡ አንዳንዶቹ ስፖርታዊ ዜናዎቹ በኢትዮጵያ ሬድዮ ስፖርት ፕሮግራም የቀረቡ ቢሆኑም ደምሴ መልሶ ሲያቀርባቸው እንደ አዲስ በተመስጦ ያደምጡት ነበር ፡፡

ድሬደዋ ስሚንቶ ክለብ ሲያሸነፍ የፋብሪካው ሰራተኞች ሰብሰብ ብለው የምጣድ ጥብስ ግብዣ ያደርጉ ነበር ፡፡ በስነ ስርዓቱ የሚዘጋጀው የምጣድ ጥብስ ሳበኝ፡፡በዚያው እግር ኳስን እየወደድሁት መጣሁ ፡፡ ከልጅነት የጥሬ ስጋ ፍቅር ጋር ሲል ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ተደምጧል ፡፡ የሀረርጌ የስፖርት መምሪያ ባልደረባ የሆኑት አቶ መላኩ ወልደማሪያም ግን ደምሴ የሚያጠናቅረውን የስፖርት ዘገባ ሰምተው ዝም አላሉም፡፡ ተሰጥኦውንተመልክተው ከጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ጋር አገናኝተውታል ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ በ13 ዓመቱ የምስራቅ በረኛ ፖሊስና ድሬደዋ ሲሚንቶ ያደረጉትን ጨዋታ
ተመልክቶ ያዘጋጀው ዘገባ ለሰለሞን ተሰማ በፖስታ ቤት በኩል ተልኮለት ፡መስከረም12/01/ 1962ዓ,ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜናው ተላለፈለት ፡፡

የትምህርት አለም

ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ የመጀመሪያ ትምህርቱን ድሬደዋ በሚገኘው በራስ መኮንን ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በከዚራ ትምህርት ቤት ተምሯል ፡፡

በ ነፃ ፅናት እስከ 7 አመት

ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ በትምህርት ቤት ውስጥ በ ሚኒሚዲያ ክፍል ስፖርታዊ ክዋኔዎችን ለተማሪዎችና ለመምህራኖች ቢያቀርብም ለዋና ጋዜጠኝነት ሙያዊ ፍላጎት መጠንሰስ ግን አባቱን አቶ ዳምጤን ከመጀመሪያ ረድፍ ያስቀምጣቸዋል ፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮ ስፖርት ፕሮግራም አዘጋጅ የሆኑት ጋዜጠኛ ይንበርበሩ ምትኬ ነሐሴ 26 ቀን 1968ዓ,ም ለ ኢትዮጵያ ሬዲዮ መምሪያ ተጠባባቂ ሀላፊ ለነበሩት ለ አቶ ከፋለ ማሞ አንድ ደብዳቤ ጽፈዋል ፡፡ አቶ ይንበርበሩ ምትኬ በወቅቱ በስፖርት ክፍሉ ውስጥ ብቻቸውን ይሰሩ ስለነበር ፡ የሰው ሀይል እንዲቀጠርላቸው ቀደም ሲል ጠይቀው የነበረ ሲሆን ” በሥራው ላይ ልምድና ዝንባሌ ያለው ሰው ጠቁመን ” ተብለው ደምሴ ዳምጤን ጠቁመዋል ፡፡

ጋዜጠኛ ይንበርበሩ ምትኬ ስለ ደምሴ ዝንባሌና ልምድ በጠቆሙበትናበፃፉት ደብዳቤያቸው የሚከተለውን ጠቅሰው ነበር ፡ ቃል በቃል እነሆ,,,
” ከ 7 ዓመታት በፊት በንፁህ አማተርነት መንፈስ የመንግስት አባል ለሆኑት ለዜና ማሰራጫዎች ለጋዜጣ ለሬዲዮና ለቴሌቪዥን የሐረርጌ ክፍለ ሀገር
ስፖርት እንቅስቃሴ ሲያቀርብ የነበረው ደምሴ ዳምጤ ለዚህ ስራ ይበቃል ብዬ መርጨዋለሁ ፡፡ ደምሴ ዳምጤ፣ የሁለተኛ ትምህርቱን በ 1964ዓ,ም ጨርሶ በአሁኑ ሰዓት በመምህርነት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ነው ፡ ደምሴ ዳምጤ ከ አሁን በፊት ራሱን ለማሻሻል ብዙ ሥራ የማግኘት እድል ገጥመውት ዝንባሌየ በስፖርት ሪፖርተርነትና ተቺነት ካልተሰማራሁ ብሎ ያሳለፈ ወጣትነው ፡፡

ወጣቱ ለዚህ ሥራ መብቃቱን የሚያረጋግጡት ለ 7 አመታት ያህል በሬዲዮ በጋዜጣና ቴሌቭዥን ለህዝብ እንዲተላለፉ ያደረጋቸው መልዕክቶች ናቸው ፡፡ ወጣቱ ለሥራው ባለው ዝንባሌና ልምድ ለዘለቄታውም ብቁ ሆኖ እንደሚቀርብ ሙሉ እምነቶች አለኝ ” በማለት አስፍረዋል ፡፡ ደምሴ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከመቀጠሩ በፊት ለ 7 አመታት በነፃ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮችን እየተመለከተ ዜናዎች ይዘግብ ነበር ፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ባልደረባ ያደረገውም ይህ የስፖርት ፍቅሩና አንድም ሳንቲም ሳይከፈለው በፅናት ለ 7 አመታትበነፃ ዘገባዎችን መዘገቡና መላኩ ነበር ፡፡፡

መሠረት መትከል በ 13 ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ወደ ሊቢያ ቤንጋዚ ያመራውን የኢትዮጵያብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ለመከታተል አንድ የጅማ ሬዲዮ አድማጭ ለጋዜጠኛ ደምሴዳምጤ ደውሎ ” ቴሌቭዥን የሌለን ሰዎች ምን ይዋጠን? ” ይለዋል ጋዜጠኛ ደምሴበጥያቄው ብዙሃንነትና አንገብጋቢነት ተጨንቆ አሰበ አሰላሰለ ፡፡ የበዛ ጭንቀቱም መላ ወለደ ” እግር ኳስን በሬዲዮ ይመልከቱ ” ፅንሰ ሀሳብን መሠረት ተከለ ፡፡

በእርግጥ በጊዜው ቴሌቭዥን በጥቂት ከበርቴ ግለሰቦች ቤት የሚገኝ ስለነበርየስፖርት ቤተሰቡ የብሔራዊ ቡድኑን ውድድራዊ ሂደት የማወቅ ዕድሉ የመርፌቀዳዳ ያህል የጠበበ ነበር ፡፡ በዚህ የገዘፈ አመክንዮ ነው ጋዜጠኛ ደምሴ የተጨነቀው ፡ ተጨንቆ ግን አልቀረም፡፡ የእግር ኳስን በሬዲዮ ይመልከቱ ፅንሰ- ሀሳብ አፍልቆ ለአለቆቹ ለወ/ሮ አሰገደች ይበርታና ለሙሉጌታ ሉሌ ንድፋዊይዘቱን አበሰራቸው፡፡ ” ቴሌቭዥን እዚህ ስቱዲዮ ላስገባና በቴሌቭዥን እየተመለከትሁ ጨዋታውን ለህዝቡ በሬዲዮ ላስተላልፍ ” አለ ፡፡ አለቆቹ ግራ ተጋቡ፡፡ ሀሳቡ ያልተለመደናእንግዳ በመሆኑ ” እንዴት ይሆናል ?” አሉት ፡፡ ” ችግር የለውም የእኛን ተጫዋቾች በተክለ- ቁመና ስለማውቃቸው ስማቸውን እጠራለሁ ፡ የእነሱን ተጫዋቾች በቁጥር እጠራለሁ” አላቸው ፡፡ ተደነቁ፡፡ ተደንቀውም ዝም አላሉም፡፡ ወይዘሮ አሰገደች ይበርታሳሪስ ከሚገኘው ቤቷ ባለ ጥቁርና ነጭ ቴሌቭዥኗን ጭና አመጣችለትና ስቱዲዮ
ተቀመጠ ፡፡

ለስፖርት ቤተሰቡ ጋዜጠኛ ደምሴ አስቀድሞ በሬዲዮ ጨዋታውን እንደሚያስተላልፍ አሳውቆ ነበርና ሰዓቱ ሲደርስ ልክ በስፍራው እንዳለ ጋዜጠኛ ሆኖ ጨዋታውን አስተላለፈ ፡፡በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ሁነት ያልተስተካከሉ የሞሉና የጎደሉ እይታዎች በጋራ እግር ኳስን በማዳመጥ እኩል ሆነው ይመለከቱ ጀመር ፡፡ በ አንድ የጅማ ሬዲዮ አድማጭ በጎ ጥያቄ እግር ኳስን በሬዲዮ ይመልከቱፍልስፍና ተተከለ፡፡ የሚሊየኖች ስሜት ምላሽ አገኘ ፡፡ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤእግር ኳስን በሬዲዮ በሀገራችን ኢትዮጵያ እንድንመለከት በማድረግ መሠረት የጣለ ግንባር ቀደም ባለሙያም ሆነ ፡፡

ነባራዊ ምስክርነት

ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ለ 40 አመት ከሁለት ወር ያህል የ ኢትዮጵያ እግር ኳስናአትሌቲክስ ነባራዊ ምስክር ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅና በመካ ከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ድል ሲያደርግ ጋዜጠኛ ደምሴ በውስጣዊና ውጫዊ ደስታረስርሷል ፡ በአትሌቲክሱም ዘርፍ በጀግኖች አትሌቶች ድል የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍብሎ ሲውለበለብ የደስታ ሳግ እየተናነቀው ድሉን በልዩ የስሜት የበላይነት ዘግቧል፡፡ ከ ሞስኮ እስከ ባርሴሎና ፡ከ አትላንታ እስከ ሲድኒ ፡ ከ አቴንስ እስከ ቤጂንግ ደምሴየ ሀገር ኩራቶች አብሪ ከዋክብቶች የደመቁበትን ደማቅድል ለሚወደው ህዝብበአይረሴና ተናፋቂ ድምፁ አስተጋብቷል ፡ ታሪክ ሲሰራ ከታሪክ ቀማሪዎች ጋርተገኝቷል፡፡ ታሪካቸውን ሰንዷል እነሆ አብሮም ታሪክ ሆኗል ፡፡፡

ስነ – ምሳሌ

ጋዜጠኛ ደምሴ በ 40 ዓመታት የኢትዮጵያ ስፖርት ውጣ ውረድ ውስጥ ደሙእስኪንተከተክ ድረስ ተችቷል፡፡ ጮኋል ገምግሟል ፡፡ ስፖርትና ስፖርትን ብቻ ዘግቧል፡፡ ስነ- ስፖርትን ዘምሯል፡፡ ለብዙ ወጣቶች በተለያዩ ስፖርቶች መሳተፍና የስፖርት ጋዜጠኞች መፈጠር ከፍላጎት መቀስቀሻ ምንጭነት ያለፈ የሙያ ስነ ምሳሌ ሆኗል ፡፡

እርዛት የባ ዶነታችን ጥግ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ አፍሪካ ዋንጫ መድረክ መታየት ባለመቻሉ አንጀቱ በግኗል ፡፡ ህዝብ ጀሮው ህውው እስኪልበት ድረስ ጨዋታቸውን ብቃታቸውን ያደመጠላቸው ፡እጁ እስኪላጥ ያጨበጨበላቸው ፡ እይኑ እስኪፈጥ አንገቱ እንስኪጣመም
ተቆልምሞ የተመለከታቸው፡ በ አበባ ዘመናቸው የሳሳላቸው ለብሔራዊቡድን
ተጫውተው የነበሩ ኮኮብ ተጫዋቾች፡የእለት ጉርስ የአመት ልብስ የጎን ማሳረፊያጎጆ አጥተው ፡ ከስታድየም ደጃፍ እራፊ ጨርቅ አንጥፈው ሲለምኑ ፡ጋዜጠኛ ደምሴበማየቱ ምርር እርር ብሎ አልቅሷል ፡፡

የ እግርኳስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች መሀከል በተፈጠረው ሰጣ ገባ ሳቢያ ብሔራዊ ቡድኑ በፊፋ ቅጣት ሲጣልበት ቆሽቱ አሯል ፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ድልድል ወቅትም በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብድን ከግብፅ ጋር የሚደለደልበትን ደባ
አይቷል ታዝቧል ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ 5 በላይ ጎሎችንሲያስተናግድ በብስጭት ነዷል፡፡ ከ 70 በላይ የብሔራዊ ቡድኑተጫዋቾች በየተራ ሲጠፉና ሲሰደዱ እህህ ብሏል ፡፡ ስለ ሀገሩ ስፖርት ቆስሏል ደምቷል ፡፡፡

በስፖርትጋዜጠኞችና አትሌቶች አድማስ

ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ከ ስፖርት ዓለም ባሻገር በሀገር ፍቅር መንቀልቀል በፅኑ ታማኝነት ዘመናትን ማገልገል ፡ ከራስ በላይ ለህዝብ ክብር መስጠት መገለጫ ባህሪዎቹ ነበሩ ፡፡በታሪካዊ ድምፁ ሞገዶችን እየሰነጠቀ በወጣቶች አይነ- ህሊና ውስጥ ስዕሉን ስሏል እያደር የሚገለጥ ከ አለት የጠነከረ ከ እሳተ ገሞራ ነበልባልነት የተስተካከለ መሻት ቀስቅሷል ፡፡ ከ አትሌቶቻችንና ከስፖርት ጋዜጠኞች ጀርባ የሙያ አባት አምድነቱን ተክሏል ፡ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ የበዙ አካላዊ ፡ ሙያዊናሀገራዊ ምስክርነቶች ባለቤት ” አንቷችን ” ነው ፡፡

ተቆርቆሪ ነው !

ጋዜጠኛ ዳንኤል ጋሻው

ከደምሴ ጋር በ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ አብሬ መስራት ከመጀመሬ በፊት በፍሪላንሰርነትዜናዎችን በነፃ እየሰራሁ ለእሱና ለጎርፍነህ እሰጥ ነበር ብዙ ጊዜ የሥራ ስምሪት ሲደረግየተለያዩ የስፖርት ውድድሮችን እንድዘግብ ይልከኝ ነበር ፡፡በወቅቱ በጣቢያውለምሰራው ዜና ክፍያ አይደረግልኝም ፡፡ደምሴ ከራሱ የትራንስፖርት ይሰጠኝ ነበር፡፡ እኔ ለሙያው ፍቅር ስለነበረኝ የራሴን ትራንስፖርት ራሴ ችየ ነበር የምሰራው፡፡ ደምሴግን “አልቀበልም ” ስለው ይቆጣኝ ነበር ፡፡ ደምሴ በሀገር ውስጥ ዘገባው ነው የሚታወቀው፡፡ ለስፖርቱ በጣም ተቆርቋሪ ነው፡፡ በጣም የሚያስገርመኝ የደምሴ ባህሪይ ስንሸነፍ ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ በተደጋጋሚበእግር ኳሳችን መውደቅ በጣም ነው የሚናደደው፡፡ የስፖርት ሰዎች እንኳን እንደእርሱ የሚቆጩ አይመስለኝም ፡፡

ብሔራዊ ቡድናችን አዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ሲኖረው ለ ➎ ጊዜ ያህል እኔደምሴና ጎርፍነህ እየተቀያየርን ጨዋታዎችን በቀጥታ አስተላልፈናል፡፡ ለእኔ ትልቅእድል ነው የሰጠኝ፡፡ ብዙዎቻችን ወጣት ጋዜጠኞች ከደምሴ ልምድ ብዙ ነገርየተማርንና የቀሰምን ይመስለኛል ፡፡ ደምሴ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር መስራች ሲሆን ከ ቤጂንግ ኦሎምፒክ መልስ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በኦሎምፒክ ዘገባ ከፍተኛ አስተዋ
ጽኦ ያበረከተ አንድ መርጠን እንድንልክ በሰጠን ዕድል ደምሴን መርጠንለረዥምአመታት ላበረከተው አስተዋፆኦ ተሸልሟል ፡፡

ከ እግርኳስም ባ ሻ ገ ር ,,,,,,,!

ጋዜጠኛ ግርማቸው እንየው

ጋዜጠኛ ደምሴን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በ 1996 ዓ.ም ባህር ዳር ከተማ ውድድር ሲያካሄድ ለመዘገብ የመጣ ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት እንደማንኛውም ሰው በሬዲዮ በድምፅ ብቻ ነበር የማውቀው ፡፡የዚያን ጊዜ እሱ በኢትዮጵያ ሬዲዮእኔ ደግሞ በአማራ ክልል ሬዲዮ ዜናዎችን ለመዘገብ ነበር የሄድነው ፡፡

በወቅቱ በጣም የማደንቀው ሰው በአካል ለማየት በመቻሌ መንገድ ላይ እየተከታተልሁ የሚያወራውን ነገር እሰማው ነበር፡፡ አዲስ አበባ መጥቼ ኤፍ ኤም 97.1ሬዲዮ ከገባሁ በኀላ ያንን ገጠመኝ አስታውሼ ነግሬው አስቄዋለሁ ፡፡ ደምሴን እኔ እንደ ሙያ አባቴ ነው የምቆጥረው፡፡ማንኛውንም ዘገባዎቼን እየሰማ አስተያየት ይሰጠኛል ፡፡ በተለይ ብዙዎቻችን በስፖርት ፕርግራም ላይ ወደ ውጭ ሀገር እግር ኳስ ስናጋድል ፡የሀገር ውስጥ ስፖርትን መዘንጋት እንደሌለብን ይነግረንነበር፡፡ በተለይ ከ እግር ኳስ ሌላ ቦክስ፡ ቴኳንዶ ፡ የሜዳ ቴኒንስ ፡ ቴኒስና፡ ብስክሌትም
አጠቃላይ ስፖርታዊ ክንውኖች መሰራት እንዳለባቸው ይነግረናል ፡፡

ደምሴ ፣ በስፖርት ዘገባዎች በጣም የሚታወቀው በቀጥታ በሚያስተላልፈው ዘገባው ነው ፡ ከእርሱ ጋር የተወሰኑ ጨዋታዎችንም አብሬ የማስተላለፍ እድል ገጥሞኛል፡፡ ብዙ ጊዜ በቀጥታ ስርጭት ላይ ” እንደእኔ ስሜታዊ እንዳትሆን እኔ ስሜቴን መቆጣጠር እያቃተኝ ነው የምጮኸው ፤አንተ ግን በተቻለ መጠን ስሜታዊ መሆን የለብህም፤ እንደ ውም እንደ ጎርፍነህ ብታቀርብ ጥሩ ነው ” ይለኝ ነበር ፡፡

ከ አንጋፋ ባለሙያነት እስከ ስታዲየም በህዝብ መሙላት !

ጋዜጠኛ አለም ሰገድ ሰይፉ
/ የ ሊግ ስፖርት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ /

ጋዜጠኛ ደምሴ በስፖርት ዘገባዎች አንደ አርአያ የምቆጥረው አንጋፋ ባለሙያ ነው፡፡ ደምሴ ብዙ ኳሊቲዎች ( ሙያዊ ብቃቶች ) አሉት፡፡ ከሁሉም ግን በሀገር ውስጥ ስፖርት ያለው ተቆርቋሪነት ዋናው ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ስፖርት ላይ ትችት መሰንዘር ፡ የራሱ የሆነ ችግር የሚያመጣ ቢሆንም ደምሴ ግን በድፍረት ያየውን ነገር የሚተች ሰው ነው ፡፡ በሀላፊነት መንፈስ የሚሰራ በመሆኑ ብሔራዊ ቡድናችን ስታዲየም ጨዋታ ሲኖረው ህዝብ ግጥምእንዲል ያደርገዋል ፡፡ ከ 15ኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ድል በኀላየህዝቡን ስሜት እንዴት አነሳስቶት እንደነበር የሁላችን የጋራ ትውስታ ነው ፡፡፡

ከ አክብሮት የመነጨ ፍርሀት ውስጤን ይሰማኛል

ጋዜጠኛ አበበ ግደይ

ከልጅነቴ ጀምሮ የስፖርት ዘገባዎቹን እየሰማሁ ነው ያደግሁት ፡ በተለይ ጨዋታዎችን ተመልክቶ የሚሰጣቸው ግምገማዎች በጣም ይመስጡኝ ነበር ፡
ለ ጋዜጠኛ ደምሴ አክብሮት አለኝ፡፡ ሁልጊዜም ደምሴን ቃለ- መጠይቅ ላደርግ ስል ፡ የማላውቀው ስሜት ይሰማኛል፡፡ ልቤም በከፍተኛ ሁኔታ ይመታል፡፡ ከ አክብሮት የመነጨ ፍርሀት ውስጤን ይሰማኛል ፡፡

ጋዜጠኛ ደምሴ የሀገር ፍቅር ያለው ባለሙያ ነው ፡፡ የሀገር ፍቅሩንም በስራው ላይ ባሳየው ትጋት አስመስክሯል፡፡ ለሙያውም ዋጋ ከፍሏል ፡፡ ለምሳሌ ደራርቱ ቱሉበባርሴሎና ኦሎምፒክ ያሸነፈች ጊዜ ሌሊት በእግሩ ከቤቱ እስከ ሬዲዮ ጣቢያ ድረስ መሄዱ ትልቅ ምስክር ነው ፡፡ ጥርሱን በስፖርት ዘገባ ነቅሏል ለማለት ይቻላል ፡፡ ለአንድባለሙያ በህዝብ ዘንድ መወደድ ከባድ ነው፡፡ ደምሴ ግን ፍቅሩን አግኝቶታል ፡፡

ደም ያለው ጋዜጠኛ

ጋዜጠኛ መሰለ መንግስቱ

አንዳንድ የሀገራችን ስፖርት ጋዜጠኞች እግር ኳስ በሬዲዮ ማስተላለፌን አድምጠው
ኢትዮጵያዊው “ጋሪ ብሉ” ብለውኛል ፡ ” ጋሪ ብሉ ” የታወቀው እንግሊዛዊ የእግር ኳስ ኮሜንታተር ነው ፡፡ ለተሰጠኝ አክብሮት እጅግ አድርጌ እያመሰገንሁ ፡እኔ ግንይሄ ክብር የሚገባው ለ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ነው ባይ ነኝ ፡፡ ደምሴ ስሜት ያለውጥሩ የቋንቋ ችሎታ ያለው ፡ እግር ኳስን መግለፅ የሚችል ደም ያለው ጋዜጠኛ ነው፡፡ለእኔ “ሮል ሞዴሌ ” ነው ፡ የእሱን የእግር ኳስ ዘገባዎች እየሰማሁ ነው ያደግሁት ፡አንድ ቀን እንደሱ ባቀርብ እያልሁ እመኝ ነበር ፡ ደምሴ ለብዙዎቻችን የስፖርት ጋዜጠኞች በር የከፈተ ሰው ነው ፡ ከአትሌቶቻችን ጀርባ ሁሌም ያለ ሰው ነው ፡ከ ጅብ ጋር እየተጋፋየደራርቱን ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበሰረ ጋዜጠኛ ነው ፡፡

በጆሮ ማየት

ጋዜጠኛ ኤርሚያስ አማረ
/ በኢንተር ስፖርት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ /

የስፖርት ጋዜጠኝነት እንዲህ እንደዛሬው ቀላል ባልነበረበት ጊዜ ደምሴናጎርፍነህ ከፍተኛ መስዋዕትነት የጠየቀ ስራ ነው የሰሩት፡፡በተለይ ደምሴ ስታዲየምየተመለከተውን የእግር ኳስ ጨዋታ ሰኞ ማታ 2:30 ላይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሲዘግበው እንደገና የማየት ያህል ነበር ፡ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችንም ማታ በቴሌቪዥን አይተነው በአዲስ መልክ ነው ጠዋት የሚያቀርብልን ፡ ለብዙዎቻችን መሠረት የሆነጋዜጠኛ ነው ፡በግሌም ከ ደምሴ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፡ እንደ እስፖርት ሌጀንድ
ልንቆጥረው የምንችለው ነውም ፡፡

ከ ጭላሎ ተራራ ግርጌ

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ / ስላሴ

ጋዜጠኛ ደምሴ ከሀገራችን አትሌቶች ጀርባ ሁሌም አለ ፡ ድላቸውን እግር በእግር እየተከተለ ዘግቧል ፡፡ጀግናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር በሞስኮ አደባባይ በ5ሺህ ና በ10 ሺህ ሜትር ድርብ ድል ሲቀዳጅ ፡ደምሴ ድሉን ለኢትዮጵያ ህዝብያበሰረው ሲቃ እየተናነቀው ነበር ፡፡ይህ የደምሴ ድምፅ ከጭላሎ ተራራ ግርጌ እኔን ወደ ሩጫው ዓለም በወደር የለሽ ፍላጎት ጠርቶኛል ፡፡

ተስፋፊ መንገድ የጎረሳት ቤት

ጋዜጠኛ ደምሴ 40 ዓመት ከ ሁለት ወር ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት ሲጮህየመኖሩን ያህል በጡረታ መውጪያ ዋዜማው ላይ ይህ ነው የሚባል ጥሪት አልነበረውም ፡፡ የሚኖረው በቀበሌ ቤት 3 ክፍል ቤት ውስጥ ነበር፡፡ከጀርመን ኤምባሲአካባቢ የሚገኘው ቤቱ ፡ መንገድ ዳር በመሆኑ ተስፋፊ መንገድ አንዷን ክፍል ልሷታል፡፡ ጋዜጠኛ ደምሴ ከስፖርቱ ጋር በተየያዘ ብዙ ውጣውረዶችን አልፏል ፡፡ ብሔራዊቡድኑ በተደጋጋሚ ሲሸነፍ ታሟል ፡፡ በስኳር ህመም ተጠቅቷል ፡፡ ለደም ግፊት ተጋልጧል፡፡
ኳስ ያንቀረቀቡ አይኖቹ እንደበፊቱ የማየት አቅማቸው ተዳክሟል ፡፡ በመጨረሻምበሀገር ውስጥ ህክምና ፈፅሞ መዳን እንደማይችል የዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታልየ ህክምና ቦርድ ወስኗል ፡ ለጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ህክምና ከሙያ ልጆቹ እስከስፖርት ቤተሰቡ በጎ አስተዋፆኦ ተደርጓል ፡፡

የቤተሰብ ህይወት

ለ 26 ዓመታት በዘለቀው ትዳሩ አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ከባለቤቱ ከ ወ/ሮ ፀሀይነሽ መንግስቱ ሦስት ልጆችን ማፍራት ችሏል ፡፡ ተወዳጁና አንጋፋውየስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ የ እድናለሁ ተስፋ ቢያዝልም ከ 1945 ዓ.ም እስከ2005 ዓ.ም በተወለደ በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በአካለ ስጋ ተለየን ፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ደምሴ ለስፖርት ጋዜጠኞች ጥሩ ተምሳሌት ነው፡፡ ለሀገሩ ትልቅ ፍቅር ያለው 40 አመት ያለአንዳች ድካም ያገለገለ ድንቅ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ሰናጆች እምነት ደምሴ ለሙያው ጥልቅ ፍቅር ያሳደረ በመሆኑ ሙያው ሊስከብረው ችሏል፡፡ ደምሴ ከውስጥ በመነጨ ስሜት የሚሰራ ሰው ስለነበር ነገር ያምርለታል፡፡ ለዚህ ነው በስፖርት አፍቃሪያን ልብ ውስጥ ወለል ብሎ የገባው፡፡ በተለይ በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ የነበሩ የስፖርት ወዳጆች የስፖርት መረጃ ረሃባቸውን ደምሴ ያረካላቸው ነበር፡፡ በዚህ ትጋቱ እንደታላቅ ባለውለታ ይቆጠራል፡፡ ደምሴ በዚህ ሙያ ለ40 አመታት እንደማሳለፉ በሙያው ላይ በቂ ልምድ አካብቷል፡፡ በ1978 ላይ ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ በኢትዮጵያ ቲቪ ስለ አለም እግር ኳስ ዋንጫ ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ ደምሴም ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር አንድ ላይ በመሆን ይጠይቅ ነበር፡፡ ደምሴ ሬድዮ ላይ ያለአንዳች መቋረጥ 40 አመት መስራቱ ራሱ ስሙን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከ20 አመቱ ጀምሮ በዚህ ሙያ ላይ የደከመ ሰው ስለነበር ኢትዮጵያ ውለታውን እንዲህ በቀላሉ የምትዘነጋው አይሆንም፡፡ ስለ ደምሴ ይህን ግለ-ታሪክ ስንሰንድ ደምሴ ለስፖርት ጋዜጠኝነት ተፈጥሮ እሱኑ ሲሰራ የኖረ ታላቅ ሰው ብለን ልንጠራው ይገባል፡፡ አዲሱ ትውልድም ደምሴን ሲያስብ የሙያ ፍቅርን አብሮ እንዲያስብ እንሻለን፡፡ / ይህ ግለ-ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ የግለ-ታሪክ ረዳት ኤክስፐርት በአንተነህ ደምመላሽ የተጠናከረ ሲሆን ከቁምነገር መጽሄትም ሀሳቦች ተወስደዋል፡፡ የቁምነገር መጽሄት መስራች አቶ ታምራት ሀይሉ ይህ ታሪክ በዚህ መልኩ እንዲሰራ ላደረገው ቀና ትብብር ምስጋናችን ይድረሰው ›፡፡ ይህ ግለ-ታሪክ ዛሬ ቅዳሜ ጥር 28 2014 አ.ም በተወዳጅ ሚድያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *