.ነገ ቅዳሜ ታህሳስ 42018 የፍጻሜ ምርጫ ይደረጋል
.መርሀ ግብሩን ትምራን እና የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር አዘጋጅተውታል
የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበርን በፕሬዚዳንትነት እና ሥራ አስፈፃሚነት ለመምራት የሚወዳደሩ ዕጩ ሴት ጠበቆች ናቸው ትምራን ባዘጋጀው የትውውቅ መርሀ-ግብር ላይ ስለማንነታቸው ማብራሪያ የሰጡት።
ዕጬዎቹ ራሳቸውን ሲያሰተዋውቁ የከረሙ ሲሆን ቅዳሜ ታህሳስ 4 2018 በግራንድ ኤሊያና ሆቴል በሚደረገው የመጨረሻ የድምፅ አሰጣጥ የማህበሩ 2 መሪዎችና 7 ሥራ አስፈጻሚዎች ይታወቃሉ።
ለመሪነት ብቁ የሆኑ ሴቶችን በመደገፍ የሕግ ዘርፉን መጻኢ ገፅታ ለመለወጥ እንተጋለን በሚል መርህ በተዘጋጀው መርሀ-ግብር ላይ አምስት እጩዎች የሠሩበትን የሥራ ሂደትና እጩ ሆነው በቀረቡበት የሥራ ኃላፊነት ላይ ለመሥራት የተዘጋጁበትን ዓላማና ቁርጠኝነት ለትምራን አባላት፣ ለሙያ አጋሮቻቸው የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበርና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች አቅርበዋል።
ታህሳስ 2/2018 በአያ ሆቴል በተካሄደው መርሀግብር ለፕሬዘዳንትነት የሚወዳደሩ መሠረት አያሌው እና መሠረት ስዩም እንዲሁም ለሥራ አስፈፃሚነት የሚወዳደሩት ጀሚላ ክብረት፣ቤዛ ንጉሴና ማርያ ካህሣይ ናቸው ሐሳቦቻቸውን ያቀረቡት።
ዕጩዎቹ ራሳቸውን ከማስተዋወቃቸው አስቀድሞ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ እትመት አሰፋ ከሰፊ ልምዳቸው ያካፈሉ ሲሆን ዕጬዎቹ ቢመረጡ ህዝብን ማገልገል እንዳለባቸው ገልፀዋል። አክለውም ሴቶች ቦታና አጋጣሚ ካገኙ ማገልገል የሚችሉበት ዕድል መኖሩን በመጠቆም ለሴት ጠበቆቹ መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።
ካሳለፉት የሥራ ቆይታና ተሞክሮ በመነሳት ሌሎች ሴቶች ላይ የሚደርስ ውጤታማ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ የገለፁት ዕጩዎቹ ሴት እህቶቻችን በሁሉም አቅጣጫ የላቁ ሆነው እንዲገኙ ማገዝ እንደሚሹ አንስተዋል። በበጎ ፈቃደኝነት፣ በትጋት፣ በመተባበር፣ በጎ ተፅዕኖ ማሳደርና ተሰሚነትን ከፍ ማድረግ ብሎም ሚዛናዊ አሰራርን መዘርጋት ላይ በትኩረት እንሠራለን ያሉት ዕጩ ሴት ጠበቆች ሥነምግባር ያላቸው፣ ሥራቸውን የሚያከብሩ ሙያተኞችን ለማፍራት ያላቸውንም ዝግጁነት አስታውቀዋል።
በዕለቱ የታደሙ እንግዶች ለዕጩ ተወዳዳሪዎች አስተያየት እና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ዕጩ ተወዳዳሪዎችም ቢመረጡ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ቅዳሜ በሚደረገው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት መሳተፍ የሚችሉት የጥብቅና ፍቃድ ያላቸው የህግ ባለሙያዎች ሲሆኑ ዕጬዎቹ ከዛሬ ታህሳስ 4 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከነገ 2:30 የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ማድረግ ይችላሉ።
የትውውቅ መርሀ-ግብሩን ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ጋር ያዘጋጀችው ትምራን በኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የምዝገባ ቁጥር 4834 የተመዘገበችና ሴቶች በሀገሪቷ ውስጥ በሚኖሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ውሳኔ ሰጪና እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ የምትሠራ ሀገር በቀል ድርጅት ነች። ብቃት ያላት ጠንካራ ፖለቲከኛና መሪ ሴቶችን በቁጥር በዝተው እንዲገኙሜፈመ እየሠራች ትገኛለች። ዓላማዋ እንዲሳካም የሴቶችን አቅም በመገንባት፣ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ የመደገፍ ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች።
በፍትህ ዘርፉ የሴቶች አመራርነት፣ ታማኝነት እና ቁርጠኝነት ሁሉን አካታች የሕግ ከባቢ እንዲኖር በማድረግ ጠንካራ ድምፅ ይፈጥራል። ሴቶችን ለአመራርነት መምረጥ ፍትህን ያጠናክራል፣ ውክልናን ያሻሽላል ብሎም የሕግ ዘርፉ ያለበትን ማኅበረሰብ እውነታ እንዲወክልም ዕድል እንደሚፈጥር ይታወቃል።
ይህን የምርጫ ቅስቀሳ እንዲደረግና መርሐ ግብሩ ዕውን እንዲሆን ሐሣቡን ያመነጩት ጠበቃ ቤዛ ሸዋንግዛው በፌዴራል ፍርድቤቶች ጠበቃ እና የህግ አማካሪ ሲሆኑ እርሳቸውም የትምራን ሲቪክ ማህበር ምክትል ሰብሳቢ እና ትምራንን ከመሠረቱት አንዷ ናቸው።
ጠበቃ ቤዛ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባል ሲሆኑ በመርሐ- ግብሩ ላይም ይህን በጎ ሀሣብ በማፍለቃቸው በዕለቱ ምሥጋና ተቸሯቸዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማህበር ሁሉም የፌደራል ጠበቆች በአስገዳጅነት አባል የሚሆኑበት ሲሆን ከተመሠረተ ከ3አመት በላይ ያስቆጠረ ነው። ከ5000 በላይ አባላቶችም አሉት።
ስለ ተወዳዳሪዎቹ
ጠበቃ መሰረት አያሌው
የሕግ ባለሙያ መሆንን የልጅነት ህልሟ አድርጋ ያደገች ሲሆን፣ በሕግ የመጀመሪያ ድግሪን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ እና በፖለቲካል ሳይንስ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝታለች። በፍርድ ቤት በረዳት ዳኝነትና በዋና ሬጅስትራርነት ያገለገለች ሲሆን፣ በሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ሥራ አስፈፃሚነትና ም/ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም የጠበቆችን ደንብ በማሻሻል ሂደት በኮሚቴነት በንቃት ተሳትፋለች። ለፕሬዚዳንትነት ያቀረበችው ዋናው እይታ “እንደ ባለሙያ መከበር ሙያውን ማክበር”
” የሚል ሲሆን፣ ጠንካራ ማኅበር በመፍጠር የሙያውን ክብር ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጻለች።16 ዓመት የሥራ ልምድም አላት።
ጠበቃ መሰረት ስዩም
በሕግ ማማከር እና ጥብቅና አገልግሎት ከ17 ዓመታት በላይ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ልምድ አላት። የማኩታ የጥብቅና አገልግሎት ድርጅት መስራችና ማኔጂንግ ፓርትነር ስትሆን፣ በበርካታ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች ላይ አማክራለች። በአንካራ ዲክላሬሽን ፈራሚ ከሆኑ 11 የሕግ ልሂቃን ብቸኛዋ አፍሪካዊት ጠበቃ ስትሆን፣ የሪፎርም አማካሪ ጉባኤ አባል በመሆን በርካታ አዳዲስ ህጎች (እንደ ጸረ-ሽብር፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የንግድ ህግ፣ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት እና የፌዴራል ጥብቅና አዋጆች) እንዲረቀቁ የበኩሏን አበርክታለች። ለፕሬዚዳንትነት ከተመረጠች የአባላትን መብት ማስከበር፣ አቅም ማጎልበት፣ ገቢ ማሳደግ እና ጠበቆች በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ያላቸውን ሚና ማጎልበት ላይ እንደምትሠራ ቃል ገብታለች።
ጠበቃ ማሪያ ካህሳይ ገብረጊዮርጊስ
የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዋን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኘች ሲሆን፣ በጠቅላላው ለሰባት ዓመታት በዳኝነት (በመጀመሪያ ደረጃና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ረዳት ዳኝነትና ዳኝነት) አገልግላለች። ከዚያም ወደ ግል ዘርፍ በመዛወር ከአስራ አራት ዓመታት በላይ በጠበቃነት ልምድ ያካበተች ሲሆን፣ ከስምንት ዓመታት በላይ ደግሞ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ነጻ የሕግ ድጋፍ በመስጠት ማኅበራዊ የሙያ ኃላፊነቷን ተወጥታለች።
ጠበቃ ወ/ሮ ቤዛ ንጉሴ ደምሴ
በሕግ የ18 ዓመታት ልምድ ያላት ሲሆን፣ ከተመረቀች በኋላ በጋዜጠኝነት፣ ከዚያም በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሕግ ኤክስፐርትነት እና ረዳት ዳኝነት አገልግላለች። በፍርድ ቤት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ፣ የመጽሄት አዘጋጅ እና የጾታ ጉዳዮች ም/አስተባባሪ በመሆን የላቀ ተሳትፎ አድርጋ የአመቱ ምርጥ ሰራተኛ ተሸላሚ ሆናለች። በመቀጠልም ለ11 ዓመታት በፍርድ ቤቶች ጥብቅና ሰጥታለች። በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ዋና ፀሀፊነት፣ እንዲሁም በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕግ አማካሪ ጉባኤ ውስጥ አባል በመሆን አገልግላለች።
ጠበቃ ወ/ሮ ጄሚላ ክብረት
በሕግ ሙያ የ16 ዓመታትና በጥብቅና ሙያ ደግሞ የ10 ዓመታት ልምድ አላት። በዓለም አቀፍ የኢንሹራንስ ኩባንያ የሕግ ክፍል ኃላፊነትና ለዘጠኝ ዓመታት የዳይሬክተሮች ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን በአመራር አገልግላለች። እንዲሁም የዘምዘም ባንክ የመጀመሪያ የምርጫና የሹመት ኮሚቴ ሊቀመንበር በመሆን የሥራ አመራር ብቃቷን አሳይታለች። የጀሚላ ክብረት እና አጋሮች (JKP) መስራችና ማኔጂንግ አጋር ስትሆን፣ ድርጅቷን በኮርፖሬትና በፋይናንስ ዘርፍ የሕግ አማካሪነት በመምራት ላይ ትገኛለች። ሥልጠናዎችን በለንደንና በአሜሪካ በመከታተል እንዲሁም በእስላማዊ ፋይናንስ ልዩ የምስክር ወረቀት በማግኘት ዓለም አቀፍ ልምዶችን ከኢትዮጵያ አውድ ጋር አዋህዳለች።