አምባሳደር አሊ አብዶ (1948-2018)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ኢንሳይክሎፒዲያ በተሰኘ ፕሮጀክቱ በመንግስታዊ የሥራ ኃላፊነት የተወጡ ግለሰቦችን የሕይወት ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። በከንቲባነት፣ በአምባሳደርነት እና በቢሮ ኃላፊነት ያገለገሉ ሰዎችን የሠሩትን ሥራ እያስተዋወቅን ለትውልድ ለታሪክ እናስቀምጣለን። በዚህ መሠረት 27ኛው የአዲስ አበባ ከንቲባ ስለነበሩትና ዛሬ ሕይወታቸው ስላለፈው አምባሳደር አሊ አብዶ ተከታዩን ታሪክ እናጋራለን። ፅሑፉን ስናዘጋጅ ትልቅ ትብብር ያደረገልን ወዳጃችን ጋዜጠኛ ጀማል አህመድ ሲሆን እርሱ በጀማል ሾው አቶ አሊ አብዶን ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ስለነበር እርሱ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ለእኛ እንደሚስማማ አድርገን አቅርበነዋል። ታሪኩንም ሂላሪያ ተስፋዬ እና ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንደውታል።

ትውልድ እና እድገት

ትውልድና እድገታቸው በአርሲ ዶዶታ ወረዳ ዴራ በምትባል ከተማ ነው። አባታቸው አቶ ዓሊ ሱለይማን፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ አፀደ ወልደማሪያም ይባላሉ። በሥነምግባር ታንጸው ካደጉበት ቤተሰብና ከተማ ተነጥለው የወጡት፣ በዚያው ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ነው፤ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና አምባሳደር ዓሊ አብዶ።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ቀጥለውም 10ኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ፣ በሰዓቱ ተግባራዊ ይደረግ በነበረው የትምህርት ሥርዓት መሠረት በ1965 ዓ.ም ሀረር ወደሚገኘው የመምህራን ማሠልጠኛ ተመደቡ። የመምህራን ማሠልጠኛ ቆይታቸውም በሀረር ይጀመር እንጂ የተቋጨውና የሁለተኛውን ዓመት ትምህርት የተከታተሉት በደብረ ብርሃን የመምህራን ማሠልጠኛ ነበር።

የመምህርነት ሙያ

በመምህርነት ሙያ የሥራውን ዓለም አንድ ብለው የጀመሩት አምባሳደር ዓሊ፣ በቀድሞ ከፋ ተመድበው ወደ ጅማ በማቅናት ለአምስት ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል። ከዚህ በኋላ ራሳቸውንም በትምህርት ለማሳደግ በማሰብ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉ ሲሆን፣ የትምህርቱ ጉዞ ግን እንዳሰቡት አልጋ በአልጋ አልሆነም። በዚህ መካከል ነው በአዲስ አበባ ናዝሬት ስኩል የመምህርነት የሥራ እድል ያገኙት። በዚያም በቆዩበት የ10 ዓመታት የመምህርነት አገልግሎት፣ በመካከል በርቀት የማኔጅመንት ትምህርት ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።

ወደ ሰላምና መረጋጋት

በ1983 ዓ.ም ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣ ጊዜ ነገሮች አዲስ መስመር ያዙ። አምባሳደር ዓሊ፣ በሰዓቱ ኢሕአዴግ የነበረውን አለመረጋጋት ለማስከን በሰላምና መረጋጋት ዙሪያ የሚሠራ ኮሚቴ ሲመሠረት፣ እርሳቸው የኮሚቴ አባል ሆነው የመመረጥ እድል አገኙ። በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ላይም በጸሐፊነት ለተወሰኑ ወራት አገለገሉ። በኋላም የተፈለገው ሰላምና መረጋጋት ሲመጣ፣ የሥራ ድርሻቸው ወደ አዲስ አቅጣጫ ጠቆመ። በ1984 ዓ.ም ማጠናቀቂያ የወረዳው አስተዳደር ምክትል ሆነው ተመርጠው ለግማሽ ዓመት በኃላፊነት ተቀመጡ። ‘ሹመት ያዳብር’ እየተባሉ ሳይመረቁ አልቀረም፣ ቀጥሎም ለክልል ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተመረጡ።

ምክትል ከንቲባ እና ከንቲባ

በ1985 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ ለምክትል ከንቲባነት በቁ።
ያንን ጊዜ መለስ ብለው ባስታወሱበት አንድ ቃለመጠይቅ ላይ፣ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ይኑራት እንጂ የተደራጀ የከተማ አስተዳደር ያልነበረ በመሆኑ ሥራው እንደ አዲስ የመጀመር ያህል እንደነበር ጠቅሰዋል። “አደረጃጀቱ እንደ አሁን አልነበረም። የመጀመሪያ አንድ ዓመት ተኩል ቢሮ በማደራጀት፣ የሰው ኃይል በማሟላት እና አሠራር በመዘርጋት ነበር ጊዜ የወሰድነው።” ብለዋል።

እርሳቸውም በእነዚህ ሥራዎች ውስጥ እንደ ምክትል ከንቲባነት የራሳቸውን ድርሻ ተወጥተዋል። በኋላ በሰዓቱ ከንቲባ የነበሩት ተፈራ ዋልዋ ወደ ፌዴራል ደረጃ ለሥልጣን ሲሰየሙ፣ አምባሳደር ዓሊ የከንቲባነት ኃላፊነት በሙሉ ተረከቡ። በምክትልነት አምስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላም በከንቲባነት ተጨማሪ አምስት ዓመት ተኩል ሠርተዋል።

አስተዋፅዖ

በዚህም በከተማዋ የሚስተዋለውን ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የንጽህና ጉድለትና የመሳሰለውን ችግር መቅረፍ አንዱና ዋናው ትኩረታቸው አደረጉ። ከከተማ ልማት ጎን ለጎን ሥራ እድል ፈጠራ ላይ በመሥራት እንዲሁም አነስተኛ ብድር እና መጠነኛ ሥልጠና በመስጠት በተቻለ አቅም የሥራ እድል መፍጠር ላይ ሠርተዋል።

ትልቁ ፈተና የነበረው የከተማው ሕዝብ ቁጥር መጨመርና የውሃ አቅርቦት አሳሳቢ መሆን ነበር። ይህን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን፣ የተደረጉ ጥናቶች ያለውጤት ይቀሩ ነበር። በኋላ የትኩረት አቅጣጫውን በመቀየርና በከርሰ ምድር ውሃ ላይ በማተኮር፣ ‘ድሬ ግድብ’ እንዲገነባና አገልግሎት እንዲሰጥ በማስቻል አስመርቀዋል። በአዲስ አበባ የቀለበት መንገድ ግንባታ ሂደት እንዲሁም ማስተር ፕላን ዝግጅት ላይ የባለሞያዎችን ድጋፍ በማስተባበር ላይም የራሳቸውን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ከዚህም ባሻገር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ፍቅርና አክብሮት አንዲያገኙ ያስቻላቸው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ያስገነቧቸው መስጂዶች ናቸው። በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው ኢሕአዴግ በእስልምና አካባቢ የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥሩ ይመልስ እንደነበር ይናገሩ የነበሩት አምባሳደር ዓሊ፣ መስጂዶች እንዲገነቡ ቦታ በመፍቀድና በመስጠት ሂደት አቅደው ያስፈጻሟቸው ተግባራት በርካታ ናቸው። በዚህ መሠረት ጦርኃይሎች ጨምሮ እና ሲኤምሲ፣ ቄራ፣ መገናኛ እንዲሁም ዓለምባንክ ያሉ መስጂዶች በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን የተሰጡ የመስጂድ ግንባታ ቦታዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።

አምባሳደር

አምባሳደር ዓሊ አብዶ ከከንቲባነት ሥራቸው ባሻገር በአምባሳደርነትም ሀገራቸውን አገልግለዋል። ከአዲስ አበባ የከንቲባነት ሥራ ከተሰናበቱ በኋላ ለሦስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል መንግስት በማስተባበሪያ ቢሮ በዋናነት በኢንዱስትሪ እና ትራንስፖርት ልማት ዘርፍ ላይ በኃላፊነት ሠርተዋል። በቆይታቸውም ከሁሉ ከሁሉ የአበባ ልማት ተጀምሮ እንዲስፋፋ ያደረጉት እንቅስቃሴ ከምንም በላይ እንደሚያስደስታቸው ይናገሩ ነበር።

ከዚህ ቀጥሎ ነው ወደ ፌዴራል የሥራ ኃላፊነት ተሻገረው ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቀላቀሉት። በዚያም የአምባሳደር ሹመት ተሰጣቸውና ለመጀመሪያ የአምባሳደርነት ኃላፊነት ወደ ሱዳን አቀኑ። በሱዳን እርሳቸውም እንዲሁም ቤተሰባቸው ጥሩ ጊዜ ማሳለፋቸውን ይናገሩ የነበሩት አምባሳደር ዓሊ፣ ከምንም በላይ በሱዳን የኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብን ማሰባሰብና ማስተባበር መቻላቸው ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል። ከጀማል አህመድ ጋር ባደረጉተሰ ቃለመጠይቅ ላይ ይህን በተመለከተ በሰጡት ሐሳብ “ሥራው ሰፊ ነው። የኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከ100 ሺህ የማያንስ ነበር። በየአቅጣጫው እየተንቀሳቀስኹ በሱዳን የተበታተነውን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማሰባሰብ ችያለሁ። ይህም ትልቁ የሠራሁት ሥራ ነው።” ብለዋል።

ሱዳን ተመድበው በሄዱ ወቅት ኤምባሲው አንገት የሚያስደፋ ሁኔታ ውስጥ ነበር። ይህንን ታሪክ ለመቀየርም የዲፕሎማት ሚናቸውን በአግባብ በመወጣት በሱዳን መዓከል ላይ ከ15 ሺህ ካሬሜትር በላይ የሚሆን ቦታ ተቀብለዋል። በዚያም ላይ በሁለት ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ያስቻሉ ሲሆን፣ ኤምባሲው በውበት እና በመገኛው በከተማዋ ደምቆና ጎልቶ የሚታይ ስፍራ ለመሆን ችሏል። አምባሳደር ዓሊ ከዚህም ባሻገር በኤምባሲው ውስጥ ኢትዮጵያዊያን የክበብ ሥራ እንዲሠሩ ቦታ ሰጥተዋል።

ከሱዳን ቀጥሎ በተመሳሳይ የዲፕሎማሲ ሥራ ባቀኑበት ናይጄሪያም የነበራቸው ቆይታ ውጤታማ ነበር። በናይጄሪያ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ባይኖሩም የሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ጋር የተያያዙ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ችለዋል። በሰዓቱ የነበረውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ በማስተባበርም የድርሻቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል።

ከዚህ ባሻገር ትልቁ ውጤታማ የሆኑበት ጉዳይ፣ የቀደሙ ዲፕሎማቶች ጀምረውና ሞክረው የነበሩትን የዳንጎቴ ኢንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ የማምጣት ሥራን ማጠናቀቅ ነበር። ከዚያ ቀደም ባለሀብቱ ዓሊኮ ዳንጎቴ ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ በተደጋጋሚ የመጣ ቢሆንም፣ ውሳኔውን እንዲያጸና በማድረግ የእርሳቸው ሚና ትልቅ ነበር። በተለይም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንዲገናኝ እና እንዲነጋገር በማድረግ ውሎች እንዲፈጸሙ ማድረግ ችለዋል።

አምበሳደር ዓሊ አብዶ ከእነዚህ ሁሉ ተግባራት በኋላ ከመደበኛ ሥራቸው በጡረታ ተገለሉ። ምንም እንኳ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በሥራቸው እንዲቀጥሉ ተፈልጎ የነበረ ቢሆንም፣ ከነበረባቸው የጤና እክሎች (ስኳር እና ደም ግፊት) ጋር በተያያዘ እረፍት ማድረግን መረጡ። ያም ሆኖ ጡረታ ከወጡ በኋላ በዳንጎቴ በአማካሪነት ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል። በኋላም በተከተሉ ዓመታት ብዙ ጊዜያቸውን በማኅበራዊ ጉዳይ እና ለቤተሰብ ጊዜ በመስጠት አሳልፈዋል።

27ኛው የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት አምባሳደር ዓሊ አብዶ፣ በ1971 ዓ.ም ከሚስራቅ ያሲን ጋር በመሠረቱት ትዳር የሦስት ሴቶች እና አንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ። አምባሳደር ዓሊ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ሌሊቱን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *