በኢትዮሚድያ አዋርድ በዜና ዘገባ ምርጥ 5 ውስጥ ከገቡት አንዱ
ኮሰን ብርሀኑ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ፣ ከመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የሥራ ታሪክ ጋር በተያያዘ መረጃ ሰጪ ጽሁፎችን ሲያዘጋጅ ነበር ።
ሀገራችን ውስጥ የሽልማት ውድድሮች ሲዘጋጁም በፕሮፋይል ስነዳ ላይ እንደ ተቋም ግለ -ታሪኮችን አጠናክሮ ለንባብ በማብቃት ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ሲያሳካ ቆይቷል።
ይህን የምናከናውነው በተወዳጅ ሚድያ መስፈርት መሠረት ሲሆን ባለፈው አንደኛው ዙር ላይ እንዳደረግነው ተስፋ የሚጣልባቸውን ወጣት የሚድያ ሰዎችን ጨምረን ማንነታቸው መታወቅ ያለባቸውን ባለሙያዎች አለፍ አለፍ እያልን እናስተዋውቃለን። ይህ ማለት ሁሉም ምርጥ 5 ውስጥ የገቡትን እናስተዋውቃለን ማለት አይደለም። ይልቁንም ፣በአንደኛው ዙር የህይወት ታሪካቸውን ያልተዳሰሱ ባለሙያዎችን በዚህ ዙር ቅድሚያ እንሰጣለን።
ይህን የምናከናውነው፣ በራሳችን ተነሳሽነት እና “ከመምረጥ በፊት የዕጩን ማንነት ማወቅ” የሚለውን መሪ ርዕስ ተግባራዊ ለማድረግ በማሰብ ነው።
ከድርጅታችን ቀዳሚ ግቦች አንዱ ፣ታሪክን መሠነድ ስለሆነ ፣ይህንኑ ተልዕኮ እናስፈጽማለን ። ይህን በውድድር ወቅት የሚደረግ የማስተዋወቅ ሥራ ስንሠራ ከማንኛውም አካል ምንም ዓይነት ክፍያ የማንቀበል ሲሆን ይልቁንም ለዚህ ሥራ ጊዜ እና ባለሙያ በመመደብ ሙያዊ ግዴታችንን እንወጣለን። ይህ ጽሁፍ የምርጫ ቅስቀሳን የማድረግ ግብ የሌለው ሲሆን ይልቁንም የአንዳንድ ተወዳዳሪዎችን ማንነት የማሳወቅ ግብ የሰነቀ ነው። ኮሰን ብርሀኑ በሚድያ አዋርድ በዜና ዘገባ ምርጥ 5 ውስጥ ከገቡት አንዱ ነው፡፡
በ1982 ዓ.ም የካቲት 18 በመዲናዋ አዲስ አበባ የተወለደው ኮሰን በተለያዩ የግል ት/ቤቶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። በትምህርቱም ፈጣንና ጥሩ የሚባል ተማሪ ነበር። ለእንግሊዝኛና ሥነ ጥበብ ነክ ትምህርቶች ፍላጎት የነበረውና ‹‹ታላቁ ፊልም›› እየተባለ የሚታወቀውን ቅዳሜ ማታ በኢቲቪ የሚተላለፈውን ፊልም ማየት ብቻ ሳይሆን ከየፊልሙ አዲስ አምስት የእንግሊዝኛ ቃላትን በመመዝገብ የፊልሙን መቼት ለቤተሰቦቹ በፅሁፍ ካሰፈረው በማስረዳት ልጅነታቸውን ካሳለፉ ብዙ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው። ለቤተሰቡም የበኩር ልጅ ሲሆን አስቸጋሪና ደፋር ልጅ እንደነበር ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በከፍተኛ አዘጋጅነት እያገለገለ የሚገኘው ኮሰን የትዳር አጋሩም በዛው ተቋም የምትሰራው ጋዜጠኛ ሜሮን በረዳ ነች። ኤብላ የምትባል የሶስት ዓመት ሴት ልጅም አፍርተዋል።
ኮሰን ብርሃኑ በሚዲያ ሙያ ከ8 ዓመት በላይ ሠርቷል። በ2007 ዓ.ም የማስተርስ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ተግባቦት በከፍተኛ ነጥብና የጥናት ውጤት እንደተመረቀ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን ተቀላቀለ።
በአዲስ አበባ አማኑኤል ቶታል አካባቢ የተወለደው ኮሰን የመጀመሪያ ዲግሪውን ከደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛና በውጭ ቋንቋዎች ስነ ፅሁፍ አግኝቷል። በግል ትምህርት ቤቶችም በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት አገልግሏል።
የሥራ ልምዱ ከሪፖርተርነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ አዘጋጅነት አድርሶታል። የምርመራ ፣ የግጭት ፣ የፖለቲካ፣ የድርቅ እንዲሁም ሰብዓዊ መብት ነክ ዘገባዎችን በስፋት ሰርቷል።
የምርመራ ዘገባውን የየስ ውሃ ፋብሪካ ሠራተኞች ያለአግባብ ከሥራ መሰናበት ቅሬታን በማጋለጥ ነበር ጉዞውን የጀመረው። በመቀጠል የጎጃም ባህል ማዕከል ግንባታ መጓተት እንዲሁም በርካታ ተፅእኖና ለውጥ ያመጡ ዘገባዎችን ሠርቷል። የአስቸኳይ ፓስፓርት እድሳትና የአርባ ሺህ ብር የሙስና ሰንሰለትም ከሥራዎቹ አንዱ ሲሆን ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተቋም አመራሮችን የማንሳት ውሳኔና በመቶዎች የሚቆጠሩ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ሲል እንዲውሉ ማድረግ የቻለ የምርመራ ዘገባ ነበር።
ከግጭት ዘገባ ጋር ተያይዞ፣ በሰሜኑ ጦርነት በአክሱም፣ በጋሸናና በአፋር ክልል ተገኝቶ በኢትዮጵያ የግጭት ዘገባ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ጦርነቱ ውስጥ በመግባት (War zone reporting) ለህዝብ አሳይቷል። ከዚህ ባለፈም፣ በጦርነቱ ወቅት የነበረውን ሰብዓዊ ቀውስ በማሳየት በተለያዩ ዜናዎች ያካተታቸው የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ ሶስት ቤተሰቦች የተመልካችን ልብ ከማሳዘን አልፎ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ አድርገው ቤታቸው እንዲሰራላቸው የማድረግ ኃላፊነትን ወስዶ ቤት አሠርቷል። በዚህም ከሚሠራበት ተቋም በተጨማሪ፣ ከመከላከያ ሚኒስትርና ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዕውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቶታል።
ከድርቅ ጋር ተያይዞ በቦረና፣ በሶማሌ ክልልና ኮንሶ በመገኘት ድርቁ የፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ በማሳየት ለችግሩ መንግስትና ህዝብ እንዲረባረብ ያደረጉ ዘገባዎችንም ሠርቷል። በኮንሶ አካባቢ በሠራው የድርቅ ዘገባ በመጀመሪያው የኢጋድ ሜዲያ አዋርድ በመወዳደር አሸንፏል ፤ የእውቅና ሰርተፍኬትና የብር ሽልማት አግኝቶበታል።
ኮሰን ተግባቢ፣ ችግሮችን መቋቋም የሚችልና ወደ እድል የሚቀይር እንዲሁም መፍትሄ ተኮር እንደሆነ የሥራ ባልደረቦቹና የሚያውቁት ይናገሩለታል። ማህበረሰብ የዜና ምንጭ ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኛም ነው ብሎ ያምናል። ዋናው ጉዳይ የነፃነትና ኃላፊነትን ሚዛን እንዲጠብቁ ማስተማር ወሳኝ መሆኑን ይናገራል። ለዚህም በሙያውና በግሉ የትምህርት ዘርፍ መካከል ያለውን ስስ ግንኙነት የራስ አሻራን በማሳረፍ ለመቀየር ዕቅድ እንዳለው ይናገራል።