የዚህ ጽሁፍ ባለመብት እና አዘጋጅ ተወዳጅ ሚድያ ነው፡፡ ሚድያዎች ምንጭ ጠቅሰው ብቻ ጽሁፉን መጠቀም ይችላሉ፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ እያዘጋጀ ለህትመት ሲያበቃ ነበር፡፡ በሀምሌ 2014አ.ም ‹‹መዝገበ-አእምሮ›› በሚል ርእስ በጠንካራ ሽፋን የተዘጋጀ የመጀመሪያው የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የቦርድ አባላት ያጸደቋቸውን ባለሙያዎች በመያዝ ታሪካቸውን ይሰንዳል፡፡ ይህ የስነዳ ፕሮጀክት በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረት ሲሆን ባለ ታሪኮችን በማስፈቀድ የሚሰናዳ ነው፡፡ የተቀመጡትን መስፈርቶች የሚያሟሉ የሚድያ ሰዎች ታሪካቸው ከምስል ጋር በተወዳጅ ሚድያ የዲጂታል ሚድያዎች እና በመጽሀፉ ላይ ይቀመጣል፡፡ ታሪካቸው በቅጽ 2 መዝገበ አእምሮ ላይ ከሚሰነድላቸው መካከል ያሁኑ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ነው፡፡
ሀገራችን በዚህ ዘመን ካፈራቻቸው የለውጥ ሞተር ከሆኑ ባለሞያዎች መካከል ዛሬ በመሪነት ደረጃ የተቀመጠውን ባለሙያ በብዕራችን ከትበን ይዘን ስንመጣ በየቦታው ያሉ በርካታ ትጉሀንን እያስታወስን ነው፡፡የሚድያ ሰው አቶ ጌትነት ታደሰ ከእነዚህ ጠንካራ ባለመያዎች አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን የተሾመው አቶ ጌትነት ከ2010-2016 ታህሳስ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን ለ6 አመት ያገለገለ ሲሆን ከዚያ በፊትም በዋልታ ሚድያ እና በአማራ መገናኛ ብዙሀን በጠቅላላ ለ20 አመት ያገለገለ ነው፡፡ ከሪፖርተር ደረጃ እስከ ዋና ሰራ አስፈጸሚ በሁሉም ደረጃ አቅሙን ያሳየው አቶ ጌትነት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ለጥሩ ስኬት ማብቃቱ ይነገርለታል፡፡ በሙያው ታታሪ የሆነው አቶ ጌትነት አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በዋና ስራ አስፈጻሚነት እንዲመራ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ጽሁፍ በሚሰናዳበት ጊዜም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ-መሀላ ፈጽሟል፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በአቶ ጌትነት ላይ ይህን የህይወት ታሪክ ጥናት ማካሄድ ከጀመረ 2 አመት ተቆጥሯል፡፡ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና ጋዜጠኛ ባንቺአየሁ አሰፋ የአቶ ጌትነትን ታሪክ እንደሚከተለው አሰናድተውታል፡፡
‹‹…..ገና በልጅነት ዕድሜዬ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነበር የጋዜጠኝነት ሙያን የጀመርኩት›› ይላል አቶ ጌትነት ታደሰ፡፡ በሙያው ወደ 20 ዓመት ገደማ አገልግሏል። አመለ ሸጋው ፣ ቁጥቡ ፣ አስቦ ተናጋሪውና ጨዋታ አዋቂው የባለ ብዙ ተሰጥኦ ባለቤቱ ደማሙ ጋዜጠኛ ። በዚያ በለጋ ዕድሜው የጀመረው ጋዜጠኝነት ዛሬ ላይ በከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ታሪኩንም አንድ ብሎ ሲተርክልን ስንት ታላላቆች ባሉበት የእኔ ሚና ትንሽ ነው፤ ቢሆንም ለትውልድ ከጠቀመ ማካፈል እችላለሁ ሲል ወግ ጀመረልን፡፡
ትውልድ
በሀገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ምስራቅ ጎዣም ዞን በትንሿ የገጠር ከተማ አማኑኤል ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ አራት (1974) መጋቢት 5 ቀን ነበር የተወለደው ።
ጌትነት በከተማ ውስጥ የተወለደ ቢሆንም የከተማዋ አናሳ መሆን የገጠራማ አካባቢውን የኑሮ ዘይቤ ለማወቅ ጥሩ ዕድልን ፈጥሮለታል። እንደ ከተማ ልጅ በብይ እና በአሻንጉሊት ሳይሆን አፈር ፈጭቶ ፣ ጭቃ አቡክቶ፣ ውኃ ተራጭቶ ከከተማና ከገጠር ልጆች ጋር ለማደግ ችሏል። በኋላም እንደማንኛውም ህፃን ዕድሜው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ በአማኑኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እውቀት ገበታ ላይ ቀርቦ ነበር። ቀጥሎም ወደአማኑኤል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አቅንቶ በዚያም የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል ።
ልጅነት
አባቱ በንግድ ሥራ የተሰማሩ በመሆናቸው ጌትነትም የንግዱን ዓለም የተቀላቀለው ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ስለነበር ከትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜ የሚያሳልፈው በሱቅ ውስጥ በመሸጥ ሆነ። ሱቋ ታዲያ ከሚሸጥና ከሚለወጥ እቃ በተጨማሪ የመጽሐፍት እና የጋዜጣ ማንበቢያ እንዲሁም መደርደሪያና የሬድዮ ማዳመጫ ቦታ ጭምር በመሆን ለተማሪው ጌትነት ታገለግል ነበር ።
በዚያን ጊዜ የአካባቢው ትምህርት ማሰራጫ ጣቢያ ቅዳሜና እሁድ የሚያስተላልፈው የትምህርት ክፍለ-ጊዜ ሳይሆን መዝናኛ ስለነበር የዕለተ ሰንበቱ የሬድዮ ንጉስ በሆነው መምህር መዝሙር ሃዋዝ የሚቀርቡ የዝክረ- ሰንበት እና ማህደረ ሰንበት ፕሮግራሞችን በሱቅ ውስጥ እየሸጠ በልዩ ፍቅር እያደመጠ አደገ።
የሚድያ ዝንባሌ
ታዲያ ቅዳሜ ቅዳሜ የጌትነት ጆሮና ልብ ትኩረቱን የሚያደርገው በሬድዮ መዝናኛ ላይ ስለነበር የሱቁን ደንበኞች በአግባቡ ለማስተናገድ ይቸገር ነበር ። ነፍስና ስጋው በስሜት ሲጣበቁ እርሱ በመካከላቸው አሸልቦ ሲጠሩት ቶሎ እስካለመንቃት እሩቅ ይጓዝ ነበር። ጌትነት የሰንበቱን ጋዜጠኛ መዝሙር ሃዋዝን ድምፅ ከመውደዱ የተነሳ የእሱ ድምጽ ለሬድዮ የተፈጠረ ነውም ይለዋል ። ከድምፁም ባሻገር ለሬዲዮ የሚልካቸውን ጠንካራ ብዕሮች በጌትነት ነገ ላይ የራሳቸውን መሰረት እየጣሉ ሄደዋል። በልጅነቱ ካደመጣቸው የልጅነት ጊዜውን ከሚያስታውስባቸው ባለውለታ ጋዜጠኞች አንዱ ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።
ጋዜጠኝነቱን በይፋ አወጀ
ጌትነት ታዋቂ እና ትልቅ ሰው የመሆን ህልም ስለነበረው በሱቅ ውስጥ የነበሩትን ጋዜጦች በማውጣት የአካባቢውን ልጆች ሰብስቦ ለእነርሱ በመንደር ውስጥ በመተረክ እምብዛም ሳያውቀው ጋዜጠኝነት ቀስበቀስ በውስጡ እያጎለበተ መጣ ። እልፍ ሲል በትምህርትቤቱ በሚዘጋጁ ጉዞዎች ወቅት የነበረውን ሂደት በዜና መልክ ሰርቶ ጠዋት በሰልፍ ላይ በመንገር በአብሮ አደጎቹ ፣ በመምህሮቹ ፣ በክፍል ጓደኞቹ ፊት ጋዜጠኝነቱን በይፋ አወጀ ።
በተጨማሪም በትምህርቤት ውስጥ ባቋቋሙት ‘ ስድቱሙ ‘የተሰኘ ክበብ አማካኝነት የነቃ ተሳትፎን ያደርግ እንደነበር ይናገራል ። ስድቱሙ ምህፃረ ቃል ሲሆን የእያንዳንዱ ትርጉም ደግሞ ይህን ይመስላል ።
ስ- ስነፅሁፍ
ድ-ድራማ
ቱ-ቱሪዝም
ሙ-ሙዚቃ
ጋዜጠኛ ጌነትነት ታደሰ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ ለኪነ-ጥበብ ልዩ ዝንባሌ ስለነበረው ዜና፡ ከማዘጋጀት እና ከማቅረብ ባለፈ ልቡ ወደትያትር ጥበብም ታጋድላለች። የሼክስፒርን እና የሌሎችን የዓለማችንን ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች በውርስ ትርጉም በመተርጎም በወረዳዎች ላይ በሚኖር የመምህራን ስብሰባ ፤ የሰራተኞች ስብሰባ ፤ የህዝብ በአላት ጊዜ ፤ ተውኔቶችን፣ ሙዚቃዎችን፣ ፅሑፎችን በማቅረብ ጎን ለጎን ትምህርት በመማር ሱቅ ውስጥ በመነገድ አሳለፈ።
በኋላም በ1993 ዓ.ም ተወልዶ ካደገባት ትንሿ አማኑኤል ከተማ 28 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘዋ የወቅቱ ታላቅ የኪነ-ጥበብ ማዕከል ወደሆነችው ደብረማርቆስ አቀና ። የጉዞው ዓላማ ትምህርትን ለማሻሻል ለሚደረግ ጥናት ቢሆንም የደብረማርቆስ የኪነ-ጥበብ ማዕከል የጋዜጠኝነት ሙያን ያሰለጥን ስለነበር ጌትነት ይህን አይቶ ለማለፍ አልቻለም ። ክፍያውን ከፍሎ የሚሰጠውን ስልጠና ለ2 ወራት የተከታተለ ሲሆን በድጋሚ በዓመቱ ስልጠናውን ለሁለተኛ ጊዜ በዚያው ወስዶ አጠናቋል።
ምንም’ኳ ታዋቂ እና ስመጥር ተዋናይ የመሆን ራእይ ቢኖረውም አንዳንድ ሰው ባላሰበበት ይውላልና ጌትነት ስልጠናውን እንዳጠናቀቀ በአካባቢው በሚገኘው ራባ ሬድዮ ጣቢያ ስቲድዮ በመግባት ራሱ ፅፎ ያዘጋጀውን ልብ-ወለድ በመተረክ ጋዜጠኝነትን ሊጀምር ችሏል ። በአካባቢው እየሰበሰበ ፊትለፊታቸው ቁጭ ብሎ ጋዜጣ ያነብላቸው የነበሩ ባልንጀሮቹ ፤ በትምህርትቤት ሰልፍ ላይ ዜና ዘግቦ ያነብላቸው የነበሩ ጓዶቹ አሁን የያኔውን አኳኋን በዓይነ-ህሊናቸው እየሳሉ የወረቀት አያያዙን ፤ የከንፈር እንቅስቃሴውን እያስታወሱ ድምፁን በሬድዮ ያደምጡት ያዙ።
ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ
ጌትነት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ትያትርና ጥበባትን መማር ቢፈልግም ይህ ሳይሆን ቀርቶ በ1995 ዓ.ም ወደባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተጉዞ ታሪክ በማጥናት በ1997 ለመመረቅ ችሏል ። በተመረቀ ሰሞን ደግሞ በሚኖርበት የባህርዳር ከተማ የባህርዳር ኮሙኒኬሽን ለአማራ ብዙሃን መገናኛ በፈቃደኝነት የሚሰሩለት ጋዜጠኞች እንደሚፈልግ የሰሙ ጓደኞቹ መረጃውን ያጋሩታል ። እርሱ ግን ቢሰማም ለሥራው ልቡ አልደነገጠም። ምክንያቱም ይላል ጌትነት
” ምክንያቱም እኔ ገጠር ገብቼ ለአንድ ዓመት ያህል ማስተማር እፈልግ ነበር ። በማስተምርበት ወቅት ገጠር ላይ ያለውን ቋንቋና ባህል እንዲሁም ዘዬ ጠልቄ ለመመራመር ያስችለኛል ።ይህን የምፈልገው በኋላ ለምሰራው ስራ ያግዘኛል በሚል እሳቤ ነበር ።” ይላል።
ነገር ግን ጓደኞቹ በራሳቸው ፈቃድ መረጃዎቹን ወስደው አስመዝግበው እንዲፈተን አደረጉት ። እርሱም ከ4 አመልካቾች መካከል ጥሩ ውጤት በማምጣት ከሌሎች ሁለቱ ጋር በመሆን ለማለፍ ቻለ።
ወደ አማራ መገናኛ ብዙሀን
ከዚህ በኋላ እና በእንዲህ አይነት አጋጣሚ ነው ጌትነት ታደሰ አማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅትን በጥልቀት ለመቀላቀል የቻለው ፡፡ ባለው ተወዳጅ ድምፅ ምክንያት ተመራጭ በመሆን ሬድዮ ላይ የመስራት ዕድሉን አገኘ፡፡ ብዙሃን መገናኛ ውስጥ ስራውን በይፋ የጀመረው የሬድዮ ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ በባህርዳር ኤፍሬም 96.9 ላይ የከተማ አስተዳደሩን ፕሮግራም ማዘጋጀት ጀመረ ። ጎን በጎን ለበኩር ጋዜጣ ደግሞ የብዕሩን ውጤቶች መላክ ያዘ።
ይህም ሆኖ በልቡ ውስጥ እየተቀጣጠለ ያለው ከባድ የጥበብ ፍም ስለነበር አጋጣሚውን እየጠበቀ ሰውነቱ መቃጠሉ ነፍሱ መጋሏ አልቀረም ። ይህን እረመጥ ለማብረድ ሲልም በዚያው በባህር ዳር አካባቢ በነበረው ቤዛ የኪነጥበብ ማህበር ውስጥ በስነ-ፅሁፍ ተሳትፎ ማድረግ ያዘ።
ስኬትን በትንሹ መስፈር የማይወደው ጌትነት የባህርዳር ኤፍኤም ለእኔ የጋዜጠኝነት ግብ አይደለም በማለት እጅግ ከባድ የሆነውንና በወቅቱ በቀላሉ ሊገኝ የማይችለውን የአማራ ሬድዮ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዕድል እንዲሰጠው ለያኔው ቡድን መሪ ጋዜጠኛ አስቻለው አየሁዓለም ጥያቄ በማቅረብ ጣቢያውን ለመቀላቀል ችሏል። ለሙያ ካለው ፍቅር እና ከሚሰማው ውስጣዊ ሀሴት እንዲሁም ከ250 ብር ውጪ በወቅቱ የሚያገኘው አንዳችም ጥቅም አልነበረም ፡፡ ሰዎች በሚወዱት ሙያ ሲያገለግሉ ትኩረት የሚያደርጉት ሥራቸው ላይ ለመሆኑ ጌትነት አንዱ ትልቅ ማሳያ ነው።
ጌትነት፣ በዋናው አማራ ሬድዮ ፕሮግራም በመምራት ጀምሮ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዋና ዜና አንባቢ ለመሆንም በቃ። ፕሮግራም በማዘጋጀት ፣ በመምራት ዜና በማንበብ እንዲሁም የአማራ ሬድዮ የልማት ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን በኋላም በ2003 ዓ.ም የአማራ ቴሌቪዥን ዜና አንባቢ ሆኖ በመሥራት ለሰባት (7) ዓመታት አገልግሏል ።
ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ሬድዮ ተፈጥሮን ቁልጭ አድርገው የማየት ያህል የሚሰሙ ፣ እውነት የሆኑና ከልብ የተሰሩ ከእርሻው ላይ ውሎ የበሬውን ጅራፍ ፣ የገበሬውን ፉጨትና የፏፏቴውን ድምፅ ከምንጩ በመቅዳት በርካታ የሬድዮ ዶክመንተሪዎችን አበርክቷል ። የስርጭት ጣቢያው የተጠቀማቸው እና ብዙ የአዕምሮውና የመዳፉ ውጤቶች ሌሎች እንደ አርዓያ የሚያዩዋቸው ሥራዎች በዚያ ይገኛሉ ፡፡ነገር ግን እርሱ ‹‹.. እኔ ለአማራ ብዙሀን መገናኛ ካስቀመጥኩት አሻራ ይልቅ የተማርኩት ትምህርት የጨበጥኩት ግንዛቤ ይገዝፋል ። ለአንድ ዓመት ብዬ የጀመርኩትን ሙያ ዓመታትን አስቆጥሬበታለሁ፡፡ በዚህም ብዙ ከሰራውም ብዙከተሳሳተውም ተምሬያለሁ ። ስለ discipline, Media Leadership, media Management and Editors Roles በሚገባ እንዳውቅ የአማራ ብዙሀን መገናኛ ትልቅ እገዛ አድርጎልኛል ” ይላል ። አንጋፋና የባለብዙ ሙያ ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ።
ወደ ዋልታ ቲቪ
ይህ አስተዋይ ባለሙያ የአማራ ብዙሃን መገናኛን (1997-2003) ለሰባት ዓመታት ካገለገለ በኋላ አንድ አጋጣሚ ቀድሞ እንደገጠመው ሁሉ ወደዋልታ ቴሌቪዥን እንዲመለከት አድርጎታል ። የግል ጉዳዩን ለመጨረስ ወደአዲስ አበባ ያቀናው ጌትነት ቀድሞ እንጀራው እዚያው በስሎ ስለነበር ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባወጣው ክፍት የስራ ማስታወቂያ ተመዝግቦ ተወዳድሮ በአንደኝነት ለማለፍ ችሏል ። ቢበዛ ለሁለት ቢያንስ ለአንድ ዓመት በዋልታ ለመስራት አቀደ
ዋልታ ለቅጥር በመጣበት ወቅት የገጠመው ቀጣሪ ቀድሞ በአማራ ብዙሃን መገናኛ በፍቃደኝነት በ250 ብር ደመወዝ ቀጥሮት የነበረው ጋዜጠኛ ጌጡ በላቸው መሆኑ ነው። ጌጡ ለወጣው የዶክመንተሪ ፕሮዲውሰር ማስታወቂያ በድጋሜ ጌትነትን በድጋሜ ቀጠረው። ሥራውን እንደጀመረ ቤተሰቡን እና ንብረቱን ወደአዲስ አበባ ለማጓጓዝ ዝግጅቱን በጨረሰ ጊዜ በሥራ ምክንያት ለአንድ ወር ያህል ወደቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እንዲሄድ ታዘዘ። ቤተሰቡን መንገድ ላይ በትኖ ያለምንም ማመንታት ሥራውን በማክበር ወደ ቤንሻንጉል ያቀናው ጌትነት ፕሮጀክቱ ተጀምሮ አደጋ ላይ የወደቀውን የቤንሻንጉል ቤሙ ቲቪ ከውድቀቱ ለመታደግ ጥረት ማድረግ ጀመረ። ዶክመንተሪ ፕሮዲዩስ በማድረግ ፣ ኤዲቲንግ በመሥራት እና ስልጠናዎችን በመስጠት ለ10 ወራት እዚያው ቆይቶ አቅሙን ፣ ጊዜና ጉልበቱን ተጠቅሞ እስከወዲያኛው የቤንሻንጉል ተቪን አቋቋመ ። ይህም አቶ ጌትነት ካኖራቸው አሻራዎች እንደ ዋና ተደርጎ የሚቆጠርለት ነው፡፡ እርሱም ስለ ዚህ አሻራው ሲናገር በትህትና ደስታ እና ኩራት ይሰማዋል፡፡
ባለቤቱ እና ልጆቹን እየናፈቀ ከተማውና ሰውን ሳይላመዱ እንዲሁ እንደዋዛ አሥር ተከታታይ ወራትን በጉጉትና በናፍቆት ተውጠው ሳለ በሚወደውና በሚያከብረው ሙያው ህዝብና ሀገር ለማገልገል ሲል ርቆ ለመቆየት ተገዷል ። ከአሥር ወራት በኋላ ግን በዚያ ያሉት የጣቢያው ሰራተኞች አቅማቸው በመገንባቱ እርሱና ሌሎች የተልዕኮው አባላት የማይደበዝዝ አሻራ ጥለው ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ችለዋል ።
ጌትነት ዋልታ ከገባ በኋላ በግምት ከሰባ በላይ ዶክመተሪዎችን ሰርቶ ለእይታ አቅርቧል ። በጣም ብዙና ትልልቅ ርዕሰ -ጉዳዮችንን የያዙ ዶክመንተሪዎችን ፈጠራ በታከለበት እና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ሰርቷል ። ዶክመንተሪ የራስን ጥረት የሚጠይቅ ሙያ በመሆኑ በሚሰራው ርዕሰ- ጉዳይ ላይ ከቀረፃ በፊት ጠለቅ ያለ ጥናትና ምርምር የሚፈልግ እንዲሁም ጊዜና ሌሎች ግብዓቶችን የሚሻ በመሆኑ ያለዕረፍት ለመስራት የራሱንና የቤተሰብን ጊዜ መስዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፈታኝ ሙያ ነው።
ስለሆነም ታዲያ ዶክመንተሪ ፕሮዲውሰሩ ጌትነት ታደሰ በዓመት አስር የሚደርሱ ሥራዎችን አየር ላይ ለማዋል በርካታ ሌሊቶችን በሥራ ላይ አንግቷል። እንደአስፈላጊነቱ በአጭር ጊዜ የሚሰሩ ዶክመንተሪዎችን ጥናት በሥራ ጉዞ ላይ ሆኖም አድርጓል ። ለምሳሌ ያህል የገዳ ስርዓት ዶክመንተሪ ተጠቃሽ ነው ። ይህን ዶክመንተሪ ለመስራት ጥናቱን ያካሄደው የፕሮፌሰር አሥምሮምን መጽሐፍ በግብዓትነት ተጠቅሞ እንደሆነም ይናገራል ። መጽሐፉ ለሚሰራው ስራ እጅግ ወሳኝ መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግለውም ችሏል ። ገዳ 1, 2 , 3, የተሰኘ ሁለት ክፍል ያለው አንዱ ክፍል በአማካይ 38 ደቂቃ የሚሄድ በቦረና የተሰራ ዶክመንተሪ ሲሆን ቀረፃውን ደግሞ በብቃት የተወጣው የካሜራ ባለሙያ ሙሉቀን ታደሰ ነበር ። ታዲያ በርካታ ጥናት እና ለጥናት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የሚጠይቀው ይህ ሙያ ለጌትነት ትልቅ ትምህርት የሰጠና በርካታ ሰነዶችንም ሰነዶችንም እንዲፈትሽ እድል የፈጠረለት ነው፡፡
ጌትነት በዶክመተሪው ላይ የሀዋሳ ከተማን ውበት ዙሪያ ገባዋን እየቃኘ የወፎቹን ድምፅ ፣ የንፋሱን ጩኸት የነዋሪውን እንቅስቃሴ ጥርት ባለ ምስል ሲያስቃኝ የምር ዘጋቢ ፊልም ሰራሁ ብሎ ያስባል። ይህን ስሜት በተመልካች ዘንድ ለማምጣት ደግሞ ባለሙያ ቀድሞ በራሱ አዕምሮ ውስጥ የሰራቸውን ሥራዎች እና የተጠቀማቸው የትኞቹም ግብዓቶች እንዲሁም የፈጠራ አቅም ውጤት ነው።
ሌላው በጌትነት የተሰራ ዶክመንተሪው ትኩረቱን ያደረገው በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ማዕከላት ውስጥ ነበር፡፡ በማዕከላቱ ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ ወደሆነው እና የጤፍ ምርምር ላይ ያተኮረ ክፍል ነው። ይህን ለመስራት ቀድመው የተሰሩ ስራዎችን ማገላበጥ የተካሄዱ ጥናቶችን መመልከት እና ሌሎች ጥረቶችንም ይጠይቃል ። ምርምር ማዕከላቱ ላይ በስፋት ተዳሰው ትንታኔና መላምት የተሰጠባቸውን የምርምር መጣጥፎች ( Desk Research ) ማግኘት ቀላል አይሆንም ።
ይሁን እንጂ ጌትነት ባለሙያዎቹ በሥራ የሚያሳልፉትን ጊዜ አብሮ በመሆን ነበር ጥናቱን የጀመረው ። አንድ የምርምር ባለሙያ አንድ ጉዳይ ላይ የሚያደርገው ጥናት የአንድን ሰው ዕድሜ ሊያክል ይችላል ። ስለዚህ አንድ ተመራማሪ ዕድሜውን ሙሉ አንድ ነገር ሲፈልግ ይጨርሳል ማለት ነው ።
በዚህ የምርምር ማዕከል ታዲያ በጤፍ ላይ ለ30 ዓመታት ያህል በአንድ ዶክተር የተሰራን ምርምር እና የተገኘውን ውጤት ያስቃኛል ። ተመራማሪው ግለሰብ ለረዥም ዓመታት በጥረት የለፉበትን ጤፍ በ30 ዓመቱ በአንዲት ቀን እኩለ -ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነበር ውጤቱን የደረሱበት ። 29 ዓመታትን የለፉት ተመራማሪው የጤፍ አበባ የሚከፈተው ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት መሆኑን ሊደርሱበት ችለዋል ። ዶክመንተሪው አንድን ዘር ከላይኛው ዘር በማዳቀል በሚደረገው ጥረት እና በሚጠበቀው ውጤት አዲስ ነገር ለማምጣት የሄዱትን መንገድ በተቻለ መጠን ለማሳየት ችሏል ። የተለያዩ ምርቶችን እና እንስሳትን የማዳቀል ሥራ ላይ ያሉ የግብርና ምርምር ተቋሟት እንዲሁም ባለሙያዎች ድካማቸው ምን ያህል እንደሆነ እንዲታወቅላቸው ለማድረግ በሥራ ገበታቸው ላይ በመገኘት ሙያዊ ቅኝት አድርጓል ።
ለጋ ሰውነቱን ለጋዜጠኝነት እና ለትያትር ጥበባትን እየመገበ ያደገው ፤ የራሱን ልብወለድ ፅፎ በሬድዮ የተረከው ቀልጣፋው ትሁቱ በራስ የመተማመን አቅሙ የላቀው ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ በዓመት ብዙ ዶክመንተሪዎችን ለዋልታ የሰራ በአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ያገለገለ ወጣትና ትሁት የሙያ ሰው ነው። ታዲያ በዋልታ ቆይታው ትልቁ ፈተናና ሸምቀቆ የነበረው ዋልታ ዶክመንተሪ ሲያሰራ በባለሙያው ፍቃድ ሳይሆን አሰሪዎች በመረጡትና የሥራ ስምምነት ባደረጉበት ርእሰ ጉዳይ ላይ መሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት በዶክመንተሪው ብዙ ለመጓዝ አላስቻለውም። ። እንዲህም ሆኖ የአቅሙን ከማበርከት አልቦዘነም ።
በቆይታዬ በተመረጡ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሰርቼ ቢሆን ኖሮ በሙያዬ ትልቅ አሻራን ማሳረፍ እችል ነበር ይላል ዶክመንተሪ ፕሮዲውሰሩ ጌትነት ታደሰ።
በነበረው ቅልጥፍና፣ የስራ አቅምና አበርክቶት እንዲሁም ትልቅ የፈጠራ ብቃት ዋልታ ዕድገትም ሰጥቶት ፕሮዳክሽኑን እስከመምራት ደርሷል። የትላንቱ ጋዜጠኛ ፣ኤዲተር ፣ የካሜራ ባለሙያ ፣ ፕሮዲውሰርና የኢፕድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበረው የአሁኑ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሰ ። ከአማራ ብዙሃን መገናኛ ጀምሮ እስከዋልታ የነበረውን መንገድ በአጽንኦት ለመመልከት እና ለመከታተል ሰፊ ዕድል የነበረው መምህሩ ቢባል የማያንሰው ጌጡ በላቸው እንዲህ ሲል ለጌትነት ያለውን ምስክርነት በሙሉ አንደበት አረጋግጦልናል ።
” የጌትነት ብስለት ከታች ጀምሮ ነው፡፡ የወጣትነት ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ በራሱ ጥረት አቅሙን በትምህርት እየገነባ አሁን ላለበት ደረጃ የበቃ በሳል መሪ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የጌትነት የቅርብ ኃላፊው ነበርኩ፡፡ በእነዚያ ዓመታት በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን አስተምሮኛል፤ ከነባር አሰራሮች እንድላቀቅም በእጅጉ አግዞኛል፡፡ እናም እንኳን የሚመራቸውን የበላይ ኃላፊዎቹን የመለወጥ አቅም ያለው በሳል ሙያተኛ አሁን ደግሞ መሪ ነው፡፡
በሙያተኛነት ዘመኑ የሚሰጡትን ስራዎቹን ሳይሸራርፍ በጥራት፣ በቅልጥፍና እና በመግባባት ያከናውንበት የነበረው የአሰራር ጥበቡና በሂደትም ያካበተው ልምድ አሁን ለሚመራቸው ሰራተኞቹ እርሾ ሆኖ እንደሚያገለግለው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ጌትነት ብእሩ የተባ፣ አንደበቱ ርቱእ፣ ማህበራዊ ህይወቱ በመግባባትና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ሙያውን የሚያከብር መሪ ነው፡፡ የግሉንም ሆነ የሥራ ህይወቱን በጥንቃቄ/ሳይዝረከረክ/የሚመራ እያንዳንዱን እርምጃውን አስተውሎ የሚራመድ ጥንቁቅ መሪ ነው፡፡ ጌትነት ብዙ ነው፤ብዙ ያልተነገረለት፡፡ ” ብሎናል። እኛም ታዲያ ካልተነገረለት ብዙ ላይ ጥቂቱን እየነገርናችሁ እንቆያለን ። ለሁለት ዓመት ብሎ አቅዶ በሙያው ፍቅር ውስጥ ሰምጦ ለ7 ዓመታት ከ2003-2010 ያለዕረፍት ስላገለገለው የሚድያ ሰው ጌትነት።
የለውጡ መንግሥት ወይም ዶክተር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በተደረገ የአስተዳደር ለውጥና የሹም ሽር ሂደት ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ( ኢፕድ )
ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ ተመርጧል
ኢፕድ ለ83 ዓመታት ሲያገለግል የኖረ አንጋፋ የህትመት ሚዲያ ነው ።
ጌትነት ወደዚህ የመሪነት ቦታ ሲመጣ ከባድ የኃላፊነት ቀንበርን ለመሸከም ራሱን ከመቼውም ጊዜ በላይ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በርካታ የተበላሹ አሰራሮችን የማፅዳት ፤ በየፈርጃቸው የማስተካከል ፤ የነበሩ ቅሬታዎችን የመመርመርና የመፍታት ፤ የአሰራር መዋቅሩን እንዳዲስ የመዘርጋት፣ የመገንባት እና ሌሎችም ኃላፊነቶች ከፊቱ ተደቅነው ነበር፡፡ይህ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰላሳ ሦስት ( 1933 ) ዓ.ም የተቋቋመው ቀዳሚ የህትመት መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በውስጡ ከ 400 በላይ ሰራተኞችን ያቀፈ ሲሆን ህዝባዊ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ እና ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ የመንግሥት ተቋም ነበረ ።
ተቋሙ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ዕለታዊዎቹን ‘ አዲስ ዘመን ‘ እና ‘ ዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ ‘ ሳምንታዊዎቹን ‘ በሪሳ ‘ በአፋን ኦሮሞ ሲያሳትም የቆየ ሲሆን አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ ማለትም ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ በስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ውስጥ ‘ ወጋሕታ ‘ በትግርኛ ቋንቋ እና ‘ በከልቾ ‘በሲዳምኛ ቋንቋ የሚታተሙ 2 አዳዲስ ጋዜጦችን ለንባብ ማብቃት ተችሏል ። ይህን ማድረግ የተቻለው የ1933ቱን አንጋፋ ድርጅት በድጋሜ በ2011 ዓ.ም እንደገና በማቋቋም አዳዲስ ራዕይ ፣ ተልዕኮ እና እሴቶችን በማንገብ በአመራር ቦርዱ በኩል የአደረጃጀት ጥናት ፣ የምደባና ድልድል ፣ የደመወዝ ጥቅማጥቅም እና ተያያዥ የሆኑ የሪፎርም ስራዎችን ለመምራት የሚያስችል አቅጣጫ በማስቀመጥ ነው።
ለዘመናት በድርጅቱ ሰራተኞች ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ኮሚቴ በማቋቋም ቅሬታ ያቀረቡ ሰራተኞችን ጉዳይ በመመልከትና እልባት እንዲያገኙ በማድረግ ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ለማሳየት ተችሏል። ይህን ውጤት ለማምጣት ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበረው ጌትነት ታደሰ በኢፕድ ውስጥ የወሰዳቸው ኃላፊነቶችን ስንመለከት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ አጠቃላይ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጦችን መርቷል ፡፡ የመዋቅር ጥናቶች ውስጥ በአቅም እንዲሰሩ አድርጓል ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችን አሹሟልየምደባና ድልድል ሥራውን በበላይነት መርቷል የጥቅማ ጥቅምና የደመወዝ ማሻሻያን በማስጠናት ተግባራዊ አድርጓል ሲል መረጃው ያትታል ።
ይህን ለማድረግ የሚያስችል ልዩ የአመራር ጥበብና ብስለትን የሚጠይቅ ነው። ሰርቶ ለማሰራት የማይደክመው ይሉታል የሥራ አጋሮቹ ጋዜጠኛ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌትነት ታደሰ በፕሬስ ድርጅት ያሳየው በሳል የአመራር ስልትና የአስተዳደር አቅም በሂደትና በልምድ የተገነባ መሆኑንም ያሳያል ። ትንሽ ሳለ ትልቆቹን ማስተማር የቻለ ትልቅ ሆኖ ከታናናሾቹ የሚማር አዋቂ ሰው ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሁለቱ ጋዜጦች የምረቃ ቀን ( ወጋሕታ ትግርኛ እና ባካልቾ ሲዳምኛ ) የኢፕድን ለውጥ በተግባር የተመለከቱ በመሆናቸው ጋዜጦቹ በተመረቁበት ዕለት የተገኙ የሲዳማ ክልል ተወካዮች ለኢፕድ እንዲህ ያለውን ማስታወሻ ጽፈው ለማንበብ ችለናል ።
” ይህች ቀን የእውነተኛ ፌደራሊዝም ቀን ነች ፤ እናመሰግናለን !”
በተጨማሪም ዶክተር ጌታቸው ድንቁ
” እንኳዕ አብፅሓኩም ፣ እንኳዕ ተሓደስኩም ፣ ኬሮ ፣ ሰላሜ ፣ ቀጥሉ ፕሬስ ። ሲሉ በብዕራቸው ስለተሓድሶው ማስታወሻ ትተዋል ።
እንግዲህ የኢፕድ ነገር የሞተን የማስነሳት ያህል እጅግ ከባድ ቢሆንም የጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ ቁርጠኝነት በወራት ውስጥ ትልቅ ንቅናቄ እና ለውጥን ለመፍጠር ችሏል ። የጠፋውን ስም አስመልሷል ። የታጣውን ተአማኒነት በድጋሚ አስመልሷል። የህትመት ሚዲያው እንዲያንሰራራ እና ድርጅቱ የታቀደለትን ዓላማ ከግብ እንዲያደርስ ጥረት አድርጓል ። በማድረግ ላይም ይገኛል ፡፡ ሀገርና ህዝብን በእምነት እንዲያገለግል እንዲሁም የህዝብን የተጣራ መረጃ የማግኘት መብት እንዲጠበቅ ታማኝ ምንጭ በመሆን እንዲያገለግል ማሻሻዎችን እያደረገ ይገኛል ።
የኢፕድ ጋዜጣ እንዳስነበበው ከሆነ በህትመት ጋዜጦች ላይ የሚቀርቡትን የይዘትና ቅርፅ ጥያቄዎች ተቀብሎ ማስተካከያ አድርጓል ። ለምሳሌ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይቀርብበት የነበረው የቅርፅ ይሻሻል ጥያቄ ተቀባይነትን አግኝቶ ከበርሊነር ወደ ታብሎይድ ቅርፅ ተቀይሯል ይላል ።
በ2013 ተግባር ላይ በዋለው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአደረጃጀት ጥናት መሰረት ፕሬስ የዜና ማዕከል ሆኖ ስራ ጀምሯል፡፡ ዜና ማእከሉ በዋና አዘጋጅ የሚመራ ሲሆን ዜናና ዜና ትንታኔዎችን ኦን ላይን ሚዲያን ጨምሮ ለሁሉም የህትመት ውጤቶች ተደራሽ ያደርጋል፡፡ ፕሬስ እንደዘገበው በሚል በምንጭነት ይሰራል ። በዚህም ሚዲያው ያለውን ተአማኒነት እያሳደገው መምጣቱ አይቀሬ ነው።
በተጨማሪም ኢፕድ በትንሽ ጊዜ ውስጥ መጽሐፍ ለሚሸጡ 60 ወጣቶች የሥራ ዕድልን የፈጠረ ሲሆን የስርጭት አማራጭን ለማስፋት መጽሐፍትና ጋዜጣን የሚያዞሩበት ጋሪዎችን አምርቶ ለስድሳዎቹ ወጣቶች ስድሳ ጋሪዎችን በድርጅቱ የመለያ ብራንድ አዘጋጅቶ አስረክቧል። በቀጣይም ይህን የመጽሀፍና ጋዜጣ መሸጫ ጋሪና ኪዮስክ ፕሮጀክት በማስፋት ከአዲስ አበባና ሌሎች ከተማ አስተዳደሮች፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እና ከሌሎች የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ ተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገራችን በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ከአንድ ሺህ በላይ የመጽሀፍና ጋዜጣ መሸጫ ጋሪዎችንና ኪዮስኮችን በማዘጋጀት ለስራ አጥ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ በ2013 ዓ.ም ዕትሙ ላይ እስካሁን የተሰሩትን እና ወደፊት የታቀዱትን ኹነቶች በስፋት አስነብቧል ። ይህም በህትመት ሚዲያዎች ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር እና የሥራ ዕድልና የፈጠራ አማራጭ ላይ እየሰራ መሆኑን ያሳያል ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰን ወደ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ካመጣ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ፈጣን ለውጦችን እያሳየ መጥቷል ። ከላይ የተዘረዘሩትን የኢፕድ ለውጦች በሙሉ ከዋና ሥራ አስፈፃሚው ጌትነት ጋር ተያይዘው የመጡ ናቸው ። አንድን ነገር ለመቀየር ከታሰበ ትክክለኛውን ባለሙያ ማግኘት ያሻል።
የተሻለ ውጤትን ለማስመዝገብ ሲባል የአጋርነት ሥራን ማከናወን አንዱ በመሆኑ ድርጅቱ የህትመት ሚዲያውን ለመገንባት እና ያለበትን ወጪ ለመቀነስ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመስራት ላይ ሲሆን ይህን ዕቅድ ግቡን እንዲመታ የአመራር ፣ የሰው ሀብትና ተቋማዊ አስተዳደርን በማሳደግ ላይ እየሰራ ነው። የነዚህ ነገሮች ፈር መያዝ የአንባቢያንን እርካታ ከመጨመር አንፃር ፋይዳው የጎላ ነው ተብሎለታልም። በሌላ በኩል ድርጅቱ የተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶች ያሉበት ሲሆን በዋና ሥራ አስፈፃሚው አማካኝነት በመንግሥት የልማት መርሃ-ግብር ላይም ሆነ በበጎ አድራጎት ዘርፍ ያለበትን ግዴታ እየተወጣ ይገኛል ። ይሁን እንጂ ከመጣውም ለውጥ በላይ ከፍተኛ የሆነ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቀዳሚውን ድርሻ ሚዲያዎች የሚወስዱ በመሆኑ ይህ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ በተሰማራበት ሙያ ሀገሩንና ህዝቡን በተሻለ መልኩ እያገለገለ ይገኛል ።
የመሪነቱን ወንበር በአግባቡ ተጠቅሞ አንድ ሀገር የሚያስፈልጋትን የእውቀት ብርሃን ያፈነጥቅላታል ተብሎ ተስፋም ተጥሎበታል ።ዘላቂ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ፣ የቀዘቀዘው የንባብ ባህል ዳብሮ እውቀትን መሸመት ይቻል ዘንድ ፣ ጠያቂና አመዛዛኝ ትውልድ ለመፍጠር ይቻል ዘንድ ገና ብዙ ብዙ የሚጠበቅ ቢሆንም የጀመረው ሥራ ሚዛኑ የደፋ ነውና በእርግጥም የዘመናችን ስኬታማ ሰው ነው ።
ጌትነት ወንበር ላይ ተቀምጦ ማዘዝ ሳይሆን ሰርቶ ማሰራትን ያውቅበታል ። ቢሮ ሲገባ የለበሰውን ሱፍ አውልቆ የሰራተኞችን ዩኒፎርም በመልበስ አብሮ ሰርቶ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር የሚያስተምር ዕንቁ መሪ ነው። ልክ እንደ ዋልታው ሁሉ በኢፕድ ስላለው የጎላ አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል የሆኑት ዶክተር ወዳጄነህ መሐረነ እንዲህ ሲሉ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተውናልም ።
“…..ባለፉት ጥቂት አመታት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ሆኜ አገልግያለሁ። ይህም ከድርጅቱ ኃላፊ ከአቶ ጌትነት ታደሰ ጋር አብሮ የመስራትን እድል ሰጥቶኛል። ስለዚህ ወጣት መሪ ስመሰክር በደስታ ነው።
አቶ ጌትነት አመለ መልካም ነው። ቁጥብ፣ አስቦ የሚናገር፣ ሲያሻው ደግሞ ለዛ ያለው ተጫዋች ነው። ሁሉን ሰው ያከብራል፣ በትህትና ራሱን ዝቅ ያደርጋል። በመሪነቱ “የአገልጋይነት አመራርን” ይከተላል። አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ቱታ ለብሶ እቃ ሲሸከም፣ ቢሮ ሲያፀዳ ይገኛል። ሰራተኞችን የሚመራው መመሪያ በመስጠት ብቻ ሳይሆን ሰርቶ በማሳየት ነው። አቶ ጌትነት ወደ ኃላፊነት ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በፕሬስ ድርጅት የመጣው ለውጥ በግልፅ የሚታይ፣ የሚቆጠር፣ እጅግ የሚያስደንቅም ነው። ይህም ለአስተዳደርና ለአመራር ብቃቱ ህያው ምስክር ነው። ይህ ወጣት መሪ ለወደፊትም ኢትዮጵያ ላለመችው እድገት ግንባር ቀደም ሆነው ከሚሰለፉላት ልጆችዋ መካከል አንዱ እንደሚሆን አልጠራጠርም።”
በዋና ስራ አስፈፃሚው ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ እና ኢፕድ የተያዙ የአንዲት ሀገር ኹለንተናዊ ቁልፎች መካከል የሙዚየም ግንባታን ያካተተ በርካታ ፕሮጀክት በጥናት ታቅዶ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል ። እነዚህም በ11 ቋንቋዎች በቀን 700ሺህ ቅጅ ጋዜጦችን ማተም ፤ 10 ሚሊዮን የኦን ላይን ተመልካች ማፍራት፤ 20 ኮረስፓንደንቶች ማግኘት ፤ 1.1 ቢሊዮን ብር ሽያጭ መሰብሰብ፤ ኦን ላይን ቴሌቪዥን ማሰራጨት ፤ ሶስት ማተሚያ ቤቶች መገንባት ፤ የሻትል/ባስ አገልግሎት በመጀመር ህትመቶችን ተደራሽ ማድረግ ፤ የጥናትና ምርምር፤ የትምህርትና ስልጠና የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) ፕሮጀክት መገንባት ፤ የቋሚ ሙዚየም ግንባታ ጋዜጠኛ ጌትነት ታደሰ ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ ታቅደው ውይይት ተካሂዶባቸው በ10 ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ለአንዲት ሀገር አስፈላጊና ትውልድ መሥራት የሚችሉ አጓጊ ፕሮጀክቶች ናቸው ። አንድ ሰው አንድ ሀገር መሥራት እንደሚችል ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱም ይችላሉ ። የሰው ዐይንና ጆሮ በመሆን ለዘመናት የቆየው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አሰራር ባመጣበት በእርጅና ጎብጦ የነበረ ቢሆንም አቶ ጌትነት አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋትና ሰርቶ በማሰራት ቤቱን የትጉሀን ቤት እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ስለ አቶ ጌትነት ታደሰ የተሰጡ ምስክርነቶች
አቶ ጌትነት የሀገርና የህዝብ ፍቅር ያለው፤ ሀገርን መውደድ ማለት ሀገርን ማገልገል መሆኑን በተገቢው የተረዳና የአገልጋይ አመራርን (servant leadership) መርህ አድርጎ የሚሰራ መሪ ነው።
ወ/ሮ ሔለን እስክንድር የኢፕድ የጥናትና ምርምር፣ አቅም ግንባታና ገበያ ልማት ም/ዋ/ስራ አስፈፃሚ
ስራውን በእውቀት የሚመራ፤ ሰርቶ የሚያሰራ፣ በቡድን ስራ የሚያምንና ሰውን የሚያበቃ መሪ ነው።
የኢፕድ የገበያ ስራ ከ5 አመታት በፊት በስትራቴጂ የማይመራ፣ ተቋማዊ ማንነቱ በተገቢው መንገድ የማይታወቅ እና የገበያ አቅሙም ዝቅተኛ ነበር። በእርሱ መሪነት በተሰሩ ተከታታይና የተቀናጁ የገበያ እና የይዘት ማሻሻያ ስራዎች አሁን ላይ ኢፕድ በደንበኞቹ ዘንድ ታዋቂ፣ ተአማኒ እና ተመራጭ ለመሆን የቻለ ሲሆን በጣም ውስን የነበሩት የገበያ አማራጮች አድገው አሁን ላይ በጣም በርካታ የገበያ ስራዎችን በመጠቀም ተቋማዊ የገቢ መጠኑ ከ3 እጥፍ በላይ እንዲያድግ አድርጓል።
ከአምስት አመት በፊት ምንም ተቀማጭ ገንዘብ ያልነበረው ኢፕድ አሁን ላይ አስተማማኝ የፋይናንስ ደረጃ ላይ ደርሷል። በኢፕድ የመጣው ተቋማዊ ለውጥ ከውስጥ ተጀምሮ ወደ ውጭ ያደገ በመሆኑ የተቋሙን አመራር እና ሰራተኛ ያሳተፈ፣ ተቋማዊ የስራ ባህልን ያሳደገና ተቋማዊ የእኔነት ስሜትን የፈጠረ በመሆኑ አሁን ላይ ለውጡ በአመራር ብቻ ሳይሆን በሰራተኛውም ጭምር የሚደገፍ በመሆኑ ፅኑ መሰረት እንዲኖረው አስችሎታል፡፡
ጌትነት በኢትዮጲያ መገናኛ ብዙሃን ታሪክ በሙያዉ ሰልጥነዉ፣ ከታች ጀምረው በመስራት በትጋታቸው የዘርፉ መሪ ከሆኑ ሰዎች ግምባር ቀደሙ ነው። በሙያው ያለዉ ጥልቅ እውቀት፣ በዘርፉ በየደረጃው ሰርቶ በተግባር ማለፉ፣ የዘርፉን ጠንካራና ደካማ ጎን ጠንቅቆ ማወቁ ፣ በትንሹ የማይረካ እና ዘርፋን በተለየ ሙያዊ ዕውቀት ለመምራት ያለው ፍላጎት እንዲሁም ያለዉ ተፈጥሯዊ የመሪነት ክህሎት ተደማምሮ በስራው ስኬታማ እንዲሆን አድርጎታል። በቀጣይም በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ በሳል ሙያዊ የመሪነት ሚናቸዉን በመጫወት አዎንታዊ አሻራቸውን አሳርፈው ከሚያልፉ ባለብሩህ አምሮ ወጣት የሚዲያ መሪዎች አንዱ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። ጌትነት በዘርፉ ያለውን የመሪነት ታሪክ ወደ ሙያው ባለቤቶች በመመለሱ ረገድ በተግባር ፋና ወጊ የሆነ ሲሆን ፤ ለሌሎች ወጣት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም በበሳል አመራሩ ምሳሌ መሆን የሚችል ከዕድሜዉ የቀደመ የሚዲያ መሪ ነዉ።
አብርሃም ዘሪሁን
የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ግለ-ታሪኩን ያቀረብንላችሁ የሚድያ ባለሙያ አቶ ጌትነት ታደሰ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆኖ በሰራባቸው ጊዜያት መልካም ስምን ያተረፈው የእውነትም ስለተጋ እና ለውጥ ለማምጣት ስለፈለገ ነው፡፡ ለጋዜጠኝነት ቅርብ የሆነው አቶ ጌትነት ከሪፖርተር ተነስቶ በሂደት ያደገ በመሆኑ ሁሉንም የስራ እርከኖች ደህና አድርጎ ያውቃቸዋል፡፡ ሙያውን ስለሚችለው ወይም ስለተማረው ብቻ ሳይሆን በጽኑ ስለሚወደው ወገቡን ታጥቆ ከ17 አመት በላይ ለሙያው ተጋ፡፡ ጥሩ ተግባቦት ያለው ስለነበርም ከታች እስከላይ መልካምነቱን ይመሰክራሉ፡፡
ይህን ግለ-ታሪክ በሰሩት ባለሙያዎች እምነት ደከመኝ ሳይል የሰራ ታሪኩ በወርቅ ብእር ይጻፍለታል፡፡ እንዲሁ የተሰጠውን ብቻ እየሰራ በመጠኑ የሚኖር ደግሞ ታሪክ ሊያነሳው ከቶ አይችልም፡፡ ሚድያን የሚመሩ ሰዎች አንደኛ እውቀት ይኑራቸው ሁለተኛ ደግሞ ቢሮክራሲውን ትተው ሰዎችን በወጉ ይምሩ፡፡ አቶ ጌትነት ታደሰ ለበርካታ የሚድያ መሪዎች አርአያ የሚሆን በጎ ተግባር የፈጸመ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ግለ-ታሪኩን በዚህ መልኩ ስናሰናዳ የሚድያ መሪዎች ከሰሩ መመስገን እንዳለባቸው ለማመልከት ፈልገን ነው፡፡ አቶ ጌትነት በዋልታ ቲቪ እና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ላሳየው ትጋት እንደተወዳጅ ሚድያ አክብሮታችንን እንገልጻለን፡፡
አሁን ደግሞ እኛ ይህን የህይወት ታሪክ ጽፈን ካጠናቀቅን በኋላ አቶ ጌትነት ታደሰ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆኗል፡፡ ኢቢሲ ለሚኖረው ቆይታ መልካሙን ሁሉ እንመኝለታለን፡፡
ይህ ጽሁፍ ባለታሪኩን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ፤የባለታሪኩን የቅርብ ሰዎች በማነጋገር ፤ አጠቃላይ በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉና በጋዜጠኛ ባንቺአየሁ አሰፋ የተጻፈ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ የቃለ መጠይቅ እና የምርምር ስራው ከየካቲት 2014 ጀምሮ ሲጠናከር የቆየ ሲሆን ዛሬ ታህሳስ 9 2016 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች እንዲቀመጥ የተደረገ ነው፡፡