የህግ እና የኪነ ጥበብ ሰው አበበ ባልቻ ማነው
ትናንት ታህሳስ 25 የጋሽ አቤ ልደት ነበር። መልካም ልደት
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛልደ ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል። የእነዚህን አመራሮች እና የሚድያ ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
በዚህ ፅሑፍ የሙያ ታሪኩ የሚሰነድለት ባለሙያ የህግ ባለሙያ አበበ ባልቻ ነው። ይህ ፅሑፍ አበበ ባልቻን በማስፈቀድና ማረጋገጫ እንዲሰጥ በማድረግ የተሰናዳ ነው።ዕዝራ እጅጉ እና ሳራ አህመድ ታሪኩን አጠናክረውታል።
ፀሀዬ ዮሀንስ ቢሻን ቀበና እያለ ያቀነቀነለት ወንዝ ለአበበ ባልቻ ጥሙን ከማስታገስ አንስቶ በዋና ሰውነቱ ዘና እስከማድረግ ድረስ ውለታ ውሎለታል።በ ታህሳስ 23 1948 ዓ.ም “ኦሜድላ” በሚባል ሆስፒታል ውስጥ የዛሬው ባለዘርፈ ብዙ ሙያ ባለቤት አበበ ባልቻ ተወለደ። አባቱ ኤምባሲ ውስጥ ሹፌር በመሆናቸው ልጅነቱ እና ዕድገቱ በእንግሊዝ ኤምባሲ ውስጥ ነበር። በእንግሊዝ ኤምባሲ ውስጥ ማደጉ ከዘመኑ ልጆች በተለየ መልኩ ከመጫወት ፤ቄስ ትምህርት በመሄድ የመጀመሪያውን ፊደል ከመቁጠር አላገደውም። የአበበ የትምህርት አጀማመር በቄስ ትምህርት ቤት ነበር።
ከቄስ ትምህርት ቤቱ ቀጥሎ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ቤት ታሪክ ወንዶች እና ሴቶች በአንድ ላይ የተማሩበት የመጀመሪያው የሆነው ት/ቤት ኮከበ ፅባህ መማሩ ይነገራል። ኮከበ ፅባህ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የተማረበት ትምህርት ቤቱ ሲሆን በወቅቱ በነበረው የትምህርት ሥርአት ልጆች ከ2ሰአት እስከ 11:00 ሰአት ትምህርት ቤት ረጅም ጊዜያቸውን ከመምህራን ጋር እንደሚያሳለፉ ፤መምህሮቻቸውንም እጅግ ያከብሩ እና ይፈሩ እንደነበር ይነገራል። አበበ በትምህርት ቤት ቆይታው አማካይ(average) የሚባል ተማሪ ነበር። በዚያን ወቅት ስለህይወት ያለው እይታ የቀየረበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር
ወቅቱ ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አንስቶ እስከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይህን መዝሙር እያቀነቀኑ ወደ ገጠር የሚዘምቱበት ነበር።
ለእድገት በህብረት እንዝመት
ወንድና ሴት ሆነን በአንድነት
የ11ኛ ክፍሉ ተማሪ አበበ ባልቻም ይህን እያቀነቀነ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተጓዘ።ለመጀመሪያም ጊዜ ከአዲስ አበባ ወጣ። ከዛ በፊት አለም የሚመስለው በፒያሳ ሲኒማዎች እንደሚያያቸው ፊልሞች ነበር። አበበ ስለዕድገት በህብረት ሲናገር” ሀገሬ እንዳውቅ ያደረገኝ ፤አብሮ መኖርን ያስተማረኝ ጊዜ ነበር”ይላል።
የዩኒቨርስቲ ቆይታው
እንደአሁኑ ዘመን ዩኒቨርስቲዎች በብዛት ያልነበሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና የአስመራ ዩኒቨርስቲ ብቻ የነበሩበት ዘመን ነበር ። ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለመግባት መፅሀፎችን ማገላበጥ፤ ረዘም ያለ ሰአት ማጥናት ፤ ቤተ-መፅሀፍት ውስጥ በንባብ ጊዜ ማሳለፍ የሚጠየቅበት ጊዜ ነበር። ለአበበ ባልቻ ግን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የህግ ት/ቤት ለመቀላቀል ብዙም አልደከመውም። በዩኒቨርስቲው በነበረው ቆይታም ትምህርት እና ትምህርት ብቻ የሚል ሰው አልነበረም ።የዩኒቨርስቲው ዓለም ራሱን ፈልጎ ለማግኘትም ተጠቅሞበታል። አበበ በዩኒቨርስቲው ቆይታው ቅርጫት ኳስ ይጫወት የነበረ ሲሆን ለብሔራዊ ቡድን ድረስ ተመርጦም ነበር። በኃላ በዩኒቨርስቲው እያለ የቲያትር ባህል ማዕከል ውስጥ መሥራት ጀምሮ አሁን ድረስ በህዝብ ልብ ውስጥ እንዲቀመጥ ያስቻለውን ጅማሮ በብቃት ተወጥቷል።
በባህል አዳራሽ ቆይታው ሎሬት ጸጋዬን ለማግኘት የቻለ ሲሆን ፤ፀጋዬም ከአባተ ጋር እንዳገናኘው እና አብሮ ለመሥራት ዕድል እንዳገኘም ይናገራል።በ Creative Art Center አባተ ባዘጋጃቸው ሥራዎች ላይም ተሳትፎ ማድረግ እንደቻለ ይናገራል።
የሁለት ጥምር ሙያ ባለቤት እና የሥራ አለም
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ዲግሪውን በ1974 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የተቀበለ ሲሆን ከአባተ መኩሪያ ጋር በመሥራት የዳበረ ልምድም በቲያትሩ ዘርፍ ሊያገኝ ችሏል። ከአባተ እና ከፀጋዬ ጋር መሥራት ከአንድ ዩኒቨርስቲ ከሚሰጠው ዲግሪ እኩል እንደሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። በተለይ በ70ዎቹ በነበሩት ቲያትሮች ላይ ሁለቱ ባለሙያዎች ያሳደሩት ተፅዕኖ ከፍ እያለ ነው።
አበበ ባልቻ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥብቅና የተቀጠረው አውራ ጎዳና ሲሆን በዕውቀት ከእርሱ የሚበልጡት አለቆቹ እንዲሁም የመሥሪያ ቤቱ የተቀናጀ ስርአት ረዘም ላለ ጊዜ እንዲሠራ እንዳደረገው ይናገራል።
መጓዝ ኪነጥበብ ውስጥ ላለ ሰው ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነገር መሆኑ አይካድም።አበበ ባልቻም አውራ ጎዳና በሚሰራበት ወቅት ያረገጠው የኢትዮጵያ ክፍል የለም።በዚህም ለተለያዩ ባህሎች ፤ታሪኮች ፤ወጎች ተጋላጭ ነበር። በጥብቅናው ሙያው አበበ ለተለያዩ የግል እና የመንግስት መሥሪያ ቤቶች በጥብቅና የቆመ የተሟገተ የረታ እንዲሁም የስራ
ው ባህሪይ ነውና የተረታም ጉምቱ የህግ ሰው ነው። በሙያው አሁን በህይወት የሌሉት አቶ ተሾመ ገብረማሪያምን እንደሚያደንቅ እንደሚያከብር ተናግሯል።
አርቲስቱ አበበ ባልቻ
አውራ ጎዳና እየሠራራ ቲያትርንም እየተወነ ሁለገብ አርቲስት መሆኑን አስመስክሯል። በማዘጋጃ የባህል ማዕከል በጋሽ አባተ አዘጋጅነት ኦቴሎ፤ቴዎድሮስ እንዲሁም የሊስትሮ ኦፔራ የተጫወተ ሲሆን ፤የመጀመሪያ ቲያትሩም ኦቴሎ ነበር።በኦቴሎ ቲያትር የመሪ ገፀ-ባህሪይ ወክሎ የሠራ ሲሆን 384 ጊዜ መድረክ ላይ ኦቴሎ መታየቱ እንዲሁም ቲያትሩ ለመጨረሻ ጊዜ ሲታይ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር እንደነበር ይነገራል።ከኦቴሎ በመቀጠል ቴዎድሮስ ቲያትርን ረዘም ላለ ጊዜ መድረክ ላይ መጫወቱ ይታወሳል።
በወቅቱ በነበሩት ቲያትር ቤቶች መካከል ከፍተኛ ውድድር መኖሩ የሚዘነጋ አይደለም። አንደኛው ቲያትር ቤት ከሌላኛው ቲያትር ቤት የተሻለ ቲያትር ለማቅረብ የተቻለው ሁሉ የሚያደርግበት ጊዜ ነበር።ይህ ፉክክርም ተመልካች ጥሩ ጥሩ ቲያትሮችን እንዲመለከት አስችሎታል። አበበ ባልቻ ከማዘጋጃ የባህል ማዕከል ሌላ በብሔራዊ ቲያትር በአባተ መኩሪያ አዘጋጅነት አሉላ ቲያትርን ሰርቷል።
ጋሽ አባተ አበበ ላይ ያሳደረው በጎ ተፅዕኖ
እንዲሀ ይላል አበበ፦”ለትወና፣ለቲያትር ዕውቀት፣ባጠቃላይ ለሥነጥበብ አይኔን የከፈተልኝ አባተ መኩሪያ ነው። አዋቂ፣ደግ፣ሰጥቶ፣አስተምሮ ፣ዳይሬክት አድርጎ የማይደክመው የማይሰለቸው፣የማይበቃው የኢትዮጵያ የቲያትር ጥበብ ዋርካ አባተ መኩሪያ በሰጠኝ ዕድልና ትምህርት ነው የሆንኩትን ሁሉ ሆኜ የተገኘሁት። በጥሩ ሁኔታ የሰራሁት ሁሉ የሱ ነው። ” በማለት ለጋሽ አባተ ያለውን ልዩ አክብሮት ገልጿል።
አበበ ባልቻ ሥራዎቹን በአሜሪካ ፣ በአውሮፓና በአፍሪካ በሚገኙ በተለያዩ ሀገራት ከስመ-ጥር የወቅቱ ተዋንያን ጋር በመሆን አሣይቷል።በተለይ በአሜሪካ የፀጋዬ ገ/መድን ሥራ የሆነውን “የከርሞ ሰው” ላይ በሚደነቅ ብቃት ተውኗል።
ከቲያትር ባሻገር አርቲስት አበበ ባልቻ በፊልም እና በተከታታይ ድራማዎችም ላይ ብቃቱን ያሳየና ተወዳጅነትንም ማትረፍ የቻለ አንጋፋ የጥበብ ሰው ነው።
አበበ ባልቻ ከተወነባቸው ፊልሞች መካከል አስከሬኑ ፣ ሔሮሽማ፣ 3 ማዕዘን አቡጊዳ ተጠቃሽ ናቸው።በአቡጊዳ ፊልም ላይ አርቲስት ሙሉአለም ታደሰ ዳይሬክት ያደረገችው ፊልም ሲሆን ፊልሙን ለመሥራት ስታስብ የጄነራል ገፀባህሪው አበበ ባልቻን እያሰበች እንደሰራችው እርሱም በሚገርም ብቃት መጫወቱን ገልፃለች።
ከቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ደግሞ ባለጉዳይ፣ ሰው ለሰው፣ ዘመን ፣ ግራና ቀኝ፣ በሕግ አምላክ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረው የሰው ለሰው ድራማ “ አስናቀ “ የተሰኘው ገፀ- ባሕርይ የተጫወተ ሲሆን ይህም የአበበ ባልቻን የቲያትር ቤት ትወና ማየት ላልታደለው ወጣት ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያስገኘለት ሥራው ነበር።
ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ከትወና ሌላ አብሮ የሠራቸው ሥራዎች
በሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትልቅ ለውጥ ካመጡ ተቋሟት አንዱ የሸራተን አዲስ ሆቴል መከፈቱ ነው። የሸራተን ሆቴል ሲከፈት አበበ ባልቻ የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ ነበረ። ከሸራተን ሆቴል ጋር በተገናኘ በሙዚቃው ኢንዱስትሪም ከፍተኛ መነቃቃት የተፈጠረ ሲሆን የተለያዩ ኮንሰርቶች በሆቴሉ ይዘጋጁ ነበር። እነዚያን ኮንሰርቶች ካዘጋጁት መሀል አበበ ባልቻ ተቀዳሚ ነው። አበበ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም የስፈሥነጥበብ ዝግጅት ኃላፊ ሆኖ የሠራበት ጊዜ በጣም የሚያስደስተው ጊዜ እንደሆነ ይናገራል።
ሌላው አበበ ባልቻ የሪፖርተር ጋዜጣ ባለድርሻ የነበረ ሲሆን በ1994 ለአቶ አማረ ሙሉ ለሙሉ ድርሻውን ሰጥቷል።
የትዳር ህይወት
አበበ ባልቻ የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ ከተዋወቃት መዓዛ ብሩ ጋር ቤተሰብ የመሠረተ ሲሆን የተጋቡትም አናስገባም ሠርገኛ እደጅ ይተኛ ሳይባል ሳይጨፈርላቸው ኢራን ቴህራን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ነው። አበበ ባልቻ የሁለት ወንድ ልጅ እና የአንድ የሴት ልጅ አባት ነው።
አበበ ባልቻ የሸገር ሬድዮ መሥራች ሲሆን ጣቢያው እዚህ ደረጃ እንዲደርስም ትልቅ ታሪካዊ ሥራ ያከናወነ ነው። ባለቤቱ መአዛ ብሩ የሸገር ሬዲዮ መስራች እና የጨዋታ ፕሮግራም አዘጋጅ መሆኗ ይታወቃል። ከዚህ ጋር በተገናኘ አበበ ባልቻ የሚሰራቸውን ስራዎች ላይ ከፍተኛ ሂስ እንደምሰጠው እርሱም ደስተኛ መሆኑ ተናግሯል።
ከ10 አመት በፊት የ60 ኛ አመቱ ሲያከብር እንደተናገረው የህይወቱ አመታት በሁለት 30 ቢከፈሉ ሁለተኛው 30 ቲያትር በደንብ የሰራበት ቤተሰብ የመሠረተበት ስለሆነ ትርጉም እንደሚሰጠው ተናግራል። ከሰው ለሰው በኃሏ “ባልቻ ኢንተርቴይመንት” የሚል ድርጅት ከፍቶ ፊልሞች ፤ድራማዎች ፕሮዲውስ ያደርግ ነበር።
ተወዳጇ አርቲስት ሙሉአለም ታደሰ ስለአበበ ስትናገር በ1990 ዎቹ አብራው ፊልም የሰራች ሲሆን አክቲንግ እንደሱ የሚወድ ሰው አይቼ አላውቅም። በሥራው ቀልድ የማያውቅ በዲስፕሊን የሚሠራ አርቲስት በመሆኑ ብዙዎች አክብሮት ይቸሩታል ትላለች።
በአሁኑ ሰአት የሸገር ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ እያገለገለ ሲሆን የተለያዩ ትረካዎችንም ያቀርባል።ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ከጤና ጋር የተያያዙ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆንም ሰርቷል።