ታደሰ ሙሉነህ

ታደሰ ሙሉነህ

ውልደት እና ትምህርት

‹‹በመምህሮቼ ለተለያዩ ንባቦች እኔ እመረጥ ነበር፡፡…››ተወዳጅ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ማእከል ለሀገራቸው የሰሩ ሰዎችን ግለ-ታሪክ እያፈላለገ ለታሪክ መሰነዱ ብዙዎችን ያነቃቃ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ ታሪኩን የምንሰንደው ሰው ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ ሲባል ለብዙዎች ወደ ሚድያው መምጣት ምክንያት የሆነ ሰው ነው፡፡ ቅድስት ወልዴ እና እዝራ እጅጉ ታሪኩን እንደሚከተለው አቅርበውታል፡፡

ከልጅነት እስከ እውቀቱ ያለፈባቸው እያንዳንዱ የሕይወት መስመሩ አስተማሪ የሆነው ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በ1944 ተወለደ፡፡ በእደ ማርያም ትምህርት ቤት ከመማሩም በተጨማሪ ለወላጆቹ ሁለተኛ ልጅ ሲሆን በወቅቱ ጥሩ በሚባለው በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ለተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ልዩ ትዝታ የነበረው ታደሰ ‹‹የትምህርት ቤታችን መምህራን ጥሩ ትምህርት ሲያስተምሩን እኛ ተማሪዎቹም ጥሩ እውቀትን እንቀስም ነበር ››ሲል ትዝታውን ይገልፀዋል፡፡ ገና ትንሽ ልጅ ሳለ መምህራኑ በትምህርት ክፍለ-ጊዜ እርሱ እየተነሳ እንዲያነብ ምርጫቸው ያደርጉት ነበር፤ይህ ደግሞ በልጅነቱ ለጋዜጠኝነት ሙያ ልዩ ፍላጎት እንዲያድርበት ካደረጉት መነሻዎች አንዱ ነበር፡፡
ከልጅነቱ በታላላቆቹ የተባለውን ብቻ የሚያደርግ ሲሆን ተው ከተባለ ፈፅሞ የማያደርግ ነበር፤አብዛኛውን ጊዜውንም ትምህርቱ ላይ እና የተማረውን በማጥናት ያውል ነበር፡፡ ጎበዝ ተማሪ የነበረው ታደሰ ወደ ዩኒቨርሲቲም ተቀላቅሎም ተምሯል፡፡

የጋዜጠኝነት ጅማሮ

መልሱ ፍርሃት ሆነ ጭንቀት ያልታከለበት እሺታ ነበር፡፡ የአማርኛ ዜና ክፍሉ ቴክኒሻኑ እና የዜና አስፈፃሚው ዝግጅት አድርገዋል፤ለወትሮው ቢሆን የሰዓቱ የዜና አንባቢም በሰዓቱ ተገኝቶ መዘጋጀት ነበረበት፡፡ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ዜና አንባቢው እንኳን ሊዘጋጅ ሊመጣም አልቻለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስተት የተለመደም ስላልሆነ ተጠባባቂ ዜና አንባቢም አልነበረም፤ዜናው ደግሞ በአንባቢው አለመምጣት ሳይነበብ ሊቀር አይችልም ፤ምክንያቱም የሐገሩቷን እንቅስቃሴ በሙሉ ነዋሪው ጆሮውን ቀስሮ ለማድመጥ የሚጠብቅበት ሰዓት ነበር፡፡ ብቸኛ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩት አልፎ አልፎ ዜናዎችን አቅርበው የሚያውቁት የአማርኛ ዜና ክፍል ኃላፊ ነበሩ፤በውል ባልታወቀ ምክንያት ደግሞ እርሳቸውም ዜና ማቅረቡን አልፈለጉትም፡፡ በዚህ ጭንቀት ውስጥ ሳሉ ማታ ማታ ስለ አሰራሩ ስቱዲዮ እየገባ እንዲመለከት የተፈቀደለትን ልጅ በድንገት ያዩት ልባቸው ተከፋፈለ ፤‹‹ልጁን በድፍረት ዜናውን እንዲያነብ ወደ ስቱዲዮ እንዲገባ ልፍቀድለት አሊያስ እራሴው ልግባ ››በሚል ሲያስቡ ቆይተው ሰዓቱ ደረሰ፡፡ ቢንተባተብና፣የስቱዲዮ ቤተመቅደሳዊ ድባብ ቢያስጨንቀው እና መሃል ላይ ቢያቋርጥ የሚለውን ጨምሮ ብዙ መላምቶች ወደ አዕምሯቸው ቢመላለሱም ዳይሬክተሩ ውሳኔያቸውን አስቀመጡ ፤‹‹ትሞክር›› በሚል ነፍሱ ጋዜጠኝነትን ለምትሻው ለዚህ ተለማማጅ ጥያቄን ሲያቀርቡ መልሱ ፍርሃት ሆነ ጭንቀት ያልታከለበት እሺታ ነበር፡፡

ወደ ስቱዲዮ በመመላለስ ያለውን ስርዓት ሲከታተል የነበረው ይህ ተለማማጅ እንዳየው ከሆነ የትኛውም ሃላፊ ከጋዜጠኛው ጋር ስቱዲዮ ገብቶ አያውቅም፤ ከእርሱ ጋር ስቱዲዮ መግባታቸው ያበላሸው ይሆን? ከሚል ጭንቀት መሆኑን ስለተረዳ የእ” ርሳቸውም መኖር በመርሳት እየሞከረ ባለበት ሰዓት ነው ማንበቡን እንዲጀምር እና አየር ላይ እንዳለ የሚጠቁመው የስቱዲዮ ቀዩ መብራት ብልጭ ያለው፡፡ ዜናው ወርቃማ ድምፅ የተቸረው በዚህ ልጅ መነበቡን ጀመረ፤‹‹እንደምን አመሻችሁ ዜና እናሰማለን፤ዜናውን የማቀርብላችሁ ታደሰ ሙሉነህ ነኝ፡፡››ያለምንም መደነቃቀፍ ሆነ ስህተት ዜናውን አንብቦ አጠናቀቀ ፤እጅጉን ተጨንቀው የነበሩትም ዳይሬክተሩ ዜናው ሲጠናቀቅ ቅልጥ አድርገው በደስታ ጮኹ፡፡

የጋዜጠኝነት ሕይወት

‹‹የልጅነቱ አኳኃኑ ለጋዜጠኝነት ያለውን ፍላጎት በግልፅ የሚያሳይ ነበር›› በዜና ማንበብ አጋጣሚ የተጀመረው የጋዜጠኝነት ጅማሮው ቀጥሎ በኢትዮጵያ ራዲዮ ለሩብ ምዕተ ዓመታት ያህል ማለትም ከ1959 እስከ 1985 ዓ.ም ያንን ውብ ድምፅ ብዙዎች አድምጠውታል፤ተምረውበታል፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን ‹‹ከሁሉ ሰው ጋር የመግባባት ችሎታ ያለው የሙያ ሰው ነው ፤እናም መጀመሪያ እኔ ተቀጥሬ ስገባ እርሱ የእሁድ ጠዋት እና አጠቃላይ የፕሮግም ሃላፊ ነበር›› ብሎ የሚመሰክርለት ታደሰ ሙሉነህ ለራዲዮ ጋዜጠኝነት በሚል ወደ ሙያው ከመግባቱ በፊት የወሰደው አንድም ትምህርት ባይኖርም በብዙዎች የሚታወስ ድንቅ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያን ከተቀላቀለ በኋላ ግን በበርካታ ሃገራት ተዘዋውሮም የተለያዩ የጋዜጠኝነት ትምህርቶችን ቀስሟል፡፡

በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በርካታ የራዲዮ ዘርፍ ለበርካታ ፕሮግራሞች መጀመር ተጠቃሽ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ዝናሽ ማሞ ገና ትምህርቷን ካጠናቀቀችበት ጊዜ ጀምሮ ታደሰ ሙሉነህን ታውቀዋለች፤ስለ ጅማሮዋም ስታስታውስ‹‹በ1976 ዓ.ም የሶስተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ነው ስራ ለመፈለግ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባመራሁበት ወቅት ነው ጋሽ ታደሰን የተዋወቅኩት፡፡እርሱም ማስታወቂያ ሲወጣ መጥቼ እንድወዳደር ነግሮኝ ተለያየን፡፡እርሱ በነገረኝ መሰረትም ማስታወቂያ ሲወጣ ተወዳድሬ አለፍኩኝ እና ለድምጽ ፈተና ወደ ስቱዲዮ በገባሁበት ጊዜ ነው ዳግም ያገኘሁት፡፡በእነዚህ ሁለት ጊዜያት አዕምሮዬ ወስጥ የቀረው ነገር ግን መልካም እና ቅን ሠው እንደነበር ነው፡፡››ስትል ያንን ግዜ ታስታውሰዋለች፡፡

አድማጮች በተለየ ሁኔታ ለታደሰ ልዩ አክብሮት እና አድናቆት ነበራቸው፤የቅዳሜ ከሰዓት፣የእሁድ ጨዋታ እና የእሁድ ቀን እርሶም ይሞክሩት ፕሮግራሞች ታደሰ ይሰራው ከነበሩትም ውስጥ ጉልህ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ አቶ ጸጋዬ ታደሰ በሮይተርስ የዜና ወኪልነት የሰሩ ሲሆን የታደሰ የጋዜጠኝነት ችሎታ ከልጅነት ፍላጎቱ ጀምሮ የመነጨ መሆኑን ሲመሰክሩ ‹‹እኔ እና ታደሰ ጓደኛ ብቻ ሳንሆን ዘመዳሞች የእህት እና የወንድም ልጆች ነን፤ታላቁም ስለሆንኩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱ በኋላ እኔ ነኝ ያሳደኩት እንደ ታላቅ ልጄም ነው፡፡ እኔ በምሰራው ስራ በመደነቅ ማታ ማታ ሁሌም ይጠይቀኝ የነበረው ጥያቄ ልክ ቃለ መጠይቅ እንደሚደረግ ሰው በመሆን ነበር የምሰማው፤እርሱም ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የተዘጋጀ አይነት ነበር፤ታደሰ ገና በልጅነቱ አኳኋኑ በሙሉ ለጋዜጠኝነቱ ያለውን ፍላጎት በግልፅ የሚያሳይ ነበር፡፡በተጨማሪም እኔ ትምህርትህን በርትተህ ተከታተል ስለው ይማርበት በነበረው በእደ ማርያም ትምህርት ቤት እየተማረ ለእኔ ሳይነግረኝ ራዲዮ ላይ ይለማመድ ነበር፡፡››ሲሉ በትውስታ የእርሱን የልጅነት የነፍሱን መሻት ይገልጹታል፡፡

ታደሰ ሙሉነህ እያንዳንዷ ሰዓት እና ደቂቃን በአግባቡ የመጠቀም ጠንካራ ልማድ እንዳለው በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ የሚመሰክሩለት ሰው ነው፤ ስለእርሱ የስራ ትጋትም ሲመሰክሩ ምንም ይፍጅ ሌት ሆነ ቀን ቁጭ ብሎ ስራውን በአግባቡ የሚሰራ ሰው ነበር ሲሉ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ዝናሽ ማሞ‹‹ተቀጥሬ አንድ ሁለት ዓመት ከሰራሁ በኋላ ወደ እሁድ ጠዋት ፕሮግራም እንድቀላቀል ተደረገ፤ይሄም የጋሽ ታደሰን የጋዜጠኝነት ህይወት፣ብቃት እና የአስተዳደር ችሎታውን በቅርበት የማየት እድሉ እንዲኖረኝ አድርጓል፡፡በጣም የተደራጀ እና ጥንቁቅ ሰው እንደነበር አይቻለሁ፡፡ማክሰኞ ማክሰኞ ሁሉም ሰው እቅድን በማቀድ ሁሉም የራሱን ሃሳብ የሚሰጥበት ሲሆን እቅዱ በዚህ መልኩ ዳብሮ ሁሉም በእቅዱ መሰረት ተሯሩጦ ሰርቶ አርብ ኤዲት አድርጎ አጠናቆ ለእለቱ አስተናጋጅ ይሰጣል፡፡ ቅዳሜ ደግሞ ለኮንቲኒቲ የሚሆን ፅሁፍ ይዘጋጃል፡፡

እሁድም ከፕሮግራሙ መጀመር በፊት አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ በመገኘት ሁሉም ከተጠናቀቀ በኋላ ነበር ወደ ቀጥታ ስርጭቱ የሚገባው፡፡ይሄ የተስተካከለ እና የተደራጀ አሰራሩን ተምሬበታለሁ፡፡ ››ስትል ከታደሰ ሙሉነህ ጋር የሰራችባቸው ጊዜያት ምን ያህል በጥንቃቄ እና በስርዓት ይሰራ እንደ ነበር በትውስታ መለስ ብላ ታነሳዋለች፡፡ የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም አስተባባሪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ስራ ላይ ከአንጋፋዎቹ ገዳሙ አብርሃ፣ጳውሎስ ኞኞ እና አሸናፊ ዘደቡብ በተጨማሪ አባይነሽ ብሩ፣አዲሱ አበበ፣ንጉሴ አክሊሉ፣ታምራት አሰፋ፣ብሩክቲ መላኩ፣መዓዛ ብሩ እና ተፈሪ አለሙአብረውት ሰርተዋል፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን ታደሰ ሙሉነህን እንደ ጋዜጠኛ አለፍ ሲል እንደ አለቃ ሲያስበው ‹‹ለጋዜጠኝነት የተፈጠረ ሰው ነው፤ሁላችንም ጋሽ ታዴ ብለን ነው የምንጠራው፤ስራ ሲጀምር የመጀመሪያ ስልጠና ከሰጡን ሰዎች ውስጥ አንዱ እሱ ነው፡፡ ከስልጠናው ሌላም በሚሰራቸው ስራዎች እንደ አርዓያችን በማየት እርሱን አስመስሎ ለመስራት እንሞክር ነበር እና የእርሱ ተፅዕኖ በጋዜጠኛው በተለይ በራዲዮ ጋዜጠኛው ላይ ከፍ ያለ ነበር፡፡

ግላዊ የሆኑ ቃለ መጠይቆች በተለይ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ይደረግ የነበረው ደረቅ ያለ ነበር፤በጣም ዘና ያሉ እና ህብረተሰቡ በፊት ለፊት የሚያውቃቸው ሳይሆን ከጀርባ ያሉ ያልተሰሙ እንደ የቤተሰብን ጉዳይ የያዙ ጉዳዮችን ለቀቅ ያሉ በማድረግ እርሱ በራሱ ምልከታ በተለየ ሁኔታ በሚገባ ይሰራበት ነበር፡፡›› ፍጹም ደከመን ሳይል የሚሰራው ታደሰ ለራዲዮ ስራ ያለውን ፍቅር የሚያቁት ጓደኞቹ ታዴ ራዲዮ ላይ ሳይሰራ ከዋለ ያመዋል እስኪሉ ድረስ በሁሉም የራዲዮ ፕሮግራሞች እና ዜናዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ ነበረው፡፡

ጋሽ ታደሰ ስብሰባ ሲመራ አቤት የነበረን ደስታ የምትለው ጋዜጠኛ ዝናሽ ማሞ ‹‹አንዳንዶች ስብሰባን ሲመሩ በጣም ያረዝማሉ፣ድግግሞሽ ይኖረዋል እናም ሰዓቱ ይለጠጥ እና አሰልቺ ይሆናል፡፡ጋሸ ታደሰ ከሆነ ግን በሰዓቱ ነው የሚጀምረው ፣የሚያነሳውን ነጥብ አይስትም፤ሰዎችም የሚያነሱት ሃሳብ ካለ እድል ይሰጣል፡፡የተነሳበትን ዓላማ ሳይስት መነሳት ያለበትን አንስቶ ሳያረዝም ሳያሳጥር የሚጨርስ ጥሩ ብቃት ያለው የስብሰባ መሪ ነበር፡፡››በማለት የምትመሰክርለት ጋሽ ታደሰ አብረውት በሚሰሩት ሰራተኞች ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡

የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ሀያ ዘጠነኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት ትዝታህን አጫውተን ሲሉት ቀልድ አዋቂው ታደሰ‹‹ሀያ ዘጠነኛ ዓመት ስትሉ እዚህ ላይ የእኛ እድሜ ሊጨመር ነው፤በየሳምንቱ የተለያየ ትዝታ ነው በእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ላይ ያለን እንደው ብፅፈው እራሱ አያልቅም ፤በተለየ ግን ሁሌም የማሰላስለው እሁድ ጠዋት ላይ ይሰሩ የነበሩት ሁሉም ጭምር የሚያሰላስሉት ይመስለኛል፡፡››ሲል ነበር ያወሳው፡፡ ታደሰ ሙሉነህ በኢትዮጵያ ራዲዮ ከሪፖርተርነት እስከ መምሪያ ኃላፊነት ሲደርስ የተለያዩ ድራማዎችንም በመጻፍ አቅሙንም ማሳየት ችሏል፡፡ ደጀኔ አንዱን ድራማውን ሲያስታውሰው ‹‹ የደሞዝ ሰሞን የሚለው ተከታታይ ድራማው በእሁድ ጠዋት ይቀርብ ነበር፡፡በወቅቱ በጣም ተወዳጅ የነበረው ይህ ድራማ ሰዉ ደሞዙን ምን ያደርግበታል፣ምን ላይ ያውለዋል የሚለውን የሚያሳይ ነው፡፡››ሲል ያስታውሰዋል፡፡ ታደሰ ሙሉነህ ለራዲዮ ጋዜጠኝነት ድምፅ ወሳኝ ነው ብሎ ያምናል፤ድምፅ ከሌለ ደግሞ የሚሰራበት ርዕሰ ጉዳይ በሳል መሆን አለበት ሲል ሃሳቡን ያጠንክራል፡፡

የሃሳብ ሰው

‹‹የጋሽ ታደሰ ኮንቲኒቲ እጅጉን የተለየ ነው፤ፅፎ የገባውን ነገር ለአድማጭ ሲያቀርብ ንግግር እንጂ ፍፁም እያነበበ አይመስልም ነበር፡፡ይህም አፃፃፉ ንግግር አድርጎ ያዘጋጀው ሰለነበር ነው፡፡ይህንንም ለእኛ አስተምሮናል፡፡ የሚያነሳቸው ሃሳቦች የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት አኗኗር ሕይወት የሚነካ ፣ጆሮ የሚይዝ ፣አድማጭ ከራዲዮኑ ዞር ሳይል እንዲሰማው የሚያደርግ በጣም አቅም የነበረው ኮንቲኒቲ ነበር የሚፅፈው፡፡ ሃሳቡም፣አቀራረቡም፣አነባበቡም ልዩ ነው፡፡››ስትል ጋዜጠኛ ዝናሽ ማሞ ታደሰ ሙሉነህ ያለውን ሃሳብ እንዴት እንደሚያጋራ እንዴት እንደተማረችበትም ታወሳለች፡፡

እርሶም ይሞክሩት የተሰኘውን ፕሮግራም ለመጀመር ከበላይ ሃላፊዎች ጋር ካቀደ በኋላ ፕሮግራም አቅራቢዎችን በሙሉ ጠርቶ ስለ ፕሮግራሙ አስረድቷቸው ፕሮግራሙ ተጀመረ፡፡የተወሰኑ ጊዜያት ከሰራ በኋላ ሌሎች ባልደረቦቹ እንዲሰሩበት አድርጎ እርሱ እዛው በቦታው እየተገኘ ይከታተል የነበረ ሲሆን ሽልማት የሚያቀርቡትም የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ነበሩ፡፡ በአንድ አጋጣሚም በኢሚግሬሽን እና በፖሊስ መካከል በሚደረገው የጥያቄ እና መልስ ውድድር ላይ ሁለቱም እኩል ውጤት ሲኖራቸው የመለያ ጥያቄን እንዲጠይቅ ታደሰን ጋበዙት፡፡

ጥያቄውን እዛው ባለው ጉዳይ ላይ ተነስቶ የጠየቀው ታደሰ ‹‹እስኪ ሦስት የሴት መኮንኖችን ስም ጥቀስ››በማለት ለኢሚግሬሽን ቡድንጠየቀ፤ተጠያቂውም ሁለቱን አከታትሎ ከመለሰ በኋላ ሶስተኛዋን ‹‹አልማዝ›› ካለ በሁዋላ የአባቷን ስም ከየት ያምጣው ፤ታዲያ በዚያው አዳራሽ ነጭ በነጭ ለብሳ የነበረችው አልማዝ ቆም ብላ ስትታይ ጥያቄውን መመለስ ያቃተው ተጠያቂ ‹‹አይ አልማዝዬ ስንት ዓመት አብረን ሰርተን የአባትሽን ስም ይጥፋኝ››ብሎ መጮኹ ሳቅን ፈጠረ በዚህም እንዲሸነፉ ሆነ፤ታደሰ እንዲህ ያሉ ቀላል የሚመስሉ ግን የማናስተውላቸውን በርካታ ጉዳዮች በትኩረት ይመለከት የነበረ ንስር ጋዜጠኛ ነበር፡፡

ጋዜጠኛ ዝናሽ ማሞ‹‹ጋሽ ታደሰ እንግዶቹን አጫውቶ አዝናንቶ ነው ወደ ቃለ መጠይቅ እንዲገቡ የሚያደርገው፡፡የእርሱ የቃለ- መጠይቅ አደራረግ ፍፁም የተለየ ነበር፡፡አዳዲስ ሰው ጆሮ ሲደርሱ የሚያስደንቁ እንዲህም አለ የሚያስብሉ ከመሆናቸው የተነሳ ቢረዝሙ እንኳ ርዝመታቸውን የማናስተውልበት ጊዜያት የበዛ ነበር፡፡››ስትል የቃለመጠይቅ የማድረግ ችሎታው ምን ያህል እንደነበር ነው የምታስታውሰው፡፡ ታደሰ ሙሉነህ በጋዜጠኛነት ሙያ በቆየባቸው ዓመታት ላበረከተው አስተዋፅኦ በ1994 ዓ.ም የስነ ጥበባት እና የመገናኛ ብዙሃን ሽልማትን ወስዷል፡፡

የትዳር ሕይወት

ታደሰ ሙሉነህ በ1974 ዓ.ም ከሙያ አጋሩ ከወ/ሮ ማርታ አማረ ጋር ትዳር መስርቶ ሕይወቴ በማለት የሰየሟትንም ልጅን ወልዷል፡፡የታደሰ የመጨረሻ ዘመናት ‹‹በጣም ከባድ ስቃይ ውስጥ ነበር፡፡›› ጋሽ ታደሰ በጣም ራሱን የሚጠብቅ፣ንጹህ ፣አለባበሱ፣አካሄዱም፣ንግግሩም ፣ጨዋታው፣ፈገግታው፣ግርማ ሞገስ የተሞላው ልዩ አክብሮት የተቸረው ሰው ነበር ሲሉ አብረውት ይሰሩ የነበሩ ባልደረቦቹ እና ጓደኞቹ በኩራት የሚመሰክሩለት ሰው ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ህመሞች ያጋጥሙት የነበረ ሲሆን በአንድ ወቅት ደግሞ አቶ ጸጋዬ ስለ ታደሰ የህመም ጊዜ ሲያስታውሱ‹‹በደቡብ አፍሪካ ቀዶ ጥገና ያደረገው ጀርባውን አከርካሪው ላይ ነበር፤በዚህም በጣም ከባድ ስቃይ ውስጥ ነበር፡፡ደውዬ ሳወራው ይሄንኑ ነበር ከድምፁ የተረዳሁት፤ሆኖም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡

ጤናውም ጥሩ ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ስራውንም አላቋረጠም፡፡በኋላ ላይ ግን በሽታው ተቀሰቀሰበት እና ወደ ባንኮክ ሄደ፤እንደውም ሁለት ጊዜ ነው የሄደው ሁለተኛ ላይ ሄዶ ከተመለሰ በኋላ ታመሃል የተባለው ኩላሊቱን ነበር፡፡የልብ ሀኪም ቤትም ሲሄድ ከልቡ ጋር የተገናኘ ህመም እንዳለበት ተነግሮት ነበር፡፡በዋነኛነት ግን የኩላሊቱ ስራ ማቆም ነው እኔ የማውቀው ፡፡›› ደጀኔ ጥላሁን ወደ ሁዋላ መለስ ብሎ ‹‹ሻውል ባምነው በተባለ የቀድሞ ጋዜጠኛ አማካይነት የጋሽ ታዴን መታመም ሰምቼ ልጠይቀው ሄጄ ነበር፡በሁዋላም ማረፉን ደውሎ ነገረኝ፡፡››

በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ታደሰ ሙሉነህ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በሚገኘው ቤተክርስቲያን ስርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡ ታደሰ ሙሉነህ ‹‹መመኘት ብቻ ሳይሆን የተመኙትን ለማግኘት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፤ምኞታችን ቤታችን ድረስ አንኳኩቶ አይመጣም ለመሆኑ የምትፈልግበት ቦታ ለመድረስ መታገል ይኖርብሃል፡፡ያሉብህን እንቅፋቶች ሁሉ በአግባቡ መዝለል ይኖብሃል፤ስኬት ለእኔ ከዚህ ሃሳብ የሚርቅ አይደለም፡፡››ሁሌም ቢሆን የሚናገረው ከአፉ የማይጠፋ ጊዜ ቢለዋወጥም ሁሉም ሰው መቼም ቢሆን ሊማርበት የሚገባ ቋሚ አባባሉ ነበር፡፡

መዝጊያ

ከ1970ዎቹ ፈርጦች አንዱ ጋሽ ታደሰ ሙሉነህ ነው፤፤ በተለይ ስለ ሀገራችን የሬድዮ የመዝናኛ ታሪክ ሲነሳ ጋሽ ታደዛ ከአስደማሚ ድምጹ ጋር አንድ ላይ ይነሳል፤፤ ጋሽ ታደሰ ለብዙዎች ፈር የቀደደ፤ መንገድ ያመላከተ ድንቅ ባለውለታቸው ነው፤፡ ብዙዎች ለቁምነገር የደረሱ ሁሉ ይህንን በሙሉ አንደበታቸው ይመሰክሩታል፡፡ ጋሽ በህይወት በኖረባቸው ዘመናት ከልብ የሚወደውን የጋዜጠኝነት ሙያ ለማስከበር ብዙ ታግሏል፡፡ አዳዲስ የሚመጡ የሚድያ ፍቅር ያሳደሩ ታዳጊዎች ፕሮፌሽናሊዝምን በጠበቀ መልኩ እንዲሰሩ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ ሰርቶ የሚያሰራ ብርቱ አለቃ ስለነበር ብዙዎች ዛሬ ስለ ጋሽ ታደሰ ሙሉነህ አውርተው የሚጠግቡ አይደሉም፡፡

ከ40 አመት በፊት የእሁድ ጠዋት የሬድዮ ፕሮግራም እጅግ ተናፋቂ እንዲሆን ካደረጉት መካከል ጋሽ ታደሰ ቀዳሚው ነው፡፡ በዚህ ልዩ ጥረቱም ዛሬ ህይወቱ አልፎ እንኳን ስሙ በክብር ይነሳል፡፡ የቆዩ የተቀረጹ የጋሽ ታዴን ድምጽ ጥሞና ሰጥተን ብናደምጥ የሰው ልጅ የተፈጥሮ ችሎታ በእጅጉ እናደንቃለን፡፡ ጋሽ ታዴ የእውነትም ይችላል፡፡ እንደ ጋሽ ታዴ አይነት ሰዎች በየአመቱ ታሪካቸው በደማቅ ብእር ቢጻፍ በሬድዮ ፕሮግራሞች ላይ ቢዘከሩ ከዚህ በላይ ትልቅ ነገር ወደየትም አይገኝም፡፡ስለ ሀገራችን የሬድዮ ታሪክ አንስተን ጋሽ ታደሰን ስናነሳ ታሪኩን የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ዛሬ ለስኬት የበቁት እንደ መአዛ ብሩ ፤ ተፈሪ አለሙ ፤ አባይነሽ ብሩ ፤ አዲሱ አበበ ያሉ በሳል የሚድያ ሰዎች ከጋሽ ታደሰ ስር ሆነው እውቀትን የቀሰሙ ናቸው፡፡ ጋሽ ታደሰ ታሪኩ በወጉ ሊሰነድለት የሚገባ ፤ ድምጹ በአርካይቭ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን እንደ ማስተማሪያ ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባ ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንደተወዳጅ ሚድያ ጋሽ ታደሰን በዚህ መልኩ ገልጸነዋል፡፡ / ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና በጋዜጠኛ ቅድስት ወልደ ዛሬ ታህሳስ 21 2014 ተጻፋ














Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *