ማስረሻ ፍቅሬ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ ከ120 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል ጋዜጠኛ ማስረሻ ፍቅሬ ይጠቀሳል፡፡ ማስረሻ ፍቅሬ ከ20 አመት በፊት በለገዳዲ ሬድዮ ጽሁፍን በማቅረብ ወደ ሚድያ አለም ዘለቀ ፡፡ ከዚያም ለተወሰኑ አመታት በመምህርነት ካገለገለ በኋላ ባለፉት 10 አመታት በሚድያው ዘርፍ ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የቻለ ነው፡፡ ማስረሻ ማነው? ግለ-ታሪኩን አጠር አድርገን አቅርበናል፡፡
ውልደትና ትምህርት
ጋዜጠኛ ማስረሻ ፍቅሬ አባቱ አቶ ፍቅሬ አንዳርጌ ሲባሉ እናቱ ወ/ሮ ብዙነሽ አስፋው በመባል ይታወቃሉ፡፡ ማስረሻ በደቡብ ክልል ልዩ ስሙ አባያ እርሻ ልማት በሚባል ቦታ በታህሳስ 8፤ 1973 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡ የልጅነት ጊዜው ከተወለደበት አካባቢ ተፈጥሮ ጋር በጣም የተቆራኘ ነበር፡፡ የአባያ ሐይቅ፣ የብላቴ ወንዝ፣ የበረሃ ሎሚና በደናን የመሳሰሉ የበረሃ እፅዋቶች፣ ፍራፍሬ፣ የአርብቶ አደሮች ህይወትና መልክአ- ምድሩ ሁሉ የልጅነት ሕይወቱ ትዝታና ቡረቃዎቹ ናቸው፡፡ ይህም በልጅነት ሕይወቱ ያደረበት ተፅዕኖ በኋላም የጂኦግራፊ ትምህርት እንዲያጠና ምክንያት ሆኖታል፡፡
እስከ 6ኛ ክፍል በአባያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተማረ በኋላ ወደ አዲስ አበባ አያቱ ዘንድ በመምጣት 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን በፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረ፡፡ ሀለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በመድሀኒዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ የዲፕሎማ ትምህርቱን በኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ተከታትሎ በ1997ዓ.ም በጂኦግራፊ ትምህርት ተመርቋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ፕሮግራም በጂኦግራፊ እንዲሁም በጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን ትምህርቶች ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት በ2002 እና 2003 ዓ.ም በተከታታይ በመጀመሪያ ዲግሪዎች ተመርቋል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪውንም በመቀጠልና የጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን ትምህርትን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማጥናት ሊመረቅ ችሏል፡፡
የስነ-ፅሁፍ፣ ቲያትርና ጋዜጠኝነት ዝንባሌዎች
ጋዜጠኛ ማስረሻ ፍቅሬ፤ የቲያትርና ስነ-ፅሁፍ ዝንባሌውን ለማርካት በኢትዮጲያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ኮልፌ ቅርንጫፍ ውስጥ በተቋቋመው “ኢትዮ ራዕይ የቲያትርና የጋዜጠኝነት ክበብ” ለ5 ዓመት የመድረክ ቲያትሮችን በመስራት ተሳትፏል፡፡ ማስረሻ ከ “ኢትዮ ራዕይ” በኋላ መሳለሚያ ሰፈረ-ገነት በሚባለው አካባቢ በተቋቋመው “ከዋክብት የቲያትር ክበብ” ውስጥ በርካታ ቲያትሮችን በመስራት ለህዝብ በማሳየት ተሳትፏል፡፡ ቲያትሮችንም በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጪ ለህዝብ አቅርበዋል፡፡ በእነዚህ ክበባት ውስጥ ከቲያትር በተጨማሪ የጋዜጠኝነት ልምምዶችንም በማድረግ በስነ-ፅሑፍ ይሳተፍ ነበር፡፡
የጋዜጠኝነት ሀ ሁ
ማስረሻ ፍቅሬ የቲያትር ክበባት ውስጥ እየተሳተፈ ሳለ ነበር በለገዳዲ ሬዲዮ በፍሪላንሰርነት ለመስራት አጋጣሚው የተፈጠረው፡፡ አጋጣሚውም እንዲህ ነው፡፡ የአንድ ጓደኛውን እውነተኛ የፍቅር ታሪክ በአጭር ልብወለድ መልክ ያዘጋጀውና ከቲያትር ክበብ ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ዛሬም ደረስ ጓደኛው ለሆነው መርእድ አባተ እንዲገመግምለት ያሳየዋል፡፡ መርእድም እንዲያስተካክል አስተያየት ከሰጠው በኋላ መስተካከሉን ሲመለከት ለምን ወደ ለገዳዲ ሬዲዮ አንወስደውም? በሚል ሀሳብ ያቀርብለታል፡፡በለገዳዲ ሬዲዮ በወቅቱ የነበረችው የሻረግ ነጋሽ ታነበውና ስራው ማለፉንና መጥቶ እንዲተርከው ትነግረዋለች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማለትም ከ1992 – 1997 ዓ.ም ድረስ በጣቢያው የቅዳሜና እሁድ ፕሮግራሞች ማለትም ማህበራዊ፣ ከትምህርት አምባ፣ ብእር በሴት አምባ ፣ በእሁድን ለአንድ አፍታና በሌሎችም ፕሮግራሞች ላይ መጣጥፎችን፣ አጫጭር ልብወለዶችን፣ ወጎችንና የሬዲዮ ድራማዎችን በመፃፍ፣ በማንበብና በመተረክ በፍሪላንሰርነት ሰርቷል፡፡ ማስረሻ በለገዳዲ ሬዲዮ ከቅዳሜና እሁድ የመዝናኛና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች በተጨማሪ በጣቢያው መደበኛ የሬዲዮ ትምህርት ፕሮግራሞችም ላይ እንደ መምህር ወይም ትምህርት አቅራቢ በመሆን ሰርቷል፡፡ በለገዳዲ ሬዲዮ መስራቱም ለጋዜጠኝነት ሞያ ክብርና ፍቅር እንዲኖረው አድርጎለታል፡፡
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት
ማስረሻ የ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ማንበብና መፃፍ የማይችሉና በተለያዩ ምክንያቶች መደበኛ ትምህርት መማር ያልቻሉ ወጣቶች ፣ አዛውንትና ጎልማሶችን በወቅቱ በየቀበሌው ይሰጥ በነበረውን የጎልማሶች ትምህርትን ያለምንም ክፍያ በበጎ ፍቃደኝነት አስተምሯል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ለዚህም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳትፎ በ 1994 ዓ.ም የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥቶታል። ሌላው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሜሪጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅት ውስጥ ያበረከተው ነው። በድርጅቱ ውስጥ HBC (Home Based Care) የሚባል የቤት ለቤት የእንክብካቤ ፕሮግራም ነበር። ፕሮግራሙ በተለያዩ ህመምች በተለይ ደግሞ በኤች. አይ . ቪ. ተይዘው ከአልጋ ለዋሉና አቅመ ደካማ ለሆኑ ሰዎች የቁሳቁስ ፣ ቀላል ወይም የመጀመሪያ ደረጃ የሚባል የህክምና እርዳታ እና የስነልቦና ድጋፍን የሚያደርግ ነው። እናም ማስረሻ በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ ድጋፉን ለሚሹት ሁሉ አስተዋፅኦ አድርጓል።
ሌላው በ 1999 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ ላይ በሱማሌ ክልል አውበሪ (ተፈሪ በር) በሚባል ቦታ ተመድቦ ቆጠራው እንዲሳካ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። እነዚህ የበጎፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ መሳተፉ የመንፈስ እርካታን ያገኘ ሲሆን ለተጨማሪም በጎ ስራ እንዲነሳሳ አድርገውታል።
መምህሩ ጋዜጠኛ
በ1997 ዓ.ም ከኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ከተመረቀ በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኦዳ ቡልዲግሉ በምትባል አንዲት የገጠር ቀበሌ በመምህርነት ለአንድ አመት ያህል አገልግሏል፡፡ ወደ አዲስ አበባም በመመለስ በጉለሌ ፋና እና በመድሃኒዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለ4 ዓመታት የታሪክ፣ የሲቪክና የጂኦግራፊ ትምህርቶችን አስተምሯል፡፡ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ከተመረቀ በኋላ ሬዲዮ ፋናን በ 2003 ዓ.ም ተቀላቀለ፡፡ ከጀማሪ ሪፖርተርነት እስከ ረዳት ዋና አዘጋጅነት በደረሰበት በሬዲዮ ፋና ከትምህርታዊ ፕሮግራሞች “የህብረት ስራ” ፣ “መንገድ” ፣ “ግብርና” ፣ “ምርት ገበያ” በቋሚነት በማዘጋጀትና በማቅረብ እንዲሁም “እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?” እና “ተጓዥ ነቃሽ”ን የቀጥታ የስልክ ውይይት ፕሮግራሞችን በመምራት፣ ወቅታዊ የዜና ርእሰ ጉዳይ የሚተነተንበትን “ዳሰሳ”ን ለረጅም ጊዜ አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡ ማስረሻ ፍቅሬ በሬዲዮ ፋና በርካታ ህዝባዊ የመድረክ ውይይቶችንም መርቷል፡፡ ከመዝናኛ ፕሮግራሞችም መካከል ከተረካቸው ትረካዎች “ካፖርቱ” ፣ “እያስመዘገብኩ ነው” ፣ “ሄላ” ፣ “የደስታ አረፋ” ፣ “ለነፋስ የተበተነ አመድ” ፣ “ካርሜን” ፣ “ምኞት” ፣ “የእሁዱ ቀጠሮ” ፣ “በሸለቆው መሃል” ፣ “መቶ ሺ ብር” ፣ “እንቆቅልሽ” ፣ “አንተነህ” ፣ “እስስት” ፣ “ጠቋሚው የልብ ትርታ” ይጠቀሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የቴሌቪዥን ወቅታዊ ውይይትን በማዘጋጀትና በመምራት እና በትምህርታዊ ፕሮግራሞች አርታኢ በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡
የጋዜጠኛው የመስክ ስራ ትውስታዎች
የመስክ ስራ በጋዜጠኝነት ህይወቱ ውስጥ በርካተ ሀገራዊ እውነታና ቁምነገሮችን እንዲረዳና ማህበረሰብን እንዲያውቅ አስችሎታል። ሬዲዮ ፋና በተቀጠረ በሳምንቱ ነበር የመጀመሪያ የመስክ ስራውን የጀመረው። የተጓዘውም ወደ ደብረማርቆስ ነበር። ከዚያም ወደ አራቱም የሀገራችን አቅጣጫዎች ተጉዞ የህብረት ስራ፣ የግብርና ፣ የመንገድ፣ የምርት ገበያና የቡናና ሻይ ፕሮግራምችን በመስራት ከተወሰኑ አካባቢዎች በቀር አብዛኛውን የሀገራችን አካባቢዎች ለማወቅ ችሏል። በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች የተመለከታቸውን እና ያስተዋላቸውን ባህሎች ፣ ወግና ልማዶችን በፕሮግራሞቹ ለአድማጮች ጆሮ እንዲደርስ አድርጓል። ልክ እንደዚህ ቀደሞቹ ጋዜጠኞች ለመስክ ስራ ወደ ክፍለ ሀገር ሲንቀሳቀስ በህዝብ ትራንስፖርት መሆኑ ከብዙ ሰዎች ጋር እንዲተዋወቅ እና ከሰዎችም ሀሳብን እንዲጋራ እድል ፈጥሮለታል ። መኪና የማይገባባቸው የገጠር መንደሮችን በእግር አቋርጧቸዋል። በአህያና በፈረስ ጀርባ ተጉዞባቸዋል። ሆቴልና የእንግዳ ማረፊያ በማይኖርበት አካባቢ ደግሞ በአርሶ አደሮች ቤት አድሮም ያውቃል ። ያቺ አነስተኛዋ የውሎ አበልም ስታልቅም ቁርስን አልያም ምሳን መዝለልም ለሱ አዲስ ነገር አይደለም።
ፈታኝ ከነበሩት የፊልድ ገጠመኞች አንዱ በጋምቤላ ክልል ያጋጠመው ነበር። የከተማውን መሬት አለአግባብ ለግለሰቦች በማስተላለፍ የግል ጥቅማቸውን አንዳንድ ባለሞያዎችና የስራ ሀላፊዎች መኖራቸውን የህብረተሰቡን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ይደርስበታል። ከሀላፊውና ከባለሞያዎች ቃለ መጠይቅ በኋላ ንገሩን እንደደረሰበት ሲረዱ ለመተናኮል ማሰባቸውን ስለደረሰበት ከሬዲዮ ጣቢያው የስራ ሀላፊዎች ጋር በመነጋገር ቶሎ ከተማውን ለቆ እንዲወጣ በመደረጉ ምንም ክፉ ነገር ሳይደርስበት ሊያመልጣቸው ቻለ። የህብረተሰቡ ምሬትና ከስራ ሀላፊዎቹ ጋር የተደረገው በማስረጃ የተደገፈው ቃለ ምልልስ ለአየር ከበቃ በኋላ ቀድሞም የስነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ጉዳዮን ያውቀው ነበርና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ከህገ ወጥ እንቅስቃሴው ጋር ግንኙነት በነበራቸው አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ችሏል ።
ለመስክ ስራ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች በስራ አጋጣሚ የሚተዋወቃቸው ሰዎች ለጋዜጠኛና ለሙያው ያላቸውን ጠለቅ ያለ አክብሮትና ፍቅር እንዳላቸው ተመልክቷል። አድማጭ ተመልካቾች በሬዲዮ በድምፅ የሚሰሙትን እና በቴሌቪዥን ደግሞ በምስል የሚመለከቱትን ጋዜጠኛ በአካል ሲያገኙት የሚፈጠርባቸው መደመም እሱንም ያስደምመዋል። በአጠቃላይ በመስክ የጋዜጠኝነት ስራው የህይወትን ሌላ ገፅታ እንዲመለከት አጋጣሚዎችን ፈጥሮለታል። የኢትዮጵያን የተለያዮ ማህበረሰቦች ወግ፣ ባህልና ልማድ አውቆ እንዲያሳውቅ አስችሎታል። በትምህርት የዳሰሰውን ጋዜጠኝነት በተግባር እንዲፈትሸውና እንዲያገናዝበው አድርጎታል።
ወደ ማስታወቂያው ዓለም
በሬዲዮ ፋና ከተፈጠረለት አንዱና ለሱ ትልቁ የሆነው አጋጣሚ ወደ ማስታወቂያ ሙያ የገባበት ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራው ማስታወቂያ ዳሽን ኬክ ነበር፡፡ ቀስ በቀስም ሞያውን እያዳበረና እያሻሻለ ከ1000 በላይ ማስታወቂያዎችን ለ250 ድርጅቶች አዘጋጅቶ አንብቧል፡፡ ለአመታት ከሰራቸው እንዲታወቅበትና እንዲታወቁ አስተዋፅኦ ካደረገላቸው ድርጅቶች ወይም ማስታወቂያዎች መካከል ቴክኖ ሞባይል፣ ቃሊቲ ብረታብረት፣ ሱፐርፋይን፣ ቤንቬኒዶ፣ ሀገሬ ውሃ፣ ሚ ኤንድ ማይ ወተት፣ ኢስት ስቲል የአርማታ ብረት፣ ሮድሻይን ጎማ፣ ፉጂያ የመኪና ባትሪ፣ ፎግ ዲኦዶራንት፣ ቀርሜሎስ አስጎብኚ፣ ፕሮሚስ ውሃ፣ ጂ ኤስ ኤም ሲል ኮንሲላንት፣ ዲኦ ማክስ ዲኤም 12፣ ሱፐር ማግ፣ ሀቄ ስፖርት ከጥቂቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡በተጨማሪም በርካታ የጤናና የአካባቢ ጥበቃ የሬዲዮ ማስታወቂያዎቹ ከማስረሻ የማስታወቂያ ስራዎች መካከል ይገኛሉ፡፡
በሬዲዮ ፋና ያገኘው የማስታወቂያ ስራ ልምድና እውቅና የተግባቦትና ማስታወቂያ ድርጅት እንዲከፍትም አድርጎታል፡፡ ለሰራቸው የሬዲዮና የቴሌቪዥን የማስታወቂያ እንዲሁም የመድረክ መምራት ስራዎች ከበርካታ ድርጅቶች የምስጋናና የአድናቆት ሰርቲፍኬቶችን ተቸሮታል፡፡ ከዶክመንታሪ ስራዎቹ ውስም ከዓለም አቀፍ የውሃ ምርምር ተቋም (IWMI) ጋር የሰራው ” water value for sustainable development” የተሰኘው ይገኝበታል፡፡
የቤተሰብ ሕይወት
ጋዜጠኛ ማስረሻ ፍቅሬ ለቃለ መጠይቅ ስራ ከቢሮዋ ሄዶ ከተዋወቃት የትዳር ጓደኛው ዳግማዊት ፀጋዬ ሁለት ወንድ ልጆችን (በናያስ እና ኤልካን) ወልዷል፡፡
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላትንና የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሀሳብ የሚንጸባረቅበትና የታመነበት ነው፡፡ጋዜጠኛ ማስረሻ ፍቅሬ በሚድያው አለም በቆየባቸው አመታት በሚድያዎች ላይ ከመሳተፍ አንስቶ እንዴት ጥረት በማድረግ ማደግ እንደሚቻል በተግባር ያስመሰከረ ሰው ነው፡፡ በተቻለ መጠን ሙያውን ፕሮፌሽናል ለማድረግ የሄደባቸውን መንገዶች ስናይ ለሙያው ትልቅ አክብሮት እንዳለው ማየት እንችላለን፡፡ ጋዜጠኛ ማስረሻ ፍቅሬ ፈታኝ በሆነው የጋዜጠኝነት ቆይታው የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች ለማየት ችሏል፡፡ ከከተማ ወጥቶ መስራት የገጠር መንገዶች አስቸጋሪ በሆኑበት ሁኔታ ሙያን አክብሮ መሰራት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ ማንም ሊገነዘበው ይችላል፡፡ ጋዜጠኛ ማስረሻ በበርካታ ውጣ ውረዶች አልፎ ዛሬም ለሙያው ክብር እየሰጠ ይገኛል፡፡
የዚህ ዊኪፒዲያ ዋና ግብ የባለሙያዎችን ያልተነገረ ጥረት እያሳዩ የበለጠ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ማድረግ ስለሆነ ጋዜጠኛ ማስረሻም ለሙያው የደከመ በመሆኑ ይህ ጥረቱ ለቀጣዩ ትውልድ እንደ ማስተማሪያ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ የሰራ ሰው ሁሉ በሰራው ልክ ጎልቶ እንዲወጣ መድረኩን ስናመቻችም በእድሜ ታናናሽ የሆኑትም ነገ በርትተው ሙያውን አክብረው እንዲመጡ በማሰብ ነው፡፡ ማስረሻ ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር በማስታወቂያ ኢንዱስትሪው ላይ በመዝለቅ የራሱን ትልቅ አሻራ ለማኖር የቻለ ነው፡፡ በዘጋቢ ፊልም ስራዎችም ሊነገር የሚችል ተግባር የሰራ ነው፡፡ ማስረሻ በበጎ አድራጎት ሰራዎች በመሳተፍም የአርአያነት ተግባሩን በአግባቡ የተወጣ ሰው ነው፡፡ ራሱን በትምህርት ለማሳደግም ከ 3 በላይ ዲግሪዎችን በመያዝ ሙያውን በበለጠ ደረጃ ለማሳደግ ጥሯል፡፡ ጋዜጠኛ ማስረሻ ለራሱ እና ለቤተሰቡ ገቢ መፍጠር ያስፈልጋል በአንድ ገቢ ብቻ አይኖርም የሚል የጸና እምነት ስላለውም ኑሮን ለማሸነፍ ይሯሯጣል፡፡ ጋዜጠኛው እዚህ ከተጻፈለት በላይ ብዙ ያከናወነ ነው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ ግብ የሰዎችን ታሪክ መሰነድ እና ለቀጣዩ ትውልድ ማቀበል ነው፡፡ ስናቀብል ግን የተጨበጠ የተሰራ ሊነገር የሚችል ታሪክ መያዝ አለብን -ልክ እንደ ማስረሻ፡፡ ጋዜጠኛ ማስረሻ በዚህ ብቻ አያቆምም፡፡ ይቀጥላል፡፡ በስራው በሁሉ ነገሩን መልካሙን ሁሉ እንዲገጥመው እንመኛለን፡፡