በአርቲክል ዘርፍ የሚድያ አዋርድ ላይ ምርጥ 5 ውስጥ የገባች
መልካም ሥራ አፈወርቅ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ፣ ከመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የሥራ ታሪክ ጋር በተያያዘ መረጃ ሰጪ ጽሁፎችን ሲያዘጋጅ ነበር ።
ሀገራችን ውስጥ የሽልማት ውድድሮች ሲዘጋጁም በፕሮፋይል ስነዳ ላይ እንደ ተቋም ግለ -ታሪኮችን አጠናክሮ ለንባብ በማብቃት ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ሲያሳካ ቆይቷል።
ይህን የምናከናውነው በተወዳጅ ሚድያ መስፈርት መሠረት ሲሆን ባለፈው አንደኛው ዙር ላይ እንዳደረግነው ተስፋ የሚጣልባቸውን ወጣት የሚድያ ሰዎችን ጨምረን ማንነታቸው መታወቅ ያለባቸውን ባለሙያዎች አለፍ አለፍ እያልን እናስተዋውቃለን። ይህ ማለት ሁሉም ምርጥ 5 ውስጥ የገቡትን እናስተዋውቃለን ማለት አይደለም። ይልቁንም በሚድያ አዋርድ፣በአንደኛው ዙር የህይወት ታሪካቸውን ያልተዳሰሱ ባለሙያዎችን በዚህ ዙር ቅድሚያ እንሰጣለን።
ይህን የምናከናውነው፣ በራሳችን ተነሳሽነት እና “ከመምረጥ በፊት የዕጩን ማንነት ማወቅ” የሚለውን መሪ ርዕስ ተግባራዊ ለማድረግ በማሰብ ነው።
ከድርጅታችን ቀዳሚ ግቦች አንዱ ፣ታሪክን መሠነድ ስለሆነ ፣ይህንኑ ተልዕኮ እናስፈጽማለን ። ይህን በውድድር ወቅት የሚደረግ የማስተዋወቅ ሥራ ስንሠራ ከማንኛውም አካል ምንም ዓይነት ክፍያ የማንቀበል እና ያልተቀበልን ሲሆን ይልቁንም ለዚህ ሥራ ጊዜ እና ባለሙያ በመመደብ ሙያዊ ግዴታችንን እንወጣለን። ይህ ጽሁፍ የምርጫ ቅስቀሳን የማድረግ ግብ የሌለው ሲሆን ይልቁንም የአንዳንድ ተወዳዳሪዎችን ማንነት የማሳወቅ ግብ የሰነቀ ነው። ባለሙያዎችም ሥራቸው ከማንነታቸው ጋር እንዲታወቅ ማድረግ አሁንም ትልቁ ኃላፊነታችን ነው
መልካምሥራ አፈወርቅን በወፍ በረር
ልጅነት – ማርና ወተት
‹‹መልካምሥራ›› ይሉትን ሥያሜ ያገኘችው ከቅድመ አያቷ ነው፡፡ወላጅ እናቷ አያታቸውን በእጅጉ ይወዱ ነበርና ለእሳቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሴት ልጃቸውን ‹‹መልካምሥራ›› ሲሉ ሰየሟት፡፡ እርሷም በየካቲት 1 1969 ነበር የተወለደችው።
መልካምሥራ አፈወርቅ፣ ልጅነቷ የታጀበው በታላላቅ ወንድምና እህቶቿ ነበር፡፡የዛኔ አፏን በወጉ ሳትፈታ ከሬዲዮ ልዩ ፍቅር ያዛት፡፡ ይህ እውነታ ታዲያ በምትሰማቸው ቁምነገሮች ተጠምዳ እንድትውል ያስገድዳት ነበር፡፡በዕድሜዋ ከፍ ማለት ስትጀምር ደግሞ ጋዜጠኛው አባቷ አፈወርቅ አሰግድ ከታላላቆቿ ጋር መፅሀፍትን አስይዘው ንባብን እንድትወዳደር ዕድል ሰጧት፡፡
እርሷ ታዲያ የዋዛ አልነበረችም፡፡ፈጣን አንደበቷ ቃላትን ሳይስት ውብ ቅላፄውን ያሳምረው ያዘ፡፡ በንባቡም ከሌሎቹ የላቀች ሆነች ፡፡ ይህን ያሰተዋሉት ጋዜጠኛው አባትም ፈለጋቸውን እንደምትከል የገባቸው ገና በጠዋቱ ነበር፡፡ የተገመተው አልቀረም፡፡መልካም ሥራ አጸደ ህጻናትን አልፋ መደበኛ ትምህርት ስትጀምር ከሥነጽሁፍ ያላት ቁርኝት የተለየ ሆነ፡፡
ሁሌም ከእጆቿ መጽሀፍት አይጠፉም፡፡ከልቦለድ፣ግጥምና ድርሰት ጋር የተለየ ፍቅር ያዛት፡፡ አለማንበብ ነውር እስኪመስላት ከፅሁፍ ጋር ውላ አደረች ፡፡ በትምህርት ቤቷ ከአማርኛ መምህራን ጋር ቅርበት የነበራት መልካምሥራ በእነሱ ዓይኖች ሞገስ ለማግኘት አልዘገየችም፡፡የተለየ ችሎታዋን ያስተዋሉ ሁሉ የምትፅፋቸውን ግጥምና ልቦለዶች ለጓደኞቿ እንድታነብ ዕድሉን ቸሯት፡፡
ትንሽዋ ልጅ የአጻጻፍ ጥበቧ፣የአነባበብ ስልቷ ብዙዎችን ማረከ፡፡ ስለእርሷ የሚያደንቁ፣ አስተያየት የሚሰጡ በረከቱ፡፡ በክፍል ውስጥ ጎልቶ የሚደመጥ ምንባብ ሲኖር በመምህራኖቿ ብቸኛዋ ተመራጭ እንደሆነች ዘለቀች፡፡
ብላቴናይቱ መልካም የመክሊቷን ስታገኝ ውስጧ በረታ፡፡ የነገ ህልሟን ለማሳካት ማንበብን ባህል አድርጋው ቀጠለች፡፡ አንድ ቀን በክፍል ውስጥ የአማርኛ መምህሩ ቲቸር ዘውድነህ ተማሪዎቻቸውን እያስነሱ ወሳኝ ያሉትን ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ የዛኔ እርሷ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡
ለተማሪዎቹ የቀረበው የመምህሩ ጥያቄ አንድ አይነት ነበር፡፡ ‹‹እናንተ ስታድጉ ምን መሆን ትፈልጋለችሁ?›› የሚል ፡፡ እያንዳንዱ ተማሪ የራሱን ምኞት መግለጽ፣መተንተን ጀመረ፡፡አብዛኞች ዶክተር መሆንን ተመኙ፡፡ገሚሶቹ ደግሞ እጃቸውን እያወጡ አስተማሪ፣ፓይለት፣ወታደር ሳይንቲስት ሲሉ ተናገሩ፡፡ ተራው የመልካምሥራ ሆነ፡፡ ‹‹እኔ ጋዜጠኛ መሆን እፈልጋለሁ›› ስትል መለሰች ፡፡ክፍሉ በጭብጨባ ጋየ፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በልጅነት ጨዋታዎች ተዋዝቶ ፣በቁምነገር ተዳብሶ ተጠናቀቀ ። የስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪን አልፋ ወደ ሰባተኛ ክፍል ስትገባ ራሷን ያገኘችው በዑራኤል መለስተኛ ትምህርት ቤት ወስጥ ሆነ፡፡ይህ ጊዜ ለመልካምሥራ ፍላጎት እጅጉን የሚያመች ነበር፡፡በትምህርትቤቱ የሥነጽሁፍ ፣ የድራማና የክርክር መድረኮች በስፋት ይካሄዳሉ፡፡፡ይህ እውነት ጥበብን አጥብቃ ለምትሻው ታዳጊ ‹‹በበሶ ላይ ቅቤ›› ይሉት ዓይነት ተመቻችቶ ቀረበላት፡፡ ከሥነጽሁፉ፣ ከክርክር መድረኩ እንዳሻት ናኘችበት፡፡
የሙያ እርሾ …
የዳበረ ልምዷን ይዛ ወደ ቦሌ አጠቃላይ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ያመራችው መልካም አሁንም ለፍላጎቷ የሚበጀውን አላጣችም፡፡ ገና ዘጠነኛ ክፍልን ስትቀላቀል የሚኒ ሚዲያ አባል የመሆን ዕድል ገጠማት፡፡ ጣዕም ያለው ድምጿ ከአድናቂዎቿ ሲያስተዋውቃት አልዘገየም፡፡ በ1981 ቦሌ ሀይስኩል ስትገባ፣ የምታቅርባቸው ግሩም ፅሁፎች ጆሮ ገብ ነበሩ፡፡ይህ አጋጣሚ በስነጽሁፍ ትምህርትቤቷን ወክላ ከሌሎች አቻ የአዲስአበባ ትምህርትቤቶች ጋር እንድትወዳደር ዕጩ አደረጋት፡፡
መልካምሥራ ለውድድር የሚያበቃትን ግጥም በወጉ ፅፋ በትምህርትቤቷ ብቸኛዋ ሴት ተወዳዳሪ ሆና ቀረበች ፡፡ በወቅቱ በቋንቋዎችና ሥነጽሁፍ ምሩቅ የነበሩት እናቷ ወይዘሮ መነን ገድሉ ሞራሏን በመገንባት ከጎኗ ነበሩ፡፡ፅናትና ድፍረትን ይዛ በመድረክ የቀረበችው ተማሪ በትምህርትቤቶች መሀል በሚካሄደው ውድድር ግጥሟ ለአሸናፊነት በቃ ፡፡ታላቅ አድናቆትና ሽልማትን ይዛ ተመለሰች፡፡ይህ የአሸናፊነት ክብር አስራሁለተኛ ክፍልን አጠናቃ እስክትወጣ አብሯት ዘለቀ፡፡
በጊዜው የአስራሁለተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን አጠናቃ ውጤትን የምትጠብቅበት ነበር፡፡ የማትሪክ ውጤቷ ከእጇ ሲደርስ ተስፋ የሚያስቆርጥ አልነበረም፡፡ በእሷም ባይሆን በእናቷ ምክርና ግፊት የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋምን እንድትቀላቀል ሆነ፡፡
መልካምሥራ ከልጅነቷ ጀምሮ አብሯት የዘለቀው የጋዜጠኝነት ፍቅር ነው፡፡አሁንም ድረስ በልጅነቷ የተመኘችውና የደመቀው የጓደኞቿ ጭብጨባ ከጆሮዋ አልጠፋም፡ በቃ! እቅድ ምኞቷ ጋዜጠኝነት ብቻ ነው፡፡ እናቷ የትምህርት ባለሙያ በመሆናቸው በእርሳቸው መንገድ ብታልፍ አይጠሉም፡፡እርሷ ግን ውስጠቷ ከአባቷ ሙያ ሌላ አስቦ አያውቅም፡፡ እውነቱን ለመናገር ወደ ደብረብርሀን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም የገባችው ከታላቅ ለቅሶና ተስፋ መቁረጥ ጋር ነበር፡፡
የደብረብርህንን ብርድ በፍቅር ብርድልብስ …
ደብረብርሀን ትምህርቷን ለመከታተል ዘለቀች፡፡በወቅቱ በምክንያት አሳባ ትምህርቷን ለማቋረጥ አስባ ነበር፡፡ ግቢውን እግሯ ሲረግጥ ግን የተለየ ፍቅር ያዛት፡፡ ብርዱን፣ውርጩን፣ፍላጎት ማጣቱን ረሳች፡፡ ለአንድ አመት ያህል የቆየው ትምህርት አይረሴ ትዝታዎችን፣ከበርካታ የኪነጥበብ ሙያዎች ጋር አተረፈላት፡፡
በደብርብርሀን ማሰልጠኛ ዛሬ ድረሰ የማትረሳቸውን ተወዳጅ ባልንጀሮችን ተዋወቀች፡፡ ቆይታዋን አልጠላችውም፡፡አሁንም በሥነጽሁፍ፣በድራማና በሚኒ ሚዲያው እውቅና ተቸራት፡፡ ጣፋጩ፣ የትምህርት ግዜ ሲጠናቀቅ የተመደበችበት ቦታ በዕጣ ተለይቶ ተነገራት፡፡ ምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ባሶሊበን ወረዳ፣ ቤተንጉስ ትምህርትቤት፡፡
ይህ እውነት ከተማ ተወልዳ ላደገችው የአዲስአበባ ልጅ እጅግ ከባድና አስደንጋጭ ነበር፡፡በርካታ ኪሎሜትሮችን አቋርጦ እልም ካለው ገጠር መግባት ከፈተናም በላይ ፈተና ይሆናል፡፡ሁኔታው ቢያስፈራትም እናቷ መነን አንደልጅነቷ እጇን ይዘው ስፍራው አድረሰዋት ተመለሱ፡፡የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ሰዎች ስለተመደበችበት አካባቢ አንድ በአንድ አስረዷት ፡፡
ሰፍራው ለመድረስ በእግር ሰድስት ሰአታት ያሰኬዳል፡፡ቦታው የአባይ በረሀ አጎራባች በመሆኑ እባብና ዘንዶ አያጣውም፡፡ ዙሪያገባው ተራራውን ተተግነው በመሸጉ ሽፍቶች የተሞላ ነው፡መልካምሥራ አይቀሬውን እውነት ልትጋፈጠው ግድ ሆነ፡፡
ተጓዝ ያለው እግር
የሰአታት መንገዱን በእግርና በበቅሎ ተጉዛ ከተመደበችበት ባሶሊበን ቀበሌ ደረሰች፡፡አዲስ ህይወት ሌላ በሆነ ዓለም ተቀበላት፡፡በግራ መጋባት መሽቶ የማይነጉ ቀናትን አንድ ሁለት ብላ ቆጠረች፡ ፡ማልቀስ፣መጨነቅ ስራዋ ሆነ፡፡
በትምህርት ቤቱ ከእሷጋር የተማረች እፀገነት አምሳሉ የተባለች ጓደኛዋ ተመድባለች፡፡ በስፍራው ከሁለቱ ሴቶች በቀር ማንም የለም፡፡ ዓመቱ በስቃይ ተጋመሰ፡፡ በፍላጎት ደብተር ይዞ የሚመጣ ዕውቀት ፈላጊ ተማሪ የለም፡፡ ተማሪዎችን ቀስቅሶ አሳምኖ ማምጣት ደግሞ ከሁለቱ መምህራን የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
‹‹ቤተ-ንጉስ›› እንደስሙ ውብ አይደለም፡፡ ብዙ ችግሮች የበረከቱ ችግሮች አሉበት፡፡ መልካምሥራ ሆድ ይብሳት፣ይከፋት ያዘ፡፡ ቀና ቢሉ ሰማይ ፣ዝቅ ቢባል ምድር ብቻ፡፡ ለቅሶ ትካዜው፣ናፍቆቱ የአዲስአበባዋን ልጅ አከሳት፣ አጠቆራት፡፡ በሽፍቶቹ ስጋት ሰውነቷ አለቀ፡፡ ‹‹ሙጀሌ›› ይሏት ክፉ ነገር እግሮቿን ጨርሳ. በእጆቿ ጣቶች ተደብቃ አቆሳሰለቻት፡፡ደምና መግል በሰውነቷ ተመላለሰ፡፡
ልጅነቷን ያዩ የአካባቢው ሰዎች ስለእሷ መኖር አብረዋት አዘኑ፣አነቡ ፡፡ በዚህ ቦታ የከተማ ሰው ብርቅ ነው፡፡አዲስአበባ እንደ ሰማይ ይርቃል፣ይናፍቃል፡፡ ከወራት አንዴ ብቅ የሚለው ሱፐርቫይዘር ጋሽ አዳም ታደሰ ብቻ ነው፡፡ እሷንና ባልንጀራዋን ‹‹አይዟችሁ›› ብሏቸው ይመለሳል፡፡በየቀኑ ከአንድ ሰው ጋር መፋጠጥ ከባድ ነው፡፡ ወሬ ሁሉ ያልቃል፣ጨዋታ ይጠፋል፡፡ ተመልሳ በብቸኝነት ትዋጣለች፡፡የአዲስአበባ ህይወት መብራት ድምቀቱ ውል ይላታል፡፡
መልካምሥራ አሁን የኩራዝ፣ጭሱን፣የወንዝ ውሀውን፣የሙጀሌ ቁስሉን በአጠቃላይ የገጠር ኑሮውን ለምዳለች፡፡ ጥቂት መረጋጋት ስትጀምር ታዲያ ዝም አላለችም፡፡ብዕር ከወረቀት አዛምዳ ደብረማርቆስ ለሚገኘው ‹‹የራባ›› ሬዲዮ ጣቢያ እነሆ!ማለት ጀመረች፡፡የምትጽፋቸው፣ተረኮችና ፣ድራማዎች ተወዳጅ ሆነው ተደማጭነትን አተረፉ፡፡ ዓመቱ ደርሶ ትምርትቤት ሲዘጋ በሬዲዮ ጣቢያው ተገኝታ ድምፅዋን ለታዳሚያን አሰማች፡፡አሁንም የበዛ አድናቆት ተከተላት፡፡
መክሊትን ፍለጋ …
ጥቂት ጊዜያትን በሌላ ትምህርትቤት የገፋችው መልካምሥራ መምህርነትን ከአንድ ዓመት በላይ አልዘለቀችበትም፡፡ የመክሊቷን ብርሀን ፈልጋ አገኘችው፡፡ በአማራ መገናኛ ብዙሀን ተወዳድራ ተቀጠረች፡፡ይህን ተከትሎ በአዲስአበባ ዩንቨርስቲ የመገናኛ ብዙሀን ገብታ በህትመት ጋዜጠኝነት ተመረቀች፡፡ተመልሳ በደብረማርቆስ የምስራቅ ጎጃም ዞን ወኪል ሪፖርተር በመሆን አገለገለች፡፡
ከዚህ በኋላ ብዙ አልቆየችም፡፡ወደክልሉ ርዕሰ መዲና ባህርዳር ተዛውራ ጋዜጠኝነትን አጣጣመች፡፡ተወዳጅ መጣጥፎችና ድንቅ አርቲክሎችን በበኩር ጋዜጣና መጽሄት ላይ አሰነበበች፡፡
በሬዲዮ ጣቢያው ላይ ዜናዎችን አስደመጠች፡፡ በተለያዩ ስፍራዎች ተዘዋውራ የጋዜጠኝነት ልኩን አሳየችው፡፡ደስ አላት፤ሙያዋን ይበልጥ ወደደችው፡፡ መልካምሥራ ቤተሰብ ለመጠየቅ አዲስአበባ በመጣችበት አጋጣሚ “ዕለታዊ አዲስ “የሚባል ጋዜጣ በ1993 ዓ.ም ስለመጀመሩ ሰማች፡፡ፊቷን ወደባህርዳር አልመለሰችም፡፡ ለጋዜጣው ተወዳደረችና በሙያዋ ቀጠለች፡፡
አሁንም መልካምሥራና ጋዜጠኝነት አልተለያዩም፡፡ከጋዜጣው መበተን ጥቂት ጊዜያት በኋላ በወቅቱ አጠራር በማስታወቂያ ሚኒስቴር የህትመትና ክትትል ባለሙያ ሆና ተቀጠረች፡፡ይህ አጋጣሚ ከምትወደው ስራ ጥቂት ፈቀቅ ቢልም ከሙያዋ አልራቀችም፡፡የአየር ሰአት ካላቸው ባለሙያዎች ጋር የሬዲዮ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ያዘች፡፡
ይህ ልምዷ ወደቀጣዩ ምዕራፍ ሊያሻግራት አልዘገየም፡፡በፖሊስና ሕብረተሰብ ሬዲዮ የፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን ክፍሉን ተቀላቀለች፡፡ይህ ወቅት ፣ለመልካምሥራ በርካታ ፍሬዎችን ያስገኘላት ድንቅ ጊዜ ነበር፡፡ክፍሉ አንጋፋና ታዋቂ ሰዎችን ያፈራ፣ ዕውቅ የሙዚቃና ቲያትር ባለሙያዎች ደምቀው የሚጠሩበት ነው፡፡በፖሊስ ሬዲዮ፣ቴሌቭዥንና ጋዜጣ ላይ የሚወጡት ሥራዎችም የተለየ አድናቆት አላቸው።
መልካምሥራ በተቋሙ ሲቪል ቅጥር ነች፡፡ አብዛኞቹ ለእርሷ፣እሷም ለመላው ሠራዊት በማይፋቅ ልዩ ፍቅርና አክብሮት እንደተሳስሩ ስትናገር ግን በተለየ ስሜት ነው፡፡መልካምሥራ በዚህ የሙያ ቤቷ ለተለየ ሥራ ታጭታ በሓላፊነት ግዴታዋን ተወጥታለች፡፡በወታደር ማሰልጠኛዎች፣በፈታኝ የበረሀ ቦታዎች፤ በአስቸጋሪ ውጣውረዶች መሀልም ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር እኩል ድርሻ ነበራት፡፡ ሁሉንም የተወጣችው በተለየ ጥንካሬ ነው፡፡
የምትወደውን የሙያ ቤቷን ፖሊስን ተሰናብታ ከወጣች በኋላ ለ2 ዓመታት በቅርስ ባለአደራ ማህበር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን አገልግላለች፡፡ ከደሟ የሰረፀው የጋዜጠኝነት ሙያ ግን ባለችበት አላከረማትም፡፡ዓይኖቿ ሙያዋን ማትረው ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አደረሷት፡፡
በርካታ ጋዜጠኞች ያሉበት ይህ ተቋም በሀገራችን ድንቅና ታዋቂ ሰዎችን ያፈራ አንጋፋ ነው፡፡ለእርሷ በዚህ ሰፊ የሙያ ባሕር ውስጥ መጥለቅ ታላቅ ዕድል ሆነላት፡፡ ዐምዶችን ይዛ መጻፏን ቀጠለች፡፡ብዙዎች በሚወዱላት የፊቸር አፃፃፍ በርካቶች በስልክ በደብዳቤ፣በአካል ጭምር እየመጡ አደነቋት ‹‹በርቺልን›› አሏት፡፡የምትጽፋቸው የመዝናኛ አርቲክሎችም ቢሆኑ ከማስፈገግ አልፈው ቁምነገር ማስጨበጣቸው አልቀረም፡፡
መልካምሥራን በተለየ ያሳወቃት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር ስታዘጋጀው የቆየችው‹‹ተናጋሪው ዶሴ›› የተባለው ዓምድ ነው፡፡ዓምዱን ለንባብ ለማብቃት በርካታ ዶሴዎችን ማየት፣ ማገላበጥ ይጠይቃል፡፡እንዲህ ለማድረግ ደግሞ ሆደ ሰፊ መሆን፣ዕንባን አምቆ መያዝ፣ከራስ ስሜት ጋር መታገል ግድ ነው፡፡ስራው በባህረይው የወንጀል ድርጊቶችንና ውሳኔያቸውን የሚጠቁም ነው፡፡፡ይህን አጣርቶ ጽሁፍ ለማድረግ ህይወትን፣ከነሰንኮፏ፣ ከነአሰቃቂነቷ ማየትን የግድ ይላል፡፡ይህን ሀቅ ደግሞ ደርሶ ዕንባ የሚቀድማት መልካምሥራ በድል ተወጥታዋለች፡፡እየሰቀጠጣትም ቢሆን አስገራሚዎቹን የወንጀል እውነታዎች በብዕሯ ከትባለች፡፡
መልካምሥራ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› በሚለው ዓምዷ ከብዙዎች ጋር አንብታለች፣አዝናለች፡፡ የብዙ ወገኖች በርካታ አይታመኔ ችግር ችግሯ ሆኖም የአቅሟን ለማካፈል ተጥራለች፡፡‹‹በአንድ እጇ ማይክ በሌለው እጇ እንባ ማበስ›› የሚባልላት ጠንካራዋ፣ሆደ ቡቡዋ ጋዜጠኛ ዛሬም ድረሰ በዐምዶቿ ትኩረት የብዙሀንን ነፍሶች ከችግር ለመታደግ እንደ ሮጠች ትውላለች፡፡ዶክመንተሪ ፊልሞችም ላይ አበርክቶዋ የላቀ ነው፡፡ ራሷ ያዘጋጀቻቸው ሥራዎች ቁምነገር ያዘሉ ናቸው፡፡ መልካምሥራ በህትመት ጋዜጠኝነት ዲፕሎማ ከአዲሰአበባ ዩኒቨርስቲ(1990)፣ በቋንዎችና ሥነጽሁፍ ደግሞ ዲግሪዋን ደግሞ በባህርዳር ዩንቨርስቲ ተምራለች፡፡
መድረክ መሪዋ
የመልካምሥራ እጆች ማይክ ጨብጠው መድረክ ላይ ከወጣች እርጋታዋ ብዙዎችን እንደሚገዛ ይነገርላታል፡፡ድምጸ- መልካም ነችና በርካታ አድናቂዎች አሏት፣እንደ አልቃሻነቷ ሁሉ ልቀልድ ላስቅ ካለች ጥርስ አታስገጥምም፡፡መልካምሥራ በተለያዩ የሙያ ማህበራት ትሳተፋለች፡፡በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙን ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣በዜማ ብዕር ኢትዮጵያ ሴት ጸሀፍት ማህበርና በሌሎችም በአባልነት እያገለገለች ነው፡፡ሁሌም እገዛን በሚሹ ጉዳዮች ላይ በኮሚቴና በማህበራዊ ተሳትፎዋ
ትታወቃለች፡፡በብዙ ውጣውረዶች የታጀበው የመልካምሥራ አፈወርቅ የጋዜጠኝነት ህይወት በሻካራማ መንገዶች የታለፈ በጣፋጭ የሙያ ውጤት የታጀበ ነው፡፡