ሌተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ(የበጋዉ መብረቅ) ህይወታቸው ካለፈ ዛሬ መጋቢት 29 2010 አንድ አመት ሆናቸው

ሌተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ

ተወዳጅ የሚድያና የኮሚኒኬሽን ማእከል የሀገር ባለውለታዎች እንዲከበሩና ለሀገር የዋሉት ውለታ በይፋ እንዲነገር ሁል ጊዜም ይሰራል፡፡ የሀገር ባለውለታዎች በህይወት ሳሉም ሲሞቱም ታሪካቸው ለትውልድ እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡ የሀገር ባለውለታዎች የትውልድ ቀን ፤ የህልፈት ቀንን ብሎም ምክንያት በመፈለግ እንዲዘከሩ ያደርጋል፡፡

በዚህም መሰረት ዛሬ ስለ ሌተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ እነሆ ጽፈናል፡፡ የ ሌተናንት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ 95ኛ አመት የልደት በአል ጥር 20 2008 ፤ ሲከበር አንድ መጣጥፍ ለመጻፍ ብእር ከወረቀት አዋሃድኩ፡፡ ጦር ሀይሎች በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ነበር 95ኛ አመት የልደት በአላቸው የተከበረው፡፡

ልደታቸው የተከበረ እለት በስልክ ያነጋገርኩዋት የጄነራል ጃገማ ኬሎ የመጨረሻ ልጅ ምህረት ጃገማ የልደት በአሉ እርሳቸው ባሉበት ሞቅ ደመቅ ያለ እንደነበር አጫውታኛለች፤፤ የ ሌተናት ጄኔራል ጃገማ ልጆች እንደ እድሜያቸው ቅደም ተከተል ይህን ይመስላል ፡፡ አቶ ሰለሞን ጃገማ ፤ ጸዳለ ጃገማ ፤ የትምወርቅ ጃገማ ፤ ሸዋዪ ጃገማ ፤ ብሩክታዊት ጃገማ ፤ እና ምህረት ጃገማ ናቸው ፡፡

ሌ/ጀ/ጃገማ ኬሎ የተወለዱት በጥር 20 ቀን 1913 ዓ.ም ነው:: ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ልጅ ቢሆኑም ከሁሉም ጎበዝ ብርቱ ነበሩና አባታቸው የቤተሰቡ አለቃ አደረጓቸው::

አባታቸው ጃገማ ገና ሳይወለዱ ለወላጅ እናታቸው ‹‹ልጃችንን ስሙን ጃጋማ ብየዋለሁ›› በማለት ነበር ጃገማ ብለው የጠሯቸው:: “ጃገማ” የአባታቸው የፈረስ ስም ሲሆን በኦሮምኛ ሀይለኛ ማለት ነው:: ሌ/ጀ/ ጃገማ እስኪወለዱ ድረስ የፈረሳቸውን ስም የሚሰጡት ሁነኛ ልጅ አላገኙም ነበር::

የኢጣሊያ ጦር የአድዋ ላይ ሽንፈቱን ሊወጣ ጦሩን እጅግ አግዝፎ ከ40 ዓመት ዝግጅት በኋላ በ1928 በድጋሚ ሀገራችንን ወርሮ ህዝብ ሲፈጅ ሀገሩን ሊታደግ ሁሉም በየፊናው ሲራወጥ በ15 ዓመት ዕድሜ የአባታቸውን ጀብድ ሊደግሙ በዱር ዘምተው ጠላትን አርበድብደዋል። በዚህም “የበጋ መብረቅ” ተብለው ተሰይመዋል።

ሌ/ጀ/ ጀገማ ፤ ከኢጣሊያ ጋር 5 ዓመት ሲዋጉ አንድም ቀን ድል ሆነው አያውቁም:: ጥይት ሲያልቅባቸው ብቻ ቦታውን ለቅቀው ይሄዳሉ:: ጥይት መልሶ ለማግኘት እንዴት ያደርጉ እንደነበር እንዲህ ብለዋል፡፡ “<<ጥይት ሲያልቅብን ማታ ምሽግ ላይ እንተኩሳለን:: አስራ አምስት ተኩሰን ከሆነ ሃያ ተኩሻለሁ ይልና አምስቱን ይሸጣል:: ጥይቱን የሚሸጡት ባንዳዎች ናቸው::>>

ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጊዜ እንግሊዝ ኢጣሊያን ከአፍሪካ እንድታስወጣ ተወሰነ:: ስለዚህ ወቅት ጃገማ ኬሎ እንዲህ ብለዋል…<<ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያንም ይመለከታልና ከንጉሡ ጋር ሆነው የእንግሊዛውያን ወታደሮች ሲመጡ የከዳውም ባንዳ እየተመለሠ ጣሊያን ተባረረ
ከዚያ በኋላ ንጉሡ ተመልሠው ዙፋናቸው ላይ ቢቀመጡም ጎንደርና ጅማ አልተለቀቁም ነበርና የጎንደሩ ይቀመጥ መጀመሪያ የቅርቡን እናስለቅቅ ተብሎ ወደ ጅማ ሲሄዱ ጀኔራል ጋዜራል የግቤን ድልድይ ቆርጦ መከላከል ጀመረ::

በዚህ ጊዜ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ያውቁኝ ነበርና ለጃንሆይ “ጃገማን ቢያዙልኝ በአምቦ መንገድ ሄዶ በኃላ ይቆርጥልኛል” በማለታቸው ጃንሆይ ከደጃች ገረሱ ጋር እንድትዘምት ብለው ደብዳቤ ላኩልኝ:: እኔ በወቅቱ 3500 ወታደኖች ነበሩኝ፡ ፡ መሣሪያውን ግማሹን ማርኬ ግማሹን ገዝቼ ያከማቸሁት ነውና መሳሪያ የመንግስት ነው ስለተባለ ሲፈልጉ መሣሪያውን ይውሰዱ ብዬ እምቢ አልኩ::

ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ የተባሉ የውስጥ አርበኛ ያውቁኝ ነበርና ለጃንሆይ “ህፃን የሚያምር ልጅ ነው እንዴት ከሞት ወደ ሞት ይልኩታል፡፡ ያሰናብቱት ጦሩን ቢያዩለትም መልካም ነው” ብለው ተናገሩ:: ጃንሆይም “እውነት ነው ተሣሥተናል እናያለን” አሉ:: “ጦርህን መጥተን እናያለን ተዘጋጅተህ ጠብቅ ፉከራም ታሰማለህ” ብለው መልዕክት ላኩብኝ፡፡ መጡ:: እኔም ታወር ሰርቼ ጠበኳቸው:: ፎክር ተብያለሁና ፉከራ ባልችልም ‹‹አባቱ ኦሮሞ እናቱ ኦሮሞ ግዳዩን አስቆጠረ ከምሮ ከምሮ›› ብዮ ፎከርኩ፡፡

ከዚያ በኃላ ምሣ አብረን በልተን ከእርሳቸው ጋር አዲስ አበባ ቤታቸው መጣሁ:: 25.000 ብር እና የወርቅ ሠዐት፤ ሙሉ ገበርዲን ሱፍ ሰጡኝ:: ከዚያ ደጃች ገረሱ ጋር ዘምቼ አጋሮ ወርጄ ድልድዩን ዘጋሁት:: መኮንኖቹ ተማረኩ:: ጋዚራም እጁን ሰጠ:: ጠቅላላ 600 እስረኛ ተቀብዬ ጦርነቱ አበቃ::

ሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ከነበሩት ሌ/ጀኔራሎች መካከል በህይወት የሚገኙት ብቸኛው ጀኔራል ሲሆኑ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆች፣ አምስት የልጅ ልጆችና አራት የልጅ ልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የታላቁ አርበኛ የሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎ የቀብር ስነ ስርዓት የዛሬ አመት እሁድ ሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም አርበኞችና ታዋቂ ሰዎች በሚቀበሩበት በቅድስተ ስላሴ ካቴድራል በክብር ተፈጽሟል፡፡

አባት አርበኞች፡ ቤተሰቦቻቸውና በርካታ ህዝብ የተገኘበት የቀብር ስነ ስርዓት ወጣት ኢትዮጵያዊያንና አባት አርነኞች በቀረርቶና ሽለላ በማጀብ ታላቁን አርበኛ ሽኝት አድርገውላቸዋል፡፡ ወደ 5 የሚጠጉ የቪድዮ ሊንኮችን እነሆ አቅርቤአለሁ፡፡

https://youtu.be/ADASwZN9pvg
https://youtu.be/5JtoJ_FiwWQ
https://youtu.be/J0z6W2KJhIg
https://youtu.be/JdlUCf2EqjI
https://youtu.be/rUFMKCRrMxI

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *