ጌጡ ተመስገን

ጌጡ ተመስገን

ባለ ንሥር ዓይኑ ጋዜጠኛ”


ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሐምሌ 30 2014 ዓ.ም አሳትሞ ባስመረቀው “መዝገበ- አእምሮ ” ቅፅ 1 የሚድያ ሰዎች ግለ-ታሪክ ውስጥ ታሪካቸው ከተሰነደላቸው የመገናኛ ብዙኀን ሰዎች አንዱ ጌጡ ተመስገን ነው፡፡ ጌጡ በተለይ በማኀበራዊ ሚድያ ባለፉት 10 ዓመታት ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን የቻለ እና ይህንን የማኀበራዊ ሚድያ ለበጎ ማዋል የቻለ ነው፡፡1.6 ሚልዮን ተከታዮችም አሉት። ግለ-ታሪኩ እንደሚከተለው ተጠናክሯል፡፡ ዕዝራ እጅጉ እነሆ ሰንዶታል።


“የሰው ልጅ ኖርኩ ማለት የሚችለው፣ በሥራው መታወስ እስከቻለ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው!” የሚለው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን፣ ነሐሴ 24 ቀን 1968 ዓ.ም. ነበር በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ አዲሱ ቄራ፤ አልማዝዬ ሜዳ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የተወለደው፡፡ ከአንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል በአፄ ዘርአያቆብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከ9ኛ እሰከ 12ኛ ክፍል በሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረው ጌጡ ተመስገን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ፋካልቲ (School of Journalism and Communication Faculty) የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል።

በለጋ ዕድሜው የጋዜጠኝነት ጉዞውን በፋና ዴሞክራሲ አሳታሚ ድርጅት ሀ ብሎ ጀመረ፡፡ በእፎይታ መጽሔት እና ጋዜጣ ላይ የማኅበራዊ፣ የጤና እና ኪነ ጥበብ አምድ አዘጋጅ ሆኖ ያገለገለው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን፣ በተለይ ከህትመት ሚዲያው አንባብያን ጋር ትውውቅ የፈጠረውም ለቁም ነገር መጽሔት እና ለሪፖርተር ጋዜጣ ያበረክታቸው በነበሩት የተለያዩ ጽሑፎቹ ነበር፡፡ ሰኔ 1 ቀን 1997ዓ.ም. ጌጡ ተመስገን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሪፖርተርነት ደረጃ ተቀጠረ። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በነበረው የ12 ዓመታት ቆይታ በዜና߹ በአፍሪቃ ጆርናል እና በ120 ዝግጅት ክፍሎች ሠርቷል። በተለይ በመዝናኛ ፕሮግራም ያዘጋጃቸው በርካታ አስተማሪና አዝናኝ ዶክመንተሪ ፊልሞች በተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትንና አድናቆትን አትርፈውለታል፡፡

በሙያው በርካታ ሽልማቶችን ለማግኘት የበቃው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ‹‹የአረንጓዴ ሽልማት ፕሮግራም 2002›› በቴሌቪዥን ዘገባ ምድብ አንደኛ ደረጃ አሸናፊ በመሆን፣ የላቀ ዘጋቢ የክብር ዋንጫ ከቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትና የአረንጓዴ ሽልማት ፕሮግራም የበላይ ጠባቂ ከነበሩት፣ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ በክብር ተሸልሟል፡፡ ጋዜጠኛው በኢቴቪ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ በርካታ አስተማሪና አዝናኝ ዶክመንተሪ ፊልሞችን ያቀረበ ሲሆን ሥራዎቹም በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትንና አድናቆትን አትርፈውለታል፡፡
የ2002 የአረንጓዴ ሽልማትን ያሸነፈው ‹‹ኾንሶ ኻኖ›› (የኛ ኮንሶ) እና ‹‹ሐርላ ፡- ጥንታዊ የንግድ ከተማ›› በተሰኙ ዶክመንተሪ ፊልሞቹ ነው፡፡ ፊልሞቹ፣ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ እንዲሁም በባህልና ቱሪዝም ላይ የሚያተኩሩ ሥራዎቹ ናቸው፡፡

የጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን የአረንጓዴ ሽልማት አሸናፊነትን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ሔራልድ ጋዜጣ፣ የጥበብና ባህል አዘጋጅ የነበሩትና አሁን በሕይወት የሌሉት ጋዜጠኛ መለሰ ጥላሁን፣ በሽልማቱና በሙያ ተመክሮው ዙሪያ ቃለ መጠይቅ አድርገውለት ነበር፡፡ የሔራልዱ ጋዜጠኛ ‹‹የኢቴቪ ዘጋቢ የአረንጓዴ ሽልማት የላቀ ተሸላሚ ሆነ›› በሚል ርዕስ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በንባብ በቀረበው አጭር ታሪክ ውስጥ ‹‹ጌጡ ተመስገን የጋዜጠኝነት ሙያውን ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም ዘብ የቆመ፤ ብዕር የጨበጠ ወታደር ነው›› ብሎ ያወድሰዋል። ´የኮንሶ ባህላዊ መልከዓ ምድር በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለኮንሶም- ለኢትዮጵያም ትልቅ ውለታ የሠሩልን፤ አራቱ ‹‹ዝምተኛ ጀግኖች››፦ ዶ/ር ዮናስ በየነ (አርኪዮሎጂስት)፣ ዶ/ር መታሰቢያ በቀለ (አንትሮፖሎጂስት)፣ ዶ/ር ብርሃኔ አስፋው (ፓሊዮ አንትሮፖሎጂስት) እና ጌጡ ተመስገን ( ጋዜጠኛ) በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በካራት፣ ኮንሶ ከተማ ተሸላሚ ነበሩ።

‹‹ኾንሶ ኻኖ›› (የኛ ኮንሶ) የተሰኘው ዘገባው፣ የኮንሶ መልክዓ ምድርን ለመታደግ ባህላዊ አምባ መንደሮች የጥበቃ ከለላ ድንበር (Buffer Zone) እንዲበጅላቸው ለአገር እና ለህዝብ ጥያቄ ያቀረበበት ሲሆን፣ ዝግጅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከቀረበ ከአራት ወራት በኋላ የጥበቃ ከለላ ድንበር ተበጅቶላቸዋል። ይህም ብቻ አይደለም፤ የኮንሶ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ዘጠነኛ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህን ተከትሎም ጋዜጠኛው ላበረከተው አስተዋጽኦ ዩኔስኮ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የኮንሶ ልዩ ወረዳ በጋራ ከሦስቱ ‹‹ዝምተኛ ጀግኖች›› ጋር በክብር ሸልመውታል።
‹‹ሐርላ ፡- ጥንታዊ የንግድ ከተማ›› የተሰኘው ሌላው ዶክመንተሪውም ከድሬዳዋ ወደ ሐረር በሚወስደው መንገድ በአሥራ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስለምትገኘው ጥንታዊቷ የንግድ ከተማ፣ ስለ ሐርላ የሚተርክ ነው፡፡ ሐርላ ከ13ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ሮም፣ ቻይና እና ፐርሺያ (የአሁኗ ኢራን) እየተሻገሩ፣ እጣንና ከርቤ ስለሚነግዱ ነጋዴዎች የሚያወሳ ነው፡፡ በዶክመንታሪው ላይ አቶ አሊ ሙሳ ማያ እና ሸኽ ኡመር አብደላ ቡሮቾ የተባሉ ሁለት የአካባቢው ሽማግሌዎች፣ በቢዮ ሐርላ ቀበሌ ሙዚየም እንዲገነባ አገራዊ ጥሪ አቅርበው ነበር።

ፕሮግራሙን የተመለከቱ በአሜሪካ የሚኖሩ፣ የሥነ-ሰብ ምሁሯና ኪዩሬተር ወ/ሮ መስከረም አሰግድ (አንትሮፖሎጂስት እና ጸሐፊ ናት) እና አርቲስት ኤልያስ ስሜ የስሚዝሶኒያን የአፍሪቃ ኪነ-ጥበብ (African Art Award) ሽልማት ተሸላሚ ሙዚየም በመገንባት በተለያዩ ገበሬዎች እጅ ላይ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው አድርገዋል፡፡ ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቆይታው የሠራቸውን (ለተመልካቾቹ እነሆ ያላቸውን ዶክመንታሪዎች) ቆጥሮ ለመጨረስ አዳጋች ነው፡፡
በወፍ በረር አንዳንዶቹን እናንሳ ከተባለ ግን፣ ከ‹‹ሰው በምድር›› ቀድሞ ከፊት የሚሰለፍ አይኖርም፡፡ ‹‹ሰው በምድር›› ሞትን እየሸሹ ስለሚኖሩት አባባ ገብረየስ ሸዋንግዛው፣ የአስከሬን ሣጥን ቤታቸው ያስቀመጡ ወ/ሮ አበበች ካሳ (እማማ ሶርፌላ) እና ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሐት ለአብ ገብረእግዚአብሔር የሚተርክ ተወዳጅና በብዙዎች ልብ ውስጥ ታትሞ የቀረ ዘጋቢ ፊልሙ ነበር፡፡


‹‹በሁላችንም ኪስ ውስጥ የሚገኘው ሰው›› የሚለውና በኢትዮጵያ የአንድ ብር እና የአምስት ብር ኖቶች ላይ የሚታዩትን ግለሰቦች ማንነት ያስተዋወቀበት ዘጋቢ ፊልሙ፤ እንዲሁም ያገሬ ገበሬ ፩ (በሞረት እና ጅሩ)፣ ያገሬ ገበሬ ፪ (በምንጃር ሸንኮራ)፣ ጎንደር በመካከለኛው ዘመን፣ የምድራችን ጀግና – ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር (በ2006 ዓ.ም በሲንጋፓር፣ ማሌዥያ “Champion of the Earth” ሽልማት ላይ የሚያጠነጥን፣ ዱባይ “የበርሃ ገነት”፣ ጥበብና ፍቅር በየመን፣ የቆሎ ተማሪ ከደብረገነት ኤልያስ እስከ ዲማ ጊዮርጊስ፣ የአደን ስፖርት በኢትዮጵያ (ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሪፊት ቫሊ ሳፋሪሰ ሙሩሌ ካምፕ)፣ የአርሆ መንገድ (ከምሥራቅ ትግራይ እንደርታ እስከ አፋር ረገድ በጨው ነጋዴዎች ሕይወት ላይ የሚያተኩር)፣
“ኢትዮጵያውያን አርመኖች በጥምቀት ክብረ በዓል፣ ጉዞ ወደ ፍቅር እስከ መቃብር (የደራሲ ሀዲስ አለማየሁ መጽሐፍ ላይ ተንተርሶ)፣ ሃዲያ “የማር ተራራ “፣ የቁመት ነገር ፩ – የፍቅር ነገር ፪ (በቁመታቸው የአጭር አጭር የሆነው ረዥም መለሎ ማግባቱን የሚያሳይ እና የሕይወት ስንክሳር – ልብ አንጠልጣይ ነበር)፣ ከሃያ ዓመታት በኋላ (በ9/9/99 – 9 ሰዓት የተቀጣጠሩ የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች)፣ የሰላም አባት – ፓሊዮአንትሮፖሎጂስት ዶ/ር ዘረሰናይ ዓለምሰገድ፣ ከባሌ ተራራ ሥር፣ የንባብ መንደር (አንብብና ኑር፤ አንብብና ሙት – ለ 40 ዓመታት አሮጌ መጽሐፍት የነገዱ የአቶ መስፍን አርጋው ታሪክ ነው)፣ ዘጌ – የባሕር ላይ ንግድ (ከዘጌ እንጨት በደንገል ጭነው የጣናን ሐይቅ 12 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ባሕር ዳር የሚነግዱ (ኑሮን ለማሸነፍ የሚታትሩ) ገበሬዎች (ይህ ዝግጅት ከሊሊቱ 9:00 ሰዓት በጠፍ ጨረቃ የተቀረጸ ነው፡፡) … ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ልደት (መስከረም 17 ቀን 2000 ዓ.ም. በመኖሪያ ቤቱ ብርቱ ወግ)፣ ‹‹ቡርባክስ – የዓለም አጫዋች መንደር›› (የመሰንቆ ተጫዋቾችን አስደማሚ ሕይወት ይዳስሳል)፣ የዓባይ ልጆች (የስደስቱ ልጆች የሥም አወጣጥ ከዓባይ ወንዝ ጋር የተያያዘ ነው። ተፈራ ዓባይ፣ ስንታየሁ ዓባይ፣ ተናኘ ዓባይ ፣ የግብጽ ሕይወት ዓባይ፣ ይገደብ ዓባይ እና ይታያል ዓባይ ናቸው። በነገራችን ላይ፣ ይገደብ ዓባይ መጋቢት 23 ቀን 1984 ዓ.ም. የተወለደ ሲሆን የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለው ደግሞ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ፓሪስ (የፍቅር ከተማ)፣ አናጂና – (ድሬ ሸኽ ሁሴን)፣ ጎዳና ላይ የወደቁ ከዋክብት፣ የድሆች አባት – ካርል ሄንዝ በም፣ ፍቅር እስከ መቃብር (እናት እና ልጅ – ሲልቪያ ፓንክረስት እና ሪቻርድ ፓንክረስት )፣ የፀሐይ መውጫ ልጆች፣ የአርሲ ሳዱላ (ለ50 ዓመታት በፖስት ካርድ ባህል እና ቱሪዝምን ያስተዋወቁ አዮ ጉደቱ ካዎ) ወዘተ ሥራዎቹን ሳይጠቅሱ መዝለል አይገባም።

የሚሠሩ እጆች – ማድነቅ መሠልጠን ነው።


በአንድ ወቅት የፈረንሳይ ቴሌቪዥን ባለሙያዎች፣ ተመልካቾች (አድማጮች) ላይ ተንተርሰው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ቅኝት ካደረጉ በኋላ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ባቀረቡት ዘገባ፣ “ጌጡ ተመስገን፤ የራሱን አዲስ የአቀራረብ ስልት ያስተዋወቀ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ነው፡፡ የሚያቀርባቸው ዝግጅቶች በሚዲያ ያልተዳሰሱ፣ ያልቸኩ፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ስለሆኑ በተመልካቾች ዘንድ ይወደዳሉ፤ ይናፈቃሉ። ዝግጅቶቹ ምንጊዜም አይረሴ ናቸው።” በማለት የተመልካቾችን እማኝነት ዋቢ አድርገው “ባለ ንሥር ዓይኑ ጋዜጠኛ” ~ A Journalist with an eagle eye›› በማለት መስክረውለታል፡፡


በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሠራቸው ውስጥ ሦስቱ ሥራዎቹ በፈረንሣይኛ ቋንቋ በቅንጭብ ተተርጉመው ቀርበውለታል። እነርሱም፣ የቁመት ነገር ፩ – የፍቅር ነገር ፪ (በቁመታቸው የአጭር አጭር የሆነው ረዥም መለሎ ማግባቱን የሚያሳይ እና የሕይወት ስንክሳር)፣ የአንድ ኢትዮጵያዊ ገበሬ የአንድ ቀን ውሎ የሚተርከው – ያገሬ ገበሬ ፩ (በሞረት እና ጅሩ)፣ ያገሬ ገበሬ ፪ (በምንጃር ሸንኮራ) እና የንባብ መንደር (አንብብና ኑር፤ አንብብና ሙት – ለ 40 ዓመታት አሮጌ መጽሐፍት የነገዱ የአቶ መስፍን አርጋው ታሪክ ነው) የተሰኙ ሥራዎቹ ናችው።


በነገራችን ላይ …


“እናንት ያገሬ ልጆች – እናንት የኢትዮጵያ ልጆች” የሚል አገላለጽን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሠራቸው በርካታ ዝግጅቶች በመግቢያና መውጫነት በመጠቀም የሚታወቀው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን፣ በዚህም በተመልካቾች ዘንድ አዎንታዊ ተቀባይነት አግኝቷል። አሁን አሁንም በተለያዩ መድረኮች “እናንት ያገሬ ልጆች – እናንት የኢትዮጵያ ልጆች” የሚሉ ድምጾች ተደጋግመው መደመጥ መጀመራቸው፣ የጋዜጠኛውን በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያመላክት ነው።

Journalism is more than reporting.


የኢትዮጵያ ተረት ነው፡፡ ‹‹ሰማይ ተቀደደ ቢሉት የአገር ሽማግሌዎች ይሰፉታል!›› አለ ይባላል፡፡ ጌጡ ተመስገን አገር በቀል ዕውቀት (Indigenous knowledge) ላይ ተንተርሶ ባህላዊ ዳኝነት (የኢትዮጵያ ሽምግልና) ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ (case study) ዘገባዎች (ዶክመንተሪዎችን) ሠርቷል፡፡ አበጋር – የወሎ ባህላዊ ዳኝነት እና የማርካ ቅጠል (የኮንሶ የእርቅ ሰላም ቅጠል) መጥቀስ ይቻላል፡፡ የፀሐይ መውጫ ልጆች ደክመንተሪ በሐረር አካባቢ በተፈጠሩ ግጭት እና የግጭት አፈታት ዙሪያ ለሕዝቦች ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት (አብሮነት) – Peace Journalism – ዘውግን ይዞ ሠርቷል። በሐረር ጀጎል ግንብ ውስጥ የምትገኘው መገራዋ ዊጌር – የአስታራቂዋ መንገድ ትዕይንት ተመልካቾችን አስደምሞ ነበር። ይህቺ ናት አገሬ፤ ይህቺ ናት ኢትዮጵያ በማለት …
በረጅም ዓመታት የጋዜጠኝነት የሙያ ጉዞው ከአገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ የተለያዩ የአጭር እና የረዥም ጊዜያት ሥልጠናዎችን በመውሰድ ሙያዊ ክህሎቱንና ብቃቱን የበለጠ ለማሳደግ ጥረት በማድረግ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ጌጡ፣ በሥራዎቹ፤ በዘጋቢ ዶክመንተሪዎቹ ምክንያት አውሮፓ (ጀርመን፣ ጣልያን፣ ፈረንሣይና ቤልጂየም) የሥራ ጉብኝት እና ትምህርታዊ ሥልጠና ወስዶ ወደ እናት ሀገሩ፤ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡ ይሁንና ከእርሱ ጋር ባሕር ማዶ የሄዱ የሥራ ባልደረቦቹ አንዳንዶቹ አልተመለሱም። ወደ ሀገር ቤት መመለሱ ጥያቄ አስነስቶበታል። ‘’ለምን አልጠፋህም?!… በጣቢያው (ረዣዥም እጆች) እየተገፋህ ለምን አልኮበለልክም!?’’ ባዩ ብዙ ነበር፡፡ ለዚህ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሁሌም የሚሰጠው መልስ አንድ መስመር ነበር … “እኔ የሰው ሀገር እንግዳ እንጂ ነዋሪ አይደለሁም!” የሚል ነበር። ለእምዬ ኢትዮጵያ፤ ለሙያው – ለአገር እና ለሕዝቡ ታማኝ መሆኑን አስመስክሯል፤ ይህም ሕዝባዊ አመኔታ፤ ሕዝባዊ ከበሬታን አስገኝቶለታል።
በህትመትና በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ዘርፍ ከነበረው የረጅም ዘመን ቆይታ በኋላ አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ (New Era – Online Media) – አዲስ ዓለም – በማዞር የሚዲያ መንገድን ተያይዞታል፡፡ ሙያዊ ሥነምግባርን በጠበቀ መልኩ ሚዛናዊ፣ ትክክለኛ እና ፈጣን መረጃዎችን በማቅረብ በአገር አቀፍ ደረጃ በቀደምትነት ከሚጠቀሱ ማኀበራዊ ድረ ገጾች አንዱ የሆነውና በስሙ የተከፈተው Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን) የፌስቡክ ገጽ የአገር ቤት ድምፅ ሆኗል። በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ በርካታ ተከታዮችን ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ከአንድ ሚሊዮን (1,000,000) በላይ ቤተሰቦች (Followers) አሉት። በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍም በሠራቸው ሥራዎችም የተለያዩ ሽልማቶች እና ስጦታዎች ተበርክተውለታል። ከእነዚህም ውስጥ በጣና ሚዲያ አዋርድ እንዲሁም በኢትዮ ሶሻል ሚዲያ አዋርድ በፈጣን፣ ተአማኒ እና ወቅታዊ መረጃ ዘርፍ በተከታታይ ዓመታት አሸናፊ ሆኗል።


እግረ መንገድ …
እግረ መንገድ …


በካፒታልም ሆነ በሰው ኃይል ከፍ ያሉ የሚዲያ ተቋማት የአፋልጉኝ እና የአግዙኝ ተማጽኖ በነጻ አይሠሩም። የአገልግሎት ክፍያ ይጠይቃሉ። ጌጡ ተመስገን ሚዲያና ኮሙኒኬሽንስ በማኅበራዊ ሚዲያ ሰብአዊነት ይቅደም! … ሰብአዊነት ይለምልም! በሚል መርህ የአፋልጉኝ እና የእርዳታ ተማጽኖ በነጻ እየሠራ፤ ያለመታከት እየታተረ ይገኛል።

ጌጡ – መልካም ሥራ ሥራና ሰይጣን፤ ሸይጣን ይፈር! – ይላል።


ደህንነቱ የተጠበቀ ደም ለሁሉም (Safe Blood for all)- በሚል ዓለም አቀፍ መርህ፤ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የነፍስ አድን ስጦታ በማበርከት፤ ደም በመለገስ ይታወቃል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ በጎ ፈቃደኝነትን በማበረታታት፣ የሰብአዊ ድጋፍና እርዳታ ጥሪዎችን በማስተላለፍና በማስተባበር ከሚሠራላቸው ድርጅቶች መካከልም መቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ መርጃ ማዕከል፣ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር፣ የኒያ ፋውንዴሽን እና የጆይ ኦቲዝም ማእከል߹ ዘውዲቱ መሸሻ የሕጻናት የበጎ አድራጎት ልማት ማኅበር … ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡


• በደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ አርታኢነት ለንባብ በበቁት እፍታ ቅጽ አራት እና እፍታ ቅጽ አምስት መጽሐፍት ላይ እንዲሁም ደቦ በተሰኘውና በደራሲ እንዳለጌታ ከበደ አርታኢነት በታተመው 60 ደራሲያንና ጋዜጠኞች የተሰባሰቡበት መጽሐፍ ውስጥ የጌጡ ሥራዎች ለንባብ በቅተዋል። አሁን ደግሞ፣ የጋራውን መንገድ ተወት አድርጎ በግሉ የጉዞ ማስታወሻ እና ሌሎች ወጎች መጽሐፉን ለአንባቢዎቹ ጀባ ለማለት ተፍ ተፍ እያለ ነው።


• ስለሙያ ጉዞው በተጠየቀ ቁጥር “ሁሌም ተማሪ ጋዜጠኛ መሆኔን አምናለሁ‘’ ሲል የሚደመጠው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን፣ “ጋዜጠኝነት ሙያ በተግባር ፊደል ያስቆጠሩኝ ባለውለታዎቼ በሙያው ‹ቆንጥጦ የማሳደግ› ድርሻ ያላቸው እጅ የምነሳቸው የኔታዎቼ (Mentors) ማመስገን አልረሳም!”- ይልና ሥማቸውን መዘርዘር ይጀምራል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህሬ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በሙያው ካበረከተልኝ ‹‹ቆንጥጦ የማሳደግ›› ያህል ሚና በተጨማሪ፣ ጊዜውን መስዋዕት በማድረግ የመጽሐፉን ረቂቅ አንብቦ የማዳበሪያ አስተያየት ሰጥቶኛልና ምስጋና ይገባዋል፡፡ ከጥልቅ እውቀታቸው ሳይሰስቱ በማካፈል ልቦናዬን ያበሩልኝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሬ ዶ/ር አርካ አቦታ፣ ጋዜጠኛና መምህር ስለሺ ተሰማ እንዲሁም መምህር አቤል አዳሙ (መካሪዬ) በጋዜጠኝነት ሕይወቴ ላይ አስተዋፅኦቸው ቀላል አይደለምና አመሰግናቸዋለሁ፡፡

ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዜና ክፍል አዘጋጅ ታደሰ መለሰ፣ ‹‹አፍሪካ ጆርናል›› ተመድቤ በምሠራበት ጊዜ ደግሞ ዋና አዘጋጁ መኮንን ገ/ሊባኖስ ‹‹አገርና ሕዝብን ማክበርህን በሥራህ መተርጎም ይኖርብሃል›› የሚል ምክራቸው የትጋት ምንጭ ሆኖኛልና – ምስጋናዬ ይድረሳቸው – ይላል

ጌጡ እናቱን፤ ወይዘሮ አለምነሽ ፀጋውን ሳይጠቅስ አይዘልም


“እናቴ – አንድም ቀን ‹እድሜና ጤና ይስጥህ!› ከሚለው ምርቃት በላይ ማሳረጊያዋ ‹የጉንዳን ጉልበት ይስጥህ!›› የሚል ምርቃቷን ታከናንበኛለች። እኔ የጉንዳንን ያህል ታታሪ አልነበርኩም፡፡ የሚጠበቅብኝን ያህል ለሀገሬ ሠርቻለሁ ብዬም አላምንም፡፡ ዛሬም ድረስ ግን፣ የእናቴን ምክር እያስታወስኩ በትጋት መታተሬን ቀጥያለሁ” ይላል፡፡

መዝጊያ


ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ጌጡ ተመስገን ኢትዮጵያ ቲቪ በሠራባቸው 12 ዓመታት ከሌሎች የሚድያ ሰዎች በተለየ መልኩ የራሱን ቀለም ለመፍጠር የሞከረ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በእርግጥ ጌጡ ከኢቲቪም በፊት በልዩ ልዩ ሚድያዎች አሻራውን አኑሯል።
በተለይ በመዝናኛው ዘርፍ ላይ ሰው ያልሞከራቸውን ፕሮግራሞች አየር ላይ በማዋል ከበሬታን ማትረፍ ችሏል፡፡ ከ 10 ዓመት በፊት አየር ላይ ያዋላቸው ፕሮግራሞች ዛሬ ድረስ ከሰው አእምሮ ውስጥ መውጣት ያልቻሉት ታስቦባቸው የተከወኑ ስለሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የጌጡ ተመስገንን ጥረት ማድነቅ ያስፈልጋል፡፡ 12 ዓመት በመንግሥት ሚድያ ላይ ሠርቶ ድንቅ አቅም በመፍጠሩ ዛሬ ጌጡ በማኅበራዊ ሚድያ በራሱ መንገድ መጥቶ ተአማኒ መረጃዎችን በፍጥነት እያደረሰ ይገኛል፡፡ ዛሬ የጌጡ የፌስ ቡክ ገጽ በርካታ ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ተከታይ ያለው ሲሆን በየጊዜውም ቁጥሩ በማደግ ላይ ይገኛል፡፡ አጠቃላይ ጌጡ በሚድያው አለም ከ 20 ዓመት በላይ እንደመቆየቱ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም የራሱን አሻራ ለማኖር የቻለ ነው፡፡ የተወዳጅ ሚድያም አላማ የለፉ ታሪካቸው በስፋት ይነገር ነውና እነሆ ጌጡን አቅርበናል፡፡

2 thoughts on “ጌጡ ተመስገን

  1. Proud of you my husband ❤️
    You are the most amazing Ethiopian journalist ever
    This is so perfect
    I really loved it

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *