የአቶ በቀለ ሙለታ አጭር የህይወት ታሪክ

አቶ በቀለ ሙለታ፣ ከአባታቸው አቶ ሙለታ ቶላ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ወርቄ ዓለሙ    ሰኔ 16 1963 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተወለዱ።  የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወሰን ሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃን ደግሞ  በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

አቶ በቀለ በልጅነታቸው የስነ-ጽሁፍ ፍቅር ስለነበራቸው ይህን ፍላጎታቸውን ለማርካት ገና በወጣትነታቸው ራሳቸውን ከንባብ ጋር በማቆራኘት ተጠምደው ነበር፡፡ በተጨማሪም ብእር ከወረቀት በማዋሀድ መጣጥፎችን ለመጻፍ ሙከራ ያደርጉ ነበር፡፡ የዛን ጊዜው ወጣት በቀለ ሙለታ ገና በ21 አመቱ   በ1980 ተስፋ የኪነጥበብ  መድረክን በመመስረት መርካቶ በሚገኘው የቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት  የጥበብ ድረኮችን በማዘጋጀት ለጥበብ ያሳደረው ፍቅር እምን ድረስ እንደሆነ አሳይቷል፡፡

በሚድያው እና በስነጽሁፉ አለም ላለፉት 30 አመት የዘለቁት አቶ በቀለ ሙለታ ያኔ በልጅነታቸው  በተስፋ የኪነ-ጥበብ መድረክ ላይ ወጣቶች ወደ ስነ-ጽሁፍ አለም እንዲሳቡና  መጽሀፍ የማንበብ ልምድ  እንዲያዳብሩ ምክር ይለግሱ ነበር፡፡ አብረዋቸው በኪነጥበብ ማህበር የዘለቁት እንደሚያስታውሱት አቶ በቀለ በዚያን ወቅት እንደ ወጣት የኪነጥበብ መሪ ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው ይሰሩ ነበር፡፡

በጊዜው የተስፋ የኪነጥበብ ማህበር አባላት  በእጅ እየተጻፋች ለህትመት የምትበቃ ‹‹ብርሀን›› የተሰኘች ህትመት የነበረቻቸው ሲሆን አቶ በቀለ በአፍላነት ዘመናቸው   ጋዜጣዋን በኃላፊነት የማዘጋጀቱን አደራ በብቃት ይወጡ ነበር፡፡ 

ብርቱውና ዝምተኛው ብእረኛ አቶ በቀለ ሙለታ፣ በ1984 ፍካት የስነጽሁፍ ክበብን ከመሰረቱና በመሪነት ካገለገሉ ባለሙያዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ይህ ማህበር  የስነ-ጽሁፍ ምሽቶችን እያዘጋጀ  በመጽሀፍ ዙሪያ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ጉልህ ተግባር ማከናወኑ በብዙዎች አይዘነጋም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ ታዋቂ መምህራንንና ታዋቂ ደራሲዎችን በመጋበዝም የተሳካ የልምድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር፡፡   ይህ አይነቱ ወጣቶች ለስነ-ጽሁፍ እንዲነሳሱ የሚያደርግ  ስርአት እንዲዘረጋ ፤በአመራር ደረጃ  ክበቡ አድጎ ለቁምነገር እንዲበቃ ከጣሩት እና ምስጋና ከሚቸራቸው አንዱ አቶ በቀለ ሙለታ ነበሩ፡

ከንባብ ጋር ምንጊዜም የማይለዩት አቶ በቀለ ገና በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ  ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚሆኑ መጣጥፎችን በማዘጋጀት ተሳትፎአቸውን አጠናክረው ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት በሚገኘው ቤተ-መጽሀፍት  በየእለቱ በመሄድ ራሳቸውን በንባብ ያጎለብቱ ነበር፡፡ ይህ ንባባቸው ደግሞ ኋላ ለደረሱበት የሚድያ መሪነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ በቅርበት የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡

አቶ በቀለ የጠለቀ ስነ-ጽሁፋዊ እውቀት ያላቸው፤ በብዛት ያነበቡ ያነበቡትንም ለማካፈል ፈጽሞ የማይሰስቱ ሰው መሆናቸውም ይነገራል፡፡

 በተለይ ደግሞ በሥነ-ጽሁፍ ጉዳይ ላይ  ጥናት ለማድረግ የተነሳን ገጣሚ ወይም ደራሲን ለማገዝና ሀሳቦችንና የሚመለከታቸውን ሰዎች ለመጠቆም ያሳዩት የነበረው ተነሳሽነት እና ልበ-ቀናነት በብዙዎች አድናቆት የሚቸረው ነበር፡፡ ከሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት ያዳበሩ በመሆኑም ‹‹የመረጃ ቋት የሚል ስያሜ ሊሰጣቸው በቅቷል፡፡ታዲያ የአቶ በቀለ የመረጃ ቋትነት መንታ ባህሪይ ነበረው፡፡ አንድም ስነጽሁፋዊ ምርምሮችን ለማድረግየተነሳን ተመራማሪ  በምርምሩ ርእሰ-ጉዳይ ዙሪያ ቀደም ሲል የተሰሩ  ስራዎችን ሳያዛቡና ሳይሰስቱ በመጠቆም ግንባር ቀደም ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ነበር፡፡ ይህም የእውቀት ደረጃቸውን ከፍታ የሚያሳይ ነበር፡፡ አንድ ሰው አቶ በቀለ ሙለታ ጋር ደውሎ የአንድን ሰው መገኛ ፈልጎ ከሆነ ሊያጣው አይችልም፡፡ 

በ1985 እና በ1986 አ.ም የአዲስ ዘመንን ገጾች ያገላበጡ አንባቢዎች  የበቀለ ሙለታን ወይም የአንቀጸ ደስታን የመርካቶ ወጎች ፈጽሞ አይረሷቸውም፡፡ አንቀጸ ደስታ፣ አቶ በቀለ ለረጅም ዓመት የተጠቀሙበት የብእር ስማቸው ሲሆን  ይህ የብእር ስም ከቤተሰባቸው ጋር ተዋህዶ አንቀጸ እንደ መዝገብ ስም የሚጠሩበት ስም እስኪመስል ድረስ ለዘመናት የቆየ ስም ነበር፡፡ አቶ በቀለ ይህን ስም ለምን እንደመረጡ ተጠይቀው ሲመልሱ አንድ ጽሁፍ ላይ ጥሩ አንቀጽ ተጽፎ ስመለከት ልዩ ደስታን ስለሚሰጠኝ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡

 አቶ በቀለ ሙለታ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሊድስታር ዩኒቨርሲቲ ኮለጅ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ወስደዋል።

  አቶ በቀለ ሙለታ ቀድሞ የነበራቸውን የስነ-ጽሁፍ ችሎታ በመያዝ ከየካቲት ወር 1986 ዓ.ም ወደ  በመስራች ጋዜጠኝነት የማህቶት ጋዜጣ  ዝግጅት ክፍልን በመቀላቀል ሙያዊ  ክህሎታቸውን አሳይተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በሳል መጣጥፎችን ወደ አንባቢ በማድረስ የልዩ ችሎታ ባለቤት መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ 

  እስከ ጥር 2000 ዓ.ም ድረስ በኢህአዴግ ምክር ቤት ጽ/ቤት ይዘጋጁ በነበሩ የተለያዩ ህትመቶች ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሰርተዋል፡፡ 14 አመት በእነዚህ ህትመቶች ላይ ሲያገለግሉ በስራቸው ላይ ፍጹም ደከመኝን የማያውቁ ይልቁንም ሰርተው የሚያሰሩ ነበሩ፡፡

 አቶ በቀለ ከየካቲት 1 ቀን 2000 ዓም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2001 ዓም ድረስ በዋልታ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን የአማርኛ ዜና ፣ አርቲክልና መጽሔት ዋና አዘጋጅነት፤ ከሚያዚያ 1 ቀን 2001 እስከ ሰኔ 30 2002 ዓም ድረስ የፕሮሞሽን ዋና ክፍል ኃላፊ፤ ከሐምሌ 1 ቀን 2002 ዓም እስከ ጥር 30 ቀን 2004 ዓም የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ዋና ክፍል ኃላፊ፤ ከየካቲት 1 ቀን 2004 እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2006 የጥናትና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ መምሪያ ስራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል። ዋልታ ባገለገሉበት 6 አመታት ውስጥም በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡ በተለይ ከስልጠና እና ከፖሊሲ ጋር በተያያዘ ደማቅ ስራ እውን አድርገዋል፡፡  በዋልታ ለውሳኔና ፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የህዝብ አስተያየት ጥናት እንዲጀመር: ለክልሎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠትና በተለያያዩ ክልሎች ግጭት አፈታት ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠዎች   ላይ የነበረው አበርክቶ የላቀ ነበር::

ከየካቲት 1 ቀን 2006 ዓም ጀምሮ በቀድሞ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /የዜናና ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ዳይሬክቶሬት/ ዳይሬክተር፤ ከታህሳስ 17 ቀን 2007 ዓም እስከ 2011 ዓም ድረስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው መርተዋል። በተለይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ከኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ወጥቶ ራሱን ችሎ ዳግም እንደ ኤጀንሲ እንዲዋቀር የአቶ በቀለ ሙለታ አስተዋጽኦ ትልቅ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ፡፡  በተለይ በዜና ረጅም አመት ታሪክ ያካበተው  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስሙን እና ክብሩን በጠበቀ መልኩ በባለሙያ እና በግብአት የተሟላ የሚድያ ተቋም እንዲሆን  አቶ በቀለ ታሪክ የማይረሳውን ትልቅ አሻራ አሳርፈዋል፡፡  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘመናዊ የሚድያ ህንጻ እንዲገነባና የተሟላ ስቱዲዮ እንዲኖረው አድርገዋል፡፡  በተጨማሪም ኢዜአ ዘመኑን የዋጀ ሚዲያ እንዲሆን ከድረ ገፅ ጀምሮ እስከ ኦንላይን ቲቪ በፅሁፍና በድምፅና ምስል ዜና የሚሰራጭባቸው አማራጮች እንዲኖሩ አቶ በቀለ ሙለታ የማይዘነጋ አሻራ አኑረዋል፡፡

ይህም ጥረታቸው  የስራ ፍሬያቸውን በተከታተለ ሁሉ  ዘንድ የሚመሰከር ሀቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለ 5 አመት ያገለገሉት አቶ በቀለ ቀጣይ መዳረሻቸው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ነበር፡፡

ከነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓም እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓም ድረስ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተቋሙን መርተዋል። በጊዜው ፋና ብሮድካስቲንግ ውስጥ መሰረታዊ የአሰራር ለውጥ እንዲመጣ በማስጠናት የበኩላቸውን የመሪነት ሚናንም መወጣት ችለዋል፡፡ እርሳቸው መሪ በነበሩበት ጊዜ ኮቪድ በመላ ሀገሪቱ ስለነበር በርካታ ሚድያዎች ከፍተኛ ኪሳራ ባጋጠማቸው ወቅት ፋና በኢኮኖሚ ተጠናክሮ የመጣውን ችግር ተቋቁሞ እንዲያልፍ አቶ በቀለ በአመራርነት  ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን በቅርበት የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክሩላቸዋል፡፡

በመቀጠልም ከታህሳስ 07/2013 እስከ የካቲት 17/2015 ዓ/ም ድረስ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል። አዲስ ሚድያ ኔትወርክ በቆዩበት 2 አመት ጊዜ ውስጥ የበለጠ  አዳዲስ ለውጦች  እንዲመጡ አድርገዋል፡፡ ይህም ሲባል ለአዲስ አበባ የሚመጥናትን የሜትሮፖሊታን ሚድያ  ማለትም የከተማ ማህበረሰብን ማእከል ያደረግ የሚድያ ተቋም እውን ለማድረግ ሞክረው ተሳክቶላቸዋል፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም  ህዝቦች ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ ለዚያ የሚሆን ዘመናዊ የሚድያ ማእከል እንዲፈጠር ሌት ተቀን ለፍተዋል፡፡  የአዲስ ሚድያ ኔትወርክ በልዩ ልዩ የሀገር ቤት ቋንቋዎች ስርጭት እንዲኖረው  እና ተደራሽነቱም እንዲሰፋ አቶ በቀለ ሙለታ የሰጡት አመራር በሚድያ ባለሙያዎች ሳይቀር መመስከር  የቻለ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዲስ ሚድያ ኔትወርክ በቅርቡ የሚዛወርበት አዲስ የሚድያ ጽ/ቤት በማደራጀት አቶ በቀለ እና ባልደረቦቻቸው ትልቅ ተግባር አከናውነዋል፡፡

አቶ በቀለ ሙለታ በ2007 አንቀጸ ደስታ በሚለው የብእር ስማቸው ‹‹የከሀዲዎች ወግ›› የተሰኘ በ144 ገጽ የተሰናዳ መጽሀፍ አሳትመው ለአንባቢ ያደረሱ ሲሆን ‹‹ዜማ›› በተሰኘው መድብል ውስጥ 2 አጫጭር ልቦለዶች ለህትመት በቅተውላቸዋል፡፡ አቶ በቀለ ከአጫጭር ልቦለዶች ባሻገር ግጥሞችንም በመድረስ ይታወቃሉ፡፡

አቶ በቀለ ሙለታ በሀምሌ 25 1995 ከወይዘሮ ደኗ ግዛው ጋር ጋብቻ ፈጽመው  አንድ ወንድ  እና 3 ሴት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን በኑሯቸውም ከሰዎች ጋር ተግባቢ ሰዎችን ለማገዝ ወደ ኋላ የማይሉ ነበሩ፡፡ አቶ በቀለ ሙለታ በሚድያ አለም ላለፉት 30 አመታት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በታማኝነት እና የሚድያ ስራን በመውደድ ሙያዊ አደራቸውን ሲወጡ የነበሩ ብእረኛ እና የሚድያ መሪ ሲሆኑ  ስለራሳቸው ብዙም እንዲነገር የማይሹ ልታይ ልታይ የማይሉ በመሆናቸው ብዙም ለሀገር የሰሩት ስራ ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡ ይሁንና አቶ በቀለ አብረዋቸው በሰሩ ባልደረቦች ብሎም በትልልቅ የመንግስት የስራ መሪዎች ሳይቀር ለትጋታቸው የሚመሰከርላቸው ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡

አቶ በቀለ ሙለታ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሀሙስ ጥቅምት 16 2016 በተወለዱ በ52 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ 

አቶ በቀለ፣ ባለትዳርና የአንድ ወንድና ሶስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ። ለቤተሰባቸው አሳቢ  ባለቤታቸውን እና ልጆቻቸውን የሚወዱ እና ከፍተኛ ክብካቤ የሚሰጡት አቶ በቀለ ይህን ፍቅር ለመላ ቤተዘመዱ በመስጠት ህይወታቸውን በመልካም ሁኔታ አሳልፈዋል፡፡  አቶ በቀለ ሙለታ ምንም እንኳን ህይወታቸው ቢያልፍ የሰሩት ስራ ለመቃብር በላይ ሲነሳ ይኖራል፡፡ ነፍሳቸውን በገነት ያኑር፡፡

ብርቱውና ዝምተኛው ብዕረኛ(ኤዲተር) ክንዱን ተንተርሷል

ስለ በቀለ ሙለታ የተሠጡ ምስክርነቶች

ታደሰ ማሞ (ጓደኛ)

የማወራውም ሆነ የምፅፈው ስለ ዝምተኛው ጋዜጠኛ እና ደራሲ በቀለ ሙለታ ነው ።በዕርግጥ እኔም ሆንኩ ሌሎች ብዙዎች የምናውቀው አንቀፀ ደስታ በሚለው የብዕር ስሙ ነው።የአንቀፀ ብዕር የዋዛ እንዳትመስላችሁ።በ1985 እና በ1986 ዓ ም የአዲስ ዘመን ጋዜጣን የተለያዩ ገፆች ያገላብጡ የነበሩ አንባቢዎች የአንቀፀ ደስታን የመርካቶ ወጎች አይረሷቸውም።

ከመርካቶም በተለይ ምናለሽ ተራ፣ኮርቻ ተራ፣ዶሮ ተራ፣አውቶብስ ተራ ፣ወበቀኝ ሰፈር፣ፎዴ ተራ፣ቦምብ ተራ፣ጣፋጯ የተቀመመች ምግብ ቤት፣…ኧረ ስንቱ።አንቀፀ በብዕሩ የመርካቶን ገበና እና ጓዳ ጎድጓዳ ግልጥልጥ ካደረገ በኋላ መስሎኝ ሌሎች ጋዜጠኞች ወደ መርካቶ በድፍረት መዝለቅ የሞከሩት።

ምክንያቱም አንቀፀ(በቄ) የመርካቶ ሰባተኛ ልጅ ስለሆነ መርካቶን መግቢያ መውጫዋንና ዕድፍ ጉድፏን በሚገባ ያውቃልና የሚፅፋቸው ወጎች አስደማሚ ነበሩ።ለነገሮች ግድ ስለሌለው፣ልታይ ልታይ ስለማይል፣የመርካቶ ልጅ ነኝ ብሎ ጮክ ብሎ ስለማያወራ የበቄን የአዲስ አበባ ልጅ መሆን የሚጠራጠሩ ብዙ ናችው።ዕድል ገጥሞት ወይ በሆነ መድረክ አሊያም በሻይ ቡና ላይ አብሮት የተቀመጠና አብሮት ያወጋ አሊያም ማዕድ የቆረሰና ጫወታውን የተቀላቀለ ይሄ ሰውዬ እንዲህ ወግ ያውቃል እንዴ? ብሎ መጠየቁ የተለመደ ነበር።

እኔና አንቀፀ የምንተዋወቀው ከ1982 ዓ ም አንስቶ ነው።በወቅቱ በክረምት ወራት የባህልና ስፖርት ቢሮ ባዘጋጀው የስነ ፅሁፍ ስልጠና ላይ ለመታደም በአዲስ አበባ 70 ደረጃ አካባቢ እሱ ከመርካቶ እኔ ከአብነት አካባቢ የማስታወቂያ ጥሪ አይተን ከተገኘንበት ጊዜ ጀምሮ ነው።በወቅቱ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ልጆች በቲያትርና ስነ ፅሁፍ ሲሰለጥኑ እኛም ተደምረን በስነፅሁፉ ዘርፍ በሰርቲፊኬት ተመረቅን።በጊዜው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እነ ረዳት ፕሮፌሰር ደበበ ሰይፉ፣ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ጋሽ ዘሪሁን አስፋው፣ጋሽ ደረጄ ደመቀ፣ስብሀት ገብረ እግዚአብሄር፣የሺጥላ ኮኮብ፣ሀይማኖት ዓለሙ፣ጋሽ አስፋው ዳምጤ እና ሌሎችም በተጋበዥነት ያሰለጥኑን ስለነበር የተመረቅነው በታላቅ ወኔ ነበር።ደራሲ ለነሆን!!

ከዚያ በኋላም ፍላጎቱ ያላችሁ የሙያ ክበብ መስርታችሁ ተንቀሳቀሱ ስንባል የቲያትር ሰልጣኞች እንደ አፍለኛው ያሉ የቲያትር ክበባትን እኛ ደግሞ ፍካት የስነ ፅሁፍ ክበብን መስርተን መመሪያና ደንብ ሁሉ ተዘጋጅቶልን በ1984 ዓ ም ህጋዊ ፈቃድ አገኘን።ከዚያ በተመሳሳይ በየአዳራሹ ታላላቅ የአገሪቱን የስነ ፅሁፍ ሰዎች እየጋበዝን፣የስነ ፅሁፍ ምሽቶች እያዘገገጀንና በመፃህፍት ዙሪያ እያነበብንና እየተከራከርን አቅማችንን ለማጠንከር ስንታትር በአመራር ደረጃ ከፊት ቀድመው ክበባችንን ካሳደጉት መሀል አንቀፀ ቀዳሚው ተጠቃሽ ነበር።

ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ እኛም ክበባችንን እና ራሳችንን ከህዝብ ጋር ለማስተዋወቅ በማሰብ በወቅቱ እንደ አሸን ፈልተው በነበሩ ጋዜጦች ላይ የተለያዩ ዓይነት ዘገባዎችና አርቲክሎች በክበባችንና በስማችን መፃፍ ጀመርን።ያን ጊዜ ነው የክበባችን አመራር በቀለ ሙለታ አንቀፀ ደስታ በሚለው ብዕሩ ከመርካቶ ወጎች ጋር ለአንባቢያን ብቅ ያለው።

በሂደትም በጋዜጠኝነት ዘርፍ ተመርቀው የሚወጡ ፀሀፊያንን ማግኘት የተቸገሩት ጋዜጦችና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በወቅቱ በነበሩና በክበባት ተደራጅተው በተለይም ሀሳብና ገጠመኞቻቸውን በፅሁፍ መግለጽ በሚችሉት ላይ በማተኮርና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት መቅጠር ጀመሩ።እኔ ወደ አዲስዘመን ጋዜጣ ሳመራ በቀለ ማህቶት ወደተባለች የብአዴን ልሳን አቀና።ሌሎቹም አባላት እንዲሁ በየሚዲያው ተበተኑ።

ከዚያ በኋላ ጋዜጠኝነት እንጀራችን ሆኖ እኔና በቀለ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ አብረን ሰርተናል።የስነፅሁፉ ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል ብለን በጋዜጠኝነቱ ዓለም ሰመጥንና በኋላም ዲግሪና ዲፕሎማ በሙያው አግኝተን ከሪፖርተር እስከ አርታኢ ያለውን ደረጃ ዘለቅን።

አንቀፀ የፍካት ልጆች ተሰባስበው ባሰተሟት ዜማ የተሰኘች የአጭር ልቦለዶች ስብስብ ላይ ሁለት ትረካዎችን አካቶ ለንባብ አብቅቷል።በኋላም የከኃዲዎች ወግ በተሰኘ ርዕስ በግሉ የአጫጭር ለቦለዶች መድብል በማሳተም ለስነ ፅሁፍ ያለውን ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል።በዙዎቻችን የጋዜጠኝነት ዓለም ውጦ ከስነ ፅሁፍ መንገድ ካራቃቸው ብዕረኞች አንዱ አንቀፀ መሆኑን ብናምንም በጋዜጠኝነቱ ጉዞም የተሳካለትና ለተለያዩ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች በስኬት ዓለም መጓዝ የድርሻውን የተወጣ በመሆኑ በብዙዎች ልብ ውስጥ ሲታወስ ይኖራል የሚል ስንቅ ቋጥረናል።

አንቀፀ ፅፎ ያስቀመጣቸው ልቦለዶች እና መጣጥፎቹ አንድ ቀን የህትመት ብርሀን እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ በጋዜጠኝነት መንገዱ ላይ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ባይሰለችም የልቡ ሳይደርስና በቃኝ ሳይል ሞት ቀድሞታል።

ከህትመት ሚዲያዎች በተጨማሪ በዋልታ፣በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከኤዲተርነት አልፎ በዋና ዳይሬክተርነትና ዋና ስራ አስኪያጅነት መርቷል።ከወጣትነቱ ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት በሚዲያ አመራርነት ብዙ የለፋው አንቀፀ ለስራ እና ለለውጥ ፊት ለፊት ሁሌ ቆሞ የሚገኝ በመሆኑ በተለይ በሀላፊነት በመራባቸው የሚዲያ ተቋማት ውስጥ ወዳጅና ጠላት ያፈራ ቢሆንም እሱ ግን ሁልጊዜም በሰራው ስራ የማያፍርና በልበ ሙሉነት ኩራት እንደተሰማው ይቺን ዓለም ተሰናብቷል።

ሁሉን በሆዱ ይዞ የግንባር ስጋ እየሆነ ከስራ ጋር በተያያዘ የሚጋፈጠው አንቀፀ በየትኛውም ቦታ የችሎታ ዕጥረት እንደሌለበት እና ጠንካራ ክህሎት እንዳለው የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል።ሆኖም ለእንደ አንቀፀ ዓይነት ሰዎች ይቺ ዓለም የምትደላ ባትሆንም አርዓያነቱንና ብርቱነቱን በቅርብ የሚያውቁትና ከዕውቀቱ ሳይሰስት ባቋደሳቸው ዘንድ እየተዘከረ ይኖራል።

አንቀፀ ካለፈው የካቲት 2015 ዓ ም ጀምሮ በመጨረሻ  በአመራር ላይ ከነበረበት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ይሄን አርገሀል እንኳን ተብሎ ሳይነገረው ከስራው ተነስቶ ቃል የተገባለትን የምደባ ቦታ በጉጉት እንደጠበቀ ስልኩ በጮኸ ቁጥር የት ሊመድቡኝ ይሆን ብሎ እንደጓጓ ይቺን ዓለም ተሰናብቷል።ኧረ ባክህ የመንግስትን ምደባ ብቻ አትጠብቅ ገልበጥበጥ በል ስለው እንኳን ቆይ እንጂ የጀመርኩትን ከዳር ሳለደርስ ወዲህም ሌላ ቦታ ትመደባለህ እንጂ አጥፍተህ ተባረሀል አልተባልኩ እያለ በትዕግስት ጠብቆ አልፏል።የቸገረህ ነገር ካለም እንነጋገር ስለው በቀን አንድ እንጀራ ካገኘሁ ይበቃኛል ለዚያ ደግሞ የባለቤቴ ደመወዝ ትበቃለች እያለ አራት ልጆቹን፣የሚወዳትን ባለቤቱንና እኛን ወዳጆቹን ሳይፈልግ ጥሎ አልፏል።

የገረመኝ ነገር ከስራ ተገልሎ ምደባ እየጠበቀ ችሎታውንና አቅሙን የተረዱ የግል ሚዲያ ባለቤቶችና የሚዲያ ስልጠና ማዕከላት ከኛ ጋር እንስራ እያሉ ጥሩ ክፍያ ቢያቀርቡለትም ደመወዝ እንኳን ተቋርጦበት መንግስትን በተስፋ እየጠበቀ እስከወዲያኛው አሸልቧል።አሳዛኙና የከፋው ነገርም ይሄው ነው።ሞትንማ ሁላችንም እንሞታለን።የአንቀፀ ለኔ የተለየና የሚቆጭ የሆነብኝም ለዚሁ ነው።በምድር ያልደላህ ወዳጄና ሚስጥረኛ ጓደኛዬ አንቀፀ የሰማዩ አምላክ በመልካም ይቀበልህ።ነፍስ ይማር በቄ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *