የፋና ታሪክ በአጭሩ
ህዝብ ሀሳቡን በነፃነት የሚገልፅበት እና ድምፅ ለሌላቸወ ድምፅ ሆኖ መገኘትን አላማው አድርጎ በረሀ ላይ የተፈጠረው የሬድዮ ጣቢያ መነሻው ታናሽ ቢመስልም ሩቅ አሳቢነቱን ከመነሻው ሰንቆ ዳሽን ተራራ ላይ የጀመረውን ጉዞ ቀጥሎ በልኡል አስራተካሳ ግቢ ውስጥ ስርጭቱን በአንድ እርምጃ አሳደገ። በህዳር 12/1987 ዓ.ም ታድያ ለራሱ ስያሜ በማውጣት ”ሬድዮ ፋና ” በሚለው መጠሪያው የንግድ ሚድያ ሆኖ ተገለጠ። ፋና በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ እኩል ሰዓት ነበር ስርጭቱን የጀመረውና ስያሜውም ሁለቱንም ቋንቋ የሚገልፅ ብርሀንና የዳና መገለጫን እንዲይዝ የተፈለገው ያለምክንያት አልነበረም። ወደ ፊት የሚመለከትን ሀሳብ የያዘ የብርሀን መንገድ እንዲሆን በማሰብ ስያሜው ፀና እንጂ።
መስፍን አለማየሁና መስፍን አሸብር ፋና ሲነሳ አብረው የሚነሱ የቤቱ ፈርጦች ነበሩ፡፡ ተቋሙ ዛሬ ላይ ለመድረሱ ትልቅ መሰረትን የጣሉ ተብለው ይመሰገናሉ። እነርሱም ብቻ አይደሉም የግዜው አመራሮችም በብቃት መምራት መቻላቸው ለስኬቱ ምክንያት ነበሩ። ከ1994-95 ባለው ጊዜ ፋና የመደራጀት ግዜው ነበር ማለት ይቻላል ፤ቋንቋዎች ማለትም አፋርኛና ሱማሌኛ የተጨመሩት በዛ ወቅት ነበር። ስርጭቱ ጠዋት ቀንና ማታ 1 ሰዓት የነበረው ሬድዮ እየጠፋ ነበር የሚበራው በይዘቱ ደግሞ በተለይም በፖለቲካዊና ጠንከር ባሉ የህዝብ ድምፅ ሊሆኑ በሚችሉ ፎርማቶች ብቅ ሲል በመዝናኛው ረገድ የአድማጭን ደብዳቤ ለማስተናገድ የሚቻል እንዲሆን ተሰራ።
ፋና ሲነሳ ሌላው አብሮ የሚታወሰውና በተለይም በዜና አቀራረቡ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ግዜውን መለስ ብሎ ሲያስታውስ በወቅቱ አቶ ሙሉጌታ ገሰሰ የተባሉትን መሪ በማነጋገር በልዩ ፍላጎት በለሊት እየገባ ዜና ያነብ እንደነበረ በደስታ ያስታውሰዋል፡፡ ጋዜጠኛ ደግአረገ ነቅአጥበብ ደግሞ ሙዝ እንደመላጥ ቀላል አድርጌ ነበር የማስበው በማለት በፋና ውስጥ መስራት በሁሉም ረገድ የተሻለ ሰይፍ ሆኖ እንዲቀረፁ የሚያደርግ ቤት ነውና በጥበባት አለም ላይ ይሰራ እንደነበር ሁሉ በሌሎቹም ጉዳዮች መሳተፉ እንደጠቀመው ምስክርነት ይሰጣል። በጊዜው በፋና ውስጥ ዝናን ካተረፉ ፎርማቶች መካከል አራዳ ነቃሽ አንዱ ነበር።
አራዳ ነቃሽ ጋዜጠኛው በራሱ ነቅሶ የሚመለከተውን ጉዳይ የራሱ ጉዳይ አድርጎ የሚቀርብበት ፎርማት ሲሆን ካሳ አያሌው ካሳ ወዶ የመረጠው ፎርማት ሲሆን የራሱ ብራንድ እስኪመስል ድረስ በብቃት የተፈፀመ ሆኗል፡፡ የህዝቡም ጥያቄ በአግባቡ የተደመጠበት ፎርማት ነበር። ከዚህ ፎርማት ጋር በተያያዘ በፊት በብሄራዊ ጣቢያው ህዝቡ ምን ይላል? በሚል ተደማጭነትን ያተረፈ በመሆኑ ካሳ አያሌው ካሳ ልምድ ካላቸው የብሔራዊ ጋዜጠኞች ጋር በመተጋገዝ በመስራታቸው ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ይናገራል። በፋና ውስጥ የፎርማት ምስረታ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን ለ10 ቀን ቁጭ ብለው አውርተው ጥናትና ምርምር በማድረግ ነበር የሚሰሩት። ስፖርት ፋና፣ ህዝቡ ምን ይላል፣እርሶ ቢሆኑ፣ልብ ለልብ፣ደብዳቤዎቻችሁ እና የመሳሰሉት ፎርማቶችም ተጠቃሽ ናቸው።
ጊዜው በቴክኖሎጂ የዘመነ አቅም የነበረበት ባይሆንም በነበረው ኋላ ቀር ሪል ቴፕ ኡኸር የተባለ 5 ኪሎ የሚመዝን መቅረፀ- ድምፅ ተሸክመው በመሄድ ጋዜጠኛው በሚያመጣው ህዝቡን ይመጥናል ባለው ሀሳብ አየሩን ሲያስውብ ቆይቷል።በጊዜው የመሳሪያ እጥረት ቢኖርም እንኳ በጋዜጠኛው መካከል ተባብሮ በመስራት ባህሉ የማን ስራ ይቀድማል ተብሎ ተናብቦ መስራት በመቻላቸው ግዜውን ተሻግረውታል። ሰራተኛው በስነምግባር፣ ከትግል ጀምሮ በተለመደ የንግግር ባህል በጋራ ብሪፍ ተነጋግሮ በመግባባት ስራው በፍቅርና በጥራት እንዲሰራ አድርጓል። ሞርኒንግ ብሪፍ በ15 ደቂቃ የሚነጋገሩበት የስራ ግምገማ ነገርን ሁሉ ፊት ለፊት ለመነጋገር እድል ፈጥሮ ቆይቷል።
ፋና ወደ ሚሊኒየሙ መዳረሻ በአዲስ አቅም በኤፍ ኤም ስርጭቱ ብቅ ለማለት ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ በመጋቢት 1/1999 ፋና ኤፍ ኤም 98.1 ጀመረ። በኤፍ ኤም ስርጭቱ ታድያ ተጓዥ ነቃሽ እንዳለ ሁሉ 90 ደቂቃ በሚል አጫጭር ይዘቶችን የያዘ እና ተወዳጅነትን የፈጠረ በብዙ ሌሎች ጣቢያዎችም መማሪያ መሆን የቻለን ፎርማት በቀዳሚነት ይዞ በመቅረብ ዳግም ማበብ ችሏል።
በክልል ጣቢያ ስርጭት ረገድ ጎንደርና ጅማ የመጀመሪያ የኤፍ ኤም ስርጭት የጀመረው ፋና ከጊዜ ወደጊዜም በርካታ ኤፍኤም ጣቢያዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በማቋቋም አድማጩ የራሱን ጉዳይ በራሱ ቋንቋ እንዲያቀርብ እድል ፈጥሯል። አሁን 13 የኤፍ.ኤም ጣቢያዎችን የያዘ ሲሆን ይሄንን መንገድ ደግሞ የግዜው ከፍተኛ አመራሮች ኤንፒአር ከተባለው የአሜሪካን ሀገር ሬድዮ ጣቢያ ልምድ በመውሰድ ማኔጅመንት ላይ በመወሰን ያስመዘገበው ውጤት ነው።
የፋና ልዩ ባህል የሚባለው በሰራተኛው ውስጥ የእኔነት ስሜት መፍጠር መቻሉ ሲሆን ሁሉም ራሱን ሰጥቶ የሚሰራበት ወጥቶ የሚመለስበት በባዶ መጥቶ በብዙ እውቀት የሚወጣበት ድንቅ የመማሪያ መድረክ መሆን መቻሉ የሚያስመሰግነው ነው። በክልል ጣቢያዎቹ የአካባቢን ባህል ባለቀቀ መልኩ የነዋሪው ድምፅ እንዲሆኑ ተደርገው የተዋቀሩ ሲሆኑ በአካባቢው ተወዳጅና ተናፋቂ የሆኑ ፎርማቶችን በክልል ጣቢያዎች መስራት መቻላቸውም የዚሁ ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደምሳሌ የመቀሌው ድራር፣ ድባታ ደሴ አሻም በሚዛን የሚዘነጉ አይደሉም።በፋና ውስጥ፡፡
ይዘት እና አቀራረብ ላይ የሚሰጠው ትኩረት ለስራው ውጤታማ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። የምርመራ ጋዜጠኝነትን የሚጠይቁ እና የቅሬታ ዜናዎች ላይ በመስራት የቀጠለው ጣቢያው ዛሬም ድረስ ከዚህም በላይ በጥልቀት የመስራት እቅድ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው። ረዥም አመትን ያስቆጠሩ ፎርማቶችን ይዞ የዘለቀ የሬድዮ ጣቢያም መሆኑን ልብ ይለዋል። የፋና ገቢ ምን ይሆን ብሎ ለሚጠይቅ ሰራተኛው በላቡ የሚያገኘው ገንዘብ ገቢው መሆኑን ማየቱ የሰራተኛውን ትጋት የሚመሰክር ሆኖ እናገኘዋለን። ተቋሙ የንግድ ተቀም እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ መንገዶችን በመፍጠር እራሱን ሲደጉም የቆየ ሲሆን ከተባባሪ አዘጋጆች ጋር በመተባበር በሚሰሩ ርዕሰ ጉዳዮች በታላቅ የመድረክ ዝግጅቶች እና የዶክመንተሪ ዝግጅቶች በማስታወቂያም ጭምር የራሱን ገቢ በራሱ ለማሳደግ የሰራ እድገቱም በአይን የሚታይ መሆን የቻለ ነው።
በ2000 ዓ.ም በኮርፖሬት ደረጃ ከተዋቀረ ወዲህ በ2010 ደግሞ በቴሌቪዥን ብቅ አለ ፋና። በጣም ዘመናዊ የተባለ የቴክኖሎጂ አቅም ይዞ የቀረበ መሆኑ አንዱ ስኬቱ ሲሆን በይዘቱ ደግሞ ቀድሞ ከነበረው የአሰራር ልምድ በመነሳት ለአድማጭ ተመልካቹ በመጨነቅና ዋጋ በመስጠት ሀገርንም በማስቀደም ሲሰራ ቆይቷል፡፡ እየሰራም ይገኛል። ፋና በቴክኖሎጂ በጥራት በአዳዲስ ፎርማት ይዘቱን ከቀደመውም በላይ ከፍ አድርጎ የህዝብን ድምፅ ባዳመጠ መልኩ ዛሬም እንደቀደመው በትጋት ለመስራት ቁርጠኝነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። እነሆ ፋና ዘንድሮ ህዳር 12 2015 ሲመጣ 28 አመት ይሞላዋል፡፡ ለጣቢያው እዚህ መድረስ ቀን ተሌት ሲለፋ የኖረው ባለሙያው በቀዳሚነት ሊመሰገን ይገባል፡፡ በመቀጠልም የአሁንና የቀድሞ አመራሮች ይመስገኑ፡፡ ለማንኛውም ይህ ሩብ ክፍለ -ዘመን ያሳለፈ ቤት 28 አመት ሞላው፡፡