ፊታውራሪ መሐረነ ምንዳ (1917-1971)

የዶክተር ወዳጄነህ መሐረነ አባት

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ መፅሐፍ ፣ከ20 በላይ ዘርፎች ይኖሩታል። ከእነዚህም ዘርፎች አንዱ “ከተማ እና አገር ያስተዳደሩ ” የሚለው ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፍ ታሪካቸውን የምንሰንደው የፊታውራሪ መሐረነ ምንዳን ነው። ቤተሰቦቻቸውን በማስፈቀድ እና ማረጋገጫ እንዲሰጡ በማድረግ እዝራ እጅጉ እና ሐና ምንዳዬ ታሪኩን ሰንደውታል።
ፊታውራሪ መሐረነ ምንዳ ማናቸው?

ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ በልዩ ልዩ የኃላፊነት ሥራ ላይ ተመድበው ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት ፊታውራሪ መሐረነ ምንዳ አገራቸውን በማገልገል የሚታወቁ ሰው ናቸው።

ፊታውራሪ መሐረነ ምንዳ ግንቦት 4 ቀን በ1971 ዓ.ም በ54 አመታቸው የሞቱ ሲሆን ቀብራቸው በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል ።

ፊታውራሪ መሐረነ ምንዳ ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ በፖሊስ ሠራዊት ውስጥ ተቀጥረው እስከ መቶ እልቅና ደረጃ ደርሰዋል ። ከዚያም ወደ ጉምሩክ መሥሪያ ቤት ተዘዋውረው በኢንስፔክተርነት ለቀላፎ ለሙሉታሂልና ለፌርፌር ጉምሩኮች ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል።

ከ1946 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስአበባ ጉምሩክ ምክትል ሹም ፣ የአሰብ ጉምሩክ ምክትል ዳይሬክተር ከ1948 ዓ.ም አንስቶ የዋርዴር ወረዳ አስተዳደሪ በ1950 ዓ.ም የኦጋዴን አውራጃ ህዝብ ፀጥታ ጥበቃ ክፍል ኃላፊ እና ዳይሬክተር እስከ 1949 ዓ.ም ድረስም የጅጅጋ አውራጃ አስተዳዳሪ በኦጋዴን አውራጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ደረጃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ኦጋዴንን ያስተዳድር ለነበረው ሦስተኛ ክፍለ ጦር ዋና አማካሪም ነበሩ።እና ከጦሩ አዛዥ ቀጥሎ ምክትል አስተዳዳሪ በመሆን እስከ 1959 ዓ.ም ድረስ ሀገራቸውን አገልግለዋል ። ከዚያም የሐረርጌ ምክትል ዋና አስተዳደሪ ከ1966 – 1967 ዓ.ም ደግሞ የወሎ ክፍለሀገር ዋና አስተዳዳሪ ከዚያም እስከ 1969 ዓ.ም ድረስ የሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ሆነው በመሥራት ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡ ናቸው ።

በ1969 ዓ.ም በጡረታ ክልል ውስጥ ከተመደቡበት ጊዜ አንስቶ ባላቸው ልዩ ሙያ እና የበሰለ ችሎታ የኢትዮጵያን አንድነትና ዕድገት ሲረዱ ቆይተዋል ።

ፊታውራሪ መሐረነ ምንዳ የቀዳማዊ ሐይለስላሴ የቅርብ ሰውና የዶ/ር ወዳጄነህ መሐረነ አባት ነበሩ”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *