ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል።
ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል።በተጨማሪም በሳይንስ፣ በመምህርነት ፣በምህንድስና እና በሌሎችም ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ አንባቢ እያመጣን እንዲታወቁ ጥናትና መረጃ ማድረግ ለሚሻም ተደራሽ ስናደርግ ቆይተናል።
የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
በዚህ ፅሑፍ የሕይወት ታሪኳ የሚሰነደው የዶክተር ቤተልሔም አትፊልድ ሲሆን እርሷም በሥነፅሑፍ ሥራ ተሠማርታ የምትገኝ የዘርፉ ባለሙያ ናት። የኢትዮጵያ የድርሰት ሥራዎች በእንግሊዝ ተተርጉመው ሥነ ፅሑፋችን መታወቅ አለበት የሚል የፀና እምነት ያላት ዶክተር ቤተልሔም ከሰሞኑ የአዳም ረታን ሥራዎች ተርጉማ ለንባብ አብቅታለች።
ዶክተር ቤተልሔም አትፊልድ ከተወዳጅ ሚድያ የቀረበላትን ጥያቄ ተቀብላ፣ ታሪኳ እንዲሰነድም ፈቅዳለች።ለዚህም ረቂቁን መመልከቷን በመግለፅ ማረጋገጫ ሰጥታለች። ዕዝራ እጅጉ እና ጆን ዘለቀ ታሪኳን ሰንደውታል።
ኑሮዋን በእንግሊዝ አገር ያደረገችው በአሁኑ ሰዓት በባለቤቷ ሥራ ምክንያት በናይጄሪያ የምትገኘው ቤተልሔም አትፊልድ በትርጉምና በአርትኦት ሥራዎቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትታወቃለች። በተለይ በትርጉም ሥራዎቿ አሻራ ለማኖር ሞክራለች።
የመጀመሪያ ዲፕሎማዋን በሴክሬታሪያል ሳይንስ ከአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ አግኝታለች። የመጀመሪያ ዲግሪዋንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ አግኝታለች። ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ ከእንግሊዝ አገር፣ በርቤክ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሎንዶን በሥነ-ጾታ፣ ባህልና ማኅበረሰብ የትምህርት ዘርፍ አግኝታለች። በዚያው እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦቭ በርሚንግሃም ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪዋን በትራንስሌሽን ስተዲስ አግኝታለች።
ቤተልሔም የሥነ-ጽሑፍ ጥልቅ ፍቅር ያላትና ሌሎችንም ሥራዎች የምትሠራ ቢሆንም በአማርኛ ቋንቋ የተደረሱና የተሰናዱ በአገራችን የተዘጋጁ የልቦለድ ሥራዎችን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎም ሥራ ጎላ ብላ ትጠቀሳለች። በዚህ ሥራዋ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ መጽሐፍትን በመተርጎም በማሳተም በማስተዋወቅና መስኩ እንዲጎለብት ጥናታዊ ፅሁፎች በማቅረብ የኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ለዓለም ማኅበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል የበኩሏን አስተዋጽኦ ታደርጋለች።
የትርጉም ሥራ
የመጀመሪያ የትርጉም ሥራዋ የይስመአከ ወርቁን “ክቡር ድንጋይ” የሚል የልብ-ወለድ መፅሃፍ ሲሆን “ዘ ሎስት ስፔል” በሚል ስያሜ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉማው እንግሊዝ አገር በሚገኝ አሳታሚ ታትሞ የደራሲያን የመጀመሪያ የትርጉም ሥራ ሽልማት ማኅበር (2022 እ.ኤ.አ) ለሽልማት ቀርቦ ለመጨረሻ ደረጃ ዕጩነት ደርሷል ።
ከዚህ ሥራዋ በመቀጠል፣ የአዳም ረታን የድንች መዋስት “Requiem for Potatoes” በሚል አርእስት ወደ እንግሊዝኛ መልሳዋለች።
የአዳም ረታን ሥራዎች ትርጉም በመቀጠል ከ“እቴ እሜቴ የሎሚ ሽታ” መፅሃፍ አራት አጫጭር ልብ-ወለድ ታሪኮች በመተርጎም ለዶክትሬት የጥናት ፅሁፏ መሠረት በማድረግ አገራዊ የትርጓሜ ስልቶች አዋቅራ አቅርባለች። ይኸው የትርጉም ሥራዋም በሆላንዱ ፊዴሳ ፐብሊሽንግ አሳታሚ ድርጅት “Couch Grass” (ኮውች ግራስ) በሚል አርእስት ታትሞ ይገኛል። የዚህን ሥራዋን የሥርጭትና ማከፋፈል ሥራ በኢትዮጵያ የሚያከናውነው ሊትማን ቡክስ ነው።
መገኛውን አሜሪካ ያደረገው “ታንግ” መጽሔት ከሌላኛው የአዳም ረታ ቅንጫቢ የትርጉም ሥራዋ ከሆነው “መረቅ” ከተሰኘው ሥራዋ በመውሰድ “Broth” በሚል የእንግሊዝኛ አርእስት አሳትሞላታል።
ሌሎች በከፊል የተወሰዱና ለሕትመት የበቁ ሥራዎቿ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
ዳኛው ማን ነው? “Who is the Judge” በሚል የእግሊዝኛ አርእስት የተረጎመችው በአሴምፕቶት ጆውርናል ታትሟል።
በለስ አልባ ገነት በሙሉጌታ አለባቸው የተፃፈ “Heaven Without Prickly Pears” በሚል ከሙሉጌታ ጋር ወደ እንግሊዝኛ የተረጎመችው በአሴምፕቶት ጆውርናልና በሂፖክሪት ሪደር መፅሔት ታትሟል።
ካልታተሙ ሥራዎቿ፡-
“ወድቆ የተገኘ አገር” በይፍቱ ሥራ ምትከለ የተፃፈ “The Abandoned Nation” በማለት ቅንጫቢውን ወደ እንግሊዝኛ ትርጉም የሠራችው ይጠቀሳል።
በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ከሚካኤል ሺፈራው ‘ሚስጥረኛው ባለቅኔ’ በሚል ከጻፋቸው የፀጋዬ ገ/መድኅን የተመረጡ ሥራዎች የግምገማ ሥራውና ከሱራፌል አበበ “የሰለባ ገዳይ” በሚል ከጻፈው የተረጎመቻቸውን ሥራዎቿን መሠረት በማድረግ የድኅረ-ዶክትሬት ጥናቷን ለመሥራት በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
ደግሞም የመሠረት ኃይሌ ዝምተኛው ልኡል የተሰኘውን የእውነተኛ ታሪክ ሥራ በመተርጎም ላይ ትገኛለች።
ድርሰት፣ አርትኦትና ተያያዥ ሥራዎች
ቤተልሔም ከተርጓሚነቷ ባሻገር ፀሃፊና አርታኢም ናት። በአሴምፕቶት ጆርናል ለናይጄሪያ በዋና አርታኢነት ታገለግላለች።
ከድርሰት ሥራዎቿ መካከልም በሻክራ አሳታሚ የታተመዉ Tarik የተባለ የታሪካዊ ልብወለድ ስብስብ ይገኝበታል። የትርጉም ሥራዎቿን ቅንጭብ የምታቀርብበት የራሷ የዩቲዩብ ፖድካስትም አላት።
ከትርጉምና የአርትኦት ሥራዋ በተጨማሪ፣ በሥነ-ጽሑፍ ትርጉም መስክ ዝንባሌውና ፍላጎቱ ላላቸው ለጥቂት ሰዎች የማማከር ሥራዎችን ሠርታለች፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም በፓናል ውይይት ላይ አስተያየቷንና ተሞክሮዋን ታጋራለች።
ተቋማት
በግሎባል ሳውዝ ሀብ በማኅበረሰብ ተሳትፎ አስተባባሪነትና ፖድካስት ሥራ-አስኪያጅነት፣ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና በሕጻናት አድን (ዩኬ) በመጀመሪያ በጸሐፊነት በኋላ ደግሞ በረዳት የፕሮጀክት ኃላፊነት የሥራ መደብ አገልግላለች።
በተለያዩ ክፍለ ዓለማት በመዘዋወርም በቬትናም አገር የዩኔስኮና የዩኤን የሴቶች በአማካሪነት አገልግላለች።
በእንግሊዝ አገር በሰሴክስ ኢንተርፕሬተርስ ሰርቪስስ አገልግላለች።
በዚያው በእንግሊዝ አገር ኦንላይን የሚሠራ “ብሬይን ሸር አፍሪካ” የተሰኘ በኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶችን በተለያዩ ጉዳዮች የሚያማክር ከኢትዮጵያ የዳያስፖራ ባለሙያዎች ጋር ትስስር ያለው ድርጅት መሥርታለች።
ሌሎች የግል ሥራዎቿና ጥረቶቿ
በተለያዩ ተቋማቶች የምትሠራቸው ሥራዎች አዘውትሮ ከአገር አገር መጓዝን በባህሪያቸው የሚጠይቁ በመሆኑ ምክንያት “ከቆዳ ውጤቶች የሚሠሩ የእጅ ቦርሳዎችን ዲዛይን የማድረግና የማምረት” ሥራዎችን ጀመርኩ ትላለች ቤተልሔም። ይህንን ከቆዳ ውጤቶች የተሠሩ የቅንጦት ቦርሳዎች ሥራዋንም በቬትናም አገር ‘ቤት ኤም. አለም’ በሚል የንግድ ምልክት ማምረት የጀመረች ሲሆን ይህንን ሥራዋን ወደ ዚምባብዌ በሄደችበት ጊዜም ቀጥላበታለች።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብም ‘ብሬን ሼር አፍሪካ’ የሚባል በዩኬ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሥርታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በኦንላይን የማማከር ሥራ ሰርታለች።
በካኖ፣ ናይጀሪያ ከቆዳ ውጤቶች የሚመረቱ የቅንጦት እጅ ቦርሳዎች አምራች የሆነው “አፍሮፒያ” የተሰኘው ድርጅት መሥራች ዳይሬክተር ነበረች። ድርጅቱ የቅንጦት ቦርሳዎችን ለአውሮፓ ብራንድ ኩባንያዎች አቅራቢ የነበረ ሲሆን በብዛት ወደ እስፔን አገር ነበር የሚላከው።
በታንዛኒያ የሀኒ ፋሽን ጀውለሪ እና የሽዘን የውበት መጠበቀያ ምርቶች አከፋፋይ ነበረች።
በካትማንዱ ደግሞ ፖፕ-አፕ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ከጓደኛዋ ጋር በመሆን አቋቁማለች።
የሙያ ድርጅት አባልነት
ቤተልሔም የኢትዮጵያ ተርጓሚዎች ማኅበር አባል ስትሆን ማኅበሩ ከመመሥረቱ በፊት ስለሙያ መስኩ ለመወያየትና መስኩን ለማሳደግ ከጥቂት የሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን የመሠረተችው የሥነ-ጽሑፍ ተርጓሚዎች ድር መሥራችና አባል ነች።
ሽልማት
ቤተልሔም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2023/24 ከአፍሪካ ተቋም የግሎባል አፍሪካ ትራንስሌሽን አዋርድ ሽልማት አግኝታለች።
ውልደት፣ እድገትና ቤተሰብ
ቤተልሔም አትፊልድ የተወለደችው መጋቢት 7/1962 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ከቤተሰባቸው አምስት ልጆች መካከል ሦስተኛዋ ናት። ሁለቱም ወላጆቿ የሕክምና ባለሙያዎች የነበሩ ሲሆን በትምህርቷ የላቀ ውጤትን እንድታስመዘግብ ይጠብቁ ነበር።
በልጅነቷ እናቷ አለርት ሆስፒታል ትሠራ ስለነበር በሆስፒታሉ አብረዋት ይሠሩ የነበሩ የውጭ አገር የሙያ ባልደረቦቿ ልጆቻቸው የተጠቀሙበትን የእንግሊዝኛ መጽሐፍት እቤት ይዛላት ትመጣ ነበር ።ገና ከትንሽነት እድሜዋ ጀምሮ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የማንበብ ፍላጎት እንዲኖራት አድርጓል። በተመሳሳይ በአማርኛ ቋንቋ ተጻፉ የተረት መጽሐፍትን ታነብብ ነበር።
የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የተማረችው ድሮ መሠረተ ህይወት አሁን ደግሞ ቃለ ሕይወት የሚባለው ጌጃ ሠፈር ያለ ት/ቤት ነው። ቤተልሔም ስለዚህ ት/ቤት ስትናገር “እጅግ ጥሩ ጥሩ ትዝታዎች አሉኝ። ዛሬ የሆንኩትን እንድሆን መሠረት የተጣለው በዚህ ት/ቤት ነበር። መምህራን በእኛ ላይ የክርስትና እሴቶችንና ጠንካራ የሥራ ባሕልን ለማስረጽ እጅግ ተግተው ይሠሩ ነበር። ተማሪው ሁሉ የሚመኛቸውን ከአንድ እስከ ሦስት ደረጃዎች ባልይዝም በክፍሌ ጥሩ ጥሩ ውጤቶችን አስመዘግብ ነበር” ትላለች። እንደ ናንሲ ድሪው ያሉ ተከታታይ የሚስጥር ዘውግ ያላቸውን ረጅም ልብ-ወለዶችን ማንበቧንም እንዲሁ ታስታውሳለች። “ብዙውን ጊዜ ዝምተኛና ሕልመኛ ነበርኩ” ትላለች ቤተልሔም። አጫጭር ልብ-ወለዶችን ትደርስ የነበር ሲሆን ወላጆቿም እንድትጽፍ ያበረታቷት ነበር።
ከዚያም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በናዝሬት ስኩል ተማረች። “ናዝሬት ስኩል ስገባ በራስ መተማመኔ እየቀነሰ ሄደ። የክፍል ጓደኞቼ ፈጣን የሚባሉ፣ ሁልጊዜም ቀልድ አዘል አስተያየቶችን የማያጡ ሲሆን እኔ ግን ምላሷ የሚተሳሰርባት የምባል ዓይነት ነበርኩ። ይህንን በራስ የመተማመን ችግር ለማምለጥ ብዙውን ጊዜዬን የፍቅር ዘውግ ያላቸውን ረጅም ልብ-ወለዶችን በማንበብ አሳልፍ ነበር፤ ለጥናቴ የምሰጠው ጊዜ ግን አነስተኛ ነበር።…. በዚህም ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ውጤት የምጠብቀውን ያህል አልነበረም” ትላለች።
ቤተልሔም የመጀመሪያ ዲፕሎማዋን ከኮሜርሻል ኮሌጅ በሴክሬታሪያል ሳይንስ አግኝታለች። ከልጅነቷ አንስቶ ማንበብና መፃፍ ትወድ ስለነበር የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝኛ ሥነ-ጽሑፍ አጠናች። ሁለተኛ ዲግሪዋን በእንግሊዝ አገር በሥነ-ፆታ፣ ባሕልና ማኅበረሰብ የትምህርት ዘርፍ በርክቤክ ዩንቨርሲቲ ኦቭ ሎንዶን አግኝታለች። በዚያው እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦቭ በርሚንግሃም ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪዋን በትራንስሌሽን ስተዲስ አግኝታለች።
በ1990 ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪዋን ለማጥናት ወደ እንግሊዝ አገር ሄደችና በዛው ከብሪታንያዊ ሰው ጋር ትዳር መሠረተች። “ያኔ ነው እንደነሱ ባሕል ስሜን ወደ ባለቤቴ ቤተሰብ መጠሪያ ስም አትፊልድ የቀየርኩት። ስለዚህ የአባቴ የባዩህ ስም የአባት ስም ሆኖ ሲቀጥል የባለቤቴን የቤተሰብ መጠሪያ ስም እንደ አያት ስም በመውሰድ ስሜ ቤተልሔም ባዩህ አትፊልድ ተብሎ ተጠራ” ትላለች ተርጓሚ ቤተልሔም አትፊልድ።
ባለቤቷ በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ተራድኦ የጋራ ብልጽግናና ልማት ድርጅት ውስጥ አማካሪ ሲሆን ለሥራው በየተለያየ አገር ስለሚመደብ በ26 ዓመት የትዳር ቆይታቸው ከእንግሊዝ አገር መደበኛ ኑሯችው ውጭ 7 የእስያ አገራትና በአፍሪካ ኖረዋል። ሦስት ሴት ልጆችም አፍርተዋል። በየ3-4 ዓመት ወደ ተለያዩ አገራት ተቀይረው ይሄዱ ስለነበር ከልጆቿ ጋር ጊዜ ለማሳለፍና የሚያስፈልጋቸውን ክብካቤ ለመስጠት እንዲሁም አዲስ ኑሮ በጀመሩበት አገር ቤተሰቦቿን ለማረጋጋት የሚያስችላትን የራሷን ሥራ ለመሥራት የፈጠራ ችሎታዋን በማዳበር ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን አትርፋለች።
ሴት ልጆቿም በአሁኑ ሰዓት ለአካለ መጠን ደርሰዋል። ሦስቱም በእንግሊዝ አገር ዩንቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተምረዋል። ታላቋ ሴት ልጇ በፓሪስ በሚገኝ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት እየሠራች ትገኛለች። መካከለኛዋ ደግሞ በአካባቢያዊ ጂኦ-ሳይንስስ የዶክትሬት ዲግሪዋን እየሠራች ትገኛለች። ሦስተኛዋ ልጇ ደግሞ ተልእኳቸውን የጨረሱ የኑክሌር ኃይል መሣሪያዎችን ከተልእኳቸው የማንሳት ሥራን በሚሠራ በእንግሊዝ አገር በሚገኝ ድርጅት ትሠራለች።
ብሩህ ተስፋ የተሞላ የሕይወት እይታ
የቤተልሄምን ቀና፤ ተስፋ የተሞላ አመለካከቷን ወዳጆቿና ቤተሰቦቿ ይወዱላታል። በበጎው ላይ ማተኮር፣ ከሰዎች ጋር ወይንም በአካባቢዋ ከሚያጋጥሟት ነገሮች ውስጥ በብዛት መልካም እይታቸው ላይ ማተኮርን ትመርጣለች። ቤተልሔምን የሚያውቋት ወዳጆቿና ቤተሰቦቿ ሰዎችን ለመርዳት ያላትን ፍላጎት፣ ፈጥኖ አዳዲስ ሃሳቦችን፣ ባሕሎችንና ሁኔታዎችን ለመልመድ ያላትን ችሎታና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመጀመር ሒደት የሚያጋጥመውን ፈተና የመጋፈጥ ችሎታዋን ያደንቃሉ። በተለያዩ አገራት ያፈራቻቸው ጓደኞቿ የኢትዮጵያን ባሕል ለሌሎች ለማሳወቅና እንዲያከብሩት ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ያደንቃሉ።
የወደፊት ራእይ
“የወደፊት ራእዬ፡- በአፍሪካ ሀገር በቀል ቋንቋዎች የተጻፉ ጽሑፎችንና የትርጉም ሥራዎችን ለማስፋፋት የማደርገውን ጥረቴን አጠናክሮ መቀጠል፤ በተተረጎሙ ሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ላይ አተኩሮ የሚሠራ የሕትመት ድርጅት መጀመር ነው” ትላለች ቤተልሔም።
ቤተልሔምን በሚከተሉት የኢ-ሜይል አድራሻና የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ማግኘት ይቻላል።
ኢ-ሜይል፡- ethiolitrarytranslators@gmail.com, ethioymc@gmail.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/EthioLiteraryTraslator
ሊንክድኢን፡- https://www.linkedin.com/in/bethelhem-attfield