ሌፍተናንት ጀነራል ጃገማ ኬሎ ሀውልታቸው ተመረቀ
ባለ 35 ደቂቃ ኦድዮ ሲዲም ታተመ፤
“ጃገማ” የአባታቸው የፈረስ ስም ሲሆን በኦሮምኛ ሀይለኛ ማለት ነው:: ዛሬ ሚያዝያ 7 በስላሴ መንበረ-ጸባኦት ቤተ-ክርስቲያን ሀውልታቸው ሲመረቅ የቅርብ ዘመዶቻቸውና ታላላቅ የሀገር ባለውለታዎች ታድመው ነበር፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም ፤ የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን እንዲሁም በርካታ ጀግኖች ታድመዋል፡፡ ከጠዋቱ 1ሰአት እስከ 4 ሰአት በተደረገው የ1ኛ ሙት አመት መታሰቢያ ላይ የጀነራል ጃገማ ኬሎ የቅርብ ሰው የነበሩት ጀነራል ዋሲሁን ንግግር ያደረጉ ሲሆን ጃገማ ገና ከልጅነታቸው አንስቶ የሀገር ፍቅር ያደረባቸው ሰው መሆናቸውን መስክረዋል፡፡
ጃገማ ኬሎ የኢጣሊያ ጦር የአድዋ ላይ ሽንፈቱን ሊወጣ ጦሩን እጅግ አግዝፎ ከ40 ዓመት ዝግጅት በኋላ በ1928 በድጋሚ ሀገራችንን ወርሮ ህዝብ ሲፈጅ ሀገሩን ሊታደግ ሁሉም በየፊናው ሲራወጥ በ15 ዓመት ዕድሜ የአባታቸውን ጀብድ ሊደግሙ በዱር ዘምተው ጠላትን አርበድብደዋል። በዚህም “የበጋ መብረቅ” ተብለው ተሰይመዋል።
ሌ/ጀ/ ጀገማ ፤ ከኢጣሊያ ጋር 5 ዓመት ሲዋጉ አንድም ቀን ድል ሆነው አያውቁም:: ጥይት ሲያልቅባቸው ብቻ ቦታውን ለቅቀው ይሄዳሉ::
ሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ከነበሩት ሌ/ጀኔራሎች ለረጅም አመታት በህይወት የኖሩ ብቸኛው ጀኔራል ሲሆኑ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆች፣ አምስት የልጅ ልጆችና አራት የልጅ ልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡
የታላቁ አርበኛ የሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎ የቀብር ስነ ስርዓት የዛሬ አመት እሁድ ሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም አርበኞችና ታዋቂ ሰዎች በሚቀበሩበት በቅድስተ ስላሴ ካቴድራል በክብር መፈጸሙ ይታወቃል፡፡ አባት አርበኞች፡ ቤተሰቦቻቸውና በርካታ ህዝብ የተገኘበት የቀብር ስነ ስርዓት ወጣት ኢትዮጵያዊያንና አባት አርበኞች በቀረርቶና ሽለላ በማጀብ ታላቁን አርበኛ ሽኝት አድርገውላቸዋል፡፡
የጀነራል ጃገማ ኬሎን ሀውልት የሰራው ቀራጺ ተፈሪ መኮንን ሲሆን ሀውልቱም 2ሜትር ርዝመት አለው፡፡ ይህ ሀውልት ቢከፈል ኖሮ 300ሺህ ብር ያወጣ የነበረ ሲሆን ቀራጺው ግን ለጀግናው ጃገማ ኬሎ ካለው አድናቆት የተነሳ ቅናሽ በማድረግ በ120ሺህ ብር ሊሰራው መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀራጺ ተፈሪ መኮንን የአርት ስኩል በ1988 በዲፕሎም ከተመረቀ በኋላ በ1999 የዛሬ 11 አመት መሆኑ ነው በከፍተኛ ማእረግ ከአርት ስኩል መመረቁን ይናገራል፡፡
አጠቃላይ በቀራጺነት ሙያ ላለፉት 22 አመታት የሰራው ተፈሪ ከዚህ ቀደም የታወቁ የሀገር ባለውለታዎችን ሀውልት ሊቀርጽ ችሏል፡፡ ከሰራቸው ስራዎችም መካከል የጅግጅጋን ትልቁን አደባባይ፣ ደብረዘይት የሚገኘውን የአባ ገዳ ሀውልት ፣ በወሊሶ የሚገኘውን የባልቻ አባነፍሶንና ደብረ-ዘይት ያለውን የመለስ ዜናዊን ሀውልት ሰርቷል፡፡ አዲስ አበባ ተወልዶ አዲስ አበባ ያደገው ተፈሪ መኮንን የጃገማ ኬሎን ሀውልት በጣም ቅናሽ በሆነ ዋጋ ሊሰራ የቻለው ሰውየው ትልቅ የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ግምት ውስጥ ስላስገባ ነው፡፡
ይህ የጃገማ ኬሎ ሀውልት እንዲሰራ ከፍተኛውን የገንዘብ ወጪ ያወጡትና የጄነራል ጃገማ ኬሎ የቅርብ ቤተሰብ የሆኑት አቶ ሀይሌ ገብሬ ናቸው፡፡ አቶ ሀይሌ ጀነራል ጃገማ በህይወት በነበሩበትም ወቅት ጠያቂያቸው ለክፉ ቀን ደራሻቸው ነበሩ፡፡ አሁንም የጃገማ ኬሎ አንደኛ አመት ሲታሰብም ትልቁን አስተዋጽኦ ለማድረግ መነሳሳታቸውን ይናገራሉ፡፤
ከዚህም በተጨማሪ በእለቱ ለታደሙ የቅርብ ሰዎች የጃገማን ታሪክ የያዘ ባለ 35 ደቂቃ በኦድዮ የቀረበ ሲዲ ተሰጥቶአል፡፡ ይህን ሲዲ ያሳተመው ግለ-ታሪኮችን በሲዲ በማሳተም የሚታወቀው እዝራ እጅጉ ነው፡፡ አሳታሚ ድርጅቱ ተወዳጅ የሚድያና የኮሚኒኬሽን ማእከል ከዚህ ቀደም የ8 የሀገር ባለውለታዎችን ታሪክ ማሳተሙ አይዘነጋም፡፡ ሌተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ(የበጋው መብረቅ) በሚል ርእስ የተዘጋጀው ኦድዮ ሲዲ የጃገማን የቅርብ ሰዎች በማነጋገር ብሎም የራሳቸውን የቆዩ ድምጾች በማካተት የተሰናዳ ነው፡፡