መኮንን ተሾመ ቶሌራ

መኮንን ተሾመ ቶሌራ

(የኢትዮዽያ የሳይንስ ጋዜጠኝነት ጠንሳሽ)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡

150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል መኮንን ተሾመ ነው፡፡ መኮንን የልጅነት ህልማቸውን ካሳኩ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ በይፋ የጥበቡን አለም ከተቀላቀለ 16 አመት የሞላው ሲሆን “በተለይ በሳይንስ ጋዜጠኝነት የራሱን አሻራ አኑሯል። እንዲህ አይነት ሰዎች ቢነበቡ ብዙ ገጽ አላቸው፡፡ በመሆኑም የመኮንን ተሾመ ታሪክ ለትውልዱ ይጠቅማል ብለን ሰንደነዋል፡፡ የህይወት ታሪኩን መነሻ ጽሁፍ ከባለታሪኩ ያገኘን ሲሆን የስነዳ ተግባሩን ደግሞ እዝራ እጅጉ አከናውኖታል፡፡

መኮንን ተሾመ ለበርካቶቹ የሀገራችን የህትመት ፣ የብሮድካስትና የበይነ-መረብ የሚዲያ አውታሮች ከአስራ አምስት አመት በላይ በማገልገል በተለይም በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመፃፍ ይታወቃል። በተጨማሪም የተዋጣለት የተግባቦት (Communication) እና የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ ፣ መምህርና ፀሀፊ ሲሆን ለተለያዩ አለማቀፍ ሚዲያዎች ሳይንስ ነክ ዘገባዎችንም ይፅፋል። መኮንን በሀገራችን “የሳይንስ ጋዜጠኝነት”ን በማስተዋወቅም ፈር ቀዳጅ ነዉ።

ትውልድና እድገት

የጋዜጠኛና የተግባቦት ባለሞያዉ መኮንን በ1966 ዓ.ም በመዲናችን በአዲስ አበባ ከተማ የጦር ሀይሎች ሆስፒታል ይቺን አለም ተቀላቀለ። እድሜዉ ስድስት አመት ሲሞላዉ ያለአባት የሚያሳድጉት እናቱ ችግር ስለገጠማቸዉ ብቸኛ ልጃቸዉን ያኔ ወሎ ክፍለሀገር የጁ ምድር በሚባለዉ አካባቢ ለሚኖሩት ለሴት አያቱና ለአክስቱ ለአንድ አመት እንዲቀመጥ ሰጥተውት ተመለሱ። ቀደም ሲል ተወልዶ ባደገበትና “ገዳም ሰፈር” በሚገኘዉ በገነተ-ልዑል ቅ/ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተክርስቲያን ጊቢ ዉስጥ በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት ፊደል እየቆጠረ የቆየ ሲሆን ሰባት አመት ሲሞላዉ መደበኛ ትምህርት እንደሚያስገቡት እናቱ ስለነገሩት እሱን በጉጉት እየጠበቀ እያለ ነበር ወሎ ክፍለሀገር የተወሰደዉ። ከአዲስ አበባ ለአንድ አመት ከሶስት ወር ያህል የራቀዉ መኮንን ወደማያዉቀዉ ገጠራማ ቦታ መወሰዱ እስካሁን ድረስ የማይረሳቸዉ የቋንቋ ዘዬዎችና ልዩ እይታዎችን ያስገኘለትና ስነ-ፅሁፍና ግጥምን ለመስራት የሚያግዘዉ መሆኑን ይናገራል።

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት

ወሎ ክፍለሀገር መሄዱ አዲስ አበባ ከሚገኙት የእድሜ እኩያዎቹ ትምህርት በመጀመር በአንድ አመት እንዲዘገይ በማድረጉ በእሱና በእናቱ ላይ ቁጭት ቢፈጥርም ወደ መዲናችን ተመልሶ ደጃች ዉቤ ሰፈር በሚገኘዉ “የትምህርት ብልጭታ ት/ቤት” ሲገባ ከነበረበት ክፍል ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በመጀመሪያዉ ሴሚስተር 1ኛ በመዉጣት በዛዉ አመት ሁለተኛ ክፍልን ሶስተኛ በመዉጣት የባከነዉን ጊዜ ለማካካስ ችሏል። በመቀጠልም እስከ ስድስተኛ ክፍል በዚሁ ትምህርት ቤት ትምህርቱን በጥሩ ዉጤት በመከታተልና በወቅቱ በስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በሚደረግ “የጥያቄና መልስ” ዉድድር ትምህርት ቤቱን ወክሎ ያሸለመ ሲሆን በስድስተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና 99 ነጥብ በማስመዝገብ ያኔ እዚያዉ ደጃች ዉቤ ሰፈር አፍንጮ በር አካባቢ በሚገኘዉ በኢትዮዽያ ትቅደም ት/ቤት የ7ኛ እና የ8ኛ ክፍል ትምህርቱን በመጀመሪያዉ አመት ከአጠቃላይ ከሴክሽን ቀጥሎም ከክፍሉ አንደኛ በመዉጣትና በስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናም 99 ነጥብ በማስመዝገብ ወደ መነን ት/ቤት (የያኔዉ የካቲት 12 ሁለተኛ ደረጃ /ት/ቤት) በመዛወር ትምህርቱን አጠናቋል።

ከፍተኛ ትምህርትና የስራ አለም

የከፍተኛ ትምህርቱን ለማጥናት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያቀናዉ መኮንን የመጀመሪያ ምርጫዉን ለምን “የዉጭ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ” እንዳደረገ ሲናገር “እንደ ገረመዉ ገብሬ (የ Spoken English መፃህፍት አዘጋጅ) ያሉ የመነን ት/ቤትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት አስተማሪዎቼ እንዲሁም በልጅነቴ “ቀለሜ” እያሉ በቅፅል ስም የሚጠሩኝ የሰፈር ሰዎች ተፅዕኖና የወሎ ክፍለሀገር የአንድ አመት ቆይታዬ የጫረብኝ የቋንቋ ዉበት ሳይሆን አይቀርም” ይላል። በመሆኑም በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ወቅት እንደዋና ትምህርት/ሜጀር/ “የዉጭ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ” በሁለተኛ ደረጃ /ማይነር/ “የኢትዮዽያ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ/አማርኛ/” ትምህርቶችን ተከታትሎ በማጠናቀቁ በእንግሊዝኛም በአማርኛም ቋንቋዎች ጥሩ ፀሀፊ እንዲሆን አስችሎታል።

መኮንን የመጀመሪያ ዲግሪዉን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም (Institute of Language Studies/ILS/) በዉጭ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪዉን ከስነ—ትምህርት ክፍል በእንግሊዝኛ ቋንቋ የማስተማር ዘዴ አግኝቷል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታዉ የወሰዳቸዉ የእንግሊዝኛና የአማርኛ ቋንቋ ፣ የፅሁፍ ጥበብ ፣ የጋዜጠኝነትና የህዝብ ግነኙነት ትምህርቶች አሁን ለደረሰበት ሞያዊ ስብዕና አግዞታል። ከመጀመሪያ ዲግሪ በኋላ በኢሚግሬሽንና በደህንነት ባለስልጣን ስራዉን የጀመረዉ መኮንን ጥቂት አመታት ካገለገለ በኋላ የመምህርነትን ሞያ ተቀላቀለ። በመምህርነት ሶስት አመታት ያህል ካገለገለ በኋላም በጣም የሚፈልገዉንና የሚወደዉን የጋዜጠኝነት ሞያ በቀድሞዉ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የ “ኢትዮዽያ” መፅሔት ሪፖርተር በመሆን አሀዱ አለ።

በመቀጠልም በኢትዮዽያ ፕሬስ ድርጅት የ ዘኢትዮፒያን ሔራልድ ጋዜጣ ከሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ አዘጋጅነት አገለገለ። በመቀጠልም በቀድሞዉ “የኢትዮዽያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት” በአሁኑ ኢቢሲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ከፍተኛ አዘጋጅነት ከዛም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በኦንላይን ይዘት (online content editor) አዘጋጅነትና ተርጓሚነት አገልግሏል። በመቀጠልም የቀድሞዉ መስሪያ ቤት የኢትዮዽያ ፕሬስ ድርጅት ባደረገለት የዳግም ቅጥር ግብዣ በድጋሚ በመፈተንና በብልጫ ፈተናዉን በማለፍ በማታ ሽፍት የዜና አዘጋጅነት በመቀጠልም በዜና ክፍሉ አስተባባሪነት በብቃት ያገለገለ ሲሆን በብቃቱና በመልካም ባህሪዉ በባልደረቦቹ ዘንድ በጣም ተወዳጅ ለመሆን የበቃ የዘርፉ ባለሞያ ለመሆን የበቃም ነዉ።

መኮንን በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በሚሰራበት ወቅት በማእከሉ የህዝብ ግንኙነት ፕሮሞሽን ክፍል ተከፍቶ በወቅቱ በነበሩት ሃላፊ “ወደዚህ ክፍል ብትዛወርና ከሌሎች ባልደረቦችህ ጋር ክፍሉን ብታጠናክሩት ምን ይመስልሃል” የሚል ጥያቄ ሲመጣለት “ሁኔታዉን እስቲ ትንሽ ላስብበት። እኔ እንኳን ለጊዜዉ ዜናን መስራቱ ነዉ የሚያስደስተኝ።” የሚል መልስ ሰጥቶ ለማንኛዉም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዉ የህዝብ ግንኙነት ኮርሶች የተማረበትን ደብተሮች መልሶ ማገላበጥ እንዲሁም ከገበያ ላይ የዘርፉን መፅሀፎች ፈልጎ በመግዛት ሰፊ ንባብ ማድረግ ቀጠለ። ይህም በመጨረሻ “የህዝብ ግንኙነት ሥራ ፡ ተግባራዊ መመሪያ “ የተሰኘ መፅሃፍ ለመፃፍ አስችሎታል።

በመቀጠልም መኮንን በሀገራችን በትልቅነቱ የመጀመሪያዉን ደረጃ ለሚይዘዉ ለሚድሮክ ኢትዮዽያ ከስምንት አመታት በላይ እንዲሁም ለጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ደግሞ ለጥቂት ጊዜአት በህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርነት ያገለገለ ቢሆንም ለአንድም ቀን ለሚዲያ ከመፃፍ ተቆጥቦ አያዉቅም። በዚህም በሀገራችን የሳይንሰ ጋዜጠኝነትንና የፍሪላንስ ፀሃፊነትን ያስተዋወቀ ጋዜጠኛ ከመሆኑም በላይ በርካታ ፅሁፎችን ለአለም አቀፍ ሚዲያዎች በመፃፍም ትልቅ ስራ የሰራ ባለሞያ ነዉ።

እዉቅናና ፌሎሽፖች

መኮንን በርካታ አለማቀፍ ፌሎሽፖችን ያገኘ ሲሆን በምርጥ የሳይንስ ጋዜጠኝነትና ዘገባም ተሸላሚ ጋዜጠኛ ነዉ። ካገኛቸዉም ፌሎሽፖች መካከል የቅርብ አመታቱን ስናይ የአለማቀፉ የሳይንስ ጋዜጠኝነት ፌዴሬሽን ጉባኤ ፌሎሽፕ (ሎዛን ከተማ እ∙አ∙አ∙ ጁላይ 2019 ዓ∙ም∙) https://www.wcsj2019.eu/travel-fellowships ፣ የደቡብ አፍሪካ የሳይንስ ጉባኤ ፌሎሽፕ (ጆሀንስበርግ እ∙አ∙አ∙ ዲሴምበር 2018 ዓ∙ም∙) https://www.dst.gov.za/index.php/media-room/latest-news/2725-pretoria-hosts-africa-s-premier-science-forum-as-world-enters-era-of-fourth-industrial-revolution፣ የህንድ ሳኒቴሽንና ንፅህና ንቅናቄ ፌሎሽፕ (ኒዉ ዴልሂ እ∙አ∙አ∙ ጃንዋሪ 2020 ዓ∙ም∙) https://www.cseindia.org/understanding-india-s-experiments-in-rural-sanitation-9799 ፣ እ∙አ∙አ∙ በኖቨምበር 2023ዓ ∙ም∙ በግብፅ ሻርማል ሼክ ከተማ የተካሄደዉን የ COP27 አለማቀፍ የአየር ለዉጥ ጉባኤ በቨርቿል ከአዲስ አበባ ለመዘገብ በ “ሜሻ ኬንያ” ያገኘዉ የገንዘብና የስልጠና ፌሎሽፕ https://meshascience.org/leading-african-science-journalists-network-to-support-fellows-for-cop28/ ጥቂቶቹ ናቸዉ። መኮንን ከነዚህ ትልልቅ ፌሎሽፖች ሌላ በጣም በርካታ የገንዘብና የስለጠና ድጋፎች ከመላዉ አለም በማግኘትና በአፍሪካ ፣ በኤዢያ እና በአዉሮፓ አህጉራት በመዘዋወርም የሳይንስ ዘገባዎችን ሰርቷል።

ሽልማቶችን በተመለከተም በሀገር ዉስጥ እ∙አ∙አ∙ በ 2020 እን 2022 ዓ∙ም∙ የኦፕን ፎረም ፎር አግሪካልቸራል ባዮቴከኖሎጂ (OFAB) የኦንላይን ዘርፍ የአንደኝነት ማዕረግ ተሸላሚ ከመሆኑም በላይ በህንድ ሀገር “ የአፍሪካ ሳኒቴሽንና ንፅህና ሻምፒዮን“ የተባለዉን ሽልማት አግኝቷል። ጋዜጠኛ መኮንን ኢትዮዽያ አቆጣጠር በታህሣስ 12 ፣ 2003 ዓ∙ም∙ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሳይነስ ጋዜጠኞች ማህበርን አንዲቋቋም ማድረገ ከመቻሉም በላይ ማህበሩን በፕሬዝደንትነት በመምራትም ለሀገሪቱ አዲስ ሀሳብ መመንጨይ የራሱን አሻራ ማሰቀመጥም ችሏል። በአሁኑ ጊዜም የማህበሩ ምክትል ፕሬዝደንትነት በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል።በአሁኑ ጊዜም ጋዜጠኛ መኮንን የሳይንስ ጋዜጠኝነት ሞያዉን ይበልጥ ከፍ በማድረግ ለተለያዩ አለም አቀፍና የሀገር ዉስጥ ሚዲያዎች እየፃፈ ከመሆኑመ በላይ በሳይንስ ጋዜጠኝነትን ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያ ለመሰል ኢትዮዽያዊ የሰራ ባልደረቦቹና ሳይንቲሰቶችም ስልጠና በመስጠትና የሳይንስ አደቮኬሲ በመሰራት የራሱን በጉ አሰተዋፅኦ በማበረከተ ላይ ይገኛል።

አሁን ላይ አፍሪካን ዲሚስቲፋየር

https://www.africandemystifier.com/ ለተባለዉና ሳይንስ ዘገባ ላይ ትኩረተ አደረጎ ለሚሰራዉ ድረ—ገፅ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ይሰራል። በተጨማሪም ከወዳጆቹ ጋር በመሆን አሊያንስ ፎር ሳይንስ — ኢትዮዽያ (Alliance For sciernce – Ethiopia) የተሰኘና በሳይንሰ ተግባቦትና ጋዜጠኝነት ዙሪያ ላይ አተኩሮ የሚሰራ ድርጅት ያቋቋሙ ሲሆን ይህንኑ ድርጅት መኮንን በዳይሬክተርነት እንዲያገለግል ተመርጧል።

በአሁኑ ጊዜም ፅሁፍ ከሚፅፍላቸዉ አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት መካከል የአሜሪካን ጂኦፊዚካል ዩኒየን፣ ከሰሃራ በታች ያለው የ SciDev.net ቅርንጫፍ፣ የኬንያዉ ሳይንስ አፍሪካ – ፣ የህንዱ ዳዉን ቶ ኧርዝ ፣ የደቡብ አፍሪካዉ አይ∙ፒ∙ኤስ (American Geophysical Union (Eos), the sub-Saharan branch of SciDev.net, ScienceAfrica – Kenya, Down To Earth, India, IPS, South Africa) ጥቂቶቹ ናቸዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *