መንሱር አብዱል ቀኒ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ፣ባለፉት 3 ዓመታት በሚድያው ዘርፍ የተሠማሩ ባለሙያዎችን የህይወት ታሪክ ሲያስነብብ እንደነበር ይታወቃል ።አንዳንዶቹን በመጽሐፍ ሌሎችን በድረ- ገጽ እያደረግን የግለ- ታሪክ ክፍተትን ለመሙላት የተቻለንን ጥረት አድርገናል ። የሽልማት ውድድሮች ሲዘጋጁም የዕጩዎችን ማንነት ስንነግር ቆይተናል።
ይህ ሥራችን ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ድርጅታችንም ቡድን አቋቁሞ እና ስርዐት ዘርግቶ የስነዳ ተግባሩን ሲያከናውን ቆይቷል። በሐምሌ 30 2014 ዓ.ም በጠንካራ ሽፋን የወጣው እና 600 ገፆችን የያዘው፣ ” መዝገበ- አእምሮ የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ የሚተርክ ነው። ይህ መጽሐፍ 11 የቦርድ አባላት ባሉት ቡድን የተሠናዳ ሲሆን ቅፅ 2 እየተዘጋጀ ይገኛል።
በቅጽ 2 የህይወት ታሪካቸው በመጽሐፍ ውስጥ ከሚካተትላቸው መካከል የእግር ኳስ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ይገኝበታል ። መንሱር ባለፈው ግንቦት በክብር ሽልማት የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ በሚለው ዘርፍ ማሸነፉ ይታወቃል ። ዘንድሮ ደግሞ የሚድያ አዋርድ ላይ ምርጥ 5 ውስጥ ገብቶ ድምጽ እየተሰጠው ይገኛል። የህይወት ታሪኩን አይናለም ሀድራ እና ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው አጠናክረውታል።
“እግር ኳስ ቅሪላ ከመግፋት በላይ መሆኑን በደንብ ያሳየ ነው፡፡ ከፍ ሲልም በእኔ እምነት ለረጅም ጊዜ ለኢትዮጲያ የስፖርት ጋዜጠኝነት standard/መለኪያ ሆኖ የቆየ ነው፡፡”
ዮናስ አዘዘ ( ስፖርት ጋዜጠኛ)
“መንሱር በምንም አይታማም፡፡ ሁሌም ዘገባዎቹ ሚዛናዊ እንዲሆኑ ይጥራል፡፡ ሁሉ የሚያከብረው የመርህ ሰው ነው፡፡”
ዮናስ ሃጎስ( የአራዳ ኤፍ ኤም መስራች)
Football is not just a game. እግር ኳስ ከጨዋታም በላይ ነው፤
የአስተዳደር ጉዳይ ነው፤ የፊዚዎሎጂ ሳይንስ ጉዳይ ነው፤….. ስፖርት ብዙ ነገር ነው፡፡ በእግር ኳስ ዙሪያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች
አሉና it not just a game.
መንሱርአብዱል ቀኒ
አዎ ለመንሱር እግር ኳስ ቅሪላ ከመግፋት በላይ ነው፡፡ ግራ፣ ቀኝ፣ ኋላና ፊት ያለው ትስስረ ብዙ፡፡ እሱ እግር ኳስን በቅጡ ያውቀዋል፤ ቋንቋውን ይናገራል፤ አመሉን ይረዳል፣ አወጣጥ አገባቡም አይቸግረውምና ስለ ኳስ ቢያወራ ያምርበታል፡፡
ስለኳስ መናገር ሲጀምር ነገረ ሥራው በአንድ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሌክቸር የሚሰጥ እንጂ እንዲያው ዝም ብሎ የኳስ ወሬ የሚያወራም አይመስልም፡፡ እግር ኳስን የሆነ ደረጃ ላይ አድርሶት ጉዳይ ማድረግ ተክኖበታል፡፡ ቢሰሙት ቢሰሙት የማይሰለች፤ የሚለው የማይነጥፍበት የኳስ ወዳጅ ደግሞም አስወዳጅ መንሱር አብዱል ቀኒ፡፡
ለአድማጭ ተመልካቹ ከፍ ያለ፣ ከሚታየው የዘለለና የተሰወረውን እውቀት ለመግለጽ የማይሄድበት ርቀት የለም፡፡ ያነባል፣ ይጠይቃል፤ይመለከታል…. መዘርጋት የቻለበት ርቀት ድረስ ሄዶ ሁሉን ያደርጋል፡፡
ሲፈልግ እግር ኳስን ከጦርነት ጋር ያጣምረዋል፤ ከሚሊታሪ ሳይንስ ጋር ያዛምደዋል፡፡ ከበድ ያለውን የእግር ኳስ ጥበብ የውትድርና ጽንሰ- ሃሳቦች ውስጥ ከቶ ፍትትት አድርጎ ያቀርበዋል፡፡
እንደውም ኋላ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ለንባብ የበቃው “The art of war” የሚሊታሪ ስልት መጽሃፍ የመንሱር መጽሃፍ በመባል ይታወቃል፡፡ እሱ ድሮ…ድሮ አንብቦታል፡፡ የስፖርቱን መከላከል፤ ማጥቃት፣ ጸረ ማጥቃት የሚሉትንና የመሳሰሉትን ሃሳቦች እንደ አንድ መኮንን ከሚሊታሪ ሣይንስ ጋር አገናኝቶ ሲተነትን አፍ ያስከፍታል፡፡
መንሱር አብዱል ቀኒ፣ እግር ኳስን ሲጽፍም ሲናገርም ያምርበታል፡፡ለዚህ ነው አጋሩ የስፖርት ጋዜጠኛ ዮናስ አዘዘ እንደ እኔ መንሱር ለኢትዮጲያ የስፖርት ጋዜጠኝነት standard/መለኪያ ነው ሲል ያሞካሸው፡፡
አንጀት አርሱ የእግር ኳስ ተንታኝ (ተንታኝ መባሉን እርሱ እምብዛም ባይወደውም ሥራው ግን ያስብለዋል) መንሱር አብዱል ቀኒ ዛሬን ያየው መውጣት ግድ ያለውን ተራራ ወጥቶ ቁልቁለቱንም ወርዶ እንጂ እንደው እንደቀልድ አይደለም ፡፡
የቀደሙትን ዓመታት እስራኤላውያን ከነአን ከመግባታቸው በፊት ካለፉበት የ40 አመት የሲና በረሃ ጉዞ ጋር፤ ዛሬ የደረሰበትን ስኬት ደግሞ ከወረሷት መልካሚቱ ምድር ከከንአን ጋር ልናመሳስለው እንችላለን ።
ገና ታዳጊ እያለ የጀመረው የውጭ ጉዞ እስኪጠናቀቅ ለጊዜው በሚል ቻምፒዮን ጋዜጣ ላይ መጠነኛ ክፍያ እየተከፈለው ሥራ ጀመረ፡፡ ቀዳሚ ሥራውም የአራሚነት የሥራ መደብ ነበር።
የመጀመሪያ ስምሪቱን በጥሩ ሁኔታ መወጣት በመቻሉ ሥራው ቀጠለ፡፡ አንድ ሁለት እያለም ብቃቱን አስመሰከረ፡፡
በመሃል ታላቅ ወንድሙ ሁሴን አብዱል ቀኒና ጋዜጠኛ ወንደወሰን ኢንተር ስፖርትን ሲጀምሩ ከእነርሱ ጋር ተቀላቀለ፡፡ በኢንተር ስፖርት ቆይታው እንደ ጀማሪ ሪፖርተር ሆኖ ዘገባዎችን አጠር አጠር ያሉ ቃለ- መጠይቆችን ሰርቷል፡፡
በሥራ ሂደቱ ከዘገባው ባሻገር ለሌይ አውትና ዲዛይን ልዩ ፍቅር ስላደረበት የተለያዩ ሶፍትዌሮችንና ጠቃሚ ግብአቶችን በማሰባሰብ በጥልቀት ስለ ስራው አጥንቶ ሌይ አውትና ዲዛይን መስራትም ጀመረ፡፡ መንሱር የያዘውን ነገር በልህቀት ማከናወንን ስለሚመርጥ የሌይ አውትና ዲዛይን ሥራውንም ከውጭ ተሞክሮዎችንም በመውሰድ በሚገባ መሥራት የጀመረው ያኔ በኢንተር ስፖርት እያለ ነው፡፡ በዚህም የተዋጣለት ባለሙያ መሆን ችሏል፡፡
ኢንተር ስፖርት በ15 ቀን አንዴ የሚወጣ ጋዜጣ ነበር፤ የመንሱር የሥራው ፍቅርና ትጋት ግን 15 ቀን ጠብቆ የሚያሠራ ብቻ አልነበረም፡፡
በ1993 ዓ.ም በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትነት የምትታተመዋን ዕለታዊ አዲስ ጋዜጣን የሩህ አዘጋጆች ደረጄ ደስታና ሰለሞን አባተ ሲመሩት መንሱር ስፖርቱንና ሌይ አውት ዲዛይኑን እንዲይዝላቸው ባቀረቡለት ግብዣ ተስማምቶ ሥራ ጀመረ፡፡
በሳምንት ሰባት ቀናት ቀን ከሌት ሠራ፡፡ አብዛኛውን የሳምንቱን ቀናት ከለሊት 7 ሰዓት በፊት እቤቱ ገብቶ አያውቅም፡፡ በመሰጠት፣ በፍቅርና በትጋት ሠራ፡፡
ከጊዜ በኋላ በወቅቱ ተከስቶ በነበረ ውዝግብ እለታዊ አዲስ ተቋረጠ፡፡ይሄኔ መንሱር ሌት ተቀን መባከኑ ቀርቶ ለ3 ወራት ጥሩ የእረፍትና የጥሞና ጊዜ መውሰድ ቻለ፡፡
ኢትዮ ስፖርት
በዚህ ጊዜ ነው ኢትዮ ስፖርት የተወለደው፡፡ የሮሃ ባንድ ጊታሪስት የነበረው ጆቫኒ ሪኮ ኮምፓስ ኮምፒውተርስ አሶሼትስ የሚል ከጋዜጣ ህትመት ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰራ ቢሮ ነበረው፡፡ እርሱና የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አለማየሁ የመንሱርን አቅም ያውቁ ነበርና መንሱር የራሱን ጋዜጣ እንዲያሳትም ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ሃሳቡን ቢወደውም ለሥራው የሚያስፈልጉ በቂ ቁሳቁሶች የሉኝም ነበር ምላሹ፡፡
እነ ጆቫኒ፣ አስፈላጊውን ኮምፒውተሮች ከድርጅቱ እንዲጠቀም አድርገው ቢሯቸውንም አጋርተውት መንሱር ዮናስ ሃጎስ፣ አቢይ ተ/ማሪምና ኢብራሂም ሻፊን ይዞ በ1994 ዓ.ም ኢትዮ ስፖርትን አቋቋመ፡፡
ስራን እንደነገሩ የመከወን ልማድ ያልፈጠረበት መንሱር አብዱል ቀኒ ለጋዜጣው ስኬት ህይወቱን ሰጥቷል ወዳጆቹ እንደሚሉት፡፡ ቀንም ሌሊትም ለእርሱ አንድ ነው፤ ሥራ እስካለ እንቅልፍ የለም፡፡ የስራ አጋሩና ወዳጁ ዮናስ ሃጎስ እንደሚለው መንሱር አስገራሚ የስራ ትጋት ነበረው፡፡ ጥርት ያለ እንጂ ውሽልሽል ስራ አይወድም፤ የያዘውን ከግብ ሳያደርስም አይለቅም፡፡ ጊዜውን ፣ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና የሚያስፈልገውን ሁሉ ሰውቶ ጽድት ያለ ነገር መስራት የሚፈልግ ሰው ነው፡፡
በኢትዮ ስፖርት ጊዜ ፈር ቀዳጅ ልምምድም ነበረው፡፡ የሃገር ውስጥ ጨዋታዎች ሲኖሩ አንድ ተጫዋች ስንት ኳስ ያዘ፣ ስንት ክሮሶች ተደረጉና የመሣሰሉትን ዳታዎች በማንዋል በሰው ሃይል በመያዝ ግራፎች ተሰርተው ትንታኔ ይሰጥ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ የተሰራውን ዘገባ አሰልጣኞችና ክለቦችም ይጠቀሙበት ነበር፡፡
ከመደበኛ የውጤት ዘገባዎች የዘለሉ ጥልቅ ትንታኔዎች ሽፋን ይሰጣቸዋል፡፡ ስፖርት ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር ተሳስሮ ይዳሰስበታል፡፡ ተራ የሚመስል መረጃ ከብዙ አቅጣጫ ይተነተናል፤ ያልታዩ አንግሎች አቅጣጫዎች ከስር መሰረታቸው ይመዘዙበታል በኢትዮ ስፖርት፡፡
ሥራው ብዙ ልፋት ብዙ መውጣት መውረድ ጠይቋል፡፡ የነካውን ሁሉ በልህቀት የመከወን ፍላጎቱ ለሙያው ያለውን እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡ የጋዜጣ ህትመቱ ዘገባውን መስራት ፣ ኤዲት ማድረግ፣ ሌይ አውትና ዲዛይን መስራት፣ ኮፒ ኤዲቲንግና ሌሎች የህትመት ሂደቶችን ማለፍ የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ነበር፡፡ አስፈላጊ ወጪዎችን ለመሸፈንና የሰራተኞችን ደሞዝ ለመክፈልም ብርቱ የማርኬቲንግ ሥራን ጠይቋል፡፡
ታዲያ መንሱርና የአጋሮቹ ሁሉን በብቃት ተወጥተውታል፤ ልፋታቸውም መና ሆኖ አልቀረም ፡፡
ኢትዮ ስፖርት የስፖርት አፍቃሪው ሱስ ሆነች፡፡ የስፖርት ጋዜጠኛው ዮናስ አዘዘ እንደሚያስታውሰው በዘመኑ በእለተ ቅዳሜ አዲስ አድማስን ያልያዘ እንደ አላዋቂ ይቆጠር እንደነበረው ማክሰኞ ደግሞ ኢትዮ ስፖርትን ይዞ ያልታየ የስፖርት ቤተሰብ የስፖርት ፍቅሩ ጥያቄ ውስጥ ይገባ ነበር፡፡ ጋዜጣው እጅግ ተጽዕኖ ፈጠረ፡፡ ይዘቱና የጋዜጣው የተለየ ቅርጽ ተወዳጅና እጅግ ተጠባቂ እንዲሆንም አደረገው፡፡
በተለምዶው ሃያ ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቢሮ ተከራይተው ስራውን በስፋት ቀጠሉ፡፡
ኢትዮ ስፖርት እየታተመ ጎን ለጎን ፍሰሃ ተገኝ፣ አቢይ ተ/ማሪያምና ሚሊዮን አለሙ በ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ እሁድ ጠዋት ላይ የሚተላለፍ “ቶክ ፉትቦል “የሚል ፕሮግራም ጀምረው ነበርና መንሱር የዛ ፕሮግራም ቋሚ ተንታኝ ሆኖ ይሰራ ነበር፡፡ ቶክ ፉትቦል ዛሬ ላሉት በርካታ የስፖርት ፕሮግራሞች መነሻ እንደሆነም ይነገራል፡፡ በወቅቱ ፕሮግራሙ ከብዙ አድናቆት ጋር መነጋገሪያ መሆን ችሎም ነበር፡፡ መንሱርም በዚህ ሁሉ ተሳትፎው እውቀቱ እየጨመረ እራሱን እያሳደገ መጣ፡፡
የኢትዮ ስፖርትም ተፅዕኖ ጨመረ ስኬቱም እንደዛው፡፡ በዚህ መልኩ ኢትዮ ስፖርት ለ12 ዓመታት ዘለቀች፡፡ በስተመጨረሻ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ እየጨመረ ሲመጣ ማንም ሰው መረጃን በትኩሱ በእጁ የሚያገኝበት አማራጭ ሲሰፋና በአንጻራዊነት የጋዜጣ ስራ ፌዝ አውት ሲደርግ መንሱር አብዱል ቀኒም ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውን ተቀላቀለ፡፡ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በብስራት ኤፍ ኤም ብስራት ስፖርትን ጀመረ፡፡ ብስራት ስፖርት እነሆ ዘንድሮ 9 አመትን አስቆጥሯል፡፡
የመንሱር እይታ
የጂሲኤው( አብዮት ቅርስ) መንሱር ፈረንሳይኛን አቀላጥፎ ይናገራል፡፡ በዚህም ብዙዎች መንሱር የሊሴ ገብረማሪያም ተማሪ ነበር ሲሉ ቢደመጡም የመንሱር ታላቅ ወንድም ሁሴን አብዱል ቀኒና ሌሎቹ እህቶቹ እንጂ መንሱር የሊሴ ተማሪ አልነበረም፡፡
ትምህርቱን የተከታተለው የመንግስት ትምህርት ቤት በሆነው ጂሲኤ (አብዮት ቅርስ) ነው፡፡ ከየመናዊው አባቱ… አብዱል ቀኒ….እና ከኢትዮጲያዊቷ እናቱ ወ/ሮ ብርቄ ደበሌ ነው የተወለደው፡፡ ታላላቆቹ ሊሴ በመማራቸውና አባቱ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በመሆናቸው ቋንቋው ለቤተሰቡ እጅጉን ቅርብ ነው፡፡ እንደውም አንዷ ታላቅ እህቱ ፈረንሳዊ ነው ያገባችው፡፡ የመንሱር አባት ከፈረንሳይኛ በተጨማሪ አረቢኛም አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡
በዚህ መልኩ ለቋንቋው የቀረበው መንሱር ፈረንሳይኛ ቋንቋን ማወቁ ለስራውም ጠቅሞታል፡፡
መንሱር ከ25 አመት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት አገልግሏል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ስፖርት ጨወታ ብቻ አለመሆኑን ያምናል ያንንም በሥራዎቹ አሳይቷል፡፡ ለዚህም ነው “Football is not just a game. እግር ኳስ ከጨዋታም በላይ ነው፤ የአስተዳደር ጉዳይ ነው፤የፊዚዎሎጂ ሳይንስ ጉዳይ ነው፤….. ስፖርት ብዙ ነገር ነው፡፡ በእግር ኳስ ዙሪያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች አሉና it’s not just a game.” ሲል የሚደመጠው፡፡
ይህንን መሰረት በማድረግም የስፖርት ጋዜጠኞች ከውጤት ገለጻ አለፍ ያለውን ይህንን ሁሉ ሃሳብ ሊመለከቱ ሊተነትኑ እንደሚገባ ያምናል፡፡ ይህንን ለማሳካትም የመንሱር መጽሃፍ የሚባለውን “The art of war” የተሰኘውን መጽሃፍ ጨምሮ የተለያዩ መጻህፍትን የማንበብ ልምድ አለው፡፡
እግር ኳስ እንኳን ጨዋታው ሜዳውም ሳይንስ አለው እናም መስኩ ብዙ እንድታነብ ይገፋሃል ይላል መንሱር፡፡
ስለ እግር ኳስ አስተዳደር ሲያወራ የማኔጅመንት እውቀትን ይጠቀማል፣ ስለ ስፖርት ሳይኮሎጂ ሲያወራ የሥነልቦና እውቀትን ይዋሳል፡፡ እርሱ ስለሁሉ የሚያጣቅሰው የንባብ መሰረት አያጣም፡፡ የውትድርና ጥበብን መሰረት ካደረገው በተደጋጋሚ ሲጠቅሰው ከሚሰማው “The art of war” መጽሃፍ ሃሳቦችን ወስዶ የስፖርት ሳይንስን ያብራራል፡፡
እንዲህ በማድረግ ዮናስ አዘዘ እንዳለው በተለይ እግር ኳስ ቅሪላ ከመግፋት ያለፈ ጥልቅ ነገር እንዳለው ያሳያል፡፡
መንሱርና የሃገር ውስጥ ስፖርት
መንሱር የውጭ እግር ኳስ ላይ ብቻ ያተኩራል ለሃገር ውስጥ ስፖርት እምብዛም ትኩረት አይሰጥም የሚሉ እንዳሉ ይሰማል፡፡ መንሱርስ ምን ይላል?
እርግጥ ነው ከዝንባሌው አንጻርና የንግድ ሚዲያ አካል እንደመሆኑ አብዛኛውን የማህበረሰብ ፍላጎት ማሟላት ላይ ቢያተኩርም ለሃገር ውስጥ ስፖርት ምንም አላበረከትኩም ብሎ አያምንም ፡፡ የሃገር ውስጥ ስፖርት አድጎ የውጭውን ያህል ቀን ከሌት የሚወራለት ነገር ባይኖረውም መንሱር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መሥራቱን ይናገራል፡፡
በተለያዩ የመረጃ ሰአቶቹ ለስፖርቱ እድገት የሚረዱ የፖሊሲ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሃሳቦችን ያነሳል ይጠቁማል፡፡ የየእለት መረጃዎችን ከመስጠት ይልቅም በተለይ እግር ኳሱን ሊጠቅሙ የሚችሉ ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ሃሳቦች ላይ ያተኩራል ክፍተቶችን ይጠቁማል፡፡ በዘርፉ ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ ከመተቸት ይልቅ ከመከሰታቸው በፊት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ አትኩሮ ይሰራል፡፡
እርሱ ያለፈበት የ25 ዓመታት የሥራ ጉዞና ልምድ እንዲህ ላሉ መሠረታዊና ወሳኝ ጉዳዮች ሊውሉ እንደሚገባ ያምናል፤ያንን ስለማድረጉም ይናገራል መንሱር አብዱል ቀኒ፡፡
ከዚህ ሃሳብ ጋር በተያያዘ”፣ በኢትዮ ስፖርት ባልደረባው የነበረው ዮናስ ሃጎስ የራሱ ምልከታ አለው፡፡ የዝንባሌን የምርጫን ጉዳይ ማክበር እንደሚገባ ያምናል ዮናስ፡፡ መንሱር በመረጠው በወደደው መንገድ ሄዷልና ያ ሊከበርለት ይገባል ባይ ነው፡፡
ከዛ ባለፈ ግን መንሱር የአለማቀፍ ኳስ እውቀቱንና ግንኙነቶቹን ተጠቅሞ በክለቦች አወቃቀር፣ በውድድሮች አካሄድ፣ በጤና ዙሪያና በመሰል ጉዳዮች ላይ ሃሳቦችን ሰቷል ከሚመለከታቸውም ጋር በተለያዩ ጊዜያት መክሯል፤ ለውጥም አምጥቷል ነው የሚለው፡፡
ዮናስ አዘዘ በበኩሉ መንሱር በኢትዮጲያ ስፖርት ወሳኝ ጊዜያት ሁሉ መገኘቱን ያነሳል፡፡
ወደ ኋላ ብንሄድ የኢትዮ ስፖርት ርዕሰ አንቀጽ የሃገር ውስጥ ስፖርት ላይ ያተኩር ነበር፡፡ ክፍተቶች ይጠቆሙበታል፤ በዘርፉ ሊመጡ ያሉ አደጋዎች ይመላከቱበታል፡፡
በተጨማሪ፣ የተለያዩ ውዝግቦች ሲነሱም ነገሩን በማጥራት መፍትሄ ለማበጀት ባለሙያዎችን በመጋበዝ ይመክራል፤እሱም ጥናቶችን በማድረግ ሃሳብ ይሰጣል፡፡
መንሱር ፣በየቀኑ የሃገር ውስጥ ስፖርትን አያንሳው እንጂ እርሱ የሠራቸው የመከረባቸው አጋጣሚዎች መሠረታዊ አቅጣጫ አመላካች ናቸው ይላል ዮናስ አዘዘ፡፡ መንሱር የቁርጥ ቀን ልጅ ነው critical ጉዳዮች ሲከሰቱ መንሱር አለ ባይ ነው፡፡ ፖሊሲን ለማስለወጥ፣ የአሰራር መንገድን ለማስቀየር፣ አሻሚ ጉዳይም ሲኖር ግልጽነት ለመፍጠር ሰርቷልም ይላል፡፡
ዮናስ ሃጎስ ስለ መንሱር፡-
በ1994 ኢትዮ ስፖርት ሲጀመር ነው በቅርብ የተዋወቁት፡፡ ሲፈላለጉ የነበሩ ሁለት ሰዎች የተገናገኙ ያህል ነው የሆነላቸው፡፡ ሁለቱም ብዙ ነገሮች ላይ ተመሳሳይ ምልከታ ስለነበራቸው ሳይነጋገሩ ይግባባሉ፤ ሳያወሩ ይናበባሉ፡፡ በዚህም በጋራ ለስኬት በቅተዋል፡፡
ዮናስ የመንሱርን ትጋትና አለመሰልቸት ያደንቃል፡፡ ህይወቱን ሙሉ ለእግር ኳስ መስጠቱ ያስገርመዋል፡፡ ልፋት ጥረት በሚጠይቀው በጋዜጣ ህትመት ጊዜም ለፍቷል ደክሟል፡፡ ዛሬም ከብዙ ዓመታት በኋላም ፍቅሩ ሳይቀንስ ስለ ስፖርት ጥንቅቅ ያለ መረጃ ያቀርባል ሳይሰለች ይሰራል፡፡
ዘገባዎቹ ላይ ሚዛናዊ ለመሆን ይሞክራል፡፡በምንም አይታማም ራሱን ያስከበረ ነው፡፡ የመርህ ሰው ስለሆነ የማንንም ፊት አይቶ የማያዳላ ነው፡፡ ሁሉም አክባሪው ነው ይላል ዮናስ፡፡
ቀድሞም የተለየ ነገር ለመፍጠር ይፈልግ ነበርና አስፈላጊውን እርቀት ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮ ስፖርት ዘመን ለዘገባዎቹ የሚመጥን ጥሩ ፎቶ እንዲኖር በሚል ፕሮፌሽናል ካሜራ አስመጥቶ ፎቶ እያነሳ ይጠቀም ነበር፡፡
የንባብ ፍቅሩም የትየለሌ ነው የውትድርና ነገሮችን ያነባል፣ አስትሮኖሚ ያነባል፣ ልቦለዶች ሌላም ሌላም፡፡ ዛሬ የደረሰበት ላይ ለመድረስ የታላቅ ወንድሙ ተጽዕኖና የግል ጥረቱ እጅጉን እንደጠቀሙት ይናገራል፡፡
ከራሱ አልፎ ሌሎች ጋዜጠኞች ላይም በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል ብሎ ያምናል፡፡
ዮናስ አዘዘ ስለ መንሱር፡-
እግር ኳስ ቅሪላ ከመግፋት በላይ መሆኑን ከጋዜጣ ጀምሮ እስከ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ያሳየ ነው፡፡ ብዙዎች ወደ ሙያው እንዲሳቡ አድርጓል፡፡ ባለሙዎች እሱ ወዳስቀመጠው standard ለመምጣት እንዲሰሩ አስችሏል፡፡
ዮናስ አዘዘ መንሱር ለኢትዮጲያ የስፖርት ጋዜጠኝነት መለኪያ ሆኖ የቆየ ምስጉን ባለሙያ እንደሆነ ይናገራል፡፡
ከዲሲፒሊን ጀምሮ ፕሮፌሽናሊዝምን በመተግበር እስከሚችለው ጥግ ድረስ ሄዶ ሙያውን አስከብሯል፡፡ ሁላችንም እንደ አርዓያ የምናየው ነው ይላል፡፡
በህትመት ሚዲያ ለረጅም ዓመት ተፈትኖ ማለፍ ችሏል፤አሁን ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ሌላ ውጤታማ ጊዜ እያሳለፈ ነው፡፡
እንዲህ በእግር ኳስ ትንታኔ ልህቀቱ የሚነገርለት መንሱር አብዱል ቀኒ በሃገር ውስጥ የበጎ ሰው ሽልማትና የክብር ሽልማትን አግኝቷል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ ደግሞ በባሎን ዶር ምርጫ ተሳታፊ የመሆንን እድል አግኝቷል፡፡
ይህ ጽሁፍ በየጊዜው ማሻሻያ የሚደረግበት ፣ ባለ ታሪኩን በማስፈቀድ የተሰናዳ ነው። የተወዳጅ ሚድያን የባለታሪኮች መስፈርቶችንም ያሟላ ነው።