ጌታቸው ዻውሎስ
ጌታቸው ዻውሎስ የመጀመርያው የነጻ ፕሬስ ጋዜጣ አሳታሚ -ዕይታ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሚድያ ስራ ሚና የነበራቸው፣ የማይረሳ አሻራ ያኖሩ ግለሰቦችን እና የሚድያ ተቋማትን ታሪክ እየሰራ ለትውልድ ያቆያል፡፡ ‹‹ዕይታ›› ጋዜጣ በሀገራችን ነጻ ፕሬስ በታወጀ ማግስት የታተመች ጋዜጣ ስትሆን አሳታሚዋም በአሁኑ ሰአት የ80 አመት ሰው የሆኑት አቶ ጌታቸው ዻውሎስ ብርሀኔ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ለመጀመርያ ጊዜ ከእኛ ጋር ተጨዋውተዋል፡፡ እዝራ እጅጉ የቀድሞ የዕይታ ጋዜጣ እትሞችን በመቃኘት ዕይታ እና ጌታቸውን በሚከተለው መልኩ ሊያሳየን ያስባል፡፡
የልቤ ትርታ
የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ፣ የ7ኛ ክፍል ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ 8ኛ ክፍል ስዛወር በ1985አ.ም መሆኑ ነው በወቅቱ በብዛት ይታተሙ የነበሩ ጋዜጣ እና መጽሄቶችን አፈላልጎ ገዝቶ ማንበብ ልማዴ ነበር፡፡ ይህ እቅዴ እንዲሳካ ደግሞ ከጋዜጣ አዟሪዎችና ከጋዜጣ ገዥዎች ጋር የግድ መወዳጀት ነበረብኝ፡፡ ይህን ማድረጌም ጠቀመኝ፡፡ ነገ ጋዜጠኛ መሆኔ ስለማይቀር ማንበቤ የግድ መሆኑን በጠዋቱ ተገንዝቤ ነበር፡፡ እናም ህትመቶችን ማሳደዴ ተጠናከረ፡፡ አንድ ቀን በ1985 ይመስለኛል፡፡ ‹‹ዕይታ›› የምትል ጋዜጣ ከእጄ ገባች፡፡ ቀልቤን ሳበችው፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወሎ ሰፈርን ትንሽ እልፍ እንዳልኩ ‹‹ዕይታ የዝግጅት ክፍል›› የሚል ሰሌዳ አይቼ የልቤ ትርታ ጨመረ፡፡ ልሂድ አልሂድ -ልተዋወቅ አልተዋወቅ እያልኩ ሳመነታ ሳልገባ ቀረሁ፡፡ ዕይታ ላይ የወጡ ጽሁፎችን ግን ሳላመነታ አጣጣምኩ-የ14 አመት ልጅ፡፡ዕይታ ውስጤ እንደኖረች 21 አመታት ነጎዱ፡፡
መነጽር ቤት-ዕይታ መጣች
ይህ ከሆነ ከ21 አመት በኋላ የ14 አመት የጋዜጠኝነት ልምድ አካብቼ ፤ የራሴን ተወዳጅ ሚድያ የተሰኘ ኩባንያ አቋቁሜ በ2006 የአይን መነጽር ለማሰራት ደምበል ወደ ሚገኘው መነጽር ቤት አቀናለሁ፡፡
‹‹ ደህና ነህ? ›› አሉኝ አንድ በእድሜ 70ዎቹ መጀመርያን የተቃረቡ አባት፡፡ ተግባቢ ናቸው፡፡ ደህና ነኝ ብዬ ጨዋታቸው ተመችቶኝ እናወራ ጀመር፡፡ ጋዜጣ እንደነበራቸው፡፡ ስማቸው ጌታቸው ዻውሎስ እንደሚባል ከ21 አመት በፊት በኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ ታሪክ የመጀመርያዋን ነጻ ጋዜጣ ያሳትሙ እንደነበር አጫወቱኝ፡፡ አሁን ትኩረቴ ተሳበ፡፡ ታሪክ እና የቆየ ያልተነገረ ነገር ርካታ እና ትርጉም ስለሚሰጠኝ የበለጠ ተሳብኩ፡፡ ‹‹ዕይታ.›› ጋዜጣ የሚለውን ቃል ገና ሲጠሩ ከመቅጽበት በትዝታ ወደ 14 አመት እድሜዬ ተመለስኩ፡፡ በሃሳቤ ያን ወርቃሜ ዘመኔን አስታወስኩ፡፡ ከአንድ አንባቢያቸው ጋር እያወሩ መሆኑን ስነግራቸው ፊታቸው ሲፈካ ታየ፡፡ ጋሽ ጌታቸው የዛን ቀን ከ30 ደቂቃ በላይ ስለ ስነ-ጽሁፍ ጥቂት ከተጨዋወትን በኋላ ስልክ ተለዋውጠን ተለያየን፡፡ ጋሽ ጌታቸው ስለ ራሳቸው መናገር አይወዱም፡፡ እናም ቃለ-መጠይቅ ላደርግላቸው ስሞክር እየጠፉብኝ 8 አመታት አለፉ፡፡
የዕይታ 30ኛ አመት
በኢትዮጵያ በ1984 የመንግስት ለውጥ ተደርጎ ነጻ ፕሬስ ሲታወጅ ለህትመት የበቃችው የጋሽ ጌታቸው ዕይታ ነበረች፡፡ ይህ ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ በጊዜው ጋዜጣዋ ምን አይነት ይዘት እንደነበራት በጊዜው አንባቢያን ትዝ የሚላቸው ይመስለኛል፡፡ለእኔ ይህች ጋዜጣ እና አሳታሚዋ ልዩ ትርጉም ሰጥተውኛል፡፡ ስለሆነም ዕይታና ጋሽ ጌታቸውን ለማስተሳሰር ይህን የዛሬውን ቀን መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ የሚድያ እና የሚድያ ሰዎችን ታሪክ እንደሚሰራ ታሪክ ሰናጅ በ14 አመቴ የጀመርኩትን የዕይታ ጋዜጣ አንባቢነቴን ለመቀጠል ወደ ወመዘክር ቤተ-መጽሀፍት አቀናሁ፡፡ ጋሽ ጌታቸውን በአንድ በኩል በስልክ እያወራሁ በሌላ ደግሞ ዕይታን እያነበብኩ በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጣ መታተም የጀመረበትን 30ኛ አመት አከበርኩ፡፡ በድሮ ጋዜጦች ታጅቤ፣ በወመዝክር ባለሙያዎች ተከብቤ ሰኔ 2 2014 ከዕይታ ጋር ዳግም የአንባቢነትን ውሌን ፈረምኩ፡፡ ትናንት ታዳጊ ሁኜ የንባብ ጥሜን ያረካውን ጋዜጣ ዛሬ ደግሞ የህይወት ታሪኩን ለመጻፍ ዕይታዬን አሰፋሁ፡፡
የዕይታ አሳታሚ አቶ ጌታቸው ዻውሎስ ዘንድሮ የ80 አመት እድሜያቸውን ይደፍናሉ፡፡ ዻውሎስ አሳታሚን ሲከፍቱ የ50 አመት ጎልማሳ ነበሩ፡፡ በ1984 የመንግስት ለውጥ ተደርጎ ‹‹ሰዎች የፈለጉትን ይናገሩ፤ ሳንሱር ተነስቷል›› ሲባል አቶ ጌታቸውም እኔም ልተንፍስ ብለው መተንፈሻ አዘጋጁ፡፡ ከበፊት ጀምሮ ለመጽሀፍ ለስነ-ጽሁፍ ታላቅ ፍቅር የነበራቸው እኒህ ሰው ዕይታ ጋዜጣን አንድ ብለው ሲጀምሩ የህትመት ጋዜጠኝነትን ለማጠናከር ትልቅ ራእይ ሰንቀው ነበር፡፡ መልእክት ከዕይታ በሚለው የአሳታሚው ማስታወሻ ጌታቸው ዻውሎስ ይህን ብለው ነበር
‹‹….. ይህች ጋዜጣ ለቻርተሩ፤ ለፕሬስና ለማህበራዊ ህጎች እንዲሁም ደንቦች ተገዥ ትሆናለች፡፡
ስርጭቱን በተመለከተ በመላው ኢትዮጵያ ለማዳረስ ዝግጅት አድርገናል፡፡ አንባቢ ሆይ የፕሬስ ነጻነት ለሚለው ሀሳብ እኛም እርስዎም አዲሶች አይደለንም፡፡ይህም ነጻነት ሀገራዊ ባህሪይና መልክ ይዞ እንዲገኝ የሁላችንም መብትና ግዴታ ነው፡፡የዛሬው ትውልድ ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ እይታ የእርስዎም የእኛም ናትና በጋራ የዚህ አይነት ነጻነት ልምድ በሀገራችን ውስጥ ለማዳበር እንድንችል እግዚአብሄር አቅጣጫውን ያመላክተን፡፡ ›› ብለው ርእሰ-አንቀጽ ጽፈው ነበር፡፡ ጌታቸው ዻውሎስ ብርሀኔ ባለቤትና አሳታሚ
ዕይታን በ60ሳንቲም
ግንቦት 10 1984 አ.ም በ10,000 ቅጂ የታተመችው ‹‹ዕይታ›› በጥቂት ቀናት ውስጥ 6,000ብር አስገባች፡፡ የአንዷ ዋጋ 60 ሳንቲም ነበር፡፡ ኢህአዴግ፣ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ በአንድ አመቱ የህትመት ብርሀን ያየችው ‹‹ዕይታ›› ገና የሰኔ 14ቱ ቻርተር ከመጽደቁ በፊት በሽግግር መንግስቱ ጊዜ የሀሳብ ነጻነትን ለማንሸራሸር የተቻላትን ሞክራለች፡፡ በጋዜጣዋ የፊት ለፊት ገጽ ዳንዴው ሰርቤሎ የፕሬስ ነጻነት በሚል ርእስ በሳል መጣጥፍ አቅርበው ነበር፡፡ 12 ገጽ የነበራት እይታ 14 አምዶችን ይዛ ነበር፡፡ የጋዜጣዋን ይዘት ስናየው በመጠኑ ደርበብ ያለች፤ መንግስትን በሰፊው ከመተቸት ይልቅ ለስለስ ያሉ ጉዳዮች በጥሩ አቀራረብ በማውጣት አንባቢን ለማርካት ትጥር ነበር፡፡ የዕይታ ጋዜጣ ተጠባባቂ አዘጋጅ የነበሩት አቶ ዳኜ ገሰሰ ሲሆኑ ጋዜጣዋ በየሳምንቱ ትወጣ ነበር፡፡
ይህች ታሪካዊ ጋዜጣ በመጀመርያ እትሟ፣ ‹‹የፕሬስ ሰው›› በሚለው አምዷ ከአቶ ነጋሽ ገብረማርያም ጋር ቆይታ አድርጋ ነበር፡፡ ጋሽ ነጋሸ በጊዜው በጣም የተከበሩ ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘመናዊነት ፈር የቀደዱ የተባለላቸው ነበሩ፡፡ በተጨማሪም፣ የመጀመርያዋ ሴት ልቦለድ ደራሲ ፀሀይ መላኩ ‹‹ብእሲቷ›› በሚለው አምድ ላይ እንግዳ ሆና ልምዷን አካፍላለች፡፡
‹‹ዕይታ›› ሰኞ ጥቅምት 1 1986 አ.ም በፊት ለፊት ገጽ ላይ ባወጣችው ዜና ትኩረት ለመሳብ ሞክራ ነበር፡፡ ርእሱ እንዲህ የሚል ነበር ‹‹…. የክልል 14ቱ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ገና ዛሬ ተናገሩ›› ቃለ-ምልልስ ከእይታ ብለው ያወጡ ነበር እነ ጋሽ ዻውሎስ በዚያን ጊዜ ፡፡ የሁሉም ዜና እና ጽሁፍ ርእስ አወጣጣቸው ሳቢ ነበር፡፡ ምናልባትም ዕይታን በቀላሉ ተናፋቂ ያደረጋት ይህ መስህቧ ሊሆን ይችላል፡፡ በ1960ዎቹ ግድም እነ ጋሽ ዻውሎስ ኞኞ እነ ከበደ አኒሳ ሲያዘጋጇት የነበረችው ድምጽ ጋዜጣ እንዲህ ሳቢ እና ተወዳጅ ነበረች፡፡
ጋሽ ጌታቸው ወደ ኋላ መለስ ብለው ጥሩ ጥሩ አምደኞች እንደነበሯቸው ያስታውሳሉ፡፡ ደምሴ ዳምጤ ፣ ዳንዴው ሰርቤሎ ፤የመሳሰሉ ሰዎች ዕይታ ውበትን ተላብሳ እንድትወጣ ጥረት አድርገዋል፡፡ ራሳቸው ጋሽ ጌታቸውም ህልማቸውን እውን ለማድረግ ከጋዜጣዋ ርእስ ጭምር ሳቢና ገላጭ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ‹‹ ዕይታ የሚለውን ስያሜ የሰጠኋት ራሴ ነኝ፡፡ ስያሜው ለአንድ ነገር ያለንን ምልከታ የሚነግር ሲሆን ስሙም ቀለል ያለና ብዙ ሀሳቦችን አምቆ የያዘ ነው ›› ሲሉ አቶ ጌታቸው 30 አመት ወደ ኋላ ተጉዘው አጫውተውኛል፡፡
የፖላንዱ ጌታቸው
በ1934 በባሌ ጎባ ተወልደው ገና በልጅነት አዲስ አበባ የመጡት አቶ ጌታቸው ተፈሪ መኮንን ገቡ፡፡ ከዚያም በትምህርታቸው ብሩህ የሆኑ ልጆች ወደ ዊንጌት ይላኩ በነበረበት ጊዜ ጌታቸው የዊንጌትን ደጃፍ ረገጡ፡፡ ከዚያም በጊዜው እንደሚደረገው ነጻ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ፖላንድ ዋርሶ ያቀናሉ፡፡ እዚያም ፖለቲካል ኢኮኖሚ አጥንተው ወደ እናት ሀገራቸው ይመለሳሉ፡፡ አቶ ጌታቸው የመጻፍ እና ጥልቅ ንባብ የማካሄድ ልምድ ያካበቱት ፖላንድ ሳሉ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያን ስተዲ ውስጥም ይሳተፉ ስለነበር ይህም ትልቅ አቅም ሆኗቸው ነበር፡፡ ፖላንድ ለጥናትና ምርምር የሚመች አጋጣሚ አግኝተው እዚያም የንባብ ልምዳቸውን አዳበሩት፡፡ ወደ ሀገር ቤት እንደመጡ በ1955 ግድም በእርሻ ሚኒስቴር ውስጥ ተቀጠሩ፡፡ በጊዜው የእርሻ ሚኒስቴር ውስጥ ከእነ አቶ አበበ ረታ ጋር የሰሩት አቶ ጌታቸው በየጊዜው ከማንበብ አልተቆጠቡም ነበር፡፡ የ1966ቱ ለውጥ እስኪመጣ ድረስ በእርሻ ሚኒስቴርና በእርዳታ ማስተባበርያ የሰሩት አቶ ጌታቸው ደርግ ሲመጣ ለተወሰኑ አመታት አሰራቸው፡፡ ከዚያም ከእስር ከወጡ በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ተቀላቀሉ፡፡
ጋሽ ጌታቸው እንደሚናገሩት ዕይታን ለመጀመር አይን የከፈተላቸው ‹‹አልሃራም›› የተሰኘው ጋዜጣ ነበር፡፡ ይህ ጋዜጣ በዚህ መልኩ መስራት ከጀመረ እኛም የራሳችንን ምርጥ ጋዜጣ መጀመር አለብን ብለው አቶ ጌታቸው ግብ ሰነቁ፡፡ በጊዜው የቅርብ ወዳጆቻቸው የነበሩት እነ አቶ ተፈሪ ወሰን ፤ ታቦቱ ወልደሚካኤል እና የመሳሰሉት ዕይታ ላይ የማማከር አሻራቸውን ለማሳረፍ ችለው ነበር፡፡
ማሳረጊያ
አቶ ጌታቸው 28 አመት ወደ ኋላ ተመልሰው ስለ ጋዜጣቸው ሲያስረዱ በተቻለ መጠን መንግስትን ከመሳደብ በወጉ መተቸት ላይ ያተኩሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ቢሆንም ግን ጋዜጣዋ በመንግስት ሰዎች የጥቁር መዝገብ ላይ መስፈሯ አልቀረም፡፡ ጋዜጣዋ ለበርካታ ጋዜጣ አዟሪዎች የስራ እድልና ገቢ ከመፍጠሯ ባሻገር ለስለስ ያለ አቀራረብን ትከተል ነበር፡፡ ከገቢ አንጻር አቶ ጌታቸው እንዳልተጠቀሙ ነግረውኛል፡፡ ይሁንና ፈተና ቀስ እያለ መጣ ሲሉ ተስፋ የቆረጡበትን ዘመን አስታውሰው ያጫውቱናል‹‹…. ፍርድ ቤት መቆም ጀመርን፡፡ ስለ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በጻፍነው ጽሁፍ ምክንያት ወያኔዎች ጠመዱን፡፡ ከዚያ በኋላ መስራት አዳጋች እየሆነብን ሄደ፡፡ እነርሱ ደግሞ ስለ መረጃ ነጻነት የሚያውቁት አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ በረባም ባልረባም ምክንያት እንከሰስ ነበር፡፡ይህም 2 አመት ከ100 እትም በላይ የሄደችውን ጋዜጣ እንድናቆም አስገደደን ›› ሲሉ ትዝታቸውን አወጉን፡፡
53 አመታቸውን ካከበሩ በኋላ የፖለቲካል ኢኮኖሚው ምሁር ጌታቸው ብዕር ከወረቀት አዋህደው መጻፋቸውን ቀጠሉ፡፡ ዶክተር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ ከ7 አመት በፊት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግጭት መንስኤ እና መፍትሄ የሚለውን መጽሀፍ ሲያሳትሙ አብረው በመጽሀፉ ላይ ትልቁን ድርሻ የተወጡት አቶ ጌታቸው ነበሩ፡፡ አቶ ጌታቸው ዻውሎስ የ3ልጆች አባት ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰአት ሙሉ ጊዜያቸውን ድርሰትን እየጻፉ ለአንባቢ በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ይህም ትልቅ ርካታን ይሰጣቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት ሮፓክ ኢንተርናሽናል በገዙት ቤት እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ መልካሙን ሁሉ ለጋሽ ጌታቸው ፡፡