ደጃዝማች አምሀ አበራ ካሳ / 1920 እስከ 1996 /

ደጃዝማች አምሀ አበራ ካሳ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በልዩ ልዩ ዘርፍ ሀገራቸውን ያገለገሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በማህበራዊ ድረ ገጽ ሲያወጣ ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ለእናት ሀገራቸው ታላቅ ፍቅር የነበራቸው እና በትጋት ያገለገሉ ነበሩ፡፡ የእነዚህን ታላላቅ ሰዎች ታሪክ በተምሳሌትነት ማቅረብ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ተምሳሌት ከሆኑት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ከ 20 አመት በፊት ህይወታቸው ያለፈው ደጃዝማች አምሀ አበራ ካሳ ናቸው፡፡ ደጃዝማች አምሀ በ1940ዎቹ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከተማሩ ቀደምት እና ጥቂት ኢትዮጵያውያን አንዱም ናቸው፡፡ የራስ ካሳ የልጅ ልጅ የሆኑት ደጃዝማች አምሃ አበራ ካሳ የአርበኛ ወይዘሪት ሆይ ከበደች ስዮምና የደጃዝማች አበራ ካሳ ልጅም ናቸው፡፡ በአገራችን ለውጥ እንዲመጣ ሁሌ የሚተጉት ደጃዝማች አምሀ አበራ በንጉሱ ዘመን የምርጫ ቦርድ እንዲጀመር መሰረት የጣሉና በልማት እና በሰው ልጅ እድገት ላይ ትልቅ ስራ የሰሩም ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ያለውን ገነት ኢየሱስ የአረጋውያን ማእከልን በመምራት በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ የበኩላቸውን የተወጡ ናቸው፡፡

ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ እና ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ስለ ደጃዝማች አምሀ አበራ ካሳ የሚሉት ይኖራል፡፡

ታሪክን ወደኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ ከጀግኖች ህይወት የሚመዘዙ ታላላቅ የተጋድሎ መስመሮችና ድሎች በቅብብል በትውልድ ውስጥ ጎልተው ይታያሉና የታሪኩን ጅማሮ ከጀግናዋ አርበኛ ከበደች ስዩም ማድረጉ ምርጫ የማይቀመጥለት ጉዳይ ሆኗል።

ልኡል ራስ ስዩም መንገሻና ወይዘሮ ጀንበር በርሄ የጀግናዋ አርበኛ ከበደች ስዩም ወላጆች ናቸው። አርበኛ ከበደች ስዩም ጥቅምት 17 ቀን 1904 ዓ.ም ነበር በመቐሌ ከተማ የተወለዱት።በተወለዱበት አካባቢ ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ጊዜው በሚፈቅደው መሰረት ቤተሰቦቻቸው ገና በለጋ እድሜያቸው ለልኡል ራስ ካሳ ሀይሉ ልጅ ለደጃዝማች አበራ ካሣ ዳሯቸው።

ታዲያ ከዓድዋ ጦርነት 40 ዓመታት በኋላ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረ ስትነሳ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ በእነ አርበኛ ከበደች ስዩም ቤተሰቦችም ዘንድ የጭንቅ ጊዜ መሆኑ አልቀረም። ማይጨው ላይ በተደረገው ጦርነት ምንም እንኳን ፋሺስት በከባድ መሳሪያ ቢወጋንም የልኡል ራስ ካሳና የልኡል ራስ ስዩም ጦር በከባድ ውጊያ ለመከላከል ታግሏል፡፡ ግርማዊነታቸው ወደ አለም መንግስታት አቤቱታ ለማቅረብ ወስነው ሲሄዱ የደጃዝማች አበራ ጦር ወደ ሰላሌ ሄዶ በተገቢው መልኩ ለመደራጀት ሞክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ጣሊያን የተከለከለ የመርዝ ቦምብ በመጠቀም አሰቃቂ እልቂት ኢትዮጵያውያን ላይ ሲያደርስ ሶስቱ የልኡል ራስ ካሳ ልጆች ላይ ትልቅ ክትትል ለማድረግ ሲወሰን ደጃዝማች አበራ ካሳ እና ደጃዝማች አስፋወሰን ካሳ ህዝቡን ላለማስጨረስ እጃቸውን ለመስጠት ወሰኑ፡፡ ይህ አይነቱ ውሳኔ ላይ የደረሱትም በቂ የሆነ ጣሊያንን ለመፋለም የሚያስችል ከባድ መሳሪያ ስለሌላቸውና ጣሊያንም እነርሱን እስከሚይዝ ድረስ ጭፍጨፋውን እንደማያቆም በመረዳታቸው ነው፡፡ ጣሊያን ግን ልክ እጃቸውን እንደሰጡ ፍቼ ከተማ ላይ ነው የረሸናቸው፡፡ 3ኛውን ወንድማቸውን ደጃዝማች ወንድወሰን ካሳን ደግሞ ላስታ ላይ ነበር የገደላቸው፡፡

በዚህ ወቅት አርበኛ ከበደች ስዩም የመጀመሪያ ልጃቸውን ደጃዝማች አምሀን በ8 አመቱ ይዘው ለመዝመት ወሰኑ፡፡ 2ኛ ልጃቸው ፊታውራሪ አምዴ አበራ የ3 አመት ልጅ ሳለ ጣሊያን ከተቀመጠበት ቦታ አግኝቶ እስረኛ አድርጎ ጣሊያን ሀገር ወሰደው፡፡

ከ3 አመት ውጊያ በኋላም ከሌሎች ስመጥሩ የኢትዮጵያ ጀግኖች ከእነራስ መስፍን ስለሺ እና ጄነራል አቢይ አበበ እንዲሁም ከራስ አበበ አረጋይ ጦር ጋር በመቀላቀል ትንሽ ጊዜ በበረሀ ከቆዩ በኋላ በረሀ ላይ ለተወለደው ልጃቸው ህጻኑ ልጅ ታሪኩ አበራ እና ለደጃዝማች አምሀም እየከበደ ስለመጣ ወደ ሱዳን ድንበር ተንከባክበው ሸኝተዋቸዋል፡፡

የዛሬ ባለታሪካችን ክቡር ደጅአዝማች አምሀ አበራ ሐምሌ 29/1920 ዓ.ም በጊዜው አጠራር ሸዋ ክፍለሀገር ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ነበር የተወለዱት። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም መምህር ተቀጥሮላቸው የሀገራችንን ባህላዊ ትምህርት እንዳጠናቀቁ አዲስ አበባ በሚገኘው የስዊድን ሚስዮን ገብተው ዘመናዊ ትምህርት መከታተል ቢጀምሩም በጣሊያን ወረራ ምክንያት ለማቋረጥ ተገድደዋል።

ገና በልጅነት እድሜያቸው ከአርበኛ ከበደች ስዩም ጋር በጦርነቱ ውስጥ እያለፉ ያደጉ ነበሩና ፋሽስቱ የጣሊያን መንግስት ታሕሳስ 12/1929 ዓ.ም አባታቸው ደጃዝማች አበራ ካሳና አጎታቸው በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ መደረጉ በፈጠረው ቁጭት የተነሳ ታላቋ አርበኛ እናታቸው ክብርት ከበደች ስዩም ሕፃኑን ደጃዝማች አምኃ ትጥቅ አስታጥቀው እራሳቸውም ታጥቀው “የአባትህንና የአገርህን ደም ተበቀል።” ብለው እናትና ልጅ መርሃ ቤቴ:- ግንደበረትና ጎጃም በከፍተኛ ጀግንነት ከጠላት ጋር ተዋግተዋል።ክቡር ደጃዝማች አምኃ የአርበኝነቱንና የሀገር አለኝታ አርአያነቱን በተግባር ያስመሰከሩት ገና በለጋ ዕድሜአቸው ነበር። በዚህ ክፉ የፈተና ወቅት የእናታቸው ወገን የሆነው የአገው ምድር ሕዝብ በሥንቅና ትጥቅ ከለላ ከመሆኑ በላይ ትጥቁን ይዞ አብሯቸው በመሰለፍ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል።በኋላም እስከ ሱዳን ድንበር ድረስ ተንከባክቦ ሸኝቷቸዋል።

የኋላ ኋላ ቤተሰቡ ለስደት ሲዳረግም በመጀመሪያ ሱዳን ቀጥሎም ወደ ግብፅ ተሰደዋል። ቤተሰቡ በልዑል ራስ ካሳ አማካኝነት ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በዛው በኢየሩሳሌም መማር ጀመሩ። በኢየሩሳሌም የስደት ዘመናቸው ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪ የመንፈሳዊ ትምህርት እውቀታቸውን በሚገባ አዳብረዋል። የኢትዮጵያ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው ኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ትምህርት ቤት በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቃቸው ከንጉሰ-ነገስቱ ሽልማት ተቀብለዋል።

1938 ላይ ሁለተኛው የአለም ጦርነት ማለቁን ተከትሎ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሀገር ተልከው መጀመሪያ ሞልቨርን ኮሌጅ ተቀላቀሉ፤ ቀጥሎም ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ብሬዝንኖዝ ኮሌጅ በፍልስፍና በፖለቲካና በኢኮኖሚክስ በከፍተኛ ክብር ደረጃ (Honours) ተመርቀው የማስተር ኦፍ አርትስ ዲግሪ ተቀብለዋል።በማከታተልም በማህበራዊ አስተዳደር እና በስነ-መንግስት ትምህርት በተመሳሳይ ከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል።

ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው በመመለስ በ1944 ዓ.ም የሀገር ግዛት ሚንስቴር አማካሪና በደጃዝማችነት ማዕረግ የሰላሌ አውራጃ ገዢ ሆነው ተሾሙ። የሰላሌ አውራጃ ገዢ በነበሩበት ጊዜ የህዝቡን ችግር ለማቃለል ትምህርት ቤት እና የጤና ጥበቃ አገልግሎት እንዲስፋፋ ፣የመንገድ አውታር እንዲዘረጋ፣ህዝቡ በልማት ስራ እንዲተባበር በማድረግ ከፍተኛ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። በ1948 ዓ.ም የፓርላማ ምርጫቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲሰሩ የኢትዮጵያ ህዝብ መብት እና ግዴታውን ለይቶ በማወቅ የምክርቤት እንደራሴውን መንግስት ከሚመርጥለት ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱ የሚወክለውን መምረጥ እንዲችል

በጠቅላይ ግዛቱና በየአውራጃው እየተዘዋወሩ በሬድዮና በጋዜጣ ሕዝቡን በማነቃቃት ረገድ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

ታሪካቸው እንደሚነግረን 1950 ዓ.ም በዩጎዝላቪያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙበት ጊዜ ሲሆን ከ1953 መፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ የቤጌምድር ሰሜን እንደራሴ ሆነው አገልግለዋል። በጌምድር ለ2 አመት ሰርተው በቃኝ ብለው ለመውጣት ተገድደው ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሀገሩ ለም ሆኖ ሳለ ልማት እንዳይስፋፋበት ግን የተመደበለት በጀቱ አነስተኛ በመሆኑ ለአገር ግዛት ሚኒስቴር የበጀቱን አነስተኛ መሆን እና የሚያስፈልገውን የበጀት መጠን ሲያቀርቡ በወቅቱ ሊረዷቸው ባለመቻላቸው ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡

ደጅአዝማች በአገልግሎት ዘመናቸው ሁሉ የህዝቡ ኑሮ እንዲሻሻል ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር።በ1957 ዓ.ም በምዕራብ ጀርመን አምባሳደር ሆነው ሲሾሙ በተጨማሪነትም ፅህፈት ቤቱ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ለሆነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንጉሰ ነገስቱ ባለሙሉ ስልጣን መልዕክተኛና አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። ከ1963 እስከ 1966 ድረስ በዘውድ ምክርቤት አባልነት ሰርተዋል።

በ1955 የተጀመረውን የልዑል ራስ ካሳ ልጆች የበጎ አድራጎት ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነውም አገለግለዋል፡፡ ይህንኑ ከአያታቸው የተረከቡትን የበጎ አድራጎተ ኃላፊነት ከተወለጆቹ ጋር በመሆን በእንጦጦ ገነተ ኢየሱስ አካባቢና በተለያዩ አውራጃዎች ትምህርት ቤት በመክፈት አቢያተ ክርስቲያናት በማሳነጽ በማሳደስ ለአረጋውያን የሚሆን መጦሪያ ቦታ በማዘጋጀትና አንድ ድንገተኛ የጤና ክሊኒክ በገነተ ኢየሱስ በማቋቋም በርካታ የህዝብ አገልግሎቶችን ሰጥተዋል፡፡

የደርግ መንግስት የወንድማቸውን የክቡር ፊታውራሪ አምዴ አበራን፣ የአጎታቸውን ልዑል ራስ አስራተ ካሳን ፣ የአክስታቸውን ልጅ ክቡር ልጅ ሀይሉ ደስታን እና ሌሎች በርካታ ዘመዶቻቸውን እንዲሁም የስራ ጓደኞቻቸውን ህዳር 14/1967 በግፍ ሲገድል እርሳቸውን ለአብዮቱ እንቅፋት ይሆናሉ በሚል ለስምንት አመታት በማሰር እንግልትና ስቃይ አድርሶባቸዋል።

ደጅአዝማች ያለጥፋታቸው ለእስር በተዳረጉበት ዘመን ለእስረኞች ትምህርት በመስጠት ከፍተኛ አድናቆትና ከበሬታን አግኝተዋል። እስረኞቹም” ኢንሳይክሎፒዲያችን ናቸው ” ብለው ነበር የሚገልጿቸው። “

ደጅአዝማች ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላም በሰሜን አሜሪካ በኖሩበት ጊዜ ሁሉ ስለ አገራችን ሰላምና አንድነት ስለ ታሪካችንና ስለ ባህላችን መጠበቅና መከበር ያለመታከት ሰርተዋል።

ልጃቸው ወይዘሮ ዮዲት አምሀ ስለ ወላጅ አባቷ ምስክርነት ስትሰጥ ‹‹…. አባቴ አስተዋይ ቁጥብ አርቆ አሳቢ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ዝምታው ከኩራት ቢቆጠርበትም በጣም አዛኝና ሩህሩህ ሰው ነው፡፡ ወዳጆቹ ስለ እርሱ ሲገልጹ ያስቀመጡት ቦታ የሚገኝ ሰው ነው ብለው ቁምነገረኛነቱን ይገልጹታል›› ብላለች፡፡

ዮዲት አያይዛም ” ከፖለቲካ ውጪ ወንበር ላይ ያሉ ባለስልጣኖችን አግኝተው ለሀገር ልማት እንዴት እንስራ የሚለው ላይ ነበር ትኩረትና መሻቱ ፡፡ አባቴ ቁጥብና ዝምታ የሚመርጥ የያዘውን ሥራ ግን አጥብቆ ግብ እስኪደርስ በትጋት የሚቀጥል ነው ብላለች፡፡

ደጃዝማች ምንም እንኳን እንግሊዝ ሀገር ቢኖሩ ከመሰረታቸው በሀይማኖታቸው እና በባህላቸው ስርአት በወግና ማእረግ ያደጉ ናቸው፡፡

ከሀገራቸው በስርዓትና በወግ ታንፀው ያደጉ ስለነበሩ ከሀገረ እንግሊዝ ህዝብ ጋር ለመኖር አንዳች አልተቸገሩም ነበር። ለንባብ ደግሞ ያላቸው ፍቅር እጅግ የተለየ ነው፡፡

በኦክስፎርድ ተማሪ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረትን መመስረት ብቻ ሳይሆን የህብረቱም የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡

ደጅአዝማች ከስልጣኔ አንፃር እነ ጃፓንን፣ ሆላንድ፣ እንግሊዝ ፣ፈረንሳይንና የመሳሰሉትን ያድንቁ እንጂ ሀገራቸው ጥንታዊ ስልጣኔ እንዳላት ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ የውጭው አለም ስልጣኔ ወደ ሀገራችን እንዲገባ የሁልጊዜ ምኞታቸው ስለነበር ለግርማዊነታቸው በተለያዩ አገራት በአምባሳደርነት ሲሰሩ በነበረበት ወቅት የተለየ ጉብኝት እንዲያደርጉም ሁኔታዎችን አመቻችተውላቸዋል፡፡ በግድብ ሥራም ላይ የተለያዩ ባለሙያዎችን በማነጋገር ወደ ሀገራችን መጥተው እንዲሰሩ አድርገዋል፡፡

በደርግ ጊዜ ምንም እንኳን በ40ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ ቢሆኑም በርካታ ችግርና ሀዘኖችን አሳልፈዋል፡፡ነገር ግን በሀይማኖታቸው በጣም ጠንካራ ስለነበሩ ብዙም መንፈሳቸው ሳይጎዳ ከ 8 አመታት እስር በኋላ ተፈተዋል፡፡

በ1974 ከተፈቱ በኋላ ለህክምና አሜሪካ ሄደው ለ17 አመታት በኒዮርክ ከተማ ኖረዋል፡፡

ደጃዝማች ብዙውን ጊዜያቸውን በማንበብ እና በስፖርት ነበር የሚያሳልፉት፡፡ በዚህም ምክንያት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በሚገኘው የግል ቤተ መጽሀፍት ውስጥ ከ3000 በላይ መጻህፍት ነበሯቸው፡፡ እነዚህንም ልዩ ልዩ መጽሀፍት ልጃቸው ወይዘሮ ዮዲት አምሀ ለህዝብ መገልገያ እንዲሆን ለወመዘክር ቤተ መጽሀፍት በእርሳቸው ስም አበርክታለች፡፡ እነዚህም መጽሀፍት የህግ፣ የፍልስፍና፣ መንፈሳዊ መጻህፍት ነበሩ፡፡ ፒያኖ ፈረስ ግልቢያ ቴኒስ ዋናና ጎልፍ ለመዝናናት የሚጠቀሙባቸው እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡

ክቡር ደጅአዝማች አምሀ አበራ ለሀገራቸው ለወገናቸውና ለባህላቸው ከፍተኛ ፍቅርና ጥልቅ ዕውቀት የነበራቸው እንደነበሩ ብዙዎች ይገልፃሉ። የቤተክህነት ሥርዓትና ደንብ ጠንቅቀው የሚያውቁ ስለነበሩም በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አሳቢና ተቆርቋሪም ነበሩ። በሀገራቸው ውስጥም ሆነ ከሚወዷት ሀገራቸው ተለይተው በስደት በኖሩበት የውጪ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ስለሚስፋፋበትና ቤተክርስቲያን ስለምትጎለብትበት ያለማቋረጥ የሰሩና ፈጣሪያቸውውን ከልብ ያገለገሉ የእምነታቸው ተገዢ ጿሚ ፀሎተኛ ትሁት ለጋስ ቅን አሳቢ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር ነበሩ ታሪካቸው እንደሚነግረን። ኢትዮጵያ ዘመናዊና የበለፀገች እንድትሆን ከፍተኛ ጉጉት ከነበራቸውና የራሳቸውን ድርሻ በሚችሉት ሁሉ ከተወጡ ሀገራችን ካፈራቻቸው አርበኞችና ታላቅ የታሪክ ሰዎች አንዱ ክቡር ደጃዝማች አምኃ ናቸው።

ደጃዝማች ከልጅነታቸው ጀምሮ በጣም አንባቢና ጎበዝ ተማሪ ሲሆኑ በመንፈሳዊ ህይወታቸውም ጠንካራ እንደነበሩ ይገለፃል።

ደጃዝማች አምኃ በአገልግሎትታቸውና በአርበኝነታቸው ውጤታማነት የተለያዩ የክብር ሽልማቶችን አግኝተዋል።መላው ቤተሰብ ለክቡርነታቸው ካለው ፍቅርና አክብሮት የተነሳ የአያታቸውን የልዑል ራስ ካሳ ሀይሉን በጎ አድራጎት ድርጅት በበላይነት መርተዋል።እንደተመኙትና የሁልጊዜ ህልማቸው የነበረውን የአገራቸውን ልማት ብልፅግና የፀና አንድነትና ሰላም እውን መሆን ሳያዩ በረዥሙ የእስር ቤት እንግልትና ስቃይ ሳቢያም ለደረሰባቸው የጤና መታወክ ህክምና ለማግኘት ከመጡ ጀምሮ በሚኖሩባት የኒውዮርክ ከተማ ህዳር 24/1996 ዓ.ም በድንገት ከዚህ አለም ቢለዩም መንፈሰ ጠንካራነትን ፅናትን ታማኝነትን አገር ወዳድነትን ታሪክና ባህል ተከታታይነትን በጎ ሰውነትንና ልባዊ ኢትዮጵያዊ ኩራትን በተግባር ያሳዩ በመሆናቸው አርአያነታቸው ምንጊዜም ህያው ነው።

ክቡር ደጃዝማች አምኃ አበራ ከባለቤታቸው ከክብርት ወይዘሮ አሰለፈች መኮንን ሦስት ልጆች ነበር ያፈሩት ሁለቱ በህይወት ባይኖሩም ለታሪካቸው መውጣት ምክንያት የሆነችው ልጃቸው ዮዲት አምሀ ግን በህይወት አለች። ዮዲት ከአባቷ በተደጋጋሚ ታገኘው የነበረው ምክር ፈጣሪዋን እንድታውቅ ፣ እራሷን እንድትችል፣ ኢትዮጵያዊነትን እንድታውቅና እንድትኮራ ነበር። ዮዲትም እያየች ባደገችው የንባብ ፍቅርና የአባቷ ምክር የተነሳ ዛሬ የደረሰችበት እንድትደርስ ትልቅ መሰረት ሆኖላታል።

ታዲያ የደጃዝማች አምሀ አበራ ልጅ ዮዲት አምሀም ብትሆን በትጋት የምትታወቅ ታላቅ ባለሙያ ናት፡፡

ወይዘሮ ዮዲት አምሀ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሳይኮሎጂ ማስተርሷን ደግሞ በማህበረሰብ ሳይንስ ያገኘች ናት፡፡ በተጨማሪም ከዬል ዩኒቨርሲቲ እና ብሬን ምዋር ኮሌጅ የሊደርሺፕ እና ማኔጅመንት ሰርተፊኬቶችን ከኒው ሀምሻየር ዩኒቨርሲቲ የላይፍ ኮች ሰርተፊኬት አግኝታለች፡፡

ዮዲት በስራው አለም ውስጥ በተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎቶች በድርጅቶች ውስጥ በፕሮግራም አስተዳደር በፖሊሲ መቅረጽ እና በአእምሮ ጤና ዙሪያ የተለያዩ የግንዛቤ ትምህርትን በመስጠት ከ30 አመት በላይ በአሜሪካ እያገለገለች ትገኛለች፡፡ እዚህም እናት ሀገሯ ላይ ላለፉት 10 አመታት በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት እና በቦርድ አባልነትም በትጋት እያገለገለች ትገኛለች፡፡

ዮዲት ለታሪክም ልዩ ፍቅር አላት፡፡ የታዋቂዋ አርበኛ የወይዘሪት ሆይ ከበደች ስዩም የልጅ ልጅ በመሆኗ ያሳደጓት አያቷም ስለሆኑ ገና በልጅነት ታሪክን ከእነ መስረቱ ስታጠና ስትሰማ አድጋለች፡፡ የወደፊቱ ትውልድ ሀገሩን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት የምትለው ዮዲት አምሀ ወይዘሪት ሆይ በሚል ርእስ አርበኛ ወይዘሪት ሆይ ከበደች ስዩምን የሚዘክር የማስታወሻ መሰናዶ ለማዘጋጀት ካሰበችበት ቆይታለች፡፡ ይህ ሀሳቧ እውን ለመሆን 2 ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ወይዘሮ ዮዲት አምሀ ይህን መሰናዶ ከተወዳጅ ሚድያ እና ከሳቤህዞን ጋር በትብብር ያዘገጀች ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 3 2016 ከጠዋቱ 3ሰአት በብሄራዊ ወመዘክር ታላላቆች በዝግጅቱ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ልጅ ባለ ታሪክ አያቱን ሲያስብ ደስ ይላል፡፡ ማን ያውቃል ዮዲት ደግሞ ስለ አባቷ የምትለን ይኖራል፡፡ ወደፊት አብረን የምናየው ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *