የአሰብ ወደብ ሥራ

(ከጥር ፲፱፻፶ እስከ ኀዳር ፲፱፻፶፬)

በበየነ ወልደ ገብርኤል
ኀዳር ፳፻፲፩

“የተባለው ይጻፍልኝ፣ እርስዎ ይንገሩት ይጻፍ ልጁ
ዕውቀትዎን ይዘው ወደ መቃብር እንዳይሄዱ።
ለዚህ የሚያገለግል አለኝ ወረቀትና ቀለሙ፣
ቤቴም ያውና፣ እራትም አለ ለሁላችን የሚበቃ
ታዲያስ ይግቡልኝ ቃል? እሺ ይበሏ!”

ላዎትሴ አገር ጥሎ መጓዝ ላይ ሆኖ
የጻፈው፣ ዳዎዴሺንግ የተባለው፣
መጽሐፍ አፀናነስአፈታሪክ

የዘመናት ታሪኮች
በቤርቶልት ብሬኸት
በየነ ወልደ ገብርኤል በ፲፱፻፺፯ እንደተረጐመው

መቅድም

ኢትዮጵያ ለ፭ ዓመት በፋሺስት ኢጣሊያ በተወረረች ጊዜ የተማሩ ኢትዮጵያውያን በያለበት ተገድለዋል። ወራሪው ድል ተደርጎ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ አዲስ አበባ ገቡ። እንደገቡም የዛኑ እለት ባደረጉት ዲስኩር “ይህ ቀን የኢትዮጵያ አዲስ ዘመን መክፈቻ ነው” አሉ። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ወጣቶች ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰውና ያለፈው ጭምር እንዲማሩ በመደረጉ እኔም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆንኩ።የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ራዕይ “የኢትዮጵያ ልጆች ተማሩ፣ ተምራችሁ አስተምሩ፣ ሠርታችሁ አሩ፣ ኢትዮጵያን አልሙ” ነበር። በዚህ ራዕይ መሠረት ለትምህርት ለተሰጠው ከፍተኛ ሥፍራ እና ለተገኙት ውጤቶች ይህ መጽሐፍ ምስክር ነው።

የአሰብ ወደብ ሥራ እና ከእርሱም ጋር ተያይዞ የመጠጥ ውሃና፣ ኤሌክትሪክ ለወደቡና ለከተማው ነዋሪ መቅረቡ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው። በሕይወቴ ከተሳተፍኩባቸው ሥራዎች አንዱ የሆነውን የአሰብ ወደብ ሥራ ፕሮጀክት በዚህች አጭር “የአሰብ ወደብ ሥራ” አርእስት በሰጠኋት ጽሑፍ ውስጥ አቀርባለሁ።የአሰብ ወደብ ሲሠራ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራት ተከናውነዋል። በአሰብ ወደብ ሥራ ፕሮጀክት ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከውጭ አገር ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሥራት የሚታዩ ውጤቶች አስገኝተዋል። በፕሮጄክቱም ሂደት ውስጥ ችግሮች አልተከሰቱም። በግንባታው ጊዜ አደጋ አልተፈጠረም፡። ሆኖም አንድ ከዩጎዝላቪያ የመጣ ሠራተኛ በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ህይወቱ አልፎ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በአሰብ ተፈጽሟል። በሰፊው ቢታወቅ ቁምነገር ይገኝበታል በሚል ሐሳብ፣ ሥራዎቹ እንዴት ይከናወኑ እንደነበር እነሆ አቀርባለሁ።

በመሠረቱ ይህ ውጤት የተገኘው በዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ለትምህርት በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ኢትዮጵያውያንን ማስተማር በመቻላቸው ነው። በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት የተጀመረው ኢትዮጵያውያንን በዘመናዊ ትምህርት አስተምሮ ሀገር ልማት ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ እቅድ አቅም በፈቀደ በአገር ቤት ዘመናዊ ትምህርት ቤት በማቋቋምም ሆነ ውጭ ሀገር በመላክ የተማሩ ዜጐችን ማፍራት ተችሏል። ይህ በጐ ጅምር ግን በ፲፱፻፳፰ እስከ ፲፱፻፴፫ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ምክንያት ተቋርጦ ነበር። ከአምስቱ ዓመት ወረራ በፊት ከተማሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ብዙዎቹን ፋሽስት ጣሊያን ገድሏቸዋል።

ካርበኞች ተጋድሎና ድል በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ባደረጉት ዲስኩር “የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መግቢያ” ባሉት መሠረት ለትምህርት ቅድሚያ የሰጠ ሥርዓት ታየ። አንዱና ዋናው፣ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ወደ ውጭ አገር እየላኩ እንዲማሩ ማድረግ ነበር። ከዚህ ጐን ለጐንም በአዲስ አበባ እና ያን ጊዜ ጠቅላይ ግዛት በሚባሉ የኢትዮጵያ ክፍለ አገሮች ውስጥ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ብዙዎችን ማስተማር ተችሏል።

የእኔ የትምህርት ቆይታ ወደ ፊት በሚታተመው የሕይወት ታሪኬ ውስጥ በሰፊው የማነሳው ቢሆንም እሱ ማን ነው፣ የትነው የተማረው፣ ከቀድሞ ተማሪዎች ጋር ምን ያገናኘዋል እና መሰል ጥያቄዎች በአንባቢያን ዘንድ መነሳታቸው አይቀርም እና በጥቂቱ፤ በተለይ የውጭ አገር ትምህርቴን ላንሳ። እዚሁ ኢትዮጵያ ተሆኖ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚቻልበትን እቅድ ለመተግበር በመንግሥት ይታሰብ ነበርና ይሄም ዕቅድ ተሳክቶ የለንደን ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው በዘመኑ ማትሪኩሌሽን በ፲፱፻፴፱ በ፯ ተማሪዎች ተፈታኝነት ተጀመረ። በሚቀጥለው በ፲፱፻፵ ከተፈተኑት ፷ ያህል ተማሪዎች አንዱ ሆኜ ተፈተንኩ። በዚህም ፈተና ካለፍነው አራት ተማሪዎች አንዱ ሆኜ አለፍኩ። በተጨማሪም በዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ሰኔ ፲፱፻፵ ተፈትኜ አለፍኩ። ፮ኛ ወጥቼም ተሸለምኩ። ወደ እንግሊዝ ሀገር ተልኬ በለንደን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የሲቪል እና የማዘጋጃ ቤት ምሕንድስና ትምህርት ተምሬ ከለንደን ዩኒቪርስቲ ተመረቅሁ።

በዚያን ጊዜ በተለያየ መንገድ ለትምህርት ወደ ውጭ ሀገር የተላክነው ተማሪዎች ትምህርታቸንን እንደጨረስን በውጭ ሀገር በቂ የሥራ ልምምድ ካደረግን በኋላ ወደ ሀገራችን መመለስን እንጂ የድህረ ምረቃ ትምህርት መማር አናስብም ነበር። እኔ እንደ ዘመነኞቼ እንደተመረቅሁ ለንደን ውስጥ በሚገኝ የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አማካሪ መሐንዲስ መሥሪያ ቤት ተቀጠርኩ። ከዚሁ መሥሪያ ቤት ገብቼ ሥራ መሥራት ጀመርኩ። በመሥሪያ ቤቱ በነበረኝ ቆይታ ግን ይህን ያህል የሚጠቅመኝ ልምድ የማገኝ መስሎ ስላልታየኝ እና ሌላ መሥሪያ ቤት የመግባት ምርጫ ስለነበረኝ ይህን ሥራ ለመተው ወሰንኩ።

በለንደን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የሲቪልና የማዘጋጃ ቤት ምሕንድስና በምማርበት ጊዜ ትምህርት ቤቱ ከሰኔ እስከ ጥቅምት ይዘጋል። በዚህ የዕረፍት ጊዜ ተማሪዎች የሥራ ልምምድ ያደርጋሉ። እኔም በዘመኑ ተማሪዎችን ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጋር በሚያገናኘው አቀነባባሪ መሥሪያ ቤት ጠቋሚነት ሁለት ጊዜ ወደ ጀርመን ሀገር ሄጄ ነበር። ለሁለተኛ በሄድኩበት ጊዜ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ “ፍላጐቱ ካለህ ትምህርትህን ስትጨርስ እዚሁ ልትሠራ ትችላለህ” ብሎኝ ስለነበረ ነው ወደዚያው ለመሄድ የወሰንኩት።

ከዚሁ መሥሪያ ቤት ጋር ግንኙነት አደረግሁ፣ በደስታም እንደሚቀበሉኝ ገለጹልኝ። ስለዚህ ለንደን ካለው መሥሪያ ቤት ተሰናበትኩ። እነሱም ጥሩ አሸኛኘት ከማድረጋቸው ባሻገር “በሄድክበት ይቅናህ” ብለው ሸኙኝ። እኔም ወደ ጀርመን አገር ሄድኩ። በጀርመን አገር ቆይታዬ ዋናው ሥራ አስኪያጅ አስበውልኝ የነበረውን የሥራ ዓይነት ከበታች ሠራተኞች ላገኝ አልቻልኩም። ስለዚህ መቁረጥ ነበረብኝ።”እዚህ እንዲህ ከሆነ ወደ አገሬ ገብቼ ባገኘሁት ትምህርት እና የሥራ ልምድ በልማት ሥራ ልካፈል” ብዬ እንግሊዝ አገር ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሄድኩ። መመለስ እንደምፈልግም ነገርኳቸው። አስፈላጊው ነገር ሁሉ ተሟልቶልኝ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ።

እንደተመለስኩ በትምህርት ሚኒስትሩ በክቡር አቶ አካለ ወርቅ ሀብተወልድ አማካይነት ጃንሆይ ፊት ቀርቤ ኢትዮጵያ አውራ ጎዳና ባለሥልጣን መመደቤ ተገለጸላቸው። በኢትዮጵያ አውራ ጎዳና ባለሥልጣን በተለያየ ኃላፊነት ብሠራም ልረካ አልቻልኩም። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ባስብም ይሄነው የምለው መፍትሔ ላገኝ አልቻልኩም። ግን ሥራውን ቀጠልኩ። በዚህ መሀል የሥልጠና ዕድል አግኝቼ ቱርክ ሄድኩ። ሥልጠናውም ስለመንገድ ሥራ እና ድልድይ ዲዛይን ነበር። ከዚያም ተመልሼ በሥራ ላይ እያለሁ የገና ዕለት አንድየምስራች ሰማሁ። በዕለቱ ኳስ ጨዋታ ለማየት ኳስ ሜዳ ሄጄ ነበር። አቶ ጌታቸው በቀለም እንደኔው ለኳስ ጨዋታው መጥቶ ተገናኘን። ጌታቸው እንግሊዝ ሀገር የተማረ ጓደኛዬ ነው። እንዳየኝ በደስታ “እኛ ጋ ልትመጣ ነው” አለኝ።

እሱ የሚሠራው በመከላከያ ሚኒስቴር ባህር ክፍል ነበር። የእኔን መገረም አይቶ ጉዳዩን በዝርዝር አስረዳኝ። “የአሰብ ወደብ ሥራ ሊጀመር ስለሆነ አንተ የአሰብ ወደብ መሐንዲስ ሆነህ፣ ከተቋራጩም፣ ከአማካሪ መሐንዲሱም፣ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም፣ በተለይ ከጉምሩክ ጋር እንድትተባበር እና አገናኝ መኮንን ሆነህ እንድትሠራ እንዲሁም አማካሪ መሐንዲስ እስኪመጣ ሥራውን እንድትቆጣጠር ነው የታሰበው” አለኝ። የአውራ ጎዳና ሥራዬ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ስላላረካኝ ይህንን ዜና እንደ ምስራች ነበር የቆጠርኩት።

ይህንን የሚገልፅ ደብዳቤ ለእኔም ለኢትዮጵያ አውራ ጎዳና ባለሥልጣን እንደሚመጣ ነግሮኝ ስለነበር እሱኑ መጠባበቅ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ እንደተባለው ደብዳቤዎቹ መጡ። የአውራ ጎዳና ባለሥልጣናት ግን እንድቀር ስለፈለጉ “እንዲህ እንዲህ የሚል ደብዳቤ መጥቷል። ስለዚህ ለደብዳቤው መልስ እንሰጣለን የምንሰጠውም መልስ በትዕዛዙ መሠረት እንፈፅማለን። ግን የጀመረው ሥራ ስላለ ይህን እስኪያጠናቅቅ እኛ ጋ ይቆይ ብለን ነው። እኛ ግን በጐን በሆነ ባለሥልጣን አማካይነት እዚህ እንድትቀር እናደርጋለን” አሉኝ።

እኔ ግን በትዕዛዙ መሠረት ይፈፀም ዘንድ ፍላጐቴ መሆኑን ገልጬ ወደ ተባለው መሥሪያ ቤት እንድዛወር “አስፈላጊው ተፈጽሞ ልሰናበት” ስል በጽሑፍ ገለጽኩላቸው። ለካ እኔም እዚሁ መቆየት እፈልግ ይመስላቸው ኖሮ “እኛ እኮ አንተም እዚሁ መቆየት የምትፈልግ መስሎን ብለው የሠራሁበትን ደሞዝ ከፍለው በሰላም ሸኙኝ። ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ አንድ ሳምንት ሳልቆይ በጥር ወር መጀመሪያ ፲፱፻፶ ወደ አሰብ አቀናሁ። የአሰብ ወደብ ፕሮጀክት በሕይወቴ ከረካሁባቸው እና ለአገሬ አገልግሎት ከሰጠሁባቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው። ባህር ክፍል በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር የነበረ ተቋም ነው። በተለይ የአሰብን እና የምፅዋን ወደብን በበላይነት ይመራ ነበር።

ወደ ባህር ክፍል ከመዛወሬ በፊት የኢትዮጵያ አውራ ጎዳና ባለሥልጣን እያለሁ ደሞዜ አራት መቶ ሰማኒያ አምስት ብር ነበር። የተዘዋወርኩበት የባህር ክፍል ደሞዜ ደግሞ አራት መቶ ሃምሳ ብር ነበር። ይሄም የሆነው በበጀት ጉዳይ ስለሆነ ቅናሹን ተቀበለኩት። የኔ ትኩረት የሚያረካኝ ሥራ መሥራት ላይ ነበር። ከአሰብ ወደብ ሥራ ደግሞ እርካታን እንደማገኝ እርግጠኛ ነበርኩ። በባህር ክፍል አስፈላጊውን

የቅጥር ሁኔታ ካሟላሁ በኋላ በተመደበልኝ ላንድሮቨር መኪና በኮምቦልቻ አድርጌ አሰብ ገባሁ። የአንድ መሥሪያ ቤት ሥራ የአንድ ሰው ሥራ አይደለም። ልክ እንደ እግር ኳስ ቡድን ነው። አንድ ተጫዋች ብቻውን ምንም አይፈይድም ጎል የሚያስቆጥረውም፣ ጎል ጠባቂውም፣ ቡድኑም፣ ቲፎዞዎቹም፣ አራጋቢውም ሳይቀር የየራሳቸው ሚና አላቸው። አብሮ ካልተሆነ ወይም አንዳቸው ቢጐድሉ አሁን የምናውቀው ኳስ ጨዋታ አይኖርም። የዚህን ፕሮጀክት ታሪክ በመጽሐፍ መልክ ለማዘጋጀት ስሞክርም “እኔ ብቻዬን ሠራሁ” ለማለት ወይም “የኔ ሚና የተለየ ነበር” ለማለት ሳይሆን በጋራ ስለተሠራ ውጤታማ ፕሮጀክት ለማውሳት ነው።

የአሰብ ወደብ ሥራ ፕሮጀክት ብዙ የተማርኩበት ብዙ የሠራሁበት እንዲሁም ውጤታማ የሆንኩበት ነበር። ስለ ወደቡ ሥራ ቀጥታ ከመግባቴ በፊት ለወጣት ሲቪል መሐንዲሶች እና የዚህ ሙያተኞች ላልሆኑ ለሌሎች አንባቢያንም ይጠቅማል ብዬ ያሰብኩትን ላካፍል። የፕሮጀክቶች የሥራ አፈፃፀም እንደ ሥራው ፀባይ ከፕሮጀክት ፕሮጀክት ይለያያል። አንድ የግንባታ ሥራ ከመሠራቱ በፊት ብዙ አማራጮች አሉ። ለትልልቅ ፕሮጀክቶች የተለመደው በተቋራጭ ማሠራት ሲሆን አልፎ አልፎ በመሥሪያ ቤት ደረጃም ቢሆን ከሀ እስከ ፐ ድረስ ሥራውን በራሳቸው አቅም የመሥራት ጉልበት ያላቸው አሉ።

እዚህ ላይ የኢትዮጵያ አውራ ጎዳና ባለሥልጣንን መጥቀስ ተገቢ ነው። በአንድ ዘመን ራሱ ቀይሶ፣ መንገድ ሠርቶ፣ ጠግኖ፣ በአጠቃላይ መንገድን በተመለከተ ሁሉን አጠቃሎ በራሱ ሠራተኞች ይሠራ ነበር። ይህ ለአብዛኛው ድርጅት አይሠራም፣ ምክንያቱም የሚሠራው ሥራ በብዙ ዓመት አንድ ጊዜ የሚመጣ በመሆኑ ቋሚ ሠራተኞችን መቅጠር ተገቢ አይሆንም። አያዋጣምም።

አንዱ የተለመደው አሠራር፣ መሥሪያ ቤቱ በሚያወጣው ዕቅድ መሠረት አማካሪ መሐንዲስ ቀጥሮ የሥራውም ዝርዝር ከታወቀ በኋላ ጨረታ ይወጣል። ተቋራጮች ተወዳድረው የረከሰ ወይም ዝቅተኛ ዋጋን በማየት ሳይሆን አጠቃላይ አቅም እና ብቃት ታይቶ በኃላፊነት ሥራውን ይወጣዋል ወይ? በሚል ተቋራጩ ተመርጦ ወደ ሥራ ይገባል። ሥራው ከተጀመረም በኋላ በተቆጣጣሪ መሐንዲስ ቁጥጥር ይፈፀማል። እዚህ ላይ ካለኝ የግል እይታ የማካፍለው አለ። አንድ መሥሪያ ቤት የራሱ ዐይኖችና እጆች ሆኖ የሚያገለግለው ቋሚ ባለሙያ ከሌለው ወደ አማካሪ መሐንዲስ ከመሄዱ በፊት ሊያማክረው የሚችል ግለሰብን ወይም ድርጅትን ቀድሞ ቢያገኝ እና ተመካክሮ አማካሪ መሐንዲሶችን እንደ ሁኔታው መርጦ ወይም አወዳድሮ ቢቀጥር ይመረጣል።

ሌላው አማራጭ “ቁልፍ ማስረከብ” የሚባለው ነው። ይህም ዝርዝር ጥናቱን የሚያዘጋጅ፣ ሥራውን የሚፈጽም ማለት፤ በአጠቃላይ ሁሉን ነገር ጨርሶ የሚያስረክበው አንድ ተቋራጭ ነው። በእንግሊዘኛ Design and Build ይባላል። እንዲህ ካልሆነ ግን ሌላው ያጠናውን ሌሎች ተወዳድረው እንዲሠሩ ይደረጋል። ወደ አሰብ ወደብ ፕሮጀክት ስመለስ፤ አሰብ ከአዲስ አበባ ርቀቱ ፰፻፹ ኪሎ ሜትር ሆኖ በቀይ ባህር ዳር የሚገኝ ከተማ ነው። በቀይ ባህር ለሚያልፉት መርከቦች አቀማመጡ የተመቸ ነው። ይህም ሆኖ አሮጌው የአሰብ ወደብ ሊያስተናግድ ይችል የነበረው አንድ ትልቅና አንድ አነስተኛ መርከብ ብቻ ስለነበር መጠኑ እየጨመረ ለመጣው የመርከብ ትራፊክ በቂ አልነበረም። ስለዚህ በዘመናዊ አኳኋን ተስፋፍቶ እንዲሠራ አስፈላጊ ነበር።

እንደሰማሁት፣ መጀመሪያ አንድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን የፈረንሳይ ኩባንያን ይዘው በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር ከነበሩት ከክቡር ራስ አበበ አረጋይ ፊት ቀርበው ነበር። ምክኒያታቸው ይሄ የፈረንሳይ ኩባንያ የአሰብ ወደብን እንዲሠራ ነበር። ራስ አበበ አረጋይ የኩባንያውን ሀሳብ ከሰሙ በኋላ “የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ የት አለ?” ብለው ሲጠይቁ “ዘውዴ (ደጃዝማች) ነው። አሁን ለሥራ ጉዳይ ከሀገር ውጭ ሄዷል” ሲባል “ዘውዴ ለሥራ ቢሄድ ሰው ሳይወክል ይሄዳል?” ሲሉ “ወክሏል” ቢሏቸው “እንግዲያው የተወከለውን ሰው ጥሩት!” ይላሉ። ተወካዩ አቶ ጌታቸው በቀለ መጥቶ ይህን በፈረንሳይ ኩባንያ የቀረበውን ሐሳብ በማስረጃ አስደግፎ፤ “የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን” ለራስ አበበ ገለፀ። ራስ አበበም “እኛ የምንሰማው የእኛ ሰው የሚነግረንን ነው ወይስ የውጭ ሀገር ሰው የሚነግረንን?” ብለው በፈረንሳይ ኩባንያ የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።

በዘመኑ በኢትዮጵያና በዩጐዝላቭ መሪዎች መካከል በነበረው የቅርብ ግንኙነት መሠረት ለአሰብ ወደብ ግንባታ ከዩጐዝላቭ መንግሥት ብድር ተገኘ። የዩጎዝላቭ ኩባንያው የመርከብ ሥራ ተቋራጭ ፖምግራድ ስለ ወደቡና ስለ መርከብ መጠጊያዎቹ አቀማመጥ አስፈላጊ ጥናቶች አደረገ። የተመረጠው አሠራር “ቁልፍ ማስረከብ” በሚባለው የአሠራር ዓይነት ነው። ይህም ማለት ዝርዝር ጥናቱን እና ውሉን የሚያዘጋጅ፤ሥራውን የሚፈፅም፤ በአጠቃላይ ሁሉን ነገር ጨርሶ ቁልፍ የሚያሰረክበው የዩጎዝላቭ የወደብ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ ፖምግራድ ሆኖ ነው።

በጥቅምት ወር ፲፱፻፶ ክቡር ራስ አበበ አረጋይ የዩጎዝላቭ ኩባንያው የወደብ ሥራ ተቋራጭ ፖምግራድ ያዘጋጀውን የሃያ ስድስት ሚሊዮን ብር ውለታ ፈረሙ።

የአሰብ ወደብ ሥራ ፕሮጀክት የበላይ ኃላፊዎች፣

  • ከመጀመሪያው አንስቶ አስከ ታህሳስ ፲፱፻፶፫ አቶ ጌታቸው በቀለ በመከላከያ ሚኒስቴር የባህር ክፍል ረዳት ሚኒስትር
  • ታህሳስ ፲፱፻፶፫ እስከ ፕሬጀክቱ ፍፃሜና ምርቃት አቶ ከተማ አበበ በመከላከያ ሚኒስቴር ክፍል ረዳት ሚኒስትር
  • አቶ ግርማ በለው በመከላከያ ሚኒስቴር የባህር ክፍል ፀሐፊ

ቀደም ሲል ለአንድ መሥሪያ ቤት የራሱ ዐይኖችና እጆች ሆኖ የሚያገለግለው ቋሚ ባለሙያ ያስፈልገዋል ብዬ እንደገለጽኩት ለአሰብ ወደብ ፕሮጀክት ከሃምቦርግ ወደብ መሥሪያ ቤት በተውሶ የተገኙት ጀርመናዊ መሐንዲስ ሚስተር ሐንስ ዲተር ኸፍት ደሞዛቸውን ከኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ሆኖ ይህን አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ እኔ ከኢትዮጵያ አውራ ጎዳና ባለሥልጣን ወደ ባህር ክፍል የተዛወርኩት የወደብ መሐንዲስ፣ እና አገናኝ መኰንን ሆኜ እንድሠራ ነበር። አሰብ ከደረስኩ ከጥቂት ቀናት በኋላ በጥር ወር ፲፱፻፶ የወደብ ሥራ ተቋራጩ ኩባንያ ፖምግራድ ሠራተኞቹን ይዞ አሰብ ሲገባ ተቀበልኩት።

ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሥራውን የሚቆጣጠር አማካሪ መሐንዲስ አልተቀጠረም፡፡ አማካሪ መሐንዲስ ተመርጦ እሰኪመጣ ድረስ በእኔ ተቆጣጣሪነት የወደቡ ሥራ ተጀመረ። ተቋራጩም የዩጎዝላቭ ሠራተኞች መኖሪያ ቤት ግንባታን በራሱ ሠራተኞች ጀመረ፡፡ በባህር ክፍል ለተቆጣጣሪ መሐንዲስነት ጨረታ ወጥቶ “ኖር ኮንሰልታንት” የሚባል የኖርዌይ ኩባንያ ተመረጠ። በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወደ አሰብ መጥቶ ሥራውን ጀመረ።

የአሰብ ወደብ ፕሮጀክት ሥራ፣ በኢትዮጵያ በኩል፣ ብዙ መሥሪያ ቤቶችን ይመለከት ነበር። እነሱም የጉምሩክ መሥሪያ ቤት ያለ ቀረጥ የሚገቡ የኩባንያው ዕቃዎች ስለነበሩ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ደግሞ ወደቡን በኃላፊነት የሚቆጣጠር በመሆኑ፣ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴር የገንዘቡ ጉዳይ ስለሚመለከተው፣ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች በጋራ ይሠሩ ነበር።ሁሉም ይህ ፕሮጀክት “የእኛ ኘሮጀክት ነው” በሚል ቅን መንፈስ እና መተባበር ይሠሩ ነበር።

በዘመኑ በሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የልማት ሥራ ላይ ሲሳተፉ “ባለቤቱ እኔ ነኝ” በሚል “የኔነት” ስሜት ነበር። የእኛም ስሜት ይሄው ነበር። በዚህ መንፈስ በባህር ክፍል መሥሪያ ቤት የነበርን ሰዎች የአሰብ ወደብ ፕሮጀክት የሥራ ውል ምንም እንኳን ውሉ የተፈጸመው “ቁልፍ ማስረከብ” በሚባለው አሠራር ቢሆንም አማካሪ መሐንዲሱ የኖር ኮንሰልታንትን ይዘን አላስፈላጊ የሆኑትን፣ ተጨማሪ እና የሚሻሻሉ ሥራዎችን በዝርዝር አስቀመጥን። ይህንኑ ጥናት ለፖምግራድ ሥራ አስኪያጅ ገለጽንላቸው።የዚህ ጥናት ተሳታፊዎች የባህር ክፍል መሥሪያ ቤት ረዳት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው በቀለ፣ ጀርመናዊው ዋና መሐንዲስ ሚስተር ሀንስ ዲተር ኸፍት፣ የአማካሪው የኖር ኮንሰልታንት መሐንዲሶች እና እኔ ነበርን።

የሥራ ለውጦቹ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ናቸው።

  1. አላስፈላጊ የሆኑ ሥራዎች የተባሉት:-

1.1 የወደቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያውን እና
1.2 በምፅዋ ወደብ እንዳሉት በሀዲድ ላይ የሚሄዱ የዕቃ መጫኛና ማውረጃ መሣሪያዎችን የሚመለከቱ ናቸው።

የወደቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ይሠራ ቢባል:-

  • ተጨማሪ ሠራተኞች መቅጠርን
  • ናፍጣ መግዛትን እና
  • መሣሪያዎችን መንከባከብን ያስከትላል።

በአማራጭ ለወደቡ የሚያሰፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን ሊያቀርብ ስለሚችል ይህን በሚመለከት የባህር ክፍል መሥሪያ ቤት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን ለወደቡም ሆነ ለአሰብ ከተማ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያቀርብ እንደሚችል ስለታመነበት።

የዕቃ መጫኛና ማውረጃ መሣሪያዎች

  • የዘመኑ ባለሙያዎች እንደገለጹት አብዛኞቹ መርከቦች የራሳቸው ለመጫንም ሆነ ለማራገፍ የሚያገለግል መሣሪያ ያላቸው በመሆኑ
  • የወደቡ ሥራ ተቋራጭ ለግንባታው ሥራ ይዞት የመጣው የዕቃ መጫኛና ማውረጃ ክሬን መሣሪያ ስላለው ክሬኑን ገዝቶ በአንድ የተወሰነ ቦታ እንዲቆም በማድረግ የዕቃ መጫኛና ማውረጃ ለሌላቸው መርከቦች አገልግሎት መስጠት ስለሚቻል፤ ከዋናው ውል ለወደቡ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራና የክሬን አቅርቦት፣ እንዲወጡ ተደረገ።
  1. ከዋናው ውል በኋላ የተጨማሩ ሥራዎች

2.1. ለአነስተኛ መርከቦች ማቆሚያ
2.2 ሙቀት ሊያበለሻቸው ለሚችል ዕቃዎች መጋዘን
2.3 ዕቃ ለሚጭኑ እና ለሚያራግፉ ሠራተኞች የመታጠቢያና የመታከሚያ ክፍል
2.4. የወደብ ጽሕፈት ቤት
2.5 የጉምሩክ ጽሕፈት ቤት
2.6. አጥር ማጠር
2.7 መንገዶችን በአስፋልት መሥራት
ለአነስተኛ መርከቦች ማቆሚያ ለትንንሽ መርከቦች መቆሚያ ለመሥራት ልዩ ቦታ ተገኝቶለት እንዲመችም ሲባል የባህር ውሃ የማያበላሸው ደቡብ አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ እንጨት ገዝቶ መጠቀም ይቻላል።

የግርጌ ማስታወሻ

ይህንን በተመለከተ ሁጎ እሸፔንግለር ለወደብ መሐንዲሳችን ሚስተር ሀንስ ዲተር ኸፍት፣ የመርከብ ማቆሚያ ተብለው የተሠሩት እንጨቶች በመበስበስ ላይ መሆናቸውን የነገረው መሆኑን አጫውቶኛል፡፡ መቼ እንዳለው ቢታወቅ

የወደቡ ጽሕፈት ቤት፣የጉምሩክ ጽሕፈት ቤት እና የወደቡ አጥር፣

  • በባህር ክፍል አርኪቴክት፣ መሐንዲስ እና የንድፍ ሠራተኞች አማካይነት ለወደቡ ጽሕፈት ቤት፣ ለጉምሩክ ጽሕፈት ቤት እና ለወደቡ አጥር የሚያስፈልገው ዲዛይን፣ የቅየሳ ሥራ፣ እና የዋጋ ግምት ተዘጋጅቶ በዚያው መሠረት ግንባታው እንዲፈፀም

የአስፋልት መንገድ

  • የውስጥ መንገዶች አስፋልት ቅየሳ፣ የግንባታ እና የዲዛይን ሥራ በተቋራጭ እንዲዘጋጅ እና እንዲሠራ
  1. የሚሻሻሉ ሥራዎች
    3.1 ማዕበል መከላከያ እና
    3.2 የዕቃ ማስቀመጫ መጋዘኖች

የማዕበል መከላከያ

  • የታቀደው የማዕበል መከላከያ ቁመት እና አቅጣጫ መሻሻል ስላለባቸው የዚሁ የማዕበል መከላከያው ማዕከላዊ አካል ሥራ እና የመርከብ ማቆሚያዎች ሥራ ሳይቋረጥ በጀርመን ሀገር ሃኖቨር ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ጥናት እንዲደረግ የባህር ክፍል መሥሪያ ቤት አስፈላጊውን አርምጃ እንዲወስድ

የዕቃ ማስቀመጫ መጋዘኖች

  • በፕሮጄክቱ ሊሠሩ ከታቀዱት ስድስት የዕቃ መጋዘኖች ለጊዜው ሦስት የዕቃ መጋዘኖች ተሠርተው ቀሪዎች ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ በሀገር በቀል ተቋራጮች እንዲሠሩ
  1. ተቋራጩ ፖምግራድ የሠራቸው የሠራተኛ መኖሪያ ቤቶች ተቋራጩ ሥራውን አጠናቆ በሚሄድበት ጊዜ
    ለሠራተኞቹ የሠራቸው መኖሪያ ቤቶች ለመንግሥት ሠራተኞች መኖሪያ ይሆኑ ዘንድ ዋጋቸው ከፕሮጄክት ገንዘብ የሚታሰብ እንዲሆን።

ከተቋራጩ የፖምግራድ ኃላፊ ጋር ከዚህ በላይ በዝርዝር በተገለጹት የሥራ ለውጦች እና በሚያስከትሉት የዋጋ ለውጦች ተደራድረን ፕሮጀክቱ ቁልፍ ማስረከብ በሚባለው አሠራር በሃያ ስድስት ሚሊዮን ብር ውል የተፈረመ ቢሆንም በሥራ ለውጦች መሠረት የሚቀነሰው ተቀንሶ የሚደመረው ተደምሮ ጠቅላላ የሥራ ዋጋ ሃያ አምስት ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ብር ሆነ።

ከዚህ በኋላ እነዚህን ለውጦች የአሰብ ፕሮጀክት ኮሚቴ እንዲያጸድቅ አቀረብኩ። በኮሚቴው ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ ሰጠሁ። ኮሚቴውም በአንድ ድምፅ የቀረበውን ሐሳብ አጸደቀው። በተቋራጩ የዩጎዝላቭ ኩባንያ ሆነ በሌሎቹ ባለ ድርሻ አካላት እና በዚህ ፕሮጀክት ተሳታፊዎች የተወሰኑት ሥራዎች በታቀደው መሠረት እንዲቀጥሉ ተደረገ፡፡

ጃንሆይ በተደጋጋሚ አሰብን ሲጎበኙ የወደቡንም ሥራ በትኩረት ይከታተሉ ነበር። እንዲሁም አጠቃላይ ዕቅዱ ተገልጾላቸው በአዲሱ ጥናትም የተገኘውን የማስተካከያ ሐሳብ አውቀው “በዚሁ ቀጥሉ’’ በማለት አበረታተውናል። የወደቡ ሥራ የካቲት ወር ፲፱፻፶ ተጀምሮ በባህር ክፍል ዋና መሥሪያ ቤት ኃላፊነትና በኖር ኮንሰልታንት አማካሪ መሐንዲሶች ተቆጣጣሪነት ተሠራ።

ከላይ ከተገለጹት ተጨማሪ ሥራዎች የአጥርና የአስፋልት ሥራ :-

ለዕቃዎች በደንብ መጠበቅ ለጉምሩክ ሥራ እና ወደብ ውስጥ የሚገቡትንና የሚወጡትን ሰዎችና መኪናዎች በደንብ ለመቆጣጠር እንዲቻል ወደቡ በአዲስ አጥር ታጥሮ ከከተማው ተለይቷል። ሆኖም ወደቡ ለከተማው ቅርብ ስለ ሆነ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር ግንኙነት ለማድረግ ቀላል ነው። ወደ ወደቡ የሚገቡትና ከወደቡ የሚወጡት ከባድ መኪናዎች የከተማውን ዋና መንገድ እንዳያጣብቡና ትራፊኩን እንዳያስቸግሩ በማለት ለከባድ መኪናዎች ልዩ አዲስ በአስፋልት የተነጠፈ ሰፊ መንገድ ተሠርቷል። በወደቡ አጥር ግቢ ያሉትም ልዩ ልዩ መንገዶች በአስፋልት የተነጠፉ ናቸው።

በባህር ክፍል እና በአሰብ ወደብ ጽሕፈት ቤት ከተቋራጩ ፖምግራድ ጋር ከተደረገው ውል ውጭ በባህር ክፍል በጀት የሚከተሉት ሦስት ሥራዎች ተከናውነዋል

  • የምልክት መስጫ ሰገነት አስፈላጊ ስለሆነ በባህር ክፍል አርኪቴክታችን እና ዋና መሐንዲሳችን አዘጋጅነት ሀገር በቀል በሆነ ተቋራጭ ገንቢነት የምልክት መስጫ ሰገነት ተሠርቷል።
  • የወደቡ ሥራ አስኪያጅ እና የፋይናንስ ክፍል ሠራተኛ መኖሪያ ቤቶች ታድሰዋል።
  • ለወደቡ አስተዳዳሪ እና ለእኔ ለወደብ መሐንዲሱ ሁለት ቤቶች ከነአጥራቸው በምፅዋው ዋና መሐንዲስ በተዘጋጀው ዲዛይን እና የግንባታ ዕቃ አቅርቦት፣ በተቋራጩ ገንቢነት ተሠርቷል።

ልዩ ልዩ ቢሮዎችን የዕቃ ቤቶችንም ሌሎችንም በወደቡ ውስጥ ያሉ ተገቢ ቦታዎችን የሚያገናኝ ዘመናዊ የሆነ የስልክ መሥመር ተሠርቷል። መርከቦች ከከተማው ጋር በቀጥታ ሊገናኙ የሚችሉበትም የስልክ መስመር ታስቦበታል። ወደቡን ግሩም በሆነ አኳኋን የሚያበሩ መብራቶች ገብተዋል። ለመርከብ መጠጊያዎችም የኤሌትሪክ ግንኙነት እንዲኖር ተደርጓል።

አዲሱ የአሰብ ወደብ የቦታ አደረጃጀት በአምስት ምድብ ሊዘረዘር ይቻላል። እነዚህም፣

  1. በስተስሜን ያለው የመርከቦች መጠጊያ፣
  2. በስተደቡብ ያለው የመርከቦች መጠጊያ፣
  3. የአነስተኛ መርከቦች መጠጊያዎች፣
  4. የማዕበል ማገጃ እና፣
  5. የአነስተኛ የጀልባዎች ወደብ ናቸው።

የአሰብ ወደብ በዋና ውሉ መሠረት እና በለውጥ ሥራ የተከናወኑት ሥራዎች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው

  • የማዕበል ማገጃ
  • በስተስሜን ያለው የመርከቦች መጠጊያ፤
  • በስተደቡብ ያለው የመርከቦች መጠጊያ፤
  • የአነስተኛ መርከቦች መጠጊያዎች፤
  • አነስተኛ የጀልባዎች ወደብ
  • ሦስት የዕቃ ቤቶች
  • የወደብ ጽሕፈት ቤት
  • የጉምሩክ ጽሕፈት ቤት
  • አዲስ የወደብ ሞያተኞች የመታጠቢያ እና
  • የመታከሚያ ክፍል
  • ባለማቀዝቀዣ የዕቃ ቤት
  • ከባድ የዕቃ መጫኛና ማራገፊያ መሣሪያ
  • የወደቡ የደህንነት አጥር እና የመግቢያ በር
  • የወደቡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና ከወደቡ ውጪ
  • ያሉ መንገዶች የአስፋልት ሥራ
  • ለመንግሥት ሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች

መቼም ተሳካ ያለው ፕሮጀክት ነውና የታቀደለትን ያህል ጊዜ እንኳን ሳይቆይ ከተመደበለት በጀት ባነሰ በሃያ አምስት ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ብር የአሰብ ወደብ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ። ለሁላችንም ትልቅ ደስታ ነበር። በኀዳር ወር ፲፱፻፶፬ የአሰብ ወደብ ፕሮጀክት በንጉሠ ነገሥቱ በታላቅ ድምቀት ተመረቀ።

በትርፉ … አሰብ የውሃ ጥሟን ታርካ!

ደስታችን በቃን ብለን ግን አልረካንም። መቼም በቃ አበቃ የሚባል ነገር የለም። የአሰብ ወደብ ሥራ ሲጠናቀቅ ስድስት መቶ ሺህ ብር ተረፈ። በዘመኑ ትልቅ ገንዘብ ነበር። ይህ ገንዘብ ለአሰብ ወደብ እና ለከተማው ነዋሪ የመጠጥ ውሃ እንዲውል ፈለግን። የተቋራጩ ሥራ አስኪያጅ “እኔ ወደብ እንጂ የመጠጥ ውሃ አልሠራም” የሚል ቁርጥ ያለ እውነተኛ መልስ ሰጠ።

ይህ ጉዳይ ለበላዮቻችን ቀርቦ ሃሳባችንን ተረድተው ከዩጎዝላቭ መንግሥት ጋር በከፍተኛ ደረጃ ተነጋግረው ገንዘቡ ለአሰብ የመጠጥ ውሃ ማሻሻያ እንዲውል ስምምነት ተደረገ። አማካሪ መሐንዲሱ ኖር ኮንሰልታንት በአሰብ አካባቢ ውሃ ሊገኝባቸው በሚችሉት ቦታዎች ላይ ባደረገው ምርመራ ከአሰብ ፲፫ ኪሎ ሜትር ርቀት ካለ ስፍራ ላይ የከርሰ ምድር ውሃ ተገኘ። በዚህ ጥናት ውጤት መሠረትም የግንባታው ሥራ ተቋራጩ ፖምግራድ እንዲሠራው ውል ተፈረመ።

ጀርመናዊ መሐንዲሳችን እና እኔ በጋራ ሆነን የቅየሳ ሥራ በእኛ ኃላፊነት እንዲከናወን ተደርጎ ለአንድ ኢትዮጵያዊ የቅየሳ ሥራ ለሚሠራ ሰው ውል ሰጠን፤ ሥራውንም ሠርቶ አስረከበ።ከተረከብን በኋላ እንደ ደንቡ የቅየሳው ሥራ በትክክል ለመሠራቱ መመሰካከሪያ የሂሣብ ሥራዎችን ስንመለከት የቀረበው መመሰካከሪያ የቅየሳው ሥራ በትክክል መሠራቱን የሚገልጽ ሆኖ አገኘነው። በዚህ ሙቀት እንደዚህ ዓይነት ውጤት ሊገኝ ስለማይችል የቀረበው መመሰካከሪያ ሊሆን የሚችለው የታረመ መሆኑን አረጋገጥን። ስለዚህ አዲስ አበባ ባህር ክፍል የነበረ ጀርመናዊው ዋና መሐንዲሳችን እና እኔ ሆነን “ሀ” ብለን መቀየስ ጀመርን። በጥሩ ሁኔታም አሳካነው።

ነባሩን የአሰብ የመጠጥ ውሃ የሚያስተዳድረው የአሰብ ማዘጋጃ ቤት ነበር። የአሰብ እና የምፅዋ ወደቦች የሚተዳደሩት በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ባህር ክፍል ስለነበር የተሻሻለው የመጠጥ ውሃ በአሰብ ወደብ ጽሕፈት ቤት እንዲተዳደር ተወሰነ። በዚሁ መሠረት ነባር የከተማውን የመጠጥ ውሃ ሁኔታ አንድ በአንድ ከባልደረቦቼ ጋር በመዘዋወር ተመለከትን። የመጠጥ ውሃ የአቅርቦትን ዋጋ አግባብ ባለው እና ከተጠቃሚው አቅም ጋር ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እንዲሆን አድርገን ተመኑን አወጣን። በነባሩ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በየቤታቸው ውሃ ቆጣሪ ያስገቡ ደንበኞች ለነዋሪው ውሃ በውድ ዋጋ ይሸጡ ነበር።

ለአስተዳደር ሥራውም የሚያስፈልጉ ቋሚ ሠራተኞች ቀጠርን። የውሃ መስመሮችከተዘረጉ በኋላ የሚችሉት ቤታቸው ሲያስገቡ ቤታቸው ለማስገባት አቅማቸው ላልፈቀደው በየአካባቢው በተተከለው ቦኖ በተመጣጣኝ ዋጋ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ አደረግን። ሕዝቡም ተደሰተ። የወደብ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች “ከወጣው የዋጋ ተመን ለእኛ ቅናሽ ይደረግልን” ብለው ቢጠይቁም የእኛ መልስ “እኛ እንደማንኛውም ሠራተኛ ደሞዝተኞች ስለሆንን እኩል መክፈል አለብን” የሚል ነበር።

ለአሰብ ወደብ እና ለከተማው ነዋሪ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከግለሰብ ወደ መንግሥት ማዛወር

ከላይ እንደተገለጸው የአሰብ ወደብ ፕሮጀክት የሥራ ውል ምንም እንኳን ውሉ የተፈጸመው “ቁልፍ ማስረከብ” በሚባለው አሠራር ቢሆንም አላስፈላጊ የሆኑትን፣ ተጨማሪ እና የሚሻሻሉ ሥራዎችን በሚመለከት በዝርዝር ስናስቀምጥ አላስፈላጊ የሆኑ ሥራዎች በሚለው ሥር የገለጽነው የወደቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንዲተካነው። በዘመኑ ለአሰብ ከተማ እና ለወደቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እና መብራት ይቀርብ የነበረው በአንድ ከመንግሥት ፈቃድ በተሰጠው ጣሊያናዊ ነበር።ይህ አቅራቢ ያስከፍል የነበረው ዋጋ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን በሀገሪቱ ከሚያስከፍለው ዋጋ በላይ ነበር።

ስለዚህ ለአሰብ ከተማም ሆነ ለአሰብ ወደብ ኤሌክትሪክ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን ይሁን ብለን ሐሳብ አቀረብን። ሐሳቡም ፀደቀ። ለከተማውና ለወደቡ ኤሌክትሪክ ያቀርብ የነበረው ጣሊያናዊ ካሣ ተከፍሎት እንዲለቅ ተወሰነ። በቶሎ ይለቅ ዘንድ ካልጠፋ ቦታ አዲሱ የወደብ ጽሕፈት ቤት ሕንፃ የኃይል ማመንጫው ባለበት ቦታ ላይ እንደሚሠራ በፕላኑ ላይ ተመለከተ። ይኸውም ጃንሆይ የወደቡን ሥራ ሲጎበኙ የተለያየን ሰዎች ስለፕሮጀክቱ ሥራ እና የሥራ ለውጥ መግለጫ ስናቀርብ ስለዚህም ሕንፃ እተባለው ቦታ ላይ ማረፍ አስረድተናል። በበኩላቸውም መልካም ነው ቀጥሉ ብለው አበረታተውናል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አዘጋጅቶ ሥራውን ጀመረ። ለጣሊያናዊው ኤሌክትሪክ አቅራቢ የሚከፈለው ካሣ ሲተመን የመሣሪያዎቹ ኪሣራ እና ለቀሩት ዓመታት ሊያገኝ የሚችለው ትርፍ ተተምኖ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን ክፍያውን እንደፈጸመለት የዚሁ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ነግረውኛል።

የአሰብ ወደብ ፕሮጀክት የሥራ አፈጻጸም

በአጠቃላይ የአሰብ ፕሮጀክት በዘመኑ የፕሮጀክት አፈፃፀም መለኪያ የነበሩትን ሦስቱንም መስፈርቶች አሟልቷል።
እነዚህም፡-

  1. ከተባለው ጊዜ በፊት ማለቁ፣
  2. ከተገመተው ዋጋ ባነሰ መጠናቀቁ፣
  3. በተሻለ ጥራት መፈፀሙ ናቸው።

በእውነቱ ማንኛውም ፕሮጀክት ተሳካ የሚባለው በተባለው ጊዜ በተመደበለት በጀት እና በታሰበው እንዲያውም በተሻለ ጥራት መፈፀሙ ነው።የአሰብ ፕሮጀክት ሦስቱን መስፈርቶች ከማሟላቱ በተጨማሪ ልዩ የሚያደርገው በተረፈው ገንዘብ ለአሰብ ወደብ እና ለከተማው ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ መቅረቡ እና የመብራት ኃይል ከግል ወደ መንግሥት እንዲዛወር መደረጉ ነው።

እኔ በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የወደቡ መሐንዲስ በመሆን፣ወደቡ በመሠራት ላይ እያለም ሆነ ከመሠራቱ በፊት የወደብ አገልግሎቱ አልቆመም ነበርና በወደብ ሥራ አስፈፃሚነት፣ ዋናው ተቆጣጣሪ መሐንዲስ እስኪመጣ በተቆጣጣሪነት፣ እንዲሁም የራሳችንን ሕንፃ ጨምሮ ለወደቡ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ከዋናው ፕሮጀክት ውጪ የሆኑ የመኖሪያ ቤት፣ የምልክት መስጫ ሰገነት እና ሌሎች ሕንፃዎች ሲታደሱና እንደ አዲስ ሲሠሩ በመሪነትና በአቀነባባሪነት ተሳትፌአለሁ።

የአሰብ ፕሮጀክት ሥራን በምንሠራበት ጊዜ አኗኗሬ ምቹ አልነበረም ግን ደስታ የተሞላበት ነበር። አሰብ እንደገባሁ ሆቴል ነበር ያረፍኩት። ትንሽ ቆይቶ መሥሪያ ቤቱ ቤት ተከራየልኝ፤ የማዘጋጃ ቤት ሆኖ አንድ ጣሊያን ተከራይቶት የነበረ ነው። እኔ ስገባ ጣራው አሮጌና በየቦታው የተሸነቋቆረ ስለነበር ቀን ፀሐይ ሌሊት ጨረቃና ኮከብ እያየሁ ነበር የኖርኩት። ውሃ እንኳን ስለሌለው ባህር እየሄድኩ ነበር ፊቴን የምታጠበው።የነበረው ሙቀት አይጣል ነው። ሰው በላብ ተነክሮ ሲታይ በተለይ ምግብ ቤት ውስጥ ያለው አሳላፊ ላቡ የምንበላው ሾርባ ውስጥ ሳይገባ የቀረ አይመስለኝም፣ ግን ሳንጸየፍ እንበላ ነበር። ደግሜ ብኖረውም የሚያስደስተኝ ሕይወት ነው። ሥራው በተሳካ ሁኔታ ወደ መጠናቀቁ ሲቃረብ እኔ ዕድገት አግኝቼ ከአሰብ ወደ አዲስ አበባ የቴክኒክ አገልግሎት ኃላፊ ሆኜ ዋናው መሥሪያ ቤት ተመለስኩ።

ምስጋና

ወይዘሮ ገነት ደምሴ፣ “ኑ ፊልም ፕሮዳክሽን” የወይዘሪት ዙፋን ኡርጋ እና የአቶ ኤሊያስ ዘሪሁን የሆነውን ድርጅት ስለአስተዋወቀችኝ፣ አቶ ኤሊያስ ዘሪሁን፣ ወይዘሮ ገነት ደምሴ፣ ከአቶ ነብዩ ዮሐንስ እና ከአቶ መዝገቡ ከፍያለው ጋር ሆነው ድምጼን በመቅረጽ የተቀረጸውን በኰምፒውተር በማዘጋጀት የተዘጋጀውንም በማተም ለእርማት ስላቀረቡ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። የመጀመሪያ ረቂቅ ስለቀረበ ወይዘሮ ገነት ደምሴ እቤቴ ድረስ እየተመላለሰች ከእኔ ጋር አብራ እየተነጋገረች አስፈላጊዎቹን እርማቶች በማድረግ፣ ይህን መጽሐፍ በተቻለ መጠን በፍጥነት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ስለአደረገች ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን የመጨረሻ ረቂቅ አይተው፣ አስተያየት ለሰጡኝ ለአቶ ተሰማ ደምሴ፣ ለልጄ ዶክተር መኩሪያ በየነ፣ ለባለቤቴ ወይዘሮ ኩላ ዜርቮስ፣ ለዶክተር ይሔይስ ፈለቀ፣ ለዮፍታሔ ይሔይስ፣ እና ለምስክር ይሔይስ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *