የሚድያ ሰዎችን ታሪክ የያዘ መጽሀፍ ሊወጣ ነው

የኢትዮጵያውያን የስራና የህይወት ተሞክሮ በልዩ ልዩ መገናኛ ዘዴዎች በማቅረብ የሚታወቀው ተወዳጅ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ማዕከል በቅርቡ ደግሞ በኢንሳይክሎፒዲያ ቅርጽ የተዘጋጀ መጽሀፍ ያወጣል፡፡ ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› የሚል ርእስ ያለውና በኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ባለስልጣን የቀዳሚ የባለቤትነት ማስረጃ ያገኘው ይህ ስብስብ ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ 2004 ድረስ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያላቸውንና የነበራቸውን ባለሙያዎች ተሞክሮ ያካተተ ነው፡፡

‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› ደረጃውን በጠበቀ ጠንካራ ሽፋን / hard cover/ በ600 ገጽ የቀረበ ሲሆን 180 የሚድያ ሰዎች ልምድና ህይወታቸውን ያጋሩበት ነው ፡፡ በዚህ ቁጥር ልክ የሚድያ ሰዎች ግለ-ታሪክ ሲቀርብ የመጀመርያ ያደርገዋል ተብሎለታል፡፡

የሰው ልጅ በህይወት እያለ ያለፈበትን መንገድ ለቀጣዩ ትውልድ ጽፎ በማስቀመጥ መንገር አለበት የሚል መርህ ይዞ የበርካታ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ከራሳቸው ከባለቤቶቹ ማሰባሰብ የቻለው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሀን የግማሽ ክፍለ-ዘመን ታሪክ በሚድያ ሰዎች ተሞክሮ ለማሳየት እንደቻለ ተነግሮለታል፡፡

አንድ አመት የወሰደው ይህ ታሪክን ለትውልድ ሰንዶ የማቆየት ስራ በጥንቃቄ የተሰራ ሲሆን መጽሀፍ ከመሆኑ አስቀድሞ ታሪኩ በተወዳጅ ሚድያ ብሎግና የፌስ ቡክ ገጽ ሲወጣ እና አስተያየት ሲሰጥበት የቆየ ነው፡፡ ታሪካቸው የሚጻፍላቸውን ሰዎች የበለጠ አሻራ ያኖሩ መሆን ያለባቸው ሲሆን ይህንንም የተሳካ ለማድረግ ተወዳጅ ሚድያ በጠንካራ ባለሙያዎች የተደራጀ 6 የመማክርት ቡድን ፤ እንዲሁም 6 አማካሪዎችን ይዞ ይህን ስራ እውን ያደረገ ሲሆን ባለሙያዎቹን መለካት የሚችሉ መመዘኛዎችን በማውጣት የሚድያ ሰዎቹን ታሪክ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡

ከተወዳጅ ሚድያ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው በመዝገበ-አዕምሮ ላይ ለመካተት በጽናት ሙያው ላይ ማገልገል እንዲሁም ለሙያው ታላቅ ፍቅር ማሳየት ከመስፈርቶቹ አንዱ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሙያ እንዲሁም ለጋዜጠኝነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉና እያደረጉ ያሉ ባለሙያዎች ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡የኮሚኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ፤ የጋዜጠኝነት መምህራን ፤ የዜናእና የፕሮግራም ኤዲተሮች ፤የፕሮግራም ፎርማት ፈጣሪዎች እንዲሁም በተመደቡበት ሙያ ሳይታክቱ ስራቸውን በአግባቡ የከወኑ ባለሙያዎች ታሪካቸው በመጽሀፉ ላይ ሊከተብ ችሏል፡፡

‹‹….ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ቋንቋ የተዘጋጀ ኢንሳይክሎፒዲያ ያስፈልጋቸዋል ፤ ቤተ-መጽሀፍት ውስጥ በጠንካራ ሽፋን የታተሙ፣ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው የሚቆዩ ደረጃቸውን የጠበቁ መጽሀፍት መቀመጥ አለባቸው የሚለው የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ እዝራ እጅጉ ይህ ስራ ለሀገር በጣም አስፈላጊና በተለይ ምርምር ለሚያደርጉ ፤ ለእውቅናና ሽልማት ሰጪ ተቋማት ትልቅ ክፍተትን የሚሞላ በመሆኑ መንግስት ትልቅ እገዛ ሊያደርግለት ይገባል ይላል፡፡

‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› በህይወት ያሉ እና ስራቸውን በማከናወን ላይ ያሉ 144 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ያካተተ ሲሆን ቀሪዎቹ 36 ያህሉ አሻራ አኑረው ህይወታቸው ያለፈ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ከጠቅላላ ከ180 ታሪካቸው ከተነበበላቸው ውስጥ 52 ያህሉ ወይም 30 ለመቶ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ሁሉም ታሪኮች ራሳቸው ፈቅደውና ቤተሰቦቻቸው አረጋግጠው የተገኘ በመሆኑ ስራውን አስተማማኝ ያደርገዋል፡፡

የመጽሀፉ ዋና አርታኢያን እዝራ እጅጉ እና እስክንድር መርሀጽድቅ ሲሆኑ የጠቅላላ ይዘቱ ዋና አማካሪ ደግሞ ቤርሳቤህ ጌቴ ናት፡፡የግራፊክስ ንድፍ ባለሙያው ደግሞ ዘሪሁን አሰፋ ነው፡፡ ከ29 መገናኛ ብዙሀን የተውጣጡ ባለሙያዎች ታሪካቸውን ያሰፈሩ ሲሆን ከዚህ ቀደም የራሳቸውን ታሪክ የመጻፍ ባህል ያልነበራቸውን ሰዎችም ባህል እንዲኖራቸውና ታሪክን ማጋራትን እንዲጀምሩ/ እንዲለምዱ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው ተብሎለታል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት ዋና ሀሳብ አፍላቂ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ እዝራ እጅጉ የ44 ኢትዮጵያዌያን ታሪክ በሲዲ ሰርቶ ያስመረቀ ፣ እንዲሁም 6 መጽሀፍትን ያሳተመና በጋዜጠኝነት ባለፉት 22 አመታት ያገለገለ ነው፡፡ እዝራ ወደ ፊትም ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› በሚል ርእስ ልዩ ልዩ እውቀቶችን እና ግለ-ታሪኮች በኢንሳይክሎፒዲያ ቅርጽ አሳትሞ የማውጣት ግብ ሰንቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *