የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊው የህትመት ጋዜጠኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ከንቲባ ደስታ ምትኬ የራሳቸውን ግለ-ታሪክ የጻፉበትን ባለ 3 ገጽ የእጅ ጽሁፍ እንዳየሁት የተወለዱት ሀምሌ 29 1874 በሸዋ ሸንኮራ በሚባል ስፍራ ነው፡፡ የእጅ ጽሁፋቸው ልቅም ያለ ሲሆን ከዚህ ጽሁፍ ጋር ያያያዝኩት ስለሆነ ሊመለከቱት ይችላሉ፡፡ ከንቲባ ደስታ 14 አመት እስኪሆናቸው ድረስ በአባታቸው ቤት ንባብ እና ጽህፈትን በወጉ ተማሩ፡፡ከዚያም በመቀጠል ጀር በሚባል ገዳም ለተማሪ ቤት ገቡ፡፡በ19 አመት እድሜያቸው በዳግማዊ ምኒልክ ፈቃድ የቴሌግራም ጽህፈት እንዲማሩ ታዘዙ፡፡በ1898 ደግሞ የስራ ልምዳቸው ከግምት ውስጥ ገብቶ ለትግሬ አውራጃ በአድዋ የስልክ ቤት ጸሀፊ ሆኑ፡፡ በ1900 ደግሞ በ26 አመታቸው መሆኑ ነው ከአዲስ አበባ ወደ ሀረር በማቅናት ዋና የቴሌግራም ጸሀፊ ለመሆን በቁ፡፡በአመቱም በ1901 ከጅቡቲና ከሀረር እንደዚሁም ከድሬደዋ ለሚላኩ ፖስታዎች ዋና ጸሀፊ ሆንኩ፡፡
ከንቲባ ደስታ ይህን ሁሉ እኔ እያሉ ከእነ አመቱ ወረቀት ላይ ያሰፈሩ ነበር፡፡ ቀጠሉ ከንቲባው ‹‹…በ1903 ደግሞ በምእራብ ወለጋ በኩል ለስልክ ስራ ታዝዤ በቦታው ስልክም አስገባሁ፡፡በ1903 ሼህ ሆጀሌና ደጃዝማች ጆቴ ተጣልተው ነበርና፡፤ሰዎቻቸውም ተዋግተው ስለነበር ምርኮኛ እንዳመላልስ ታዘዝኩ፡፡›› ብለዋል፡፤ ከንቲባው ራሳቸው ደስታ ራሳቸው የከተቡት በመሆኑ ወደ ትክክለኛ እውነት ማድላቱ አይቀርም፡፡
ከንቲባ ደስታ በ1906 ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከሙሴ ሚሼል ዘንድ በመሄድ የቴሌግራም ትምህርትን ለማስተማር ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡
በ1909 የሰገሌ ጦርነት በተነሳ ጊዜ ከአድዋ በአስመራ በኩል ወደ ጅቡቲ ከጅቡቲም አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ‹‹……በ1910 ከከንቲባ ወሰኔ ዛማኑኤል ጋራ ለአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት መቋቋም ታዝዤ ነበር፡፡ የእኔም የክፍል ስራ በመንገድና እና በታክስ ስራ ትልቅ እገዛ መስጠት ነበር፡፡በ1913 የወሰን ተመልካችነትን ሹመት አገኘሁ፡፡ቀጥሎም በ1915 የወሰን ተመልካችና በማጂ አውራጃ ነጋድራስ በመሆን ተሾምኩ፡፡›› በማለት ግለ-ታሪካቸውን ጽፈው ነበር፡፡ ከንቲባ ደስታ በሀገራችን የመጀመሪያው ጋዜጠኛ በ 1887 ዓ.ም ሲመሰረት በጋዜጣው ላይ ስራ የጀመሩ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ ናቸው።
ከንቲባ ደስታ ምትኬ በጽሁፋቸው ጣዕም የተነሳም በአንባቢያኖቻቸው ዘንድ ጋዜጠኛ የሚል ስም የወጣላቸው ናቸው። ከንቲባ ደስታ ጋዜጠኛ ብቻ አልነበሩም። ከመጀመሪያዎቹ የፖስታ ሚንስቴርና ስልከኞች አንዱ ናቸው ከመጀመሪያዎችም 11 የሬዲዮ ኦፕሬተሮች ውስጥም አንዱ ሲሆኑ ደሞዛቸውም በወቅቱ ስድስት ብር ነበር። በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጊዜ እንደ መጀመሪያው ጋዜጠኛ ሲጠቀሱ የነበሩትን ጋዜጠኛ (ከንቲባ) ደስታ ምትኬን ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ አነጋግሯቸዋል። ደስታ ምትኬ ምኒልክን ተከትለውና እንዲያውም የእቴጌ ጣይቱን ቀሚስ እየጐተቱ ወደ አድዋ ጦር ግንባር ከዘለቁ ለጋ ወጣቶች አንዱ ነበሩ። ወደ አድዋ ስለተደረገው ጉዞ፣ ስለአገራቸው ሠራዊት ልበ-ሙሉነት፣ ስለ ጦርነቱ ውሎ ደኅና ሲያወሩላችሁ ቆይተው አፈፍ ብለው ቆመው እየየ ይላሉ። የወደቀው የአገራቸው አርበኛ ከፊታቸው ይመጣባቸዋል። ይሰለፋል። ታንክ በጐራዴ የተባለበትን እሾሁ እንኳ ስለማይወጋው ጦረኛ
ያወጉአችኋል። እየየ ይላሉ። አንዳንድ ሰነፍ ተዋጊ ለመሸሽ ሲሞክር እቴጌይቱና ደንገጡሮቻቸው “አንተ ወዴት ነው የምትሸሸው- እያሸነፍህ? እየረፈረፍኸው? የምኒልክ ጮማ- የምኒልክ ጠጅ ይኽ ነው?” እያሉ የፈሪ ልብ ሆነው ሲያዋጉ የነበረበትን ሁኔታ ያነሡና ያለቅሳሉ። ጦርነቱ አልቆ በምኒልክ ድንኳን ውስጥ ከነበሩት መሳፍንት መካከል ራስ መኰንን የተናገሩትን ያስታውሳሉ። ደስታ ምትኬ እንድሚሉት ራስ መኰንን “ግርማዊ ጃንሆይ! እናቴ እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር በዚች ዕለት ወደፊት በሚነሡ የኢትዮጵያ ትውልዶች ላይ የሚያመጣውን ጦርነት ሁሉ እኛው እንድንገላገለው ቢሰጠን ምንኛ መታደል ነበር?” እንዳሉ ይጠቅሳሉ።
ይህን ትዝታ ያወርዱና ከንቲባ ደስታ እየየ ይላሉ። በእንባ ይጠመቃሉ። ራስ መኰንን ከእነሱ በኋላ የሚበቅለውን ትውልድ የተጠራጠሩ ይመስላል። ለአገር አንድነት የሚኖረውን እሴት፣ የወገንን ሉዓላዊነትና ክብር በማስጠበቁ በኩል የሚያድርበት የውጊያ መንፈስ፣ “የኢትዮጵያ እና የመስዋዕትነት ፋይዳ ምን ያህል ለትውልዶች ሊወርድ እንደሚችል ጠርጥረዋል። በእኛ ላይ ተስፋ የቆረጡ ነበር…ልበል? ” ደስታ ምትኬ አለቀሱ። አለቀሱብኝ። መላልሼ አነጋግሬያቸዋለሁ። ደጋግመው አለቀሱብኝ። ደስታ የሉም። እኔ ቀርቻለሁ።
አላቅሱኝ ልበል ወይ? ወይስ የደስታ ምትኬ ስሜት ያላችሁን ሁሉ እናላቅሳችሁ ወይ? (በነገራችን ላይ ከንቲባ ደስታ ምትኬ የኮሎኔል መንግሥቱን ሥርዓት ለመለወጥ ተነሥተው ከተሰውት ጄኔራል መኰንኖች የአንደኛው የጄኔራል አምሐ ደስታ አባት ነበሩ። የጀግና ልጅ ጀግና) – በተጨማሪ ሊነሳ የሚችለው የጋዜጠኝነቱ ጉዳይ ሲወሳ ደግሞ ኤርትራ በወቅቱ በኢጣልያ ሥር ስለነበረች እንጂ በጋዜጣ ባለሙያነት ረገድ ምጽዋ ውስጥ ይታተሙ የነበሩት ጋዜጦች አዘጋጅ የነበሩት ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላይ ይጠቀሳሉ። እኒህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ደግሞ በጋዜጣቸውና በሌሎችም ጽሑፎቻቸው ቅኝ ገዥውን አምርረው የታገሉ አርበኛ ናቸው። የብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላይ There is no medicine fot the bite of the White Snake ዋናው ነው። የስካንዲኔቪያው ምሁር የፕሮፌስር ተከስተ ነጋሽ ሥራዎች ለዚህ ምስክር ናቸው።
ቀደም ሲል ለጠቀስኋቸው ጋዜጠኛ (ደስታ ምትኬ) ሁለት ጥያቄዎችን አንስቼባቸው ነበር። አንደኛው ጥያቄ “ለመሆኑ የአርበኝነቱ ዘመን- የጀግንነቱ ፍጻሜ” አድዋ ነው ብለው ያምናሉ?” ሁለተኛው ጥያቄ “እቴጌይቱ የምኒልክ ጮማ- የምኒልክ ጠጅ እንዲህ ነው ወይ? ሲሉ ለመሆኑ ያ ሁሉ ሠራዊት የምኒልክን ጠጅና ጮማ ያውቅ ነበር ማለት ነው?” አልኳቸው። አረጋዊው ከንቲባ የምኒልክ ጮማና ጠጅ ይትበሐል ነው። በምኒልክ ጊዜ ሕዝቡ ሰላም ነግሦለት፣ ፍትሕ አግኝቶ ያለሥጋት የሚኖርበት መሆኑን በሙሉ እርግጠኝነት ይናገራሉ። አገር የመጠበቅን እሴት አንሥተው በዚያ መንፈስ ሕዝቡ በአንድነት እየተመመ ወደ ጦር ሜዳ በደስታ እንደ ዘመተ ያወሳሉ።
ኢትዮጵያን የጠበቀ ይህ መንፈስ ነው። ይህ እምነት ነው። ያ ወኔ ነው። የእነዚህ የሦስቱ ባሕርያት ውህደት እየተሸረሸረ መምጣቱን ደግሞ በዓይናቸው በብረቱ አይተውታል። በፋሺስቱ ወረራ ወቅትና በኋላም። በኋላም እስከ እኛ ድረስ! አዎን እንደሚባለው ምኒልክና ጣይቱ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ራስ መኰንን፣ ራስ መንገሻ ወዘተ ያሉትም በማዕዳቸው ከበርካታ ሕዝብ ጋር ይመገቡ እንደነበረ ይታወቃል። በኃላም በዘመኑ <ጋዜጣው ደስታ > በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ከንቲባ (ደስታ ምትኬ) አዋቂነትና የንግግር ስልታቸውን በመጠቀም፤ የአደባባይ እየሱስን ካህናት በማማከር ከመባቻ ጀምሮ ለሰባት ቀናት በጃንተከል ዋርካ ንዋየቅዱሳት ወጥተው ከጸሎት በኋላ ከንቲባው ለሕዝቡን ስለዘመናዊ ትምህርት ጥቅምና አሰራር፣ ስለመምህራኑ ተግባር አስተዋወቁ።
ሜጀር ጀነራል አመሀ ደስታ
አምኃ ደስታ ከከንቲባ ደስታ ምትኬና ከወይዘሮ የሺወርቅ ጎዳና በ 1932 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። (የአምኃ ደስታ አባት ከንቲባ ደስታ ምትኬ የመጀመሪያው የህትመት ጋዜጠኛ ናቸው።) አምኃ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በ1949 ዓ.ም በአውሮፕላን ሜካኒክነት ሙያ አየር ኃይልን ለማገልገል ተቀጥረዋል። የመካኒክነቱን ስልጠና እጅግ ከፍተኛና ልዩ በሆነ ውጤት በመጨረስ ተመርቀዋል። ቁመታቸው ዘለግ ያለ መልከ መልካም ስለነበሩ በወቅቱ የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሰው በግቢው ሲዘዋወሩ አይተዋቸው ከዛሬ ጀምሮ በራሪ መሆን አለብህ ብለው በረራ ትምህርት ቤት እንዲገቡ አደረጓቸው። ትንሽ እንደተከታተሉ በ1950 ዓ.ም ለከፍተኛ የበረራ ሙያ ኮርስ አሜሪካ ተላኩ። እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ ነው ተብሎ የሚገመተውን የበረራ ትምህርት ኮርስ ቀድመው በመጨረስ አስተማሪዎቻቸውን አስደንቀው ተመለሱ።
አምኃ ለሁለተኛ ጊዜ በ1953 ዓ.ም እንደገና ወደ አሜሪካ ተልከው ልዩ የጀት ተዋጊነት ኮርስ ተከታትለዋል። አሁንም እጅግ አመርቂ ውጤት በማምጣት ኮርሱን ጨረሱ። ከነጭም ከጥቁርም እንዲሁም ከሌሎች ዜጎች ሁሉ በአንደኝነት ጨረሱ። በዚሁ ዓመት የምክትል መቶ አለቃ ማዕረጋቸውን አገኙ። ምክትል መቶ አለቃ ሆነው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገሮች የበረራ አገልግሎት አበርክተዋል። እጅግ ብዙ ጀብድ ፈጽመዋል። የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሽልማቶችና ሜዳሊያዎች ተሸልመዋል። ከኮንጎ መንግሥትና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተሰጧቸው ሽልማቶች ቀዳሚ ሆነው ይገኛሉ። በሀገር ውስጥም በተለይ በ1969 ዓ.ም ጦርነት ላደረጉት ርብርቦሽ የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል። በዚህ ወቅት ማዕረጋቸው ኮሎኔል ነበር።
ለጦር ሜዳ ጀብዱ ያበቃቸውን የጦር ሜዳ ውሎ አጥኚ ኮሚቴ የፃፈላቸው የምስክርነት ቃል እንዲህ ይነበባል…”…የምንለው ሁሉ እውነትና በግብር የተሠራ ነው። ኮሎኔል አምኃ ደስታ የምስራቁ ጦርነት ሐምሌ 1969 ዓ.ም በተከፈተበትና የበራሪዎች እጥረት በነበረበት ጊዜ ፋታ ሳያገኝ እስከ አምስት ሶርቲ (ምልልስ) በቀን በመብረር ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል። ይኸውም በጎዴ፣ በደገሀቡር፣ ፈዲስ፣ ጅጅጋ፣ ቆሬ፣ ኮምቦልቻ፣ ኤጀርሳ ጎሮ፣ ሐራዎ፣ ጄልዴሳ፣ አነሮ፣ ባቢሌ ግንባሮች ሲሆኑ፣ በተለይም የጠላት ጦር ድርጅቱን የመደበቅ ከፍተኛ ችሎታ ቢኖረውምና አካባቢውን በተጠናከረ የአየር መቃወሚያ መሳሪያ ቢያጥርም የሀገርን አንድነት ከራሱ በማስቀደም ሚሳዬልና ሽልካ እንዲሁም ሳም- 6 ሳያግደው ተነፃፃሪ የሌለው ተጋድሎ አድርጓል። ሐምሌ 9 ቀን 1969 ዓ.ም የሱማሌ ጦር የድሬዳዋን አየር ጣቢያ ለመያዝ በተቃረበበት ጊዜ ከደብረ ዘይት እየተነሳ በመመላለስ ጠላትን በመደብደብ ተዳክሞ ወደ ኋላ እንዲመለስ ካደረጉት በራሪዎች መካከል አንዱ ነው።
ነሐሴ 6 ቀን 1969 ዓ.ም የጅሬን ጦር ሰፈር ሱማሌ ውስጥ ገብተው እንዲመቱ ከታዘዙት በራሪዎች አንዱ በመሆን በረራውን በመምራት ወደ ኢላማው በሚያመራበት ጊዜ ከ100 የማያንሱ ተሽከርካሪዎች ያለው ኮንቮይ ከጅሬ ወደ ሐራሪት ሲያመሩ መታየታቸው የተሻለ ኢላማ መሆኑን በማወቅ አብረውት ለነበሩት ጉዳዩን ካስታወቃቸው በኋላ በያዙት ሮኬትና ጥይት ስልሳዎቹን ተሽከርካሪዎች ከጥቅም ውጭ በሚያደርጉበት ወቅት ኃላፊነቱን በመውሰድ ተካፋይ ነበር። ሐምሌ 10 ቀን 1969 ዓ.ም ጠላት እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ የድሬዳዋን ከተማ ለመያዝ በታንክ፣ በመድፍና በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በጣም በርካታ በሆነ ፀረ- አውሮፕላን መሳሪያ በመጣበት ጊዜ የአየሩ ሁኔታ ከሰዓት በኋላ ዘግይቶ ሲሻሻል ያለ አፍታ እረፍት ከአንዱ አውሮፕላን ወደ ሌላው በመዝለቅ አውሮፕላን በመቀያየር ቀኑ ከመጨለሙ በፊት ያልተቆጠበ ተጋድሎ አድርጓል።
በነሐሴ 1969 ዓ.ም ጠላት የጂጂጋን ለመያዝ በመጣበት ጊዜ ወገንን ለመከላከልና ከተማይቱን ለማዳን በዝቅተኛ ከፍታ በመብረር ከጠላት ጋር የጨበጣ ያህል ተዋግቷል” በማለት በወቅቱ ተመርጦ የነበረው ኮሚቴ ስለ ጀኔራሉ ተሳትፎ ከጦር ሜዳ የሰበሰበውን መረጃ በመጠቅም ለሽልማቱ እንዲበቁ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ጀኔራል አምኃ ደስታ በተዋጊነት፣ በበረራ አስተማሪነት፣ በምድብ አዛዥነት፣ በምክትል አዛዥነት በመጨረሻም በአየር ኃይል አዛዥነት ኢትዮጵያን ያገለገሉ ፍፁም ሀገር ወዳድ፣ ትጉህ፣ ብልህ ቅን የአየር ኃይል አርበኛ ናቸው። ጄነራል አምኃ ቅርጫት ኳስ ለአየር ሀይል ቡድን ለረጅም ጊዜ ተጫውተዋል። ለኢትዮጵያ የደከመና ለኢትዮጵያ የደማ ሁሉ ኖረንም ሆነ በታሪክ እንዳየነው መጨረሻው አያምርም። የጀነራል አመሀ ጽዋም የሆነው ባልተሳካ የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ሲከሽፍ የመጨረሻው ጽዋቸውን በራሳቸው እጅ ተጎንጭተዋል።