ወንድዬ አሊ
የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓቱ በሕብረት አምባ ቃለ ሕይወት ዛሬ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቱም በቅዱስ ዮሴፍ መካነ መቃብር ይፈፀማል።
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በስነጽሁፍና በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ያሉ ባለሙያዎች የህይወት ታሪክን እያፈላለገ ለንባብ እያበቃ ይገኛል፡፡
የብዙ በሳል የስነጽሁፍ ሰዎች የህይወት ታሪክ በቀላሉ በማይገኝበት በዚህ ሀገር ተግባሩ መአድንን የመቆፈር ያህል ፈታኝና ከባድ ነው፡፡ ታሪካቸውን ከምንሰንድላቸው የግለ-ታሪክ አሰናጅ እንዲሁም ብርቱ ገጣሚዎች ውስጥ ወንድዬ አሊ ይገኝበታል፡፡ በአሁኑ ሰአት በ65ኛ አመቱ ህይወቱ ያለፋው ይህ ታላቅ ሰው ከ25 በላይ መጽሀፎችን ወደ አንባቢ አድርሷል፡፡ ጥር 27 2015 ደግሞ ወንድዬን ለማክበር በሀገር ፍቅር ቴአትር ጠዋት ላይ አንድ መሰናዶ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ አንዱ በጎ ጅምር ስለሆነ ይበል እንላለን፡፡ የህይወት ታሪኩን አረጋ ጋሻው እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡
ጠቅላላው ቤተዘመዱ እና የልቡ ሰዎች ‹‹አባት ወንድዬ›› ነው ብለው የሚጠሩት፡፡ ይህም አንድ ቁምነገር ያስገነዝበናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንኳን በቅርበት ለሚያውቁትና ለታናናሾቹ ቀርቶ በዕድሜ አቻዎቹና ታላላቆቹ ሁሉ የአባትነት መንፈሱ ስለሚገዝፍባቸው ይመስለኛል፤ ‹‹አባት ወንድዬ›› እያሉ የሚጠሩት፡፡
ደረጀ በላይነህ ባንድ ወቅት እንዳለው ‹‹ወንድዬ ዓይናፋር ገጣሚ ነው››፡፡ ከዚያ በላይ ግን ወንድዬ ዓይናፋር ደራሲ፣ አርታኢ፣ ባዮግራፈር፣ የምርምር ሰው፣ ፊልም ስክሪፕት ጸሐፊ … ወዘተም ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ራሱን ‹‹የሥነ ጽሑፍ ወዛደር›› እያለ የሚጠራው፡፡ለዚህም ምክንያቱም፡- ራሱን በገጣሚነት ወይ በደራሲነት፣ አለዚያም በሕይወት ታሪክ ጸሐፊነት … አጥሮ መሰየምን አልወደድም ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡
አባት ወንድዬ በእውነትም ‹‹የሥነ ጽሑፍ ወዛደር›› ነው፡፡ ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ‹‹የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ›› ብቻ ሆኖ ነበር የሰከነ ሕይወት እየመራ ያለው፤ (የአብራኩ ክፋይ የሆኑ ልጆቹንና ዘመዶቹን እያስተማረ፣ ቤት ኪራይ እየከፈለ፣ ችግረተኞችን እያገዘ) . . .፡፡ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ሆኖ ሃያ ያህል ዓመታት የዘለቀ የሥነ ጽሑፍ ሰው የማውቀው ወንድዬን ብቻ ነው፤ ሌላ ሰው ካለ ለመታራም ዝግጁ ነኝ፡፡
የመዘገባቸው ሥራዎቹ ሃያ አምስት ይህል ናቸው፤ ያልመዘገባቸው በርካቶች እንዳሉ ምንም አያጠራጥርም፡፡
አንድ ልጨምር፡- በአባትነት መንፈሱ፣ የኮተኮታቸው፣ ፅንሳቸውን ያዋለዳቸው፣ የጥበብ መንገዱን ያሳያቸው ወጣት ደራሲያን በርካቶች ናቸው፡፡ ለሚተማመንባቸው ለአንዳንዶቹ የጀርባ ጽሑፍ እና መቅድም እንደጻፈላቸው አውቃለሁ፡፡
እንግዲህ የዚህን ሰው እና ‹‹የዚህን ብዙ ሰው›› አጭር ታሪክ ለመጻፍ የተነሳሁት፡፡ ይለናል አረጋ ጋሻው ፡፡
ወንድዬ ዓሊ በ1950 ዓ.ም (እኤአ 1957) በቀድሞው የወሎ ጠቅላይ ግዛት፣ ወረኢሉ አውራጃ ካቤ በምትባል መንደር ታክል ከተማ ተወለደ፡፡ ለወላጆቹ አምስተኛ ልጅ የሆነው ወንድዬ በእናቱ ፍቅር ተምበሽብሾ፣ ወደ ጫና በሚያደላው በአባቱ ጥብቅ ሥነ- ምግባር ተኮትኩቶ አደገ፡፡
ግጥም መግጠም የጀመረው ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ነበር፡፡
‹‹የእናትና አባቴ ትዳር ከፈረሰ በኋላ አባቴ ሌላ ሚስት አገባ፡፡ የእንጀራ እናቴ – በራሷ “ክፉ ቀን! ክፉ ሰው!” ሆነችብኝ፡፡ ፊቷ በገረፈኝ ቁጥር ቁጭቴን የምወጣው ወረቀት ላይ ነበር፡፡ አምስተኛ ክፍል ስደርስ እንጉርጉሮዎቼ አንድ ደብተር ሞሉ፡፡ ጥራዟን “ሲከፉ” የሚል ርእስ አወጣሁላት›› ይላል ወንድዬ አጀማመሩን ሲያስታውስ፡፡
ግጥሞቹ ግን ከባድማ ልቡ ብቻ የወጡ አልነበሩም፤ ከማንበብና መጻፍ በስተቀር ምንም ዘመናዊ ትምህርት ያልቀሰሙት አባቱ ለሕክምናም ሆነ ለፍርድ ቤት ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ባሉ ቁጥር ብርቅዬ ጫማ እና አልባሳት ሳይሆን መጻሕፍት ገዝተውለት ነበር የሚመጡት፡፡ ጦቢያ (የመጀመሪያው ልቦለድ በአፍሪቃ)፣ ወዳጄ ልቤ፣ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም፣ ፀሐይ መስፍን፣ እንቅልፍ ለምኔ ወዘተዎቹን. . . ያነበበው ካቤ መንደሩ ሳለ በኩራዝ ነው፡፡ የንባብ ፍቅር በዚያው ተጠናውቶት ቀረ፡፡
***
በጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ በሚገኘው በታዋቂው የወይዘሮ ስኅን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ደሴ ከተማ በ1965 ዓ.ም (1972 እኤአ) ሲሄድ እንጀራ እናቱ ከሚያደርሱበት ሃበሳ ተገላገለ፡፡ እንጉርጉሮ – ጎርጉሮ የመክተቡም ነገር አብሮ ቀጥ አለ፡፡
ኪነ-ጥበባዊው ደመ-ነፍሳዊ አደራ ግን እንደ ጪስ (ጢስ) መውጪያ ስንጥቅ አታጣምና መንፈሳዊ ግጥሞችን መጫጫር ጀመረ፡፡ በደብረ ዘይት የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ በ1971 ዓ.ም (1978 እኤአ) ገበቶ የደብረ ዘይት መካነ ኢየሱስ ኳየር ሲቀላቀል አምሮቱን ተወጣ፤ 200 ግድም ዜማ-ግጥሞችን (Lyrics) ዘመረ፤ አዘመረ፡፡ ስለ ዜማ-ግጥም ሥራዎቹ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
‹‹እነሱ እኮ! … ግጥሞቼ ሳይሆኑ፣ የዐውደ ዕለት ማስታወሻዎቼ (Diary) ናቸው፤ ግጥሞቼ ደግሞ – ታሪኮቼ››፡፡
ከነፍሱ ጥሪ በተቃራኒ እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የገባው በጊዜው ከነበረው ቀይ ሽብር አደጋ ለመሰወር ያህል ብቻ እንደ ነበረ – ያስታውሷል፡፡
***
ከኮሌጅ ሲመረቅ በሐምሌ 1972 (1980 እኤአ) አርሲ ተመደበ፡፡ በእንስሳት ሐኪምነትና በእንስሳት እርባታ ማኔጀርነት ዘጠኝ ዓመት ተኩል በሠራባቸው ዓመታት እውነተኛ ገጣሚነቱ ተፍለቀለቀ፡፡ በ1984 ዓ.ም (እኤአ 1992) በታተመቺው የመጀመሪያ መድበሉ “ወፌ ቆመች” ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች አብዛኛዎቹ የተጻፉት በአርሲ ቆይታው ነበር፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና ኮተቤ ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት “በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ” ክፍል ለማስተማሪያነት ካሪኩለም ውስጥ ለመካተት የበቃቺው “ወፌ ቆመች” እንግዲህ የእንስሳት ሐኪሙ – የቅኔ ዛር ምጥ ናት ማለት ነው፡፡
የወፌ ቆመች መታተም እና ዝና ኋላ ላይ ፍቅሩም፣ እንጀራውም ወደ ሆነው የሥነ ጽሑፍ ሙያ ይቀላቀል ዘንድ መንገድ ጠረገለት፡፡ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት የሥነ ጽሑፍ ድርጅት ባልደረባ ይሆን ዘንድ ጋበዘው፡፡ (በዚህ ረገድ የአቶ ጌታቸው በለጠ ድርሻ ትልቅ ነበር፡፡ ግብርና ምኒስቴርን ለቆ (ሞፈሩን ሰቅሎ፣ ቀምበሩን ሰብሮ) በትንሽ ደመወዝ በረዳት መጽሔት አዘጋጅነት ተቀጠረ፡፡
‹‹መጽሔት፡- እንደ ‹ቡፌ› ገበታ የተለያዩ መልእክቶች፣ በተለያዩ አቀራረቦች፣ በተለያዩ የአቀራረብ ቀለሞች፣ የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች መከሸን ይገባዋል፤›› ብሎ የሚያምነው
ወንድዬ የቃለ ሕይወትን መጽሔት እንደ ልቡ ናኘባት፡፡ እያንዳንዷን ቅጽ፡- የመጣጥፍ፣ የታዋቂ ሰዎች ፕሮፋይል፣ የቃለ ምልልስ፣ የግጥሞች . . . ገበታ አደረጋት፡፡ (እንዳሰኘው ይጽፍ ዘንድ ሙሉ ነፃነት ያጎናጸፉትን የቅርብ አለቆቹን ያመሰግናል)፡፡
በዚህ ወቅት ነበር ከሥነ ግጥም በተጨማሪ በሌሎችም የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች ለመጻፍ ተሰጥዖ እንዳለው ራሱን ያሳመነው፡፡ በተለይም በታሪክ እና የሕይወት ታሪኮች አተራረክ ረገድ ብዙ እርምጃ ተራመደ፡፡
ለዚህም ነበር፣ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንን ከፊል ታሪክ የሚሸፍነውን (1920-1966 ዓ.ም) ለመጻፍ የቻለው፡፡
በሁለት ቅጽ የተዘጋጁት መጻሕፍት “በመከራ ያበበች” እና “የእኩለ ሌሊት ወገግታ” ይሰኛሉ፡፡ እንደ ቅደም ተከተላቸው በ1990 ዓ.ም እና 1992 ዓ.ም የታተሙ ናቸው፡፡ መጻሕፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የፕሮቴስታንት (ወንጌላውያን) ቤተ እምነት ታሪክ በመሆናቸው በርካታ የሥነ መለኮት ኮሌጆች ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ውስጥ ተካተቱለት፡፡
በዚህ ደስ የተሰኙት አለቆቹ Tear fund England ከሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር ኬኒያ – ናይሮቢ በሚገኘው Daystar ዩኒቨርስቲ የትምህርት ዕድል አመቻቹለት፡፡
በ40 ዓመቱ ተመልሶ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በአራት ዓመት ቆይታ ለመጀመሪያ ድግሪ መርሐ ግብር የተላከው ወንድዬ፣ በሦስት ዓመት ቆይታ የማስተርስ ዲግሪውን ይዞ ተመለሰ፡፡ ይህ ለብዙዎች ታምር ያህል እውነት ነው፡፡ ጥያቄም ነው፡፡
‹‹ሰው እንዴት ከveterinary ዲፕሎማ ተነስቶ በሦስት ዓመት፣ ለዚያውም ለMature Students የሚሰጠውን መሸጋገሪያ ኮርስ (Bridging Course) ሳይወስድ፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ለዚያውም በሦስት ዓመት ብቻ ሊያጠናቅቅ ይችላል?›› ይህን ዝርዝር ለመዘርዘር ውጥኔ አይፈቅድልኝም፡፡
የወንድዬን የአዕምሮ ጉልበትና ሥራዎቹን በደንብ የተረዱ ሰዎች ‹‹ይህን ሰው ለመጀመሪያ ድግሪ ማስተማር “ማባከን ነው” በማለት ከዩኒቨርስቲው ጋር የተሟገቱ እንደ ነበሩ ወንድዬ ያስታውሳል፡፡ የአቶ ወርቁ ኃይለ ማርያምን ግትገታ (ውትወታ) ግን ከሁሉ የበለጠ ነበርና ወንድዬ ሁሌም ያስታውሰዋል፡፡
ወርቁን እና ወዳጆቹን አላሳፈራቸውም፡፡ የመመረቂያ ወረቀቱን፡, “THE CONTRIBUTION OF ORAL LITERATURE IN COMMUNICATING THE GOSPEL TO THE OMOTIC PEOPLE OF SOUTHERN ETHIOPIA: A CASE STUDY OF THE WOLIATE PIONEER EVANGELISTS” በሚል ርእስ ሠርቶ በ2003 (እኤአ) በማስተርስ ድግሪ ተመረቀ፡፡
***
ከናይሮቢ እንደ ተመለሰም የቃለ ሕይወት ሥነ ጽሑፍ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ተመደበ፡፡ ግና ምን ያደርጋል? ሹመቱን ሰጥተው የቀድሞውን ነፃነቱን ነፈጉት፡፡ ከሁለት ዓመት መፍገምገም በኋላ ሥራውን ለቆ Population Media Center (PMC) በኤክስፐርትነት ተቀጠረ፡፡ ጥቂት፣ ግን መልካም የፊደላት የምርት ዘመን አሳለፈ – 2 ዓመት ብቻ፡፡ በክብር ተሰናብቶ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ሆነ፡፡
ሁለተኛዋን የግጥም መድበል “ውበትና ሕይወት” (ወፌ ቆመች – ቅጽ -2) የታተመችው በ1998 ዓ.ም (2005 – እኤአ) ነበር፡፡ ይህም ማለት በ1ኛዋ እና በ2ኛዋ የግጥም መድበል መካከል የ15 ዓመት ግድም ክፍተት አለ ማለት ነው፡፡ በስሎ፣ ሰክኖ፣ ነትሮ ራሱን የገለጠባት መድብል ሆነች፡፡
ከሌላ 17 ዓመት ቆይታ በኋላ 3ኛ ቅጹን ለማሳተም ኮምተራይዝ እያደረገ ይገኛል፡፡ አልፎ አልፎ በፌስ ቡክ በሚለቃቸው ያልታተሙ ግጥሞቹ፣ የወፌ ቆመች 3ኛ ቅጽ አቀማመር ካለፉት ሁለቱ ለየት እንደሚል ያመላክታሉ፡፡ ለኅትመት ጉድ ጉድ ማለቱን የሰማ አንድ ወዳጁ ‹‹የማያርጠው ገጣሚ›› በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሳያሳትማት ዘገየች፤ ‹‹እየታመምን እንጽፋለን፣ እየጻፍን እንታመማለን›› ይላል በራሱ ሲቀልድ፡፡ አሁንም እየጻፈ፣ እየታተመም ነው፡፡ ከህመሙ በኋላ እንኳን አራት መጽሐፎች ታትመውለታል፡፡
***
ስለ ግጥሞቹ ውበትና ለዛ፣ ይዘትና ቅርጽ አብዝተው ከጻፉት መካከል፡- አቶ ዘሪሁን አስፋው (በሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን መጽሐፉ)፣ እንዲሁም ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ (በሥነ ግጥም ማኑዋል መጽሐፉ) ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ሁለቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ናቸው፤ (ብርሃኑ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ያስታውሷል)፡፡ በህትመትሚዲያው ደጋግመው ከጻፉት መካከል ደግሞ፡- ደረጀ በላይነህ፣ ተሻገር ሺፈራው (ዶ/ር) እንዲሁም ወጣቱ ገጣሚ መዘክር ግርማ ይገኙባቸዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ሥራዎቹን ተመርኩዘው የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን የጻፉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች 15 ያህል እንደሆኑ አንድ ወዳጁ ለወንድዬ ነግሮታል፡፡
ታዲያ ምን ያደርጋል፤ ገጣሚውና ሐያሲው ደረጀ በላይነህ ‹‹ዓይናፋሩ ገጣሚ›› ሲል እንደ ገለጸው፣ በእርሱ ዙሪያ የተጻፉትን የትውልድ ቅርሶች ቢያንስ ለልጆቹ እንኳ ሲል ያሰባስባቸው ዘንድ ጥረት አላደረገም፡፡ ይህ ልክ ያለፈ ትህትናው (Humility)፣ ምናልባት ልክ ያለፈ ድካሙ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጋባዡ ብዙ ቢሆንም፣ በመድረክ፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ . . . ትዕይንታት አይሳተፍም፡፡ ከተሳተፈም በጥንቃቄ መርጦ ነው፡፡ ውካታና ሆያ-ሆዬ አይወድም፡፡
***
ወንድዬ፡- ገጣሚ? ደራሲ? Church Historian? Biographer? Researcher? ኤዲተር?
ጥሩ ደመወዝ የሚከፍለውን PMCን በወዙ (1999 ዓ.ም) የተሰናበተው የራሱ ጌታ ‹‹Self-employed›› ሆኖ፣ ከአለቃ የሚሰጠውን ብቻ ሳይሆን የሚወደውን ሥራ ለመሥራት ነበር፡፡ ከኮንሰልታንሲ ተቋማት ጋር ሕብረት ፈጥሮ አንድ ዓመት ያህል የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ሠራ፡፡ ነባራዊውን እውነት ዘወር ብሎ ሲያጤነው ይህኛውም ዓለም “ዘመናይ መሸቀጫ” ሆነበት፡፡ (ጥቂቶቹን የምርምር ሥራዎቹን ጉጉል ያውቃቸዋል)፡፡
ደግነቱ ገና PMCን ሳይለቅ ‹ሁሉን የታደሉ›፣ ነገር ግን ‹ሃሳባቸውን ወደ ፊደል መለወጥ› የማይችሉ ተቋማት እና ግለሰቦች በዝናው አፈላልገው፣ የትርጉም፣ የግለ ታሪክ ዝግጅት፣ የኤዲቲንግ የቤት ሥራዎች ይሰጡት ነበር – ለወንድዬ፡፡
ከደጋግ ወዳጆቹ መካከል አንዱ ‹የቤት ሥራ› በታተመ ቁጥር ሌላውን እየጎተተ ‹‹ሥራ ሲበዛለት›› የኮንሰልተንሲውን ‹‹ሽቀጣ›› እርግፍ አድርጎ ተወው፡፡ ወደ ታሪክና ግለ ታሪክ ዝግጅት ፊቱን አዞረ፡፡
ሕይወት ገፍታ ገፍታ ከነፍሱ ጥሪ ጋር አገናኘቺው፤ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ሆኖ አረፈው፡፡ በሴኩላሩ ዓለም ግን የሚታወቀው በገጣሚነቱ ነው፡፡ አልፎ አልፎ በመገናኛ ብዙኃን ብቅ ሲል፡- ታሪኩን ያጠኑ ጋዜጠኞች፡-
‹‹ማን ብለን እንጥራህ?›› ይሉታል፡፡
“የሥነ ጽሑፍ ወዛደር” የሚል ነበር አጭር መልሱ፡፡
ገጣሚ ብቻ፣ ደራሲ ብቻ፣ ባዮግራፈር ወይንም ኤዲተር … ብቻ መባል፡- ሥነ ልቡናዊ ጥበት ስለ ሚፈጥርበት ወይንም ያው ‹‹ልክ ያለፈ ትህትናው›› ድምር ተፅዕኖ ይመስላል፡፡
ወንድዬ በሥነ ጽሑፍ ወዛደርነቱ የሚያስታውቸውን ኹነኛ ሥራዎቹን አባሪ ማድረጉ ይሻላል፡፡ ዝርዝሮቹን ያነበበ ብቻ ነው፡- ገጣሚ ብቻ፣ ባዮግራፈር ብቻ፣ ኤዲተር ብቻ፣ ሪሰርቸር ብቻ መሆኑን መበየን የሚችለው፡፡
ከማስታውሳቸው ሥራዎች መካከል …
የሥነ ግጥም ሥራዎች
1. ወፌ ቆመች፤ 1984 ዓ.ም፤ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በኮቴቤና በሌሎችም የአካዳሚያ ተቋማት ካሪኩለም ውስጥ የተካተተች)፡፡
2. ውበት እና ሕይወት፤ 1998 ዓ.ም (ወፌ ቆመች ቅጽ 2 እንደ ማለት ናት)፡፡
አጭር ልቦለድ
3. ከሚላ፤ 1998 ዓ.ም፤ (ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር፣ ‹‹ወንዞች እስኪሞሉ›› መድብል ውስጥ ያሳተማት) ተሸላሚ ነበረች፡፡
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ
4. በመከራ ያበበች ቤተ ክርስቲያን፤ 1990 ዓ.ም፤ (የኢትዮጵያ ቃለ ሕወት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ 1920 – 1933)፡፡
5. የእኩለ ሌሊት ወገግታ፤ 1992 ዓ.ም፤ (የኢትዮጵያ ቃለ ሕወት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ 1934 – 1966)፡፡
የሕይወት ታሪክ (ባዮግራፊ)
6. ፈለገ ብርሃኑ፤ 2002 ዓ.ም፤ (የዶ/ር ብርሃኑ ሃብቴ የሕይት ታሪክ)፡፡
7. የሕይወት ጉዞዬ፤ 2010 ዓ.ም (የጀ/ል ታዬ ጥላሁን የሕይወት ታሪክ)፡፡
8. በእሳት የተፈተነ ሕይወት፤ 2012 ዓ.ም (የወይዘሮ በቀለች ባቾሬ ትዝታዎች)፡፡
9. ትዕግሥት በቁመናው፤ 2013 ዓ.ም (የሲዳማው አቶ ቲቦ የሕይወት ታሪክ)
10. ሺፈራው፡ በፊደላት ሥዕል፤ 2013 ዓ.ም (የአቶ ሺፈራው ወ/ሚ የሕይወት ታሪክ)፤ ምናልባት የኔ ዋናዬ (ማስተርፒስ) የምለው ሥራዬ ነው፡፡
11. ያልባከነ ዕድሜ 2015 ዓ.ም (የወ/ሮ ዐመለወርቅ አበበ) የሕይወት ታሪክ፡፡
በ‹‹ኤዲቲንግ›› ስም ያዘጋጀኋቸው ወይንም ዳግም የጻፍኳቸው እና የታተሙቱ
12. ተስፋዬ በእግዚአብሔር ጥላ ሥር፣ 2014 ዓ.ም (የቄስ ተስፋዬ ዲነግዴ የሕይወት ታሪክ) በኦሮሚኛ ተተርጉሟል፡፡ የተመረቀው አሜሪካን አገር ነው፡፡
13. ትውስታዬ፤ 2010 ዓ.ም (የአቶ ሚሊዮን በለጠ የሕይወት ታሪክ)፡፡
14. BEYOND THE FAIRY Tale “ከገራገር ወጎች ማዶ ብዬ እንደገና የተረጎምኩት” 2009 ዓ.ም (የዶ/ር መስከረም ክፈተው መጽሐፍ)፡፡
15. ሕይወቴና ጰንጠቆስጤአዊ እንቅስቃሴ አጀማመር፤ 2009 ዓ.ም (የዶ/ር ዘለቀ ዓለሙ የሕይት ታሪክ)፡፡ (እምብዛም የማልደሰትበት ሥራ)
16. የታምራት አምላክ ታምረኛ፤ 2008 ዓ.ም (የታምራት ኃይሌ የሕይወት ታሪክ)፡፡
17. የማኅበር አህያ ፤ 2007 ዓ.ም (የአቶ ተክሌ ወልደ ጊዮርጊስ የሕይወት ታሪክ)፡፡
18. የምድረበዳው እረኛ ፤2005 ዓ.ም (የዶ/ር ጥበበ የሕይወት ታሪክ) በጣሙን የምኮራበት ሥራ ነው፡፡
19. ጥበበ ሕጥወት፤ 1996፣ (የሕይወት ክኅሎት መመሪያ/ማኑዋል)
ያልታተመ
20. ድምፅ ዐልባው ሞገድ፤ 2009 ዓ.ም (የኢቫሱ ታሪክ፤ ምናልባት ‹ሺፈራው በፊደላት ሥዕል›ን ሊያስከነዳ የሚችለው ይህ መጽሐፍ ብቻ ነው፡፡)
አርትዖት ብቻ፡-
21. መንፈስ ቅዱስ ፤ 1989 ዓ.ም (የቢሊ ግራሃም የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ)፡፡
የፊልም ጽሑፎች፡-
22. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጉዞ፤ 2011 ዓ.ም፡፡
23. ትውልድም እንደ ዐባይ (ለልዕሥምማ – 2000 ዓ.ም) ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከመጀመሩ በፊት የተሠራ ዶኪዩመንተሬ፡፡
24. ሰው ማለት ምንድነው? (2005 ዓ.ም)
በመጠናቀቅ ላይ ያሉ መጻሕፍት
25. ብርሃን ይሁን፤ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ)
26. የግንባር ሥጋው፤ (የሕይወት ታሪክ)
ትዳር የለውም ወይ?? ካለው ባለቤቱ መጠቀስ አያስፈልጋትም ወይ?? ጥያቄ ነው። ትዳር ካለው ባለቤቱን አለመጥቀስ ፅሁፋችሁን ሁሉ ከንቱ ያደርገዋል። ምክንያቱም ታደለች መንገሻ የምትባል እህት ባል ነው ሲባል ስለሰማሁ ነው። እኔም የማውቃት ብርቱ እህት ናት።