ከብካብ አስፋው

ከብካብ አስፋው

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በሚድያው ዘርፍ አንዳች አሻራ ያኖሩ ሰዎችን ለታሪክ እያስቀመጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም መዝገበ-አእምሮ በሚል በጠንካራ ሽፋን የተሰናዳ መጽሀፍ ታትሞ ማስመረቁ ይታወቃል፡፡ በቁጥር 2 መዝገበ- አዕምሮ ላይ ታሪካቸውን ከምንሰንድላቸው የሚድያ ሰዎች መካከል ከብካብ አስፋው ትጠቀሳለች፡፡ ከብካብ በኢትዮጵያ ቲቪ ለ 8 አመት ፣ በዋልታ ሚድያ እና ኮርፖሬት ደግሞ ለ 9 አመት በድምሩ 17 አመት ያገለገለች ባለሙያ ናት፡፡ ከብካብ አስፋው፣ በተለይ በዘጋቢ ፊልም ሥራዋ ትታወቃለች፡፡ የህይወት ታሪኳን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

ልጅነት እና ትምህርት

ትውልዷና እድገቷ ኑሮዋም ጭምር እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ የካቲት 11 1974 የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በገዳመ ስታዊያን ማርያም ፂዬን ት/ቤትና በምስካየ ኸዙናን መድሀኒያለም ትምህርትቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በየካቲት 12 ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ዩኒቨርሲቲን ስትቀላቀል በምርጫዋ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በኢትዮጲያ ቋንቋዎችና ሥነ-ፅሁፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀበለች፡፡ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በጆርናሊዝም ነው የተመረቀችው፡፡ ከዛው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፡፡

ራስን ፍለጋ

የልጅነት ዘመኗ በነፃነት የተሟላ ነው፡፡አባቷ አቶ አስፋው ሺበሺ ለሥነ-ፅሁፍ እጅግ የቀረበና በቀድሞው ኩራዝ አሳታሚዎች ድርጅት በአርታዒነትና በደራሲነት ሥራ ይሰራበት በነበረበት ጊዜ ነበር የእርሷም የራስን ፍለጋ ጉዞ የተጀመረው፡፡መፅሀፍ እንደእህል ውሀ በብዛት የሚገኙበት የመፅሀፍት መደርደሪያን ደጋግማ የመጎብኘት እድሉ ነበራት፡፡ለእድሜዋ ታስበው ከተዘጋጁ መፅሀፍት ይልቅ ልቦለዶችና የግጥም መድብሎች ቀልቧን ይገዙታልና በድብቅ ደጋግማ አንብባቸዋለች፡፡በተለይም የፀጋዬ ገ/መድህንን እሳት ወይ አበባን ሳታነብ ያንቀላፋችበትን ቀን አታስታውስም፡፡መፅሀፍትን ስታነብ ደግማ ደጋግማ ነው፡፡ ገፀ- ባህሪያቱ በቅርብ ከምታውቃቸው ቤተሰቦቿ እኩል ያሉ እስኪመስላት ታስባቸዋለች፡፡ ሲያዝኑ አዝናለች፡፡ ሲደሰቱ ደስታቸው ተጋብቶባታል፡፡ ኑሯቸውን በቅርብ የምትከታተል ያህል ገጠር ከተማውን ከነሱ ጋር ቃኝታለች፡፡ድካማቸውን ደክማ በስኬታቸው ተደስታለች፡፡
በልጅነት እድሜዋ ከሥነፅሁፉም በላይ በሙዚቃ ትማረክ ነበር፡፡

እንደውም በቤት ውስጥ ከወንድሟና ከወንድሟ ጓደኞች ጋር በመሰረቱት ባንድ ውስጥ የዘፋኝነት ስራው የእርሷ ነበር፡፡በባንዱ የተገለበጡ ቆርቆሮዎች በድራምነት ማማሰያ እንደ ሳክስፎን መጥረጊያ እንደክራር ሲያገለግል ጭልፋ ደግሞ ማይክራፎን በመሆን ባንዱን ሙሉ ባንድ አድርገውታል፡፡በዚህ ባንድ ውስጥ የከብካብ ስራ አዳዲስ ዘፈኖችን አጥንቶ መዝፈን ሲሆን ማታ ማታ ለቤተሰቡ አባላት የሚቀርበውን ኮንሰርትም ባስተዋዋቂነትና በድምፃዊነትም ትመራው ነበር፡፡ይህ ስራ ከቤት አልፎ ወደ ትምህርት ቤት ቢሻገርም የባንዱ አባላት ከሷ በቀር መምህራንና ተማሪዎች ፊት ማቅረብን ይፈሩ ስለነበር በቤት ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንዲቆይ ሆነ፡፡አባቷም ድምፃዊ የመሆን ፍላጎቷን ሲያይ ዘፋኝ ልትሆን ይሆን? የሚል ሀሳብ ያድርበት ነበር፡፡

የሥነ-ፅሁፍን ስራን ፍላጎቷን ለመግለፅ ደጋግማ ትጠቀምበታለች፡፡አንድ ቀን በቤት ከተረፈች አንድ ብርቱካን ላይ አይኗ አረፈ የቤቱ ደንብ ተካፍሎ መብላት ነውና ድርሻዋን ብቻ ለይታ መብላት ጀመረች፡፡ ብርቱካኑ ግን ጣፋጭ ነበረ፡፡ ማቆም ፡፡ ተጨማሪ በላች፡፡ ቀጠለች ጨረሰችው፡፡አሁን ፀፀት ተሰማት ወንድሟን ይቅርታ ማለት ይጠበቅባታል እናም ወረቀትና እስኪሪብቶዋን ተጠቅማ ሂደቱን ፃፈችው፡፡ ለወንድሟ ስትሰጠው ከመገረም አልፎ አቅፎ ሳማት፡፡ በጣም እኮ ጎበዝ ነሽ ሲላት አንድ ነገር በአእምሯዋ ተጫረ፡፡ ለካ መፃፍ እችላለሁ አለች፡፡ይህ አጋጣሚ ለስነፅሁፍ ስራዋ በር ከፋች ነበር፡፡የ4ኛ ክፍል ተማሪ ሆና ለ11ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሥነፅሁፍ ስራቸውን ደጋግማ ሰርታለች፡፡ላገኙት ውጤትም ምስጋናቸውን በጠጠርና በዱላ ከረሜላ ገልፀውላታል፡፡

እናም ሥነፅሁፍን በትምህርት ማገዝ ህልሟ ሆኖ አብሯት አደገ ፡፡ለዚህም ነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ስትቀላቀል በፍላጎቷ የቋንቋና ሥነፅሁፍ ተማሪ የሆነችው፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ መድረክ ያገኙ ስራዎችን ጨምራ በጓደኞቿ ዙሪያ የሚመላለሱ ስራዎችን ሰርታለች፡፡እየተማረች የብእር ስጦታዎች ሲሰጧትም ለጋዜጠኝነት ስራዋ ትቆጥብ ነበር፡፡ አንድ ቀን ጋዜጠኛ እንደምትሆን ግን ተጠራጥራ አታውቅም ነበር፡፡

ከብካብና ኢቲቪ

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተመረቀች በስድስት ወሩ ኢቲቪ ለመዝናኛ ክፍል ባልደረባ የሚሆኑ ጋዜጠኞችን ማወዳደር ጀመረ፡፡ለመቅጠር የሚፈልገው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡የፅሁፍ ፈተናውን ለመፈተን ወስና ስትሄድ ግን አይኗን ማመን አልቻለችም፡፡ከሷ በቀር ሁሉም ሰው ታዋቂ ነበር፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የማልፈው? አለች ግን መሞከርን አልጠላችም ሞከረች፡፡በሚገርም ሁኔታ ከዛ ሁሉ ሰው መሀል ተመርጣ አንደኛ ወጥታ ኢቲቪን ተቀላቀለች፡፡ የካቲት 1/1997 ዓም ለሷ ይሄ ህልም የሚመስል አጋጣሚ ነበር፡፡ የስሟ ለየት ማለትና በወቅቱ በርከት ያሉ ፕሮግራሞችን የማዘጋጀቱን እድልም ስላገኘች ታዋቂ ለመሆን ጊዜ አልፈጀባትም፡፡በተለይ ደግሞ ቀደምቶቿ የጀመሩትን ብታምኑትም ባታምኑትም የሚለውን ፕሮግራም የሀገር ውስጥ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች በመፈለግ መጀመሯ እራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ባለተሰጥኦዎችን ለማግኘት አቅም ፈጥሮላታል፡፡ የእሁድ መዝናኛ እንግዳና አርሂቡ ደግሞ ስሟን የተከለችባቸው የኢቲቪ መሰናዶዎች ናቸው፡፡

በአርሂቡ ፕሮግራሞች በኪነጥበቡ ዘርፍ ትልቅ አሻራን ከጣሉ ከሳክስፎኑ ንጉስ ከጋሽ ጌታቸው መኩሪያ፤ከኩኩ ሰብስቤ፤ከሀይሉ ፀጋዬ፤ከቀድሞ የህዳሴ ግድቡ ኢንጂነር ከኢንጂነር ስመኘው እና ኢ/ር አዜብ አስናቀን የግጥምና ዜማ ደራሲ አበበ መለሰንና ፀጋዬ ደቦጭንና ሌሎች በርካታ ሰዎችን በእንግድነት አቅርባ ልምድና ህይወታቸውን እንዲያካፍሉ አድርጋለች፡፡ በሂደት በሪፖርተርነት የተቀላቀለችውን ሙያ እስከ አዘጋጅነት ሰርታበታለች፡፡ ቀጥታ ስርጭቶችን የመምራት አጋጣሚዎቿ ነበሯት፡፡ ዶክመንተሪዎችንም የመስራት እድሎችንም አግኝታለች፡፡ በተለይም በዜማው ሊቅ በቅዱስ ያሬድ ዙሪያ የሰራችው ዶክመንተሪና ከክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ ህልፈት ጋር ተያይዞ ህይወቱን የሚዘክረው የዘጋቢ ፊልም ስራዋ በኢቲቪ ቆይታዋ ከተመሰገነችባቸው ውስጥ የሚጠቀስ

ከብካብና ዋልታ

አሁን ዝንባሌዋ ወደ ዶክመንተሪ አድልቷል፡፡ እናም ፍላጎቷን ይበልጥ እውን የምታደርግበት ተቋም ላይ ማማተር ጀመረች፡፡ የሀገሬ ዶክመንተሪዎችን ከሳይት ኢትዬጲያዊው ናሽናል ጆግራፊ ከሚሰራበት ተቋም ተቀላቀለች፡፡ የዶክመንተሪ አዘጋጅ ሆና፡፡ሐምሌ1/2005ዓ.ም፡፡
እዚህ ሁሉም ነገር ይለያል፡፡ በጥቂት ባለሙያዎች ብዙ ስራዎችን የመስራት ኃላፊነት ሀገርን አይቶ የማሳየት ተግባር ከእያንዳንዱ ስራ ጀርባ የበርካቶችን ደሞዝ ተሸክሞ የመስራት ኃላፊነት፡፡እናትነትና ጉዞ የቀናት ብቻ ሳይሆን የወራት ጉዞ ኃላፊነቱን መወጣት የሚቻለው በሙያ ፍቅር ብቻ ነው፡፡ሀገርን በሁሉም አቅጣጫ የማየት እድለኝነት ለካ ኢትዮጲያ ውብ ናት፡፡ ህዝቦቿ እንግዳ ተቀባይ አላምደው የሚያስቀሩ ቋንቋቸው ስብጥር እነሱ ግን አንድ አይነታቸው ለየቅል እነሱ ግንፍቅር የሆኑ ህዝቦች መኖሪያ፡፡

የበረሀውን ሙቀት የመልክአ ምድሩን ውበት የወንዞቿን ፍሰት የአትክልቱን የፍራፍሬውን የባህላዊ ምግቦቿን ጣእም ከነሙሉ ክብሩ በፍቅር ተቋድሳለች፡፡
የእግር መንገዱን ውጣ ውረዱን በመሰረተ ልማቱ አለመመቻቸት ተፈትናለች፡፡ውርጩን ንፋሱን ዝናቡን አቧራና ጭቃውን ተጉዛበታለች፡፡ ከሰሜን እስከደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ያልፈተሸችው ጓዳ የለም፡፡ በዋልታ ቆይታዋ አድናቆት ያተረፈችባቸውና እርሷም በፍቅር ከምትገልፃቸው ዶክመንተሪዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን የተሰራው አቴቴ፤በደቡብ ክልል ያሉ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ግን ከዘርፉ ብዙም ያልተጠቀምንባቸውን ቦታዎች ያሳየችበት ያልታዩ ውበቶች ዶክመንተሪ፤ኢትዮጲያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸውን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ያስቃኘችባቸው ከራስ ያለፉ ትሩፋቶች አሁን ላይ ደግሞ ባለው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ዳግማዊ አድዋ፤የመካነ ስብእናና ሌሎችም ዶክመንተሪዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እነዚህ አመታት ለሷ ጋዜጠኝነትን ወደ ልእልና ማእረጉ ያደረሰችባቸው ናቸው፡፡ከብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች ጀርባ ሆና በብእሯ ሁነቶችን ዘግባለች፡፡ ውብ ባህሎች ነጥረው ወጥተዋል፡፡ የተቀነበቡ ስራዎችን በብእሮቿ አስቃኝታለች፡፡ በክዋኔ ከትውልድ ትውልድ የተሸጋገሩ እሴቶች መሀል ተገኝታም የታሪኩ አካል ሆናለች፡፡ በእነዚህ ጥቂት አመታት ውስጥ ብዙ የሚባሉ ዶክመንተሪዎችን ሰርታ አየር ላይ አውላለች፡፡ስለሥራዋም ተቋሟን ጨምሮ ብዙዎች እውቅናን ሰጥተዋታል፡፡

ከብካብ እንደ ሥራ መሪ

በኃላፊነት ከኤዲተርነት(አዘጋጅነት) ጀምሮ በየደረጃው ባሉ ሙያው በሚጠይቃቸው እርከኖች ላይ አልፋለች፡፡ በዶክመንተሪና ደንበኞች ክፍል በዋና አዘጋጅነት እንዲሁም በዳይሬክተርነት በትምህርታዊ ክፍል በዳይሬክተርነት በመዝናኛ ክፍል በዳይሬክተርነት እንዲሁም አሁን ላይ ዋልታ አዲስ በከፈተው የአፍሪካን ታሪክ ባህል አሴት ወግ ልማድ ማንነትና ውበት ለማጉላት በተቋቋመው የአፍሮ ኒውስ ቻናል የቻናል ማናጀር በመሆን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ለከብካብ ጋዜጠኝነት ከሙያም በላይ ሱስ ነው ፡፡ ከብካብ ለሚድያ ስራ ነው የተፈጠርኩት ብላ ታስባለች፡፡ በመሆኑም ከጋዜጠኝነት ስራ ውጭ ሌላ ምንም አይታያትም፡፡ ከብካብ አብረዋት በሰሩት ሰዎች በጥሩ መልኩ ይመሰከርላታል፡፡ ሺበሺ አለማየሁ በአሁኑ ሰአት በፋና ቲቪ የዶክመንተሪ ክፍል የስራ መሪ ሲሆን የከብካብ አስፋው አለቃ ሆኖ ያላትን ትጋት በቅርበት ለመረዳት የቻለ ነው፡፡ ሺበሺ እንደሚለው ከብካብ ካሉት ሴት ጋዜጠኞች ዘጋቢ ፊልም የመሥራት ሙሉ ብቃት ያላት ጋዜጠኛ ነች፡፡ ከመዝናኛ ፕሮግራሞች አንስቶ እስከ ዘጋቢ ፊልም ስራ ድረስ ጥንቅቅ አድርጋ መስራት እንደምትችል ሺበሺ ይመሰክራል፡፡ በአስተባባሪነትም ሙሉ ኃላፊነት የሚጣልባት ብርቱ ጋዜጠኛ ናት ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *