እስከዳር ግርማይ

እስከዳር ግርማይ -ዛሬም ለጥብብ ፍቅር ያሳደረች

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ እና ቻት ጂፒቲ ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል።

ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል።በተጨማሪም በሳይንስ፣ በመምህርነት ፣በምህንድስና እና በሌሎችም ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ አንባቢ እያመጣን እንዲታወቁ ጥናትና መረጃ ማድረግ ለሚሻም ተደራሽ ስናደርግ ቆይተናል።

የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።

እስከዳር ግርማይ ደራሲና በማህበራዊ ጉዳይ ላይ የተሰማራች አገር ወዳድ ስትሆን የሕይወት ታሪኳም መዝገበ አእምሮ ቅፅ 2 ላይ እንደሚከተለው ተሰንዷል።

ውልደት እና ልጅነት

እስከዳር ግርማይ እኤአ በ1977 አ.ም ወልድያ ከተማ ተወለደች። በልጅነቷ ኮረምና አሰብ ያደገች ሲኾን፣ ከፍ ስትል ወደ ዐዲስ አበባ በመዛወር አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ‹ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ›፣ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ‹ሽመልስ ሀብቴ› ት.ቤት እንዳጠናቀቀች ብዙም ሳትቆይ ወደ ባህሬን ተሰደደች።

የሥነ ፅሑፍ ዝንባሌ የባህሬን ቆይታ

ከልጅነቷ ጀምሮ ለሥነ ጽሑፍ ፍቅር የነበራት እስከዳር ገና ኻያ ዓመቷን ሳትደፍን ብትሰደድም፣ በልጅነቷ ኢቲቪ የልጆች ፕሮግራም ላይ በነበረ ውድድር ላይ በመሳተፍ፣ የቅጠል ዐይነቶችን ጥቅምና ጕዳታቸውን በጽሑፍና በአልበም መልክ ሠርታ በማቅረብ ከአሸናፊዎቹ አንዷ በመኾን ከአባባ ተስፋዬ ሣህሉ እጅ ሽልማት ተቀብላለች።በሰው አገር ብትኖርም፣ ከሥነ ጽሑፍ ብዙ አልራቀችም። ባህሬን በሚገኝ ‹ሬድ ሀውስ ማርኬቲንግ ሚዲያ ሀውስ› የሚያሳትመው መጽሔት ላይ ለዐምስት ዓመት አገልግላለች። ከማርኬቲንግ ሥራዋ በተጨማሪም በፋሽን ‹ስታይልሲት›ነት ሠርታለች። በዚህ ሥራዋ ላይ በነበረችበት ጊዜም፣ በሚወጡት ዕውቅ መጽሔቶች ላይ የኢትዮጵያ አልባሳት፣ አትሌቶች፣ አርቲስቶችና የኢትዮጵያን ምግብ እንዲሁም የአገር ገጽታ የሚወክሉ ዜናዎች በሚዲያ እንዲወጡ በማድረግ አገሯን አስተዋውቃበታለች።

በተጨማሪም፣ በበጎ ፈቃደኝነት ታገለግልበት ለነበረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በባህሬን ‹ሐበሻዊ› የተሠኘ መጽሔት ዐብረዋት ከሚያገለግሉት ጋራ በመኾን አዘጋጅታለች።ባህሬን ላይ የአገሯን የኢትዮጵያን ባህልና ትውፊት ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ የአገሪቱንና ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ውድ እንቊዎችንና አልባሳትን በማስተዋወቅ በሞዴልነት ትታወቃለች፡፡ ጥላሁን ገሰሰን፣ ንዋይ ደበበን፣ ዶ/ር ምሕረትን፣ አዜብ ወርቁን፣ ጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉን እና መሰል ሰዎችን ወደ ባህሬን በእንግድነት በመጋበዝ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሥነ ጽሑፍ፣ ከኪነት እና ከስፓርት ጋራ እንዲገናኙ አድርጋለች።

በበጎ ፈቃደኝነት ለረዥም ዓመታት ለረጅም ጉዜ በኮሚኒቲው አመራር አባልነትና ለጥቂት ዓመታት አገሯን በመወከል በክብር ቆንስላነት ያገለገለችው እስከዳር ግርማይ፣ በ2020 ‹ሰላም› እና ‹ሴቶች በዚህ ወር› በተባሉ መጽሔቶች የባህሬን ባለሥልጣናትንና ባለሀብቶችን ጨምሮ በአገሪቱ ከሚኖሩ ሌሎች ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል ተካታለች።የክብር ቆንስላ ኾና በባህሬንና በአገሯ ኢትዮጵያ መካከል ላደረገችው የባህል አስተዋፅኦም ከአገሪቱ የውጭ ጕዳይ ሚንስቴር የምስጋና ደብዳቤ ተሰጥቷታል። ወገኖቿን ለበርካታ ዓመታት በበጎ ፈቃደኝነት በማገልገል የኖረችው እስከዳር፤ በቤት ሠራተኝነት ወደ ባህሬን ለሚጓዙ ተጓዦች የሚያገለግል ሰነድ፣ በአነስተኛ መጽሔት መልክ በማዘጋጀት ባህሬን ከመግባታቸው በፊት በዐምስት ቋንቋ ተዘጋጅቶ እንዲደርሳቸው አድርጋለች።የአባይ ግድብ መጀመሩን አስመልክቶ ‹አባይ› መጽሔትን በዋና አዘጋጅነት አሰናድታ ከ500,000 ብር በላይ አሰባስባ ገቢ አድርጋለች። እኤአ በ2019 ‹ዲስከቨር ኢትዮጵያ› በሚል ርእስ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት እንዲሁም ለቱሪዝም እንዲያስቧት የሚገፋፋ መጽሔት በእንግሊዝኛ በማዘጋጀት፣ ለጋዜጠኞች፣ ለመንግሥታዊ ተቋማት፣ ለታዳሚዎችና ለኢንቨስተሮች እንዲዳረስ አድርጋለች።

የመፅሐፍት ሥራዎቿ እና ወደ ፊልም ጉዞ

በ2014 ዓ.ም ‹‹ኢትዮጵያዊ አገሩ የት ነው?›› ብላ የሰየመችውን የመጀመሪያ መጽሐፏን ለንባብ አብቅታለች፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ‹‹አልተማርኹም›› የሚል ጽሑፏን በማስታወሻነት በ‹ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ› አንደኛ እና ለ‹ሽመልስ ሀብቴ› ኹለተኛ ደረጃ ት.ቤቶች ዐማርኛ ላስተማሯት መምህራን አበርክታለች። መጽሐፉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችና አርቲስቶች በተገኙበት የዕለቱ የክብር እንግዶች የ‹‹አሮጌ መጻሕፍት ሻጮች›› በታደሙበት ተመርቋል፡፡በምረቃው ዕለት አንዱ መጽሐፍ ከ50 ሺህ ብር ጀምሮ የተሸጠና ከ250,000 ብር በላይ የተሰበሰበ ሲኾን፣ የዕለቱን ሙሉ ገቢ በልጅነቷ የመጻሕፍት ፍቅር እንዲያድርባት ላደረጉት፣ ‹‹ማዕቀብ›› በተሠኘ መጽሐፍ ላይ ታሪካቸውን በማንበብ በዕለቱ የክብር እንግዳዎቿ ላደረገቻቸው ‹‹አሮጌ መጻሕፍት ሻጮች›› ምስጋና ለማቅረብና በሕመም ምክንያት ላልተገኙትም መታከሚያ ይኾን ዘንድ በስጦታ አበርክታላቸዋለች።

እስከዳር፣ ‹‹የፈረንጅ ሚስት›› የተባለ በራሷና መሰል ሰዎች ታሪክ ላይ ያጠነጠነ ኹለተኛና ‹‹ናፍቆት›› የተባለ የዐጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ሦስተኛ መጽሐፎቿን ለንባብ አብቅታለች። ‹‹የፈረንጅ ሚስት››ን ወደ እንግሊዝኛ ስትመልሰው፣ እንግሊዛዊው ክርስቲያን ሀሪሰን አርትዖቱን የሠራው ሲኾን፣ መጽሐፏ እኤአ በ1919 በተመሠረተውና በዐረብ አገራት በርካታ ቅርንጫፍ ባለው ዝነኛው ‹ጃሻማል ስቶርስ› ውስጥ ይሸጣል፤ ‹አማዞን› ላይም ይገኛል።በቅርቡም በሞሮኮዋዊ ተርጓሚ ወደ ፈረንሳይኛ የተቀየረው ለንባብ ይበቃል።

‹‹ናፍቆት›› በሚለው የዐጫጭር ልቦለዶች ስብስቧም እኤአ በ2024 የክብር አዋርድ አሸናፊ ኾናበታለች፡፡እስከዳር፣ ‹‹ጥቊር እንግዳ›› የሚል፣ በማደጎ ተወስዳ ወደ ኢትዮጵያ ወላጆቿን ፍለጋ የተመለሰች ጋዜጠኛ ታሪክ ላይ በሚያጠነጥን ፊልም በመሪ ተዋናይነት ተሳትፋ ፊልሙን ፕሮዲውስ አድርጋለች። የራሷ ድርሰት በኾነው ኹለተኛ ፊልሟ ‹‹ሰውነቷ›› ፊልም ላይም በፕሮዲውሰርነትና በመሪ ተዋናይነት ተሳትፋለች፡፡ ፊልሙ የሕገ ወጥ ስደትን አደገኛነት በማሳየት፣ ሕጋዊነትን እንዲሁም ከኅብረተሰብና መንግሥት የሚጠበቀውን መፍትሔ ይጠቊማል።እኤአ በ2014 ለእይታ የበቃው ‹‹ጥቊር እንግዳ›› ለመጀመሪያ ጊዜ የዐረብ አገር ባለሥልጣናትና ታዋቂ አርቲስቶች በተገኙበት በሲፍ ሞል በሚገኝ ሲኒማ ቤት ተመርቋል፡፡ በአዲስ አበባ ብሔራዊ ቴአትር ሲመረቅ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ተገኝተው የመረቁ ሲኾን፣ በ2019 ኹለተኛ ፊልሟ ‹‹ሰውነቷ›› ሲመረቅ ደግሞ የቀድሞዋ ክብርት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በ‹ሐያት ሪጄንሲ› ሆቴል ተገኝተው መርቀዋል።

እስከዳር ግርማይ በባህሬን የመጀመሪያው የሴቶች መጽሔት ለኾነው ‹ውመን ዚስ መንዝ› የብራንድ አምባሳደር ከመኾኗም ባሻገር የመጽሔቱም ተባባሪ ኤዲተር ኾና በመሥራት ላይ የነበረች ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት በግል ሥራዎቿ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *