አብዱልከሪም ጀማል አባገሮ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በቴአትር በስነጽሁፍ እና በፊልም ዘርፍ የጎላ የሚና ያላቸውን ሰዎች ታሪክ እየሰነደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስራ በጀመሩበት ዘመን ካሉት ባለሙያዎች የተሻለ አፈጻጸም እና ጉልህ አሻራ የነበራቸውን ለይቶ በማውጣት የስራ እና የህይወት ታሪካቸውን ያስቀምጣል፡፡ ይህም ወደፊት በሚታተመው መዝገበ-አእምሮ ላይ የሚካተት ይሆናል፡፡ ከእነዚህ ታሪካቸው ከሚሰራላቸው ጠንካራ ባለሙያዎች አንዱ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዳይሬክተር የሆነው አብዱልከሪም ጀማል ነው፡፡ ባንቺአየሁ አሰፋ እና እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡
በሀገራችን በምእራብ ኢትዮጵያ ከምትገኘው ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ጅማ፣ 45 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ባለች አጋሮ በተሰኘችው ከተማ ነበር የተወለደው፡፡ ጅማ የበርካታ ታላላቅ የጥበብ ባለሙያዎች መፍለቂያ እንደመሆኗ መጠን የባለ ብዙ ሙያ ዘርፍ ባለቤት የሆነውን የታላቁ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዳይሬክተር ፣ ተዋናይ ፣ ሀያሲ እና አዘጋጅ አብድልከሪም ጀማልንም ከማይነጥፍ ማህፀኗ አፍርታለች ፡፡ አብዱልከሪም መካከለኛ የሚባል የኑሮ ደረጃ ካላቸው እና ዴሞክራቲክ ከሆኑ ወላጆች የተገኘ፣ እንደማንኛውም ህፃን ከእኩዮቹ ጋር ቦርቆ ያደገ ሲሆን ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በራስ ደስታ ዳምጠው ት/ቤት እስከ 6ኛ ክፍል ሲማር ከ 7- 12ኛ ክፍል በአጋሮ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቋል፡፡ በዚህ የትምህርት ቤት ቆይታው ታዲያ ከመምህራኖቹ እና ከትምህርት ጓደኞቹ ጋር እጅግ ተግባቢ እና በትምህርት ቤቱ ባሉ ክበባት ሁሉ ተሳታፊም እንደነበር ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር በነበረው ቃለ-ምልልስ ወቅት የኋሊት ተጉዞ ዘመኑን ያስታውሳል፡፡
እንደስነጽሑፍ፣ ቀይመስቀል፣ ሚኒሚዲያ፣ ፀረ-ኤድስ፣ ፀረ-ዕፅ እና ሀገርህን እወቅ የመሳሰሉ ክበባት ውስጥ ጎድሎ አያውቅም፡፡ በጊዜያዊ እና ዓመታዊ የክበባት ክብረ-በዓል ላይ መርሀ-ግብሮችን በማዘጋጀት፣ በመምራት እና በማስተባበር ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ አብዱልከሪም እንደሚለው ከሆነ ታዲያ የያኔው የክበባት ተሳትፎ እና የመምህራኖቹ እንዲሁም የትምህርት ጓዶቹ ወደፊት እንዲገፋበት የሚሰጡት ማበረታታት አሁን ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቶለታል፡፡
የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ በ 1995 ዓ.ም ወደ መዲናችን አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት ለ 1 ዓመት ገደማ ያህል በ Holy Land Art ጥቂት የሰርተፍኬት ሥልጠናዎችን ወስዶ በ1996 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማታ መርሃ-ግብር በቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተወዳድሮ ገባ፡፡ በ 2000 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡ በሙያው ተጋብዞ ሥራዎችን እየሰራ በ 2003 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በቴአትር ሙያ ተቀጠረ፡፡ የቴአትሮች አዘጋጅ፣ ገምጋሚ እና ተዋናይ በመሆን ቴአትር ቤቱን እና የጥበብ ዘርፉን በሙያው አገልግሏል፡፡ በቴአትር ትወና 7 ያህል ቴአትሮችን የተጫወተ ሲሆን የ13 ወር ፀጋ፣ ክሊዮፓትራ፣ የቬኑሱ ነጋዴ፣ ረመጥ፣ የጉድ ቀን፣ አሉ፣ የበአል እንግዶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቴአትር ዝግጅት፡- ገፅ ሁለት ፣ ገራገር ፣ በቴሌቪዥን ድራማ ትወና፡- ደንብ አምስት (ሲትኮም) ፣ ዘጠነኛው ሺህ (ሲትኮም)፣ በቴሌቪዥን ድራማ ዝግጅት ከ 80 በላይ አጫጭር ድራማዎች በመስኮት የአዲስ ቲቪ ዝግጅት እና ችሎት የኢቲቪ መዝናኛ አዘጋጅቷል፡፡ በፊልም ትወና:- ስርየት ፣ቁልፉን ስጪኝ ፣ ኮመን ኮርስ ፣ ልእልት ፣ ዱካ : ፎርጅዱ ፣ ቪአይ ፒ በፊልም ዝግጅት:- ፎርጅዱ : ቪአይፒ ከሰራቸው ሥራዎች ለአብነት የጠቀስናቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
አብዱልከሪም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ውስጥ የቴአትር ባለሙያ ሆኖ ለጥቂት ጊዜ ያህል ጊዜ ካገለገለ በኋላ ለ 4 ዓመት ያህል የቴአትር ክፍሉ ዋና ኃላፊ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በወርሃ መስከረም 2012 ዓ.ም የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ /`Director ሆኖ በኃላፊነት ቦታ ላይ ተሹሟል፡፡ የቴአትር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሥራ ከጀመረ በኋላ የቴአትር ቤቱን ውስጣዊ እና ውጫዊ ገፅታ በማሻሻል እና በመለወጥ ለቴአትር አፍቃሪው ምቹ እንዲሆን አድርጓል፡፡
መነቃቃት እንዲፈጠርም አስችሏል፡፡ አብዱልከሪምን ተከትለው በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዉስጥ ከመጡ ዋና ዋና ለውጦች መካከል ምቹ ያልሆኑና ለዓይን የሚጎረብጡ የተመልካች ወንበሮችና አጠቃላይ መጋረጃዎች በጥራት፣ በጥንካሬና ውበት ዘመናዊ ሆነው ተቀይረዋል፡፡ በግቢው ውስጥ ለፀጥታ አስቸጋሪ የነበረው መጠጥ የሚሸጥበት መዝናኛ ክበብ ተለይቶ ለብቻ ራቅ ተደርጎ ተሰርቷል
- ለጋለሪና ለሚኒ ላይብረሪ የሚሆን ቦታ በአዲስ ተደራጅቶ ተዘጋጅቷል
- የዘመናዊና ባህላዊ ሙዚቃ ስቱድዮ አዲስ ተሰርቷል
- በአጠቃላይ ጊቢውና የስራ ቦታው ያማረና ለስራ የሚያነሳሳ ሆኗል::
አብዱልከሪም የቴሌቪዥን ፊልምና ድራማን በተመለከተ በርካታ አጫጭር ኮርሶችን ወስዷል፡፡ በ 2008 በ Theatre and Development ማስተርሱን ይዟል፡፡ የማስተርስ ትምህርቱን ጥናት የሰራውም በህፃናት ቴአትር ላይ ሲሆን በዚህም ዘርፍ ሰፊ ሥራን መስራት እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ አብዱልከሪም የተለየ የህይወት ፍልስፍና የሌለው በሙያዉ ሀገሩን የሚያገለግል ባለሙያ ሲሆን በግል ህይወቱም ባለትዳር እና የ 3 ልጆች አባት ነው፡፡