አበበ አንዱአለም

አበበ አንዱአለም

የኢዜአ ታላቅ ሰው

አቶ አበበ አንዱአለም፣ በጠንካራ የሚድያ ሰውነታቸው ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ናቸው፡፡ ግለ-ታሪካቸውን ከቤተሰቦቻቸው ያገኘን ሲሆን እንደሚከተለው አጠናክረነዋል፡፡

ጋዜጠኛ አበበ አንዱአለም ከአባቱ ከአቶ ዋሴ እና ከእናቱ ወይዘሮ አካሌ ደረሰው ደብረ ማርቆስ ከተማ አጠገብ ከሚገኘው ስናንጭሮ ወረዳ ልዩ ስሙ ደብረዘይት ከሚባል ደብር መስከረም 19 ቀን 1925 ተወለደ፡፡ አበበ፣ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜ ያሳለፈው በገጠር ነበር፡፡ በ1934 ዓ.ም ደብረማርቆስ ከተማ ከአጎቱ ከአለቃ አንዷለም አያናው ቤት በሚኖርበት ጊዜ ተክለሃይማኖት አንደኛ ደረጃ ት ቤት ሲመዘገብ በአጎቱ በአለቃ አንዷዓለም አያናው ስም ስለተመዘገበ አበበ አንዱአለም ተብሎ መጠራት ጀመረ።

አበበ በ1939 ዓም በአገር አቀፍ ደረጃ ጄነራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ት ቤት የሚሰጠውን ፈተና ከአንድ ጓደኛው ጋር አልፎ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በ1941 ዓ.ም በዚሁ አጠናቀቀ። ከዚያም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሲመሰረት ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ነበር። ሆኖም በችግር ምክንያት የኮሌጅ ትምህርቱን አቋርጧል። ከዚያም ሲቪል አቪዬሽን ት/ ቤት ገብቶ በአየር ምርመራ በሰርተፍኬት ተመርቋል።
የነፃ ትምህርት ስላገኘ አሜሪካን አገር ከሚገኘው ፔንሲልቬንያ ስቴት ዩኒቨርሲቲም በአየር ምርመራ ምርመራ ዲፕሎማ አግኝቷል።
ሁለት አመት ያህል በአየር መርማሪነት ካገለገለ በኋላ ዝንባሌው ስነፅሁፍ ስለሆነ በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ ተቀጥሮ የእንግሊዝኛው ክፍል ምክትል አዘጋጅ እና ተጠሪ በመሆን 3 አመት አገልግሏል።

ለሁለተኛ ጊዜ የነፃትምህርት ዕድል ስላገኘ አሜሪካን አገር ከሚገኘው ከታወቀው የሚዙሪ ስቴት ዩንቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት የመጀመሪያውን ዲግሪ ካገኘ በኋላ የድህረ- ትምህርቱን እንዳገባደደ የነፃ ትምህርቱ ጊዜ ስላለቀ ወደ አገሩ ተመልሷል። በ1957አ.ም ማስታወቂያ ሚኒስትር ተቀጥሮ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ካቋቋሙት ከመሩት ጥቂት ኋላፊዎች መካከል አንዱ ሲሆን እስከ 1967 ዓም ድረስ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ አገልግሏል።

ከዚያም ለአንድ አመት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ለአንድ ዓመት የማስታወቂያ ሚኒስትር ቋሚ ተጠሪ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ የጽ/ ቤት የውጭ ግንኙነት የፕሬስ አገልግሎት ኃላፊ ለ3 አመት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት በቢዝነስ ዲቨሎፕመንት ስራ አስኪያጅ ሆኖ በመንግስት መስሪያ ቤት 28ዓመታት ካገለገለ በኋላ በ1980 ዓም በጡረታ ተገለለ። በዚሁ አመት ለታዋቂው አሶስዬትድ ፕሬስ ለሚባለው የአሜሪካ ኢንተርናሽናል የዜና አገልግሎት በኢትዮጵያ ወኪል ሆኖ እስከ ነሐሴ 1 1995አ.ም ድረስ አገልግሏል።

በ 1959 ዓም ከወይዘሮ ሸዋረግ ታደሰ ጋር የህግ ጋብቻ ፈፅመው ሀይማኖት አበበ፣ አለማየሁ አበበ እና ዳዊት አበበ የተባሉ ልጆችን ወልደዋል፡፡ እንዲሁም ትእግስት አበበ የተባለች የልጅ ልጅ አይተዋል። አቶ አበበ ባደረባቸው ህመም ለብዙ ጊዜ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ1996 በተወለዱ በ70 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *