አምባሳደር ተስፋዬ መካሻ በ92 አመታቸው አረፉ

አምባሳደር ተስፋዬ መካሻ

1918 – 2010

አምባሳደር ተስፋዬ መካሻ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በምክትል ሚኒስትርነት ከ36 አመት በላይ ያገለገሉ፣ የሀገር ባለውለታ ሲሆኑ መጋቢት 11 2010 ህይወታቸው አልፏአል፡፡ የቀብር ስነ-ስርአታቸውም ቅዳሜ መጋቢት 15 2010 በእንጦጦ ኪዳነ-ምህረት ተፈጽሞአል፡፡

አምባሳደር ተስፋዬ መካሻ ከአባታቸው ከአቶ መካሻ አማረና ከእናታቸው ከወይዘሮ የሸዋአረግ መንገሻ በከፋ ከፍለ ሃገር ሸራዳ ከሚባል የገጠር ከተማ በነሐሴ 9 ቀን 1918 ዓ ም ተወለዱ። ( የሂሳብ ስሌት ለያዛችሁት የሚመጣው ነሐሴ ሲደርስ 92 ዓመታቸውን ይደፍኑ ነበር) አባታቸው አቶ መካሻ አማረ በጤንነት እክል ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ሲገደዱ ሕጻን ተስፋዬን ሴት አያታቸው ወይዘሮ አስካለ አምበርብር ኃላፊነቱን ወስደው አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረጉ የልጅ ልጃቸውን አሳድገዋል።

ወይዘሮ አስካለ በዘመኑ ልማድ መሠረት ወደ ቤት የሚመጣ አስተማሪ ለሕጻኑ ተስፋዬ ቀጥረውለት፤ አማርኛንና ግእዝን ጠንቅቆ በመማር በሰባት አመት እድሜው ዳዊት አስደግመው፤ መርቀው ለቀጣይ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ ሸኝተውታል። በዘመናዊውም ትምህርት አዲስ አበባ ላይ በአድቬንቲስት ሚሲዎን አንደኛና ሁለተኛ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው፤ ለከፍተኛ ትምህርት እንግሊዝ አገር ወደ ሚገኘው ወደ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተልከው በትምህርት ላይ ሳሉ፤ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ላንድ አመት ያህል ያልጋ ቁራኛ ሆነው አሳልፈዋል።

ይህም ሕመም በሕይወታቸው ዘመን በሙሉ የዘለቀ የመስማት መሳን ቢያደርስባቸውም፤ ብሩህ አንጎልና የነቃ የማሰብ፤ የማስተዋል ችሎታ ስለነበራቸው የደረሰባቸውን የጤንነት መሰናክል ወደጎን በማድረግ እንደተሻላቸው ቤይሩት ወደሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ አምርተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በክብር ለመቀበል በቅተው ነበር።

ከዚያም ወደስራው ዓለም በማቅናት ለ36 ዓመታት አገራቸውንና ወገናቸውን በቅንነትና በትጋት ለማገልገል በቅተዋል። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ- መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በልዩ ልዩ ክፍል ሰርተው እስከ ምክትል ሚኒስትር ማዕረግ ደረሰው ነበር። ከዚያም በደርግ ዘመን ዋና የፖለቲካ አማካሪ በመሆን በተለይ በአለም አቀፍና በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የተለየ ችሎታ በማካበታቸው እጅግ ብዙ በሆኑ በተከታታይ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤዎችና በአፍሪካ አንድነት የመሪዎች ስብሰባዎች የኢትዮጵያ መልክተኛ ሆነው ከመሳተፍም በላይ፤ ኒውዮርክ በሚገኘው ሚሲዎን በምክትል አምባሳደር ማዕረግ አርኪና አጥጋቢ አገልግሎት ሰጥተዋል። እንዲሁም በዚያኑ ዘመን የገለልተኞች መንግሥታት ኮንፈረንስን በተመለከተ ከወቅቱ መሪ ጋር በመሆን በፍሪታውን፤ በኒው ዴልሂ እና በሀቫና ስብሰባዎች ላይ ከፍተኛ አማካሪ ሆነው አገልግሎት አቅርበዋል።

በወቅቱ የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ ጉዳዮች በስሜት የተወጠሩት ባለሥልጣኖች የአገሪቱን ዘላቂ ጥቅሞች አጉል መንገድ እንዳይሄዱ በዘዴ መክረዋል። አምባሳደር ተስፋየ ፈጣን የንባብ ችሎታ ስለነበራቸው፤ በየጉባኤው የሚቀርቡትን አከራካሪ ጉዳዮች ፈልፍለው ምስጢሩን ቶሎ በመረዳትና አስፈላጊውንም የተቀናጀ መልስ በማዘጋጀት በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ ስብሰባዎች ላይ የኢትዮጵያ ልኡካን ተደናቂነት እንዲያተርፉ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የአማርኛም ሆነ የእንግሊዝኛ ድርሰታቸው እጅግ ተደናቂ ነበር።

አምባሳደር ተስፋየ አንድ ዓለም አቀፋዊ ዜና አያመልጣቸውም ነበር። ስለወቅታዊ ጉዳዮችም የሚያቀርቡት ትንታኔ መሬት ጠብ አይልም። አምባሳደር ተስፋየ ጨዋታና ወግ ይወዱ ነበር። ይህም ሲሆን በልበ ሙሉነታቸው ቁጡና አትንኩኝ ባይነታቸው አይዘነጋም። ከአለቆቻቸው ጋር ቅርበት የሚፈጥሩ ከመሆናቸውም በላይ ይከበሩ ነበር።

ከረጅም ጊዜ ወዳጃቸውና አለቃቸው ከክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ጋር በጣም ይዋደዱ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በደርግ ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከነበሩት ከኮሎኔል ፈለቀ ገድለ ጊዎርጊስ ጋር አብረው ሲሰሩ እጅግ ተቀራርበው ነበር። ለምታውቋቸው ክቡር ሚኒስትር ፈለቀ ቶሎ ቶሎ ግልፍ ግልፍ የሚላቸው ሰው ነበሩ። ተስፊሽ ታድያ ፈሉ ብሎ ሲያነጋግረው ሚኒስትሩ የተሞከሸ እየመሰለው ፈገግ ፈገግ ሲል በውስጠ ወይራ ግን እንደውሃ ፈሉ የሚለው ትርጉም የገባቸው ይስቁ ነበር።

አምባሳደር ተስፋየ ለወዳጆቻቸው ተቆርቋሪና እስከመጨረሻው ታማኝ ነበሩ። የቅርብ ወዳጃቸው የነበሩት የኢትዮጵያ ቁርጠኛ ቀን ልጅ ክቡር ፕሮፊሰር አስራት ወልደየስ ባሳዛኝ ሁናቴ ካረፉ በኋላ ከማንም ይበልጥ አስበው፤ ተከራክረው፤ ተቆጣጥረው ተመጣጣኝ መታሰቢያ ሐውልት እንዲሰራላቸው ያደረጉት ትግል መቸም ቢሆን አይዘነጋም።

ለወጣቶች፤ ለመጭው ትውልድ ይሰጡት የነበረው መልእክት በአገራችሁ ኩሩ ጠንክራችሁም ስሩ የሚል ነበር። አምባሳደር ተስፋዬያጋጠመቸውን የአካል እክል በጸጋ ከመቀበልም በላይ የመንፈሳዊ ሃይል ምንጭ በማድረግ ለብዙዎች ተምሳሌት ነበሩ። ኒውዮርክ ከተማ በኢትዮጵያ ሚሲዎን በሚያገለግሉበት ጊዜ ወደአዲስ አበባ ለሥራ ተጠርተው እንደመጡ፤ እድለኛ አጋጣሚ ሆኖ የትዳር ባልደረባቸውን ወይዘሮ እሌኒ ጣሰው ዋለሉን በማግኘት ትዳር መስርተው የሁለት ወንዶች ልጆች አባት ከመሆንም በላይ በጠቅላላው የሶስት ልጆችና የሶስት ልጅ ልጆች አያት በመሆን ጌታ የፈቀደላቸውን የሕይወት ዘመን በደስታና በጸጋ አሳልፈዋል።ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ለመላ ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡





Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *