አልታየወርቅ ዘለቀ

ከመጀመሪያዎቹ የቴአትር ጥበባት ተመራቂዎች አንዷ

አልታየወርቅ ዘለቀ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ሥራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡

ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ? የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 185 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር የፊልም ሰዎች ታሪክን አሰባስበናል። በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል ከመጀመሪያዎቹ የቴአትር ጥበባት ምሩቃን መካከል አንዷ ናት። ከእነ ማንያዘዋል እንደሻው ጋር በ 1974 የተመረቀችው ይህች ባለሙያ እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ በባህል ሚንስቴር በሙያዋ አገልግላለች። በአሁኑ ሰዓት በባህር ማዶ የምትገኘው ይህች ሴት ወይዘሮ አልታየወርቅ ዘለቀ ትባላለች። እዝራ እጅጉ እና አይናለም ሀድራ የህይወት ታሪኳን አሰናድተውታል።

ውልደትና ትምህርት

በህጻናት ቲያትር ጅማሮ ስማቸው ከሚነሳ ቀዳሚ ባለውለታዎች አንዷ የሆነችው አልታየወርቅ ዘለቀ በአዲስ አበባ አምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም አካባቢ ከአቶ ዘለቀ አቦዬና ከወ/ሮ ሃረገወይን አማረ በ1950 ዓ.ም ተወለደች። አልታዬ ለቤተሰቧ 2ተኛ ግን ደግሞ የመጀመሪያ ሴት ልጅ ናት።

ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ አቅራቢያዋ ባለው ናዝሬት ትምህርት ቤት ትምህርቷን ተከታትላለች። በትምህርት ቤት ቆይታዋ ጭምት የምትባል አይነት ልጅ የነበረች ስትሆን ወዳጅነታቸው ዛሬም ድረስ የዘለቀ ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ አብረዋት የነበሩ በርካታ ጓደኞችን አፍርታለች።

11ኛ ክፍል እንደደረሰች ለውጥ መጣና የወቅቱ መሪ ጓድ መንግስቱ ሃይለማሪያም የዕድገት በህብረት ዘመቻን በማወጃቸው ዘመቻውን ተቀላቀለች።ከዘመቻ መልስ የማታ ትምህርት ተምራ ማትሪክ በመውሰድ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ በማስመዝገቧ በ1971 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግባት ቻለች።

በወቅቱ ትምህርት በኮታና በምደባ ነበርና ለመመማር ያልፈለገችው ትምህርት ክፍል ተመደበች።የተሸለ አማራጭ በማፈላለግ ላይ ሳለችም የቲያትር ትምህርት ክፍል መግባት የሚፈልጉ ተማሪዎች እድሉ እንደሚሰጣቸው በመስማቷ ቲያትር መርጣ መማር ጀመረች።

አልታዬ ወርቅ ከሚሚ ስብሃቱ፣ አዲስ ህዝቅያስና ገነት ኢሳያስ ጋር የመጀመሪያዋ ሴት የቲያትር ተማሪ ነበረች።ገነት ኢሳያስ በመሃል ብታቋርጥም 3ቱ ሴቶች አብረው እየሰሩ እየተጋገዙ ማሳለፋቸውን ትናገራለች።በጊዜው ከነበሩት የውጭ ዜጋ መምህራን በተጨማሪ እነ ሃይማኖት አለሙ፣ ተስፋዬ ገሰሰና መንግስቱ ለማም አስተምረዋታል።

የስራ ህይወት

በ1973 ከ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቀች ባህል ሚኒስቴር ተመደበች። በወር 500 ብር ደሞዝ እየተከፈላት በኤክስፐርትነት የህጻናት ቲያትር ክፍልን ተቀላቅላ ለ9 አመታት አገልግላለች።ያን ጊዜ ክፍሉን አለምጸሃይ ወዳጆ ትመራው እንደነበር ታስታውሳለች።

የህጻናት ቲያትርን አስመልክቶ እምብዛም ግንዛቤው አልነበረምና በዚህ ዙሪያ ማንበብ እውቀትን መሰብሰብን ቀዳሚ ሃላፊነት አድርጋ ቆየች።ያገኘችውን እውቀት ይዛ የህጻናት ቲያትር ቤት ለማቋቋም የሚያስችል ማንዋል አዘጋጀች። ከተለያዩ ኤምባሲዎች የባህል አታሼዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የህጻናት ቲያትርን አስመልክቶ የየሃገራቸውን ልምድ ለመቅሰምም ችላለች።በተለይም ከጀርመን የባህል ማዕከል ጋር ቅርብ ግንኙነት ነበራቸው።

አልታየወርቅ ባደረገችው ጥረትም ህጻናትን የሚመጥን ስራ ለመስራት ልምዱ ካላቸው ሃገራት ዳይሬክተር አስመጥተው የህጻናት ቲያትር ማሳየት ችለዋል።ከዛ ባሻገር ህጻናትን የሚያሳትፉ በርካታ ውድድሮችና ጨዋታዎች በክፍሉ እንዲከወኑ አስተዋጽኦ አበርክታለች።

የህጻናት ቲያትር ወወክማ የሚያስፈልገውን መሳሪያዎች በሙሉ ከጃፓን አስመጥታለች። ከተለያዩ ሃገራ ጋር ተጻጽፋም ለክፍሉ ገንዘብ አሰባስባለች።ቀድሞ ቀድሞ በህጻናት ቲያትር ክፍል ሙዚቃና ውዝዋዜ ይቀርብ የነበረ ሲሆን አልታዬና ባልደረቦቿ የህጻናት ቲያትር እንዲታይ እንዲጀመር እድል ፈጥረዋል።ቲያትር ሲጀመርም በልጆች ዘንድ እጅግ አስደሳችና ተወዳጅ የነበረ ሲሆን በርካታ ተመልካቾችም ነበሩት።ከቲያትር በተጨማሪም ድራማዎችና የአሻንጉሊት ትዕይንቶች እንዲጀመሩ አድርጋለች።

ስራው በዚህ መልኩ ቅርጽ እየያዘ ቢሄድም የጊዜው ሹመኞች ባንድም በሌላም በሚያሳድሩት ተጽዕኖ አልታዬ የምትፈልገውን እርቀት መሄድ አልቻለችም።የቅርብ የስራ መሪዋ የነበረችው አለምጸሃይ ወዳጆ የሰውን ሃሳብ በቅጡ የምትረዳ ከየትኛውም ተጽዕኖ የምትከላከልላቸው ብትሆንም አልታዬ ስራዋን በነጻነት መስራት አልቻለችም ነበር።

ስደት

አልታየወርቅ ጫናው በርትቶባት በ1982 ዓ፣ም ለዕረፍት ሃገረ አሜሪካ እንደሄደች በዛው ቀረች።በኢትዮጲያ የህጻናት ቲያትርን መሰረት ከጣሉ ቀዳሚ ባለሙዎ አንዷ ብትሆንም በገጠማት ተጽዕኖና ጫና ከቲያትር ጋር ተቆራረጠች።

በሃገረ አሜሪካ ከቲያትር እጅግ ርቃ IT በመማር ኑሮዋን በዛው መስርታለች።

One thought on “አልታየወርቅ ዘለቀ

  1. ይድረስ ለተወዳጅ ሚዲያ አዘጋጆች፣
    አልታዬወርቅ ዘለቀን በተመለከት ያቀረባችሁት አጭር ባዮግራፊክ ዘገባ ፣ አነበብኩት ፣ ልትመሰገኑበት የሚገባ ሥራ ነው ።
    በወቅቱ እኔም የስፍስት ኪሎ ተማሪ ስለነበርኩ እና ጨርሰን ከተመረቅን በሗላም በባህል ሚኒስቴር በአንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት አብረን ስለሰራን አልታዬወርቅ ዘለቀን ከወጣትነት ጀምሮ ለረጅም ጊዜ አውቃታለሁ ፣ የቅርብ ጓደኛሞችም ነበርን ። ከተፃፈው በላይ አልታዬወርቅ ዘለቀ በጣም ጥልቅ እውቀት ያላትና ብዙ ያነበበች ምሁር ነች ። የተፈጥሮ ፀባይዋም ሰው አክባሪና ትሁትነቷ ተወዳዳሪ አይገኝለትም ።
    አልታዬወርቅ ዘለቀና ጋደኞቿ (እኔንም ጨምሮ) አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የገባነው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1970 ዓ.ም ነበር (በ1971 ተብሎ የቀረበው ስህተት ነው ) ። እነርሱ ፪ተኛ አመት ላይ ወደ ቲያትሪካል አርትስ ሲገቡ እኔ ሂስትሪ ዲፓርትመንት ገባሁ ። እነ አልታዬወርቅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያዌቹ የቲያትሪካል አርትስ ተማሪዎችና የመጀመሪያዎቹ ተመራቂዎች ነበሩ ። አብረው የመጀመሪያዎቹ ተመራቂሴቶችም ፣
    አልታዬወርቅ ዘለቀ
    ሀዲስ
    ሚሚ ስብሀቱ ብቻ ይመስሉኛል ።
    የእነርሱ ባች ወንዶቹም ብዙዎቹ ጓደኞቻችን ነበሩ፣
    አሊሹ ሙሜ
    ይግረም ረታ
    ክፍሌ እንግዳሰው
    ዘሪሁን
    አበበ አዲስ
    ማንያዘዋል
    በቀለ ተፈራ
    ትዝ ይሉኛል ። ዛሬ ዘሪሁንና ክፍሌ በህይወት እንደሌሉ ሰምቻለሁ ፣ ሌሎቹ ግን የት እንደደረሱ አላውቅም ?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *