ነቢይ መኮንን

ገጣሚ እና ተርጓሚ

ነቢይ መኮንን

ገጣሚ ጸሀፌ ተውኔትና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን ፣ከአባቱ ከአቶ መኮንን ወንድም እና ከእናቱ ከወይዘሮ በለጤ በድሉ በነሐሴ ወር 1946 አ.ም በናዝሬት በአሁኑ አጠራሩ በአዳማ ከተማ ተወለደ፡፡

ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመግባቱ አስቀድሞ፣ መምህር ተከስተ ጋር የቄስ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን እዚያም ዳዊትን በቃሉ በመሸምደድ የማስታወስ ችሎታውን አዳብሯል፡፡

ተርጓሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን፣ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በዚያው ናዝሬት (አዳማ) አጼ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት ሲሆን በትምህርት አቀባበሉም ጎበዝ እንደነበር ይነገራል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበሩት አባቱ ለትምህርት ትልቅ ፍቅር ያሳደሩ ነበሩ። ነቢይ፣ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ህይወታቸው ያለፈው አባቱ አቶ መኮንን ወንድም ልጃቸው በትምህርቱ ብርቱ ሆኖ እንዲገኝ ምክር ይለግሱት ነበር፡፡ ነቢይም፣ ከክፍሉ የአንደኝነትን ደረጃ በመያዝ አባቱን ደስ ለማሰኘት ሞክሯል፡፡ በልጅነቱ፣ ከትምህርት ባለፈ በናዝሬት ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር አይረሴ ትዝታን ያሳለፈው ነቢይ በህይወት ሳለ ያንን የልጅነት ትዝታውን ሲያወጋ ብዙ ጉዳዮችን ከማስታወሱ ባሻገር ለሰው የሚነግርበት መንገድም እጅግ ማራኪ ነበር፡፡ ሀሣቦችን ኪናዊ ለዛ ባለው መልኩ የመግለጽ ችሎታውም ወደር አይገኝለትም ።

ነቢይ መኮንን ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ልኡል በእደ ማርያም ተማሪ ቤት ከገቡ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ነበር፡፡ በመቀጠልም በ1966 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ በመግባት ኬሚስትሪን በዋናነት ሲያጠና በሁለተኛ ማይነር ደግሞ ሂሳብን በማድረግ አይረሴ የኮሌጅ ህይወትን አሳልፏል ። በጊዜው በተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ከነበሩ ስመ ጥር ሰዎች ጋርም ከህሊና የማይጠፉ ገጠመኞችን አሳልፏል ። ነቢይ ስለ ሁለተኛ ደረጃ ትዝታው ሲጠየቅ አብረውት ያሳለፉት እንደ ወይዘሮ አስካለ ነጋ ፣ ወንድምአገኝ ማሞ የመሣሠሉትን አብሮ አደጎቹን ሳይረሳ ያነሳቸዋል።

ነቢይ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኬሚስትሪ ትምህርቱን የተከታተለ ቢሆንም በጋዜጠኝነት፣ በተርጓሚነት እና በደራሲነት በርካታ ሥራዎችን ለአንባቢያን ያበረከተ ታላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነበር።

በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን አዲስ አድማስ ጋዜጣን ከመሠረቱት ባልደረቦች አንዱ የነበረው ነቢይ ከመሥራቹ አሰፋ ጎሳዬ ጋር በመሆን ለአዲስ አድማስ ዕድገት ሌት ተቀን የለፋ ሠው ነበር።

የአዲስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ መኮንን፣ በጋዜጣው ላይ በየሳምንቱ በተረት እና ምሳሌ እያዋዛ በሚጽፋቸው ርዕሰ አንቀጾች ይታወቃል። እነዚህ ርዕሠ-አንቀጾች ጥልቅ ሀሣብ በውስጣቸው የያዙና በአቀራረብም አዲስና ፈጠራ የታከለባቸው ነበሩ።

የአዲስ አድማስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ ከዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ ከማብቃቱም በላይ በትወናም ተሳትፏል።

የእዚህ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ጭብጥ ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ሲሆን፣ ታዋቂዎቹ አበበ ባልቻ እና ፈቃዱ ተክለማሪያም እና ፍቅርተ ጌታሁንን ጨምሮ ራሱ ነቢይ መኮንን እና ሌሎችም ታዋቂ ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

ሜጋ ኪነጥበባት ማእከል ከዛሬ 32 አመት በፊት ሲመሰረት መስራች ከነበሩት አንዱ የነበረው ነቢይ መኮንን፣ በጊዜው በሜጋ ኪነጥበባት ማእከል አሳታሚነት ትወጣ የነበረችውን ‹‹ፈርጥ›› የኪነ-ጥበብ መጽሄትንም በዋና አዘጋጅነት ይመራ ነበር፡፡ ነቢይ፣ ከዚህ በተጓዳኝ በኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኦፍ አፍሪካ በኮሚኒኬሽን አማካሪነት የሠራ ሲሆን በበርካታ ሀገራት ጉብኝት በማድረግም የህይወቱን ጣእም ለመለካት ሞክሯል፡፡ ከሄደባቸው ሀገራትም መካከል ፈረንሳይ ፣ ጀርመን ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ዛምቢያ፣ አሜሪካ ፣ኬንያ፣ ሱዳን እና ኢራን ይገኙበታል፡፡

ነቢይ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ” እና “ጁሊየስ ቄሳር” የተሰኘ ተውኔቶችንም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል።

“ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ነቢይ ባለካባ እና ባለዳባ በተሰኘው ተውኔት ላይም በትወና ተሳትፏል።

“ስውር ስፌት” የተሰኘ የግጥም መድብል በሁለት ቅጽ ለንባብ አብቅቷል።

በደርግ ዘመን በኢህአፓ አባልነት ለ10 ዓመታት የታሰረው ነቢይ፣ በእስር ቤት እያለ ‘ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ’ የተሰኘውን ታዋቂ ረጅም ልቦለድ መጽሐፍን ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ በሚል ወደ አማርኛ ተርጉሞ ለንባብ አብቅቷል።

ነቢይ ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ የተሰኘውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ እስር ቤት ሳለ ነበር የተረጎመው።

ይህንንም የትርጉም ሥራውን በሲጋራ ወረቀት ላይ እየጻፈ በድብቅ ከእስር ቤት በማስወጣት በመጨረሻ ሲፈታ መታተሙን በሕይወት እያለ ተናግሯል።

ነቢይ “የኛ ሰው በአሜሪካ” – የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ሲወጣ ቆይቶ፣ ኋላ ላይ በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃ ሌላኛው ሥራው ነው።

ሌላው ለንባብ የበቃው የነቢይ መጽሐፍ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲሆን “ዘ ላስት ሌክቸር” የሚለው መጽሐፍ ትርጉም ነው።

የማይሰለች፣ ጨዋታ አዋቂው፣ ፈገግታ የማይታጣበት ነብይ ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም፣ የእውነትና የግልጽነት ድምጽ ጭምር እንጂ። ጥልቅ የሆኑት የዘገባና የትንተና ሥራዎቹ የተወሳሰበውን ባህል፣ ታሪክና ፖለቲካችንን መልክ አስይዞ ፍንትው አድርጎ የማሳየት ብቃቱ ምስክሮች ናቸው። በህይወት ዘመኑ ከፍትህና ከእውነትጋ ቆሞ፣ መስዋዕትነትንም ከፍሎ በመረጃ የዳበረ፣ በውይይት የጎለበተ ማህበረሰብን ለመፍጠር ነቢይ የበኩሉን ጥሯል።

የነብይ ግጥሞች ነፍስና ስጋ ያላቸው ህያው ፈጠራዎች ናቸው። የሰውን ስብዕናና መንፈስ ጠንቅቆ ለመረዳቱ ምስክሮች ናቸው። ውስጥን የሚገልጹና ዘልቀው የሚሰሙም ናቸው። የቃላቱ ውበት፣ ከሃሳብ ጥልቀት ጋ ታጅቦ የፍቅርን፣ የማንነትን፣ የጽናትንና ሌሎች የሰብዕና መገለጫ ስሜቶች ነጸብራቅ ሆነው ለሁላችን፣ ከሁላችን ጋ ይኖራሉ።

ሥራዎቹ የሃገራችንን ስነጽሁፍ አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ ካገዙ ምጡቅ ስራዎች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው። ነብይ አስተምሮናል፣ አዝናንቶናል፣ የውስጣችንን እሬት በማር ለውሶ አውጦናል፣ ማህበራዊ ስንክሳሮቻችንን፣ የተሰወሩ ጉድፎቻችንን በጥበብ ብርሃን አሳይቶናል። ጸጋና ውበታችንን፣ ባህልና ትውፊቶቻችንን፣ ታሪክና ሃገራችንን በውብ ስራዎቹ ከሽኖ እንደምቅባቸው ዘንድ አጎናጽፎናል። ብዙ ከያንያንንም ፈለጉን ይከተሉ ዘንድ የተምስጦ ሻማን ለኩሶላቸዋል።

ህይወታቸውን በበጎ መንገድ በዳበሳቸው ሰዎች ልቦና ውስጥ ሃውልት አለው። በሱ መነሻነት በተሰሩ በጎ ነገሮች፣ በተነሳሱ የፈጠራ ክህሎቶች ላይ ሁል ጊዜ ተንጸባርቆ ይታያል። በጎ መንፈሱን፣ የፈጠራ ክህሎቱንና ብቃቱን፣ ጥንካሬና ጽናቱን ወርሰን የተሻለ፣ ትህትናና በጎነት የሰፈነበትን ህይወት እንድንኖርና ነቢይ ስሜቱን ያለአንዳች ስስት አጋርቷል።

የነቢይ የህይወት ተሞክሮ፤ ሁላችንንም ከእውነት፣ ከፈጠራና ገደብ ከሌለው ተስፋ ጋ እንድንኖር የሚያግዘን ነው።

ነብይ መኮንን አፄ ገላውዲዮሰ ትምህርት ቤት(ናዝሬት) ካፈራቸው አንዱ ከመሆኑ አንፃር የታሪኮቹ ሁሉ መነሻ ያደርገው ነበር። ያልተነገሩ ታሪኮቹ የሚጀምሩት ከአፄ ገላውድዮስ ት/ቤት ነበር፡፡ የጥበብ ህይወቱ ሀ ሁ የተጀመረበት ጊዜም ያ ወቅት ነበር ፡፡ የብዙዎች ጓደኛ ነብይ እያንዳንዱ ሰው ወደ ኋላ ሄዶ መነሻው ላይ ራሱን እንዲፈልግ ይጠይቃል፡፡ ራስን ለመፈለግ ብዙ መንገድ ለሚጓዙት እና ራሳቸውን ፈልገው ላላገኙት ያልተነገሩት የእሱ ታሪኮች ብዙ ያስተምራሉ፡፡

በ1970ዎቹ ሀገራችን ወደ ተሻለ የመንግሥት አስተዳደር እንድትለወጥ በነበረው ፍላጎት በጊዜው ከነበረው የደርግ መንግሰት ጋር በተደረገው ትግል ነቢይ አንዱ ነበር፡፡ በደርግ ዘመን በኢህአፓ አባልነቱ ለ10 ዓመታት ለእስር መዳረግ እጣ ፈንታው ነበር፡፡ በእነዚህ 10 ዓመታት ውስጥ ያልተነገሩ ምናልባትም ለጥቂት ወዳጆቹ ብቻ ያካፈላቸው ታሪኮችን አሳልፎበታል፡፡ የእስረኞች አለቃ ከመሆን አንስቶ እስከ በእስር ቤት የጥበብ ክበብን በመምራት አስደማሚ ታሪኮችን ያሳለፈበት ሲሆን ሌሎችም ይማሩበት ዘንድ እንዳይረሳ አድርጎ አስተላልፏቸዋል፡፡

በተለይም ከክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በእስር ቤት ያሳለፋቸው ታሪኮች ብዙ ያልተነገረላቸው ቢሆንም አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ማን ነበር የሚለውን የተረዳበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ታሪኮች በላይ የሚገዝፈው ታሪክ ግን የቱንም ያህል የእስር ቤት ታሪክ ህመም ያለውም ቢሆንም ደርግንም ሆነ ሀገሪቱን አልያም ሌላ ወገን ነቢይ ሲወቅስ ወይም ሲያወግዝ አይሰማም፡፡ ይልቁንም ሌሎች እንዲማሩበት ይተጋል እንጂ፡፡ ምናልባትም ፖለቲካን በአግባቡ ለመረዳት ብሎም ስለ ኢህአፓ የፖለቲካ ታሪክ ለመረዳት ነቢይ መኮንንን ጆሮ ሰጥቶ ማድመጥ በቂ ነበር፡፡

ከዚህ የተጠቀሙ ጥቂቶች ቢሆኑም፡፡ ነብይ የሁሉ ጓደኛ ለወጣቱ ደግሞ የቅርብ ዘመድ ነው፡፡ ከጥበብ ጋር ተቆራኝቶ ለሚመጣ ሁሉ በጥበብ መንገድ ለመምራት አይረፍድበትም ነበር፡፡ እጅ ይዞ መንገድ የማሻገር ያህል ለነብይ እጅግ ቀላል ነበር ማለት ድፍረት አይሆንም፡፡ ነብይ የግጥም ሥራዎቹ በተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎሙለት ታላቅ ብዕረኛ ሲሆን በተለይም በፈረንሳይ ሀገር በነበረው ቆይታ “ኑሮዋም ለብለብ” የሚለው ግጥሙ በተለይም ‘ለብለብ’ የሚለው ቃል በፈረንሳይኛ አቻ ትርጉም በመታጣቱ አዲስ ቃል መፍጠር እንዲችሉ ማድረግ የቻለ ታላቅ ገጣሚ ነበር፡፡ ነብይ መኮንን ከታተሙት በላይ ያልተነገሩት ታሪኮቹ ብዙ ገጾች ያላቸው በርካታ መጽሐፍት ይወጣቸዋል።

. ነቢይ ከሰራቸው ሰራዎች የሚጠቀሰው “ማለባበስ ይቅር” ነው፡፡ HIV- AIDS የሀገር አደጋ በሆነበት ዘመን ነቢይ መኮንን “ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትን ማግለል በሽታውን ያባብሳል። ስለዚህ ፍቅር እንስጣቸው። አናግልላቸው” የሚል መልእክት ያለው ግጥም ገጥሞ የዘመኑ ወጣት ዘፋኞች እንዲዘፍኑት አድርጎአል። የዘፈኑ መጠሪያ “ማለባበስ ይቅር” ሲሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ይታይ ነበር።

ነቢይ መኮንን አሜሪካ በሄደበት ጊዜ በዚያ ስለሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን የጻፈው አስገራሚ፣ አስቂኝ እና አስተማሪ የጉዞ ማስታወሻ ነው። ማስታወሻው መጀመሪያ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ከቀረበ በኋላ በ1997 ገደማ በአንድ መጽሐፍ ታትሞ ወጥቷል።

ነቢይ በ1999-2000 ዳን ብራውን የጻፈውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረውን “The Davinci Code” የተሰኘ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በተከታታይ ያስነብብ ነበር።

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ1995 በፓሪስ ከተማ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሀገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ስታስገኝ በመላው ሕዝባችን ስሜት ላይ ከፍተኛ ደስታ ነው የፈጠረችው። ነቢይ መኮንንም ደስታው ፍንቅል ብሎ ወጥቶ ለጥሩነሽ ያለውን አድናቆት “ነገር የገባት ሰጎን” በሚል ግጥም ገልጾላታል። ግጥሙም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ወጥቶ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ነቢይ ለሀገሩ ኪነጥበብ ማደግ ከወጣትነቱ ጀምሮ ብዘ የለፋ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ነው፡፡ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት የቅርብ ወዳጆቹ ግንቦት 30 2011 በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ነቢይ በሀገሩ ይከበራል የሚል የምስጋና መሰናዶ አዘጋጅተውለታል፡፡ ይህም የሰው ልጅ በቁም ሳለ ይመሰጋገን የሚለውን በጎ ባህል ያስጀመረ የቅርብ ሰዎቹንም ዛሬ ሲያስቡት ፍጹም ቁጭት ውስጥ የማይከት ክስተት ነበር፡፡

የነብይን ግዙፍ ስበዕና ስንዘክር፣ በትውስታው ውስጥ ተመስጦንና በጎ ተጽዕኖን እናገኛለን። መንፈሱ በፈጠራ ስራዎቹ ውስጥ ዘላለም ይኖራል።

የሁሉ ወዳጅ ከልጅ ከአዋቂው ጋር የሚግባባው ነቢይ ከወይዘሮ ንጹህ …….. ጋር ትዳር መስርቶ ራእይ ፣ ፐርል እና ራኬብ የተባሉ ሴት ልጆችን አፍርቷል፡፡ 7 የልጅ ልጆች አፍርቷል።አንጋፋው ገጣሚና ‹ፀሀፊ ተውኔት ተርጓሚ ነቢይ መኮንን ሮብ ሰኔ 26 2016 ረፋዱ ላይ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ69 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡ የቀብር ስነስርአቱም ዛሬ ሰኔ 27 2016 በአዳማ ናዝሬት ቅድስተማሪያም ቤተክርስቲያን ይፈጸማል፡፡ ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናት እንመኛለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *