ቴዎድሮስ ንዋይ

ቴዎድሮስ ንዋይ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ቴዎድሮስ ንዋይ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ንዋይ በኢትዮጵያ ሬድዮ በዜና ፋይል ያገለገለ በተጨማሪም በልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች በኮሚኒኬሽን ባለሙያነት የሰራ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ደግሞ በብሄራዊ ሎተሪ የኮሚኒኬሽን የስራ መሪ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ቴዎድሮስ ንዋይ የሰጠውን መረጃ መሰረት በማድረግ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኩን ሰንዶታል፡፡

ውልደትና ትምህርት

አውራ ጎዳና ሰፈር በ1963 ነሐሴ ወር ነው የተወለደው፤ አዲስ አበባ፣ ከሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጀርባ፣ ጨርቆስ፡፡ አባቱ ንዋይ ኃይሌ መምህር፣ በኃላም የትምህርት ሚኒስቴር የፋይናንስ ባለሙያ፣ እናቱ ወ/ሮ ሸዋዬ ተ/ማርያም የቤት እመቤት ነበሩ፡፡ ቴዎድሮስ በሽመልስ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣በሲቢስቲ ነጋሲ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እና በየካቲት 12 ሁለተና ደረጃ ት/ቤት ተምሯል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ የኬሚስትሪና የሒሳብ የላቀ ችሎታ ቢኖረውም የኢኮኖሚክስ ትምህርት ለማጥናት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አራት ኪሎ ካምፓስን ትቶ ስድስት ኪሎ ካምፓስን መርጦ ቢገባም የመረጠውና የሚመኘውን ሳይሆን ያልመረጠውን ቋንቋና ስነጽሀፍ ተምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ በ1983 ዓ.ም በቢኤ ዲግሪ ተመርቋል፡፡በኋላም ከዚሁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ1997 ዓ.ም የኢኮኖሚክስ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ህንድ ሀገር ከሚገኘው ከኢንድራ ጋንዲ ዩኒቨርስቲ(ኢግኑ) በተልእኮ በንግድ የኤም ኤ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ ሁለት ኮርሶች ይቀሩታል፡፡

የስራ የመጀመሪያ ቀን

በኢትዮጵያ ሬድዮ ተመድቦ ወደ ጣቢያው የሄደው በ1984 አ.ም ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡መጀመሪያ ያገኘው የሕይወቱን የመጀመሪያውን የሥራ አለቃ እውቁንና አንጋፋውን ጋዜጠኛ ዳሪዮስ ሞዲን ነበር፡፡ ዳርዮስ ፈተና ከሰጠው በኃላ ወዲያው “ድምጹ ሊገራ ይችላል፤ቢቀጠር መልካም ነው፡፡” የሚል ጽሑፍ ለሰው ኃብት አገልግሎት ሲልክ የቴዎድሮስ ትኩረቱ ግን እምብዛም በፈተናው ላይ ሳይሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ሲያዳምጠው ከኖረው አንጋፋ ጋዜጠኛ አጠገብ መገኘቱ ነበር፡፡

ጋዜጠኛው ቴዎድሮስ

ቴዎድሮስ ንዋይ በ1984 ህዳር ወር በኢትዮጵያ ሬድዮ በዜና ፋይል በከፍተኛ ሪፖርተርነት ተቀጥሮ ስራ ጀመሯል፡፡ በዜና ፋይል ስራ ሲጀምር መጀመሪያ የተረዳው ዜና ክፍል ውስጥ ስራ እንዳለ ነበር፡፡ ሁሉም ጋዜጠኛ ዜና ለማድረስ ይተጋል፣ ይፈጥናል፡፡

ከመጀመሪያው በጋዜጠኝነት ስለመቀጠል አለመቀጠሉ እርግጠኛ ያልነበረው ቴዎድሮስ የነዳርዮስ ሞዲ፣ ነጋሽ መሀመድ፣ ዋጋዬ በቀለ፣ ተፈሪ ለገሰ፣ተፈሪ አንለይ፣ ዳንኤል ወ/ሚካኤል፣ አማረ መላኩ፣አለምነህ ዋሴ፣ እሸቱ ገለቱ፣ ብርቱካን ሀረገወይን፣ ንግስት ሰልፉ የስራ ትጋት ምክንያት የዜና ባለሙያ ሆኖ እንደሚቀጥል ለመረዳትና የሬድዮ ጋዜጠኝነት ሲዋሀደው ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም ፡፡

የዜና ፋይል ፎርማት የተፈጠረው በእውቁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃ/ማርያም ነው፡፡የዚያን ጊዜ የዜና ፋይል ጋዜጠኞች የሚለኩበት ዋና ጉዳይ ጌታቸው ኃ/ማርያም ዜና ፋይልን ሲፈጥር የነበረው የዜና ጥራት ምንም ሳይቀነስ ይዞ መቀጠልና ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ነበር፡ለዚህ ነው በዚያ ትጋት፣ ብቃትና ጥራት ደረጃ ዜና ፋይል ይቀርብ የነበረው፡፡ይህ ባይሆን ኖሮ አስራ አምስት ቀናት የማታዘልቅ ደመወዝ እያገኙ፣ አንዱን ወንበር ሁለት ጋዜጠኞች እየተቀመጡበት፣ ከሪፖርት ስራ በተጨማሪ ለግዢ፣ለአስተዳደር፣ለሰርቪስ በሚያገለግሉ ሶስት ተሸከርካሪ ብቻ እየሰሩ፣በኮምፒዩተር ሳይሆን በአስክሪፕቶና ታይፕ ራይተር ጽሁፍ እየመቱ፣ጣት በምታክል ድምጽ መቅረጫ ሳይሆን የጀርመን ጎረምሳ በማይችለው ኡሀርና ናግራ የድምጽ መቅረጫ ተሰርቶ እንዴት ጥራት ያለው ዜና ይጠበቃል፡፡

በዜና ፋይል ውስጥ በአንድ ቀን ውስጥ እስከ አምስት የሚደርሱ ረጃጅም አለም አቀፍ ዜናዎች ለሬድዮ በሚሆን ውብ አድርጎ መተርጎም፤እስከ ሰባት ዜና የአርትኦት ስራ መስራት፣እስከ 20 ደቂቃ የሚረዝም ወቅታዊ ዘገባ መስራት ብዙም የሚከብድ ስራ አልነበረም፡፡በወቅቱ የሰላምና መረጋጋት፣ዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ፣የምርጫ ጅምር ስራዎች፣መንግስት ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር የነበረውን ግብግብ፣አነስተኛም ቢሆኑ የማህበራዊ ተቋማት ግንባታና የጤናና የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስራዎች፣የድርቅ፣የረሀብ ክስተቶች የወቅቱን ትላልቅ አለም አቀፍ ጉዳዮች መዘገብ የእለትተእለት ስራዎቻቸው ነበሩ፡፡

ቴዎድሮስ ንዋይ ከሰራቸው ዜናዎች ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔና አራት ሚኒስትሮች፣እንዲሁም ከሶስት የቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ጋር በመሆን በደቡብ ኢትዮጵያ በ1987ዓ.ም በከፍተኛ ደረጃ የተከሰተውን ድርቅ ከሀዋሳ ከተማ እየተነሱ በሄሊኮፕተር ለአምስት ቀናት ተዘዋውረው መዘገቡንና በድርቁ ላይ ከ20 ደቂቃ በላይ ርዝመት ያላቸውን ዘገባዎች በተከታታይ በመስራት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድርቅ የተጎዳውን ዜጎች ለመርዳት እንዲረባረብ መደረጉን ያስታውሳል፤በ1980ዎቹ የኤች አይ ቪ/ኤድስ በተስፋፋበትና ለሀገር አስጊ ደረጃ በደረሰበት ጊዜ ተከታታይ ዘገባዎች በመስራትና በማስተማር በተለይ ኤች አይ ቪ በደሟ እንዳለ ለመጀመርያ ጊዜ ወደሚዲያ የመጣችውን ሴት ለሕዝብ በማስተዋወቅ የመጀመርያው መሆኑን ያስታውሳል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተከሰው በኢትዮጵያ ፓርላማ በ1989 ጥቅምት ወር ላይ በቀረቡበት ጊዜ ውይይቱ እስከ ምሽቱ አንድ ሰአት ቢቆይም መረጃውን ለሁለት ሰአት ዜና ቀድሞ ለሕብረተሰቡ ማድረሱ ዜናን በሰአቱ ለማድረስ የነበረው ሩጫ ቀላል እንዳልነበር ይገልጻል፡፡ በዚያን እለት አቶ በረከት ከፓርላማው ሲወጡ መግቢያው በር ላይ ጋዜጠኞቹን ያገኙዋቸዋል፡፡ሙሉ ውይይቱ ምሽቱን ከዜና በኋላና በነጋታው ጠዋት ከአንድ ሰዓት ዜና ቀጥሎ እንዲተላለፍ ለአለቆቻቸው እንዲነግሩ በጋዜጠኞቹ በኩል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ሲያስታውስ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን እንደ የፖሊት ቢሮ አባል ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ የሬድዮ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅም ሆኖ እንደሚሰራ ጥሩ ምስክር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፓርላማን ውይይቶች፣በኢትዮጵያ አደራዳሪነት የሱማልያ ተፋላሚ ወገኖች በጊዮን ሆቴል ያደርጉት የነበረውን እልህ አስጨራሽ ድርድር፣የአማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት በግዮን ሆቴል ያደረገውን አነጋጋሪ ጉባኤ ዘግቧል፡፡የ4.4 ሚሊየን ዕድሜ ያለው የአውስትራሎፒቲከስ ራሚደስ አጽም እ.ኤ.አ1996 በኢትዮጵያ አፋር ውስጥ መገኘቱን የአለም ሚዲያዎች ከመዘገባቸው በፊት የመጀመርያው ዘጋቢ ሆኖ ለኢትዮጵያ ህዝብ አድርሷል፡፡

እውነትን መዘገብ ያለመቻል ፈተና

አለቃው ዳርዮስ ሞዲ የኦነግ አባላት ጎተራ የሚገኘውን የሞቢል የነዳጅ ዴፖ ሊያቃጥሉ ሲሉ ስለተያዙ ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ጊዜ ሳይወስድ እንዲሄድ ያዘዋል፡፡ ጊዜውም በ1985 ነበር፡፡ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደደረሰ አንደኛውን እስረኛ ሲያይ አይንኑ ማመን አልቻለም፡፡ ደርባባው አዛውንት ከተፈሪ መኮንን ት/ቤት ከፍ ብሎ የሚገኝ አንድ የታወቀ መድኃኒት ቤት ባለቤት ነበሩ፡፡በልጅነቱ በመድኃኒት ቤቱ በር ላይ ሲያልፍ በራቸው አጠገብ ቆመው ያያቸው ነበር፡፡

በዚያን እለት ተደብድበው ፊታቸው አብጦ እግራቸው በፋሻ ታሽጎ ሲመለከታቸው ቃለ መጠይቅ ማድረግ አልቻለም ፡፡ አብረውት በነበሩ የኢዜአና የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በጠየቋቸው ጥያቄዎች ተረድቶ አስፈላጊውን መረጃ ከሰበሰበ በኃላ ወደ ቢሮ እየተመለሰ እያለ “እኛን ሲያስተባብር የነበረው አራተኛው ሰው አብሮን ታስሮ ነበር፣እሱን ለቀውታል” ብለው ደጋግመው የተናገሯቸው ቃላትና የሚያውቃቸውን ሰው በዚያ ሁኔታ ማየቱን፣የዜናው እውነታና ፕሮፓጋንዳ እንደተደበላለቁበት እያሰበ ቢሮ ሲደርስ ዜናውን ተወው፣አትስራ የሚል መልዕክት ከአለቃው ሲደርሰው ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ ተሰምቶት ነበር፡፡ በሳምንቱ ግን ዜናው በቅጽል ስድብ ተሞልቶ በኢዜአ በኩል በቴሌፕሪንተር ዜና ፋይል ደረሰ፡፡ ዜናው ፓርቲ ጽ/ቤት ተሰርቶ እንደመጣ ግልጽ ነበር፡፡ የአራተኛው ግለሰብ ሚስጥር ዜና ሳይሆን ቀረ፡፡ ሌላው ተመሳሳይ ገጠመኝ አንድ እለት ስለቀድሞ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዜና ለመዘገብ በተለምዶ አለም በቀኝ ወደሚባለው እስር ቤት ተላከ፡፡

የቀድሞ ባለስልጣናቱ በአለም በቃኝ እስር ቤት ደህንነታቸው እየተጠበቀ እንደሚኖሩ የሚያሳይ ዜና እንዲሰራ የተላከ በመሆኑ ሻለቃ ደበላ ዲንሳንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖችን በጉዳዩ ላይ ቃለ-መጠይቅ አድርጎ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ በሩ እየተመለሰ እያለ አንድ እስረኛ ሰላምታ ያቀርቡለታል፤ አፀፋውን መልሶ ሊሄድ ሲል አላወከኝም? ብለው ሲጠይቁት እንደማያውቃቸው ይነግራቸዋል፡፡ ሆኖም ሰፈርህ ጨርቆስ አይደለም? ብለው ሲጠይቁት በአለበት ደርቆ ይቀራል፡፡ በገና ጠጅ ቤት በር ላይ ልብስ ስፌት ይሰሩ እንደነበር፣ልጅ ሆኖ ከእናቱ ጋር እየመጣ ልብስ ያሰፋ እንደነበር ሲነግሩት በደንብ እንደሚያውቃቸው ገልጾላቸው ብዙ ነገሮችን አውርተው ተለያዩ፡፡

ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንዴት እንደታሰሩ ሲጠይቃቸው ለሳቸውም ግራ እንደገባቸው ገለጹለት፡፡ ጥያቄው፣የዜናው እውነት በዝቅተኛ ደረጃ ያለ ግለሰብ በእስርቤቱ ከነበሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ከነደበላ ዲንሳ፣ ፍሰሀ ደስታ፣ ፍቅረስላሴ ወግደረስና ከሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ለምን ታሰሩ? ወይስ የደርግ ባለስልጣናት በአለም በቃኝ እስር ቤት ደህንነታቸው ተጠብቆ እየኖሩ ነው የሚለው ሲሆን ለጥያቄው መልስ ቢያገኝም በዚህ አንግል ዜና መስራት አለመቻል በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙት ፈተናዎች ነበሩ፡፡

ጋዜጠኛ ከሰራ ይከበራል

ሩዋንዳ፣ ኪጋሊ፣በ1986 ግንቦት ወር ምሽት ሁለት ሰስዓት ላይ፣የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደሮች በኪጋሊ አለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ተርሚናል ውስጥ መኝታ ፍራሻቸው ላይ ጋደም ብለው ያወጋሉ፡፡በምሽቱ 2፡00 ሰዓት ዜና፣የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ኪጋሊ፣ሩዋንዳ ገባ፤ ለዝርዝሩ… የሚለው የነጋሽ መሀመድ ድምጽ በአለም አቀፉ የሬድዮ ሞገድ ሰንጥቆ ኤርፖርቱ አዳራሽ ሲደርስ ፀጥታ ሰፈነ…. ቴዎድሮስ ከሶስት የቴሌቭዥን ጋዜጠኞችና አንድ የፕሬስ የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ጋር ሆኖ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጋር አመሻሹ ላይ ኪጋሊ ሲደርስ ግምቱ አንድ ትልቅ ሆቴል እንደሚያርፍ ነበር፡፡ሆኖም አዛዡ ኮሎኔል ታደለ ገ/ህይወት በተርሚናሉ አንድ ጥግ ላይ እንዲያድሩ ነበር ያዘዟቸው፡፡

አምስቱ ጋዜጠኞች በዚያን እለት አንድ ሜትር ስፋት ባላቸው ሁለት ፍራሾች ላይ ተጣበው አደሩ፡፡ ቴዎድሮስ በነጋታው ከዋናው አዛዡ ኮሎኔል አጠገብ ሳይለይ አላማችሁ ምንድነው? ብዛታችሁ ስንት ነው? ለምን ያህል ጊዜ ትቆያላችሁ? ምን ስትሰሩ ትቆያላችሁ? የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎች ሲጠይቃቸው በቂ መረጃ ስለሰጡት ስለሰላም አስከባሪ ሀይል ምንም ግንዛቤ ላልነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ሶስት ደቂቃ የሚረዝም ዜና ወደ አዲስ አበባ በስልክ ንባብ ልኮ ከጓደኞቹ ጋር ተቀላቀለ፡፡

በዛች ምሽት ቴዎድሮስ ዜናውን አንብቦ እንደጨረሰ አዛዡ ኮሎኔል በቀጥታ ወደ ጋዜጠኞቹ መጥተው ከነበሩበት የአዳራሹ ጥግ ስፍራ አስነስተው እሳቸው አጠገብ እንዲያድሩ አደረጉ፡፡ትናንሾቹ ፍራሾች በትላልቅ ፍራሾች፣አቃቂ ይሰራ የነበረው የቆርቆሮ ምግብ በትልቁ የካናዳ የቆርቆሮ ምግብ ተቀየረላቸው፡፡ቡናም አፍልተው ሰጧቸው፡፡ሌሊቱን ከጋዜጠኞቹ ጋር ሲያወሩ አደሩ፡፡በነጋታው ጋዜጠኞቹም እንደ ወታደሩ የሰላም አስከባሪውን የተባበሩት መንግስታት ወታደራዊ ልብስ ለበሱ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሰላም አሰከባሪው ጋር አብረው የተጓዙ በመሆኑ አዳራሽ ውስጥ አብረው እንዳደሩ ይገምታል፡፡

የሕገመንግስት ጉባኤ

ቴዎድሮስ የኢፌድሪ ሕገመንግስት በ1987 ሲጸድቅ ከሕገ-መንግስቱ ጉባኤ የአንድ ወር ቆይታ 80 በመቶውን ጊዜ በመገኘት ዘግቧል፡፡ ከ500 በላይ የሚሆነው መቀመጫ በ99 በመቶ የኢህአዴግ አባላት በተያዘበት በዚያ ጉባኤ፣ ሻለቃ አድማሴ ከ500 በላይ የሆነውን አባል ብቻቸውን በመከራከር ከኢሕአዴግ በተቃራኒ የሆነውን ሀሳብ ለሕዝብ በማድረስ ብቻቸውን ያደረጉት ተጋድሎ ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ነው፡፡ሻለቃ አድማሴ በዚያ ጉባኤ ባይኖሩ ኖሮ ዜናው ከባድ ይሆንበት እንደነበር ይናገራል፡፡ዜናው ጠንካራ እንዲሆን፣ዜናው ሚዛናዊ እንዲሆን የረዳው በኢሕአዴግ ተቃራኒ የነበረው የሻለቃ አድማሴ ሀሳብ ስለነበር ነው፡፡

በዜና ፋይል የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ጄነራል ኢብራሂም ባባንጊዳን ዜና ሰርቶ በማንበብ ጀምሮ እስከ 1989 መጨረሻ ድረስ ለስድስት አመታት ሰርቷል፡፡ በ1989 መጨረሻ የኢትዮጵያ ራድዮን ለቆ ፓርላማ ሲቀጠር ጋዜጠኝነትን ለመተው ከራሱ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የወቅቱ ኃላፊዎች ስለጋዜጠኛው መብት፣መልካም አስተዳደር ስለማስፈን፣ከአድልዎ ነጻ የሆነ የስራ አካባቢ ስለመፍጠር፣ማግኘት ስለሚገባው ጥቅማጥቅምና ስልጠና እውቀቱ ያልነበራቸው፣ብዙም የሚገዳቸው አልነበሩም፡፡ይልቁኑ ዘሩ ምንድነው?የፖለቲካ አመለካከቱ ምን ይመስላል፣ፖለቲካችንን እንዴት ሊያገለግል ይችላል የሚሉት ጉዳዮች ያስጨንቋቸው ነበሩ፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ መሳርያ ከሆነ ቤት ወደ ፖለቲካ ቤት ቢሆንም ጋዜጠኝነቱን መተው ሚዛን ደፍቶ ሬድዮ ኢትዮጵያን ለቆ ወጥቷል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ስራ

ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ ራድዮን ለቆ ከወጣ በኋላ በሕዝብ ግንኙነት በኢትዮጵያ ፓርላማ፣በኢትዮጵያ የመድሀኒት ጅምላ አከፋፋይና ሽያጭ ድርጅት(ፋርሚድ)፣በካርታ ሥራ ባለስልጣን፣በሕብረት ኢንሹራንስ ካምፓኒና በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ሰርቷል፡፡ የፓርላማ ዜና በተደጋጋሚ ይሰራ ስለነበር እዚያ በሚሰራ በቅርብ በሚያውቀው ሰው ጋባዥነት ለመቀጠር የበቃ ሲሆን በፓርላማ ቆይታው በፓርላማ ዜና መጽሄት አዘጋጅ ሆኖ ለአራት አመታት ሰርቷል፡፡ የፓርላማውን መደበኛ ስብሰባዎች፣አውደ ጥናቶች፣አፈ ጉባኤውና የፓርላማው የተለያዩ ኮሚቴዎች ኃላፊዎች ከውጭ ሀገር ከሚመጡ እንግዶች ጋር የሚያደርጓቸውን ውይይቶች ለዜና መጽሔቱ ይዘግባሉ፡፡

በፓርላማው የመጀመርያዎቹ ጥቂት ወራት ቆይታው ከአንድ ትልቅ የዜና ተቋም ይዞት የመጣውን እውቀት ለመጽሔቷ ማበርከት አልቻለም ነበር፡፡የፓርላማው የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊ ዜናዎችን ኤዲት የሚያደርጉት በእስክሪፕቶ ብቻ ሳይሆን በመቀስ ጭምር ነበር፡፡እያንዳንዱን የዜና ዐረፍተነገር በመቀስ ለየብቻው ከቆረጡ በኋላ እያንዳንዱን ዐረፍተነገር በራሳቸው ይጽፉታል፤እያንዳንዱን አረፍተነገር ደግሞ መልሰው በስቴፕለር ይሰፉት ነበር፡፡የሚገርመው ዜና የመጻፍ ችሎታም አልነበራቸውም፡፡

የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ በኃላፊዋ የአርትኦት ስራ ከመበሳጨቱ በላይ ተስፋ ቆርጦም ነበር፡፡ሆኖም አንድ ቀን ከበላይ ኃላፊ ጋር በስራው ላይ በተደረገው ግምገማ ችግሩን በዝርዝርና በማስረጃ በማስረዳቱ ከዚያን ቀን በኃላ እሱ የሚሰራው ዜና ኤዲት እንዳይደረግ ከመወሰኑም በላይ ዜና መጽሔቱ ትክክለኛውን የዜና ቅርጽና ስርአት ይዞ እንዲወጣ ማድረግ ችሏል፡፡

በፋርሚድ ቆይታው ዜና ፋርሚድ መጽሄት በቅርጽና በይዘት የተሻለ ሆና እንድትወጣ፣የሕዝብ ግንኙነት ተግባር ባልነበረበት ተቋም የዶክመንተሪ ስራ በመስራት፣በሰው ሀብት መምርያ ይሰሩ የነበሩ የሕዝብ ግንኙነት፣የስፖንሰርሺፕ፣የዘመን መለወጫ ሕትመቶች፣ኤግዚብሽን የማደራጀት ስራዎች በራሱ በባለቤቱ እንዲሰሩ የበኩሉን ጥረት ያደረገበት ነበር፡፡ በሕብረት ኢንሹራንስ የሚዲያና የማርኬቲንግ ኦፊሰር ሆኖ ሲሰራ ትላልቅ ሁነቶች በኃላፊነት የማዘጋጀት፣የቢል ቦርድና በርካታ የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት ሚዲያዎች የስፖንሰርሽፕና የማስታወቂያ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ለአስራ ስድስት አመታት በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት በሰራበት በብሔራዊ ሎተሪ በሙሉ ትኩረቱ የኮሞዩኒኬሽን ስራዎች ሲሰራ የቆየበት አሁንም እየሰራ የሚገኝበት ተቋም ነው፡፡

ብሔራዊ ሎተሪ የስፖንሰርሽፕ፣የዶክመንተሪ በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ማስታወቂያ የግሉን ሚዲያ ጨምሮ በሰፊው እንዲሰራበት የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡የሎተሪ ዕጣ አወጣጥ ሥነስርአቶች በቴሌቭዥን ቀጥታ ስርጭት እንዲተላለፉ በመስራት፣ሕብረተሰቡ ስለሎተሪ ያለው እምነት እንዲጨምር በማድረግ፣የሎቶ ሎተሪን የዕጣ አወጣጥ ሥነስርአት በሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች እንዲወጣና ሕብረተሰቡ ስለሎተሪ ግንዛቤ እንዲኖረው በመቀስቀስ ሂደቱን ከእቅድ ጀምሮ በመምራት፣በተለያዩ ከተሞች በወጣቶች መካከል በሎተሪና በሌሎች ጉዳዮች የጥያቄና መልስ ውድድሮች እንዲዘጋጁ በማድረግ፣ ዕድለኞች በመኖርያቸው አካባቢ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አደባባዮች ሽልማታቸው እንዲሰጥ በማድረግና ግንዛቤ እንዲኖር በመስራት፣ትላልቅ ሁነቶችን ከዕቅድ እስከ ዝግጅት በመምራት፣የከፋ ማህበራዊ ችግር ላይ ያሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት በማድረግ፣ተቋሙ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በገባበት ወቅት ለሚዲያዎች ተከታታይ መግለጫ በመስጠትና የመስርያቤቱን መልካም ዝና በመጠበቅ በሙሉ ትኩረቱ የኮሙዩኒኬሽን ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ብሔራዊ ሎተሪ የአድማስ ዲጂታል ሎተሪን እንዲጀምር በኮሚቴ ተሳትፎ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ በማድረግ፣ መስርያ ቤቱ በቴክኖሎጂ፣በአሰራር፣በሰው ሀይልና በአደረጃጀት እንዲቀየር ከኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን በመስራትና የመስርያቤቱን የአምስት አመት ስትራቴጂ በኮሚቴ በማዘጋጀት፣የቤቲንግ ጨዋታ በኃላፊነትና ስርአት ይዞ እንዲካሄድ የተዘጋጀውን አዲስ መመርያ በሰብሳቢነት በመምራትና በተለያዩ ኮሚቴዎች በመሳተፍ፣በየአመቱ የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብና በመስርያቤቱ የለውጥ ስራ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ የሶስት ልጆች አባት የሆነው ቴዎድሮስ በማሕበራዊ ተሳትፎው የአካባቢውን የነዋሪ ማህበራት በአባልነትና በሰብሳቢነት መርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሲቪዲኤ (CVDA) የተሰኘ የበጎአድራጎት ድርጅት በቦርድ ሰብሳቢነት ይመራል፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላትን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ቴዎድሮስ ንዋይ በወርቃማው የዜና ፋይል ዘመን የሰራ የማይረሳ አሻራውንም ትቶ ያለፈ ነው፡፡ 6 አመት በኢትዮጵያ ሬድዮ በዜና ፋይል በኩል በርካታ በታሪክ አጋጣሚ የሚገኙ ዜናዎች ን ሰርቷል፡፡ ህገ-መንገስቱ ከዛሬ 28 አመት በፊት በ1987 ሲረቀቅ ዜና የመዘገብ እድል አግኝቶ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ታሪካዊ ሆነቶች ላይ ለባለታሪኩ የሚሰጠው ትርጉም ልዩ ነው፡፡ በተለይ ዘመን ካለፈ በኋላ ለካስ ይሄ ሁሉ ነበር ያሰኛል፡፡ ቴዎድሮስ በሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ስራ በቆየባቸው 31 አመታት ራሱን በእውቀትና በንባብ ለማሻሻል ትልቅ ጥረት ማድረጉ አልቀረም፡፡ በእኛ እምነት የሰዎች ልዩ አበርክቶ ዘመናቸውን በመልክ በመልክ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ቴዎድሮስ ንዋይ በሙያው በቆየባቸው አመታት ስራውን ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ለመምራት ሲያደርግ የነበረውን ጥረት አይተናል፡፡ በተለይ ደግሞ እጅግ ክቡር በሆነው የህዝብ ግንኙነት ሙያ ላይ ጥሩ ስራ ለመስራት ሞክሯል፡፡ ይህም ከታሪክ መዝገብ ላይ ይሰፍር ዘንድ ይገባዋል፡፡ ሰዎች ወደ ኋላ መልሰው ብዙ ካጤኑ ብዙ በጎ አሻራ ማኖራቸውን ማስተዋል ይጀምራሉ፡፡ ቴዎድሮስ ንዋይ በ1980ዎቹ አጋማሽ በኢትዮጵያ ሬድዮ ዜና ፋይል ላይ ታዋቂ ስም ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ በህዝብ ግንኙነት ሙያ አገሩን ለማገልገል እያጣረ ይገኛል፡፡ በዚህ ጥረቱ አንዲቀጥልም እንፈልጋለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *