ከሆሴእም ልዩ አድናቆት ተበረከተለት
ቅዳሜ ህዳር 10 2015አ.ም ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከንቲባ በተገኙበት የተመረቀው የረር ሆምስ ብዙ ሁነቶችን ያስተናገደ ነበር፡፡ የዚህ ዝግጅት የህዝብ ግንኙነት እና የሚድያ የማማከር አገልግሎቱን የወሰደው ደግሞ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከጋዜጠኛ ሮማን ተገኝ ጋር በመተባበር ነበር፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ህዳር 6 2015 አ.ም ከምረቃው ቀን ቀደም ብሎ ጋዜጣዊ መግለጫ በፕሮፌሽናልና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከማዘጋጀት አንስቶ የሚድያ ዘገባዎችን በመምራትና በመከታተል ልዩ ሚናውን ተወጥቷል፡፡ ይህንን ተግባር በሚገባ ለመወጣት ውል ፈጽሞ ኃላፊነቱን በሚገባ የተወጣው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹ሆሴእ ቤቶችን ሊያስረክብ ነው›› የሚለውን ዋና መረጃ በመያዝ የጋዜጣዊ መግለጫውን ሙሉ ይዘት በማሰናዳት፣ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎችን በመጋበዝ ጋዜጣዊ መግለጫው የሚሰጥበትን ስልት ነድፎ ይህም በጥሩ ሁኔታ እውን መሆን የቻለ ነበር፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ ስራ ተገቢውን ልምድ ያካበተ እና ከበርካታ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች እና የስራ መሪዎች ጋር ቅርርብ የፈጠረ በመሆኑ የሆሴእ ዜናን ብዙዎች መዘገብ እንዲችሉ አድርጓል፡፡ ከህዳር 7 2015-ህዳር 11 2015 ባሉት 5 ቀናት 29 ሚድያዎች ‹‹ሆሴእ ቤቶችን አስረከበ›› የሚለውን ዜና ዘግበውታል፡፡ ይህ በፍጥነት እና በጥራት የተሰራ መረጃ የሆሴእን የማኔጅመንት ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ያስደሰተ ነበር፡፡ በመሰረቱ ተወዳጅ ሚድያ ዘገባን ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ አድማጭ፣ ተከታይ ፣ ተመልካች ያላቸውን ሚድያዎች በመምረጥ ለሁነቱ ተገቢውን ሽፋን እንዲሰጡ አድርጓል፡፡
የጋዜጣዊ መግለጫው ሥነ-ስርአት ላይ የሚታደሙ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎችን አስተባብሮ የግንባታ ሳይቱ ድረስ ማምጣት አንዱ የተወዳጅ ሚድያ ትልቅ ኃላፊነት ነበር፡፡በተጨማሪም የሚድያ ባለሙያዎቹ የአዘጋገብ ስልት መቼ እና እንዴት ይሁን የሚለውን በተገቢው መልኩ በማጥናት ተወዳጅ ሚድያ ዘገባዎች እንዲሰሩ አድርጓል፡፡ ከሚድያ ሰዎቹ ጋር በስልክ ፤ በቴሌግራም ፤ በዋትስ አፕ እንዲሁም በአካል ጭምር በመገናኘት ለሚድያዎቹ ተገቢውን ይዘት በመስጠት ፕሮፌሽናል እገዛውን ሰጥቷል፡፡ ይህም ይዘት የጋዜጠኞቹን ነጻነት በማይጋፋ መልኩ የአንዱ ዘገባ ከአንዱ እንዲለይ ፤ ሁሉም በልዩ ልዩ አንግል ዘገባውን እንዲሰሩት ማድረጉ ትልቅ ስኬትን ያመጣ ነበር፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ይህን ትልቅ ሀገራዊ ሁነት የመንግስትም ሆኑ የግል ሚድያዎች በኃላፊነት መንፈስ እንዲዘግቡት አድርጓል፡፡ ‹‹…ቤት ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጉዳይ ነውና ከዚህ የበለጠ ዜና የለም›› የሚለውን መርህ አንግቦ የመንግስት የሚድያ የሥራ ኃላፊዎች ጋርም በመነጋገር ይህ ሁነት ለህዝቡ እንዲቀርብ አስፈላጊውን ጥረት ፣ ክትትል እና የምዘና ስራዎችን በቂ በሚባል መልኩ አከናውኗል፡፡ በመሆኑም ኢቲቪ ፤ ዋልታ ፤ ኢዜአ ፤ አዲስ ሚድያ ኔትወርክ እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዲሁም ሌሎች 25 ተጨማሪ ሚድያዎች ለጉዳዩ ተገቢውን ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ የዘገቡትን ሚድያዎች በመከታተልም አስፈላጊውን የሚድያ ሞኒተሪንግ ስራ በመስራት ለሆሴእ ማኔጅመንት በየጊዜው ሲያቀርብ ነበር፡፡
ተወዳጅሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከጋዜጠኛ ሮማን ተገኝ ጋር በትብብር ያዘጋጁት ይህ የህዝብ ግንኙነት ስራ ለምረቃው እለት የሚሆኑ የመድረክ መሪዎችንም ያዘጋጀ ነበር፡፡ የሆሴእ የማኔጅመንት አባላት እና ባለቤቱ አቶ የማነ ገብረስላሴም ተወዳጅ ሚድያ ላሳየው ከፍተኛ አፈጻጸም የምረቃ ስነስርአቱ ላይ በአይነቱ ለየት ያለ ከጠንካራ ሽፋን የተሰራ የአድናቆት ስጦታቸውን አበርክተዋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከየካቲት 2 1996 ጀምሮ ባለፉት 18 አመታት በሚድያ ስራ ላይ የቆየ በርካታ የሚድያ ባለሙያዎችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የሚድያ ሰዎች ኢንሳይክሎፒዲያ ያዘጋጀ ነው፡፡ በተጨማሪም ከግብርና ሚኒስቴር ፤ ከሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በርካታ ሁነቶችን የሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም የ45 ሰዎቸን የህይወት ታሪክ በሲዲ የ6 ሰዎችን ታሪክ ደግሞ በመጽሀፍ ያወጣ ነው፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽንም ይህን ስራ በታላቅ ድል በመወጣቱ በዚህ ፕሮጀክት ባለቤቶች በጋዜጠኛ ሮማን ተገኝ እና በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ስም ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ የሆሴእ የማኔጅመንት አባላትም ከብዙዎች ተወዳጅን መርጠው እድል ስለሰጡ የተወዳጅ ሚድያ የማኔጅመንት አባላት እያመሰገኑ ወደፊትም በወዳጅነት እንቀጥል ማለት ይወዳሉ፡፡
የፕሮጀክት ባለቤቶች ሮማን ተገኝ እና እዝራ እጅጉ