ዘካርያስ ኃይለማርያም ጉደታ በጥበቡአለም ፣ድንቅ አሻራ ያኖረ ለ20 አመት በሚድያው እና በመዝናኛው ዘርፍ በትጋት ያገለገለ ብርቱ ባለሙያ ነበር፡፡ ጎሬ ተወልዶ ልጅነቱን በዚያው ያሳለፈ ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶም ቴአትርን ያጠና ነው፡፡ ዘካርያስ የገና ሙሽራን፤ የዘማሪዋ ወፍ ህልም ሰናይት የተሰኙ ፊልሞችንም የሰራ ነበር፡፡
ህዳር 22 2015አ.ም ህይወቱ ያለፈው ዘካርያስ ኃይለማርያም ቅዳሜ ህዳር 24 2015 በለቡ ገብርኤል ስርአተ-ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡በወንጌል አማኞች የእምነት ስርአት መሰረት የቀብር ስነ-ስርአቱ የመጽሀፍ ቅዱስን ቃል በማሰማት የተፈጸመ ነበር፡፡ ከ1978-1998 በሀገራችን የቲቪ ድራማዎች፣ ፊልሞች እና ማስታወቂያዎች ጀርባ ዘካርያስ ነበር፡፡ ለብዙዎች ወደ ሚድያው እና ጥበቡ አለም መምጣት ምክንያት ሆኗል፡፡ ህዳር 23 2015 የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የዘካርያስን የህይወት ታሪክ ስጽፍ ብዙ ያላካተትኳቸው እውነታዎች ነበሩ፡፡ በጊዜ ሂደት ማካተቴ አይቀርም በሚል እሳቤ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ መነሻ የሚሆን የህይወት ታሪክ ጽፌ ማስነበቤ ይታወቃል፡፡
ያኛውን ጽሁፍ እንደ መጀመርያ ክፍል ውሰዱልኝና ሁለተኛውን አሁን ማስነበብ ጀምራለሁ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ስለ ዘካርያስ ብዙም ያልተነገሩ ጉዳዮችን እያነሳሁ ይህን ብርቱ ሰው ላስተዋውቅ ሞክራለሁ፡፡ እኔ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የሰዎችን አስተዋጽኦ ከተገቢው ምንጭ በመውሰድ ለትውልድ እንዲቀመጥ የአቅሜን ያህል እየጣርኩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እና አሁንም ስለ አንድ ባለውለታ ወግ ብጀምርስ? ዘካርያስ ኃይለማርያም ባለፉት 37 አመታት በኪነ-ጥበብ እና በመንፈሳዊ አገልግሎት በተለይ መጽሀፍ ቅዱስን በማስተማር ለብዙዎች መትረፍ የቻለ ነበር፡፡ ዘካርያስ በ1998 አ.ም ሙሉ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሜሪላንድ ክፍለ ግዛት ደረሰ፡፡ በኋላም encore global or psiv በተሰኘ ተቋም ውስጥ የሁነት ከፍተኛ ኤክስፐርት ሆኖ ስራ አገኘ፡፡ ገና በሄደ በ3 ወሩ ስራ ማግኘቱ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር ፡፡ ሀገር ቤት ሳለ 4 የሚሆኑ ፊልሞችን÷ ከ200 በላይ ዶክመንተሪዎችን በርካታ ማስታወቂያዎችን የሰራው ዘካርያስ አሜሪካን ሀገር ከደረሰ በኋላ ከጥበቡ አለም ሙሉ ለሙሉ ወጥቶ በሁነት ዝግጅት ሁለተኛ ዲግሪውን ተቀብሎ በአዲስ ሙያ አዲስ ኑሮን መኖር ጀመረ፡፡ የ 5 አመት እና የ4 አመት ሴት ልጆቹን አይካን እና አይዳን ይዞ ባለቤቱ ገነት ተስፋዬ ጋር በመሆን ኑሮን በሜሪላንድ አሀዱ ብሎ ጀመረ፡፡
ዘካርያስ በሜሪላንድ
ሀገር ቤት ሳለ 20 አመት በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላይ ያገለገለው ዘካርያስ ሜሪላንድ ሲገባ የ45 አመት ልደቱን አክብሮ ነበር፡፡ 1998 ዓ.ም ወደ አሜሪካ የገባው ዘካርያስ በዋናነት የልጆቹን የወደፊት እጣፋንታ ምቹ ለማድረግ በሚል ነበር መኖርያውን ወደ አሜሪካ ለማድረግ ከውሳኔ ላይ የደረሰው ፡፡ ባለቤቱም ብትሆን ይህን ማሰቧ አይቀርም፡፡ ዘካርያስ ግን ለእናት ሀገሩ ካለው ፍቅር የተነሳ ከኢትዮጵያ ምድር ባይወጣ ደስ ይለው ነበር፡፡ ግን ለአይካና አይዳ ሲል ሜሪላንድን መረጠ፡፡ በነገራችን ላይ አይካ ልጁ ስትሆን ጸማኮ ከሚለው ፊልም ላይ አይካ የምትባል ገጸ-ባህሪይ ነበረች፡፡ በዚያን ሰሞን ልጁ ስትወለድ አይካ ብሎ ስም አወጣላት፡፡ እና ዘኪ ለአይካ ሲል አሜሪካ የግድ ስራ ማግኘት ነበረበት፡፡
‹‹ ምን አይነት ስራ አገኝ ይሆን?›› እያለ ዘኪ በልቡ ይጠይቃል፡፡
‹‹ እንደ ሌሎች የሀገርህ ዜጎች ፓርኪንግ ልትሰራ ?›› ይለዋል ሌላው ማንነቱ
‹‹ ለዚህ እንኳን የሚሆን ችሎታም ሆነ አቅም የለኝም ›› ሲል ይመልሳል፡፡
በእንዲህ አይነት የውስጥ ምልልስ ውስጥ ሳለ አንድ ምርጥ ስራ አገኘ፡፡
‹‹encore global or psiv በተሰኘ ተቋም ውስጥ የሁነት አዘጋጅ የተሰኘው ስራ በጣም ጥሩ እድል ነው፡፡››አሉ የቅርብ ሰዎቹ፡፡
ዘካርያስ ይህን ጥሩ የስራ እድል ማግኘቱ ደስታን ፈጠረለት፡፡ በቅርብ አለቆቹም ሆነ በባልደረቦቹ በጣም የሚወደድ ሆነ፡፡ ሥራው ዓለም አቀፍ ሁነቶች ሲደረጉ ያንን ማስተባበር ስለነበር ለዘኪ ስራው እጅግ አድካሚ ነበር፡፡ ቢሆንም ዘኪ በስራው ደስተኛ መሆኑን ለቅርብ ሰዎቹ ይናገር ነበር፡፡
‹‹ በመጀመርያ ማስታወቂያ ላይ የስራ እድል እንዳለ ተመለከትኩ፡፡ ዓይኔን አላሸሁም፡፡ ወዲያው የትምህርት ማስረጃዬን ላኩኝ›፡፡ ተቀበሉኝ›› ሲል ዘካርያስ ሥራ ያገኘበትን አጋጣሚ ለወንድሙ ለሳሙኤል ነግሮት ነበር፡፡ ዘኪ በዚህ ሥራ ትጋቱ እየታየ በአለቆቹ የሚወደድ ሆነ፡፡ አሜሪካም በስራ የምትወጥር ሀገር ስለሆነች የዘኪ ነገር ስራሥ ቤተሰብ ልጅ ማሳደግ ሆነ፡፡ ዘካርያስ ሜሪላንድ እንደደረሰ ሚዜው አትክልት ጥላሁን ጥሩ አድርጎ ሀገር አላመደው፡፡ ምርጥ ማኪያቶ እየጋበዘ እንደ ወንድሙ የሚያየውን ዘኪን ሀገር እንዲለምድ አድርጎታል፡፡ ዘኪም በቶሎ ሀገር ለመደ፡፡
ፀማኮ
ፀማኮ የካቲት20 1993 የተመረቀ በዘካርያስ ኃይለማርያም የተደረሰ የመጀመርያው ኤትኖግራፊክ ፊልም ሲሆን በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነበር፡፡ በቀረጻ ወቅት እነ ዘኪ የገጠማቸውን ውድነህ ክፍሌ በፌስ ቡክ ገጹ እንደሚከተለው አስነብቦ ነበር፡፡ የፊልሙ ቀረጻ የሚካሄድበት ደቡብ ኦሞ በረሃ ነው። አዘጋጁና ደራሲው ዘካሪያስ ኃ/ማርያም ቡድኑን ይዞ የከተመው እዚሁ ስፍራ ነው። ሲቀርጹ ውለው መሸ። በረኻው ላይ ሁለት ድንኳን ተደኩኗል። ለሁለት ተከፍለው በድንኳን ነው የሚያድሩት። እናም ጨለማው እስኪገፍ ንቅንቅ የለም። ምክንያቱም ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል። አደገኛ ነፍሳትና አንበሳን ጨምሮ የዱር አውሬ ሊተናኮላቸው እንደሚችል። ብቻ በስጋት ውስጥ እያሉ እኩለ ሌሊት ከአንደኛው ድንኳን ኡኡታ ተሰማ። ሁሉም ክው አሉ። ኡኡታው አላቋርጥ አለ። በቃ አውሬ ነው አሉ። ቢሆንም ከአውሬ ለማስጣል ቆረጡ። ፈራ ተባ እያሉም ወደድንኳኑ ተሰባሰቡ። ዘካሪያስ ጆሮ ግንዱን ይዞ ይጮሃል። አጠገቡ ያሉት ራሱን ከመሬት ጋ አጣብቀው አይዞህ ይሉታል።
አውሬ ነክሶት ሳይሆን ምንነቱ የማይታወቅ ነፍሳት ጆሮው ውስጥ ገብቶ አልወጣም ማለቱ ነው ዘኪሽን ስቃይ ላይ የጣለው። ለማውጣትም ቢሞከር ይበልጥ ወደውስጥ ካልገባሁ ብሎ ድርቅ አለ። በመጨረሻም በቅርብ ርቀት ካለ ኪሊኒክ ባለሙያ ይምጣ ብለው የጤና ሀኪም አመጡ። ሀኪሙ ነገሩ ስለገባው “ጥሩ ብርሃን ያለው ባትሪ አምጡ! ብርሃን በደንብ ሲበራባት ይወጣል!” አለና ወደ ጆሮው ባትሪውን ደገነ። እውነትም ወጣ አለ ነፍሳቱ። ግን እየተመለሰ ቅርቅር ይላል። በመጨረሻ የሆነ መቆንጠጫ ነገር ተፈልጎ ሳይወድ በግዱ ተጎትቶ ወጣ። ዘኪሽም ነፍሱ ተንፈስ እስኪልለት አረፍ አለና ወዲያው የቡድኑን አባላቶች አንድ ጥያቄ በመጠየቅ አፋጠጣቸው፥ “የሆነውን ሁሉ ቀረጻችሁት?” ሲል። እሱን ከኡኡታ መገላገል እንጂ ስለቀረጻ ያሰበ ማንም አልነበረም።
ስለ አዳኙ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር
ዘካርያስ ከ1998 በፊት ባህር ማዶ ከመሄዱ በፊት ጥልቅ ኮሚኒስት እንደነበር ይነገራል፡፡ ገና በልጅነቱ የኮሚኒዝም ጽንሰ -ሀሳብ ላይ ያተኮሩ መጽሀፍትን ያነብ ስለነበር በፖለቲካም የበሰለ ነበር፡፡ ገና በ17 አመቱ ለእስር የበቃውም በኢህአፓ ደጋፊነቱ ሰበብ ነበር፡፡ እና 5 አመት የእስር ቤት ኑሮን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሲሆን ያኔም ቢሆን የጊዜውን የኮሚኒዝም ሀሳብ ለማራመድ ይጥር ስለነበር ለሀይማኖት ወይም ፈጣሪ ለሚባለው ነገር ብዙም እውቅና አይሰጥም፡፡ ይሁንና ለስነ-ጽሁፍ ይጠቅማል ብሎ በማሰብ ግን መጽሀፍ ቅዱስን ለእውቀት ያነብ እንደነበር ባለቤቱ ወይዘሮ ገነት ታስታውሳለች፡፡
ከ1998 ወዲህ ግን ዘካርያስ መንፈሳዊ ህይወት ውስጥ ጥልቅ ብሎ ገባ፡፡ መጽሀፍ ቅዱስን ከበፊቱ በተለየ መንገድ እያነበበ ኢየሱስን አወቀ፡፡ ይህ ወቅት ምናልባት ባለቤቱ እንደነገረቺኝ በ2005 የዛሬ 10 አመት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ዘካርያስ አዲስ ፍጥረት ሆነ፡፡ አማኝ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እኔ ያገኘሁትን እውነት መረዳት አለባቸው ብሎ በስሙ የዩቲዩብ ገጽ ከፍቶ መስበኩን ተያያዘው፡፡ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ጥሞና ሰጥቶ ስብከቶቹን እንዳደመጠው ዘካርያስ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ተመስርቶ በሚደንቅ ሁኔታ ይሰብካል፡፡ ምናልባት የስብከቶቹን ሊንኮች ለማድመጥ ይህ ጽሁፍ ተነቦ ካለቀ በኋላ ስለሚቀመጥ ሊንኩን በመጫን የዘኪን ስብከት ማድመጥ ይችላሉ፡፡ ይህ ከ45000 በላይ ተከታይ ያለው ገጽ የዘኪንም መንፈሳዊ ግጥሞች ያካተተ ስለሆነ በዚህ እርሱን በምናስብበት ሰሞን ከፍታችሁ አድምጡት ስንል እንጋብዛለን፡፡
ሜሊ ተስፋዮ ስለ ዘኪ በፌስ ቡክ ገጽዋ ያሰፈረችው
“ጌታን ሰው ሳይመሠክርልኝ በወንጌል ብቻ ጌታ አብርቶልኝ :እሱ ራሱነው ያገኘኝ.. አሁን በጌታ ገና ብላቴና የሆንኩ::ክብሩ ሁሉ ለጌታ ይሁን::” ይላል: ዘኪ እዚህ አሜሪካን ከመጣ ጀምሮ፡፡ በBetel Gaithersburg Youtube channel ከ200 በላይ የጌታ ቃል ትምህርቶችን ቀርፆ ኤዲት አድርጎ አስተላልፏል:: በራሱም ስም በYouTube channel “Zekarias Hailemariam” ሥራዎቹን እያቀረበ ነበር:: ዘኪ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ግጥሞቹን ለአገልግሎት በጋበዝኩት ግዜ አቅርቦልናል:: በጣም ጥሩ ገጣሚም ነበር:: ዘኪ ከዚህ አለም በሞት ቢለየንም በልጆቹ በባለቤቱ በቤተሰቡ በወዳጅ ጎደኞቹ በጥበብ ስራዎቹ ሲታወስ ይኖራል:: ከሁሉ በላይ ዘላለማዊ ወደ ሆነው ወደ አባቱና አምላኩ ስለሄደ በዚህ እንፅናናለን::
From Solomon abate
እንደሰው እጅግ በጣም ጥሩ፣ በሥነ ምግባር የታነፀ፤ በክፉ ቀኖችህ ሌሎች በፍርሃትም፣ ተስፋ ሲሸሻቸውም ቢሸሹህ እርሱ ግን ይበልጥ የሚቀርብህ፤ “እኔ አለሁ” የሚልህ ምሉዕ ሰው!! ጓደኛ!!! ደፋር! ዋጋው ምንም ይሁን ምን በዚያች ቀን አጠገብህ ታገኘዋለህ። ዘካርያስ የነበረበት ሁሉ ደምቆ ነው የማስታውሰው። ማድነቅ የሚገባውን ለማድነቅ የማይሰስት፣ መወገዝ፣ መወቀስ ይገባዋል የሚለውንም ሃሳብና አድራጎት ለመፀየፍ የማያመነታ ሰው ነበር። የሥራ፣ የፍቅር፣ የሰላም ሰው ዘካርያስ።
እንደባለሙያ አዕምሮው አዳዲስ ሃሳቦችን ከማፍለቅ የማይቦዝን፣ ለማዳመጥ የማይታክት፣ ምንም ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ለመሥራት ወደኋላ የማይል እጅግ ታታሪ ባለሙያ!! ሪፖርተር፣ ፀሃፊ፣ አቅራቢ፣ አዘጋጅ፣ ፕሮድዩሰር፣ ፊልም ሠሪ፣ ተዋናይ። ከደቡብ ፀማይ እስከ ሰሜን ራስ ዳሸን ጫፍ የረገጠ፣ የዘገበና የመዘገበ እንቁ ሰው ነበር ዘካርያስ ኃይለማርያም።
ምን ዓይነት ማጣት ነው?! በጣም በጣም በጣም አዝኛለሁ
ወይንሸት አዳሙ ስለ ዘካርያስ
ዘካርያሰ ኃ/ማርያምን ከሌሎች ባልደረቦቹ ከዳግማዊ ፈይሳ፣ ከዘላለም ጌታሁን፣ፋንታሁን ኃ/ማርያም አሸብር ካብታሙ አትክልት ጥላሁን ጋር በመሆን እጅግ በርካታ ዶክመንተሪ ፊልም ማስታወቂያ ዳይሬክት በማድረግ ስክርፕት በመፃፍ ሀገርን የሚያሳዩ ስራዎችን ሰርቷል ። እኔ እድለኛ ሆኜ እነዚህን ከመሰሉ ባለሙያዎቾ ጋር ከእነሱ ጋር በመስራቴ እጅግ ኩራት ይሰማኛል ። በህይወቴ ከፈጣሪ ቀጥሎ እኔን በመሰራት ሙያዬን አክብሬ ሁሌም ያስተማሩኝን ትምህርት በመተግበር እስከአሁን ቆይቻለሁ ። ዘካርያስ ኃ/ማርያምን ስገልፀው እጅግ ጠንካራና ለሙያው የተሰጠ ነው። በቪዲዮ ኤዲቲንግ ቆይታዬ ከመወሰን በፊት ደጋግሞ ስዕሎችን ማየት መልዕክቱን ማወቅ ተደራሽነቱ ጎልቶ እንዲታይ የሚያስችሉ የተለያዩ ቴክኒኮችን በማጋራት እኔን ቀርፆኛል
የማልረሳዉ ማስታወቂያ ሲስራ / ሲቀረፅ/ ለ 45 sec ለ30sec በፊልም መልክ ነበር የሚቀረፀው በ30sec ውስጥ ምን መልዕክት እንደሚተላለፍ አስቡት እኔ እጅግ ይገርመኝ ነበር ። እያንዳንዱ ፍሬም መልዕክት አላት ዋጋ አላት ሌላው በድምፅ በNatural sound የሚተላለፋ መልዕክቶች ለእሱ ትልቅ ዋጋ አለው በኤዲቲንግ አምሮና ተውቦ እንዲታይ በቀረፃው ወቅት እንደሚደክመው ኤዲቲንግ ላይም ይውላል ያድራል ጠንቃቃ ነው ።
የዘኪ የማይረሱ የዘወትር ተግባሮች ቁጣውና ፣ጩኸቱ ያሰደነግጡን ነበር ነገር ግን ቅፅበታዊ ናቸው ። የሚገርመው ዝም ሲል ይጨንቀን ነበር በቃ ጩኸቱ ሁሉ ይናፍቃል ። ዘኪ በማስታወቂያው፣ በፊልሞቹ፣ በዶክመንተሪው ቱሪዝምን ለማስተዋወቅ ከባልደረቦቹ ጋር በረሀ ለበረሀ ተንከራቷል ። በከፍተኛ ብቃት ትልቅ አሻራውን ጥሎልን አልፏል ። ዘኪ ፈፅሞ አንረሳህም ። ነፍስህ ከደጋጎቹ ጎን በሰላም ትረፍ !
ወይንሸት አዳሙ
ዘካርያስ በዳግማዊ ፈይሳ አንደበት
ዳግማዊ ፈይሳ ዘካርያስን ሲያውቀው 37 ዓመት ይሆነዋል፡፡ ዳግማዊ የ1ኛ አመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳለ ዘካርያስ 4ኛ አመት ነበር፡፡ ትውውቁ ያኔ ጀመረ፡፡ ዳግማዊ በ1990 ወደ ሜጋ በፊልም ዳይሬክተርነት ሲገባ በጊዜው ዘካርያስ የሜጋ ከፍተኛ የፊልም ዳይሬክተርነት ነበር፡፡ ዳግማዊና ዘካርያስ በሜጋ የበለጠ ተቀራረቡ፡፡ በጊዜው ሜጋ ከ130 በላይ ዶክመንተሪዎች ለመስራት ተዋውሎ ነበር፡፡ ቢሆንም የፊልም ዳይሬክተር እጥረት ሲፈጠር የዳግማዊ እና የፋንታሁን ኃይለማርያም መቀጠር ለዘካርያስ ትልቅ እፎይታን ሰጠ፡፡ ምክንያቱም የስራ ጫናውን መቋቋም አቅቶት ስለነበር ነው፡፡ ዳግማዊ ሜጋ ከገባ በኋላ የዘማሪዋ ወፍ ህልም የተሰኘ የዘካርያስ የፊልም ድርሰት ላይ ተወነ፡፡ አሁንም መቀራረቡ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ዳግማዊ ስለ ዘካርያስ ሲናገር ምኑ ይደንቅሀል ሲባል ድፍረቱ በጣም የሚደንቀው እንደሆነ ነግሮናል፡፡ አንድን ፊልም ለመስራት ሂሊኮፕተር አስፈላጊ ከሆነ ዘካርያስ ያንን የታሰበ አውሮፕላን ካላመጣ እንቅልፍ አይወስደውም፡፡ይህም ለሙያው ያለውን መሰጠት ያሳያል ሲል ዳግማዊ ያስረዳል፡፡
‹‹ ዘኪ የሚቆጣ ከሆነ በምክንያት ነው የሚቆጣው፡፡ በዚያ ላይ ፈጣን ነው፡፡ ከአርሱ ጋር እኩል ከማይሄድ ሰው ጋር ሊጋጭ ይችላል፡፡ ቢሮክራሲ አይወድም ነገሮች ፈጥነው እንዲሰሩም ይመኝ ነበር፡፡ ዘኪ የሚሰራቸው ማስታወቂያዎች እጅግ ፈጠራ የታከለባቸው ስለነበሩ ሁላችንም እንማርባቸው ነበር›› ሲል ዳግማዊ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ዘካርያስ ከሜጋ ወጥቶ ሀሌታን ሚድያ ሲጀምር አብረውት እንደ ንግድ አጋር ከጀመሩት አንዱ ዳግማዊ ነበር፡፡ ዳግማዊ አሁንም ሀሌታ ሚድያ ላይ ከዳግማዊ ጋር ሲሰሩ ጥረቱ የሚደነቅ ነበር ይላል፡፡ ዳግማዊ ስለ ዘኪ ቀናነት ሲናገር ብሩህ ተስፋን የማጋባት ሀይል አለው፡ ይላል፡፡ ‹‹…እንሰራለን ፤ ነገሮች ይሳካሉ በርታ በማለት ለሰዎች ሞራል የሚሰጥ ሰው እንደነበርም ተናግሯል፡፡
ዘካርያስ በብርሀኑ አየለ አንደበት
ዘካሪያስን ከ1994 ከሜጋ ማስታወቂያ ጀምሮ አውቀዋለሁ።በስራው ፍፁም ታታሪ ነው።ታማኝ ነው።በሙያው የአዕምሮ ፍጥነቱ ድንቅ ነው ነገሮችን የሚያይበት መንገድ ያስቀናል “ከዘኪ ትልቁ”ጋ ሰርቶ እራሱን ለማሳደግ የማይጥር አልነበረም።ብዙዎቻችንን ነጥረን እንድንወጣ በተለያየ መንገድ ቀርፆናል።ዘኪ ተዋጊ ነው የማይሸምቅ ነገሮችን እንደአመጣጣቸው ለመመለስ ፊት ለፊት የሚጋፈጥ ብርቱ። በዘመኑ በፊልሙም ሆነ በማስታወቂያው ዘርፍ ጉልህ አሻራውን ትቶ ያለፈ ታታሪ። የመጀመሪያውን ኢትኖግራፊክ ፊልም ፀማኮን ፅፎ፣ቀርፆ፣አዘጋጅቶ ለተመልካቹ ያበረከተ የሙያው ሰው ነበረ።በማስታወቂያው ዘርፍ ዛሬም ድረስ ወዘናቸው ያልደበዘዙ ልዩ ልዩ ስራዎቹ ህያዋን ሆነው ይታወሳሉ።እነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣አዋሽ ወይን ጠጅ፣አቡወለድ፣ማጂ መረቅ መጥቀስ ይቻላል። ተዋናይም ተዋናይትም ለሙያው ለማብቃት ለሱ ቀላል ነው። ሀሌታን ከጓዶቹ ጋ መስሮቶ ስራውን በሰፊው ሲያያዙት የመጀመሪያው ተቀጣሪ ነበርኩ።የኮሌጅ ትምህርቴን ስጨርስ በብርቱ ከረዱኝ መካከል ዘኪ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ ነበር፤በሙያዬ ላቅ ያለ ስፍራ ላይ እንድደርስ ብዙ ምክሮችን ለግሶኛል ።
ሕዳር 23 ጠዋት ገደማ በስራው ዓለም የቅርብ ጓደኛው እና ሀሌታ በነበርኩ ጊዜ ስራ አስኪያጁ ዛሬ ወዳጄ ዳግማዊ ፈይሳ “አሳዛኙን እውነት አረዳኝ”
ዘካሪያስ አገሩ መጥቶ ታሞ ሰንብቶ ያለአንዳች ጠያቂ”ከጓደኞቹ”ብቻውን ከርሞ ማረፉ ነገረኝ።አሜሪካን አገር ለ17አመታት ኖሯል እዛ በነበረ ጊዜ ለተወሰኑ ጊዜያት በፌስ ቡክ ተፃፅፈናል ደውሎም ስለ ስራዬ(ስለ ድምፄ)ምክር ጣል አድርጎልኝ ተቀላልደን መለያየታችን ትዝ ይለኛል። በስተመጨረሻ በተለይ የቀብሩ- ሰዓት እየቀረበ ሲመጣ ለእኔ እንግዳ የሆነ ነገር ፈፅሞ ልገምተው የማልችለውን ነገር ሰማሁ፡፡
ደስታና ፤ሃዘን ወረሩኝ የዘልዓለም አምላክን አመሠገንኩ፡፡ ነብሱ በጌታ ዘንድ እንዳረፈች ተሰማኝ፡፡ ልቤ ሃሴት አደረገ።በምድር አንድ ነብስ ሲድን በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል የሚለው ቃል ተስፋዬን ሞላው።ዘኪ ከምድር እንቶ ፈንቶ ተላቆ ነገን በተድላ ለመኖር ወደ አባቱና አባቴ ወደ ጌታ እንደሄደ ገባኝ።ከኢትዮጵያ ወጥቶ አሜሪካን በኖረ ጊዜ “ፋኖ”እጁን፣ነብሱን፣ማንነቱን ለጌታ ሰጥቶ ታዞ አገልግሎት እንደነበር ይበልጥ ገባኝ። ሲቀበር መልዓክት በክብር ወደ አባቱ እንደወሰዱት አወቅሁ።እኛም ጌታን በዘኪ እያከበርን እየዘመርን ግባ ከመሬትን ፈፅመን ተመለስን። የቆጨኝ ነገር:- አንዴ አውርቼው ፣ቀና አድርጌው ስለጌታ ተጨዋውተን፣ቃል አንብበን ፍፃሜውን አለመቅደማችን ብቻ ።ሆኖም ጌታዬ በነገር ሁሉ አይሳሳትም እና ስለሆነው ሁሉ አመሰግነዋለሁ።
የዘኪ 72 ምስልና ሰነዶች እንዲሁም አንዳንድ ነገሮች
ሰነድና ምስሎች ብዙ ይናገራሉ፡፡ ከምስል ተነስተን ታሪክ መናገር ብሎም መተንተን እንችላለን፡፡ ዘካርያስ ወደ መንፈሳዊ ህይወት ከገባ በኋላ ከሰራቸው ስራዎች ይልቅ የእግዚአብሄር ነገር በልጦበት ነበር፡፡ የተረዳው የክርስቶስ እውነት ልቆበት አዲስ መረዳት ውስጥ ነበር፡፡ በመሆኑም በአሜሪካንም ሆነ ሀገር ቤት ከሚደረጉ የጥበብ ድግሶች ጋር ርቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ሳሙኤል ኃይለማርያም የዘኪን ሰነድና ምስሎች ጠብቆ በማቆየት አስረክቦኛል፡፡ ምስልና ሰነዶቹ ብዙ ይናገራሉ፡፡ ዘካርያስ ከልጅነት እስከ አሁን ያለፈበትን ይናገራሉ፡፡ዘኪ ገና የ10 አመት ልጅ ሳለ በጎሬ የተነሳው ምስል ይታያል፡፡ በነገራችን ላይ የዘኪ አባት አቶ ኃይለማርያም ጉደታ የታወቁ ዳኛ ነበሩ፡፡ በአብዮቱ ጊዜ በ1971 ገና የ51 አመት ጎልማሳ ሳሉ ሕይወታቸው ያለፈ ሀገር ወዳድ ናቸው፡፡ እናቱ ወይዘሮ ባሪቱ መጫ አሁንም በህይወት አሉ፡፡
ዘካርያስ 3 እህቶችና አንድ ወንድም ያለው ሲሆን ስማቸውም ታላቅ እህቱ ብሩክታዊት ፤ ቸርነት፤ ሳሙኤልና መቅደስ ይባላሉ፡፡ ዘኪ ገና 14 አመቱን ማከበረ ማግስት የጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ቤት ሳለ የእናት ሀገር ጥሪን አክብረሀል፤ይህንንም በመዝመት ግዳጅህን ፈጽመሀል ተብሎ የምስክር ወረቀት ተቀብሏል፡፡ ይህንን ምስክር ወረቀት ሳጤን የዘኪ የሀገር ፍቅር ገና በ14 አመቱ አንድ ማለቱን መገንዘብ ችያለሁ፡፡ ይህንን የምስክር ወረቀት ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሬ ፖስት ስላደረግኩት ፈልገው መመልከት ይችላሉ፡፡ ሌሎች ፎቶዎችም አሉ፡፡ ዘኪ በስፖርት የጠነከረ ሰውነት ማዳበሩን የምታዩበትም ምስል አለ፡፡ በምስሎቹ ላይ የ1978 የቴአትር ጥበባት ተማሪዎች፤ የ1980ዎቹ የኢቲቪ ባልደረቦች ፤ የዘኪ የ1992 ሰርግ እና የማዘጋጃ ቤት የፊርማ ስነስርአት ሁሉ አለ፡፡ምስሎቹን ቢመለከቱ ዘመንን ከሁኔታ ጋር አሰናስለው ስለሚናገሩ ቢመለከቱት አይከፋም፡፡
ዘኪና ያልታተመው ማስተማርያ መጽሀፉ
‹‹የፊልምና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ጥበብ ሚስጥር›› ይላል የመጽሀፉ ርእስ፡፡ ዘኪ በዚህ ርእስ መጽሀፍ ለማዘጀት የረጅም ጊዜ እቅድ ነበረው፡፡ እና ይህንን ህልሙን እውን ለማድረግ መጽሀፍ ጀምሮ እንደነበር ወንድሙ ሳሙኤል ይናገራል፡፡ ዘኪ በመጽሀፉ መግቢያ ላይ ያሰፈረውን እስቲ በፊል እንመልከት ፡፡ ‹‹…….በአገራችን የፊልም ፕሮዳክሽን እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ ላይ መገኘቱ ይህንን ስራ ሰርቶ ለህዝብ ለማቅረብ ትልቅ አጋጣሚ ሆኗል፡፡ ዛሬ በፊልም ሙያ ለመዝለቅ ለሚፈልግ ሁሉ በአገሩ ቋንቋ የተዘጋጀ የዚህ ጥበብ መጀመርያ ሊሆን የሚችል መጽሀፍ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡፡፡ ›› እያለ ይቀጥላል፡፡
ዘኪ እና የታተመው መጽሀፉ
‹‹የመከራ ቋት›› በ1986 የዛሬ 29 አመት ዘኪ የ33 እድሜውን ያከበረ ሰሞን ያሳተመው የልቦለድ ድርሰቱ ሲሆን በ5000ቅጂ የታተመ ነው፡፡ ይህ መጽሀፍ በዚያን ጊዜ በ7 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን በመጽሀፉ ላይ የጀርባ ሽፋን አስተያየት የሰጡት ደግሞ ሙሉጌታ ጉልማ የተባሉ ሰው ነበሩ፡፡
ሙሉጌታ ጉልማ የዘካርያስን የመከራ ቋት የተሰኘ ልቦለድ ድርሰት ካነበቡ በኋላ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡ ‹‹…. አንዴ ብቻ ጥቂት መስመሮችን ያንብቡ፡፡ በሙሉ ካልጨረሰሱት በስተቀር ፈጽሞ አያስቀምጡትም፡፡
ይህ ፈጣን በተንኮል የተሞላ በፍቅር በጥላቻና በስግብግብነት የተጠላለፈ ታሪክ እዚህች ሀገር ውስጥ ከምታገኙዋቸው አልፎ አልፎ ስሜትን ከሚያስጨንቁ የፈጠራ ስራዎች መሀል አንዱ ነው፡፡ የመከራ ቋት በአጥማጅ ላይ የተጠመደ ወጥመድ የሚስተዋልበት ፈር ቀዳጅ የስነ-ጽሁፍ ስራ ነው ›› ብለው ነበር ሙሉጌታ ጉልማ
ዘካርያስ ኃይለማርያም
ስለ ዘካርያስ ኃይለማርያም ብዙ ነገሮችን ማለት ይቻላል፡፡ ከእኔ በፊት ስለ እርሱ ምስክርነታቸውን የሰጡ ብዙ ሰዎች ያሉትን ሳልጨምር በመንፈሳዊ ሕይወቱ ላይ የነበረውን መረዳትና መሰጠት ትኩረት በማድረግ፣ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን ስለነበረው አገልግሎት ባጭሩ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡ ዘኪ ለእኔ በቤተ ክርስቲያን ብቻም ሳይሆን በሜሪላንድ ግዛት አሜሪካን አገር ጎረቤትም ነበርን፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙ የምንተዋወቅ ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ እንድተዋወቀው የረዳኝ ነገር ብዙ ተከታታይ የመጽሐፍ ቅዱስ የደቀ መዝሙር ትምህርቶችን ሳስተምር ነበር፡፡ ዘኪ ጊዜውና ትኩረቱን ሰጥቶ በሙሉ ልቡ ተምሮ የጨረሰና እግዚአብሔርንና ቃሉን የሚወድ፤ እንዲሁም በሰው ሁሉ ዘንድ የተወደደ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ስለሚወድ ብዙ በማንበቡ ቃሉን ለመረዳት ረጅም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በመጽሐፍ ቅዱስ ኅብረት ውስጥ አብረን እናጠና ስለ ነበር የእርሱን ጥያቄዎችና የሚሰጣቸውን መልሶች ለመስማት እንወድ ነበር፡፡
በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያናችን የነብሩትን ስብከቶችን በመቅረጽ ኩልልና ጥርት ብለው የሚሰሙ በማድረግ አርሞ በዩቱብ በመለጠፍ ለብዙዎች የሕይወት መለወጥና መታነፅ ምክኒያት የሆነ ሰው ነበር፡፡ ዘኪ የመቅረጫ መሣሪወችን በራሱ በማምጣት አንድም ቀን ሳይሰለች እግዚአብሔር ያገለገለ ውድ ወንድማችን ነበር፡፡ የስበከት ጊዜም ሲሰጠው በምስል በማስደገፍ በሕይወታችን የማይረሱ ትምህሮችን በማቅረብ ምሳሌያችን ሆኖልናል፡፡ እርሱ የፊልም ባለሙያ ስለነበረም መጽሐፍ ቅዱስን በተለያዩ ምስሎች በማስደፍ መልዕክቶቹን የማይረሱ አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ ያቀርባቸው የነበሩ ግጥሞችና መጣጥፎችም በጉጉት የሚወደዱ፤ ለጆሮ የሚስቡ፣ ወደ ሰው ልብ ሰርጸው የሚገቡ ነበሩ፡፡ዘኪ ስብከት ከሰበከ ስዕሎችንና የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያወችን መያዝ የተለመደ ነበር፡፡ እርሱ በፕሮጀክተር እያሳየ ሲያስተመረን እኛም ተመስጠን ስንሰማ ሳይሰለቸን ነበር የሚጨርሰው፡፡ እርሱ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር በተመስጦ እንሰማውና እንደነቅ ነበር፡፡ ለዓመታት ከእርሱ ያየሁት ነገር ቢኖር በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ብዙ ዝናን በሥራው ቢያተርፍም፤ በመጨረሻወቹ ዘመኖቹ ጌታን ኢየሱስን ማወቁና መከተሉ ከሁሉ ይበልጥበት ነበር፡፡ ዘኪ ለብዙ ዓመታት በሚዲያ ሥራው ብዙ ዝናን ያተረፈ ቢሆንም የወደፊት ዕቅዱ ደግሞ በወንጌል ሥራ የጀመረውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በሚዲያ ለማስፋፋት ነበር፡፡ እኛም የዚህን ታላቅ ሰው ራዕይና ፈለግ በመከተል ሥራውን እናስቀጥላለን፡፡
ዶክተር ወርቁ ተገኝ ወልደሩፋኤል (መጋቢ) የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ወንጌላዊ ቤተ ክርስቲያን ከሜሪላንድ አሜሪካ ዘካርያስ ባለፉት 12 ወራት በኢትዮጵያ 17 አመታት መኖርያውን በባህር ማዶ አድርጎ የነበረው ዘካርያስ በአንድ በኩል በ encore global በሁነት አዘጋጅነት እየሰራ ደግሞ በሌላ በኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ኢቫንጀሊካል ቸርች ጀርመንታውን አጥቢያ የእግዚአብሄርን ቃል በማካፈል እያገለገ ኑሮን እየገፋ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ግን መጠነኛ የነርቭ ህመም እንዳለበት ሀኪሙ ይነግረዋል፡፡ እናም ዘኪን ማድረግ ያለበትን ህክምና ሁሉ በምድረ-አሜሪካ አደረገ፡፡ እና ምናልባት የአየር ለውጥ ለጤናው ከጠቀመ በሚል የሀኪም ምክር የዛሬ አመት ህዳር 2014 ሀገር ቤት ይገባል፡፡ ህመሙ ጥልቅ እረፍትና መረጋጋት ስለሚሻ ዘኪ ከቅርብ ቤተሰቦቹ ጋር ሆኖ ራሱን ማስታመም ነበረበት፡፡ ታዲያ በእዚያ ሰአት ዘኪ ድኖ ጓደኞቹን ለማየት ትልቅ ናፍቆት ነበረው፡፡‹‹ ጌታ ቢፈቅድ ደህና ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር የማዋራበት ቀን ይመጣ ይሆናል ›› እያለ በተደጋጋሚ ይናገር ነበር፡፡ እስከዚያ ግን ብዙ ሰዎችን ሳያገኝ ለ1 አመት ቆየ፡፡ ህዳር 22 2015 ግን የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖ ወደ ጌታ ሄደ፡፡
ወንድሙ ሳሙኤል እንደነገረኝ ከሰሞኑ ዘኪ ደህና ነበር፡፡ የአለም ዋንጫ ሁሉ እያየ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የኢቲቪ እና የሜጋ ትዝታዎችን ማውጋት ደስ ያሰኘው ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ይህ ጨዋታ ዳግሞ ከጓደኞቹ ጋር ለማድረግ የፈጣሪ ፈቃድ አልሆነም፡፡ ዘኪ ህዳር 22 2015 በጌታ እቅፍ ውስጥ ሆነ፡፡
ከተወዳጅ ሚድያ÷ ይህ ጽሁፍ የዘካርያስ ሀይለማርያምን የቅርብ ቤተሰቦች በማነጋገር አስፈላጊ ሰነዶችን በማመሳከር የተጻፈ ነው፡፡ የጽሁፉም አላማ ዘካርያስ ኅይለማርያም በህይወት በቆየባቸው 62 አመታት በጥበብ እና በመጽሀፍ ቅዱስ ማስተማር ላይ የሰራው ስራ ትውልድ እንዳይዘነጋው አጽንኦት ለመስጠት ነው፡፡ በተጨማሪም በሀገሪቱ የሰሩ ሰዎች ካለፉ በኋላ ታሪካቸው ተረስቶ እንዳይቀር ለምርምር ይረዳ ዘንድ አንድ መነሻ ለማቅረብ በሚል የተሰናዳ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ በተወዳጅ ሚድያ የኢትዮጵያውን የክብር መዝገብ ታሪክ ውስጥ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚቀመጥ ሲሆን የጽሁፉም አሰናጅ በግለ-ታሪክ ላይ የ23 አመት ልምድ ያካበተው ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው፡፡ ጽሁፉ አስፈላጊው የማከልና የማሻሻል ስራዎች ተጨምረውበት በየጊዜው እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡
የዘካርያስ የመጽሀፍ ቅዱስ ትምህርቶች
- https://youtu.be/wioa2hTofwo
- https://youtu.be/MkmpfARtukc
- https://youtu.be/wj6SUkxysQE