ዶክተር ሀይለገብርኤል ዳኜ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ በትምህርት ሚኒስትርነት ፣በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉት ዶክተር ሀይለገብርኤል ዳኜ ከ 3ቀን በፊት ሚያዝያ 5 2010 ህይወታቸው አልፏል፡፡ ተወዳጅ የሚድያና የኮሚኒኬሽን ማእከል በእኚህ ምሁር ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለመላ ቤተሰባቸውም መጽናናትን ይመኛል፡፡ ዶክተር ሀይለገብርኤል ዳኜ ለሀገር ትልቅ ውለታ የዋሉ በመሆናቸው ታሪካቸውን በእንዲህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡፡
ኃይለገብርኤል ዳኜ ከወ/ሮ ወርቅነሽ ራስወርቅና ከቀኛዝማች ዳኜ ኃይሌ መስከረም 10 ቀን 1923 ዓ.ም. በቀድሞ አጠራሩ በሀረርጌ ጠቅላይ ግዛት በወበራ አውራጃ ጎላ ወረዳ ተወለደ፡፡ አባቱ ፀረ ፋሽስት ሽምቅ ተዋጊ ስለነበሩ በሞቃዲሾ ለእስር ሲዳረጉ በጊዜው እንደብዙዎቹ የኢትዮጵያ ህፃናት አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፏል፡፡
አባቱ ወደሀገራቸው ተመልሰው ቤተሰቡ እንደገና ሲቋቋም ህፃኑ ኃይለገብርኤል በደሩ ማርያም የኔታ መኩሪያ ዘንድ ፊደል ቆጥሮ ዳዊት ደግሟል፡፡
በአዲስ አበባ ዘመድ ዘንድ ሆኖ ዘመናዊ ትምህርት እንዲማር እናቱ ወ/ሮ ወርቅነሽ ራስወርቅ ከደደር አምጥተውት ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በዚያም ከት/ቤት ጓደኞቹ ከእነዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ አቃቤ ህግ ተሾመ ገብረማርያም፣ ዳኛ ንጉሤ ፍትዓወቅና ከሌሎችም ጋር የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡
ኃይለገብርኤል ዳኜ በ1943 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብቶ ለአንድ ዓመት ከተማረ በኋላ ወደግሪክ አቅንቶ አቴንስ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሥነ-መለኮት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ኃይለገብርኤል ዳኜ ወደሀገሩ ኢትዮጵያ በመመለስ ሐረር ከተማ በሚገኘው መንፈሳዊ ት/ቤት በርእሰ መምህርነት አገልግሏል፡፡ በ1948 ዓ.ም. ደቡብ ሮዴዢያ ኮንፍረንስ ለመካፈል ሄዶ በወቅቱ የነበረው የነጮች የአፓርታይድ አገዛዝ እጅግ ስላሳዘነው ለጥቁሮች ነፃነት በዚምባቡዌ፣ በናሚቢያና በሌሴቶ በመዘዋወር ፀረ አፓርታይድ ትግል አካሂዷል፡፡
ከዚያም ወደኢትዮጵያ ተመልሶ ስለአፓርታይድ አገዛዝ ሥርዓት አስከፊነት በየትምህርት ቤቱ በመገኘት ለወጣቶች ግንዛቤ አስጨብጥዋል፡፡ በ1955 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል በሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ላይ ተካፍሏል፡፡ ወጣቱ ኃይለገብርኤል ለትምህርት በነበረው ጽኑ ፍቅር ወደጀርመን አገር በመሄድም ፍሪ ዩኒቨርስቲ ኦፍ በርሊን በመግባት በኢዱኬሽን የትምህርት ዘርፍ እንዲሁም በታሪክና በሶሲዮሎጂ በ1959 ዓ.ም. በዶክትሬት ተመርቋል፡፡
ዶ/ር ኃይለገብርኤል በጀርመን ሀገር በትምህርት ላይ በነበረበት ጊዜ ለእናት አገሩ ኢትዮጵያ እድገትና ለህዝቧ ኑሮ መሻሻል በጎ በመመኘት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበርን ከመሠረቱት አንዱ በመሆን ድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ ከፍተኛ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደኢትዮጵያ በመመለስ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢዱኬሽን ዲፓርትመንት በሥነ-ትምህርት ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት በማስተማር አያሌ ምሁራንን አፍርቷል፡፡
ጎልማሳው ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ በ1966 ዓ.ም. በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የመጨረሻው የሥልጣን ዘመን የትምህርት ሚንስትር ሆነው በመሾም ሶስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በመቀጠልም ከ1969 ዓ.ም. አንስቶ ለሰባት ዓመት በምዕራብ ጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡
አምባሳደር ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ ወደአንጋፋው የትምህርት አንባ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው ከ1976 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ የማስተማርና የምርምር ተግባራትን ያከናወኑ አሶሺዬት ፕሮፌሰር ነበሩ፡፡ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል በዚህ የኃላፊነት ዘመናቸው ተማሪዎች መንግሥትን ሲቃወሙ ወታደሮች እንዳይጎዷቸው ፊት ለፊት በመጋፈጥ የማረጋጋት ሥራ ያከናውኑ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
በ1977 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርቅ አጋጥሟት በነበረ ጊዜ ተጎጂ ወገኖችን ውሀና ለም መሬት ባለበት የአገራችን ክፍሎች ለማስፈር በተደረገው ጥረት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችንና መምህራንን በማስተባበር ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል የኢትዮጵያን መምህራን ማኅበር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ሊቀመንበር በመሆንም ማኅበሩን በከፍተኛ ኃላፊነትና ብቃት መርተዋል፡፡
ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጥናትና መርምር ሥራ ላይ ማሳለፍን ይመርጡ ነበር፡፡ በዚህ መሠረትም በርካታ የምርምር ውጤቶችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለህትመት አብቅተዋል፡፡ ከታተሙት ሥራዎቻቸው መካከል ‹‹ባሕልና ትምህርት በኢትዮጵያ›› የተሰኘው መጽሐፍ ይገኛል፡፡
በሌላም በኩል በልዩ ልዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካሪና አሠልጣኝ በመሆን በልዩ ልዩ መስኮች በይበልጥም በሥነ – ተዋልዶ ጤና ትምህርት ረገድ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አሠልጥነዋል፡፡ ለሥልጠናዎቹ የሚያገለግሉ መመሪያ መጻህፍትንም አዘጋጅተዋል፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ሩቅ አሳቢ በመሆናቸው የእውቀት እጦትና ጎጂ ልማዶች እየተወገዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዲሸጋገር ምሁራዊ ድርሻ አበርክተዋል፡፡
‹‹ሶሺያል ፋውንዴሽን ኦፍ ኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ ከሉሲ አንስቶ በተለይም የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን፣ የደርግን ጊዜና የአሁኗ ኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓቶች በጥልቀት በመመርመር እጅግ ጠቃሚ ሰነዶችን አዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህን ሥራዎች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ተረክቦ በሁለት ተከታታይ ቅጾች በማሳተም ላይ ይገኛል፡፡
ዶ/ር ኃይለገብርኤል ሕይወታቸው ሊያልፍ ጥቂት ቀናት እስከቀሩ ድረስ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ሃያ ስድስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናት ላይ ትኩረት በማድረግ የብራና መጻህፍትን በሙሉ በመመዝገብና ቅርጽና ይዘቶቻቸውን በመግለጽ (ካታሎግ በማድረግ) ላይ ነበሩ፡፡
በአንኮበር የሚገኘውን የቀድሞውን የዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት በማይጨው ጦርነት ጊዜ የጣሊያን ፋሺስቶች አውድመውት ስለነበረ የአስተናነጹን ባሕርይ ጠብቆ በአዲስ መልክ ‹‹አንኮበር ሎጅ›› በመባል የሚታወቀው ህንፃ እንዲገነባ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የህንፃው ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላም እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ በዋና ሥራ አስኪያጅነት አገልግለዋል፡፡
ዶ/ር ኃይለገብርኤል የአንኮበር ልማት ማኅበር ሊቀ መንበር በመሆን ከአገር ውስጥና ከውጭ የገንዘብ ድጋፍ በማፈላለግ አካባቢው እንዲለማ የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡ አንኮበር ውስጥ በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ስም ለተሠራው ቤተ-መዘክር የሙያ እገዛ አድርገዋል፡፡
በቤተ-መጻህፍትና በቤታቸው ውስጥ ማንበብ የሚያዘወትሩት ዶ/ር ኃይለገብርኤል በትርፍ ጊዜያቸው የእግር ጉዞ ማድረግንና በውይይትና በሚኒባስ ታክሲዎች በመጓዝ ከወገኖቻቸው ጋር መጨዋወትን የሚወዱ ነበሩ፡፡ ለአስር ዓመታትም ‹‹ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ›› ስፖርታዊ ውድድር ተሳትፈው ሩጫዎቻቸውን በብቃትና በጥንካሬ አጠናቀዋል፡፡
ዶ/ር ኃይለገብርኤል ባከናወኗቸው በጎ ተግባራት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከውጭ አገር መንግሥታት የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ በ1963 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ከወ/ት መቅደስ ዓለሙ ጋር ተጋብተው ሁለት ሴት ልጆችና አንድ የልጅ ልጅ አፍርተዋል፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ከባለቤታቸው ከወ/ሮ መቅደስ ዓለሙ ጋር በባልና ሚስትነት ብቻ ሳይሆን እንደጓደኛም ሆነው ልጆቻቸውን በፍቅርና በሥነ – ምግባር አሳድገውና አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡
ዶ/ር ኃይለገብርኤል ከቅርብ ቤተሰቦቻቸውም አልፈው ዘመድ አዝማድን በማቀራረብ እንደመልህቅ ሆነው ያገለገሉ እጅግ ተወዳጅና አለኝታ ነበሩ፡፡ ለዚህም በአባታቸው የፀረ ፋሺስት ትግል ማስታወሻ ጽሑፍ ላይ ተመስርተው ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ስለዘመድ አዝማዶቻቸው ያካተተና በእርሳቸው ጥረት የታተመው መጽሐፍ ቋሚ ምስክር ነው፡፡
ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ ባጋጠማቸው የጥቂት ቀናት ህመም ሚያዚያ 5/2010 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩን ቢሆንም አርአያነት ያለው ሰብእናቸው ምንጊዜም የማይከስም በመሆኑ ለቤተሰባቸው፣ ለዘመዶቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡ በባህርያቸው ፍፁም ቅን፣ በምሁራዊ ማንነታቸው ለእውነትና ለእውቀት ቆመው ድርሻቸውን አበርክተው ያለፉ በመሆናቸው ምንጊዜም ይታወሳሉ፡፡ ዶክተር ሀይለገብርኤል እሁድ ሚያዝያ 7 2010 ኮተቤ በሚገኘው የሀና ማሪያም ቤተክርስቲያን የቀብር ስነ ስርአታቸው የተፈጸመ ሲሆን ለመላ ወዳጅ ዘመድ መጽናናትን እንመኛለን፡፡