የሚድያ ሰው ጌታቸው ኃይለማርያም  ማስታወሻ ተደረገለት

የዛሬ 30 ዓመት ህይወቱ ያለፈው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም በሙያ ባልደረቦቹ  የማስታወሻ ዝግጅት ተደረገለት ፡፡

የእሁድ መስከረም 12 2017 ዓ.ም  ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ  በወመዘክር አዳራሽ  በተከናወነው በዚህ ዝግጅት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን  ባልደረቦች ታድመወል፡፡

የማስታወሻ ዝግጅቱ ሀሳብ አመንጪ እና አዘጋጅ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሲሆን   በዕለቱም ጋዜጠኝነትን የሚያጠኑ የጋዜጠኝነት ማዕከል ተማሪዎች  በመሰናዶው ላይ ታድመው ነበር፡፡

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ በጠቅላላው ከ 24 ዓመታት በላይ ያገለገለ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ በተለይም በዜና አቀራረብ እና አንባቢነት ለብዙዎች አርአያ የሆነም የሚከበር ጋዜጠኛ ነበር፡፡

በማስታወሻ ዝግጅቱ ላይ፣ ስለ ጌታቸው ምስክርነት የሰጡት ጋዜጠኛ ሚሊዮን ተረፈ ፤ እና ጋዜጠኛ  ታዬ በላቸው ጋዜጠኛ ሀይሉ ወልደጻድቅ ÷ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ወልደሚካኤል  ጋዜጠኛ ዘሪሁን ብርሀኔ ሲሆኑ በተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን  የተዘጋጀ የ20 ደቂቃ የድምጽ ዘጋቢ ሥራም ተደምጧል፡፡

የሚድያ ሰው ጌታቸው ኃይለማርያም፣ አሁን በአንጋፋነታቸው እውቅና የተቸራቸውን  እንደ  ዋጋዬ በቀለ ነጋሽ መሀመድ፣ አለምነህ ዋሴ፣ ንግስት ሰልፉ እና ብርቱካን ሀረገወይንን የመሰሉ ባለሙያዎች ለሙያዊ ብቃት እንዲደርሱ በማሰልጠን እና ልምዱን በማካፈል የበኩሉን የተወጣ ባለሙያ ነበር፡፡ ,ዜና ፋይል “የተሰኘውን ፎርማት ለመጀመረያ  ጊዜ እንዳስተዋወቀ እና እንደፈጠረ የሚነገርለት ይህ ሰው በብስራተ ወልጌል የሬድዮ ጣቢያም ሙያዊ አደራውን ሲወጣ ነበር፡፡ 

ታላቁ የሚድያ ሰው ጌታቸው፣ ከዚህ ቀደም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባሳተመው ‹‹መዝገበ አእምሮ የሚድያ ሰዎች ኢንሳይክሎፒዲያ›› ላይ ታሪኩ የተሰነደለት ሲሆን ከዚህ ቀደም ያነበባቸው ዜናዎች እና ምስሎቹም ወግ በያዘ መልኩ ለታሪክ እንዲቀመጥለት ተደርጓል፡፡

ይህ የማስታወሻ ዝግጅት እውን እንዲሆን የጋዜጠኝነት መምህር አብርሀም ፀሀዬ እና ስብሀቲዝም ቡድን አባላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም የተወዳጅ ሚድያን የስነዳ ሀሳቦች ምንግዜም የሚደግፈው ታሜሶል ኮምዩኒኬሽን (ሰለሞን ከበረ) የዝግጅቱ ተባባሪ በመሆን አለኝታነታቸውን አሳይተዋል፡፡

የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መስራች ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ከዚህ ቀደም የ45 ሰዎችን ታሪክ  በሲዲ፣ የ20 ሰዎችን የህይወት ታሪክ በመጽሀፍ ያዘጋጀ ሲሆን ባለሙያዎች በህይወት እያሉና ካለፉም በኋላ ስማቸው በድምቀት መነሳት አለበት የሚለውን ዓላማ አንግቦ በመነሳት እስከዛሬ ከ 30 በላይ ሁነቶችን ለማዘጋጀት በቅቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *