ዓለምፀሐይ ወዳጆ

የቴአትር ጸሀፊ ፤ገጣሚና አዘጋጅ ዓለምፀሓይ የተወለደችው በ1948 ዓ.ም ዐዲስ አበባ ውስጥ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ‹ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ት.ቤት› ተከታትላለች። የሙዚቃ መምህሯ፣ ደራሲ መላኩ አሻግሬ ለቴአትር መርጠዋት በ‹አገር ፍቅር ቴአትር› መድረክ ላይ የምትተውንበትን ዕድል አገኘች። በተመሳሳይ፣ በዐማርኛ መምህሯ አየለ አበረታችነት በክፍል ውስጥ ግጥሞች ታቀርብ ነበር።

ዓለምፀሓይ ያደገችው በአያቶቿ ክብካቤ ነው። ከወንድ አያቷ ንባብን፣ ከሴት አያቷ ደግሞ ጥንካሬና ብርታትን መውረሷን ትናገራለች። ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በተከታተለችበት ‹መድኃኔ ዓለም ት.ቤት› በሥነ ጽሑፍ ውድድርና ክርክሮች ላይ፣ አንዳንዴም በዕድሜና በትምህርት ደረጃ ከሚበልጧት ጋራ ተሳትፋ ታሸንፍ ነበር።በዚሁ ትምህርት ቤት የተማሪዎች መማክርት ጉባኤ ውስጥ በምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግላለች። እንዲሁም ‹የቴአትር ዕድገት ክበብ› ውስጥ አባል ነበረች። የክበቡ አባላት ከትምህርት ቤት ሲወጡ በ‹አገር ፍቅር› ተሰብስበው ቴአትር ይሠራሉ።

በዚህም አጋጣሚ በአገሪቱ ውስጥ ‹ዕንቊ› ከተባሉ፣ እንደ ተክሌ ደስታ፣ ሲራክ ታደሰ፣ ዓለሙ ገብረ አብ፣ ትሩፋት ገብረየስ ከመሳሰሉ ተዋናዮች ጋራ የመሥራት ዕድል ገጥሟታል።የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች፣ በሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን የተጀመረውንና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሚሰጠውን የ2 ዓመት የቴአትር ትምህርት ተከታትላ በዲፕሎማ ተመርቃለች። የቴአትር ሥራዋን ወላጅ አባቷ አልወደዱላትም ነበር። ለብዙ ጊዜም በኀይል ለማስቆም አሳደዋታል። በኋላ ግን ‹‹ሐምሌት›› የተሠኘውን ተውኔት ከወጋየሁ ንጋቱ ጋራ መድረክ ላይ ስትጫወት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከቱና ተመልካች ለልጃቸው ያለውን ፍቅርና አክብሮት ሲያዩ ይቅርታ ጠይቀዋታል።

ዓለምፀሓይ ለ17 ዓመት በቈየችበት ‹ብሔራዊ ቴአትር› የ‹‹ሕዝብ ግንኙነት››፣ የ‹‹ቴአትር ክፍል››ና የ‹‹ፕሮግራምና ፕሮዳክሽን›› ኀላፊ ኾና አገልግላለች። ከትወና ዐለፍ ብላም፣ በቴአትር ጽሑፍና ዝግጅት ተሳትፋለች፤ በዚህም የመጀመሪያ ሴት ናት። ይህን ሙያዋን ለማዳበርም ጀርመንን ጨምሮ በሶቭዬት ኅብረት፣ በቡልጋሪያ፣ በቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያና ሌሎች አገራትም ተዘዋውራለች።‹የተዋናዮች ማኅበር›ን መሥርታ ለ14 ዓመት በመሪነት አገልግላለች። በአንድ ወቅት ጀርመን ለተውኔት ሥልጠና ኼዳ እያለ የተመለከተችው የሕጻናት ቴአትር በአገሯ እንዲኖር አድርጋለች። በርሷ ጕትጐታ የተነሣም ‹‹የሕጻናት ቴአትር ክፍል›› በወቅቱ በነበረው የ‹ባህል ሚኒስቴር› ሥር ተከፍቷል። በቅድመ ዝግጅቱ ኺደትና በመጀመሪያዎቹ ሰባት ዓመታት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ ነበራት።ወደ ‹ሕፃናት ዐምባ› ልጆች በማቅናት በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በሥዕልና በመሳሰለው የጥበብ መስክ፣ አንጋፋ ባለሙያዎችን ጭምር በመጋበዝ እንዲሠለጥኑ ታደርግ ነበር። በርካታ ቅዳሜና እሑዷንም ከ‹ሕፃናት ዐምባ› ልጆች ጋራ አሳልፋለች።የ‹ኢሕአዴግ›ን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ በ1983 ዓ.ም አገሯን ለቅቃ ከወጣች በኋላ ‹ጣይቱ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ማዕከል›ን በሰሜን አሜሪካ አቋቋመች። በማዕከሉ፣ 111 የሚጠጉ አማተር ተዋናዮች አፍርታለች፤ ከ60 በላይ ቴአትር ተሠርቷል፤ ቡድኑም በዓመት እስከ 17 ግዛቶች በመዘዋወር የጥበብ ሥራዎችን አቅርቧል።ዓለምፀሓይ 30 የሚጠጉ ዓመታትን በስደት ቈይታ ወደ አገሯ ስትመለስ፣ ‹ጣይቱ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ማዕከል› በዐዲስ አበባ ላይ እንዲከፈት ማድረግ ችላለች።የንባብ ወዳጇ ዓለምፀሓይ፣ ‹‹ማረፊያ ያጣች ሕይወት››ና ‹‹የማታ እንጀራ›› የተሠኙ የግጥም ስብስብ መጻሕፍት ለአንባብያን ያደረሰች ሲኾን፣ በብርዕ ስምና በራሷም ስም ለ52 ወጣትና አንጋፋ ድምፃውያን ግጥሞችን አበርክታለች። ለእነዚህ ሥራዎቿ ከ65 በላይ ምስጋና፣ ሽልማትና ዕውቅና በተለያዩ ጊዝያት አግኝታለች። በየዓመቱ በልዩ ልዩ ዘርፍ ውጤታማ ሥራ ያከናወኑ ሰዎችን በመሸለም የሚታወቀው ‹ማኅበረ ጊዩራን ዘረ ኢትዮጵያ› (SEED) የተሠኘው ዓለም ዐቀፍ ድርጅት በኪነ ጥበብ ዘርፍ ያበረከተላት ሽልማት ተጠቃሽ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *