አቶ ነብዬ ልዑል ክፍሌ-የሀገር ባለውለታ

ነብዬ ልዑል

1926 – 1967

የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ ነጻነት ገብረሚካኤል ስትሆን ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ አቶ ነብዬልዑል በ1926 አ.ም ነበር የተወለዱት፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ባለውለታዎችን ያፈራች ሀገር ነች፡፡ በተለይ ደግሞ ከ1933 በኋላ ተምረው ሀገር ለመቀየር የደከሙት ብዙ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ አቅማቸውን ሳይቆጥቡ የሰሩ ናቸው፡፡

ከእነዚህ የሀገር ባለውለታዎች መሀል አቶ ነብዬልዑል ክፍሌ ይጠቀሳሉ፡፡ በ1967 ህዳር 14 ህይወታቸውን ካጡ ሀገር ወዳዶች አንዱ የሆኑት እኒህ ሰው ለሀገር የሰሩት ወደ ፊት በስፋት የሚነገር ይሆናል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሀገር ውለታ ውለው ግን በስፋት በየሚድያው ስለማይነገርላቸው ሰዎች የተለያዩ ዘገባዎችን ያቀርባል፡፡ ከዚህ ቀደም የ40 ባለውለታዎችን በሲዲ ሰንደን ያስቀመጥን ሲሆን ወደ ፊትም እንቀጥላለን፡፡ ዛሬ ደግሞ በዚህ ጽሁፍ አቶ ነብዬልዑል ክፍሌን እናስታውሳለን፡፡ መረጃ በመስጠት ለተባበሩን ለልጃቸው ለወይዘሮ ሰብለ ነብዬልዑል ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

አቶ ነብዬ ልዑል ክፍሌ በድህረ ጣልያን ወረራ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርታቸው ጀመሩ፡፡ የእርሳቸው ታሪክ የኢትዮጵያን የ20ኛው ክ/ዘመን የመንግስት ስርዓትና አገር ግንባታ ታሪክ ጋር የተሰናሰለ ታሪክ ነው፡፡ አቶ ነብዬ ልዑል በመጀመሪያ በአርበኞች ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት (ኮተቤ ኮሌጅ) ተምረዋል፡፡ በኋላ ም በተለያዩ የመንግስት ሲቪል ሰርቪስ መ/ቤቶች ሰርተዋል፡፡

ከመንግስት ስራ አገልግሎታቸው በመጀመሪያ በአስተማሪነት ቀጥሎ በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቪል ሰራተኝነት አገለገሉ፡፡ በኋላ በወቅቱ የመንግስት የፀጥታ መ/ቤት ሃላፊ በነበሩት ኮሎኔል ወርቅነህ አማካኝነት ወደ ፀጥታ መ/ቤቱ ተቀላቀሉ፡፡ በፀጥታው መ/ቤት የጥናት ክፍል ውስጥ ተቀጥረው መስራት ከጀመሩ በኋላ በወቅቱ በፀጥታ መ/ቤት መነሻ ሃሳብ አንሽነት ወደ ተቋቋመው የግርማዊ ንጉሰ ነገስት ልዩ ካቢኔ ተብሎ ወደ ሚታወቀው ብቸኛ ተጠሪነቱ ለንጉሰ ነገስቱ ወደ ሆነው ካቢኔ በአስተዳዳሪነት ወይም ዳይሬክተርነት ተሹመው ነበር፡፡

በሚያገለግሉበት ወቅትም የልዩ ካቢኔ አስተዳዳሪ ከመሆን በተጨማሪ የከሰም ቀበና የመንግስት እርሻ በአስተዳዳሪት አገልግለዋል፡፡
በዚህ ወቅት አቶ ነብዬልዑል ክፍሌ በተጓዳኝ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በሕግ ት/ት ክፍል ተከታትለው በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመቀበል በቅተዋል፡፡

ይህ በእንግዲህ እንዳለ በታህሳስ ወር 1953ዓ.ም ንጉሰ ነገስቱን ከስልጣን ለማንሳት በተደረገው የመንግስት ግልበጣ ሙከራ አማካኝነት የወቅቱ የፀጥታ ክፍል ሃላፊ የነበሩት ኮ/ል ወርቅነህ ገበየሁ በመንግስት ግልበጣ ሙከራው ላይ በመሳተፍ ተጠርጥረው በኋላም እርምጃ ከተወሰደባቸው በኋላ የፀጥታ መ/ቤቱን ለጥቂት ጊዜ ኮ/ል ወርቅነህ ገበየሁን ተክተው ኮ/ል ይርጉ እንዳይላሉ እንዲመሩት ከተደረገ በኋላ የፀጥታ መ/ቤት መዋቅር ለሁለት በመክፈል የሃገር ውስጥ ፀጥታ እና የውጭ አገር ፀጥታ መዋቅሮችን መመስረት ተከትሎ አቶ ነብዬልዑል ክፍሌ የውጭ ሃገር ፀጥታ መ/ቤቱን በምክትል ሚኒስትር መዓረግ፡ የንጉሰ ነገስቱ ልዩ ካቢኔ ምክትል ሚኒስትር ተደርገው ይሾማሉ፡፡

ይህ ሚኒስትር መ/ቤት እስከ 1966 አብዮት ጊዜ ድረስ በቀጥታ ተጠሪነቱ ለንጉሰ ነገስቱ ነበር፡፡ በመሆኑም በዚህ ሃላፊነት ላይ በሚኒሰትር መዓርግ ተሹመው የውጭ ሃገር ፀጥታና ደህንነት ከኢትዮጵያ ፀጥታና ደህነነት አንፃር እየተከታተሉ ያስተዳድሩ የነበሩት አቶ ነብዬልዑል ክፍሌ ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለንጉስ ነገስቱ ነበረ፡፡

በዚህ ሃላፊነት ላይ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው አገራቸውን ዘመናዊ የውጭ ፀጥታ ስራ መዋቅር በመዘርጋት፣ በመከታተልና በማስተዳደር ያገለግሉ በነበሩበት ወቅት አገሪቱ ከ1953 ታህሳስ ግርግር በመቀጠል በገጠማት መጠነ ሰፊ የህዝብ የአስተዳዳር ጉድለት እና የፍትህ መዛባት ተቃውሞ እና የንጉሰ- ነገስቱ መንግስት በገጠመው ውስጣዊ መዋቅራዊ ተቃርኖ ምክንያት የንጉሰ- ነገስቱ ስልጣን በዋናነት ጥያቄ ውስጥ በገባበት ወቅት የህዝብ አመፁንና መዋቅራዊ ተቃርኖውን ተከትሎ በወቅቱ የንጉሰ- ነገስቱ ካቢኔ ስራቸውን በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ በነበሩት አስተዳደራዊ፣ ፍትሃዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ተጠያቂ በመሆን በህግ ከለላ ስር ሁነው የምርመራ ሂደታቸውን ይከታተሉ ከነበሩ የንጉሰ- ነገስቱ ዘመን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አንዱ አቶ ነብዬልዑል ክፍሌ ናቸው፡፡


አቶ ነብዬ ልዑል ክፍሌ በአመዛኙ የኢትዮጵያን ዘመናዊ የውጭ ፀጥታ እና ደህነነት ስራ እና የአሰራር መዋቅር ጋር በመተባበር የዘረጉት ናቸው፡፡ከባልደረቦቻቸው ጋር በመተባበርም የኢትዮጵያን የወቅቱ የውጭ ደህንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሃገሪቱን የደህንነትና የፀጥታ መረጃ በማሰባሰብ፣ በማዋቀር፣ በመተንተንና ለንጉሰ ነገስቱ የውሳኔ ሃሳቦችን በማቅረብ ሲያገለግሉ የነበሩትን ህዝብና መንግስት ጨምሮ ባለቤታቸውንና 6 ልጆቻቸውን በ1966ቱን አብዮት ተከትሎ በመጀመሪያ ከሐምሌ 1966 እስከ ህዳር 13, 1967 በህግ ከለላ ስር በተጠያቂነት በመቀጠል በህዳር 14, 1967 በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳዳር በተወሰደባቸው “ፖለቲካዊ እርምጃ” አማካኝነት ሂወታቸውን አጥተዋል፡፡

አቶ ነብዬልዑል ክፍሌ በስራ ባልደረቦቻቸው በኩል በክርክር ወዳጅነታቸው፣ ለስራቸው በነበራቸው ትጋት በንባብ አፍቃሪነታቸው እና ግትር አቋማቸው የሚታወሱ ሲሆን በማህበራዊ ሂወታቸው ቤተሰቦቻቸውን ወዳድ፣ ልጀቻቸውን አፍቃሪ ለልጆቻቸው ቅርብ አባት ለባለቤታቸው ጓደኛ በትርፍ ጊዜያቸው እግር ኳስ ተጫዋች፣ ጥሬ ስጋ ቆራጭ፣ ሙዚቃና ፊልም አፍቃሪ እንደነበሩ ይመሰከርላቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *