ዝምተኛው አዘጋጅ
ተስፋዬ ገብረማርያም
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ የሥነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ህይወት ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል ፡፡ ይህም ሰነድ በመፅሀፍ፣ በድረ ገፆችና በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ይገኛል ፡፡
ተስፋዬ ገብረማርያም (ግንቦት 19፣1956ዓም ተወለደ) በ1978 ዓም ጎንደር ክፍለ ሀገር (በአሁኑ ሰሜን ጎንደር) በባህል ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ውስጥ የኪነጥበባት አደራጅ ቡድን መሪ በመሆን ሥራ ጀመረ፡፡
ከ1982 ዓ.ም ጀምሮም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ተዋናይ፤ ረዳት አዘጋጅ እና አዘጋጅ ሆኖ የሠራ ሲሆን በአስተዳደራዊ ሥራዎችም የኪነት አገልግሎት ረዳት፤ የኪነት አገልግሎት ኃላፊ (Artistic Director)በኃላም ቴአትር ቤቱ እንደገና ሲዋቀር የቴአትር ዳሬክቶሬት ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡ ኃላፊነቱን በገዛ ፍቃዱ ከለቀቀ በኃላም የቴአትር ቤቱ ሲኒየር የቴአትር አዘጋጅ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትርን ከተቀላቀለ በኃላ በኃላፊነት በቆየባቸው ዓመታት እና ከዛም በኃላ ባሉ ጊዜያቶች በሙሉ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ፤ በግል ክበባት እና የቴአትር ተቋማት ዘርፈ- ብዙ በሆኑ የቴአትር ሙያዎች ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ተስፋዬ የተወለደው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከአባቱ አቶ ገብረማርያም እና ከእናቱ ከወይዘሮ እልፏጋሽ ሀጎስ ግንቦት 19፣ 1956 ዓም ነው፡፡ እናቱ እና የእናቱ ታላቅ እህት በነበራቸው ፍቅር ምክንያት ከ6 ዓመቱ ጀምሮ ያደገው እና የኖረው ‹‹እሞድሽ›› እያለ ከሚጠራቸው ከአክስቱ ወይዘሮ አልጋነሽ ሳህለማርያም ዘንድ ነው፡፡ በትንሽነቱ ማንበብ፤ ያነበበውን መገልበጥ ወይም እንደመሰለው አድርጎ እንደገና መጻፍ ይወድ ስለነበር ‹‹እሞድሽ›› አቅማቸው በፈቀደ መጠን ይሆነዋል የሚሉትን መጽሀፍ ይገዙለት ነበር፡፡ሀሁ ይቆርጥበት የነበረውን የቄስ ትምህርት አክስቱ ዘንድ ለመኖር በሄደበት ጊዜ አቋርጦ ‹‹ሀሌሉያ›› የሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ጀምሯል፡፡ እዚህም ብዙ ሳይቆይ ራስ አበበ አረጋይ ትምህርት ቤት፤ ቀጥሎም መድሀኒ ዓለም ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በመድሀኒዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ እና የመጨረሻውን የ12ኛ ክፍል ትምህረቱን ደግሞ በጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አጠናቋል፡፡ በተማሪነት ዘመኑ ከትምህርት መጽሀፍት ይልቅ የእነከበደ ሚካኤል፤ እንዳልካቸው መኮንን፣ አቤ ጉበኛ፣ብርሀኑ ዘሪሁን ድርሰቶች ይስቡት እንደነበር ያስታውሳል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ጊዜም በወቅቱ ወደ አማርኛ ተተርጉመው ይታተሙ የነበሩ የሩስያ ድርሰቶች (ቱርጌኔቭ፤ ጎርኪ፣ ዱምባድዜ፣ ቶልስቶይ፣ ዶስቶየቭስኪ፣ ሾሎኮቭ…)ፍቅር አስይዘውት ነበር፡፡
በዚሁ ምክንያትም ፣አሁን የሩስያ የባህል ማእከል በመባል በሚታወቀው ቦታ ይሰጥ ነበረውን የራሽያኛ ቋንቋን ለመማር የገባ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ብዙ የሩስያ ታላላቅ ድርሰቶችን ለማወቅ ችሏል፡፡ በዚሁ ማእከልም ተማሪዎች የቋንቋ ችሎታቸውን ለማዳበር እንዲያግዝ በሚል ይታዩ የነበሩ ፊልሞችም ቀልቡን ይገዙት ነበር፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፣በ1972 ዓ.ም አካባቢ አዘጋጅቶት በነበረው የእናት ሀገር ጥሪ በተሰኘ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ‹‹እሞድሽ›› ከሚሠሩበት ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል አማካይነት በገዙለት የመግቢያ ቲኬት በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሄራዊ ቴአትር ተገኝቶ የመድረክ ተውኔት ተመልክቷል፡፡
ዛሬ ዛሬ ሲያስበው ያን ጊዜም የተመለከተው ተውኔት ‹‹ተሀድሶ›› ሊሆን ይችላል ብሎ ይገምታል፡፡በዚሁ ዘመንም መንግስት ያስገድደው በነበረው የወጣቶች ውይይት ላይ ይሳተፍ በነበረበት ጊዜም ‹‹እዘምታለሁ›› (1972ዓም) በሚል ርዕስ ድራማ ጽፎ እዚያው ውይይት ይሳተፉ በነበሩ ወጣቶች ተጠንቶ ለቀበሌው ነዋሪዎች ቀርቦለታል፡፡ ይህ ተውኔት አልፎ አልፎ ሀገር ፍቅር ቴአትር ለመሄድ ምክንያት ሆኖታል፡፡
ተስፋዬ በተለይ ተማሪ በነበረበት ወቅት ልዩ ልዩ ድርሰቶችን እንዲጽፉ ይጫኗቸው የነበሩ የ9ኛ ክፍል እና በተለይ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይጻፉ የነበሩ ግጥሞችን የሚያነቡላቸው፤ የሚተነትኑ እና የደራሲዎቹን የህይወት ታሪክ ያወጉዋቸው የነበሩትን የ11ኛ ክፍል መምህሮቹን የህይወት አቅጣጫውን ለመተለም ረድተውኛል ብሎ ያምናል፡፡
በ1974 ዓም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በነበረበት ወቅት አንድ የቴአትር ፖስተር አራት ኪሎ የተፈጥሮ ሳይንስ ካምፓስ በር ላይ ተሰቅሎ ይመለከታል፡፡ ፖስተሩ የአራተኛ ዓመት የቴአትር ጥበባት ተማሪዎች ያዘጋጁትን ተውኔት የዩኒቨርሲቲው ህብረተሰብ እንዲመለከትላቸው ያስተዋወቁበት ፖስተር ነበር፡፡
በዚህም የቴአትር ትምህር በዩኒቨርስቲው ውስጥ የሚሰጥ መሆኑን አወቀ፡፡ የሁለተኛ ተርም ከመገባደዱ አስቀድሞ በግቢው የሚገኙ ሁሉም የትምህርት ክፍሎች ስለክፍሎቻቸው የሚያስተዋውቁበት አንድ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
የየትምህርት ክፍሎቹ ተወካዮች የእነርሱ ትምህርት የሚያጎናጽፈውን እውቀት፤ በዚህም እውቀት ሊገኝ የሚችለውን የሥራ እድል አስተዋውቀው ነበር፡፡ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ማስተዋወቂያ በአነስተኛ የተውኔት ትዕይንት የታጀበ ስለነበር አማላይ ነበር፡፡ በዚሁ ዕለትም ተስፋዬ ቴአትር ለመማር ወሰነ፡፡
በትምህርት ቤት ቆይታው ይበልጥ ትኩረቱ የነበረው እውቁ ጸሀፌ ተውኔት እና ባለቅኔ መንግስቱ ለማ የሚያስተምሩት ‹‹የተውኔት አጻጻፍ ብልሀት›› የነበረ ቢሆንም በሥራ ዓለም ግን ራሱን ያገኘው ዝግጅት ላይ ሲያተኩር ነው፡፡ተስፋዬ በ1978 ዓ.ም ጎንደር ክፍለ ሀገር የኪነ-ጥበባት አደራጅ ቡድን በሚል የሥራ መደብ ለመሥራት ወደስፍራው እንዳቀና ከፋሲለደስ የባህል ቡድን ጋር ‹‹ካንዷም›› የተሰኘ የራሱን ድርሰት አዘጋጀ፡፡
የሥራው ባህሪ ጥበቡን ማበረታታት እና ማስፋፋትን መሠረት ያደርግ ስለነበር ማዕከሉን ጎንደር ከተማ አድርጎ በነበረው ከሰሜን ምእራብ እዝ የባህል ቡድን ለተውጣጡ ከያኒዎች፤ በኃላም አዲስ ዘመን ከተማ ውስጥ ለተደራጁ የኪነት አባላት ስለተውኔት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በዚህ የተጀመረው የሙያ ጉዞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትርን ከተቀላቀለበት ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ቀጥሏል፡፡የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትርን በ1982 ዓም ተቀላቅሎ በዚያው ዓመት ትእይንተ ጥበባት በተሰኘ ሳምንታዊ ትርኢት ላይ በተዋናይነት በመሳተፍ መድረኩን ተዋውቋል፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በዓላትን ጠብቀው በሚመደረኩ አጫጭር ድራማዎች እና የሙሉ ጊዜ ተውኔቶች ቅኝት፤ ውጫሌ ፤ 1929፤ አልቃሽና ዘፋኝ፣ካሊጉላ፣ ንጉስ አርማህ፣ነጻ ወንጀለኞች እና ባዶ እግር በተባሉ ተውኔቶች ላይ በተዋናይነት የተሳተፈ ቢሆንም ትኩረቱን ወደዝግጅት አድርጓል፡፡ በ1983 ዓም ከሙዚቃ ጋር ተቀላቅሎ የቀረበውን ‹‹ሽርሽር በጦር ግንባር›› የተሰኘ ለቴአትር ቤቱ የመጀመሪያው የሆነውን ቴአትር ካዘጋጀ በኃላ ትዕይንተ ጥበባት ዝግጅቶችን እና በትእይንተ ጥበባት ትርዒቶች ላይ የሚካተቱ አጫጭር ተውኔቶችን እያዘጋጀ እና ከሱ ቀደምት እና አንጋፋ ለሆኑ አዘጋጆች ረዳት እየሆነ ልምዱን እያዳበረ ቆየ፡፡ በ1985ዓ.ም የመጀመሪያውን የሙሉ ጊዜ ተውኔቱን ‹‹ርጉም ሀዋርያን›› ለመድረክ አብቅቷል፡፡
ከዚህ በኃላ በዚሁ ቴአትር ቤት፤ በብስራት የቴአትር ኢንተርፕራይዝ፤ በሜጋ አምፊ ቴአትር እና በሚልክዌይ ኮሚኒኬሽን የቀረቡ ልዩ ልዩ ተውኔቶችን አዘጋጅቶ በተለያዩ መድረኮች አቅርቧል፡፡ የተስፋዬ የመድረክ ሥራዎች በዓይነታቸው የበዙ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ትውፊት ላይ የተመሰረቱ (አዳብና፤ ግይድ፤ ሚስጢሩ)፤ የዓለም ብሉይ (ክሊኦፓትራ፤ ተውኔቱ፣ ቶፓዝ)
፤ ኢትዮጵያዊ ብሉይ (የአዛውንቶች ክበብ)፤ ኮሜዲ (ቤቱ፣ ግደይ ግደይ አለኝ፤ አብሮአደግ )፣ ጭፍግ ( ርጉም ሀዋርያ፤ የአመጻ ልጆች) የመሳሰሉት ይገኛሉ፡፡ ከመድረክ ተውኔቶችም ወጣ ብሎ በ2007 እና በ2008 ዓም የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በማስመልከት የአደባባይ ትርኢቶችን አዘጋጅቶ በአዲስ አበባ ስታዲየም አቅርቧል፡፡ከመድረክ ተውኔቶች ውጪም ፊልሞች እና የሬዲዮ ድራማዎችም ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን በቴሌቪዥን ያቀርበው በነበረው ‹‹መስኮት›› በተሰኘ የአጭር ድራማ ፕሮግራም ላይ የራሱን እና የሌሎችን ድረሰቶች በማዘጋጀት ለቴሌቪዝን አለም ጋር ተዋውቋል፡፡
በሜጋ አምፊ ቴአትር አማካኝነትም ‹‹ኮቴ›› እና ‹‹ልብ መች ይረሳል›› ፣ እጣ (ብሄራዊ ቴአትር) የተሰኙ አጫጭር የቴሌቪዝን ድራማዎችን አዘጋጅቷል፡፡ በእነዚህ የተጀመረው ስራም አድጎ በሙሉአለም ታደሰ የተዘጋጀችውን ‹‹አቡጊዳ›› የተሰኘ የፊልም ጽሁፍ የጻፈ ሲሆን ‹‹የእግር እጣ›› የተሰኘ ፊልምም አዘጋጅቷል፡፡
ተከታታይ በሆኑ የቴሌቪዝን ድራማዎችም ላይ የተሳተፈ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ከአለምአቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ያሰናዳውን‹‹ሚራዥ›› የተሰኘ ተከታታይ ድራማ በዋና አዘጋጅነት መርቷል፡፡በበወይዘሮ አበበች ጎበና ህይወት እና ስራ ላይ የተመሰረተውን ‹‹ተስፋ የሰነቀ ጉዞ›› በተሰኘ ርእሰ የዘጋቢ ፊልም ዓለምን ከተቀላቀለ በኃላ 9 የሚደርሱ የተለያየ ዓላማ ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ጽፏል፣ አዘጋጅቷል፡፡
እንዲሁም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በተለያየ ግዜ የተላለፉ ህልሞች፤ ሰንሰለት እና ፍኖት የተባሉ የሬዲዮ ተከታይ ድራማዎችንም ለህዝብ አቅርቧል፡፡ተስፋዬ የመድረክ ድራማዎችን፤የቴሌቪዝን እና የሬዲዮ ድራማዎችን እና ፊልሞችን ከመጻፍ ባሻገር ተተኪ ባለሙያዎችን ለማፍራት በሚደረጉ ፕሮግራሞችም ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነው፡፡ የቴአትር ሙያ እየገጠሙት ካሉት ተግዳሮቶች አንዱ የድርሰት እጥረት ነው ብሎ በማመኑ በዚህ ረገድ የራሱን ጥረት አድርጓል፡፡
ሆሊላንድ የጥበብ አካዳሚ በሚባል የቴአትር ጥበባት ማሰተማሪያ መለስተኛ ትምህር ቤት ሁለት ዙር፤ እንዲሁም ቴአትር ቤቱ በሚያዘጋጃቸው አጫጭር ስልጠናዎች የተውኔት አጻጻፍን በተደጋጋሚ ለወጣቶች አስተምሯል፡፡ ድርሰት በክፍል ትምህርት ጽንሰሀሳብ ብቻ በማስተማር የሚሆን አይደለም የሚል እምነት ስላደረበት የእሱ ስልጠናዎች በሙሉ በተግባር የተደገፉ ናቸው፡፡
ወጣት ጸሀፊ ተውኔቶችንም አፍርቶበታል፡፡ በዚህ በኩል ያለውን ልምድ እና ንባብ አክሎበት ‹‹ተውኔት መጻፍ ትችላላችሁ›› የሚል መጽሀፍ አዘጋጅቶ በዚህ ወቅት ህትመቱን እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡በቴአትር ቤቱ የቴክኒክ መርጃ ጽሁፎች እንዲታተሙ እና እንዲሰራጩ ያደረገ የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡ በቴአትር ቤቱም ትውፊት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎችን በተሻለ እውቀት ማከናወን ይቻል ዘንድ የጥናት ክፍሉ እንዲቋቋም ያደረገው ተስፋዬ ነው፡፡ተስፋዬ ገብረማርያም ባለትዳር እና የሁለት ወንዶች እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው።